Search

សារវីដេអូពីសហការីរបស់យើង

በውኑ ከውኃውና ከመንፈስ ዳግም ተወልዳችኋልን? / Have You Truely been Born Again of Water and the Spirit?

  • Teferi Oshine
  • Ethiopia
  • 02/08/2022 53069

በውኑ ከውኃውና ከመንፈስ ዳግም ተወልዳችኋልን?
ጠቃሚና ልታጤኑት የሚገባው ማሳሰቢያ!
ምንአልባት ኣታምኑበትም ወይም ደግሞ ጠቃሚ ነገር አድርጋችሁ አትወሰዱትም ይሆናል ፤ ነገር ግን መልእክቱን እስከ መጨረሻው ካነበባችሁ፥ ለእውነታው ዋጋ ሰጥታችሁታል ማለት ነው፡፡
በዓለም ላሉ ተፈጥሮአዊ ችግሮች ሁሉ መንስኤው ኃጢአት እንደሆነ ታውቃላችሁ? ለሰው ልጅ ሁሉ ሕይወት ሁሉንም ዓይነት አለመርካት ያመጣው ኃጢአት ነው፡፡ ጥፋት ሁሉ፣ በሽታ፣ ማህበራዊ ልዩነት፣ ጥላቻ፣ ስስት፣ ክፋትን፣ ሞትን ጨምሮ እነዚህ ሁሉ በኃጢአት ምክንያት  የመጡ ነገሮች ናቸው፡፡
ኃጢአት ምንድነው?
ኃጢአት የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ አለመታዘዝ ወይም የእግዚአብሔርን ሕግ መጣስ ነው፡፡ (ዘፍ 2፥17፣ 3፥17፣ ሮሜ 5፥19)
ሰው በጠቅላላው የአዳም ዝርያ ስለሆነ በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይቶ ነው ያለው። ኃጢአት ሰውንና እግዚአብሔርን የለየ ታላቅ ግድግዳ ሆኗል። (ኢሳ 59፥2) የመጀመሪያው ሰው አዳም የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ጥሶ ኃጢአተኛ ስለሆነ እርሱ የወለዳቸው የእርሱ ዘሮች ሁሉም ኃጢአተኛ ሆነዋል። (ሮሜ 5፥12-19) "በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰውን ከአፈር ፈጥሯል (ዘፍ 1፥26፤ 2፥7)። ሰው ከአፈር ተፈጠረ ማለት ደካማ ሆኖ ተፈጠረ ማለት ሲሆን በድካሙም በአታላዩ ዲያብሎስ ሲታለል (ዘፍ 3፥1)፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ጣሰ  (ዘፍ 2፥17፤ 3፥17፤ ሮሜ 5:19)። ያን ጊዜ ኃጢአት ወደ ልቡ ገባ (ሮሜ 5፥12)። መንፈሱ ሞተ (ማቴ 8፥22)። ዘሩ በኃጢአት በከለ (ማር 7፥20-23)። የሚወልዳቸው ልጆች ሁሉ ኃጢአተኞች ሆነው ይወለዳሉ (መዝ 51፥5)። ዳግመኛ ውልደት ያስፈለገው ለዚህ ነው (ዮሐ 3፥3-5)።" ሰይጣን ሰውን በሐሰት ቃሉ አታሎ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ባስጣሰ ጊዜ ኃጢአት ወደ ሰው ልብ ውስጥ ገባ። (ሮሜ 5፥12)
ስለዚህ የሰው ዘር ሁሉ የኃጢአት ተሸካሚ ሆኗል። የሰው ዘር ገና ሲፀነስ በዓመፃ ይፀነሳል በኃጢአት ይወለዳል።  (መዝ 51፥5) ስለዚህ ሰዎች ሁሉም  እኩል ኃጢአተኞች ሆነው የተወለዱ ናቸው። አሁን ሰው ገና ዛሬ ኃጢአት በመስራቱ አይደለም ኃጢአተኛ የሆነው፤ ሰው ኃጢአተኛ የሆነው ኃጢአተኛ ሆኖ በመወለዱ ነው። ሰው ኃጢአትንም የሚያደርገው ኃጢአተኛ ሆኖ ስለተወለደ ነው።
ሰው ዛሬ በሚታይ መልኩ ገድሎ፣ አመንዝሮ፣ ሰርቆ፣ . . . ባይገኝም እንኳን እነዚህን ኃጢአቶችን በልቡ ይዞ ተቀምጧል፤ ሁኔታን እየጠበቀ በራሱ ጊዜ ከልቡ ይወጣል ያረክሰውማል። ኢየሱስም በሰው ልብ ውስጥ ያለውን ኃጢአት እንዲህ ብሎ ገለጠ ፦ “ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው። ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ መጐምጀት፥ ክፋት፥ ተንኰል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስድብ፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸውና፤ ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውን ያረክሰዋል።" አለ። (ማር 7፥20-23) ስለዚህ በሰው ልብ ውስጥ እነዚህ ኃጢአቶች በመቀመጣቸው ሰውና እግዚአብሔር ተለያይተው አሉ።
የሰው ልብ በክፋት የተሞላ ነው። (ኤር 17፥9 ፤ ማር 7፥21-22)
ሰው ዝሙትን የሚፈጽመው፣ የሚሰርቀው፣ የሚገድለው፣ የሚያመነዝረው፣ የሚሳደበውና . . . ሁሉንም ኃጢአቶችን የሚሰራው እነዚህን በማርቆስ ወንጌል 7፥21 ላይ የተዘረዘሩ ኃጢአቶችን በዘር ወርሶ ስላለ ነው። ሰው ኃጢአትን የሚያደርገው ለዚህ ነው። ስለዚህ ሰው ካልሞተ በቀር ኃጢአትን ማድረግን አይተውም  ወይም አያቆምም፤ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ይቀጥላል። በሚሰራቸውም በእያንዳንዱ ቅንጣት ኃጢአቶቹም በገሃነም እሳት ሊኮነን ታጭቷል፤ ምክንያቱም የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና።
ታዲያ ስንቶቻችሁ ይሄን ታውቁታላችሁ?
ስንቶቻችሁ፦ እነዚህ በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 7 ከቁጥር 21 ላይ የተዘረዘሩ የኃጢአት ዘሮች በእናንተው ልብ ውስጥ እንዳሉና ከእናንተም እየወጡ እንደሚያረክሳችሁ ታውቃላችሁ? በመጀመሪያ ኃጢአት የመነጨው ከሰይጣን ነው። (ዮሐ 8:44፣ ኢሳ 14፥12-15 ፣ ሕዝ 28፥1-19፣ ራእ 12፥9) ሰውም በሰይጣን ተታሎ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ያልታዘዘና ያፈረሰ (ዘፍ 3:1፣ 2ኛቆሮ 11፥3)፤ በሰይጣን የሳተና ኃጢአትን ከሰይጣን የተቀበለ የክፉ አደራጊ ዘር ሆኗል፡፡ (ኢሳ 1፥4) በመጽሐፍ ቅዱስ ክፉ አድራጊ ሰይጣን ነው። ስለዚህ ሰው በተፈጥሮው ክፉ አድራጊ ዘር ወይም የቁጣ ልጅ ሆኗል። (ኤፌ 2፥3) ሰው በሰይጣን በተታለለ ጊዜ በልቡ ኃጢአትን ከሰይጣን ተቀብሏል። ሰው ልቡ በኃጢአት ስለጨለመ እግዚአብሔር በሰዎች ልብ ውስጥ ሊያድር አይችልም፡፡ (ዘፍ 1፥2፣ 1ኛዮሐ 1፥5) ምክንያቱም ኃጢአት ባለበት ስፍራ እግዚአብሔር በፍጹም ሕብረትን አያደርግምና። (1ኛዮሐ 1፥6) ስለዚህ እነዚህ በማርቆስ ወንጌል 7፥21-22 ድረስ የተዘረዘሩ ኃጢአቶች ከልባችሁ እስካልተወገዱ ድረስ እናንተ ለዘላለሙ ከእግዚአብሔር እንደተለያችሁ ትቀራላችሁ። እናንተ የእግዚአብሔር መልኩና አምሳያው ሆናቸሁ ነገር ግን በኃጢአታችሁ ምክንያት አሁን ከእግዚአብሔር ተለይታችሁ አላችሁ፡፡በኃጢአታችሁም ምክንያት እውነተኛ ደስታ ከእናንተ ርቋል፤ የእግዚአብሔርም መንግስት ከእናንተ ርቋል፡፡ ነገር ግን እኛ የውኃውና የመንፈሱ ወንጌል አማኞች እኛንና እግዚአብሔርን የለየው የኃጢአት ግድግዳ በኢየሱስ ውኃና ደም ስለፈረሰና ስለተወገደልን ኃጢአት የለብንም። (ኤፌ 2፥14-15፣ 1ኛቆሮ 6፥11፣ ዕብ 10፥10-18) እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀናል፤እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ሕብረት እያደረገ ነው። (2ኛቆሮ 5፥18-19፤ 1ኛዮሐ 1፥3-7) እንግዲያስ እናንተ ኃጢአቶቻችሁን እንዴት እናስወግዳለን ብላችሁ ታምናላችሁ? ከላይ በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 7 ከቁጥር 21 እስከ 22 ላይ የተዘረዘሩትን ኃጢአቶችን ሁሉ ላለመስራትና ብሎም በሂደት ቀስ በቀስ ለማቆም በመታገል ነውን?
በዚህ ፈጽሞ አታስወግዱም፤ ያሰወገደም የለም፡፡
ወይም ኃጢአትን በሰራችሁ ጊዜ የንስሐ ጸሎትን በማቅረብ ነውን?
በዚህም ፈጽሞ አይወገድም።
የእግዚአብሔር ቃል በዚህ መንገድ የሰራነውም የምንሰራውም ኃጢአት ከልባችን እንደሚወገዱ አይነግረንም፡፡ምንአልባት እነዚህን በማድረግ ሰዎች በስሜቶቻቸው ከኃጢአት የነጹ መስሎ ቢሰማቸው እንጂ ሕሊናቸው አሁንም በኃጢአት ታስሮ አለ። ሁልጊዜ ለመጸለይ ዝቅ ባሉ ቁጥር ባለፈው የሰሩት ኃጢአት ወዲያውኑ ፊታቸው ላይ ድቅን ይላል። ምክንያቱም የሰዎች ኃጢአት በሕሊናቸውና በእግዚአብሔር ዘንድ ባለው በምግባር መጽሐፍ ላይ ተጽፎ ይኖራልና። (ኤር 17፥1፣ ራእ 20፥12) ስለዚህ የኃጢአት ደመወዝ ሞት ስለሆነ የሰዎች እጣፈንታቸው ወደ ገሃነም እሳት መጣል ብቻ ነው፡፡ (ሮሜ 6፥23) በሰዎች ሕሊና ወይም ልብ ውስጥና በምግባር መጽሐፍ ላይ የተጻፉ ኃጢአቶች የሚደመሰሱትና ሰውም በሕሊናው ንጹህ ሆኖ ከገሃነም እሳት ፍርድ የሚያመልጠው የውኃውንና የመንፈሱን ወንጌል ቃል ሲያምንና ሲያምን ብቻ ነው። እናንተ ምንም ያህል በሥራዎቻችሁ ጥሩ ለመሆን ብትሞክሩም፣ ብዙ በጎ አድራጎቶች ቢኖሯችሁና ራሳችሁንም በኃይማኖት ጫካ ስር ብትደብቁም ያ ፈጽሞ ኃጢአትን ከእናንተ አያርቅም ወይም አያስወግድም፡፡ ይህን ሁሉ በማድረግ ከኃጢአት ነጻ መሆን አትችሉም፡፡ በግልጽ ቋንቋ እድሜ ልካችሁን በሥጋችሁ ለመቀደስ የምታደርጉት ጥረት እናንተን ኃጢአት አልባ አያድርጋችሁም። በነዚህ ኃይማኖታዊ ልምምዶች ሁሉ እግዚአብሔርን ማወቅና የእርሱንም ሥራ  ማመስገን አትችሉም፡፡
በሚገርምና በሚደንቅ ሁኔታ ኃጢአቶቻችሁን ሁሉ የምታስወግዱበት መንገድ እነሆ፦
ዕድሜ ልካችሁን ከምትሰሩት ኃጢአት ሁሉ በአንድ መንገድ ብቻ ትነጻላችሁ። ይህም፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ለማዳን ወይም ለሰው ልጆች ደኅንነት በጥምቀቱ፣ በሞቱ እና በትንሳኤው በሰራው ስራ ላይ እምነታችንን ሲንጥልና እምነታችንን በራሱ በክርስቶስ ላይና በእርሱ የደኅንነት ሥራው ላይ ሲናኖር ብቻና ብቻ እንድናለን፡፡ (ኤፌ 1፥5፣ 2፥5:8:18) እግዚአብሔር ኃጢአትን የሚጠላና ኃጢአትን የሚኮንን ጻድቅ አምላክ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን። ስለዚህ እኛ ሰዎች ኃጢአተኞች በመሆናችን በኃጢአታችን ከመሞት ወይም ከመኮነን በቀር ከእግዚአብሔር ፊት የትም ማምለጥ አንችልም። ነገር ግን የምስራቹ እግዚአብሔር እኛን ከኃጢአቶቻችን ለማዳን መውደዱ ነው። (ዮሐ 3፥16፣ ማቴ 1፥21) ስለዚህ አሁን እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ከኃጢአት ነጻ ሊያደርገን የሚችለውን የእውነት እውቀት በእኛ እንዲኖር ነው፡፡ ምክንያቱም እውነትን ማወቅ አርነት ያወጣልና። (ዮሐ 8፥32) በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ከቁጥር 5 ላይ እንደተገለጸው፦ "ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።" ተብሎ ተጽፏል።ስለዚህ ሰው ከኃጢአቱ ለመንጻትና ከኃጢአቱ ለመዳን መፍትሄው በኃይማኖት ትምህርቶች መኖሩ ሳይሆን የውኃውንና የመንፈሱን ወንጌል ብቻ ማመኑ ነው፡፡ “በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞ ለገሪክ ሰው ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ሀይል ለማዳን ነውና፤ 'ጻድቅ በእምነት ይኖራል' ተብሎ እንደተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና” (ሮሜ 1፥16-17) እንደተባለው ማለት ነው።በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ከቁጥር 5 ላይና በ1ኛ ዮሐንስ መልዕክት ምዕራፍ 5 ከቁጥር 6 እስከ 8 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃ መጥቷል።
ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃ መጥቷል ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ፦ ለኃጢአት የሚሰዋ በግ ሆኖ ወደ ዓለም በመምጣት በመጥምቁ ዮሐንስ እጆች መጫን አማካኝነት በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ የዓለምን ኃጢአት ሁሉ ወደ ራሱ ወስዷል ማለት ነው፡፡ (ማቴ 3፥15 ፣ ዮሐ 1፥29) መጥምቁ ዮሐንስ የዓለም ሕዝብ ወኪል ነው። (ሚል 4፥5-6፣ ማቴ 11:11-14፣ ሉቃ1፥76-77) በብሉይ ኪዳን ጊዜ ሊቀካህኑ አሮን የእስራኤልን ሕዝብ ወክሎ ለኃጢአት መሰዋዕት በቀረበው ነውርና እንከን በሌለው እንስሳ ራስ ላይ እጆቹን በመጫን የሕዝቡን ኃጢአት በእንስሳው ላይ እንዳስተላለፈ ሁሉ (ዘሌ 16፥21) መጥምቁ ዮሐንስም (ሉቃ 1፥5 ፣ 1ኛዜና 24፥10) ራሱ የአሮን ዘር የምድር የመጨረሻው ሊቀካህን በመሆን የዓለምን ሕዝብ በመወከል በኢየሱስ ራስ ላይ እጆቹን በመጫን የዓለምን ኃጢአት ወደ ኢየሱስ አስተላለፈ። (ማቴ 3፥15፣ ዮሐ 1:29) ሊቀካህናቱ ሕዝቡን መወከል የቻሉት እያንዳንዱ ግለሰብ በግሉ ለኃጢአቱ መሰዋዕት አቅርቦ በመሰዋዕቱ ራስ ላይ እጆቹን በመጫን ኃጢአቱን በመሰዋዕቱ ላይ አሸክሞ ስለሚያርድ ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ካልተወከለ በቀር እያንዱንዱ የዓለም ሰው በኢየሱስ ራስ ላይ እጆቹን ጭኖ መሰዋዕት ማድረግ አዳጋች ወይም የማይቻል ነውና። እግዚአብሔር ሊቀካህናትን የለየውና የመረጠው ለዚህ ዓላማ ወይም ለዚህ ጉዳይ ነው። የእጆች መጫን ጥቅም አንድን ነገር ወደ አንድ ነገር ለማስተላለፍ ነው። ይህ የእግዚአብሔር አሰራር ነው። መጥምቁ ዮሐንስ በብሉይ ኪዳን የአሮን ክህነት ሥርዓት መሰረት በኢየሱስ ራስ ላይ ሁለቱን እጆቹን ሲጭን በዛች ቅፅበት የዓለም ሁሉ ማለትም የእያንዳንዱ ግለሰብ ኃጢአት ሁሉ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ተላልፏል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአት ሁሉ በጥምቀቱ ስለተቀበለ፤ የኃጢአት ደመወዝ ሞትን ለመቀበልና ለመፈጸም ወይም ለኃጢአት ለመሰዋት ወደ መስቀል ተጓዘ፡፡ ወደ መስቀል ተጉዞና መስቀል ላይ ተሰቅሎ ክቡር ደሙን በሙሉ ስለኃጢአት ዋጋ ጨርሶ በማፍሰስና ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶ በመሞት የዓለምን ህዝብ ኃጢአት በሙሉ አስወገደ። ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀና በሞተ ጊዜ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል እርቅ ተፈጸመ፤ በሰውና በእግዚአብሔር መሐል የነበረው የጥል ግድግዳ ተወገደ፤ እግዚአብሔርም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የደኅንነት ሥራ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት በሙሉ ይቅር አለ። (ቆላ 2፥13) ኢየሱስ ከመሞቱና ነፍሱን ከማውጣቱ በፊት በመስቀል ላይ በታላቅ ድምጽ “ተፈጸመ” በማለት ሞቷል፡፡ (ዮሐ 19:30) ኢየሱስ ሞቶም አልቀረም፤ እኛን ለማጽደቅ ወይም ለእኛ አዲስ ሕይወትን ይሰጥ ዘንድ ከሞትም ተነስቷል። ሃሌሉያ!
አሁን ጥያቄው ኢየሱስ ተፈጸመ ያለው ምንድነው? የሚለው ነው።
በኢየሱስ የጽድቅ ሥራ ተፈጽሞ የነበረው ምንድነው?
ኢየሱስ ተፈጸመ ያለው ወይም በኢየሱስ የጽድቅ ስራ ተፈጽሞ የነበረው ኃጢአት ሁሉና የኃጢአት ፍርድ ነው፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሔር ኃጢአትን ከዓለም ለማስወገድ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት አቅዶ የነበረው እቅዱ ተፈጸመ ማለት ነው። (ኤፌ 1፥4፣ ዕብ 10፥7) ኢየሱስ የኃጢአታችንን ደመወዝ አስወግዷል። ዕዳችንን ከፍሏል። እኛ በኃጢአቶቻችን ምክንያት መውሰድ የነበረብንን ኩኑኔና ሞት ወስዷል። በሌላ አነጋገር በእርሱ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ሞቱ ለኃጢአቶቻችን በሙሉ ይቅርታ አግኝተናል ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ከዛሬ 2000 ዓመት በፊት በማስወገድና አዲስ የሕይወት መንገድን በመክፈት አሁን በአባቱ ቀኝ ተቀምጧል። (ዕብ 10፥19-20) በዚህ እውነት ወይም በወንጌሉ ማለትም በውኃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑትን ለመቀበልና ወደ መንግስቱ ለማስገባት፤ ያላመኑት ደግሞ ወደ ገሃነም ለማስገባት ዳግመኛ እንደሚመጣም ተስፋ ሰጥቷል።
አሁን ጊዜው የእርሱ የጸጋ ጊዜ ነው። (ሮሜ 11፥6)
ማንም ሰው በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ሞቱ ቢያምን ኃጢአቱ ሁሉ ይቅር ይባልለታል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ተሰጥቶትና በመንፈስ ቅዱስም ታትሞ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል። (ሐዋ 2፥38፣ ኤፌ 1፥13፣ ዮሐ 1፥12) ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ሊባል የሚችለው በልቡ መንፈስ ቅዱስ ሲኖረው ብቻ ነው። በልቡ መንፈስ ቅዱስ ሊኖረው የሚችለው ከልቡ ኃጢአት ሲወገድና ሰውየው የኃጢአትን ስርየት ሲቀበል ብቻ ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንደተናገረው ሰው የኃጢአትን ስርየት መቀበል የሚችለው የውኃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሲያምንና ሲያምን ብቻ ነው።
በውኑ የውኃውንና የመንፈሱን ወንጌል አምናችኋልን?
የውኃውና የመንፈሱ ወንጌል ምንድነው?
ማናችንም ይህንን ጥያቄ መመለስና በዚህ በእውነተኛውም ወንጌል ማመን አለብን። በዚህ ወንጌል ሲናምን ለዕድሜ ዘመናችን ኃጢአት አንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስርየትን እናገኛለን። ምክንያቱም የዕድሜ ልካችን ኃጢአት አንድ ጊዜ በኢየሱስ ጥምቀትና ሞቱ ተወግዷል። ኢየሱስ አንድ ጊዜ ተጠምቋል፤ አንድ ጊዜ ሞቷል። ስለዚህ አሁን በርግጥም በተጨባጭ በዓለም ኃጢአት የለም። ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአት በሙሉ አስወግዷል። (ዮሐ 1:29፣ 1ኛዮሐ 2፥2) እዚህ ጋ ዓለም ማለት፦ ይህች ዓለም ከተፈጠረችበት እስከምትጠፋበት ድረስ ያለው ጊዜ ማለት ነው። ስለዚህ የዓለም ኃጢአት ሲባል ከዓለም ጅማሬ እስከ ዓለም ፈጻሜ ድረስ የሰው ዘር የሰሩት ኃጢአት ሁሉ ማለት ነው። ልብ በሉ! አሁን እናንተ ዕድሜ ልካችሁን በሰራችሁት ኃጢአት ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጨባጭ አድርጎ በጥምቀቱ ፣ በሞቱና በትንሳኤው በሰራው ሥራ ላይ ትክክለኛ እውቀትና እምነት ባለመያዛችሁ ብቻ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለኃጢአታችሁ ቅጣትን ታገኛላችሁ። አሁን ጊዜው ዓመተ ምህረት ስለሆነ አሁን ኃጢአት የሚሆንባችሁ የእግዚአብሔርን ጸጋ (ኤፌ 1፥7) አለማመናችሁ ማለትም የውኃውንና የመንፈሱን ወንጌል አለማመናችሁ ብቻ እንጂ ስርቆታችሁ ዝሙታችሁ ስድባችሁ . . . አይደለም። (ዮሐ 16፡9) እናንተ የውኃውንና የመንፈሱን ወንጌል ካላመናችሁ ለዘላለም ኃጢአተኛ ሆናችሁ በመቅረት ለኃጢአታችሁ ደመወዝ ይሆን ዘንድ ወደ ገሃነም እሳት ትጣላላችሁ። (ራእ 20፥15) እናንተ ምንም ያህል ኃይማኖታዊ ልማዶችን ማለትም አጋንንትን ማውጣት ፣ ድንቆችን ማድረግ ፣ ልሳንና ትንቢት መናገር . . . ወዘተ ቢኖሯችሁም የእግዚአብሔር ፍቃድ በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ውኃው(በጥምቀቱ)፣ ደሙ(በስቅለቱ)ና መንፈሱ(በአምላክነቱ) ላይ ትክክለኛ እውቀትና እምነት እስከሌላችሁ ድረስ በፍርድ ቀን አመፀኞች ተብላችሁ ወደ እሳት ባህር እንደምትጣሉ ከአሁኑ አረጋግጡና መንገዳችሁን ለማስተካከል ሞክሩ። (ማቴ 7፥21-23) አሁንም የእግዚአብሔር ምህረት ክፍት ስለሆነ (ዕብ 7፥25፥ 2ኛጴጥ 3፥9) ጊዜአችሁን ተጠቀሙ ማለትም ወደ ውኃውና ወደ መንፈሱ ወንጌል ተመለሱ። ማወቅ ያለብን ነገር ፦ ማንም ሰው ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና ሞቱ ከኃጢአቱ ሁሉ በጭራሽ መዳን የማይችል መሆኑ ነው፡፡ የኢየሱስን ጥምቀት ኢየሱስ ለደኅንነታችን ከፈጸመው ሥራው ነጥሎ በደሙ ላይ ብቻ ያለ እምነት ሐሰትና ጎዶሎ እምነት ነው። ሙሉውና ትክክለኛው እምነት ውኃ ደምንና መንፈስን ይመሰክራል እንጂ ደምን ብቻ አይመሰክርም። (1ኛዮሐ 5፥6-10) ስለዚህ አሁን ሁላችሁም ከኃጢአታችሁ ሁሉ ለመዳንና ወደ እግዚአብሔር መንግስት ለመግባት በውኃውና በመንፈሱ ወንጌል ብቻ በልባችሁ እመኑ። (ዮሐ 3፥5) ማናችሁም ሁኑ ማን፦ ከኃጢአት ሁሉ ልትነጹና በኃጢአት ምክንያት ከሚመጣው ሞት ሁሉ ለመዳን የሚያስችል ትክክለኛ እምነት ሊኖራችሁ ይገባል፤ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ዘንድ መልካምና ደስ የሚያሰኘው እናንተ ሲትድኑና እውነትን ወደማወቅ ሲትደርሱ ብቻ ነው። (1ኛጢሞ 2፥3-4) ስለዚህ ለመዳን ብቸኛውና እውነተኛው የእግዚአብሔር ወንጌል የውኃውና የመንፈሱ ወንጌል ብቻ ነው። ለእኛ የሚበጀን በዚህ በውቡ በውኃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመናችን ብቻ ነው፡፡ በውኃውና በመንፈሱ ወንጌል ብቻ ማመን ያድነናል።
እመኑ! ከኃጢአታችሁ ሁሉ ዳኑ!!! 
መልዕክቱን ስላነበባችሁ በእጅጉ እያመሰገንን ፤ በዓለም ያላችሁ ሀብት፣ ክብር፣ ዝና፣ ውበት፣ እውቅና፣ ስልጣን እነዚህ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ከንቱዎች ናቸውና የእግዚአብሔርን ፍቃድ እንዲትሰሙ ፣ ልባችሁን በእግዚአብሔር ቃል ላይ እንዲታደርጉ ወደ እርሱ እንድትመለሱ እናሳስባችኋለን!!!!!!!!! "እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን።" (ራእ 1:7) በተላለፈው መልዕክት ላይ ሊነሱባችሁ የሚችሉ ጥያቄዎችና ስለ ውኃውና ስለ መንፈሱ ወንጌል የበለጠ ለማወቅ ከፈለጋችሁ፦ ለማንም በነጻ የሚሰጡ ለመንፈሳዊ እድገቶቻችን በተለያየ የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረት በማድረግ የተጻፉ ተከታታይ የክርስቲያን መጽሐፍቶችን ዲስክሪፕሽን ቦክስ ውስጥ ባሉ አድራሻዎቻችን በመጠቀም ማግኘት ትችላላችሁ!!!