Search

শিক্ষা

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 8-6] የእግዚአብሄርን መንግሥት ወራሾች፡፡ ‹‹ሮሜ 8፡16-27››

‹‹ሮሜ 8፡16-27››
‹‹የእግዚአብሄር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል፡፡ ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሄር ወራሾች ነን፡፡ አብረንም ደግሞ መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን፡፡ ለእኛ ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ስቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ፡፡ የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሄርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና፡፡ ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፡፡ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፡፡ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነጻነት ወጥቶ ለእግዚአብሄር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነጻነት እንዲደርስ ነው፡፡ ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለን፡፡ እርሱም ብቻ  አይደለም፡፡ ነገር ግን የመንፈስ በኩራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን፡፡ በተስፋ ድነናል፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፡፡ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግስት እንጠባበቃለን፡፡ እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፡፡ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፡፡ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፡፡ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል፡፡ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ለቅዱሳን ይማልዳልና፡፡›› 
         
 
ሐጢያቶቻቸው ይቅር የተባሉላቸው ሰዎች በሙሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን በልባቸው ውስጥ መንፈስ ቅዱስ አላቸው፡፡ በ1ኛ ዮሐንስ 5፡10 ላይ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በእግዚአብሄር ልጅ የሚያምን በራሱ ምስክር አለው፡፡›› በልቡ ውስጥ የእግዚአብሄር ጽድቅ ያለው ሰው መንፈስ ቅዱስም በውስጡ ይኖራል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለዘላለም በልቡ ውስጥ እንዲኖር ያስቻለው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመኑ ነው፡፡ 
እኛ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ባለን እምነት አማካይነት ሐጢያቶቻችን ይቅር በመባላቸው የእግዚአብሄር ልጆች ሆነናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን አድሮ ‹‹እናንተ የእግዚአብሄር ልጆችና ሕዝቡ ሆናችኋል›› በማለት ምስክራችን ሆነዋል፡፡ በሌላ አነጋገር መንፈስ ቅዱስ በልባቸው ውስጥ በሌለባቸው ሰዎች ላይ ሕጉ ‹‹እናንተ ሐጢያተኞች እንጂ የእግዚአብሄር ልጆች አይደላችሁም›› በማለት ይመሰክራል፡፡ 
 
መንፈስ ቅዱስ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ለሚያምኑ ሰዎች ‹‹እናንተ የእግዚአብሄር ልጆች ናችሁ፡፡ እናንተ ሐጢያት የሌለባችሁ የእግዚአብሄር ሕዝቦች ናችሁ›› በማለት ይመሰክራል፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች ለመሆን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን እንደሚገባን እናውቅ ዘንድ እግዚአብሄር በሚገባ ግልጽ አድርጎልናል፡፡          
 
‹‹ምንም ነገር አይሰማኝም፡፡ ይህ ማለት እኔ የእግዚአብሄር ልጅ አይደለሁም ማለት ነውን?›› ብለው ይጠይቁ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ሰዎች በእምነታቸው በጣም ጨቅላዎች በመሆናቸው በልባቸው ውስጥ መንፈስ ቅዱስ እንዳለ አያውቁ ይሆናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ግን ተጠራጣሪዎች ብንሆንም ‹‹እናንተ የእግዚአብሄር ልጆች ናችሁ! በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አታምኑምን? ስለምታምኑ የእግዚአብሄር ሕዝብ ናችሁ›› በማለት እያስደሰተ ማረጋገጫን ይሰጠናል፡፡ ስለዚህ ተጠራጣሪዎች ብንሆንም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የምናምን ከሆነ የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ መንፈስ ቅዱስ እኛ የእግዚአብሄር ልጆች እንደሆንን ይመሰክራል፡፡፡ መንፈስ ቅዱስ በስሜቶቻችን አማካይነት በልባችን ውስጥ የሚያድር አንዳች ነገር አይደለም፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች በልባቸው ውስጥ ሐጢያት የለባቸውም፡፡ ሐጢያት ስለሌለባቸውም መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ይኖራል፡፡ እነርሱ በእርግጥም የእግዚአብሄር ልጆች ናቸው፡፡ 
 
መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ ‹‹እናንተ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀሉ አምናችሁ ይቅር ተብላችኋል፡፡ ስለዚህ ሐጢያት ስለሌለባችሁ የእግዚአብሄር ልጆች ናቸሁ›› በማለት ይነግረናል፡፡   
 
ነገር ግን የእርሱ ማረጋገጫ ልክ እንደ ሰው ድምጽ በድምጽ ጩኸት አልመጣም፡፡ ስለዚህ የፍንዳታ ድምጽ መስማት አትጠብቁ! ድምጽን መስማት የምትፈልጉ ከሆነ ሰይጣን ድምጹን ልክ እንደ ሰው በማስመሰል ሊፈትናችሁ ይሞክር ይሆናል፡፡ ሰይጣን የሚሰራው በሰዎች አስተሳሰቦች ውስጥ ሰርጎ በመግባት ሲሆን መንፈስ ቅዱስ የሚሰራው ግን በእግዚአብሄር ቃል መሰረት ነው፡፡ 
  
 

የእግዚአብሄር ጽድቅ ያላቸው ሰዎች የእርሱ ልጆችና ወራሾች ናቸው፡፡ 

 
ቁጥር 17ን አንድ ላይ እናብብ፡- ‹‹ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሄር ወራሾች ነን፡፡ አብረንም ደግሞ መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን፡፡››  
 
እኛ የእግዚአብሄር ልጆች ከሆንን የእርሱም ወራሾች ነን፡፡ ወራሽ ከወላጆቹ ሁሉን ነገር የሚቀበል ሰው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እኛ እግዚአብሄር አብ ያለውን ነገር ሁሉ ለመክፈል መብት አለን፡፡ ‹‹የእግዚአብሄር አብ ወራሽ ማነው?›› ተብለን ብንጠየቅ ‹‹በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑና የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ የተቀበሉ ሰዎች የእርሱ ወራሾች ናቸው›› ብለን መመለስ እንችላለን፡፡ 
 
የዚህ አይነት እምነት ያላቸው ሰዎች የተባረኩ ናቸው፡፡ በመንግሥቱ ውስጥም ከክርስቶስ ጋር የእግዚአብሄርን ክብር ይወርሳሉ፡፡ እዚህ ላይ ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች መሆናችን ስለተጠቀሰ አብረን ለመክበር ከእርሱ ጋር አብረን መከራ መቀበል ይኖርብናል፡፡ ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች መሆን ማለት በአባታችን መንግሥት ውስጥ ለዘላለም መኖር ማለት ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የምታምኑ ከሆነ ከክርስቶስ ጋር አብራችሁ ወራሾች ናችሁ፡፡ አባታችን ያለውን ነገር ሁሉ ስለምንወርስ ወራሾች ነን፡፡ 
 
ከጊዜ ወደ ጊዜ የእግዚአብሄር መንግሥት ወደ እኛ እየመጣ እንደሆነ ይታወቀኛል፡፡ ሁሉም ነገር የሚሆነው በራሱ ውብ ጊዜ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት የእግዚአብሄር ተስፋዎችም እንደዚሁ አንድ በአንድ በመፈጸም ላይ ናቸው፡፡ አሁን የቀረው የሕዝበ እስራኤል ንስሐ መግባት፣ ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው መመስከርና ከጥቂት ሌሎች ነገሮች ጋር አብሮ ከሐጢያቶቻቸው መዳን ነው፡፡ እስራኤሎች በሰባቱ ዓመት መከራ ወቅት ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው እንደሚቀበሉ ይታሰባል፡፡ 
 
የእግዚአብሄር መንግሥት በምድርና በሰማይ የመታወቁ ጉዳይ ከእስራኤሎች ንስሐ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የመጨረሻው ቀን በቅርቡ እንደሚመጣ አምናለሁ፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች ለዘላለም ከእግዚአብሄር ጋር የሚኖሩበት ያ ቀን እንደተቃረበ አምናለሁ፡፡ መላው ዓለም 2,000 ዓመተ ምህረትን ጠብቆ ያ ቀን እንደሚሆን አስቦ ነበር፡፡ 2,000 ዓመተ ምህረት ግን ቀደም ብሎ አልፎዋል፡፡ ስለ ሺህው ዓመት ምስቅልቅል የታሰበው አዋኪ ጭንቀት አልፎ አሁን 2002 አጋማሽ ላይ እንገኛለን፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች በምድር ላይ የሚሆኑት ለውጦች በሙሉ በ2,000 ዓመተ ምህረት ይሆናሉ ብለው አስበው ነበር፡፡ 
 
ያም ቢሆን ለረጅም ጊዜ የጠበቅነው የክርስቶስ መንግሥት አሁንም ወደ እያንዳንዳችን እየቀረበ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም እንደዚሁ የሐጢያቶችን ይቅርታ ያገኘነውን ሰዎች የእግዚአብሄር መንግሥት መቅረቡ ስሜቱ እንዲሰማን እየመራን ነው፡፡ ዛሬም እንደ በፊቱ እግዚአብሄር በተናገረው መሰረት ሁሉም ነገር ይፈጸማል፡፡ ያንን ቀን በእምነት እንጠብቀው፡፡
 
ወደፊት እስራኤል ለዓለም ሰላም የማሰናከያ ድንጋይና እንቅፋት ትሆናለች፡፡ በዚህ ምክንያት ከብዙ አገሮች ጋር ትቃቃራለች፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እስራኤል ለረጅም ጊዜ ሲጠብቁት የነበረው መሲህ በእርግጥም ኢየሱስ እንደሆነ እንደሚገነዘቡ ይናገራል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ለሐጢያቶቻቸው ይቅርታን ያገኛሉ፡፡ እግዚአብሄር ያቀደው ዕቅድ ሊፈጸም ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ሁሉ የሚሆኑት በጊዜያቸው ነው፡፡ ስለዚህ አንዳንድ የተቀባዠረባቸው የዘመን መጨረሻ ተንባዮች እንደሚተነብዩት በተወሰነ ቀንና ጊዜ እንዲሆኑ መጠበቅ የለብንም፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች የእግዚአብሄር ትንቢቶች ሲፈጸሙ ያያሉ፡፡ ምዕመናን እግዚአብሄር ተስፋ የሰጠውና በምድር ላይ የሚቋቋመው መንግሥትና መንግሥተ ሰማይ እየመጡ እንደሆነ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ቀን እየቀረበልን እንደሆነ አምናለሁ፡፡ 
 
ጌታ ቃል የገባቸው ነገሮች አንድ በአንድ እውነት የሚሆኑበት ጊዜ በቅርብ ይመጣል፡፡ እግዚአብሄር ተስፋ የሰጠው የሺህ ዓመት መንግሥትና የእግዚአብሄር መንግሥት የሚተገብሩበት ዘመን በጣም ቅርብ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡ እናንተም እንደ እኔ በመንፈስ ቅዱስ ተመርታችሁ እንደዚህ ታስባላችሁን? እያንዳንዱ የእግዚአብሄር ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እንደሚፈጸም ታምናላችሁን? መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሄርን ተስፋዎች በሙሉ በተጨባጭ በልባችን እንድናምን ያግዘናል፡፡
 
እኛ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በመጨረሻው ዘመን የእግዚአብሄር ተስፋዎች ፈጥነው እንደሚፈጸሙ በልባችን እርግጠኞች ነን፡፡ በአእምሮዋችንና በተስፋዎቻችን ውስጥ የሚያልፈው ነገር ከእግዚአብሄር ትንቢቶች ጋር ሆኖ እንደሚፈጸም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እናምናለን፡፡ ይህ እውነተኛ እምነት ነው፡፡ 
 
እናንተና እኔ የእግዚአብሄርን የተስፋ በረከቶች ሁሉ የምንወርስ ወራሾች ነን፡፡ ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ ውስጥ መቆየት ያስፈልገናል፡፡ የእግዚአብሄር መንግሥት በቅርቡ ይመጣልናል፡፡ እስራኤሎችም በቅርቡ አምነው ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛቸው አድርገው ይቀበላሉ፡፡ 
 
ብዙ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ‹‹ጌታ ኢየሱስ እባክህ ና›› በማለት እርሱን እየጠበቁት ነው፡፡ ጳውሎስ የእግዚአብሄር ወራሽ በመሆኑ ያለፈበት መከራ በቅርቡ ከሚያገኘው ክብር ጋር ሊነጻጸር እንደማይችል ተናገረ፡፡ ከክርስቶስ ጋር አብሮ ክብርን ለመቀበል ከእርሱ ጋር አብረን መከራን መቀበል አለብን ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሄር መንግሥት እንደሚመጣ እናምናለን፤ እንጠብቃለንም፡፡ ከክርስቶስ ጋር አብረን ለመክበር ከእርሱ ጋር አብረን መከራን መቻል ይኖርብናል፡፡ 
 
የጳውሎስ ተስፋ እንስሶችንና ተክሎችን ሁሉ ጨምሮ ፍጥረት ሁሉ ከሞት አርነት እንዲወጣ ነበር፡፡ ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሄርን ልጆች መገለጥ እየተጠባበቀ ያለው ለዚህ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች ተስፋ ፍጥረታት ሁሉ ለዘላለም መኖር የሚችሉበት ቀን የሚመጣ መሆኑ ነው፡፡            
 
ስለዚህ እኛ ምዕመናኖች በዘላለም ሕይወት እንደተባረክን መረዳት አለብን፡፡ ጌታችን የሚመጣበትን ቀን በዕድሜ ዘመናችን እናይ ይሆን ወይም ጌታችን እኛን ለመውሰድ ከእንቅልፋችን ያነቃን ይሆን እርሱን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ 
  
 

በእኛ የሚገለጠው የእግዚአብሄር ክብር በእርግጥም ታላቅ ነውን? 

 
በቅርቡ ለጻድቃን የሚገለጠው ክብር ዘላለማዊ መንግሥትን የመውረስና በእግዚአብሄር ክብር ውስጥ ለዘላለም የመኖር ዘላለማዊ ክብር ነው፡፡ ከእንግዲህ ሞት፣ ሐዘን፣ ልቅሶ አይኖርም፡፡ በመንግሥቱ ውስጥ ከእንግዲህ ስቃይ አይኖራም፡፡ መንግሥቱም የሚያበራለት የጸሐይ ወይም የጨረቃ ብርሃን አያስፈልገውም፡፡ የእግዚአብሄር ክብር ያበራለታልና፡፡ ብርሃኑ በጉ ነው፡፡ ይህ ስፍራ ኢየሱስና ዳግም የተወለዱ ሐጢያት አልባ ምዕመናኖች ብቻ የሚገኙበት ስፍራ ነው፡፡ መንግሥቱ በወርቃማ ጨረሮች የተሞላ ነው፡፡ ለዘላለም የምንኖርበት የመንግሥቱ ክብር እንዲህ ታላቅ ስለሆነ ቃላቶች ሊገልጡት አይችሉም፡፡ እኛ የምንጠብቀው ይህ ክብር በጣም ታላቅ ስለሆነ ጳውሎስ የአሁኑ ዘመን መከራችን ለእኛ ሊገለጥ ካለው ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም እንዳልሆነ ይናገራል፡፡
 
አንዳንድ ጊዜ በዚህ ዓለም ላይ ለእግዚአብሄር እየሰራን ሳለ በተፈጥሮ ውስጥ የእግዚአብሄርን ክብር ማየት እንችላለን፡፡ ብዙ ቀለማት ያላቸውን አበቦች፣ የሳር ምንጣፎችን፣ በሚያብረቀርቁ ቅጠላ ቅጠሎች ላይ የሚታየውን ተፈጥሮ፣  ሞቃታማውን አየር፣  የደኖችን ትኩስ ሽታ፣  ጥርት ያሉ ነፋሶችን፣  በብርዳማ ምሽቶች ላይ ብሩህ ሆነው የሚያበሩትን ከዋክብቶች ስንመለከት፣  ስለ አራቱ ወቅቶች ስናስብ ስለ ሰማይ ከማሰብ መቆጠብ አንችልም፡፡ እነዚህን የእግዚአብሄር ፍጥረት ድንቆች ስናይ የእግዚአብሄር መንግሥት ፈጥኖ እንዲመጣ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ 
የእግዚአብሄር መንግሥት ሲመጣ ሞት አይኖርም፡፡ እኛም በክብር እንኖራለን፡፡ አንዳች እጦት ስለማይኖር በሐብትና በብልጥግና እንኖራለን፡፡ ሁሉም ነገር ፍጹምና ዝግጁ በሆነበት ስፍራ በክብር እንደምኖር ማሰብ ብቻ ልቤን በእግዚአብሄር ክብር ይሞላዋል፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ የእኛ የምዕመናን የመሆናቸው እውነታ ልክ ሕልም ይመስላል፡፡ ዳግም መወለዳችንንም ደግመን እንድናመሰግን ያደርገናል፡፡ ልቤን በተስፋ ሙላት የሞላውን ጌታ አመሰግናለሁ፡፡ 
 
አሁን ሰማይን ተስፋ የምናደርገው በአሳባችን ብቻ ነው፡፡ ወደፊት ግን የእግዚአብሄር ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ተስፋችን ይበልጥ ይጠነክራል፡፡ እየቀረበ ስላለው የእግዚአብሄር ክብር ያለን ስሜትም ቀናቶች እየነጎዱ ሲሄዱ ይበልጥ ይበረታል፡፡ 
 
ምዕመናን የወደፊቱን ተስፋ የሚያደርጉት ለዚህ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ማመንና የወደፊቱን ተስፋ ማድረግ የእግዚአብሄርን መንግሥት የሚወርሱ ሰዎች ክብርና እምነት ናቸው፡፡ ታዲያ ይህ የከበረ እምነት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ለሚያምኑ ብቻ የተሰጠ በረከት ነውን? መልሱ የማያወላውል አዎን ነው! የእግዚአብሄር ክብር ለጻድቃን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ለሚያምኑ ሰዎች ከመሰጠቱ በፊት ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ በጊዜው እግዚአብሄር ስለ ክብሮቹ የሰጣቸው ተስፋዎች በሙሉ ይፈጸሙልናል፡፡ እነዚህ የከበሩ ነገሮች በሙሉ በእርግጥም ለቅዱሳኖች ይፈጸሙላቸዋል፡፡ እኛን የሚጠብቀን ክብር እጅግ ድንቅና ውብ ነው፡፡ 
 
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ተመሳሳይ እምነት ያለን እናንተና እኔ ወደ እግዚአብሄር ክብር መንግስት እንገባለን፡፡ ግራ የሚያጋባውና ክፉ የሆነው ዓለም አንዳንድ ጊዜ ልባችንን ያጨልመው ይሆናል፡፡ እኛም ተስፋ ልንቆርጥና አቅጣጫችንን ልንስት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ዳግም የተወለዱ ሰዎች የእግዚአብሄር ወራሾች መሆናቸውን በማመን እነዚህን ችግሮች ማሸነፍ ይችላሉ፡፡ ሐጢያት በሌለባቸው ምዕመናን ልብ ውስጥ ሁሉም አይነት ችግሮች ቢኖሩም የእግዚአብሄርን ተስፋዎች እያስታወሱ ብርታትን አግኝተው በመኖር መቀጠል ይችላሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ በመኖሩ፣ እኛን በማጽናናቱና የእግዚአብሄር ልጆች መሆናችንን ለመንፈሳችን በመመስከሩ አመስጋኝ ነኝ፡፡ 
 
በቅርቡ ከሐጢያቶቻቸው የዳኑ ሰዎች የሰማይን ክብር ተስፋ ማድረግና በተስፋ መኖር ይገባቸዋል፡፡ እኛ በእኩል ደረጃ የእግዚአብሄር ሕዝቦች ነን፡፡ ለረጅም ጊዜ በቤተክርስቲያን ውስጥ የእምነትን ሕየወት ኖራችሁ ከሆነ በውስጣችሁ ያለው መንፈስ ቅዱስ በከበረው ውርሳችሁ ባለጠግነት ስትደሰቱ ማየት ይችላል፡፡ 
    
 

የጻድቃኖችም ልብ እንዲሁ በዚህ ምድር ላይ ይቃትታል፡፡ 

 
ቁጥር 23ን በአንድ ላይ እናንብበው፡- ‹‹እርሱም ብቻ  አይደለም፡፡ ነገር ግን የመንፈስ በኩራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን፡፡›› ራሳችንን ‹‹በሕይወት ስንኖር ተስፋ የምናደርገው ምንድነው?›› ብለን እንጠይቅ፡፡ እኛ ምዕመናኖቹ የሰውነታችንን ቤዛነት ተስፋ እያደረግን እንኖራለን፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች ነን ስንል ልጅ የሆነው መንፈሳችን ነው ማለታችን ነው፡፡ ሰውነታችን ገና ክብርን ስላልተቀበለ ስለዚህ ምዕመናን ሁሉ ሰውነታችን እንደሚለወጥ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ 
 
የምዕመናን ሰውነት የእግዚአብሄርን ክብር ሲለብስ በእሳት ውስጥ ማለፍ ይችላሉ፤ አይቃጠሉም፡፡ በማናቸውም አይት መሰናክሎች ወይም ግምቦች ውስጥ ማለፍ ይችላሉ፡፡ የተለወጡት አካሎቻችን ከጊዜና ከቦታ ገደቦች አርነት ይወጣሉ፡፡ 
 
ነገር ግን አካሎቻችን እስከ አሁን ድረስ አልተለወጡም፡፡ ስለዚህ በውስጣችን የመንፈስ በኩራት ይቃትታል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዳግም የተወለዱ ጻድቃን የሰውነታቸውን ቤዛነት ይጠብቃሉ፡፡ 
 
መቃተት! የመንፈስን በኩራት የተቀበልን እኛ እንኳን እንደምንቃትት ተጽፎዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችሁ ሲቃትት ተሰምቶዋችኋልን? እርሱ የቃተተው መቼ ነው? ሥጋዊ ምኞቶችን ስንከተል መንፈስ ቅዱስ ይቃትታል፡፡        
 
ዓለምን ተመልክተን የምናየውን ስንቀበል በውስጣችን ያለው መንፈስ ቅዱስ ይቃትታል፡፡ ሰውነታችን አልተለወጠም፡፡ ስለዚህ ዓለማዊ ነገሮች በመከተል ለመደሰት ይሞክራል፡፡ ነገር ግን ነፍሳችን ቀድሞውኑም ስለተለወጠ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ይቃትታል፡፡ ስለዚህ ልባችን ዓለማዊ ተድላዎችን ከመከተል መመለስና የመንፈስ ቅዱስን ምሪት መቀበል አለበት፡፡ 
 
መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሄር ወራሾች በሆንነው በእኛ ውስጥ ይቃትታል፡፡ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ነውና፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ስንኖር የወደፊቱ ምንኛ ጨለማ እንደሆነና ሰውነታችንም ምን ያህል ደካማ እንደሆነ ማየት እንችላለን፡፡ እንዲህ ባሉ ወቅቶች ቀና ብለን ወደ ላይ መመልከትና የእግዚአብሄር ወራሾች የሚቀበሉዋቸውን ባርኮቶች መናፈቅ ይገባናል፡፡ ምክንያቱም እነርሱ ሰውነታቸውም ቤዛነትን እንደሚያገኝ ያውቃሉና፡፡ ምዕመናን ሙሉ በሙሉ ቤዛነት ያገኘ ፍጹም የሆነ ሰውነት የሚያገኙበትን ቀን ይጠብቃሉ፡፡   
 
 
የከበረውን ተስፋ በመጠባበቅ መኖር፡፡ 
 
ቁጥር 24 እና 25ን በአንድ ድምጽ እናንብብ፡- ‹‹በተስፋ ድነናል፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፡፡ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግስት እንጠባበቃለን፡፡›› 
 
‹‹የሐጢያቶቻችንን ሁሉ ይቅርታ የተቀበልነው የእግዚአብሄርን መንግሥት ተስፋ በማድረግ ነውን?›› ይህንን ጥያቄ እንጠይቅ፡፡ እኛ የሐጢያቶቻችንን ይቅርታ የተቀበልነው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን እንደሆነ ተናግረናል፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግስት እንጠባበቃለን፡፡›› 
 
ወደ ሰማይ ለመሄድና ከሐጢያቶቻችን ነጻ ለመውጣት በውሃውና በመንፈስ ቅዱስ በማመን መዳን አለብን፡፡ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ከዳንን በኋላ ዓይኖቻችንን ወደ ዓለም መልሰን የሚታየውን ተስፋ የምናደርግ ከሆነ የእግዚአብሄርን ክብር አላወቅነውም፡፡ እርሱንም እየጠበቅን አይደለም ማለት ነው፡፡ የምናየውን ተስፋ የምናደርግ ከሆነ ያ ተስፋ ሊሆን አይችልም፡፡ ጳውሎስ ‹‹የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል?›› ብሎ የጠየቀው ለዚህ ነው፡፡ እኛ አሁን ጻድቃን የሆንን ሰዎች በምድር ላይ ያለውን ተስፋ ማድረግ አይገባንም፡፡ ነገር ግን እንደ ተስፋው ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር መጠበቅ አለብን፡፡ (2ኛ ጴጥሮስ 3፡13) 
 
ጻድቃን ተስፋ የሚያደርጉት ይህ አይነቱን እምነት ነው፡፡ ጻድቃን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን ተስፋ በማድረግ ይኖራሉ፡፡ በሥጋ ዓይኖቻችን የምናየው ነገር በትክክል ተስፋ የምናደርገው ነገር አይደለም፡፡ በሥጋዊ ዓይኖቻችን ማየት አንችልም፡፡ ስለዚህ በመንፈሳዊ ዓይኖቻችን ተስፋ የተሰጠውን የእግዚአብሄርን የክብር መንግሥት እንጠባበቃለን፡፡ በእርግጥ ጻድቃን የሆኑ ሰዎች ተስፋቸውን በእግዚአብሄር መንግሥት ላይ የሚያደርጉት ለዚህ ነው፡፡ ተስፋው እግዚአብሄር የነገረን ነገር በእርግጥም የሚፈጸም መሆኑ ነው፡፡ 
 
እግዚአብሄር እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹እንዲህም ከሆነ እምነት ተሰፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፡፡›› (1ኛ ቆሮንቶስ 13፡13) በመንግሥተ ሰማይ ላይ ባለን እምነትና ተስፋ የሐጢያቶቻችንን ስርየት አግኝተናል፡፡ የእርሱ መንግሥት ወደ ምድር ይመጣል፡፡ እርሱ በሰማያት ይኖራል፡፡ እኛም በመንግሥቱ ውስጥ ለዘላለም እንደምንኖር ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እግዚአብሄር ተስፋ በሰጠው ቃል የምናምነውና የአሁኑን ዘመን መከራችንን የምንታገሰው ለዚህ ነው፡፡ 
 
እዚህ ላይ ‹‹የማናየውን ተስፋ ብናደርገው በትዕግስት እንጠባበቃለን›› ተብሎ ተጽፎዋል፡፡ በትዕግስት የምንጠብቀው በዓይኖቻችን ማየት የምንችለውን ነገር አይደለም፡፡ የምንጠብቀው በአካል የማናያቸውን የእግዚአብሄር ተስፋዎች ነው፡፡ የእግዚአብሄር ተስፋዎች ለእኛ ለምዕመናን ይፈጸሙልናል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሄር ክብር በቅርቡ እንደሚገለጥ ተነግሮአልና፡፡ እኛም በዚህ ተስፋ እናምናለን፡፡ ጌታችን ዳግመኛ ወደዚህ ምድር እንደሚመጣና ስለምናምን የአሁኑን ዘመን መከራ እንታገሳለን፡፡ 
 
የእግዚአብሄር መንግሥት ያለ ምንም ጥርጥር ወደዚህ ምድር ይመጣል፡፡ ወንጌል ለአሕዛቦች ሁሉ ከተሰበከ በኋላ የእግዚአብሄር መንግሥት በእርግጥም ይመጣል፡፡ ጻድቃን ያንን ቀን በትዕግስት ይጠብቃሉ፡፡ ጌታችን እኛ እየጠበቅነው ይመጣል፡፡ ይህ በዚህ ዘመን ለምንኖረው ለእናንተና ለእኔ እውነት ነው፡፡   
 
መጽሐፎቻችንን ወደ ዩክሬናውያን ቋንቋ የምትተረጉምልን አንዲት ዩክሬናዊት ሴት አብሮ ሰራተኛ አለች፡፡ በቅርቡ የዓለም የንግድ ማዕከል ሕንጻዎች በሽብር ጥቃት ሲወድሙ አይታ ግራ እንደተጋባችና እንደፈራች ተናገረች፡፡ ይህ በራዕይ ውስጥ ያለውን ‹‹የገረጣ ፈረስ ዘመን›› የሚያስተዋውቅ ስለመሆኑና ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ማናቸውም አይነት መጽሐፎች ይኖሩ እንደሆነ ጠየቀችን፡፡ 
 
ይህ ክስተት የገረጣው ፈረስ ዘመን ምልክት ስለመሆኑ በተጨባጭ መናገር አንችልም፡፡ ነገር ግን ግንኙነት ያለው ስለመሆኑ ልንክድ አንችልም፡፡ እንደዚህ አይነት ነገሮች አዘውትረው የሚከሰቱ ከሆነ ጦርነቶች ይኖራሉ፡፡ መንግሥታቶችም እርስ በርሳቸው ይዋጋሉ፡፡ ጦርነቶች ሲፈነዱ ዓለም በረሃብ ይሰቃያል፡፡ ‹‹የገረጣው ፈረስ ዘመንም›› ድንገት ሊመጣ ይችላል፡፡ 
 
ስለዚህ የዓለምነን ጥፋት የሚተነብዩትን እነዚህን ክስተቶች ስንመለከት ወንጌልን እስከ ዓለም ዳርቻ ማሰራጨት የሚገባን የመሆኑን መሃላዬን አድሳለሁ፡፡ አሰቃቂ ነገሮች በሚከሰቱበት ጊዜ በዚህ ዓለም ተስፋ መቁረጣችንና ልባችንም መቃተቱ እውነት ነው፡፡ ቢሆንም በሕይወት እስከኖርን ድረስ በሥጋዊ ዓይኖቻችን ሳይሆን በመንፈሳዊ ዓይኖቻችን የምናየውን የእግዚአብሄርን መንግሥት መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ 
 
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ስለምናምን መንግሥተ ሰማይን ተስፋ በማድረግ በትዕግስት እንጠባበቃለን፡፡ የእግዚአብሄር መንግሥት ወደ እኛ እየቀረበ መሆኑን ስለምናምን መከራዎችን ሁሉ መታገስ እንችላለን፡፡ ይህ የሚቻለው መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ ስለሚኖር ነው፡፡ 
ተቸግራችኋልን? በሚገባ ተቋቋሙ፤ ታገሱም፡፡ የተቸገራችሁት እናንተ ብቻ ሳትሆኑ ሁላችንም ነን፡፡ ይህ ሲያበቃ ሁሉም ነገር እንደሚስተካከል ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በአካላችሁ መከራዎች ካልገጠሙዋችሁ በመንፈሳዊ ሁኔታችሁ ተስፋን ማዳበር እንደማትችሉ አታውቁምን?  ሥጋ በጣም ሲመቸው እግዚአብሄርን አንመለከተውም፡፡ ከእርሱም በረከቶችን አንሻም፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሄር እንርቃለን፡፡ ዳግም የተወለድን ሰዎች መጪውን ክብር ተስፋ ማድረግና የአሁኑን ዘመን መከራችንን መታገስ ይገባናል፡፡ 
 
እግዚአብሄር ለጌታ ሲሉ ችግሮችን በትዕግስት የሚቋቋሙ ሰዎች የተባረኩ እንደሆኑ ተናግሮዋል፡፡ የእግዚአብሄር መንግሥት ወደ ምድር የሚመጣበት ቀን ቀርቦዋል፡፡ እኛም ወደ መንግሥቱ እንገባለን፡፡ ያንን በትዕግስት መቋቋምና ያንን ቀን በሚመለከት ተስፋ መቁረጥ የለብንም፡፡ አሁን ምንም ያህል አሳዛኝና አስቸጋሪ ቢሆንም የእግዚአብሄር መንግሥት አዲስ ሰማይና ምድር ሆኖ እስኪመጣ ድረስ መጠበቅና መታገስ ይገባናል፡፡ 
       
 
መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሄር ጽድቅ ያላቸውን ሰዎች ያግዛል፡፡ 
 
ቁጥር 26ን እናንብብ፡- ‹‹እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፡፡ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፡፡ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፡፡››  
 
መንፈስ ቅዱስ ስለ እኛ ይጸልያልን? ሰዎ ይጸልያል! መንፈስ ቅዱስ ድካማችንን ስለሚያውቅ ይማልድልናል፡፡ 
 
ስለ መንፈስ ቅዱስ መቃተት ጥቂት ተናግሬያለሁ፡፡ እደግመዋለሁ፤ እግዚአብሄር እንድንሄድበት በማይፈልገው አቅጣጫ ስንጓዝ መንፈስ ቅዱስ ይቃትታል፡፡ የዓለምን ሁኔታዎች ተመልክተን በእነርሱ ስንቃተት፣ እግዚአብሄር አባታችን እንድንሄድበት በማይፈልገው አቅጣጫ ስንጓዝ ወይም የአባታችንን ፈቃድ ችላ ብለን ለፈቃዱ በግድየለሽነት ስንኖር መንፈስ ቅዱስ ይቃትታል፡፡ 
ዳግም በተወለደ ምዕመን ውስጥ ያለው መንፈስ ቅዱስ በማይነገር መቃተት ሲቃትት በልባችን ውስጥ ያለውን ጉልበት እናጣና እንደክማለን፡፡ መንፈስ ቅዱስ እንድንጸልይ የሚያደርገን በዚህ ጊዜ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ስለ እኛ ይማልዳል ወይም መጸለይ የሚገባን የመሆኑን እውነታ እንድንረዳ ያደርገናል፡፡ 
 
መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ ይቃትታል፡፡ በአባታችን ፊትም እንደ ፈቃዱ እንድጸልይ ያደርገናል፡፡ ‹‹እግዚአብሄር አምላክ በጥምቀትህና በመስቀል ላይ ባፈሰስከው ደምህ ሐጢያቶቻችንን ደምስሰሃል፡፡ በዚህም የአንተ ልጆች ሆነናል፡፡ ዳግም ምጽዓትህ በቅርቡ በምድር ላይ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ፈቃድህ ይፈጸም ዘንድ እንጸልያለን፡፡›› እንዲህ እንጸልያለን፡፡ 
 
መንፈሳዊ እምነትን እንለምናለን፡፡ ‹‹አቤቱ እኛ ምስኪኖችና በዓይኖችህም ፊት ጎስቋሎች ነን፡፡ ስለዚህ እባክህ ፈቃድህ ይፈጸም ዘንድ የሚያስፈልገውን እምነት ስጠን፡፡›› ያን ጊዜ እግዚአብሄር ያግዘናል፡፡ ምክንያቱም እርሱ ድካማችንን ያውቃልና፡፡ መንፈስ ቅዱስ ብቻችንን አይተወንም፡፡ ነገር ግን እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ እንድንጸልይ ያደርገናል፡፡ እርሱም ስለ እኛ በመጸለይ ልባችንን ያበረታል፡፡ 
 
መንፈስ ቅዱስ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ እንድንጸልይ ያደርገናል፡፡ እርዳታን ስንጠይቅም እግዚአብሄር ለእኛ ያለው ፈቃድ ምን እንደሆነ እንድናውቅ በማድረግ አዲስ ጉልበትን ይሰጠናል፡፡ 
 
‹‹እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፡፡ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፡፡››  
 
እነዚህ ነገሮች ይታወቁዋችኋልን? እግዚአብሄር እንድናደርግ ከሚፈለገው ነገር የተለየ ነገር ስታስቡና ስታደርጉ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ለጻድቃን ሰዎች አንድ የተሳሳተ ነገር እንዳለ ሲነግረን ይታወቃችኋልን? መንፈስ ቅዱስ ‹‹ተሳስታችኋል!›› ሲለን ልባችን መቃተት ይጀምራል፡፡ ይህ የመንፈስ ቅዱስ መቃተት እንደሆነ ታውቃላችሁን? ምናልባት የጻድቃን ልብ የተደሰተው መንፈስ ቅዱስ ከውስጥ በመደሰቱ ምክንያት እንደሆነ ተለማምዳችሁ ይሆናል፡፡ እንደዚያ ከሆነ ልባችሁ ሲቃትት የሚቃትተው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ታውቃላችሁ፡፡ 
 
ስንደክምና የተሳሳተ ነገር ስናደርግ መንፈስ ቅዱስ በመቃተት ስለ እኛ ይማልዳል፡፡ እግዚአብሄር አባታችንም ጉልበትን ይሰጠናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ አዲስ መንፈሳዊ ጉልበት በመስጠት ለሁሉም ነገር እንድንጸልይ አድርጎናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በልባቸው ውስጥ ያለባቸው ሰዎች በጣም ደስተኞች የሚሆኑት ለዚህ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእግዚአብሄር ቃል አማካይነት ጉልበትን ይሰጠናል፡፡ በሌላ አነጋገር መንፈስ ቅዱስ አዲስ መንፈሳዊ ጉልበትን ይሰጠን ዘንድ በቃሉ አማካይነት በልባችን ውስጥ ይሰራል፡፡ 
 
መንፈስ ቅዱስ በሌላ መንገድ መናገር አይፈልግም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያንና ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር በምናደርገው ሕብረታችን አማካይነት ጉልበትን ይሰጠናል፡፡ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በጣም አስፈላጊ የሆነችውና በመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች ውስጥ በጣም አስፈላጊ ሚና የምትጫወተው ለዚህ ነው፡፡ 
 
በቤተክርስቲያን ውስጥ ምዕመናን ሕብረታቸው፣ ምስጋናቸውና መልዕክቶቻቸው አሉ፡፡ ሰባኪዎች ማንም ይሁኑ በተገቢው ጊዜ ተገቢ መልዕክቶችን ያቀርቡ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ተገኝቶ በእነርሱ ይሰራል፡፡ መንፈስ ቅዱስ መልዕክቱን በሚሰጡና መልዕክቱን በሚቀበሉ መካከል በመስራት አእምሮዋቸውን ያድሳል፡፡ ለእያንዳንዳቸውም የሚያስፈልጉዋቸውን በረከቶች ይሰጣቸዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ይህንን የሚያደርገው ጻድቃን ሰዎች በሚሰበሰቡበት የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ለምዕመናኖች በጣም አስፈላጊ የሆነችው ለዚህ ነው፡፡ አማኙ በልቡ ውስጥ ችግር ሲገጥመው ችግሩን ለሌሎች ማጋራት የማይችል ከሆነ የእግዚአብሄር አገልጋዮች ይህንን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ያውቁታል፡፡ ምዕመናኖች በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ ሲሰበሰቡ መንፈስ ቅዱስ ልባቸውን መንካትና ማጽናናት ይችላል፡፡ መንፈስ ቅዱስ መጽሐፍ ቅዱስን አጥብቀው እንዲይዙ ያግዛቸዋል፡፡ የሚያገግሙበትንም ጉልበት ይሰጣቸዋል፡፡           
የእምነት ሕይወታችንን ስንኖር በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እናምናለን፡፡ የሐጢያቶቻችንን ይቅርታም እናገኛለን፡፡ የእግዘዚአብሄርም ልጆች እንሆናለን፡፡ እንደ ማረጋገጫም መንፈስ ቅዱስን በስጦታ መልክ እንቀበላለን፡፡ ከዚያም እግዚአብሄር የራሱን ቤተክርስቲያን ይሰጠናል፡፡ ቤተክርስቲያንን ከሰጠን በኋላ እግዚአብሄር በቤተክርስቲያን አማካይነት ለአገልጋዮቹ ይናገራል፡፡ አገልጋዮቹም መልዕክቱን እንዲሰብኩ ያደርጋቸዋል፡፡ በቃሉ ቁስላችንን ይፈውሳል፡፡ ለደከሙትም ጉልበትን ይሰጣል፡፡ በልባቸው ምስኪን የሆኑትንም ይባርካቸዋል፡፡ የእርሱን ሥራ የሚያከናወኑበትንም አቅም ይሰጣቸዋል፡፡ እርሱ በእኛ አማካይነት ፈቃዱን ይፈጽማል፡፡ ስለዚህ ምዕመናኖች ራሳቸውን በጭራሽ ከቤተክርስቲያን መገንጠል አይችሉም፡፡ 
 
ምዕመናኖች በጭራሽ ከሌሎች ጻድቃን ጋር ያላቸውን ቁርኝት ወይም በእግዚአብሄር ቃል ላይ ያላቸውን ማደግ መበጠስ አይችሉም፡፡ ፍጹም እውነት ሊገኝ የሚችለው በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን በቤተክርስቲያን ውስጥ እርስ በርሳቸው መቆራኘት ያስፈልጋቸዋል፡፡ አንድነት የሌለው እምነት ሐሳዊ እምነት ነው፡፡
 
መንፈስ ቅዱስ በልባችሁ ውስጥ እንደሚኖር ታምናላችሁን? ቃሉ እንደሚለውና ቤተክርስቲያንም በመልዕክቷ እንደምትነግረን ከእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ጋር ስንተባበር መንፈስ ቅዱስ ያግዘናል፡፡ በረከቶችንም በመስጠት ዓይኖቻችንን ለእውነት ይከፍታል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ባለ እምነት ከቤተክርስቲያን ጋር ተባበሩ፡፡ ያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ይደሰታል፡፡
 
እስከዚህች ሰዓት ድረስ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ኖረናል፡፡ ወደፊትም በእርሱ እርዳታ እንኖራለን፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሐጢያቶችን ሁሉ ይቅርታ ላገኘነው ለእኛ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ማወቅና ማመን ይኖርብናል፡፡ እኛ በመንፈስ ቅዱስ መኖርና በልባችንም ምሪቱን መቀበል እንደሚኖርብን ማወቅ አለብን፡፡ መንፈስ ቅዱስ በልባቸው ውስጥ ያላቸው ሰዎች የእርሱን ፈቃድ መከተል አለባቸው፡፡ ጻድቅ ሰዎች ከሆናችሁ መንፈስ ቅዱስ እንደመራችሁ የሕይወትን ሕግ መከተል አለባችሁ፡፡
 
ቁጥር 27ን በአንድ ላይ እናንብብ፡- ‹‹ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል፡፡ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና፡፡›› አባታችን እግዚአብሄር በውስጣችን የሚኖረውን የመንፈስ ቅዱስ አሳብ ያውቃል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በአእምሮዋችን ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ያውቃል፡፡ ስለዚህ እግዘአብሄር አብ በአእምሮዋችን ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ነገር ያውቃል፡፡ በመሆኑም ‹‹እርሱ መንፈስ ቅዱስ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳል፡፡››             
 
ይህ ማለት አባታችን በመንፈስ ቅዱስ አሳብ ውስጥ ምን እንዳለ ያውቃል፤ መንፈስ ቅዱስም እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ይጸልያል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ መኖር ይገባቸዋል፡፡ የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ያገኙ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእምነት ሕይወታቸውን ጥቅሞች የሚያገኙት ለዚህ ነው፡፡ የጻድቃን አእምሮ የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ ንቃት ነው፡፡ 
 
በልባቸው ውስጥ መንፈስ ቅዱስ የሌለባቸው ሰዎች በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ ሲገኙ በቤተክርስቲያን ውስጥ ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማያምኑ ሰዎች በውስጣቸው መንፈስ ቅዱስ የለም፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ካላቸው ከእውነተኛ ምዕመናን ጋር መግባባት አይችሉም፡፡ እነርሱ በቤተክርስቲያን ውስጥ ብዙ ችግሮችን ይፈጥራሉ፡፡ በንጽጽር መንፈስ ቅዱስ ያለባቸው ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ በተሞላ የእግዚአብሄር ባርያ የሚቀርበውን ስብከት ሲያዳምጡ ልባቸው በሰላም ይሞላል፡፡ ምክንያቱም በባርያው አማካይነት ሊናገራቸው የሚሞክረውን መረዳት ይችላሉና፡፡ 
 
የሐጢያቶቹን ይቅርታ ያገኘ ማንኛውም ሰው በውስጡ መንፈስ ቅዱስ እንደሚኖርበት የተረጋገጠ ነው፡፡ እኛ በውስጣችን መንፈስ ቅዱስ አለን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ምሪትም እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ እንኖራለን፡፡ 
 
መንፈስ ቅዱስ በእነዚህ መንገዶች ይመራናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በቤተክርስቲያን አማካይነት ከምዕመናኖች ጋር በሚደረግ ሕብረት፤ በሌላ ጊዜ በእግዚአብሄር ቃሎች አማካይነት ይመራናል፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ እንድናገኝ ያደርገናል፡፡ የእርሱን የጽድቅ መንገድ እንድንከተልም ይፈቅድልናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ወደ መንግሥቱ እስክንገባ ድረስ ከእግዚአብሄር ወገን ሆነን እንድንኖር አዳዲስ ጉልበቶችን ይሰጠናል፡፡ 
 
ስለዚህ እናንተና እኔ መንፈስ ቅዱስ በእምነት ሕይወታችን ውስጥ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብ አለብን፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ስናምን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተነገረው መንፈስ ቅዱስን በስጦታ መልክ እንቀበላለን፡፡ ‹‹ንስሐ ግቡ፤ ሐጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፡፡ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 2፡38)     
 
እግዚአብሄር እንደ ፈቃዱ እንድንኖር ይመራን ዘንድ መንፈስ ቅዱስን እንደ ስጦታ ሰጥቶናል፡፡ የአባታችን የእግዚአብሄር ፈቃድ ይህ ነው፡፡ ወደ መንግሥቱ እንድንገባ እንደ ፈቃዱ መኖር እንዳለብን ነግሮናል፡፡ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ እንኖር ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ሊኖረን ይገባል፡፡ መንፈስ ቅዱስን የሚቀበሉትም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ለመቀበል፣ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ለመኖርና ወደ መንግሥቱ ለመግባት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን አለብን፡፡ 
 
መንፈስ ቅዱስንና ደህንነትን በተናጥል አንቀበልም፡፡ ዛሬ ሰዎች እነዚህ ሁለት በረከቶች ተለያዩ ነገሮች እንደሆኑ ያስባሉ፡፡ በተራራ ላይ በሚገኙ ዋሻዎች ሄደው በልሳን ቢጸልዩና በትጋት ቢማልዱ መንፈስ ቅዱስ እንደሚወርድባቸው ያስባሉ፡፡ ያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ ወርዶ በቀጥታ መልዕክቶቹን እንደሚሰጣቸውና ከእነርሱ ጋር እንደሚነጋገር ያስባሉ፡፡ ይህ ግን እውነት አይደለም፡፡ 
 
መንፈስ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱስ ሊነጣጠሉ አይችሉም፡፡ መንፈስ ቅዱስና አማኙም እንዲሁ ሊነጣጠሉ አይችሉም፡፡ በምዕመናን በቤተክርሰቲያንና በስላሴ አምላክ --አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ -- እና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያሉት ቁርኝቶች እርስ በርሳቸው የተያያዙ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ 
   
በዚህ በመጨረሻው ዘመን የምንኖር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ መኖር አለብን፡፡ በእግዚአብሄር ፈቃድና በመንፈስ ቅዱስ እንኖራለን፡፡ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሄርን ፈቃድ በሙሉ ያውቃል፡፡ አባታችን በመንፈስ ቅዱስ አሳብ ውስጥ  ያለውን እያንዳንዱን ነገር ያውቃል፡፡ መንፈስ ቅዱስ አስተሳሰቦቻችንን በመምራት ከእግዚአብሄር ጋር ይነጋገራል፡፡ በዚህ መንገድ መንፈስ ቅዱስ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ይጸልያል፡፡ አባታችንም እንደ ፈቃዱ እንድንኖር በማድረግ እነዚያን ጸሎቶች ይመልሳል፡፡ 
 
ጳውሎስ በሮሜ ምዕራፍ 8 ከቁጥር 16 እስከ 27 ድረስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥራዎች የተናገረው ለዚህ ነው፡፡ 
 
እኛ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሄርን መንግሥት መጠባበቅ እንችላለን፡፡ የአሁኑን ዘመን መከራችንን ታግሰን በልባችን ውስጥ በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ሐይል የእርሱን መንግሥት እየተጠባበቅን እንደ ጌታ ፈቃድ እንኖራለን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እንታገሳለን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ጌታችንን ለማገልገል አቅም ይኖረናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ተሰጥተውናል፡፡ እኛ በመንፈስ ቅዱስ የምንመላለስ፣ ሁልጊዜም የእግዚአብሄርን ቃል የምናጠና፣ ልባችንን ከቃሉ ጋር ያቆራኘንና ቃሉን የምናደምጥና የምንከተል ሰዎች ነን፡፡ አባታችንና መንፈስ ቅዱስ በእኛ ሊደሰቱበት የሚችሉበትን ሕይወት መኖር አለብን፡፡ ሥጋችን ብቻ የሚደሰትበትን ሥጋዊ ሕይወት መኖር የለብንም፡፡ ጳውሎስ በዚህ ምንባብ ውስጥ የሚለው ይህንን ነው፡፡ 
   
እግዚአብሄር ሁልጊዜም ከሕይወታችን ጋር ነው፡፡ ልባችንን ይጠብቃል፡፡ ሊያግዘንም ይሻል፡፡ ጌታ እኛን መባረኩን ይቀጥላል፡፡ ጌታችን ዳግም ሲመጣ ሁሉም ነገር ወደ ክብር ይለወጣል፡፡ እኛ አሁን የእግዚአብሄር ጽድቅ ያለን ሰዎች የእግዚአብሄርን መንግሥትና ክብር ሁሉ እንወርሳለን፡፡ የእግዚአብሄርን መንግሥት መውረስ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በጥንቃቄ ማድመጥና ማመን አለበት፡፡
  
ሃሌሉያ! የእግዚአብሄር ጸጋ ከእናንተ ጋር እንዲሆን እጸልያለሁ፡፡ ተባረኩ፡፡