Search

শিক্ষা

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[9-1] ከጥልቁ ጉድጓድ የወጣው መቅሰፍት ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 9፡1-21 ››

ከጥልቁ ጉድጓድ የወጣው መቅሰፍት
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 9፡1-21 ››
‹‹አምስተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ ከሰማይም ወደ ምድር ወድቆ የነበረ ኮከብ አየሁ፡፡ የጥልቁም ጉድጓድ መክፈቻ ተሰጠው፡፡ የጥልቁንም ጉድጓድ ከፈተው፡፡ ጢስም ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጉድጓዱ ወጣ፡፡ ጸሐይና አየርም በጉድጓዱ ጢስ ጨለሙ፡፡ ከጢሱም አንበጣዎች ወደ ምድር ወጡ፡፡ የምድርም ጊንጦች ሥልጣን እንዳላቸው ሥልጣን ተሰጣቸው፡፡ የእግዚአብሄርም ማህተም በግምባራቸው ከሌለባቸው ሰዎች በቀር በምድር ያለውን ሳር ቢሆን ወይም ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ እንዳይጎዱ ተባለላቸው፡፡ አምስትም ወር ሊያሰቃዩአቸው ተሰጣቸው እንጂ ሊገድሉአቸው አይደለም፡፡ እነርሱም የሚያሰቃዩት ስቃይ ጊንጥ ሰውን ነድፎ እንደሚያሰቃይ ነው፡፡ በዚያም ወራት ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ አያገኙትምም፡፡ ሊሞቱም ይመኛሉ ሞትም ከእነርሱ ይሸሻል፡፡ የአንበጣዎቹም መልክ ለጦርነት እንደተዘጋጁ ፈረሶች ነው፡፡ በራሳቸውም ላይ ወርቅ እንደሚመስሉ አክሊሎች ነበሩአቸው፡፡ ፊታቸውም እንደ ሰው ፊት ነበረ፡፡ የሴቶችን ጠጉር የሚመስል ጠጉር ነበራቸው፤ ጥርሳቸውም እንደ አንበሳ ጥርስ ነበረ፡፡ የብረት ጥሩር የሚመስልም ጥሩር ነበራቸው፤ የክንፋቸውም ድምጽ ወደ ጦርነት እንደሚጋልቡ እንደ ብዙ ፈረሶች ሰረገላዎች ድምጽ ነበረ፡፡ እንደ ጊንጥም ጅራት ያለ ጅራት አላቸው፡፡ በጅራታቸውም መውጊያ አለ፡፡ ሰዎችንም አምስት ወር እንዲጎዱ ሥልጣን አላቸው፡፡ በእነርሱም ላይ ንጉሥ አላቸው፤ እርሱም የጥልቅ መልአክ ነው፤ ስሙም በዕብራይስጥ አብዶን በግሪክም አጶሊዮን ይባላል፡፡ ፊተኛውም ወዮ አልፎአል፤ እነሆም ከዚህ በኋላ ገና ሁለት ወዮ ይመጣል፡፡ 
ስድስተኛውም መልአክ ነፋ፤ በእግዚአብሄርም ፊት ካለው በወርቅ ከተሰራ መሠዊያ ቀንዶች አንድ ድምጽ ሰማሁ፡፡ መለከትም ያለውን ስድስተኛውን መልአክ፡- በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው አለው፡፡ የሰዎችንም ሲሶ እንዲገድሉ ለሰዓቱና ለቀኑ፣ ለወሩም፣ ለዓመቱም ተዘጋጅተው የነበሩ አራቱ መላእክት ተፈቱ፡፡ የፈረሰኞችም ጭፍራ ቁጥር እልፍ ጊዜ እልፍ እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ፤ ቁጥራቸውን ሰማሁ፡፡ ፈረሶቹንና በእነርሱም ላይ የተቀመጡትን እንዲሁ በራዕይ አየሁ፡፡ እሳትና ያክንት ዲንም የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፡፡ የፈረሶቹም ራስ እንደ አንበሳ ራስ ነበረ፤ ከአፋቸውም እሳትና ጢስ፣ ዲንም ወጣ፡፡ ከአፋቸውም በወጡት በእሳቱና በጢሱ፣ በዲኑም በእነዚህ ሦስት መቅሰፍቶች የሰዎቹ ሲሶ ተገደለ፡፡ የፈረሶቹ ሥልጣን በአፋቸውና በጅራታቸው ነውና፤ ጅራታቸው እባብን ይመስላልና፡፡ ራስም አላቸው፤ በእርሱም ይጎዳሉ፡፡ በእነዚህም መቅሰፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ለአጋንንትና ያዩ ወይም ይሰሙ ወይም ይሄዱ ዘንድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር፣ ከናስም፣ ከድንጋይም፣ ከእንጨትም ለተሰሩ ለጣዖቶች እንዳይሰግዱ ስለ እጃቸው ሥራ ንስሐ አልገቡም፡፡ ስለ መግደላቸውም ቢሆን ወይም ስለ አስማታቸው ወይም ስለ ዝሙታቸው ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሐ አልገቡም፡፡
 
 

ትንታኔ፡፡

 
ቁጥር 1፡- አምስተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ ከሰማይም ወደ ምድር ወድቆ የነበረ ኮከብ አየሁ፡፡ የጥልቁም ጉድጓድ መክፈቻ ተሰጠው፡፡
እግዚአብሄር የጥልቁን ጉድጓድ መክፈቻ ቁልፍ ለመልአኩ ሰጠው ማለት በሰው ዘር ላይ እንደ ሲዖል የከፋ መቅሰፍት ለማውረድ ወስኖዋል ማለት ነው፡፡
የጥልቁ ጉድጓድ መጨረሻ የሌለው ጥልቅ ስፍራ ማለትም ነው፡፡ እግዚአብሄር በምድር ላይ በሚኖረው በጸረ ክርስቶስ፣ በተከታዮቹና በጻድቃን ላይ በተነሱት ሰዎች ላይ መከራን ለማምጣት የጥልቁን ጉድጓድ ይከፍተዋል፡፡ የዚህ የጥልቁ ጉድጓድ መክፈቻ ቁልፍም ለአምስተኛው መልአክ ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ልክ እንደ ራሱ እንደ ሲዖል የሚያሰቅቅ አስፈሪ መቅሰፍት ነው፡፡
 
ቁጥር 2፡- የጥልቁንም ጉድጓድ ከፈተው፡፡ ጢስም ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጉድጓዱ ወጣ፡፡ ጸሐይና አየርም በጉድጓዱ ጢስ ጨለሙ፡፡
እግዚአብሄር የጥልቁ ጉድጓድ እንዲከፈት ሲፈቅድ መላው ዓለም የእሳተ ገሞራ ዓመዶችን በሚመስሉ አቧራዎች ይሸፈንና የጨለማውን መቅሰፍት ያመጣሉ፡፡ ይህ የጨለማው መቅሰፍት ጨለማን ለሚወዱ ሰዎች የተዘጋጀ ነው፡፡ እግዚአብሄር የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለሰው ሁሉ የሚሰጥ በእኛ ላይ የሚያበራ የብርሃን አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር በዚህ እውነት ለሚያምኑ ሰዎች የደህንነትን ጸጋ በመስጠት ብሩህ በሆነው ብርሃኑ ውስጥ እንዲኖሩ ፈቅዶላቸዋል፡፡ እውነቱን ያልተቀበሉ ግን የእግዚአብሄርን የጽድቅ በቀል ይጋፈጣሉ፡፡ በእነርሱ ላይ የጨለማውን መቅሰፍትና የጽቅድ ፍርዱን ያወርድባቸዋልና፡፡
ሰዎች በመሰረቱ ሐጢያተኞች ሆነው የተወለዱ ናቸው፡፡ በሕይወታቸውም ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ይመርጣሉ፡፡ ስለዚህ ጌታ የሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመናቃቸውና ባለማመናቸው ከእግዚአብሄር ዘንድ የጨለማን መቅሰፍት ሊቀበሉ ይገባቸዋል፡፡ 
 
ቁጥር 3፡- ከጢሱም አንበጣዎች ወደ ምድር ወጡ፡፡ የምድርም ጊንጦች ሥልጣን እንዳላቸው ሥልጣን ተሰጣቸው፡፡
እግዚአብሄር በዚህች ምድር ላይ አንበጦችን በመላክ በደመ ነፍሳዊ አስተሳሰቦቻቸው የእግዚአብሄርን እውነት የተቃወሙትን ሰዎች ሐጢያቶች ይቀጣል፡፡ ይህ የአንበጦች መቅሰፍት ልክ እንደ ጊንጥ መውጊያ አሰቃቂ ስቃይን ማምጣት የሚችል ነው፡፡ ስለዚህ የዚህ ዓለም ሐጢያተኞች በሙሉ በእግዚአብሄር እውነተኛ ፍቅር ማመን አለባቸው፡፡ ይህንን የማያምኑ ሰዎች የእግዚአብሄርን ፍቅር የናቁባቸውና እርሱን የተቃወሙባቸው ሐጢያቶቻቸው ምን ያህል ታላቅና አሰቃቂ እንደሆኑ የማየት ተሞክሮ ሊኖራቸው ይገባል፡፡
እግዚአብሄር አንበጦችን ወደዚህ ምድር በመላክ ሰዎች በደመ ነፍሳዊ አስተሳሰቦቻቸው የእውነትን አምላክ የተቃወሙባቸውን የሐጢያቶቻቸውን ደመወዝ ከፈላቸው፡፡ ይህ የሐጢያት ዋጋ በአንበጦቹ መቅሰፍት መሰቃየታቸው ነው፡፡
 
ቁጥር 4፡- የእግዚአብሄርም ማህተም በግምባራቸው ከሌለባቸው ሰዎች በቀር በምድር ያለውን ሳር ቢሆን ወይም ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ እንዳይጎዱ ተባለላቸው፡፡
እግዚአብሄር አስፈሪውን የአንበጦች መቅሰፍት ሲያመጣ በእርሱ የታተሙትን ሊምር አይረሳም፡፡ እርሱ አንበጦቹ ተፈጥሮን እንዳይጎዱም አዞዋቸዋል፡፡
 
ቁጥር 5፡- አምስትም ወር ሊያሰቃዩአቸው ተሰጣቸው እንጂ ሊገድሉአቸው አይደለም፡፡ እነርሱም የሚያሰቃዩት ስቃይ ጊንጥ ሰውን ነድፎ እንደሚያሰቃይ ነው፡፡
በመሃልየ ዘ ሰሎሞን 8፡6 ላይ እግዚአብሄር እንዲህ በማለት ስለ ፍቅሩና ቁጣው ይናገራል፡- ‹‹ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናትና፡፡ ቅንዓትም እንደ ሲዖል የጨከነች ናትና፡፡ ፍንጣሪዋ እንደ እሳት ፍንጣሪ እንደ እግዚአብሄር ነበልባል ነው፡፡›› ልክ እንደዚሁ ይህ መቅሰፍት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት የተገለጠውን የእግዚአብሄር ፍቅር የሚንቁ ሰዎች የሚደርስባቸው ቅጣት ምን ያህል አስከፊ እንደሚሆን ይነግረናል፡፡ ይህ መቅሰፍት ሰዎችን ለአምስት ወራት ያሰቃያል፡፡
 
ቁጥር 6፡- በዚያም ወራት ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ አያገኙትምም፡፡ ሊሞቱም ይመኛሉ ሞትም ከእነርሱ ይሸሻል፡፡
የአንበጦቹ መቅሰፍት እንዲህ ያሉ ታላላቅ መከራዎችን ስለሚያመጣ ሰዎች እየተሰቃዩ ከመኖር ይልቅ ሞትን ይመርጣሉ፡፡ ምንም ያህል ሞትን ቢፈልጉትም አያገኙትም፡፡ ይህ መቅሰፍት የመጣው ሰዎች እግዚአብሄርን ስለናቁ ነው፡፡ የሥጋ ሕይወት ፍጻሜ የሁሉ ነገር ፍጻሜ እንደሆነ በማሰብ በሕይወትና በሞት ላይ የሚሰለጥነውን እግዚአብሄርን ናቁት፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄርን ናቁት፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር በዚህ የአንበጦች መቅሰፍት ሞት እንኳን ያለ እግዚአብሄር ፈቃድ ሊገኝ እንደማይችል ያሳየናል፡፡
 
ቁጥር 7-12፡- የአንበጣዎቹም መልክ ለጦርነት እንደተዘጋጁ ፈረሶች ነው፡፡ በራሳቸውም ላይ ወርቅ እንደሚመስሉ አክሊሎች ነበሩአቸው፡፡ ፊታቸውም እንደ ሰው ፊት ነበረ፡፡ የሴቶችን ጠጉር የሚመስል ጠጉር ነበራቸው፤ ጥርሳቸውም እንደ አንበሳ ጥርስ ነበረ፡፡ የብረት ጥሩር የሚመስልም ጥሩር ነበራቸው፤ የክንፋቸውም ድምጽ ወደ ጦርነት እንደሚጋልቡ እንደ ብዙ ፈረሶች ሰረገላዎች ድምጽ ነበረ፡፡ እንደ ጊንጥም ጅራት ያለ ጅራት አላቸው፡፡ በጅራታቸውም መውጊያ አለ፡፡ ሰዎችንም አምስት ወር እንዲጎዱ ሥልጣን አላቸው፡፡ በእነርሱም ላይ ንጉሥ አላቸው፤ እርሱም የጥልቅ መልአክ ነው፤ ስሙም በዕብራይስጥ አብዶን በግሪክም አጶሊዮን ይባላል፡፡ ፊተኛውም ወዮ አልፎአል፤ እነሆም ከዚህ በኋላ ገና ሁለት ወዮ ይመጣል፡፡
ከጥልቁ ጉድጓድ የወጡት አንበጦች ጅራቶቻቸው ሰዎችን ለአምስት ወራት የማሰቃየት ሐይል አላቸው፡፡ በመልካቸው ሴቶችን ቢመስሉም እነዚህ አንበጦች እጅግ አስፈሪና ጨካኝ ፍጡራን ናቸው፡፡ ይህም ሰዎች ከእግዚአብሄር ይልቅ ሴቶችን በመከተላቸው ምን ያህል ትልቅ ሐጢያት እንደሰሩ ያሳያል፡፡ ሰይጣን ልቅ ወደሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ውስጥ ሊጥለንና እንዲህ ያሉ የሥጋ ፍትወት ሐጢያቶችን ወደ ሕይወታችን ውስጥ አጥልቆ ሊያስገባ እንደሚሻ መርሳት የለብንም፡፡
 
ቁጥር 13-15፡- ስድስተኛውም መልአክ ነፋ፤ በእግዚአብሄርም ፊት ካለው በወርቅ ከተሰራ መሠዊያ ቀንዶች አንድ ድምጽ ሰማሁ፡፡ መለከትም ያለውን ስድስተኛውን መልአክ፡- በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው አለው፡፡ የሰዎችንም ሲሶ እንዲገድሉ ለሰዓቱና ለቀኑ፣ ለወሩም፣ ለዓመቱም ተዘጋጅተው የነበሩ አራቱ መላእክት ተፈቱ፡፡
እግዚአብሄር ለሰው ዘር ሲል ለረጅም ጊዜ በትዕግስት የጠበቀው በሐጢያት ላይ የሚያወርደው ፍርድ በመጨረሻ ጀመረ፡፡ በኤፍራጥስ ወንዝ የሰውን ዘር ሲሶ የሚገድለው የጦርነት መቅሰፍት ጊዜ አሁን ነው፡፡
 
ቁጥር 16፡- የፈረሰኞችም ጭፍራ ቁጥር እልፍ ጊዜ እልፍ እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ፤ ቁጥራቸውን ሰማሁ፡፡
እዚህ ላይ የፈረሰኞቹ ጭፍሮች ቁጥር ተገልጦዋል፡፡ ይህ ዘመናዊውን ኤሌክትሮኒክሳዊ ጦርነት ያመለክታል፡፡ በዚህ ጦርነት ውስጥ የሰው ዘር ሲሶ ቢገደሉም የተረፈው ሕዝብ አሁንም ጣዖታትን ማምለካቸውን፣ እግዚአብሄርን መቃወማቸውንና ለሐጢያቶቻቸው ንስሐ ለመግባት አሻፈረኝ ማለታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ይህም በመጨረሻው ዘመን የእያንዳንዱ ሰው ልብ በሐጢያቶቹ ምን ያህል እንደሚደነድን ያሳየናል፡፡
 
ቁጥር 17፡- ፈረሶቹንና በእነርሱም ላይ የተቀመጡትን እንዲሁ በራዕይ አየሁ፡፡ እሳትና ያክንት ዲንም የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፡፡ የፈረሶቹም ራስ እንደ አንበሳ ራስ ነበረ፤ ከአፋቸውም እሳትና ጢስ፣ ዲንም ወጣ፡፡
ሐዋርያው ዮሐንስ ያየው ነገር እንደ ታንኮች፣ ተዋጊ አውሮፕላኖችና ሌሎች ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ያሉ የ21ኛው ምዕተ ዓመት አስፈሪ አውዳሚ የጦር መሳሪያዎችን ነው፡፡
 
ቁጥር 18-19፡- ከአፋቸውም በወጡት በእሳቱና በጢሱ፣ በዲኑም በእነዚህ ሦስት መቅሰፍቶች የሰዎቹ ሲሶ ተገደለ፡፡ የፈረሶቹ ሥልጣን በአፋቸውና በጅራታቸው ነውና፤ ጅራታቸው እባብን ይመስላልና፡፡ ራስም አላቸው፤ በእርሱም ይጎዳሉ፡፡
በመጨረሻው ዘመን በዘመናዊ መሳርያ የሚደረግ ግዙፍ ጦርነት ይሆናል፡፡ የሰው ዘር ሲሶ ከእነዚህ የጦር መሳርያዎች በሚወጣው የእሳት፣ የጢስና የዲን መቅሰፍት ይሞታል፡፡
 
ቁጥር 20፡- በእነዚህም መቅሰፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ለአጋንንትና ያዩ ወይም ይሰሙ ወይም ይሄዱ ዘንድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር፣ ከናስም፣ ከድንጋይም፣ ከእንጨትም ለተሰሩ ለጣዖቶች እንዳይሰግዱ ስለ እጃቸው ሥራ ንስሐ አልገቡም፡፡ ስለ መግደላቸውም ቢሆን ወይም ስለ አስማታቸው ወይም ስለ ዝሙታቸው ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሐ አልገቡም፡፡
እነዚህ መቅሰፍቶች ቢወርዱም ከጦርነቱ የተረፉ ሰዎች ጣዖታትን አብልጠው በማምለክ በፊታቸው መስገዳቸውን ቀጥለዋል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ለጥፋት የተወሰኑ ናቸውና፡፡
 
ቁጥር 21፡- ስለ መግደላቸውም ቢሆን ወይም ስለ አስማታቸው ወይም ስለ ዝሙታቸው ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሐ አልገቡም፡፡
ይህም በዘመኑ መጨረሻ የሰው ዘር በእግዚአብሄር ፊት ፈጽሞ ከሐጢያቶቹ ንስሐ እንደማይገባ ያሳየናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር እነዚህን ሐጢያተኞች ይፈርድባቸዋል፡፡ ለጻድቃን ግን አዲስና የተባረከን ዓለም ይፈቅድላቸዋል፡፡