Search

សេចក្តីអធិប្បាយ

ርዕስ 5፡ ተገቢው የሐጢያት ኑዛዜ

[5-1] እውነተኛና ትክክለኛ ኑዛዜ እንዴት እንደሚደረግ፡፡ ‹‹ 1ኛ ዮሐንስ 1፡9 ››

እውነተኛና ትክክለኛ ኑዛዜ እንዴት እንደሚደረግ፡፡
‹‹ 1ኛ ዮሐንስ 1፡9 ››
‹‹በሐጢአታችን ብንናዘዝ ሐጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመጻም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡››
 


የደሙ ወንጌል ግማሽ ወንጌል ነው፡፡

 
በደሙ ወንጌል ብቻ በማመን ወደ እግዚአብሄር መንግሥት መግባት እንችላለን? 
በፍጹም፡፡ ሙሉ በሆነው ወንጌል (በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል) ማመን ይኖርብናል፡፡
 
1ኛ ዮሐንስ 1፡9 የሚመለከተው ጻድቃንን ብቻ ነው፡፡ ገና ያልዳነ ሐጢያተኛ በዚህ ምንባብ ቃሎች መሰረት የቀን ተቀን ሐጢያቶቹን ለማስተሰረይ ከሞከረና የስህተት አድራጎቱን ከተናዘዘ ሐጢያቶቹ አይነጹም፡፡ እዚህ ላይ እያልሁ  ያለሁትን ማየት ትችላላችሁን? ይህ ምንባብ ዳግም ያልተወለዱ ሐጢያተኞችን አይመለከቱም፡፡
በዚህ ዓለም ላይ ገና ዳግም ያልተወለዱ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ይህንን ምንባብ ከ1ኛ ዮሐንስ ምዕራፍ 1 ውሰደው ይቅርታን ለማግኘት ተስፋ በማድረግ ይጸልያሉ፡፡
ነገር ግን ዳግም ያልተወለደ ሰው የኑዛዜ ጸሎቶችን በማድረግ ሙሉ በሙሉ ከሐጢያቶቹ ሊድን ይችላልን? ይህ አንዳች ርቀን ከመሄዳችን በዚህ ልናጤነውና ግልጽ ልናደርገው የሚገባን ነጥብ ነው፡፡
1ኛ ዮሐንስን ከማንበባችሁ በፊት ሐዋርያው ዮሐንስ ጻድቅ ሰው ይሁን ወይም ሐጢያተኛ መወሰን አለባችሁ፡፡ እስቲ ቀጣዩን ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በትክክለኛው የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ዳግም የተወለደ ጻድቅ ነበር ወይስ ሐጢያተኛ ነበር?
ሐዋርያው ዮሐንስ ሐጢያተኛ ነው ካላችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት እምነታችሁ ትክክል አይደለም፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በኢየሱስ ሲያምን ዳግም የተወለደ ጻድቅ ነው ካላችሁ ደግሞ ይህ እምነቱ ከእናንተ እምነት የሚለይ ስለመሆኑ ግልጽ ይሆንላችኋል፡፡ እናንተም ሐዋርያው ዮሐንስ የነበረውን አይነት እምነት ሊኖራችሁ ይገባል፡፡
ሌላም ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ እነዚያን መልዕክቶች የጻፈው ለሐጢያተኞች ነው ወይስ ለጻድቃን? ሐዋርያው ዮሐንስ መልዕክቶቹን ሲጽፍ የነበረው ለጻድቃን ነበር፡፡
ስለዚህ ዳግም ያልተወለዱ ሐጢያተኞች ሐዋርያው ዮሐንስ በምዕራፍ 1፡8-9 ላይ የጻፋቸውን ቃሎች በመውሰድ ቢጸልዩና በሕይወታቸውም ቢተገብሩዋቸው ይህ ስህተት ይሆናል፡፡ እናንተ ጻድቅ ለመሆን የምትፈልጉ ከሆነ ሐጢያቶቻችሁን በእግዚአብሄር ፊት ተናዘዙና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እመኑ፡፡ ያን ጊዜ ጌታ አስቀድሞ የዓለምን ሐጢያቶች ባነጻበት ወንጌል ሐጢያቶቻችሁን በሙሉ ያነጻል፡፡
የሐዋርያው ዮሐንስ እምነት የዚህ አይነት ነበር፡፡ በ1ኛ ዮሐንስ ምዕራፍ 5 ላይ እርሱ ‹‹በውሃ፣ በደሙና በመንፈሱ›› እምነት እንዳለው ይናገራል፡፡ በውሃ፣ በደምና በመንፈስ በመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ታምናላችሁን? የምታምኑት በመስቀሉ አማካይነት በመጣው ኢየሱስ ብቻ ነው ወይስ በጥምቀቱ፣ በደሙና በመንፈሱ በመጣው ኢየሱስ?
በደሙ ወንጌል ብቻ በማመን ወደ እግዚአብሄር መንግሥት መግባት ትችላላችሁን? እምነታችሁ የተመሰረተው በመስቀሉ ደም ብቻ ከሆነ የምታውቁት ግማሹን ወንጌል ነው፡፡ በደሙ ወንጌል ብቻ የምታምኑ ከሆነ ራሳችሁን በየዕለቱ ለምትሰሩት ሐጢያት በመጸለይ እንደምታገኙት አያጠራጥርም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ሐጢያቶቻችሁ ሊወገዱ የሚችሉት የንስሐ ጸሎቶችን በመጸለይ ነው ብላችሁ ማመናችሁ ነው፡፡
ነገር ግን በኢየሱስ የመስቀል ደም በማመን፣ ለዘወትር ሐጢያቶቻችሁ ንስሐ በመግባትና ይቅርታን በመለመን ሐጢያቶቻችሁ ሊነጹላችሁ ይችላሉን? እናንተ ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ከሆናችሁ ማንም ሰው በመስቀሉ ደም ብቻ ባለው እምነት ወይም በንስሐ ጸሎቶች  ሐጢያቶቹ ሊነጹ ስለማይችሉ ለዘላለም ሐጢያቶችን በልባችሁ ውስጥ ይዛችሁ ትቀራላችሁ፡፡ እናንተ ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ከሆናችሁ አሁንም ድረስ ትክክለኛውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል አታውቁትም፤ እምነታችሁም ጎዶሎ ነው፡፡
ሐዋርያው ዮሐንስ ዳግም የተወለደው በትክክለኛው የውሃው፣ የደሙና የመንፈሱ ወንጌል ስላመነ ነው፡፡ እናንተ ግን የምታምኑት በደሙ ወንጌል ብቻ ነው፡፡ ስለ ወንጌሉ እናንተ ራሳችሁ ግልጽ የሆነ መረዳት ሳይኖራችሁ እንዴት ሌሎችን ወደ ደህንነት መንገድ ልትመሩ ትችላላችሁ? ራሳችሁ ዳግም አልተወለዳችሁም፤ ነገር ግን ሐጢያቶቻችሁን በንስሐ ጸሎት ለማስወገድ እየሞከራችሁ ነው፡፡ ይህ መንገድ በጭራሽ የትም አያደርስም፡፡
አንድ ሰው ምንም ያህል ጠንክሮ ቢጸልይና ንስሐ ቢገባም ሐጢያቶቹ ከልቡ ሊነጹለት አይችሉም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሐጢያቶቻችሁ በሙሉ እንደነጹላችሁ የምታስቡ ከሆነ ይህ የእናንተ ምኞትና የፍላጎታችሁ ውጤት ብቻ ነው፡፡ የምትጸልዩና ንስሐ የምትገቡ ከሆነ ለአንድ ቀን የታደሳችሁ መስሎ ሊሰማችሁ ይችላል፡፡ ነገር ግን መቼም ቢሆን በዚህ መንገድ ከሐጢያቶቻችሁ ነጻ መሆን አትችሉም፡፡
ሐጢያተኞች ከሐጢያቶቻቸው ለመንጻት ተስፋ በማድረግ ይጸልያሉ፤ ንስሐም ይገባሉ፡፡ በኢየሱስ ካመኑ ከረጅም ጊዜ በኋላም አሁንም ሐጢያተኞች የሆኑተ ለዚህ ነው፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል አያውቁትም፡፡ በኢየሱስ የምታምኑ ነገር ግን ገና ዳግም ካልተወለዳችሁ እናንተም ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ልትሆኑ ትችላላችሁ፡፡ በየቀኑ በመጸለይና ንስሐ በመግባት ለሐጢያቶቻችሁ ይቅርታ የምትጸልዩ ከሆነና አሁንም ድረስ ሐጢያተኞች መሆናችሁን የምታስቡ ከሆነ ይህ ዳግም ላለመወለዳችሁ ግልጽ ምስክርነት ነው፡፡ ልክ ሐዋርያው ዮሐንስ እንዳደረገው በውሃና በመንፈስ ወንጌል የምታምኑ ስለመሆናችሁ መወሰን ይኖርባችኋል፡፡ አለበለዚያም እምነታችሁን በአስተሳሰቦቻሁና በስሜቶቻችሁ ላይ አድርጉ፡፡ አንዱ ግልጽ እውነት ሲሆን ሌላው ደግሞ እውነት አይደለም፡፡
እውነተኛው ወንጌል በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ኢየሱስ በጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ እንደወሰደና በመስቀል ላይ ለእነዚህ ሐጢያቶች ፍርድን እንደተቀበለ የሚናገረው ወንጌል ነው፡፡ አንድ ሰው በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ሞቱ የሚያምን ከሆነ ለአንዴና ለመጨረሻ ከሐጢያቶቹ ይድናል፡፡ በሌላ በኩል አንድ ሰው መተላለፎቹን በንስሐ ጸሎቶች ለማስወገድ የሚሞክር ከሆነ ከሐጢያቶቹ በጭራሽ ነጻ ሊሆን አይችልም፡፡ የዘወትር ሐጢያቶቻችሁን ማስታወስ የምትችሉ ይመስላችኋልን? እግዚአብሄር ንስሐ ያልገባችሁባቸውን ሐጢያቶቻችሁን ይተውላችኋልን? የንስሐ ጸሎቶች ለየዕለት ሐጢያቶች ችግር ግልጽ መፍትሄ ናቸውን? ለእነዚህ ጥያቄዎች ብቸኛው መልስ አይደሉም የሚለው ነው፡፡
 


እውነተኛ ንስሐና የኑዛዜ አላማ፡፡ 

 
የኑዛዜና የበጎ ምግባሮች ገደቦች ምንድናቸው? 
በሕይወታችን ሁሉ ሐጢያቶቻችንን መናዘዝ ቢኖርብንም መተላለፎቻችንን በመናዘዝና በጎ ሥራዎችን በማድረግ ብቻ ልንድን አንችልም፡፡
 
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ንስሐ ማለት ከስህተት እምነት ወደ ትክክለኛ እምነት መመለስ ፤  ለጻድቃን ደግሞ የአንድን ሰው የተሳሳተ አድራጎት አምኖ በመቀበል ወደ ወንጌሉ ብርሃን መመለስ ማለት ነው፡፡
አሁን ሐጢያተኛ ከሆናችሁ የሚከተለውን አይነት ኑዛዜ ልታደርጉ ይገባችኋል፡፡ ‹‹ውድ አምላክ ሐጢያትን ሰርቻለሁ፤ ሲዖል መወርወር ይገባኛል፡፡ ነገር ግን ከሐጢያቶቼ መዳን እናፍቃለሁ፡፡ እባክህ ከሐጢያቶቼ ሁሉ አድነኝ፡፡ ገና ዳግም አልተወለድሁም፡፡ ለሲዖል የተመደብሁ እንደሆንሁም አውቃለሁ፡፡›› ያ ትክክለኛ ኑዛዜ ነው፡፡
ዳግም የተወለደውስ ምን አይነት ኑዛዜ ማድረግ ይኖርበታል? ‹‹አቤቱ ሥጋዬን የመከተል ሐጢያት ሰርቻለሁ፡፡ ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ ሲጠመቅ ከሐጢያቶቼ፤ አሁን ከፈጸምሁዋቸው ሐጢያቶቼ እንኳን ሳይቀር እንዳዳነኝ አምናለሁ፡፡ እንደዚያ ባይሆን ኖር በሐጢያቶቼ አማካይነት እሞት ነበር፡፡ በውሃና በደም ስላዳነኝ ጌታን አመሰግናለሁ፡፡›› ዳግም የተወለደ ሰው የሚያደርገው ኑዛዜና ዳግም ያልተወለደው የሚያደርገው ኑዛዜ የተለያዩ ናቸው፡፡
እኛ ሁላችን የሐዋርያው ዮሐንስ አይነት እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ ሐጢያቶቻችሁን ለጻድቃን ከሆነው ኑዛዜ ጀርባ ለመደበቅ የምትሞክሩ ከሆነ የሐጢያት ደመወዝ ከሆነው ሞት በጭራሽ አትድኑም፡፡
ዳግም ያልተወለዱ ሐጢያተኞች በሙሉ ከኑዛዜ ጸሎቶች በስተ ጀርባ ለመደበቅ ከመሞከር ማቆምና በእውነተኛው የውሃ፣ የደምና የመንፈስ ወንጌል ማመን መጀመር ይገባቸዋል፡፡ የሐዋርያው ዮሐንስን እምነት መማርና በዚያም ደህንነትን ማግኘት ይገባቸዋል፡፡
ሐጢያተኞች ለሐጢያቶቻቸው የሚፈረድባቸው ፍርድ ምን ያህል አስከፊ እንደሚሆን አያውቁም፡፡ በእግዚአብሄር ፊት በእጅጉ አስከፊው ሐጢያት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ዳግም የመወለድን ወንጌል አለማመን ነው፡፡
በኢየሱስ የሚያምኑ ነገር ግን ገና ዳግም ያልተወለዱ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሄር ፊት ‹‹ጌታ ሆይ እባክህ ሐጢያቶቼን አንጻ›› ከማለት ታቅበው ‹‹እኔ ወደ ሲዖል እሳቶች መወርወር የሚገባኝ ሐጢያተኛ ነኝ›› በማለት መናዘዝ ይገባቸዋል፡፡ ሐጢያተኛ ኢየሱስ በዮርዳኖስ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ደሙ አማካይነት እንዳዳነው ወንጌሉን በልቡ ውስጥ ሲያኖር ከሐጢያቶቹ ሁሉ ነጻ ሊወጣ ይችላል፡፡ ሐጢያተኛ በእግዚአብሄር ፊት ከሐጢያቶቹ ሁሉ ይድን ዘንድ ሊያደርግ የሚገባው የኑዛዜ አይነት ይህ ነው፡፡
ሐጢያተኛ ገና ዳግም እንዳልተወለደ መናዘዝና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን ብቻ አለበት፡፡ ያን ጊዜ በአንዴ ይድናል፡፡ የሐጢያተኞች ደህንነት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ተጠናቋል፡፡ ‹‹መዳንም በሌላ በማንም የለም፡፡ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 4፡12) እግዚአብሄር ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በአጥማቂው ዮሐንስ እንዲጠመቅና በመስቀል ላይ እንዲሞት በማድረግ ሐጢያተኞችን ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው አዳነ፡፡
ጌታ ሰዎች ከተወለዱ አንስቶ እስከሚሞቱ ድረስ በሥጋቸውና በልቦቻቸው የሚሰሩትን ሐጢያቶች በሙሉ አነጻላቸው፡፡ ለመዳን በእውነተኛው ወንጌል ማመን አለበን፡፡ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ነጻ መውጣትና በተጨባጭ መቀደስ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ ይህ ነው፡፡ በእውነተኛው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ስናምን ለአንዴና ለመጨረሻ ጻድቃን መሆን እንችላለን፡፡
ኢየሱስ ተጠመቀ፡፡ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ አነጻ፡፡ ለእነርሱም ሕይወቱን በመስቀል ላይ ከፈለ፡፡ በሦስተኛውም ቀን ተነሳ፡፡ አሁን በእግዚአብሄር ቀኝ ተቀምጦዋል፡፡ ብቸኛው እውነት ይህ ነው፡፡
ሁላችንም ይህንን ኑዛዜ ማቅረብ ይገባናል፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ እስከ ዕለተ ሞቴ ድረስ ሐጢያትን እሰራለሁ፡፡ ከእናቴ ማህጸን ስወለድ ጀምሮ ሐጢያተኛ ሆኜ ተወልጃለሁ፡፡ ለሰራሁዋቸው ሐጢያቶቼ በሙሉ ዕዳ ስላለብኝ ወደ ሲዖል እሳት መወርወር ይገባኛል፡፡ በዚህ ምክንያት በውሃ፣ በደምና በመንፈስ በመጣው በኢየሱስ ማመንና አዳኜ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡››
በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ላይ እንደተጻፈው ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ የምንሰራቸውን ሐጢያቶች በሙሉ ጨምሮ የዓለምን ሐጢያቶች ወሰደ፡፡ ‹‹እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም አርነት ያወጣችኋል፡፡›› (ዮሐንስ 8፡32)
ኢየሱስ ያዳነን ከአዳም ሐጢያቶቻችን ብቻ ቢሆንና በየዕለቱ የምንሰራቸውን ሐጢያቶች በራሳችን እንድንፈታ ቢነግረን ኖሮ በማያቋርጥ ስቃይ ውስጥ በሆንን ነበር፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ በጥምቀቱና በደሙ ለአንዴና ለመጨረሻ ከሐጢያቶቻችን በሙሉ አዳነን፡፡ ምን የምንጨነቅበት ነገር ይኖራል? በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀሉ ደም ስናምንና ጌታን ስናመሰግነው መንፈስ ቅዱስ በልቦቻችን ውስጥ ያድራል፡፡
በኢየሱስ ታምናላችሁን? በውስጣችሁ መንፈስ ቅዱስ እንዳደረባችሁ ታምናላችሁን? እርሱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በጥምቀቱ በወሰደ ጊዜ ሐጢያቶቻችሁ በሙሉ ወደ ኢየሱስ ተላለፉ፡፡ በኋላም በመስቀል ላይ ለሐጢያቶቻችን ተፈረደበትና ከዘላለም ኩነኔ ነጻ አወጣን፡፡ እውነተኛው ወንጌል ይህ ነው፡፡ 
 

የጻድቃን ኑዛዜ፡፡  
 
የጻድቃን እውነተኛ ኑዛዜ ምንድነው? 
በየዕለቱ ሐጢያትን እንደሚሰሩና ከ2,000 ዓመታት በፊት ኢየሱስ የዘወትር ሐጢያቶቻቸውን ያነጻላቸው የመሆኑን እውነት መናዘዝ ነው፡፡ 
 
1ኛ ዮሐንስ 1፡9 እንዲህ ይላል፡- ‹‹በሐጢአታችን ብንናዘዝ ሐጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመጻም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡›› ይህ ማለት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ለማመን የወሰነ ሰው ‹‹ጌታ ሆይ በሕይወቴ ሐጢያትን ከመስራት ውጪ ሌላ ምንም እንደማልፈይድ አውቃለሁ፡፡ በይቅርታ ጸሎቶች አማካይነትም ከሐጢያቶቼ ሁሉ መዳን እንደማልችል አውቃለሁ፡፡ የሐጢያት ደመወዝ ሞት መሆኑንና ከኢየሱስ ጥምቀትና ስቅለት በስተቀር ሐጢያቶቼን ሊያነጻልኝ የሚችል እንደሌለ አምናለሁ፡፡ ዛሬ ሐጢያት መስራቴን እናዘዛለሁ፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ዛሬም የሰራሁትን ሐጢያት ከ2,000  ዓመታት በፊት በዮርዳኖስ እንዳነጻልኝ አምናለሁ›› በማለት ሐጢያቶቹን መናዘዝ አለበት ማለት ነው፡፡ ይህ ሰው በዚህ መንገድ ከጸለየ በሕሊናው ውስጥ ያለው የሐጢያቶች ችግር በአንድ ጊዜ ይፈታል፡፡    
ቀድሞውኑም ዳግም የተወለዱ ሰዎች የሚጠበቅባቸው ሐጢያቶቻቸውን መናዘዝ ብቻ ነው፡፡ የሚሰሩዋቸውን ሐጢያቶች በሙሉ ኢየሱስ እንዳነጻላቸው ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ኢየሱስ ከ2,000 ዓመታት በፊት ለሐጢያተኞች ስለተጠመቀና ስለሞተ ምንም ያህል ደካሞች ቢሆኑም ሐጢያቶቻቸው በሙሉ ፈጸመው ነጽተዋል፡፡
ዛሬ ያነበብነው ጥቅስ ለጻድቃን በጣም ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሐጢያተኛ ይህንን ጥቅስ በመውሰድ በተሳሳተ መንገድ የሚጠቀምበት ከሆነ መጨረሻው ሲዖል ይሆናል፡፡ የሆኖ ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ በተሳሳተ መንገድ ከሚጠቀሱት ምንባቦች አንዱ ይህ ነው፡፡ ይህ ለረጅም ጊዜ በክርስቲያኖች መካከል ትልቅ አለመግባባትን ፈጥሮዋል፡፡ 
ብቃት የሌለው ሐኪም በሽተኞቹን ይገድላል የሚል አባባል አለ፡፡ ብቃት የሌለው ሐኪም ከሚችለው በላይ ለማድረግ ቢሞክር በሽተኞቹን ሊገድላቸው ይችላል፡፡  
አንድ ሰው ተግባሮቹን በትክክል ማከናወን ይችል ዘንድ ብቃቱ እስከሚረጋገጥ ድረስ መሰልጠን ያለበት መሆኑ የሕይወት ሕግ ነው፡፡ በዓለም ሃይማኖት እንደዚሁ ተመሳሳይ  ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል የሚያስተምሩ እውነቱን ልክ እንደተጻፈው በትክክልና በግልጽ ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ከእነዚህ የሚማሩትም በተማሩት ነገር ላይ እምነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡
ሰባኪዎች ለተከታዮቻቸው የተሳሳቱ ትምህርቶችን ካስተማሩ ወይም ምዕመናን መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ ከተማሩ የሁለቱም መጨረሻ ፍርድና ሲዖል ይሆናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል ማስተማር የሚችሉት ዳግም የተወለዱ ብቻ ናቸው፡፡ ጥሩ መድሃኒትም በትክክል ካልተወሰደ ይገድላል፡፡ የእግዚአብሄር ቃልም እንዲሁ ነው፡፡ ይህ ልክ በሕይወታችን ውስጥ እንዳለው እሳት ሁሉ አስፈላጊ ነው፡፡ እሳት በሕጻናት እጅ ከገባ የሚያደርሰው አደጋ የከፋ እንደሆነ ሁሉ የእግዚአብሄርም ቃል በተሳሳተ እጆች ውስጥ ከገባ አስከፊ ጥፋት ሊያደርስ ይችላል፡፡      
በጻድቃን ኑዛዜና በሐጢያተኞች ኑዛዜ መካከል ያለውን ልዩነት በትክክል መረዳት አለብን፡፡ 1ኛ ዮሐንስ 1፡9 የተጻፈው ለጻድቃን ነው፡፡ ጻድቅ ሰው በጌታ ፊት ሐጢያቶቹን በእምነት ሲናዘዝ ኢየሱስ ከ2,000 ዓመታት በፊት ሐጢያቶቹን በሙሉ ስላነጻለት ከሐጢያቶቹ ሁሉ ነጻ ነው፡፡
ሐጢያተኞች ለይቅርታ በጸለዩ ጊዜ ሁሉ ሐጢያቶቻቸው እንደሚነጹ የሚያምኑ ከሆነ ተሳስተዋል፡፡ ሰው ዳግም ካልተወለደ ሐጢያቶቹ በኑዛዜ ብቻ ሊነጹ ይችላሉን?
እግዚአብሄር ጻድቅ ነው፡፡ አንድያ ልጁንም ወደዚህ ዓለም ልኮ በጥምቀቱ አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች እንዲወስድ በማድረግ በጥምቀቱ ውሃና በመስቀል ላይ ደሙ የሚያምኑትን ሁሉ አዳነ፡፡ ስለዚህ ጻድቅ የሆነ ሰው ሐጢያቶቹን ሲናዘዝ እግዚአብሄር ኢየሱስ ቀድሞውኑም ከ2,000 ዓመታት በፊት ሐጢያቶቹን በሙሉ እንደወሰደ ይነግረዋል፡፡ ይህ ግለሰብ ምንም እንኳን ሥጋው አሁንም ድረስ ሐጢያት ቢሰራም በልቡ ውስጥ ሐጢያት እንደሌለ ያረጋግጣል፡፡