Search

Проповіді

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[2-4] እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 2፡8-11 ››

እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 2፡8-11 ››
 
በጥንቷ ቤተክርስቲያን ዘመን ብዙ ክርስቲያኖች ከሮማውያን ባለሥልጣናቶች የስደት እጅ ማምለጥ የሚችሉበትን አመቺ ስፍራ በመሻት በምድሪቱ ላይ ይቅበዘበዙ ነበር፡፡ ክርስቲያኖች እየተከታተሉ የመጡትን ንጉሠ ነገሥታቶች ሥልጣን መቃወማቸውን በመቀጠላቸው የሮም መንግሥት ንጉሠ ነገሥት ኔሮ ከሞተ በኋላ እንኳን በስደት ፖሊሲዎቹ ቀጥሎዋል፡፡ የጥንት ቅዱሳን የሮማውያን ንጉሠ ነገሥታቶችን ዓለማዊ ሥልጣን ተቀብለው እውቅና ቢሰጡም እምነታቸውን እንዲተዉ በጠየቁዋቸው ጊዜ ግን ሥልጣናቸውን ለመቀበል እምቢተኞች ሆነዋል፡፡ ይህንን ዓይነቱን የሮም ባለሥልጣናት መጠይቆች በመቃወማቸው የጥንቷ ቤተክርስቲያን የታሪክ ማህደሮች በሰማዕትነትና በስደት የተሞሉ ነበሩ፡፡
 
የራዕይ ቃል ለዛሬዎቹ ምዕመናኖች አንዳች የተለየ ፋይዳ ያለው ስለመሆኑ ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል፡፡ የሆኖ ሆኖ መጽሐፉ የተጻፈው አሁን ሳይሆን ከሁለት ሺህ ዓመታቶች በፊት ነው፡፡ የተጻፈውም ለእኛ ሳይሆን በእስያ ለነበሩት ለሰባቱ ቤተክርስቲያኖች ነበር፡፡ እንዴት ለእኛ ፋይዳ ሊኖረው ይችላል?
 
ወደፊት ሊመጡ ያሉትን ምስጢሮች የሚገልጥ የእግዚአብሄር ቃል በመሆኑ ፋይዳ አለው፡፡ አሁን እኛ የምንኖረው በራዕይ 6 ላይ በተገለጡት ‹‹የአራቱ ፈረሶች ዘመናት›› ሦስተኛው ዘመን በሆነው በጉራቻው (ጥቁሩ) ፈረስ ዘመን ነው፡፡ የአምባላዩንና (ነጩን)፣ የዳማውን (ቀዩን) ፈረሶች ዘመን አልፈን አሁን ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ባለው የጉራቻው (ጥቁሩ) ፈረስ ዘመን እየኖርን ነው፡፡ መላው ዓለም በቅርቡ ሥጋዊና መንፈሳዊ የሆኑ ታላላቅ ረሃቦች ይገጥሙታል፡፡ እንዲያውም ይህ የረሃብ ዘመን አስቀድሞም መጥቷል ማለቱ ምናልባትም ተገቢ አባባል ሳይሆን አይቀርም፡፡ አሁን ያለው የጉራቸው (ጥቁሩ) ፈረስ የረሃብ ዘመን ሲያልፍ የሐመሩ ፈረስ ዘመን ይመጣል፡፡
 
በራዕይ 6 ላይ የተነገሩት ሰባቱ ማህተሞች እግዚአብሄር በመጀመሪያ ዩኒቨርስን ሲፈጥር በክርስቶስ በአጠቃላይ ሰባት ዘመናቶችን ማቀዱን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የአምባላዩ (ነጩ) ፈረስ ዘመን የሆነው የመጀመሪያው ዘመን የወንጌል ዘመን ነው፡፡ የዳማው (ቀዩ) ፈረስ ዘመን የሆነው ሁለተኛው ዘመን ዲያብሎስ በዓለም ላይ ታላቅ ሁከት የሚያመጣበት፣ ጦርነቶችን የሚፈጥርበትና የእግዚአብሄርን ቤተክርስቲያን በማሳቀቅ የሚቀጥልበት ዘመን ነው፡፡ እነዚህን ዘመኖች ተከትሎ ሥጋዊና መንፈሳዊ ረሃቦች ዓለምን የሚያርሱበት የጉራቻው (ጥቁሩ) ፈረስ ዘመን ይመጣል፡፡ ይህ የጉራቻው (ጥቁሩ) ፈረስ ዘመን ከጥቂት ጊዜ በፊት አስቀድሞ ጀምሮዋል፡፡
 
ይህ ዘመን ሲያበቃ ጸረ ክርስቶስ የሚመጣበት እንደዚሁም በራዕይ 8 ላይ የተገለጡት የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች የሚጀምሩበት የሐመሩ ፈረስ ዘመን ይመጣል፡፡ የሰባቱ መለከቶች የመጨረሻው መለከት ሲነፋ ቅዱሳን ይነጠቃሉ፡፡ ይህንንም ተከትሎ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ይወርዳሉ፡፡ ያን ጊዜ በአየር ለተነጠቁት ቅዱሳን የሰርግ እራት ይሆንላቸዋል፡፡ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች በሙሉ ሲጠናቀቁ ጌታ ከእኛ ጋር አብሮ ወደ ምድር ይመለስና የሺህ ዓመት መንግሥቱን ይጀምራል፡፡ ያን ጊዜ የሺህ ዓመቱን መንግሥት ተከትሎ የመጀመሪያ ትንሳኤያቸውን አግኝተው በሺህ ዓመት መንግሥት ውስጥ በኖሩት ቅዱሳኖች ላይ አዲስ ሰማይና ምድር ይወርዳል፡፡
 
ስለዚህ ‹‹እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን፤ የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ›› እና ‹‹ድል የነሣው በሁለተኛው ሞት አይጎዳም›› የሚሉት የራዕይ መጽሐፍ ምንባቦች በሙሉ በቀጥታ እኛን የሚመለከቱ ይሆናሉ፡፡ በሌላ አነጋገር የራዕይ ቃሎች በዛሬው ዓለም ላይ እየኖሩ ላሉት ክርስቲያኖች ወሳኝ ፋይዳ አላቸው፡፡ ራዕይ ለእኛ ፋይዳ ያለው ባይሆን ኖሮ ይህ የእግዚአብሄር ቃል ሁሉ ትርጉም አይኖረውም ነበር፡፡
 
በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጠው የሰባቱ ዘመኖች ዕቅድ በጌታችን በክርስቶስ ተግባራዊ ሆኖ ተጠናቋል፡፡ የሐመሩ ፈረስ ዘመን ሲመጣ ጸረ ክርስቶስ ይገለጣል፡፡ ጌታችን በዚያን ዘመን ለእኛ ያለውን ዕቅድ ከእግዚአብሄር ቃል ማግኘት ያስፈልገናል፡፡ ሁላችንም እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ጥቅል ዕቅዱን እንዴት እንዳቀደና እንዴት እንደሚፈጸሙ -- በዓለም ላይ ምን ዓይነት መቅሰፍቶች እንደሚወርዱ፣ በምዕመናን ላይ ምን እንደሚደርስ፣ የማያምኑ ሰዎችም ምን ዓይነት ጥፋቶች እንደሚገጥሙዋቸውና ወ.ዘ.ተ ከራዕይ ቃል መረዳቱ ፈጽሞ ወሳኝ ነው፡፡ ይህ የትንቢት ቃል ለእናንተ ያለውን ፍጹም ጠቀሜታና ፋይዳ መቀበልና ማመን አለባችሁ፡፡
 
የራዕይ መጽሐፍ ስለምን እንደሚናገርም ትክክለኛ መረዳት ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ እንደ የሰባቱ ዓመት ታላቅ መከራና የክርስቶስ ዳግመኛ ምጽዓት የመሳሰሉትን መረዳት አለባችሁ፡፡ ብዙዎቹ የዘመኑ ክርስቲያኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በ1830ዎቹ በእንግሊዝ ብቅ ባለውና በመቀጠልም በሙዲ ባይብል ኢንስቲትዩት ውስጥ ፕሮፌሰር በነበረው ሲ. አይ. ስኮፊልድ በተባለ ምሁር በስፋት ተቀባይነት ባገኘው የቅድመ መከራ ንጥቀት ትምህርት ያምናሉ፡፡
 
ይህ ጽንሰ አሳብ የቅዱሳን ንጥቀት የሰባቱ ዓመት ታላቅ መከራ ከመጀመሩ በፊት እንደሚሆን መላ ምቱን ያቀርባል፡፡ በዚህ ምልከታ በመጀመሪያ አሕዛቦች ይነጠቃሉ፡፡ ከዚያም እግዚአብሄር ለሕዝበ እስራኤል የደህንነት ሥራውን ይጀምራል፡፡ የቅዱሳኖች ንጥቀትም ከጸረ ክርስቶስ መገለጥና ከሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ይቀድማል፡፡
 
በጥቅሉ ብዙ ክርስቲያኖች ወይ የሺህ ዓመት መንግሥት የለም ብለው ያምናሉ አለበለዚያም በዚህ የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ ያምናሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ትክክለኛ ባልሆነ እውቀትና ስንኩል በሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መረዳት ላይ ተመሰረቱ ተራ መላ ምቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መላ ምቶች ምዕመናን ስለ ራዕይ መጽሐፍ ያሉዋቸውን ብዙ ጥያቄዎች በመመለስ ፋንታ ስለ ራዕይ ቃል ተጨማሪ ጥያቄዎችንና ጥርጥሮችን በመፍጠር ጥሩ ነገር ከማምጣት ይልቅ ይበልጥ ጉዳት አስከትለዋል፡፡
 
የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ ትክክል ቢሆን ኖሮ የራዕይ መጽሐፍ ለአሕዛብ ምዕመናኖች ምን ፋይዳ ይኖረው ነበር? በራዕይ ውስጥ የተተነበዩት ታላቁ መከራና ተከታትለው የሚመጡት ሁነቶች ለእኛ ፋይዳ የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም አስቀድመን እንነጠቃለንና፡፡ ብዙ ሰዎች የራዕይን ቃል የእምነት ጉዳይ አድርገው ከመውሰድ ይልቅ የእውቀት ጉዳይ አድርገው የሚወስዱት ለዚህ ነው፡፡
 
የራዕይ ቃል ግን በዛሬው ዓለም ለምንኖር ለእኛ ወሳኝ ፋይዳ እንዳለው መገንዘብ አለብን፡፡ ይህንን ልጠይቃችሁ፡- የምታምኑት በእግዚአብሄር ቃል ነው ወይስ በሊቃውንቶች ቃል? ስለ ዘመኑ መጨረሻ የሚነገሩ በጣም ብዙ ጽንሰ አሳቦች አሉ፡፡ የሺህ ዓመት መንግሥት የለም ከሚለው ጀምሮ የድህረ መከራ ንጥቀት፣ የቅድመ መከራ ንጥቀት፣ የአጋማሽ መከራ ንጥቀትና ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ ጽንሰ አሳቦች አሉ፡፡ በሊቃውንቶች የቀረቡት እነዚህ ጽንሰ አሳቦች ተራ መላ ምቶች፣ ግምቶችና ወሬዎች ናቸው፡፡
 
ከእነዚህ ጽንሰ አሳቦች መካከል እናንተ የምታምኑት የትኛውን ነው? ብዙ ሰዎች በቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ እንደሚያምኑ ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱም መጋቢዎቻቸው ያስተማሩዋቸው ያንን ነውና፡፡ ነገር ግን በግልጽና በተጨባጭ ልንገራችሁ፤ እናንተና እኔ በሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ውስጥ አልፈን በታላቁ መከራ መሐል እንኖራለን፡፡ እኛ በታላቁ መከራ ውስጥ እንድናልፍ ስለታጨን እምነታችን የሚጠብቁንን ችግሮችና መከራዎች ለማሸነፍ እውነተኛና ጠንካራ መሆን አለበት፡፡
 
እናንተ በቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ አምናችሁ ለራሳችሁ ‹‹ከታላቁ መከራ በፊት እነጠቃለሁ፡፡ ስለዚህ ነገር አልጨነቅም›› ብላችሁ በማሰብ እምነታችሁን ለመጨረሻው ዘመን ባታዘጋጁ ምን ይፈጠራል? የእግዚአብሄር ቃል እንደሚናገረው የሰባቱ ዓመት ታላቁ መከራ በሚመጣበት ጊዜ እምነታቸውን ለመከራው ያላዘጋጁ ሰዎች በታላቅ ግራ መጋባት፣ መከራና ምናልባትም ሞት ይከበባሉ፡፡ ማለትም በኢየሱስ ያላቸው እምነት በሙሉ ይናወጣል፡፡ ከእነርሱ ብዙዎቹ መከራውን ማሸነፍ ስለማይችሉ የእምነታቸውን ተጋድሎ በመሸነፍ ያጣሉ፡፡
 
የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ ከመምጣቱ በፊት ብዙ ክርስቲያኖች በሰባቱ ዓመት የመከራ ክፍለ ጊዜ ውስጥ እንደሚያልፉና ክርስቶስ ዳግመኛ ሲመጣ ያ የመከራ ጊዜ ካለፈ በኋላ ብቻ እንደሚነጠቁ በእርግጠኝነት ሲያምኑ ነበር፡፡ በሰባቱ ዓመት ውስጥ እንደሚያልፉ በማሰባቸው እምነታቸውን በጉጉት ነገር ግን በታላቅ ፍርሃት አዘጋጅተውት ነበር፡፡ ለማንኛውም ሰው አስፈሪ እንደሚሆን ሁሉ ለእነርሱ በመቅሰፍቶቹ ሁሉ ውስጥ ማለፍ አስፈሪ ትዕይንት መሆን እንዳለበት ተረድተዋል፡፡ ነገር ግን የዚህ ዓይነቱ እምነት በእውቀት ላይ የተመሰረተ ጽንሰ አሳብ ሳይሆን የእግዚአብሄርን ቃል ካለማወቅ የሚመጣ ውጤት ብቻ ነው፡፡
 
ደግሞ የሺህ ዓመት መንግሥት የለም የሚሉ ወግ አጥባቂዎችም አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የሺህውን ዓመት መንግሥት የሚያዩት ተምሳሌታዊ አድርገው ይመለከቱታል፡፡ እንዲህ ያሉ በእውቀት ላይ የተመሰረቱ ጽንሰ አሳቦች እውነት ቢሆኑ ኖሮ በዓለም ላይ ስለሚሆነው ነገር ባልተጨነቅንም ነበር፡፡ ምክንያቱም መከራው ከመጀመሩ በፊት ሁላችንም በእግዚአብሄር በአየር ላይ እንነጠቃለንና፡፡
 
ነገር ግን እውነት ባይሆኑ ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር? እምነታችን ሳይዘጋጅ ታላቁን መከራ ብንጋፈጥ አቅልን በሚያስት ፍርሃት እንጠፈር ነበር፡፡ እምነታችንን መጠበቅ ስለማንችል በችግሮችና በመከራዎች ማዕበል ፊት ተማርከን የቀረው ዓለም በሚፈስስበት በዚያው ተመሳሳይ ፍሰት ውስጥ አብረን እንፈስ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ግን ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉላቸው ማለትም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች በፍጹም እጃቸውን እንደማይሰጡ ነግሮናል፡፡
 
እግዚአብሄር በራዕይ ቃሉ ውስጥ ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች በእምነት የታላቁን መከራ ችግሮች እንደሚያሸንፉና በአየር ላይ የሚነጥቃቸውም በመከራው መካከል ያሉ እንደሆኑ ተናግሮዋል፡፡ የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የራቀ ነው፡፡ ማለትም ይህ አባባል ሰው ሰራሽ መላ ምት ነው ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እውነት ሳይሆን ውሸት ነው፡፡
 
ነገር ግን በመላው ዓለም የሚገኙ ብዙ ሰዎች አሁን ይህንን የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ ተቀብለውታል፡፡ በስኮፊልድ የቅድመ መከራ ንጥቀት ትምህርት የሚያምኑ ሰዎች በሚከተሉት ጽንሰ አሳቦች ያምናሉ፡፡
1. የታላቁ መከራ የሰባት ዓመት ክፍለ ጊዜ በመጨረሻው ዘመን ከሚነሳው ጸረ ክርስቶስ በኋላ ይጀምራል፡፡
2. ጸረ ክርስቶስ በሰባቱ ዓመት የታላቁ መከራ ክፍለ ጊዜ ዓለምን ይገዛል፡፡ በመጀመሪያው የሰባት ዓመት አጋማሽ ደግ ገዥ ሆኖ ያስተዳድራል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ክፉ ጨቋኝ ይሆናል፡፡
3. በኢየሩሳሌም ያለው ቤተመቅደስ ይገነባና የመስቃዕት አቅርቦት ዳግመኛ ይጀምራል፡፡
4. ጸረ ክርስቶስ ከእስራኤል ጋር የሰባት ዓመት ቃል ኪዳን ያደርጋል፡፡
5. ከሦስት ዓመት ተኩል መከራ በኋላ ጸረ ክርስቶስ ከእስራኤል ጋር ያደረገውን ይህንን ቃል ኪዳን ይጥሳል፡፡
6. ቀጣዮቹ ሦስት ተኩል ዓመታት ለእስራኤሎች ታላቅ የመከራና የስደት ዘመን ይሆናሉ፡፡ በዚህ ወቅት በጸጋው ወንጌል ምትክ የሺህው ዓመት መንግሥት ወንጌል ይሰበካል፡፡
7. ከእስራኤሎች መካከልም 144,000 ከመከራው ይተርፋሉ፡፡
8. መከራውም በአርማጌዶን ጦርነት ይጠናቀቃል፡፡
 
ስኮፊልድ ታላቁን መከራ ከላይ በተጠቀሱት አገባቦች ካብራራ በኋላ በመከራው ወቅት አሕዛቦች ምን እንደሚገጥማቸው አልጠቀሰም፡፡ በሌላ አነጋገር ስኮፊልድ በክርስቶስ የሚያምኑ አሕዛቦች በሙሉ መከራው ከመጀመሩ በፊት ይነጠቃሉ፤ እግዚአብሄርም በሕዝበ እስራኤል መካከል መሥራት የሚጀምረው ከእነርሱ መነጠቅ በኋላ ነው በማለት ተከራክሮዋል፡፡ የአምላክ ሥራ የሚጠናቀቀውም በ144,000 እስራኤላውያኖች ይሆናል፡፡ በዚህም የደህንነት ሥራውን ያጠናቅቃል፡፡ ያን ጊዜ የሺህ ዓመቱ መንግሥት ይጀምራል፡፡
 
በስኮፊልድና በቅድመ መከራ ንጥቀት አባባሎቹ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረበት አንዲት የጴንጤ ቆስጤ መሪ ከተገናኘ በኋላ ይህንን ጽንሰ አሳብ ማራመድ የጀመረው የፕላይሙዝ ወንድሞች ተብሎ የሚታወቀው ቡድን መስራች ጆን ኔልሰን ዳርቢ ነበር፡፡ ይህች መሪ በ1830 ዓ.ም ክርስቲያኖች ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ሲነጠቁ ከእግዚአብሄር ዘንድ በራዕይ ማየቷን የተናገረችው የአስራ አምስት አመቷ የስኮትላንድ ነዋሪ ልጃገረድ ማርጋሬት ማክዶናልድ ነበረች፡፡ ዳርቢ የቅድመ ንጥቀትን ጽንሰ አሳብ ማስተማር የጀመረው ከዚህች ሴት ጋር ከተገናኘ በኋላ ነበር፡፡
 
ያን ጊዜ የዳርቢ ትምህርቶች ወደ አሜሪካዊው የቃለ እግዚአብሄር ምሁር ወደ ስኮፊልድ ተላለፉ፡፡ ዕድሜውን በሙሉ በስፋት ጥቅም ላይ የዋለውን የስኮፊልድ ማመሳከሪያ መጽሐፍ ቅዱስ በመከወን ላይ ያሳለፈው ስኮፊልድ በወቅቱ ንጥቀት የሚሆነው ከመከራው በፊት ነው ወይስ በኋላ የሚለውን ጥያቄ ያሰላስል ነበር፡፡ ስኮፊልድ የዳርቢን የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ ሲሰማ ሙሉ በሙሉ ዋኘበት፡፡ በአባባሎቹም በሚገባ ስላመነ ይህንን አዲስ ጽንሰ አሳብ በስኮፊልድ የማመሳከሪያ መጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ በማካተት ተቀብለው ስኮፊልድ በቅድመ መከራው ንጥቀት ጽንሰ አሳብ ወደ ማመንና መከራከር የመጣው እንዲህ ነው፡፡ ብዙዎቹ የዘመኑ ክርስቲያኖችም ይህንን የተቀበሉት በዚህ መንገድ ነው፡፡
 
የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ በዳርቢና በስኮፊልድ ከመብራራቱ በፊት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች የሚያምኑት በድህረ መከራ ንጥቀት ነበር፡፡ ነገር ግን በአሜሪካ የሙዲ የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንስቲትዩት ውስጥ ፕሮፌሰር የነበረው ስኮፊልድ በመጽሐፍ ቅዱስ የትምህርት ጉዳዮች ላይ በተለይም በስኮፊልድ የማመሳከሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ጉልበት ከፍተኛ ተጽዕኖ ነበረው፡፡ የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ በመላው ዓለም በክርስቲያን ማህበረሰቦች ውስጥ በስፋት የተሰራጨው ከስኮፊልድና ካሳደረው ተጽዕኖ የተነሳ ነው፡፡
 
ከዚህ የተነሳ ብዙዎቹ የዘመኑ ክርስቲያኖች አሁን በእምነታቸው በጣም ማንቀላፋታቸው አሳዛኝ ነው፡፡ እነርሱ ተኝተዋል፡፡ ምክንያቱም የጸረ ክርስቶስ መነሳት ከእነርሱ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር እንደሌለ ያስባሉና፡፡ ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት እንደሚነጠቁ ስለሚያምኑ ለዚያ ዘመን እምነታቸውን የማዘጋጀቱ አስፈላጊነት አይታያቸውም፡፡ ጌታችን ግን ሁልጊዜም እንድንነቃ ነግሮናል፡፡ ምክንያቱም ሙሽራው መቼ እንደሚመጣ ማንም አያውቅምና፡፡ ሆኖም የእግዚአብሄርን ቃል ቸል ብለው በቅድመ መከራ ንጥቀት ትምህርቶች ላይ የሚደገፉ ሰዎች ለጥ ብለው ተኝተው የሚቀሩ መሆናቸው ያሳዝናል፡፡
 
ነገር ግን የመንቃቱ ጊዜ አሁን ነው፡፡ በቅድመ መከራ ንጥቀት ላይ ያላችሁን የተሳሳተ እምነት ጥላችሁ በእውነት ቃል የምታምኑበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብም ሆነ የድህረ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ ምንም የመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት የላቸውም፡፡ ወደ እውነተኛው የእግዚአብሄር ቃል መመለስ አለባችሁ፡፡ የራዕይ ቃል (6፡8) ይህንን ይነግረናል፡፡ ‹‹አየሁም እነሆም ሐመር ፈረስ ወጣ፡፡ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበር፡፡ ሲዖልም ተከተለው፡፡ በሰይፍና በራብም፣ በሞትም፣ በምድር አራዊት ይገደሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጠው፡፡››
 
እዚህ ላይ በሐመሩ ፈረስ ላይ የተቀመጠው ጸረ ክርስቶስ ሞት እንደነበርና ሲዖልም እንደተከተለው ተነግሮዋል፡፡ ይህ ማለት ጸረ ክርስቶስ ሰለባዎቹን ወደ ሲዖል የሚነዳ ነፍሰ ገዳይ ነው ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ በሰይፍ፣ በራብ፣ በሞትና በምድር አራዊት ይገደል ዘንድ በምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን እንደተሰጠውም ተነግሮዋል፡፡ በሌላ አነጋገር ጸረ ክርስቶስ ልክ እንደ ሮም ንጉሠ ነገሥታቶች ተመሳሳይ የሆኑ ግድያዎችን ይፈጽማል፡፡ በዚህ ዘመን ግን ክርስቲያኖችን መግደሉ፣ ማንገላታቱ፣ ማሳደዱና እምነታቸውን ማውደሙ ይበልጥ የከፋ ይሆናል፡፡
 
የሐመሩ ፈረስ ዘመን የጸረ ክርስቶስ ዘመን መሆኑን ልትገነዘቡ ይገባል፡፡ ጌታ እንዲህ ብሎናል፡- ‹‹የሰማዩን ፊትማ መለየት ትችላላችሁ፤ የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን?›› (ማቴዎስ 16፡3) የዘመኑን ምልክት መለየት የማንችል ከሆንን ምን ዓይነት እምነት ሊኖረን እንደሚገባ ማወቅ ስለማንችል ዘር መዝራትም ሆነ ፍሬ መልቀም አንችልም፡፡ በሌላ አነጋገር ለጌታ መስራት አንችልም፡፡ ዛሬ የዳማው (ቀዩ) ፈረስ ዘመን አልፎዋል፡፡ ያለነው በጉራቻው (ጥቁሩ) ፈረስ ዘመን ነው፡፡ በቅርቡ ዓለም በታላላቅ የኢኮኖሚ መቅሰፍቶች ይመታል፡፡ የአስከፊ ረሃብ ዘመንም ይጠብቀዋል፡፡ ራብና ቀጣና በመላው ዓለም ይሰራጫሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ሲሆኑ ብዙዎች በስቃይ ያዝናሉ፡፡ ከእነርሱ አንዱ አትሁኑ፡፡ በምትኩ እምነቱ የዘመኑን ምልክቶች መለየት እንደሚችል ሰው ሁኑ፡፡
 
የዛሬው ዘመን የጉራቻው (ጥቁሩ) ፈረስ ዘመን ነው፡፡ ይህ የጉራቻው (ጥቁሩ) ፈረስ ዘመን ሲያልፍ የሐመሩ ፈረስ ዘመን ይመጣል፡፡ በዚህ ዘመን ብቅ የሚለው ጸረ ክርስቶስ ማንንም ሳይለይ ቅዱሳንን በመግደልና በማሳደድ ይህንን ዘመን የሰማዕታት ዘመን ያደርገዋል፡፡
 
ዮሐንስ ራዕይ 13፡6-8 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እግዚአብሄርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም፤ በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ፡፡ ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፡፡ በነገድና በወገንም፣ በቋንቋም፣ በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው፡፡ ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል፡፡›› ይህ ጸረ ክርስቶስ ነው፡፡ ምንባቡ ከዓለም ገዥዎች አንዱ እግዚአብሄርን እንዲሳደብና ቅዱሳንን እንዲያሳድድ የሰይጣን ሥልጣን እንደሚሰጠው ይነግረናል፡፡ ይህ የዘንዶው ሥልጣን ያለው የዲያብሎስ ልጅ ነው፡፡ በሥልጣኑም ቅዱሳኖችን ተዋግቶ ‹‹ድል ያደርጋቸዋል፡፡›› ድል ማድረግ ማለት ግን ቅዱሳኖችን ሰማዕታት ያደርጋቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህ የሚያመለክተው የቅዱሳንን አካላዊ ሞት ብቻ ነው፡፡ ጸረ ክርስቶስ የቅዱሳንን እምነት ራሱን ፈጽሞ መንጠቅ አይችልም፡፡
 
የስኮፊልድ መከራከሪያ ቅዱሳን ፈጽሞ ታላቁን መከራ አይጋፈጡም የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን የሰባት ዓመቱ ታላቅ መከራ ሳይኖር ለቅዱሳን የሚሆን የሺህ ዓመት መንግሥት ሊኖር አይችልም፡፡ ቅዱሳን ከታላቁ መከራ ውስጥ ሰማዕታት ሆነው ይወጣሉ፡፡ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ከዓለም ጅማሬ ጀምሮ በክርስቶስ ኢየሱስ የታቀደ ነበር፡፡ የዓለም ታሪክ በሙሉ ክርስቶስ በሚፈጽማቸው ሥራዎች ይጠናቀቃል፡፡
 
እግዚአብሄር ለእኛ ያዘጋጃቸውን ሰባቱን ዘመኖች መለየት መቻል አለባችሁ፡፡ የመጀመሪያው ዘመን የአምባላዩ (ነጩ) ፈረስ ዘመን ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሄር ቃል ሥራውን የጀመረበት ዘመን ነው፡፡ የዳማው (ቀዩ) ፈረስ ዘመን የሆነው ሁለተኛው ዘመን የዲያብሎስ ዘመን ነው፡፡ የጉራቻው (ጥቁሩ) ፈረስ ሦስተኛው ዘመን የሥጋዊና የመንፈሳዊ ረሃብ ዘመን ነው፡፡ የሐመሩ ፈረስ አራተኛው ዘመን ጸረ ክርስቶስ የሚነሳበት ዘመን ነው፡፡ ሰዎችን ግራ እንዲጋቡ የሚያደርጋቸው ይህንን የሐመሩን ፈረስ ዘመን መለየት አለመቻላቸው ነው፡፡
 
ይህንን ዘመን ሳናውቅ ዳግመኛ የተወለዱ ክርስቲያኖች ሆነን ሕይወታችንን መኖር አንችልም፡፡ የሚጠብቀንን ነገር ሳናውቅ ብንቀር እንዴት ለወደፊቱ ልንዘጋጅ እንችላለን? ንግዳቸውን የሚያጧጡፉ ሰዎች እንኳን ስኬታማ ለመሆን የጊዜው ተለዋዋጭ እንቅስቃሴዎች ምን እንደሆኑ አስቀድመው ማወቅ አለባቸው፡፡ እኛ በክርሰቶስ የምናምን ምዕመናን ምን እንደሚጠብቀን ምንም ፍንጭ ከሌለን ለእርሱ ምጽዓት መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
 
ለታላቁ መከራ እንዘጋጅ ዘንድ ስለ እርሱ ግልጽ የሆነ መረዳት ሊኖረን ይገባል፡፡ ቅዱሳን በመጀመሪያው የሦስት ዓመት ተኩል የመከራ ዘመን ውስጥ በሕይወት ይኖራሉ፡፡ ሰማዕት የሚሆኑት በዚህ ጊዜ ነው፡፡ እነርሱ በሰባቱ የመከራ ዓመት ሁሉ ውስጥ አያልፉም፡፡ የሚያልፉት በመጀመሪያው አጋማሽ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ከዚያም በሰማዕትነታቸው ትንሳኤን ይቀበሉና ይነጠቃሉ፡፡ ቅዱሳን ሲነጠቁ ክርስቶስ ወደ ምድር ይወርዳል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ጌታ በአየር ላይ ያነሳቸውና ወደ በጉ ሰርግ እራት ይወስዳቸዋል፡፡
 
ይህችም ምድር ለጊዜው በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ትጥለቀለቃለች፡፡ ከመቅሰፍቶቹ በኋላ ከክርስቶስ ጋር ወደ ምድር የሚመለሱት በጌታ በተሰጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በማመን ሐጢያቶቻቸው ልክ እንደ በረዶ የነጻላቸው ይቅር የተባሉት ብቻ ናቸው፡፡ ይህንን ዘመንና ለእኛ ያለውን ወሳኝ ፋይዳውንና ጠቀሜታውን በመረዳት እምነታችንን ማዘጋጀት ያለብን ለዚህ ነው፡፡
 
ጌታችን ለሰርምኔስ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ አለው፡- ‹‹መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ባለጠጋ ነህ፡፡ የሰይጣንም ማህበር ናቸው እንጂ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉት የሚሳደቡትን ስድብ አውቃለሁ፡፡ ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ፡፡ እነሆ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን ወደ ወህኒ ሊያገባችሁ አለው፡፡ አስር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ፡፡ እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን፤ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ፡፡ መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡ ድል የነሣው በሁለተኛው ሞት አይጎዳም፡፡›› ከዚህ ምንባብ የሰርምኔስ ቤተክርስቲያን ክፉኛ በአይሁዶች እንደተሰደደች ማየት እንችላለን፡፡ ጌታ ግን እነዚህ አይሁዶች የሰይጣን ማህበር እንጂ በእርግጥ አይሁዶች እንዳልነበሩ ተናግሮዋል፡፡ እርሱ ይህንን የተናገረው ለሰርምኔስ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በእስያ ላሉት ለሰባቱም ቤተክርስቲያኖች በሙሉ ነው፡፡
 
በሰርምኔስ ብዙ የአይሁድ ማህበረሰብ ይገኝ ነበር፡፡ አይሁዶችም በክርስቶስ እንደሚያምኑት ምዕመናን የሚያመልኩት አንድ አምላክ ቢሆንም ሮማውያን እንዳደረጉት የሰርምኔስን ቤተክርስቲያን አሳደዱ፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ስደት እየተጋፈጡ ለነበሩት ቅዱሳን እንዲህ አላቸው፡- ‹‹እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን፤ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ፡፡›› ‹‹ድል የነሳው በሁለተኛው ሞት አይጎዳም፡፡›› እግዚአብሄር ቅዱሳንን ድል መንሳት እንዳለባቸው ነገራቸው፡፡ እኛም እንደዚሁ ጸረ ክርሰቶስን እስከ መጨረሻው ታግለን በእምነት ተጋድሎ ድል ልንነሳው ይገባናል፡፡ ያን ጊዜ ጌታችን የሕይወትን አክሊል ይሰጠናል፡፡ በሌላ አነጋገር የሺህውን ዓመት መንግሥትና አዲሱን ሰማይና ምድር በመስጠትና በዚያ እንድንኖር በመፍቀድ ይባርከናል፡፡
 
ሰማዕት የመሆን ድፍረቱ አላችሁን? የሰማዕትነት እምነታችሁን የምታዘጋጁበት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ይህንን ለማድረግም በጌታ ፊት ሙሉ በሙሉ መቆም የሚያስችላችሁ የቤዛነት እምነት -- ያለ ምንም ማመንታት ሰማዕትነትን መቀበል የሚችል እምነት ሊኖራችሁ ይገባል፡፡
ይህንን እምነት አሁኑኑ ማዘጋጀት አለብን፡፡ ጌታችን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማያምን ሰው ወደ እግዚአብሄር መንግሥት መግባት ወይም ማየት እንደማይችል ተናግሮዋል፡፡ በዚህ ወንጌል ማመን በመጨረሻው ዘመን ሰማዕትነትን መቀበል የሚያስችል እምነት እንደሆነ ነግሮናል፡፡
 
በሰዎች ልብ ውስጥ ሐጢያት ካለ እንዴት ሰማዕት ሊሆኑ ይችላሉ? ሰማዕት ከመሆን ርቀው ሌሎች የአውሬውን ምልክት እንዲቀበሉ የሚመሩ ዓይነት ሰዎች ይሆናሉ! ከሐጢያቶቻችን ሊያነጻን የሚችለው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እንጂ ሌላ ምንም ነገር አይደለም፡፡ በተደጋጋሚና በሥርዓት የምታቀርቡዋቸው የንስሐ ጸሎቶቻችሁም ቢሆኑ ሐጢያቶቻችሁን ማንጻት አይችሉም፡፡ ሐጢያቶቻችሁን በንስሐ ጸሎቶች ለማንጻት መሞከር ጊዜንና ጥረትን ማባከን ብቻ ነው፡፡
 
እንዲህ ለማድረግ የሚጥሩ ሰዎች የእግዚአብሄር ቃል በተጨባጭ የነገራቸውን ከማመን ይልቅ የቃለ እግዚአብሄር ምሁራን የተናገሩትን አብልጠው ያምናሉ፡፡ በጣም ብዙ ክርስቲያኖች የሚታመኑባቸው ሊቃውንቶች የሺህው ዓመት መንግሥት የለም ብለው መከራከራቸውና ማመናቸው ነው፡፡ ይህ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች ተብዬዎች ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱስን የማያውቁ እንደሆኑ አያሳይምን? የሺህ ዓመት መንግሥት የሚባል ነገር የለም የሚሉ ሰዎች በታላቁ መከራ ውስጥም የቅዱሳን ሰማዕትነት የለም ይላሉ፡፡ የቅድመ መከራ ንጥቀት ወይም የሺህ ዓመት መንግሥት የለም በሚል ጽንሰ አሳብ ለሚያምኑ ሰዎች የራዕይ መጽሐፍ ፈጽሞ ትርጉም የለውም!
 
የራዕይ ቃል የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ እጅግ ተወዳጅ በሆነው የክርስቶስ ደቀ መዝሙር በሐዋርያው ዮሐንስ የተጻፈ ነው፡፡ ማንም ይህንን ሊክድ አይችልም፡፡
እኔ መሰረት የጣሉትን የሥነ መለኮት ምሁራን ጽንሰ አሳቦችንና ትምህርቶችን የምነቅፈው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ይህንን የማደርገው እስከ ሞት ድረስ ለጌታ ታማኝ ትሆኑ ዘንድ እምነታችሁን ለማዘጋጀት ነው፡፡ ይህንን የማደርገው ሰማዕትነትን ለመቀበል በቆራጥነት በመዘጋጀት የታላቁን መከራ ስደት መቋቋም እንድትችሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ላሰለጥናችሁ ነው፡፡
 
ይህንን ለማድረግ እምነታችሁን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አሁኑኑ ማዘጋጀት አለባችሁ፡፡ በሌላ በኩል በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች በሰይጣን ፊት ያጎነብሱና የእግዚአብሄር ጠላቶች ሆነው ይቀራሉ፡፡ ምክንያቱም ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ያልተጻፉላቸው ሰዎች ለሰይጣን ይሰግዳሉና፡፡ የእግዚአብሄር ቃል የሚነግረንን ይህንን ነው፡፡
 
እግዚአብሄር ቅዱሳን በታላቁ መከራ አጋማሽ ላይ ሰማዕት እንዲሆኑ ይፈልጋል፡፡ የታላቁ መከራ የሰባቱ ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ዓመት ተኩል ሲያልፍ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች ሰማዕት ይሆናሉ፡፡ ከሰማዕትነታቸው በኋላ ወዲያውኑ ትንሳኤያቸውና ንጥቀት ይመጣል፡፡ የራዕይ መጽሐፍ ሁለንተናዊ ማጠቃለያ ይህ ነው፡፡ ቁልፍ የሆኑ ነጥቦቹንም የምደጋግመው ለዚህ ነው፡፡
 
የጸረ ክርስቶስ ዘመን ሲመጣ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ሰማዕት ከሆኑ በኋላ ወዲያውኑ ትንሳኤን የሚያገኙና የሚነጠቁ ብዙ ሰዎች እንደሚኖሩ ማስታወስ ይገባችኋል፡፡ የሐመሩ ፈረስ ዘመን ሲመጣ በሰማዕትነታቸው የእምነት አበቦች ያብባሉ፡፡ ትክክለኛው ጊዜ ሲመጣ እውነተኛ እምነት እውነተኛ ፍሬዎችን ያፈራል፡፡ በውብ አበቦችም ያብባል፡፡
 
በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ በምድረ በዳ የሚያጎነቁሉ፣ የሚያብቡና የሚያፈሩ የተወሰኑ ተክሎች አሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ዝናብ ብዙም ከሌለበትና ውሃም ከማይገኝበት የምድረ በዳ ሁኔታዎቻቸው ጋር ስለተላመዱ ነው፡፡ ፈጥነው ማጎንቆል፣ ማበብና ፍሬ ማፍራት ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ብዙም የማይገኘው የውሃ አቅርቦት ሊቆይ የሚችለው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነውና፡፡
 
በሰባቱ ዓመት ታላቁ መከራ ወቅት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ወደ ማመን የመጡ ሰዎች ልክ እንደ እነዚህ ተክሎች ናቸው፡፡ እነርሱ ይህንን ወንጌል ለማመን፣ ለመከተልና አብረውን ሰማዕት ለመሆን የሚበቃቸው አጭር ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በታላቁ መከራ አጋማሽ በሦስት ዓመት ተኩል ወቅት የጸረ ክርስቶስ ዕብደት ጫፍ ላይ ይደርሳል፡፡
የቅዱሳን ሰማዕትነት የሚሆነው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ አስቀድመው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ከሰሙ በኋላ ገና በልባቸው ያልተቀበሉ ሰዎች እንኳን አጭር ቢሆንም በመከራው ዘመን በኋላ ላይ በዚህ ወንጌል ካመኑ እውነተኛ እምነት ሊኖራቸውና ከእኛ ሰማዕትነት ጋር ሊቀላቀሉ ይችላሉ፡፡ ወንጌልን የምናሰራጨውና በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖችን ከመንፈሳዊ እንቅልፋቸው የምንቀሰቅሰው ለዚህ ነው፡፡ ሰማዕት እስከምንሆን ድረስ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንሰብካለን፡፡ ሰማዕትነት የማይኖር ከሆነ ይህ የምንሰብከው ወንጌል ጥቅሙ ምንድነው? በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች በመጨረሻው ዘመን ሰማዕት ይሆናሉ፡፡ አሁን እምነታችንን ለዚያ ማዘጋጀት ይገባናል፡፡
 
የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለመጠበቅ ሰማዕትነትን የሚቀበለውን እምነታችንን አሁኑኑ ካላዘጋጀነው በእግዚአብሄር ፊት ሰላም ስንሆን በኋላ ላይ ይቆጨናል፡፡ የመጨረሻው ዘመን ሲመጣ ‹‹ጌታ ሆይ አሁን በጣም ባተሌ ነኝ፡፡ ትንሽ ጊዜ ጠብቀኝ፤ አሁን ንስሐ እየገባሁ ነው›› በማለት ከራሳችን ጋር እንባትላለን፡፡ እስከ መጨረሻው ድረስ አጥብቀን የምንይዘው የእምነት ዓይነት ይህ ከሆነ ጌታ ‹‹ለምን ራስህ ዘለህ ወደ ሲዖል እሳት አትገባም? ለዚያ በሚገባ ብቁ ሆነሃል!›› ይለናል፡፡ አሁን ሐጢያት ያለባቸው ሰዎች በመጨረሻ እንዲህ ሆነው እንደሚቀሩ መገንዘብ አለባቸው፡፡ እግዚአብሄር ‹‹መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ›› ብሎ የተናገረው ለዚህ ነው፡፡
 
ቅዱሳን ሰማዕት በሆኑበት ጊዜ የዓለም ተፈጥሮአዊ ሥነ ምህዳር ሙሉ በሙሉ ይወድማል፡፡ ዛፎች ይቃጠላሉ፡፡ ባህሮች፣ ወንዞችና የውሃ ምንጮች ወደ ደም ይቀየራሉ፡፡ ጸሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብቶችም ብርሃናቸውን ስለማይሰጡ መላው ዓለም በጨለማ ይዋጣል፡፡ በክፉ መናፍስቶች የሚመሩት ሕዝቦችም አእምሮዋቸውን ይስታሉ፡፡ ባህሪያቸውም ጭካኔ የተሞላበት ይሆናል፡፡ ብቸኛው ግባቸውም ማግኘት የሚችሉዋቸውን የእግዚአብሄር ልጆች ዙሪያቸውን ከብበው መግደል ብቻ ይሆናል፡፡ የራዕይን ቃል መረዳትና ማመን የሚገባችሁ ለዚህ ነው፡፡
 
የዘመኑ ቤተክርስቲያኖች ትላልቅ ሰፋፊና ረጃጅም ቤተክርስቲያኖች በመገንባት ብቻ ተወጥረዋል፡፡ ቤተክርስቲያኖቻቸውን ለመገንባት ሚሊዮን ዶላሮችን ያፈሳሉ፡፡ በልባቸው ውስጥ የሚገኘው ግን ለኢየሱስ ሰማዕትነትን የሚቀበል እምነት ሳይሆን ሐጢያት ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በመጀመሪያ ልባቸው ከሐጢያቶቻቸው መንጻት አለበት፡፡
 
ዓለም በቅርቡ ወደ መከራው ዘመን ወደ ሐመሩ ፈረስ ዘመን ይገባል፡፡ ሰማዕትነትን መቀበል የሚችል የእምነት ዓይነት እንዲኖራችሁና ለክርስቶስም እስከ ሞት ድረስ የታመናችሁ ሆናችሁ እንድትጸኑ ተስፋ አድርጋለሁ፤ እጸልያለሁም፡፡ የራዕይን ቃል በቤርያውያን መንፈስ በሚገባ ከመረመርን በኋላ ልናምንበት ይገባናል፡፡