Search

佈道

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 6-3] ብልቶቻችሁን የእግዚአብሄር ዕቃ ጦር አድርጋችሁ አቅርቡ፡፡ ‹‹ ሮሜ 6፡12-19 ››

‹‹ ሮሜ 6፡12-19 ››
‹‹እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ሐጢአት አይንገስ፡፡ ብልቶቻችሁንም የአመጻ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ለሐጢያት አታቅርቡ፡፡ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሄር አቅርቡ፡፡ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ለእግዚአብሄር አቅርቡ፡፡ ሐጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና፡፡ እንግዲህ ምን ይሁን? ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላይደለን ሐጢያትን እንስራን? አይደለም፤ ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደሆናችሁ አታውቁምን? ወይም ለሞት የሐጢያት ባርያዎች ወይም ለጽድቅ የመታዘዝ ባሪያዎች ናችሁ፡፡ ነገር ግን አስቀድማችሁ የሐጢያት ባሪያዎች ከሆናችሁ ለተሰጣችሁለት ለትምህርት አይነት ከልባችሁ ስለታዘዛችሁ ከሐጢአትም አርነት ወጥታችሁ በጽድቅ ስለተገዛችሁ ለእግዚአብሄር ምስጋና ይሁን፡፡ ስለ ሥጋችሁ ድካም እንደ ሰው ልማድ እላለሁ፡፡ ብልቶቻችሁ አመጻ ሊያደርጉ ለርኩስነትና ለአመጻ ባርያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ እንደዚሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባርያዎች አድርጋችሁ አሁን አቅርቡ፡፡››
  
                
ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 6 ላይ ጻድቃን ከሐጢያቶች ከዳኑ በኋላ እንዴት መኖር እንዳለባቸው ነግሮናል፡፡ ‹‹እምነትን›› እንደገና ከጥምቀት ጋር አብራርቷል፡፡ በኢየሱስ ጥምቀት፣ መስቀልና ትንሳኤ በማመን ሐጢያቶቻችን ለአንዴና ለመጨረሻ ይቅር ተብለዋል፡፡
ያለ ኢየሱስ ጥምቀት በእግዚአብሄር ጽድቅና ደህንነት መሞላት አንችልም፡፡ ኢየሱስ ሲጠመቅ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ባይወሰድ ኖሮ የሐጢያቶችን ስርየት ከተቀበልን በኋላ ጻድቅ ነን ማለት ባልቻልንም ነበር፡፡
 
እኛ በድፍረት ጸድቀናል ማለት የምንችለው ሐጢያቶቻችን በሙሉ ወደ ኢየሱስ ስለተላለፉና እርሱም ለሐጢያቶቻችን ሁሉ ስለተሰቀለና ስለተፈረደበት ነው፡፡ ሮሜ ምዕራፍ 6 በእምነት ስለ መጽደቅና ጻድቁ ስለሚኖረው የምግባር ሕይወት ያስተምራል፡፡ እርሱ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ በሐጢያት ጸንተን እንኑርን?›› (ሮሜ 6፡1) ቀደም ባሉት ምንባቦች ውስጥም እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹በደልም እንዲበዛ ሕግ ጭምር ገባ፡፡ ዳሩ ግን ሐጢአት በበዛበት ሐጢአት በሞት እንደነገሰ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሳ በጽድቅ ምክንያት ለዘላለም ሕይወት ይነግስ ዘንድ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በዛ፡፡›› (ሮሜ 5፡20-21) የዓለም ሐጢያቶች ምንም ያህል የከፉ ቢሆኑም ከእግዚአብሄር ፍቅርና ጽድቅ ሊበልጡ አይችሉም፡፡ ሐጢያቶቻችን በእውነተኛው ቃል ላይ ባለን እምነት መሰረት በእግዚአብሄር ፍቅርና ጽድቅ ተሰርየዋል፡፡
 
እኛ በሥጋ የምንኖር ለሐጢያቶቻችን ሁሉ ስርየትን የተቀበልን ብንሆንም ጸጋ እንዲበዛ በሐጢያት ጸንተን መኖር እንደማንችል ይናገራል፡፡ ‹‹ለሐጢአት የሞትን እኛ ወደፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን? ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሳ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን፡፡›› (ሮሜ 6፡2-4)
 
 

በጥምቀት አማካይነት በሞት ከኢየሱስ ጋር ተቀብረናል፡፡

 
አሮጌው ማንነታችን ከኢየሱስ ጋር ተሰቅሎዋል፡፡ ይህ ማለት ለሐጢያት ሞተናል ማለት ነው፡፡ ሐጢያቶቻችን በሙሉ ወደ ኢየሱስ ተላልፈው እርሱ በምትካችን ሞተ፡፡ ስለዚህ የኢየሱስ ሞት የእኛ ለሐጢያት መሞት ነው፡፡ ‹‹ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን፡፡›› አሮጌው የስጋ ማንነታችን በሞት ጥምቀት አማካይነት ከእርሱ ጋር ተቀብሮዋል፡፡
 
ጌታ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ ወስዶ በሐጢያተኞች ምትክ በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ እርሱ በፍጥረቱ ሐጢያት አልነበረበትም፡፡ ነገር ግን የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ ወስዶ በምትካቸው ሞተ፡፡ ይህንን ታምናላችሁን? እርሱ በራሱ ሊፈረድበት አይገባውም ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ ሐጢያተኞች በእርሱ ውስጥ ሆነን ተፈረደብን፡፡ ምክንያቱም በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ሆነን ተጠምቀናልና፡፡
 
ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሱስ ጥምቀት ላይ ትልቅ ትኩረት አስቀምጦዋል፡፡ እኛም ስለ ኢየሱስ ጥምቀት እንሰብካለን፡፡ የእርሱን ጥምቀት ከታማኝነት አንጻር መስበክ ስህተት አይደለም፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ሐጢያተኛው እጆቹን በመስዋዕቱ ራስ ላይ በመጫን ሐጢያቶቹን እንዳስተላለፈ ሁሉ ኢየሱስም በጥምቀቱ አማካይነት የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች በመውሰድ ለእነዚያ ሐጢያቶች ሞተ፡፡
 
አጥማቂው ዮሐንስ የእግዚአብሄር በግ የሆነውን ኢየሱስን አጠመቀው፡፡ እርሱ የሐጢያት መስዋዕት ሆኖ በተጠመቀ ጊዜ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወሰደ፡፡ ስለዚህ የእርሱ ሞት የእኛ ሞትና የምዕመናን ሁሉ ሞት ነበር፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ የተጠመቁ ሁሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ተቀብረዋል፡፡ በኢየሱስ ውስጥ ያልተጠመቁ ሰዎች መዳን ማመንና ራሳቸውን መካድም ሆነ ዓለምን ማሸነፍ አይችሉም፡፡
 
ከእርሱ ጋር አብሮ በመስቀል ላይ መሰቀሉን የሚያውቀው በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት የሚያምን ሰው ብቻ ነው፡፡ ይህ ሰው ራሱን በመካድ ይነግሳል፡፡ ዓለምንም ያሸንፋል፤ እርሱ በእግዚአብሄር ቃል ላይ ይደገፋል፤ ያምንበትማል፡፡ የኢየሱስ ጥምቀት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ይሸከም ዘንድ ወሳኝ መንገድ እንደሆነ የሚያምኑ ብቻ የሐጢያቶችን ስርየት ማለትም የእርሱን ፍጹም ደህንነት ያገኛሉ፡፡
 
በሐጢያቶች ስርየት አማካይነት የተገኘው ደህንነት እሳቤ የኢየሱስ ጥምቀትና ደም ነው፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች ባይወስድ ኖሮ የእርሱ ሞት ከደህንነታችን ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር ባልኖረም ነበር፡፡ የደህንነት ስረ መሰረት የኢየሱስ ጥምቀት ነው፡፡ የኢየሱስ ጥምቀት ነው፡፡ የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ አጥማቂው ዮሐንስ ኢየሱስን ባጠመቀው ጊዜ ወደ እርሱ ተላልፈዋል፡፡
 
 

እኛ ከእግዚአብሄር ጋር በሕይወት ወደ መኖርና በአዲስ ሕይወት ወደ መማለስ ደርሰናል፡፡

 
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን፡፡›› (ሮሜ 6፡4) በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ የተቀበሩ ሁሉ በእምነት ቤዛነትን አግኝተዋል፡፡ ከእርሱም ጋር ተቀብረው በእርሱ ውስጥ አዲስ ሕይወት አላቸው፡፡ ይህ እምነት ትልቅ እምነት ነው፡፡ በእርሱ ጥምቀት ማመን በጽኑ መሬት ላይ የተመሰረተ እምነት ነው፡፡
‹‹እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሳ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን፡፡ ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፡፡›› (ሮሜ 6፡4-5) በኢየሱስ ጥምቀት በማመን ከእግዚአብሄር ጋር ልንተባበር እንችላለን፡፡
 
በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች በአዲስ ሕይወት ሊመላለሱ ይችላሉ፡፡ ዳግም ከመወለዳችን በፊት የነበረው አሮጌው ማንነታችን ሞቶዋል፡፡ እኛም ታድሰናል፡፡ አሁን አዳዲስ ሥራዎችን መስራት በአዳዲስ መንገዶች መኖርና በአዲስ እምነት መኖር እንችላለን፡፡ ዳግም የተወለደ ሰው በአሮጌው ኑሮውና የአስተሳሰብ መንገዱ አይኖርም፡፡ እኛ አሮጌውን የአስተሳሰብ መንገዳችንን የምንለውጥበት ምክንያት አሮጌው ማንነታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመስቀል ላይ ስለሞተ ነው፡፡
 
2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17 እንዲህ ይላል፡- ‹‹አሮጌው አልፎዋል፤ እነሆ ሁሉ አዲስ ሆንዋል፡፡›› ጌታ ሐጢያቶቻችንን ለመውሰድ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡ ተሰቀለ፡፡ ከሙታንም ተነሳ፡፡ በዚህም ሐጢያተኞች ሁሉ በአዲስ ሕይወት ይመላለሱ ዘንድ ከሐጢያቶቻቸው አዳናቸው፡፡ አሮጌው ‹‹ነገሮቻችን›› ማለትም ጉስቁልና፣ ምሬትና የቆሰለ ልብ አልፈዋል፡፡ አሁን አዲስ ሕይወታችን ጀምሮዋል፡፡ የአዲስ ሕይወታችን ጅማሬ መዳን ነው፡፡
 
እግዚአብሄር የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ወጥተው ወደ ከንዓን ከገቡ ኋላ ፋሲካን እንዲያከብሩ ነገራቸው፡፡ ከግብጽ የተደረገው ዘጸዓት ከሐጢያቶች መዳንን ያመላክታል፡፡ እግዚአብሄር ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ አላቸው፡- ‹‹እግዚአብሄርም በግብጽ ምድር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፡፡ ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ፡፡ የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁናችሁ፡፡ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ተናገሩ በሉአቸውም፡፡ በዚህ ወር በአስረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት ለአንድ ቤትም አንድ ጠቦት ይውሰድ፡፡ የቤቱ ሰዎች ቁጥርም ለጠቦቱ የማይበቃ ቢሆን እርሱና ለቤቱ የቀረበው ጎረቤቱ እንደ ነፍሶቻቸው ቁጥር አንድ ጠቦት ይውሰድ፡፡ እያንዳንዱም እንደሚበላው መጠን ከጠቦቱ ይካፈሉ፡፡ የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ይሁን፡፡ ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰድ፡፡ በዚህም ወር እስከ አስራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቁት፡፡ የእስራኤልም ማህበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት፡፡ ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን ይቀቡት፡፡ በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይብሉ፡፡ ከመራራ ቅጠል ጋር ይበሉታል፡፡ ጥሬውንም በውሃም የበሰለውን አትብሉ፡፡ ነገር ግን ከራሱ፣ ከጭኑ፣ ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት፡፡ ከእርሱም እስከ ጥዋት አንዳች አታስቀሩ፡፡ እስከ ጥዋትም የቀረውን በእሳት አቃጥሉት፡፡ ወገቦቻችሁን ታጥቃችሁ፣ ጫማችሁን በእግራችሁ፣ በትራችሁንም በእጃችሁ አድርጋችሁ እንዲህ ብሉት፡፡ ፈጥናችሁም ትበሉታላችሁ፡፡ እርሱ የእግዚአብሄር ፋሲካ ነው፡፡›› (ዘጸዓት 12፡1-11) እግዚአብሄር በፋሲካው በዓል የጠቦቱን ሥጋ ከቂጣ እንጀራና ከመራራ ቅጠል ጋር እንዲበሉት እንዳዘዛቸው ማስታወስ ይገባናል፡፡
 
ከሐጢያቶች መዳን ከተገኘ በኋላ ብዙ መራራ ነገሮች ይመጣሉ፡፡ መራራ ቅጠሎች ራስን መካድን ያሳያሉ፡፡ በእርግጥም መከራ አለ፡፡ ሆኖም እኛ ከክርስቶስ ጋር እንደተቀበርን ማስታወስ አለብን፡፡ ‹‹መሞትን አንድ ጊዜ ሐጢአት ሞቶአልና፡፡ በሕይወት መኖርን ግን ለእግዚአብሄር ይኖራል፡፡ እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለሐጢአት እንደሞታችሁ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሄር ሕያዋን እንደሆናችሁ ራሳችሁን ቁጠሩ፡፡›› (ሮሜ 6፡10-11)
 
ይህ ከእግዚአብሄር ጋር የመተባበር ምስጢር ነው፡፡ ከኢየሱስ ጋር የምንተባበረው እርሱ በፈጸመው ጥምቀት፣ መስቀልና ትንሳኤ በማመን ነው፡፡ የእርሱ አገልግሎት ውልደቱን፣ በአጥማቂው ዮሐንስ መጠመቁን፣ ስቅለቱን፣ ትንሳኤውንና ሙታንን ለመፍረድ ዳግመኛ የሚመጣ መሆኑን ይጨምራል፡፡ እውነተኛ እምነት በእነዚህ ሁሉ ነገሮች ማለትም በእግዚአብሄር ደህንነት ፍርድና ጽድቅ ማመን ነው፡፡
 
ሮሜ 6፡10 እንዲህ ይላል፡- ‹‹መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ሞቶአልና፡፡›› ኢየሱሰ ሐጢያቶቻችንን ያስወገደው በሁለት የተራራቁ ክፍተቶች ውስጥ አይደለም፡፡ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች የደመሰሰው በአንድ ጊዜ ነው፡፡ ሮሜ 6፡10-11 እንዲህ ይላል፡- ‹‹መሞትን አንድ ጊዜ ሐጢአት ሞቶአልና፡፡ በሕይወት መኖርን ግን ለእግዚአብሄር ይኖራል፡፡ እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለሐጢአት እንደሞታችሁ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሄር ሕያዋን እንደሆናችሁ ራሳችሁን ቁጠሩ፡፡›› እኛ በእርግጥም ለሐጢያት ሞተን ለእግዚአብሄር ሕያዋን ሆነናል፡፡ አዲስ ሕይወት ይዘናል፡፡ አዳዲስ ፍጥረቶችም ሆነናል፡፡  
 
‹‹እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ሐጢአት አይንገስ፡፡ ብልቶቻችሁንም የአመጻ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ለሐጢያት አታቅርቡ፡፡ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሄር አቅርቡ፡፡ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ለእግዚአብሄር አቅርቡ፡፡ ሐጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና፡፡›› (ሮሜ 6፡12-14)
 
‹‹ሐጢአት አይገዛችሁምና ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና፡፡›› በሕይወታችን ውስጥ ምንም አይነት ድካሞች ቢገለጡም ከዳንን በኋላ ሐጢያት የለብንም፡፡ ድካሞች እንዳሉብን የታወቀ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁንም የምንኖረው በሥጋ ነውና፡፡ ነገር ግን ሐጢያት አይገዛንም፡፡ ደካሞች ብንሆንም በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ በኩል በሆነው የሐጢያት ፍርድ በማመን የሐጢያቶችን ስርየት ስለተቀበልን ኩነኔ የለብንም፡፡ በደሎቻችንም ሐጢያቶች ናቸው፡፡
 
ሐጢያት ሊነግስብን እንደማይችል እውነት ነው፡፡ እግዚአብሄር ጻድቃኖች በሐጢያት እንዳይገዙ አድርጎዋል፡፡ ደካሞች ብንሆንም ጌታ ሐጢያት በእኛ ላይ እንዳይነግስ በኢየሱስ ጥምቀት አማካይነት ለአንዴና ለመጨረሻ ሐጢያቶቻችንን ጥር አድርጎ አስወግዶዋል፡፡ በመስቀል ላይ የሐጢያቶችን ዋጋ ከፍሎዋል፡፡ ጌታ የሐጢያትን ዋጋ ስለከፈለ ምዕመናን ያለ ሐጢያት ናቸው፡፡
ጻድቃን በውስጣቸው ብዙ ሐጢያቶችና በደሎች ሲገለጥ ያያሉ፡፡ ነገር ግን በእምነት በጌታ ላይ በሚደገፉበት ጊዜ ሐጢያት አይነግስባቸውም፡፡ ኩነኔም አይኖርባቸውም፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜም በአዲስ ሕይወት መመላለስ እንችላለን፡፡
 
 
ብልቶቻችሁን የእግዚአብሄር ጽድቅ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ አቅርቡ፡፡
 
ጌታ ጻድቃን በየቀኑ አዲስ ሕይወት እንዲኖሩ ባርኮዋቸዋል፡፡ ነገር ግን በሐጢያት መቀጠል ይችላሉን? በእርግጥም አይችሉም፡፡ ሮሜ 6፡13 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ብልቶቻችሁንም የአመጻ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ለሐጢያት አታቅርቡ፡፡ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሄር አቅርቡ፡፡ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ለእግዚአብሄር አቅርቡ፡፡››
 
‹‹የሐጢአት ባሪያዎች ሆናችሁ…ለእግዚአብሄር ምስጋና ይሁን፡፡›› በተፈጥሮዋችን የሐጢያት ባሮች ነበርን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንዲህ ይላል፡- ‹‹ለተሰጣችሁለት ለትምህርት አይነት ከልባችሁ ስለታዘዛችሁ ከሐጢአትም አርነት ወጥታችሁ በጽድቅ ስለተገዛችሁ ለእግዚአብሄር ምስጋና ይሁን፡፡›› (ሮሜ 6፡17-18)
 
እኛ ጻድቃን የሆንን ከሐጢያት አርነት ወጥተን የእግዚአብሄር ጽድቅ ባሪያዎች ሆነናል፡፡ በጸጋም ጸድቀናል፡፡ እኛ ለእርሱ ጽድቅ መስራት የምንችል ጻድቃን ነን፡፡
ነገር ግን ቤዛነትን ካገኘን በኋላ ሥጋችንን ምን ልናደርገው ይገባናል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባርያዎች አድርጋችሁ አሁን አቅርቡ፡፡›› (ሮሜ 6፡19) እኛ ከሐጢያቶች የዳንን ብንሆንም ሥጋ ምን ያደርጋል? በልባችን ውስጥ ሐጢያት ባይኖርም ሥጋ ሁልጊዜም በሐጢያት ይወድቃል፡፡ ስለዚህ በሐጢያት ከመውደቅ ማምለጥ የምንችለው ሥጋችንን የጽድቅ ባርያ አድርገን ስናቀርብ ነው፡፡ ይህ ማለት እኛ ስለጸደቅን ሥጋችን የጽድቅ ሥራዎችን እንዲያደርግ ማቅረብ ማለት ነው፡፡
 
 
እግዚአብሄርን ለመምሰል ራሳችንን ማስለመድ አለብን፡፡
 
ከዳንን በኋላ ሥጋችን ደካማ ቢሆንም ሐጢያት አልባ ነን? በኢየሱስ ጥምቀት፣ መስቀል፣ ትንሳኤ፣ ምጽዓትና የመጨረሻ ፍርድ የሚያምኑ ሰዎች ሐጢያት እንደሌለባቸው የታወቀ ነው፡፡ እነርሱ ሐጢያት አልባ ናቸው፡፡ እኛ ማድረግ ያለብን ሥጋችንን ለጽድቅ ሥራዎች ማቅረብ ብቻ ነው፡፡ ልባችንም እንዲሁ ጽድቅን ማድረግ ይፈልጋል፡፡ ሥጋ ግን የእግዚአብሄርን ጽድቅ ለመተግበር አይፈልግም፡፡ ስለዚህ 1ኛ ጢሞቴዎስ 4፡7 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እግዚአብሄርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ፡፡›› እግዚአብሄርን ለመምሰል ራሳችንን ማስለመድ ይኖርብናል፡፡
 
ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከናወን አይደለም፡፡ የወንጌል መጽሐፎችን ለሌሎች ሰዎች ስንሰጥ የምናውቃቸውን ሰዎች ስናገኝ እናፍራለን፡፡ ሐፍረት ስለሚሰማን እነርሱን ገለል በማድረግ ሮጠን ወደ ቤታችን ልንመለስ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ‹‹አሮጌው ማንነቴ ቀድሞውኑም ሞቷል›› ብለን በማሰብና ከዚያም በድፍረት ‹‹ቤዛነትን ካላገኘህ ወደ ሲዖል ትወርዳለህ፡፡ ስለዚህ ይህንን መጽሐፍ አንብበህ ቤዛነትን ተቀበል!›› በማለት ይህንን ብዙ ጊዜ ደጋግመን ለማድረግ ብንሞክር ይሳካልናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ስትንቀሳቀሱ ሥጋችሁን ለጽድቅ ማቅረብ ትችላላችሁ፡፡
 
ሮሜ ምዕራፍ 6 ብልቶቻችን ሊቀደሱ የጽድቅ ባሮች አድርገን እንድናቀርብ ይነግረናል፡፡ ብልቶቻችንን የጽድቅ ባሮች አድርገን ማቅረብ ይገባናል፡፡ ይህንን በተደጋጋሚ መለማመድ አለብን፡፡ ይህ በአጭር ጊዜ የሚከወን አይደለም፡፡ ደግመን ደጋግመን መሞከር አለብን፡፡ ቤተክርስቲያን ለመሄድ በምንሞክርበት ጊዜ ቤተክርስቲያን መሄድ ምንኛ እንደሚያስደስት ወደ ማወቅ እንደርሳለን፡፡ ‹‹ይህንን አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ሁሉን ነገር ቤቴ ውስጥ ሆኜ ማመን እወዳለሁ፡፡ መጋቢዬ የሚሰብከውን በግልጽ አውቀዋለሁ፡፡›› ሥጋም ልብም ቤተክርስቲያን ውስጥ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ እምነት በልብ ውስጥ ማደግ የሚችለው ብልቶቻችንን የጽድቅ ባሮች አድርገን ስናቀርብ ብቸ ነው፡፡
 
ብልቶቻችንን ለጽድቅ ሥራ ማቅረብ ይገባናል፡፡ ምን እያልሁ እንደሆነ ታውቃላችሁን? ራሳችንን አብሮ ከመሰባሰብና መሪዎችን ከመገናኘት ማራቅ አይገባንም፡፡ ወደ ገበያ በምትሄዱበት ጊዜ ቤተክርስቲያን ባለችበት ቦታ ወርዳችሁ ‹‹ወደ ገበያ ስሄድ ወረድሁ፡፡ ምን አለ?›› በማለት በሩን ከፍታችሁ ብትገቡ ይመረጣል፡፡ ብዙውን ጊዜ ቤተክርስቲያን መገኘት ማለት ራሳችሁን የጽድቅ ባርያ አድርጋችሁ ማቅረብ ማለት ነው፡፡
 
ያን ጊዜ መሪው ‹‹እህት ይህንን መጽዳት እንደምትችይ ልመልከት›› ይላል፡፡
‹‹እሺ፡፡››
‹‹እባክሽ ዛሬ ምሽት በቅ በይ፡፡››
‹‹ለምን?››
‹‹በዚህ ምሽት የወጣቶች ሕብረት አለን፡፡››
‹‹እሺ ዛሬ ምሽት ተመልሼ እመጣለሁ፡፡››
 
እኛ በዓለም ላይ እንባትላለን፡፡ ነገር ግን የዓለም ሰዎች በእነርሱ ስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ በሚጠይቁን ጊዜ መጀመሪያ ሥጋችንን ማቅረብ የሚኖርብን የት ነው?
 
ራሳችንን ለቤተክርስቲያን ማቅረብ አለብን፡፡ ከጓደኞቻችን ጋር ምግብ ለመብላት ብንጠየቅም ቤተክርስቲያን መገኘት አለብን፡፡ ልባችን ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆኖ ሳለ ሥጋችን ምግብ ቤት ውስጥ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም፡፡ ሥጋችን ከዓለም አምልጦ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንዲገኝ ስንፈቅድ ሥጋችንና ልባችን ይበረታሉ፡፡
ምን ታስባላችሁ? ሥጋችሁ አንዳንድ ሥጋዊ ቦታዎችን የሚያዘወትር ከሆነ ልባችሁ ከእግዚአብሄር ጋር ለመተባበር ቢፈልግም የእግዚአብሄርና የፈቃዳችሁ ጠላቶች ትሆናላችሁ፡፡
 
 
ሥጋን ከመንፈስ ጋር በሚገባ ማለማመድ ይገባናል፡፡
 
ሥጋችንን የጽድቅ ባርያ አድርገን ማቅረብ አለብን፡፡ ይህ ማለት ግን ሥጋ ፍጹም ነው ማለት አይደለም፡፡ ሥጋችን የወደደውን ለማድረግ ቢያዘነብልም ብልቶቻችንን ደግመን ደጋግመን ለጽድቅ ሥራዎች ማቅረብ ይገባናል፡፡ እኛ ብዙውን ጊዜ የምንጓዘው በተለመደው መንገድ ነው፡፡ ይህም ሥጋችንን ባርያ አድርገን ባቀረብንለት ነገር ላይ ነው፡፡
 
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባርያዎች አድርጋችሁ አቅርቡ፡፡ ብልቶቻችሁን የእግዚአብሄር ዕቃ ጦር አድርጋችሁ አቅርቡ፡፡›› ይህ ሥጋችሁን በመግራት ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ሥጋችሁን መጠጥ ለመጠጣት ካልገራችሁት ሥጋችሁ ወዲያውኑ ወደ መጠጥ ይሄዳል፡፡ ከዚህ የተነሳ እናንተ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆናችሁ ሥጋችሁ ወደ ቡና ቤት ይሮጣል፡፡ ቡና ቤት ውስጥ ስትቀመጡ ልብ ይሰቃያል፡፡ ቤተክርስቲያን ውስጥ ስተቀመጡ ግን ሥጋ ቢሰቃይም መንፈስ ይደሰታል፡፡
 
ሥጋ ስብዕናም አለው፡፡ ሥጋ የሚመረኮዘው ከልብ በወሰደው መገራት ላይ ነው፡፡ ደጋግመን መጠጥ ስንጠጣ ሥጋ ‹‹እኔ የሚያሰክር መጠጥ እወዳለሁ›› ይላል፡፡ ነገር ግን የማንጠጣ ከሆነ ሥጋ ‹‹መጠጥ እጠላለሁ›› ይላል፡፡ ለምን? ምክንያቱም ሥጋ አልተገራም፡፡ ጉዳዩ ልብ ቢቀደስም ሥጋ በመገራቱ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ልባችንን ይገዛል፡፡ ከቤተክርስቲያን ውጪ ብንሆንም መንፈስ ቅዱስ ይደግፈናል፡፡ ነገር ግን ሥጋችን ሊቀደስ የጽድቅ ባርያ አድርገን ልናቀርበው ይገባናል፡፡ ስለዚህ በማናቸውም አጋጣሚ ደግማችሁ ደጋግማችሁ ወደ ቤተክርስቲያን ሂዱ፡፡
 
የዳኑ ሰዎች ራሳቸውን ራሳቸውን እግዚአብሄርን መምሰል ማስለመድ አለባቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሄርን ቃል እንድንታዘዝና በእርሱም እንድንመራ ነግሮናል፡፡ በእግዚአብሄር ቃል መሰረት መመራት ያለብን ሥጋችን ደስ የሚሰኝበትን ነገር ማድረግ ስለምንወድ ነው፡፡ እኛ እንደወደድን ወደ ገበያ፣ ወደ ዳንስና ወደ መጠጥ ስለምንሄድ በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚደረገው አምልኮ ላይ ተገኝተን ማሰላሰል ያስቸግረናል፡፡ ስለዚህ የሚመራን መሪ ያስፈልገናል፡፡ ‹‹እዚያ ተቀምጠህ የእግዚአብሄርን ቃል ስማ፡፡››
‹‹እሺ፡፡›
 
‹‹እዚህ በትዕግስት መቀመጥ ይኖርብኛል፡፡ ቡና ቤት ውስጥ 3 ሰዓት መቀመጥ እየቻልሁ እዚህ ለምን ተሰላቸሁ? እዚህ ለአንድ ሰዓትም ቢሆን መቀመጥ ያቃተኝ ለምንድነው? ስብከቱን ከሰማሁ አንድ ሰዓት ያህል አልፎዋል! ቡና ቤት ውስጥ ተቀምጬ ለ5 ሰዓታት እጠጣለሁ፡፡ ያለ ዕረፍትም ለ20 ሰዓታት ካርታ እጫወታለሁ፡፡››
 
ሁሉም ነገር የተመረኮዘው ሥጋን በመግራት ላይ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ቤተክርስቲያን የሚያዘወትር ሥጋ ቡና ቤት መሄድን ይጠላል፡፡ ነገር ግን መጠጥ በመጠጣት በሚገባ ለተገራ ሰው ቤተክርስቲያን ውስጥ መቀመጥ ሲዖል ነው፡፡ ለብዙ ቀናቶች ያህል እንድትታገሱ እፈልጋለሁ፡፡ ያን ጊዜ መታገስን መማር ትችላላችሁ፡፡ ሥጋችሁን እስካልገራችሁ ድረስ ይህንን ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በጊዜያችን ሌሎች ነገሮችን ማድረግ ስንፈልግ ጊዜያችንን ቤተክርስቲያን ውስጥ ማሳለፍ ይገባናል፡፡
 
ለመገራት ከመሪዎች፣ ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር በመነጋገር ጊዜያችንን ቤተክርስቲያን ውስጥ እናሳልፋለን፡፡ እኔ በቤተክርስቲያን ውስጥ በጣም ምቾት ይሰማኛል፡፡ እዚያ እያለሁ የሚያባብለኝ ምንም ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በመንገድ ላይ ስጓዝ ብዙ ነገሮች ያባብሉኛል! በልብስ መሸጫ ሱቆች ቁምሳጥን ውስጥ እንደማያቸው አይነት ልብሶች ብዙ ፈተናዎች አሉ፡፡ ማየት የምፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ ተዘዋውሬ መመልከቱ 2 ሰዓት ይወስድብኛል፡፡ በመጨረሻ መንገዱ ሊጠፋብኝም ይችላል፡፡
 
እንግዳ የሆነ ነገር ካለ ያንን እንግዳ ነገር ለመመልከት እሄዳለሁ፡፡ በኋላም ‹‹ቤት የምደርሰው መቼ ነው? አንድ ሰው ወደ ቤቴ እንዲያደርሰኝ እፈልጋለሁ›› እላለሁ፡፡ ስለዚህ ወደ ቤታችሁ በምትጓዙበት ጊዜ ከስፍራ ወደ ስፍራ አትቅበዝበዙ፡፡ ከአምልኮ አገልግሎቶች በኋላ በቤተክርስቲያን አውቶቡስ ተሳፍራችሁ በቀጥታ ወደ ቤታችሁና መድረስ ወደምትፈልጉባቸው መዳረሻዎች ሂዱ፡፡ ‹‹ወደ ቤተክርስቲያን እሄድ ዘንድ አታሳፍሩኝ፡፡ ሁለት ጠንካራ እግሮች ስላሉኝ በቤተክርስቲያን አውቶቡስ ወደ ቤተክርስቲያን የምሄድበት ምክንያት የለም›› ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ ተፈትናችሁ ትስታላችሁ፡፡ አይረቤ ስለሆኑ ነገሮች ሳትጨነቁ በቤተክርስቲያን አውቶቡስ ተሳፍራችሁ ወደ ቤተክርስቲያን መሄድና የአምልኮ አገልግሎቱ እንዳበቃም ወዲያውኑ ወደ ቤታችሁ መመለስ በመቻላችሁ አመስጋኞች ልትሆኑ ይገባችኋል፡፡ ቤታችሁ እንደደረሳችሁም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ፣ መጸለይና ወደ መኝታችሁ መሄድ የተሻለ ነው…፡፡
 
ለእናንተ መኖር የሚሻላችሁ እንደዚህ ነው፡፡ ሰው ‹‹እኔ ጠንካራ እምነት አለኝ፡፡ ሐጢያት የለብኝም፡፡ ለራሴ አንድ ነገር አረጋግጣለሁ፡፡ ወደ ቤና ቤት ብሄድም መጠጥ አልጠጣም፡፡ ሐጢያት በበዛበት ጸጋም ከመጠን ይልቅ በዝቷል፡፡ በጸጋ ተሞልቻለሁ›› ብሎ ያስብ ይሆናል፡፡ እንደዚያ አስቦ ወደ ቡና ቤት ሲሄድ ጓደኛው ‹‹መጠጥ ጠጣ›› ይለዋል፡፡
‹‹አልጠጣም፡፡ ስጠጣ አይተኸኝ ታውቃለህን? መጠጥ መጠጣት አቁሜለሁ፡፡››
‹‹ወጣም ወረደም ጠጣ፡››
‹‹አልጠጣም፡፡››
‹‹አንድ ብርጭቆ ወይን ጠጅ ብቻ ለምን አትጠጣም?››
 
 ጓደኛው ብርጭቆ ውስጥ ወይን ያንቆረቁርለታል፡፡ ከዚያም ይሰጠዋል፡፡ እርሱ ግን ‹‹የሚያሰክር መጠጥ እንድጠጣ ብትፈታተነኝም ሶዳ (ለስላሳ መጠጥ) እየጠጣሁ ነው›› ብሎ ያስባል፡፡ ከዚያም ከረጅም ጊዜ በፊት የመጠጥ ሱሰኛ እንደነበር በማሰላሰል ‹‹ይህ ምንኛ ጣፋጭ ይሆናል! እንደገና ለምን ወይን አትሰጠኝም? አንድ ብርጭቆ መጠጥ ያስፈልገኛል›› ብሎ ያስባል፡፡ ለስላሳ መጠጡን በአንድ ትንፋሽ ይጨልጠዋል፡፡
 
 ያን ጊዜ ጓደኛው መጠጣት እንደሚፈልግ ያውቅና በባዶው ብርጭቆ ውስጥ ወይን ያንቆረቁራል፡፡
 ‹‹አይጎዳህም፤ ልክ እንደ ኮክቴል ልትጠጣው ትችላለህ፡፡››
 ‹‹አይሆንም፤ አልጠጣም፡፡ በኢየሱስ እንደማምን አታውቅምን?›› ሆኖም በመጨረሻ አንድ ብርጭቆ የሚያሰክር መጠጥ ይጠጣል፡፡ ጓደኛውም በሚገባ እንደጠጣ ያውቃል፡፡
 ‹‹ዛሬን ብቻ ጠጣ፡፡››
 ‹‹እሺ ዛሬ እጠጣለሁ፡፡ ነገር ግን አንተም በኢየሱስ ማመን ይገባሃል እሺ? ብጠጣም ሐጢያት የለብኝም፡፡ አንተ ግን ሐጢያት አለብህ? ከሐጢያቶችህ ልትድን ይገባሃል፡፡››
 
 
ዋናው ነገር ለሥጋ የተገዛንበት ስፍራ ነው፡፡
 
ሰዎች እንደዚያ ናቸው፡፡ ምንም የተለየ ነገር የለባቸውም፡፡ ዋናው ነገር ሥጋን ያቀረብንበት ስፍራ ነው፡፡ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ የጽድቅ ባርያዎች አድርጋችሁ አቅርቡ፡፡ ሥጋችሁን ለቅድስና አቅርቡ፡፡ ምክንያቱም ሥጋ ቅዱስ አይደለምና፡፡ እዚህ ላይ መጠጥ መጠጣትን እንደ ምሳሌ ተጠቀሜያለሁ፡፡ ሌሎች ነገሮችም እንደዚሁ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ጉዳዩ ሥጋን እንዴት እንገራዋለን በሚለው ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡
 
እኛ በአንድ ጊዜ በእምነት ድነናል፡፡ ይህ ዘላለማዊ ነው፡፡ የልባችንና የሥጋችን ቅድስና ግን ሥጋችንን በምናቀርብበት ስፍራ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ልባችን ንጹህ ቢሆንም ልብም እንደረከሰ ይሰማናል፡፡ ያን ጊዜ እምነታችንን ወደ መተው፣ ከቤተክርሰቲያን ወደ መቅረት፣ የእግዚአብሄርን ስም በከንቱ ወደ መጥራት፣ በሰይጣን ተታለን ከእግዚአብሄር ፊት ወደ መሸሽ እንደርሳለን፡፡ በመጨረሻም ወደ ጥፋት እንቀርባለን፡፡
 
ስለዚህ እንዳትጠፉ ራሳችሁን ጠብቁ፡፡ መጠንቀቅ ይገባችኋል፡፡ ከሐጢያቶች ከዳንን በኋላ በየቀኑ የምንሰራቸውን ሐጢያቶች የምንጋፈጠው እንዴት ነው? ‹‹ሐጢአት በበዛበት ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ፡፡›› ብዙ ጊዜ ሐጢአት ብንሰራም ዳግመኛ በፍጹም ሐጢያተኛ እንዳንሆን ጌታ በየቀኑ የምንሰራቸውን ሐጢያቶች በሚገባ አስወግዶዋቸዋል፡፡
 
ነገር ግን ሥጋ ደግሞ ደጋግሞ ወደ ክፋት የሚያዘነብል ከሆነ ችግር ሊገጥመን ይችላል፡፡ ሥጋችንን ማቅረብ ያለብን የት ነው? ሥጋ ወደተወሰነለት መንገድ ሊሄድ ይገባዋል፡፡ ይህንን እንድታስተውሉ አሁንም ድረስ እየተናገርሁ ነው፡፡
 
ልብ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ ሥጋም ቅዱስ ይሆናል፡፡ የጽድቅ አገልጋይ አደርገን ስናቀርበውም በእግዚአብሄር ፊት የጽድቅ ባርያ ይሆናል፡፡ ከዳንን በኋላ እንዴት እንደምንኖር የማናውቅ ከሆነ ሕይወታችንን በቤተክርስቲያን ላይ መትከል አለብን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ቤተክርስቲያን የእንግዶች ማረፊያን እንደምትመስል ይናገራል፡፡ በእንግዳ ማረፊያ ውስጥ እንደምንጠጣና እርስ በርስ እንደምንነጋገር ሁሉ ውሃ እንጠጣለን፤ መንፈሳዊ ምግብ እንመገባለን፡፡ አብረን ሕብረት በማድረግም እንቀጥላለን፡፡
 
ቤተክርስቲያን የእንግዶች ማረፊያን ትመስላለች፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሕብረት በማድረግ እንቀጥላለን፡፡ እርስ በርስም እንነጋገራለን፡፡ ስለዚህ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ቤተክርስቲያን መሄድን ማዘውተር ይኖርብናል፡፡ አዘውትሮ ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄድ ሰው መንፈሳዊ ሰው ይሆናል፡፡ አዘውትሮ ወደ ቤተክርስቲያን የማይሄድ ሰው ከዚህ በፊት እምነቱ ትልቅ የነበረ ቢሆንም በመንፈስ መመላለስ አይችልም፡፡ አዘውትሮ ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄድ ሰው ምንም ያህል ደካማ ቢሆንም መንፈሳዊ ልምላሜ ያገኛል፡፡ ቤዛነትን ካገኙ በኋላ መንፈሳዊ ሕብረት መፍጠር ግዴታ ነው፡፡
እኛ ከቤተክርስቲያን በስተቀር የምንኖርበት ሌላ ስፍራ የለንም፡፡ በቻላችሁት መጠን አብዝታችሁ ወደ እግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በመምጣት ከእርሱ ሕዝብ ጋር ሕብረትን እንድታደርጉ እፈልጋለሁ፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን ኑ፡፡ በእያንዳንዱ የአምልኮ አገልግሎት ላይ ተገኙ፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ስሙ፡፡ ማድረግ ስላቀዳችሁት ነገር ሁሉ ከቤተክርስቲያን መሪዎች ጋር ተማከሩ፡፡

ሕይወታችንን በእግዚአብሄር ቃል ላይ ማማከልና ራሳችንን መሰብሰብ አለብን፡፡ ያን ጊዜ ያለ ውድቀት በእምነት ሕይወታችን ስኬትን ልናገኝ እንችላለን፡፡ በከበረ መንገድ መጠቀሚያዎች ልንሆንና በጌታ ልንባረክ እንችላለን፡፡ ሥጋችሁንና ልባችሁን ለእግዚአብሄር ጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ እንድታቀርቡ እፈልጋለሁ፡፡