Search

Поширені запитання щодо Християнської Віри

Запитання 1: Народження знову з води та Духа

1-22. በደግነትህ የላክልኝን መጽሐፎች ሳነብ በኢየሱስ ጥምቀት ላይ ያሉህ አንዳንድ እሳቤዎች አስደሳች ሆነው አግኝቼአቸዋለሁ። የእኛ ጥምቀት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት፣ ሞትና ትንሣኤ ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ የምታስተምረውን ልትነግረኝ ትችላለህ?

ከሁሉ በፊት በዕብራውያን 6፡2 ላይ እንደተጻፈው “ጥምቀቶችን” ልናተኩርበት ይገባናል። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሦስት የተለያዩ ጥምቀቶች አሉ፤ እነርሱም የመጥምቁ ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀት፣ ኢየሱስ ከመጥምቁ ዮሐንስ የተቀበለው ጥምቀትና እኛ እንደ ሥርዓት የምንወስደው የውሃ ጥምቀታችን ናቸው።
እኛ የምንወስደው ጥምቀት በኢየሱስ ጥምቀት ላይ ያለንን እምነት የምንመሰክርበት ነው። ይህ ማለት እኛ የምንጠመቀው ኢየሱስ ኃጢአቶቻችንን በሙሉ ለመውሰድ እንደተጠመቀና እነርሱንም ደግሞ ለማስተሰረይ በመስቀል ላይ እንደሞተ እንደምናምን እምነታችንን ለመመስከር ነው። “አሁንስ ፍቀድልኝ፥ እንደዚህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና” የሚለውን ማቴዎስ 3፡15ን መረዳት ትችላለህ። እዚህ ላይ “እንደዚህ” ማለት ኢየሱስ ራሱ የሰው ዘር ወኪል በሆነው በመጥምቁ ዮሐንስ በመጠመቅ የዓለምን ኃጢአቶች በሙሉ ተሸክሞዋል ማለት ነው።
ይህ ከኃጢአት አስገዳጅ ወጥመድ ለማዳን የእግዚአብሔር ጥልቅ እቅድ ነበር። ጌታ እግዚአብሔር “የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ” (ኢሳይያስ 53፡6) የእርሱንም ጽድቅ ሰጠን። እዚህ ላይ “ጽድቅ” ማለት በግሪክ “Δικαιοσύνη (Dikaiosynē)” ማለት ሲሆን የሚያመላክተውም “ትክክለኛነትንና ፍትህን” ነው። ይህም ኢየሱስ በእጆች መጫን መልክ በመጠመቅ የሰውን ዘር ኃጢአቶች በሙሉ እጅግ ትክክለኛና ጻድቅ በሆነ መንገድ እንደተሸከመ ይነግረናል።
 
 

የዳንነው በኢየሱስ ጥምቀት፣ በመስቀል ላይ ሞቱና በትንሣኤው ላይ ባለን ጠንካራ እምነት ነው።

ኃጢአቶችን ሁሉ ከልባችን ውስጥ ቆርጦ የጣለው የጥምቀቱ መንፈሳዊ ግርዘት ሐይል (ሮሜ 2፡29) በልባችን ውስጥ ያሉትን ኃጢአቶች አንጽቷል። ስለዚህ ሐዋርያው ጴጥሮስ ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው፦ “ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ (ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል) እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ” (የሐዋርያት ሥራ 2፡38)።
ኃጢአተኞች በሙሉ በኢየሱስ ስም በማመን በልቦቻቸው ውስጥ ከኃጢአት መንጻት አለባቸው። የስሙ ትርጉም ምንድነው? “እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” (ማቴዎስ 1፡21)። ኢየሱስ የሚለው ስም ሕዝቡን ከኃጢአቶቻቸው ሁሉ የሚያድን ‘አዳኝ’ ማለት ነው። ከኃጢአቶቻችን ሁሉ ያዳነን እንዴት ነበር? ኢየሱስ ከኃጢአቶቻችን ሁሉ ያዳነን በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ሞቱ አማካይነት ነው።
የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ወንጌልን በሰበኩ ጊዜ የኢየሱስን ጥምቀትና መስቀል ግልጽ በሆነ መረዳት አረጋግጠው እውነተኛውን ወንጌል አስተማሩ፣ ከዚያም በዚህ የሚያምኑትን አጠመቁ። እኛ የምንጠመቀው በልቡናችን ጥልቅ ውስጥ በኢየሱስ ጥምቀትና ሞት እንደምናምን በይፋ ለመመስከር ነው። ስንጠመቅ “ጌታ ሆይ ተመስገን። አንተ በጥምቀትህ አማካይነት ኃጢያቶቼን በሙሉ ተሸከምህ፣ ስለ እኔም ሞትህ፣ እኔን ለማዳንም ዳግመኛ ተነሣህ። በወንጌልህ አምናለሁ” ብለን እንመሰክራለን። እርሱ በመጥምቁ ዮሐንስ እንደተጠመቀ ሁሉ እኛም በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ሞቱ ላለን እምነት ምልክት ይሆን ዘንድ በአገልጋዮቹ በውሃው ውስጥ እንጠመቃለን። ስለዚህ በጥንቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበሩ ቅዱሳን በወንጌል ላይ ያላቸውን እምነት ከመሰከሩና ከሁሉም ኃጢአታቸው ሙሉ በሙሉ ከተነጹ በኋላ ለእምነታቸው ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ ተጠምቀዋል።
ነገር ግን የመጠመቅ ድርጊት ለመዳን አስፈላጊ የሆነ ሁኔታ አይደለም። እምነታችንን በጣም ግልጽ ማድረጉ አስፈላጊ ቢሆንም የውሃ ጥምቀቶቻችን ከመዳናችን ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም። መዳን የምንችለው በውሃውና በደሙ ወንጌል በማመን ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በእርሱ ጥምቀት ባመንን ጊዜ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ እንደተጠመቅን (ሮሜ 6፡3፣ ገላትያ 3፡27) ይናገራል።
ታዲያ እንዴት “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን” ቻልን? ይህ የሚቻለው በእርሱ ጥምቀት ስናምን ብቻ ነው፤ ምክንያቱም ሥጋ ማለትም አሮጌው ማንነታችን ከኢየሱስ ጋር ሊተባበርና ሊሰቀል የሚችለው በእርሱ ጥምቀት ላይ ባለን እምነት ብቻ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ በጥምቀቱ ኃጢአቶቻችንን በሙሉ ስለተሸከመ ሞቱ የበደላችን ፍርድ ነበር። በመሆኑም እኛም ደግሞ ከኢየሱስ ጋር በመስቀል ላይ ሞተናል። በሌላ አነጋገር እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ኃጢአቶችን የሚሠራው ሥጋችን ለኃጢአት ሞቶዋል፣ እኛም በጥምቀቱ አማካይነት ከኢየሱስ ጋር በመተባበራችን ከበደሎቻችን ሁሉ ድነናል።
በኢየሱስ ጥምቀትና ሞት አማካይነት ከእርሱ ጋር የተባበሩ ሰዎች ከትንሣኤውም ጋር ደግሞ መተባበር ይችላሉ። የእርሱ ትንሣኤ እኛ ከኃጢአት ሞት የተነሣንበት ትንሣኤ ብቻ ሳይሆን በእርሱ ፊት ቅዱሳን፣ ንጹህና ኃጢአት የሌለብን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን ዳግም እንድንወለድም ፈቅዶልናል።
የእርሱን ጥምቀት ተጠራጥረን ኃጢአቶቻችንን ወደ እርሱ ባናስተላልፍ ኖሮ ሞቱና ትንሣኤው ከእኛ መዳን ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ትርጉም አልባ ይሆኑብን ነበር። በእምነት ኃጢአቶቻቸውን በሙሉ በእርሱ ላይ ያኖሩ ጻድቃን ሆነው ዳግም እንዲወለዱ ከሚፈቅድላቸው ከእርሱ የመስቀል ሞት ጋር የተባበሩ ሰዎች ናቸው። ነገር ግን የእርሱን ጥምቀት ባለማመን ኃጢአቶቻቸውን በእርሱ ላይ ያላኖሩ ሰዎች ከእርሱ ሞትና ትንሣኤ ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም።
አንድ ባልና ሚስት በጋብቻ ሥርዓት አማካይነት ሕጋዊ ጥንዶች መሆናቸውን እንደምንቀበል ሁሉ የምዕመናን ጥምቀትም እንደዚሁ የታመነ ነው። የቅዱሳን ጥምቀት እንዲህ ያለውን ውስጣዊ እምነት የሚገልጡበት ውጫዊ መግለጫ ነው። በእግዚአብሔር፣ በቅዱሳንና በዓለም ፊት በኢየሱስ ጥምቀትና መስቀል ላይ ያለንን እምነት ስናውጅ እምነታችን ይበልጥ የማይናወጥ ይሆናል።
ኢየሱስ በመጥምቁ ዮሐንስ የተቀበለውን ጥምቀት እውነተኛ ትርጉም በተሳሳተ መንገድ ከተረዳን በኋላ በእርሱ ጥምቀትና በፋይዳው ባናምን መዳን እንደምንችል ልናምን አይገባንም። ይህ በአጭሩ የዲያብሎስ ብልጣ ብልጥ ማታለያ ነው። በራሳችን ጥምቀት በማመን ፋንታ በኢየሱስ ጥምቀት በትክክል በልባችን በማመን ከሁሉም ኃጢአታችን ሙሉ በሙሉ መንጻትና ሰማይ መግባት እንችላለን።