Search

Поширені запитання щодо Християнської Віри

Запитання 1: Народження знову з води та Духа

1-23. በየቀኑ ኃጢአትን እየሠራሁ እንዴት “ጻድቅ ነኝ” ማለት እችላለሁ?

እኛ ሰዎች እንደመሆናችን ከተወለድንበት ጊዜ ጀምሮ እስከምንሞትበት ጊዜ ድረስ ኃጢአቶችን እንሠራለን። እንደ እውነቱ ከሆነ የዚህ ምክንያቱ መሠረታዊው ተፈጥሮዋችን ነው፤ በኃጢአት የተወለድን ነን። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ” (ሮሜ 3፡10)። ሐዋርያው ጳውሎስ በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ ያለው ለዚህ ነው፦ “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፣ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ” (1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡15)።
“አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥ እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው። ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ” (ሮሜ 3፡21-24)።
ይህ የእግዚአብሔር “ጽድቅ” ማለት መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን በዮርዳኖስ ማጥመቁ ነው። ኢየሱስ ከመጠመቁ በፊት ዮሐንስን እንዲህ አለው፦ “አሁንስ ፍቀድልኝ፥ እንደዚህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና” (ማቴዎስ 3፡15)። የሰው ዘር ሁሉ ወኪል የነበረው መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን ባጠመቀው ጊዜ፣ ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአቶች እጅግ ተገቢና ቀና በሆነ መንገድ ተሸከመ። በዚህም ዮሐንስ ኢየሱስን ባጠመቀው ማግስት እንዲህ አለ፦ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐንስ 1፡29)።
ታዲያ እዚህ ላይ “የዓለም ኃጢአት” ማለት ምን ማለት ነው? ይህ የሚያመላክተው በምድር ላይ የመጀመሪያዎቹ የሰው ፍጡራን ከሆኑት ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ በዚህ ዓለም ላይ እስከሚኖረው የመጨረሻው ሰው ድረስ ያሉትን የሰዎች ሁሉ ኃጢአቶች ነው። ያለፉትም ሰዎች የዓለም ክፍል ናቸው፣ አሁን ያሉት ሰዎችም የዓለም ክፍል ናቸው፣ ወደፊት የሚኖሩትም ሰዎች እንደዚሁ የዓለም ኃጢአት ክፍል ናቸው። አልፋና ዖሜጋ የሆነው ኢየሱስ ለሁሉም ዘመናት ኃጢአቶች አንድን መሥዋዕት አቀረበ፣ በዮርዳኖስ በጥምቀቱ አማካይነት የዓለምን ኃጢአቶች በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ በመሸከም በመስቀል ላይ በመሞት። “እንደዚህ” ተቀድሰናል።
መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንዲህ ይላል፦ “በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል” (ዕብራውያን 10፡10)። ይህ የተጻፈው የተጠናቀቀ ያለፈ ጊዜ እንደሆነ ልብ በል። በእግዚአብሔር ካመንንበት ቅጽበት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስና ለዘላለም ሙሉ በሙሉ ተቀድሰናል፣ ኃጢአትም የለብንም። ጌታ ሁሉን ቻይ አምላክ ስለሆነ የዓለምን ጅማሬና ፍጻሜ በወፍ በረር አይን ያያል። ኢየሱስ ከ2,000 ዓመታት ያህል በፊት የተጠመቀ ቢሆንም ሰዎች ከዓለም ጅማሬ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሚሠሩዋቸውን ኃጢአቶች በሙሉ ወስዶዋል። ስለዚህ በመስቀል ላይ ከመሞቱ በፊት “ተፈጸመ” (ዮሐንስ 19፡30) አለ። እርሱ ከ2,000 ዓመታት በፊት በጥምቀቱ የዓለምን ኃጢአት ሁሉ ወስዶ በመስቀል ላይ ሞተ።
ከዳንን በኋላም እንኳን ቢሆን ኃጢአትን እንሠራለን፣ ምክንያቱም ሥጋችን ደካማ ነውና። ነገር ግን ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት ኃጢአቶችን በሙሉ በሰውነቱ ላይ በመሸከም ካለፉት፣ አሁን ካሉትና ከወደፊት ኃጢአቶች በሙሉ ታድጎናል፣ እነዚህን ኃጢአቶች በመስቀል ላይ ተኮነነ። ይህ ምሉዕና ጻድቅ የሆነ የእግዚአብሔር ማዳን ነው።
ኢየሱስ ወደፊት የምንሠራቸውን ኃጢአቶች በራሱ ላይ ባይወስድ ኖሮ አንድም ሰው በየቀኑ ከሚሠራቸው ኃጢአት አይድንም ነበር፣ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና” (ሮሜ 6፡23)። ያዕቆብና ኤሳው ገናም በእናታቸው ማህጸን ውስጥ ሳሉ ምንም መልካም ወይም ክፉ ነገር ሳይሠሩ እግዚአብሔር ሁለት ሕዝብ አድርጎ ለያቸው፤ ያዕቆብን ወደደው፣ ኤሳውንም ጠላው፣ እንዲህም አለ፦ “ታላቁም ለታናሹ ይገዛል” (ዘፍጥረት 25፡23)። ይህ ምንባብ የእግዚአብሔር መዳን ከእኛ ምግባሮች ጋር ምንም እንደማይገናኝ ነገር ግን በእርሱ ጥምቀትና ስቅለት በኩል ፍጹም በሆነው የእግዚአብሔር መዳን ለሚያምኑ ሰዎች እንደተሰጠ ይጠቁማል።
እኛ ሰዎች ከተወለድንበት ቅጽበት ጀምሮ እስከ ምንሞትበት ቅጽበት ድረስ ኃጢአተኛ ፍጡራን ሆነን ለሲዖል የታጨን ነን፤ እግዚአብሔር ግን ኃጢአቶቻችንን በአንድ እይታ አስቀድሞ አይቶ ስለወደደን በኢየሱስ ጥምቀትና መስቀል ኃጢአቶቻችንን በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ አስወገደ። የምንኖረው በተባረከ ዘመን ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ አለ፦ “ለኢየሩሳሌም ልብ ተናገሩ፥ የተቀጠረችበት ወራት እንደ ተፈጸመ፥ ኃጢአትዋም እንደ ተሰረየ (ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል)፥ ከእግዚአብሔርም እጅ ስለ ኃጢአትዋ ሁሉ ሁለት እጥፍ እንደ ተቀበለች ወደ እርስዋ ጩኹ” (ኢሳይያስ 40፡2)። ስለዚህ የኃጢአት ባርያ የነበርንበት ዘመን በኢየሱስ ጥምቀትና መስቀል ወንጌል አማካይነት አብቅቷል፣ ስለዚህ በወንጌል የሚያምን ማንኛውም ሰው ከኃጢአቶቹ መዳን ይችላል። “ከዚያ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው ይላል ጌታ፡- በልባቸው ሕጌን አኖራለሁ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ፥ ብሎ ከተናገረ በኋላ፡- ኃጢአታቸውንና ዓመጻቸውንም ደግሜ አላስብም ይላል። እነዚህም ስርየት ባለበት ዘንድ (ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል)፥ ከዚህ ወዲህ ስለ ኃጢአት ማቅረብ የለም” (ዕብራውያን 10፡16-18)።
እግዚአብሔር ከእንግዲህ ወዲህ በየቀኑ ለምንሠራቸው ኃጢአቶች አይፈርድብንም፣ ምክንያቱም አስቀድሞ የሰውን ዘር ኃጢአቶች በሙሉ አንጽቶ በኢየሱስ አማካይነት ኮንኖዋቸዋልና። 
ከዚህ የተነሣ በሕይወታችን አሁንም ድረስ ኃጢአቶችን ብንሠራም እንኳን ኃጢአት የሌለብን ጻድቃን ሆነን የጌታን ምጽአት መጠበቅና ቃሉን መከተል እንችላለን።