‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 2፡1-7 ››
ሰማዕትነት ለብዙዎቻችን የማይታወቅ ቃል ነው፡፡ ነገር ግን ክርስቲያን ባልሆነ ባህል ውስጥ ላደጉ ሰዎች ደግሞ ይበልጥ እንግዳ የሆነ ቃል ነው፡፡ ‹‹ሰማዕትነት›› የሚለው ቃል በእርግጥም ብዙውን ጊዜ በቀን ተቀን ሕይወታችን የሚገጥመን ቃል አይደለም፡፡ ከቃሉ ተለይተን የራቅን መስሎ ይሰማናል፡፡ ምክንያቱም በእውነት ሰማዕት የምንሆን ስለመሆናችን ማሰቡ ምናብ ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ የራዕይ መጽሐፍ ምዕራፍ 2 እና 3 ይህንን ሰማዕትነት ያብራራሉ፡፡ ከቃሉም በልባችን ውስጥ የሰማዕትነትን እምነት ማለትም ሰማዕት መሆን የምንችልበትን እምነት ማጽናት አለብን፡፡
የሮም ንጉሠ ነገሥታት ሕዝባቸውን የሚያስተዳድሩ የመንግሥቱ አምባገነን መሪዎች ነበሩ፡፡ በግዛታቸው ላይ አምባገነን ሥልጣንን በመተግበር ልባቸው የሚሻውን ማንኛውንም ነገር ማድረግ ችለው ነበር፡፡ የሮም መንግሥት ብዙ ጦርነቶችን ተዋግቶ በማሸነፉ ብዙ አገሮችን በራሱ አስተዳደር ስር አስገዝቶ ድል በተነሱት መንግሥታቶች በሚቀርቡለት ግብሮች ራሱን አበልጥጎ ነበር፡፡ ትንሽዋ አገር በአንዱም ጦርነት ሳትሸነፍ ከዓለም እጅግ ታላላቅ መንግሥታት አንዷ በመሆን አደገች፡፡ የእርስዋ ንጉሠ ነገሥታቶች ሥልጣናቸውን ለመተግበር የገደባቸው ሰማይ ብቻ ነበር፡፡ ይህ ሥልጣን እጅግ ታላቅ በመሆኑ ውሎ አድሮ በሕዝቡ ዘንድ ሕያዋን አማልክቶች እንደሆኑ ተደርገው ተሰገደላቸው፡፡
ለምሳሌ ንጉሠ ነገሥታቶች በራሳቸው አምሳል ሐውልቶችን አሰርተው ሕዝቡ በፊታቸው እንዲንበረከክላቸው ማድረግ የተለመደ ነበር፡፡ ራሳቸውን አማልክቶች አድርገው ላወጁ ንጉሠ ነገሥታቶች በኢየሱስ ያመኑ ምዕመናኖችን ለማሰደድ፣ ለማሰር፣ ወደ ግዞት ለመወርወርና ውሎ አድሮም ስለ እምነታቸው ለመግደል ጨቋኝ ፖሊሲዎቻቸውን ዘረጉ፡፡ የጥንት ክርስቲያኖች ከስደት ለማምለጥ እንደ ካታኮምብ ባሉ ስፍራዎች የተደበቁት ይህንን ታሪካዊ ዳራ በመቃወም ነበር፡፡ ጻድቅ እምነታቸውን ለመከላከል ሲሉ ሰማዕትነትን እንዲቀበሉ መሰረትን የጣለላቸው ይህ ስደት ነበር፡፡
በጥንቷ ቤተክርስቲያን ዘመን ሰማዕታት የተነሱት እንደዚህ ነበር፡፡ በእርግጥ የዚያ ዘመን ቅዱሳኖች ሰማዕታት የሆኑት የንጉሠ ነገሥታቶችን ሥልጣን ለመቀበል እምቢተኞች በመሆናቸው ብቻ አይደለም፡፡ የእነርሱን ዓለማዊ ሥልጣን ተቀብለዋል፤ ነገር ግን ሰውን እንደ አምላክ እንዲያመልኩና ኢየሱስን ከልባቸው አውጥተው እንዲጥሉ ባስገደዱዋቸው ጊዜ ግን የገዛ ራሳቸውን ሕይወት በመክፈል ያንን ሥልጣን ዳግመኛ አንቀበልም አሉ፡፡ የሮም ንጉሠ ነገሥታት ክርስቲያኖች ኢየሱስን እንዲክዱና እነርሱንም እንደ ንጉሠ ነገሥታቶች ብቻ ሳይሆን እንደ አማልክቶች እንዲያመልኩዋቸው አዘዙዋቸው፡፡ እንዲህ ላሉት ጥያቄዎች ለመንበርከክ ባለመቻላቸውና ባለመፍቀዳቸው የጥንት ክርስቲያኖች ስደትን መጋፈጥ ቀጠሉ፡፡ በ313 ዓ.ም የወጣው የሚላን ድንጋጌ በመጨረሻ የሐይማኖት ነጻነት እስኪሰጣቸው ድረሰ እምነታቸውን ለመከላከል ሰማዕት መሆናቸውን ቀጠሉ፡፡ በፊታችን እንዳለፉት እንደ እነዚህ አባቶቻችን እኛም እምነታችንን ከመተው ይልቅ የጽድቅን ሞት መጋፈጥ ይኖርብናል፡፡
በትንሽዋ እስያ ስላሉት ሰባት አብያተ ክርስቲያናት የሚናገረው ምንባብ በዚያ ዘመን የነበሩትን ገጠመኞችና ሁነቶች የሚያብራራ ብቻ ሳይሆን ሊመጣ ስላለው ዓለም የተሰጠ መገለጥ ነበር፡፡ በውስጡ የእግዚአብሄር ባሮችና ቅዱሳን እምነታቸውን ለመከላከል ሰማዕታት እንደሚሆኑ የሚናገር መገለጥ ይገኛል፡፡ በሮም መንግሥት ዘመን እንደሆነው ሁሉ የዘመኑ የሮም ንጉሠ ነገሥት አምሳያ ሆኖ ሰውን ሁሉ ከጨቋኝ አገዛዙ ሥር የሚገዛ በራሱ አምሳልም ምስል የሚያሰራ፣ ሰው ሁሉ በፊቱ እንዲንበረከክ የሚጠይቅና እንደ አምላክ ይመለክ ዘንድ የሚያዝዝ አምባገነን ገዥ የሚነሳበት ዘመን ይመጣል፡፡ ይህ ከእኛ ዘመን ብዙም የራቀ አይደለም፡፡ ይህ ዘመን ሲመጣ ብዙ ቅዱሳኖች የጥንቷን ቤተክርስቲያን ምዕመናኖች የሰማዕትነት ዱካዎች ይከተላሉ፡፡
ስለዚህ ጌታችን በእስያ ላሉት ለሰባቱ ቤተክርስቲያኖች የሰጠውን ተግሳጽ ቃል በልባችን ውስጥ መጠበቅ አለብን፡፡ እግዚአብሄር በእስያ ያሉትን ሰባቱን ቤተክርስቲያኖች ሰላም በማለት በማደፋፈርና በመገሰጽ ‹‹ድል የነሳው›› ‹‹በእግዚአብሄር ገነት መካከል ካለው የሕይወት ዛፍ እንደሚበላ›› እና ‹‹የሕይወትን አክሊል›› ‹‹የተሰውረውን መና›› ‹‹የንጋት ኮከብን›› እና ሌላም እንደሚቀበል ተስፋ ሰጥቶዋል! ይህ እግዚአብሄር በሰማዕትነታቸው አማካይነት ድል ለነሱት ሰዎች ዘላለማዊ የሆኑትን የሰማይ በረከቶች ሁሉ የሚሰጣቸው የመሆኑ የታመነ የእግዚአብሄር ተስፋ ነው፡፡
የጥንቷ ቤተክርስቲያን ቅዱሳኖች ሰማዕትነታቸውን መጋፈጥ የቻሉት እንዴት ነው? ልናስታውሰው የሚገባን የመጀመሪያው ነገር ሰማዕት መሆን የሚችሉት ሰዎች የእግዚአብሄር አገልጋዮችና ቅዱሳን የነበሩ መሆናቸውን ነው፡፡ ሁሉም ሰው ሰማዕት መሆን አይችልም፡፡ ሰማዕትነትን መጋፈጥ የሚችሉት ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው የሚያምኑ፣ በስደት ውስጥ የማይንበረከኩና እምነታቸውን አጥብቀው ይዘው በጌታ የሚታመኑ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡
እዚህ ላይ በፍጥሞ ደሴት በስደት ሳለ የኤፌሶንን ቤተክርስቲያን ሲገስጽ የምናየው ሐዋርያው ዮሐንስ ከአስራ ሁለቱ የኢየሱስ ሐዋርያቶች መካከል በሕይወት የተረፈ የመጨረሻው ሰው ነበር፡፡ ሌሎቹ ሐዋርያቶችና እንደዚሁም ቅዱሳን ሁሉ አስቀድመው ሰማዕታት ሆነዋል፡፡ ከታሪክ አንጻር በእስያ ያሉት የሰባቱ ቤተክርስቲያናት ቅዱሳኖች እስከ 313 ዓ.ም ድረስ ሰማዕት ከሆኑት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ክርስቲያኖች መካከል ጥቂቶች ብቻ ነበሩ፡፡ እነርሱ ከሮማውያን ባለሥልጣናት ስደት በመሸሽ ሕቡዕ ገብተው ከእነርሱ ርቀው የማምለጫ ዋሻዎችን በመቆፈር ለአምልኮ ካታኮምብ በሚባሉ የመቃብር ሥፍራዎች ውስጥ በድብቅ ይሰበሰቡ ነበር፡፡ በዚህና ከዚህም በላይ በሆነው ነገር ፈጽሞ እምነታቸውን አልካዱም፡፡ በውዴታቸውም ሰማዕትነታቸውን ተቀበሉ፡፡
በእስያ ያሉት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችና ቅዱሳን እዚህ ላይ በእግዚአብሄር ብትገሰጽም የኤፌሶንን ቤተክርስቲያን ጨምሮ ሁሉም ሰማዕታት ሆነዋል፡፡ ሰማዕት እንዲሆኑ ያስቻላቸው በጌታ ላይ ያላቸው እምነት ነበር፡፡ ሁሉም ጌታ አምላክ እንደሆነ፣ ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ እንደወሰደ፣ ወደ ሺህው ዓመት መንግሥትና ወደ አዲስ ሰማይና ምድር የሚመራቸው እረኛም እንደነበር አምነዋል፡፡ ከሰማዕትነታቸው ጋር የተያያዘውን ፍርሃታቸውንና የሞት ጣዕራቸውን በሙሉ ድል መንሳት ያስቻላቸው ይህ እምነትና የተስፋ ማረጋገጫ ነበር፡፡
አሁን እየኖርን ያለነው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ነው፡፡ ዓለም በአንድ ሥልጣን ስር የሚቆራኝበትና አምባገነን ሥልጣን ተግባራዊ የሚያደርግ ገዥ ብቅ የሚልበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ በራዕይ 13 ላይ እንደተመዘገበው ይህ አምባገነን ገዥ በቅዱሳን ሕይወት ላይ በመዛት እምነታቸውን እንዲያወግዙ ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን እኛ በመጨረሻው ዘመን የምንኖር ቅዱሳን ዛቻዎቹንና ማሳቀሉን ማሸነፍና በሰማዕትነታችን እምነታችንን መከላከል እንችላለን፡፡ ምክንያቱም የጥንቷ ቤተክርስቲያን የነበራት ዓይነት ተመሳሳይ እምነት አልንና፡፡
እግዚአብሄር በቁጥር 4-5 ላይ እንዲህ በማለት የኤፌሶንን ቤተክርስቲያን ነቅፎዋል፡- ‹‹ዳሩ ግን የምንቅፍብህ ነገር አለኝ፡፡ የቀደመውን ፍቅር ትተሃልና፡፡ እንግዲህ ከወዴት እንደወደቅህ አስብ፡፡ ንስሐም ግባ፡፡ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፡፡ አለዚያ እመጣብሃለሁ፤ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ፡፡›› ይህ ምን ማለት ነው? የኤፌሶን ቤተክርስቲያን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ትታለች ማለት ነው፡፡ በኤፌሶን ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ጨምሮ የጥንቷ ቤተክርስቲያን ቅዱሳን በሙሉ በውሃና በመንፈሱ ወንጌል አምነው ነበር፡፡ ምክንያቱም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሙሉ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እያሰራጩና እየሰበኩ ነበርና፡፡ ስለዚህ በዚያን ዘመን የነበሩት ቅዱሳን ከሐዋርያት የተቀበሉት ወንጌል የተሟላ ወንጌል እንጂ ሐሰተኛ፣ ሰው ሰራሽና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም ብቻ የሚያምን ወንጌል አልነበረም፡፡
ነገር ግን እዚህ ላይ የኤፌሶን ቤተክርስቲያን አገልጋይ የቀደመውን ፍቅሩን እንደተወ ተነግሮዋል፡፡ ይህ ማለት የኤፌሶን ቤተክርስቲያን አገልጋይ በቤተክርስቲያን አገልግሎቱ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ትቷል ማለት ነው፡፡ ጌታ ንስሐ ካልገባ በቀር መቅረዙን ከስፍራው እንደሚወስድበት የተናገረው ለዚህ ነው፡፡ መቅረዙን ከእርሱ መውሰድ ማለት ቤተክርስቲያንን መውሰድ ማለት ሲሆን ይህም መንፈስ ቅዱስ ከእንግዲህ ወዲያ በኤፌሶን ቤተክርስቲያን ውስጥ አይሰራም ማለት ነው፡፡
ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን አገልጋይ ወደ ውሃውና መንፈሱ ወንጌል መመለስ በእርግጥም አስቸጋሪ ነገር አልነበረም፡፡ ነገር ግን ይህ ከችግሮቹ ሁሉ ትንሹ ነበር፡፡ ችግር ውስጥ የከተተው ነገር በልቡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ቢያምን ያመነውን በግልጽ መስበክ የተሳነው መሆኑ ነበር፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ባያምኑም ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው ብቻ የመሰከሩ ሰዎችን ሁሉ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ተቀበለ፡፡ ምዕመናን በውሃውና በመንፈሱ ላይ ያላቸውን እምነት መመስከር ማለት ለሰማዕትነት መዘጋጀት ማለት ነው፡፡
ስለዚህ በሌላ አነጋገር በእግዚአብሄርና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ተመሳሳይ እምነት ይኑራቸው ወይም አይኑራቸው ወደ እርሱ ቤተክርስቲያን የመጡትን ሁሉ ተቀበለ፡፡ ከእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ጋር መቀላቀል ብቻ መስዋዕትነትን ስለሚያስከፍልና የኤፌሶን ቤተክርስቲያን አገልጋይም እነዚህ መስዋዕትነቶች ብዙዎች ከቤተክርስቲያን ጋር እንዳይቀላቀሉ ይከለክላሉ ብሎ ስለፈራ ፍጹም የሆነውን ወንጌል ግልጽ በሆኑ ቃሎች መስበክ ተሳነው፡፡
ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ እውነት በሌለበት ስፍራ መኖር ስለማይችል እግዚአብሄር መቅረዙን እንደሚወስድ ተናገረ፡፡ እግዚአብሄር ቤተክርስቲያኑን የሚወስደው የኤፌሶን ቤተክርስቲያን አገልጋይና ቅዱሳኖች ሥራ ስለጎደላቸው አልነበረም፡፡ እንዲህ በማለቱ እግዚአብሄር ከእንግዲህ ወዲያ በቤተክርስቲያን ውስጥ እንደማይኖር መናገሩ ነው፡፡ ምክንያቱም እውነት ከእንግዲህ ወዲህ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ሊገኝ አይችልምና፡፡
የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መከተል ያለባት መሆኑ አስፈላጊ ግዴታ ነው፡፡ የእግዚአብሄር አገልጋዮችና ቅዱሳን በዚህ ወንጌል ማመን ብቻ ሳይሆን ግልጽና ፍጹም በሆኑ ቃሎች መስበክና ማስተማር አለባቸው፡፡ የእግዚአብሄርን ፍቅር፣ ጸጋውንና ለእኛ ያለውን ባርኮቶች ሁሉ ማግኘት የምንችለው በዚህ ወንጌል ውስጥ ብቻ ነውና፡፡
የኤፌሶን ቤተክርስቲያን አገልጋይ ይህንን ወንጌል በመስበክ ፋንታ በመስቀል ላይ የፈሰሰውን ደም ብቻ የሚያምኑ ሰዎችን በጉባኤው ውስጥ ተቀበለ፡፡ ነገር ግን ዳግም የተወለደ አገልጋይ ቅዱስ ሰው ወይም ቤተክርስቲያንም ቢሆን በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በወሰደው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እያመነ የማይሰበክ ከሆነ የጌታችንን ሥራዎች ሁሉ ከንቱ ያደርጋል፡፡
በጌታ ዓይን ፊት ጉድለት ያለብን ብንሆንም በዚህ ወንጌል አምነን የምንሰብከው ከሆነ ጌታ እንደ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን አድሮ ሊሰራ ይችላል፡፡ የእግዚአብሄር አገልጋዮች ወይም ቅዱሳን በጉድለቶች የተሞሉ ቢሆኑም ጌታ በቃሉ አማካይነት ሊያስተምራቸውና ሊመራቸው ይችላል፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ባለበት ቤተክርስቲያን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ተገኘ ማለት ደግሞ ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ቅዱስ ናት ማለት ነው፡፡
የእግዚአብሄር ባሮች ወይም ቅዱሳን ዳግመኛ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የማይሰብኩ ከሆነ ቅድስና ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ሐጢአት እንደሌለባቸው መናገር ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በማይሰበክበት ስፍራ ቅድስና ሊገኝ አይችልም፡፡
ይህ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የጥንቷ ቤተክርስቲያን ቅዱሳኖች ያመኑበት ጌታ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በጥምቀቱ በመውሰድና በመስቀል ላይ ሞቱ ሁሉንም በማስወገድ የሰውን ዘር ለማዳን ወደዚህ ምድር እንደመጣ የሚያውጅ ወንጌል ነው፡፡ እርሱ ድክመቶቻችንንና ጉድለቶቻችንን ሁሉ በጥምቀቱ ወስዶዋል፡፡ እግዚአብሄር ከጉድለቶቻችንና ከድክመቶቻችን የመነጩትን ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በመውሰድ ዘላለማዊ እረኛችን ሆንዋል፡፡
ሰው እንደዚህ አብዝቶ ከተባረከ በኋላ ጌታን በሮማዊ ንጉሠ ነገሥት ለውጦ ተራ የሆነ ሟች ሰውን አምላኩ አድርጎ እንዴት ሊያመልክ ይችላል? የእግዚአብሄር ጸጋ በጣም ትልቅና በጣም የተትረፈረፈ በመሆኑ የሮም ንጉሠ ነገሥት ማባበያዎችም ሆኑ ዛቻዎች ቅዱሳኖች የእርሱን ፍቅር እንዲክዱ ማድረግ ባለመቻሉ እምነታቸውን ለመከላከል በፈቃዳቸውና በደስታ ሰማዕትነትን ተቀበሉ፡፡ እነርሱ እምነታቸውን እንዲያወግዙ የሚያስገድዱዋቸውን ዛቻዎችና እምነታቸውን በቁሳዊ ጥቅሞች እንዲለውጡ ለማባባል የሕዝብ ባለሥልጣናት ሆነው እንዲሾሙ የተደረጉትን ሙከራዎች አጣጣሉ፡፡ ሰማዕት እንዲሆኑ ያስቻላቸው ይህ የማይሞት ታማኝነታቸው ነበር፡፡
የሰማዕታት ልብ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ከሐጢያቶቻቸው ላዳናቸው የእግዚአብሄር ጸጋና ፍቅር በምስጋና የተሞላ ነው፡፡ እምነታቸው ለዘላለም ከሐጢያቶቻቸው ነጻ ያወጣቸውን የእግዚአብሄር ፍቅር የማይክድ ሰዎች ከክህደት ይልቅ ሰማዕትነትን ይቀበላሉ፡፡ የሮም ንጉሠ ነገሥታቶች የጥንቷ ቤተክርስቲያን ቅዱሳኖች መለኮታዊነታቸውን ተቀብለው እንደ አምላክ እንዲሰግዱላቸው እንደጠየቁ ሁሉ እኛ ደግሞ እምነታችንን እንድንክድ የምንገደድበት ዘመን ይመጣል፡፡ ይህ ሲሆን የእምነት አያቶቻችንን ዱካዎች መከተልና እምነታችንንም በሰማዕትነት መደገፍ ይገባናል፡፡
እኛ በጉድለቶች የተሞላን ብንሆንም እግዚአብሄር እጅግ ስለወደደን ጉድለቶቻችንንና ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ ወሰደ፡፡ ምንም ያህል በፊቱ ከክብሩ የጎደልን ብንሆንም እጆቹን ዘርግቶ ተቀብሎናል፡፡ እርሱ ማቀፍ ብቻ ሳይሆን የሐጢያትንና የጥፋትን ችግሮች በሙሉ ፈትቶ ለዘላለም የእርሱ ልጆችና ሙሽሮቹ አድርጎናል፡፡ በእርሱ ላይ ያለንን እምነት ፈጽሞ መካድ የማንችለውና ስለ ስሙም በውዴታና በደስታ ሰማዕትነትን የምንቀበለው ለዚህ ነው፡፡ ሰማዕትነት እግዚአብሄር የሰጠንን የቀደመውን ፍቅር የምንጠብቅበት ነው፡፡ የሰብዓዊ ስሜቶቻችን ውጤት ሳይሆን እግዚአብሄር ድክመቶችና ጉድለቶች ቢኖሩብንም በረከቶቹን ሁሉ የሰጠን በመሆኑ እውነታ ላይ የተመሰረተ የእምነት ውጤት ነው፡፡ ሰማዕት የምንሆነው በፈቃዳችን ጉልበት ሳይሆን በአምላካችን ታላቅነት ላይ ባለን እምነት ነው፡፡
በእርግጥ ለአገራቸው ወይም ለሚያምኑት አስተሳሰብ ሰማዕታት በመሆን የሚሞቱ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ትክክል ነው ብለው ላመኑበት ነገር የማይታጠፍ እርግጠኝነት ስላላቸው ለዚያ ላመኑበት ነገር ሕይወታቸውን አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኞች ናቸው፡፡ ነገር ግን እኛስ? በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት አማካይነት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ዳግመኛ የተወለዱ የእግዚአብሄር ልጆች ሰማዕት መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? ሰማዕት መሆን የምንችለው ጌታ እኛን ለወደደበትና ላዳነበት ወንጌል በጣም አመስጋኞች ስለሆንን ነው፡፡ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጉድለቶች ቢኖሩብንም እግዚአብሄር ስለተቀበለን፣ መንፈስ ቅዱስን ስለሰጠንና በፊቱ ለዘላለም እንድንኖር ሕዝቡ አድርጎ ስለባረከን እርሱ ፈጽሞ አይተወንም፡፡
እግዚአብሄር አዲስ ሰማይና ምድርም ተስፋ ሰጥቶናል፡፡ ለዚህ ተስፋ ስንል ብቻ እምነታችንን አንተውም፡፡ ምንም ነገር ይምጣ -- ጸረ ክርስቶስ በመጨረሻው ዘመን ለሞት ቢዝትብንና ቢያሳድደንም -- ጌታችንንና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በጭራሽ አንክድም፡፡ በጸረ ክርስቶስ እግር ፊት ብንጎተትና ለሞት ተላልፈን ብንሰጥ እኛን ያዳነንን የእግዚአብሄር ጸጋና ፍቅር ፈጽሞ አንክድም፡፡ ‹‹በሬሳችንም›› ቢሆን እንኳን ጌታን አንክደውም፡፡ ሌሎች ነገሮችን እንድናደርግ እንገደደ ይሆናል፤ ነገር ግን ፈጽሞ የማንቀበለው አንድ ነገር አለ፤ ያዳነንን የክርስቶስን ፍቅር አንተውም፤ አንክድም፡፡
ጉድለቶች ስላሉብን ጸረ ክርስቶስ የሚራራልን ይመስላችኋልን? አይራራልንም! ግድም አይሰጠውም! ነገር ግን ምንም ያህል ፈጽሞ ደካሞችና ጎዶሎዎች ብንሆንም ጌታችን ችግሮቻችንን በሙሉ በመውሰድና በእኛ ፋንታ በመኮነን ሙሉና ፍጹም አድርጎናል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ያዳነንን የጌታን የደህንነት ፍቅር መተው የማንችለውና በዚህ በቀደመው ፍቅር ላይ ያለንን እምነት የማንተወው ለዚህ ነው፡፡ በመጀመሪያ በልባችን ካልተውነው በቀር ሊተው የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡
ልክ እንደዚሁ እምነታችንን በልባችን ጥልቅ ውስጥ የምንጠብቀው ከሆነ ምንም ያህል ብዙ ዛቻ፣ ማባበል ወይም ማሳቀል ቢገጥመንም እምነታችንን እስከ መጨረሻው ድረስ እንጠብቀዋለን፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን የከበረ ፍቅር በልባችን ውስጥ ካወቅነውና ይህንን ፍቅር እስከ መጨረሻው ድረስ አጥብቀን ከያዝነው ወንጌልን እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ ልንጠበቅ እንችላለን፡፡ በእምነት የሚመላለሱ ሰዎች ሰማዕትነትን መቀበል ፈጽሞ አያስቸግራቸውም፡፡
ሁላችንም ስለሚገጥመን ሰማዕትነት ኮስተር ብለን ማሰብ ይገባናል፡፡ ሰማዕትነት ስቃይንና መከራን መቋቋም ብቻ አይደለም፡፡ ሥጋችን እንደዚያ ስለሆነ ኢምንት የሆነች የመርፌ ብጣት እንኳን የሚያንገበግብ ስቃይን ትፈጥርበታለች፡፡ ሰማዕትነት እንደዚህ ያሉትን የሥጋ ስቃዮች መቋቋም ማለት አይደለም፡፡ ሰማዕትነት ሕይወታችሁን የመስጠት ጉዳይ ነው፡፡ ሰማዕትነት ማለት አካላዊ ስቃዮችን መሰቃየት ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን በተጨባጭ የራስን ሕይወት ማጣት ማለት ነው፡፡ ጸረ ክርስቶስ አምላክ ብለን እንድንጠራውና እንድንሰግድለት ሲጠይቅ ሞታችንን መርጠን እንቃወመዋለን፡፡ አምላካችን ጌታችን ብቻ ስለሆነና አምልኮዋችን የሚገባውም ለእርሱ ብቻ ስለሆነ የእርሱን ስም ለመጠበቅ ሰማዕት መሆናችን ተገቢ ነው፡፡ ይህንን እምነት በምንም ነገር ልንለውጠው አንችልም፡፡
እግዚአብሄርን የሚክደውና እንደ አምላክ ይሰገድለት ዘንድ የሚጠይቀው ጸረ ክርስቶስ በእርግጥ ሊሰገድለት ይገባዋልን? አይገባውም! ዓለምንና ዩኒቨርስን የመፍጠር ሐይል ያለው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ በሕይወትና በሞት ላይ ሥልጣን ያለውም እርሱ ብቻ ነው፡፡ በፍጥረታት ሁሉ ፊት እንከን የሌለበት፣ ሐጢያት አልባና ፈጽሞ ጻድቅ እርሱ ብቻ ነው፡፡ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ የመውሰድ ሥልጣን ያለውም እርሱ ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ጸረ ክርስቶስስ? ጸረ ክርስቶስ ያለው ብቸኛው ነገር ዓለማዊ ሥልጣን ነው፡፡ ጌታችንን በእርሱ መለወጥ የማንችለው ለዚህ ነው፡፡ ሁሉን በሚችለው አምላክ ላይ ያለንን እምነት ፈጽሞ መካድ የማንችለው ለዚህ ነው፡፡
እኛን በእርግጠኝነት ለዘላለም ደስተኞች የሚያደርገን እግዚአብሄር ነው፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ሐጢያት አልባ እንዲሆኑ የተደረጉትን ሰዎች በከበረ ሥጋ ከሙታን በማስነሳት የሺህ ዓመቱን መንግሥትና የአዲስ ሰማይና ምድርን በሮች ወለል አድርጎ ይከፍተዋል፡፡ ነገር ግን ለጸረ ክርስቶስ የሚሰግዱ ሰዎች የዘላለም ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡ ከሰይጣንም ጋር አብረው ወደ ሲዖል ይወረወራሉ፡፡ ጊዜያዊ ስቃይንና መከራን በመፍራት ብቻ ከጸረ ክርስቶስ ጋር በማበር ዘላለማዊውን ደስታችንን የምናሽቀነጥር ከሆንን ከዚህ የበለጠ ሞኝነት አይኖርም፡፡ በልባቸው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች ይህንን እውነት አውቀው ጸረ ክርስቶስን በጀግንነት በመቃወም ሰማዕት ሆነው ለመስዋዕትነታቸው ሽልማት ይሆን ዘንድ ዘላለማዊውን ደስታ ይቀበላሉ፡፡
እናንተና እኔ ሁላችንም ሰማዕት እንሆናለን፡፡ አትሳሳቱ፤ የጉራቻው (ጥቁሩ) ፈረስ ዘመን አብቅቶ የሐመሩ ፈረስ ዘመን ሲመጣ ያን ጊዜ ጸረ ክርስቶስ ብቅ ይላል፡፡ የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶችም ይጀምራሉ፡፡ ጸረ ክርስቶስ መነሳቱ በጣም የተረጋገጠ ነው፡፡ እኛ ቅዱሳኖችም ሰማዕት መሆናችን በጣም የተረጋገጠ ነው፡፡ ትንሣኤን ካገኘን በኋላም መነጠቃችን በጣም የተረጋገጠ ነው፡፡ ወደ ሺህው ዓመት መንግሥት መግባታችንም እንደዚሁ በጣም የተረጋገጠ ነው፡፡ ጸረ ክርስቶስ ሲያሳድደንና እንድንሞት ሲፈልግ በፈቃደኝነት የምንሆነው ለዚህ ነው፡፡
ተወዳጅ ከሆኑት ፊልሞች አንዱ ቁኦ ቫዲስ እምነታቸውን ለመጠበቅ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡና እየሞቱ እንኳን የምስጋና መዝሙሮችን የዘመሩ ብዙ ክርስቲያኖችን ያሳያል፡፡ ፊልሙ በራሱ ልብ ወለድ ነው፡፡ ነገር ግን ታሪካዊው ዳራ እውነት ማለትም ብዙ ክርስቲያኖች እምነታቸውን ለመጠበቅ ሕይወታቸውን መስጠታቸው እውነት ነው፡፡ ለምን እንዲህ አደረጉ? የሮም ባለሥልጣናት ከእነርሱ የጠየቁት -- እግዚአብሄርን መካድ በምትኩ ሌሎች አምላኮችን ማምለክና እምነታቸውን መጣል -- ሊቀበሉት የሚችሉት ነገር አልነበረም፡፡
የሮም ንጉሠ ነገሥታት በጠየቁት መሰረት አምላካቸውን ለውጠውት ቢሆን ኖሮ ሁሉን ነገር በለወጡ ነበር፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ አምላካቸው ሆኖ በራሱ የጭቆና ሥር ረግጦ በገዛቸውና የእርሱ አሻንጉሊቶች ሆነውም በተጋድሎ ውስጥ በሞቱ ነበር፡፡ ከሐጢያት አርነት አይወጡም፡፡ ወደ አዲስ ሰማይና ምድርም መግባት አይችሉም ነበር፡፡ እምነታቸውን ያልካዱት በፈንታው የማይቀረውን ሞት በደስታና በምስጋና የተቀበሉት ለዚህ ነው፡፡ እየሞቱ በነበረበት ጊዜም እንኳን ለጌታ ምስጋናዎችን መዘመር ችለዋል፡፡ ምክንያቱም ተስፋቸው ከሞት ጣዕራቸው ይበልጥ የላቀ ነበርና፡፡
የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መጠበቃችን በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ከሞታችን ባሻገር በአዲሱ ዓለም በሐሴትና በክብር የተሞላ ዘላለማዊ ሕይወት እንደሚጠብቀን በማመን በተስፋ መኖር ለእኛ ወሳኝ ነው፡፡
ለጌታ መከራን ተቀብላችሁ ታውቃላችሁን? ለራሳችሁ ጉድለቶች ወይም ስህተቶች ሳይሆን ለጌታ ብላችሁ በእርግጥ መከራን ተቀብላችሁ ታውቃላችሁን? መከራን የተቀበልነው ለጌታ ከሆነ ስቃያችን ሁሉ ወደ ታላቅ ደስታ ይለወጣል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ደስታ አብራርቶታል፡፡ ‹‹ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ስቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ፡፡›› (ሮሜ 8፡18) ምክንያቱም በእኛ ውስጥ የሚገለጠው የደስታ ክብር ለጌታ ከምንቀበለው የመከራ ስቃይ በጣም ስለሚበልጥ የአሁኑ ዘመን ስቃያችን ሁሉ ከእምነታችን ታላቅ ደስታና ሐሴት በታች ይቀበራል፡፡
በአጠቃላይ ሰዎች ስቃያቸውን የሚታገሱት ሊቋቋሙት እንደሚገባቸው በማሰብ ነው፡፡ ይህ አስቸጋሪና አድካሚ ተጋድሎ ነው፡፡ ትዕግስታቸው ተስፋ የሚያስቆርጡ ውጤቶችን ሲያመጣባቸው መረበሻቸው እየጨመረ ይሄዳል፡፡ መከራቸው ሁሉ ምንም የፈየደው ነገር የለም! ለእኛ ለክርስቲያኖች ግን የላቀው ነገር የጽናታችን ደስታና ሐሴት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እኛ በተስፋችንና በሽልማቶቻችን እርግጠኝነት የጸናን ነንና፡፡ ጌታን እንደ እርሱ ታማኝ አገልጋዮች ከሙሉ ልባችን ለማገልገል አእምሮዋችንን ካዘጋጀን የሚጠብቀን ደስታና መጽናናት አሁን ከምንከፍለው መስዋዕትነታችን ስቃይ በእጅጉ የላቀ እንደሚሆን እናውቃለን፡፡ ችግሮቹ ሁሉ በዚህ ደስታ ውስጥ ስለተቀበሩ ሁላችንም ሕይወታችንን ለጌታ መኖርና ስለ እርሱም ሰማዕትነትን መቀበል እንችላለን፡፡
ሰዎች ነፍስ፣ ስሜቶች፣ አስተተሳሰቦችና እምነት አላቸው፡፡ ዳግም የተወለዱ ነፍሳቶች የጌታችን መንፈስ በውስጣቸው ስለሚኖር ለጽድቃቸው መሰደድ ለሚጠብቃቸው ክብር የማይነገር ደስታና ሐሴት ያመጣላቸዋል፡፡ ነገር ግን የቀደመውን ፍቅራቸውን ቢተዉ ጌታ መቅረዛቸውን ለመውሰድ አያመነታም፡፡
የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ከሙሉ ልባቸው በደስታ የሚያገለግሉ ሰዎች ይህንን ማድረግ ቢያቆሙ ይህንን ወንጌል ሙሉ በሙሉ አሽቀንጥረው ባይጥሉትም ቀስ በቀስ ወንጌልን የማገልገል ደስታቸውንና የቀደመውን ፍቅራቸውን ትተዋል ማለት ነው፡፡ የግል እምነታቸውን የሙጥኝ ብለው ይዘው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ወንጌልን በመስበክ የማይመኩ ከሆነና ለመዳን ምን እንደሚያስፈልግ ግልጽ የሆነ መረዳት -- በመስቀል ላይ የፈሰሰው ደም ለደህንነት በቂ እንዳልሆነ -- ከሌላቸው እምነታቸው ይበረዛል፡፡ ወደ ሰማዕትነትም አይደርሱም፡፡ ያን ጊዜ እግዚአብሄር መቅረዛቸውን ከስፍራው ይወስዳል፡፡
ወንጌልን በደስታና በጽናት የሚያገለግሉ ሰዎች ሰማዕትነትን በፈቃዳቸው መቀበል ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ፈጽሞ የቀደመውን ፍቅራቸውን አልተዉምና፡፡ እነዚህ ሰዎች በክርስቶስ ፍቅር በማመናቸውና እርሱንም በመስበካቸው በእግዚአብሄር ስለተባረኩ ሰማዕት መሆን ይችላሉ፡፡ ተሰጥዖ ወይም ችሎታ ያላችሁ መሆኑ ከቁም ነገር የሚገባ አይደለም፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የማታሰራጩ ከሆናችሁ ቤተክርስቲያን ከስፍራዋ ትወሰዳለች፡፡ ይህ እግዚአብሄር እንድንረዳው የሚፈለግብን አስፈላጊ መልዕክት ነው፡፡ ይህንን እውነት ብንረዳና ብናምነው በዘመኑ መጨረሻ ልባችንን ማደስና ለጌታ ስም ሰማዕት መሆን እንችላለን፡፡
እምነታችንን የሚደግፈው መሰረታዊ ሐሳብ ምንድነው? የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ባይኖር ኖሮ የእምነት ሥራዎቻችን ጥቅም ምን ይሆን ነበር? እምነታችንን የምንጠብቅበት ምክንያቱ እግዚአብሄር ስለወደደንና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በክንዶቹ ስላቀፈን ነው፡፡ ይህ ፍቅር እኛን የሚያከብር የማይለወጥ ፍቅር ስለሆነ እምነታችንን መጠበቅ፣ እርሱን መስበክና ማሰራጨት መቀጠል እንችላለን፡፡
ድክመቶች ቢኖርብንም እስከ መጨረሻው ድረስ ወደ እግዚአብሄር መሮጥ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል አድኖናልና፡፡ በዚህ ወንጌል ውስጥም የክርስቶስ ፍቅር ይገኛልና፡፡ ሁላችንም በጉድለቶች የተሞላን ነን፡፡ ነገር ግን በጌታችን ፍቅር በተሞላው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ስለተሸፈንን ወንድሞቻንንና እህቶቻችንን፣ የእግዚአብሄርን አገልጋዮችና በዓለም ላይ ያሉትን ሰዎች ሁሉ እንወዳለን፡፡ በመሰረቱ ፍጹም የሆነ ፍቅር ሰው የሚደርስበት አይደለም፡፡ በመካከላችን ፍቅር ስለሌለ ራስ ወዳዶች ሆነን ራሳችንን ከመውደድ በስተቀር ሌላ ማንንም ሰው መውደድ ያዳግተናል፡፡ ብዙ ሰዎች ከውጪ በሚታይ ነገር ተታልለዋል፡፡ አርቴፊሻል በሆነ የሚያብለጨልጭ አስመሳይ ነገር ተስበዋል፡፡ ሰዎችን ባላቸው ቁሳዊና ውጫዊ ንብረቶች ይመዝኑዋቸዋል፡፡ በእውነተኛ ምዕመናን መካከል ግን የእግዚአብሄር ፍቅር አለ፡፡ ወንጌልን የጌታችንን ፍጹም ፍቅር እንድናሰራጭ የሚያስችለን ይህ ነው፡፡
ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ ጉድለቶቻችንን ሁሉ ለመቀበል ተጠመቀ፡፡ እኛን ለማዳንም ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አነጻን፡፡ ታዲያ የእግዚአብሄር ልጆች ያደረገንን የቀደመው ፍቅሩን እንዴት እንተወዋለን? በብዙ ረገዶች ጎዶሎዎች እንሆን ይሆናል፡፡ ነገር ግን በዚህ እውነት የሚያምን እምነት ፈጽሞ ሊጎድለን አይገባም፡፡ ይህንን ወንጌል ሙሉ በሆነው እምነታችን መስበክ አለብን፡፡ በመከራው ወቅት እጅግ የሚያስፈልገው በትክክል በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምን ይህ እምነት ነው፡፡ ችግሮችና መከራዎች ሲገጥሙን እምነታችንን የመጠበቅና ችግሮችን የማሸነፍ ጉልበት የሚመጣው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ብቻ ነው፡፡ በቀን ተቀን ሕይወታችን በሚገጥሙን በርካታ ትግሎች ብንደክምም ፊታችን በደስታ የሚያበራው በዚህ ወንጌል ሐይል ነው፡፡ ይህ የጌታችን ፍቅር ነው፡፡
ሰዎች አንዳንድ ጊዜ በሕግ አክራሪነት ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ እግዚአብሄር ባደረጉት ነገር እንደባረካቸው ያስባሉ፡፡ ይህ ፈጽሞ ውሸት ነው ማለቴ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ጌታ የሚወዱትን እንደሚወድ ተናግሮዋልና፡፡ እግዚአብሄር ሐጢያት አልባ እንድንሆን እስከሚያደርገን ድረስ አብዝቶ የወደደን እኛ ባደረግነው ነገር የተነሳ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ የሰጠንን ተስፋዎች በሙሉ ስለሚያውቅና ሐጢያቶቻችንንም በሙሉ ስለሚያውቅ ፍጹም በሆነው ፈቃዱና ፍቅሩ አቀፈን፤ አዳነንም፡፡ በደስታ መኖር የምንችለው ከእርሱ ባርኮቶች የተነሳ ነው፡፡ ለጌታ መስራት የምንችለው እግዚአብሄር ሕዝቡና አገልጋዮቹ ስላደረገን ክብሩን ስላለበሰንና ወንጌልን ለሌሎች ስለምንሰብክ ነው፡፡ ጊዜው ሲመጣም ለስሙ ሰማዕት እንሆናለን፡፡ እነዚህን ነገሮች በሙሉ እንድናደርግ ያስቻለን እርሱ ነው፡፡
በቁኦ ቫዲስ ፊልም ውስጥ ሴቶቹ ሰማዕታት ለሞት ተላልፈው በተሰጡ ጊዜ ለጌታ የምስጋና ዝማሬዎችን የሚዘምሩበትን ጉልበት ያገኙት ከየት ነበር? ጉልበትን ያገኙት ከጌታችን ፍቅር ነበር፡፡ የክርስቶስ ፍቅር ትልቅ ስለነበር ሰማዕትነትን በምስጋና መቀበል ቻሉ፡፡
ይኸው መርህ በእኛም ሕይወት ላይ ይተገበራል፡፡ ሕይወታችንን የምንኖረው ጌታ እንድንኖር ስላስቻለን ነው፡፡ የእግዚአብሄር ልጆችና አገልጋዮች ሆነን የምንኖረው ከምግባሮቻችን የተነሳ አይደለም፡፡ ይህ ይገባን ዘንድ ያደረግነው ነገር የለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስንሰናከልም እርሱን እስከ መጨረሻው ድረስ ልንከተለው የምንችለው እግዚአብሄር ለእኛ ባለው የማይለወጥ ፍጹም ፍቅርና በዚህ ፍቅር ላይም ባለን እምነት ነው፡፡ ይህ ጉልበት የእኛ ሳይሆን የእግዚአብሄር ጉልበት ነው፡፡ ሰማዕትነት ተግባራዊ መሆን የሚችለው ሙሉ ባደረገን በእግዚአብሄር ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ሰማዕትነትን መቀበል የምንችለው በእግዚአብሄር ጸጋ ብቻ ነው፡፡ ሰማዕት እንድትሆኑ የሚያስችላችሁ እግዚአብሄር የመሆኑን ይህንን እውነት አስታውሱ፡፡ እናንተ ልታደርጉት የምትችሉት አንዳች ነገር ያለ ይመስል ራሳችሁን ለሰማዕትነት ለማዘጋጀት በመሞከር ጊዜያችሁን አታባክኑ፡፡ ጌታን እስከ መጨረሻው እስትንፋሳችን ድረስ እንድናመሰግነው የሚያስችለን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያለን እምነታችን ብቻ ነው፡፡
ጌታ በእስያ ላሉት ለሰባቱ ቤተክርስቲያኖች እንዲህ አለ፡- ‹‹ድል ለነሣው በእግዚአብሄር ገነት መካከል ካለው የሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ፡፡›› የሕይወት ዛፍ የሚገኘው በአዲሱ ሰማይና ምድር ነው፡፡ በዚያም የእግዚአብሄር ዙፋን አለ፡፡ ቤቶች በከበሩ ድንጋዮች ተገንብተዋል፡፡ የሚፈስሰውም የሕይወት ውሃ በዚያ ይገኛል፡፡ ድል ለነሱት እግዚአብሄር ከእርሱ ጋር በፍጽምና ለዘላለም ይኖሩ ዘንድ ይህንን የእርሱን ገነት ሊሰጣቸው ተስፋ ገብቷል፡፡
ድል የነሱት ይህንን የሚያደርጉት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ባላቸው እምነት ነው፡፡ ከዚህ ወንጌል ውጪ ሌላ ማንኛውም ነገር በሰው ጉልበት ሳይሆን በእግዚአብሄር ጉልበት ብቻ ሊደረስበት የሚችለውን ድል መንሣት አዳጋች ያደርገዋል፡፡ ድል እንድንነሳ የሚያስችለን ጉልበት የሚመጣው ከእግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ፤ የእግዚአብሄርም ፍቅርና ማዳንም ምን ያህል ታልቅ እንደሆነ መገንዘብና መደነቅ ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ሰማዕትነትን እንድንቀበል እምነትን የሚሰጠን ይህ ወንጌል ነውና፡፡ ሁላችንም ደካሞች፣ ተስጥዖ የሌለን፣ ችሎታ አልባዎች፣ ብቃት አልባዎች፣ ሞኞችና አላዋቂዎች እንሆን ይሆናል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ሐይል አለን፡፡ ምክንያቱም በልባችን ውስጥ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል አለና፡፡
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ያመኑ ሰዎች ስሞች በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎዋል፡፡ በሌላ በኩል ስሙ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፈ እያንዳንዱ ሰው በሰይጣን ፊት ወድቆ ይንበረከካል፡፡ በዲያብሎስ ፊት የማይጎነበሱት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉ ብቻ ናቸው፡፡ ስማችሁ በዚህ የሕይወት መጽሐፍ ላይ በእርግጠኝነት ተጽፎ እንደሆነ ማረጋገጥ አለባችሁ፡፡
ሰማዕት የምንሆነው በእምነታችን ጌታችን በሰጠን የቀደመው የክርስቶስ ፍቅር ነው፡፡ ሰማዕትነታችንን ያለ ጭንቀት ወይም ፍርሃት መጠበቅ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም በውስጣችን የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ሰማዕትነታችንን የምንጋፈጥበትን ጉልበት ይሰጠናልና፡፡ የሰማዕትነት ስቃይ እኛን ከሚጠብቀን የሰማይ ክብር ጋር ሊወዳደር ስለማይችል በሞታችን ፊት አንርበተበትም፡፡ በፋንታው የከበረውን ወንጌል ለመጠበቅ ስንል ሰማዕትነታችንን በድፍረት እንቀበላለን፡፡ አሁን እንዴት ሰማዕት መሆን እንደምንችል ያሉንን ግራ መጋባቶች በሙሉ መተው አለብን፡፡ ሰማዕት የምንሆነው በጥረታችን ሳይሆን በእግዚአብሄር ነውና፡፡
ቀጣዩ ማስታወቂያ አንድ ቀን በድምጽ ማጉያዎች እንደሚነገር እርግጠኛ ነኝ፡፡ ‹‹ውድ ዜጎች ምልክቱን ለመቀበል የመጨረሻው ቀን ዛሬ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ ላደረጋችሁልን ትብብር በጣም እናመሰግናለን፡፡ ለእናንተ ምልክቱን መቀበል በጣም ጥሩና ወሳኝ ነው፡፡ ምክንያቱም የአገሪቱ ጽኑ ሥርዓት ነውና፡፡ ስለዚህ እባካችሁ ወደ ከተማይቱ አዳራሽ መጥታችሁ በተቻለ መጠን በፍጥነት ምልክቱን ተቀበሉ፡፡ ደግሜ እላችኋለሁ፤ ይህ ምልክቱን ለመቀበል የመጨረሻው ቀናችሁ ነው፡፡ ዛሬ እስከተወሰነው ጊዜ ድረስ ምልክቱን የማይቀበሉ ሰዎች ክፉኛ ቅጣት ይደርስባቸዋል፡፡ ይህንን ግልጽ ለማድረግ እስከ አሁን ድረስ ምልክቱን ያልተቀበሉትን ሰዎች ስም እጠራለሁ፡፡›› ይህ ልብ ወለድ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ነገሮች በቅርቡ ወደፊት በእርግጠኝነት ይሆናሉ፡፡
የጥንቷ ቤተክርስቲያን ምዕመናኖች እርስ በርሳቸው የሚተዋወቁት በዓሣ ምልክት ነበር፡፡ በእነርሱ መካከል የይለፍ ቃሉ ይህ ነበር፡፡ እኛም እንደዚሁ ሰማዕትነትን ለመቀበል አንዳችን የሌላችንን እምነት ማደፈፋፈር እንችል ዘንድ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ማወቅ የምንችልበትን ምልክት ማዘጋጀት ይገባናል፡፡
ሰማዕትነት በራሳችን ጥረት ልንደርስበት የምንችለው ነገር ስላልሆነ ጭንቀቶቻችንን አስወግደን በድፍረት ልንጋፈጠው ይገባናል፡፡ የጽድቅ ሞታችንን በሚመለከት ምንም የሚያስፈራን ነገር የለም፡፡ እኛ ማድረግ ያለብን በዚህ ምድር ላይ ሳለን ለጌታ ብቻ መኖር ነው፡፡ ለአምላካችን ስም ሰማዕትነትን ለመቀበል የታጨን መሆናችንን ስለምናውቅ ራሳችንን ለጌታ መስጠት እንችላለን፡፡ ሐብታችሁን የማጣት ፍርሃት አድሮባችሁ ከሰማዕትነት ለመሸሽ ብትሞክሩ የበለጠ ስቃይና መከራ እንደሚገጥማችሁ መገንዘብ ይገባችኋል፡፡ እናንተ ለክርስቶስ የምትሰዉ መሆናችሁን አውቃችሁ እስከ መጨረሻው ድረስ ሕይወታችሁን ለጌታ የምትኖሩ የእምነት ሰዎች መሆን አለባችሁ፡፡
ሰማዕት እንደምንሆን ስናውቅ በእምነታችን፣ በአስተሳሰባችንና በሕይወታችን ይበልጥ ጠቢብ እንሆናለን፡፡ ይህ እውቀት አሁን ከዓለም ጋር ያሉ ቁርኝቶቻችንን በሙሉ ወደኋላ እንድንተው በመፍቀድ ስንፍናችንን የሚፈውስ መድሃኒት ነው፡፡ ሕይወታችንን መጣል ይኖርብናል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ለጌታ እንኖራለን፡፡ የእግዚአብሄር ሐይል ሰይጣንን ወደ ጥልቁ እስከሚጥለው ድረስ ላዳነን ጌታ እንኖራለን፡፡ ሰይጣንንና ጸረ ክርስቶስን እንዋጋለን፡፡ የድሉን ክብር ሁሉም ለእግዚአብሄርና ለእርሱ ብቻ እንሰጣለን፡፡ እግዚአብሄር በእኛ ሊከብር ይፈልጋል፡፡ በእምነታችን ብዙ ነገርን ለሰጠን ለእርሱ ክብርን እንድንሰጥ የፈቀደልንን ጌታ አመሰግነዋለሁ፡፡
ጌታ ሊወስደን በቶሎ እንደሚመጣ እናምናለን፡፡ በመጨረሻው ዘመን ብዙ ነፍሳቶች ወደ እግዚአብሄር ሲመለሱ እግዚአብሄር ሁሉንም በእቅፉ ተቀብሎ ይወስዳቸዋል፡፡ እግዚአብሄር በዮሐንስ ራዕይ 3፡10 ላይ ለፊላደልፊያ ቤተክርስቲያን እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹የትዕግስቴን ቃል ስለጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ፡፡›› እግዚአብሄር በእርግጠኝነት የተስፋ ቃሉን ይፈጽማል፡፡
እግዚአብሄር ‹‹የትዕግስቴን ቃል ስለጠብቅህ›› ሲል የቅዱሳንን የታመነ ሕይወት መጠቆሙ ነው፡፡ ይህ ማለት እነርሱ ሌሎች ስለ እነርሱ ምንም ቢናገሩ ወይም በእነርሱ ላይ ምንም ቢያደርጉ እምነታቸውን አጽንተው ይዘዋል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር ‹‹ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ›› ሲል የትዕግስቱን ቃል የጠበቁት ሰዎች ከእምነት ፈተናዎች ይገላገላሉ ማለቱ ነው፡፡
በሌላ አነጋገር የመከራውና የሰማዕትነቱ ዘመን ሲመጣ በቀን ተቀን የአገልግሎትና የጸሎት ሕይወታችንን በታማኝነት ስንቀጥል እግዚአብሄር ይወስደናል፡፡ ሰማዕታት በመሆናችን ላይ አተኩረን ስናስብ ልባችን ከቆሻሻ ሁሉ ይነጻል፡፡ ከዚህ የተነሳ እምነታችንም ይበልጥ ይጠነክራል፡፡ ሰማዕትነትን በመቀበላችን ከፈተናው ሰዓት እንደምንጠበቅ የእግዚአብሄርን ተስፋ በማስታወስ በእግዚአብሄር ፊት የአሁኑን ዘመን የእምነት ሕይወታችንን መኖር ይገባናል፡፡ በአጭሩ በእምነታችን መኖር ይገባናል፡፡
የዛሬው ዘመን የራዕይ ዘመን ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ቸል በማለት በቅድመ መከራ ንጥቀት ትምህርት የሐሰት እምነታቸውን ሙጥኝ ብለው የያዙ ብዙ ሞኝ ክርስቲያኖች አሉ፡፡ የመጨረሻው ቀን ሲመጣ ምን ያህል ተሳስተው እንደነበር ያውቃሉ፡፡ የተጽዕኖና የሥልጣን ዘመናቸውም ተቆጥሮዋል፡፡ እኛ ማድረግ የሚኖርብን እግዚአብሄር የተስፋ ቃሉን የሚፈጽም በመሆኑ ተስፋችን እርግጠኝነት መኖር ይገባናል፡፡
ወደ ታላቁ መከራ አጋማሽ ላይ ስንደርስ እምነታችንን ለመጠበቅ ሰማዕት እንሆናለን፡፡ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ከመጀመራቸው በፊትም በእግዚአብሄር ወደ አየር እንነጠቅና ወደ ሺህው ዓመት መንግሥት እንገባለን፡፡ ከክርስቶስ ጋር አብረን የመግዛቱ ተስፋ ተግባራዊ ሲሆን የዚህ ምድር ስቃያችን ሁሉ እኛን በሚጠብቁን ሽልማቶች ይካሳል፡፡ ያን ጊዜ ወደ ዘላለማዊ አዲስ ሰማይና ምድር መግባታችንም በማይነገር ደስታ ያጥለቀልቀናል፡፡ ዛሬ ይህ የእግዚአብሄር ተስፋ ይፈጸማል በሚል ተስፋ በእምነት ለጌታ እንኖራለን፡፡ ጌታችን ተስፋዎቹን በሙሉ እንደሚፈጽም በማመን በከበረው ሰውነታችን ከእርሱ ጋር ለዘላለም መኖር የምንችልበትን ቀን በጉጉት በመጠበቅ እንኖራለን፡፡
ፍጹም የሆነ የሐጢያት ስርየትን የምናገኝበትን ወንጌል ስለሰጠን፣ በእርሱ ያለንን እምነት የምንጠብቅበትን ሰማዕትነት እንድንቀበል ስላስቻለንና የእርሱ ብሩካን በሆኑት መካከል እንድንቆም ስላደረገን ጌታን አመሰግነዋለሁ፡፡
የኤፌሶን ቤተክርስቲያን ቅድመ ታሪክ፡፡
በሮማውያን መንግሥት በትንሽዋ እስያ ክልል የምትገኘው ታላቋ የወደብ ከተማ ኤፌሶን የንግድና የሃይማኖት ተግባራት ማዕከል ነበረች፡፡ በጥንቷ ቤተክርስቲያን ዘመን እያደገች የነበረች ዓለም ዓቀፍ ከተማ ነበረች፡፡ ከእርስዋ በስተ ሰሜን ሰርምኔስ ከእርስዋ በስተ ደቡብ ደግሞ መላጥያ ይገኙ ነበር፡፡ አፈ ታሪክ እንደሚለው ጀግናዋ የጦርነት አማልክት አማዞን ከተማይቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ12ኛው ምዕተ ዓመት ገንብታ የአቴንስ ባለ አክሊል መስፍን ለሆነው አንድሮክሉስ ሰጠችው፡፡
በቁሳዊ አነጋገር ኤፌሶን ሐብታም ከተማ ነበረች፡፡ በጣም ዓለማዊ ከተማ ነበረች ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር የኤፌሶንን ቤተክርስቲያን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንዳታጣ እስከ መጨረሻው ድረስ በመዋጋት ሰይጣንን እንድታሸንፍ የነገራት ለዚህ ነው፡፡ የእግዚአብሄር የእውነት ቃል ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብ አለብን፡፡ እምነታችንንም በማናቸውም መንገድ መጠበቅ አለብን፡፡
እግዚአብሄር በሐዋርያው ዮሐንስ በኩል ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን ጻፈ፡- ‹‹በቀኝ እጁ ሰባቱን ከዋክብት የያዘው በሰባቱም የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚሄደው እንዲህ ይላል፡- ሥራህንና ድካምህን ትዕግስትህንም አውቃለሁ፡፡ ክፉዎችንም ልትታገስ እንዳትችል እንዲሁም ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉትን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፡፡ ታግሰህማል፤ ስለ ስሜም ብለህ ጸንተህ አልደከምህም፡፡›› የኤፌሶን ቤተክርስቲያን ስለ ሥራዎችዋ፣ ስለ ድካምዋና ስለ ትዕግስቷ፣ ክፋትን ስለ መቃወምዋ፣ ሐሰተኛ ነቢያቶችን ምርምራ ስለ ማጋለጥዋ፣ ስለ ስሙ ስትል በጽናትና በትዕግስት ያለ መሰልቸት በመልፋትዋ ተመስግናለች፡፡
ነገር ግን የኤፌሶን ቤተክርስቲያን የስህተት አድራጎቶችን በማድረግዋም ተወቅሳለች፡፡ ‹‹ዳሩ ግን የምንቅፍብህ ነገር አለኝ፡፡ የቀደመውን ፍቅር ትተሃልና፡፡ እንግዲህ ከወዴት እንደወደቅህ አስብ፡፡ ንስሐም ግባ፡፡ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፡፡ አለዚያ እመጣብሃለሁ፤ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ፡፡ ነገር ግን ይህ አለህ፤ እኔ ደግሞ የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ ጠልተሃልና፡፡ መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡ ድል ለነሣው በእግዚአብሄር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ፡፡››
ከላይ በተጠቀሰው ምንባብ ላይ እግዚአብሄር ኒቆላውያንን እንደሚጠላ ተናግሮዋል፡፡ እዚህ ላይ ኒቆላውያን የሚያመለክቱት እግዚአብሄርን፣ ቤተክርስቲያኑንና እውነቱን የሚቃወመውን የተወሰነ የምዕመናን ቡድን ነው፡፡ ኒቆላውያን በትክክል ያደረጉት ነገር በጴርጋሞን ቤተክርስቲያን ላይ ባነጣጠረው ቀጣይ ምንባብ ውስጥ ይበልጥ በዝርዝር ተብራርቷል፡፡
የኒቆላውያን የተሳሳቱ አድራጎቶች፡፡
ዮሐንስ ራዕይ 2፡14 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ የምንቀፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ፡፡›› የዚህ ምንባብ የግርጌ ማስታወሻ የሞዓባውያን ንጉሥ የሆነው የባላቅ ታሪክ በተመዘገበበት በዘሁልቁ መጽሐፍ ምዕራፍ 22 ላይ ይገኛል፡፡
እስራኤሎች ከግብጽ ከወጡ በኋላ በከንዓን ወዳለው የሞዓብ ሜዳዎች ላይ በደረሱበት ጊዜ ‹‹በሬ የምድሩን ሣር በልቶ እንደሚጨረስ›› የምድሪቱን ሰባት ነገዶች አሸንፈው ነበር፡፡ ባላቅ ይህንን ድል ከሰማ በኋላ አምላካቸውን ፈራ፡፡ የሞዓባውያንም ዕጣ ፋንታ አስቀድመው ድል የተመቱት የከንዓን ነገዶች ዓይነት እንደሚሆን ፈርቶ ነበርና፡፡ ባላቅ እስራኤሎች እነርሱን ድል እንዳይመቱ ለመከላከል መንገድን ለመቀየስ ሲሞክር ሐሰተኛው ነቢይ በለዓም በእርሱ ጥያቄ መሰረት እስራኤሎችን እንዲረግምለት ጠራው፡፡
በለዓም ሐሰተኛ ነቢይ ነበር፡፡ አሕዛቦች ግን እርሱ የእግዚአብሄር ባርያ ነበር ብለው አሰቡ፡፡ እርሱ የሊቀ ካህኑ የአሮን ዘርም ሆነ ሌዋዊ አልነበረም፡፡ የሞዓባውያን ንጉሥ ባላቅ ግን በዓለም የባረካቸው እንደሚባረኩ የረገማቸው ደግሞ እንደሚረገሙ አምኖዋል፡፡ በዚያን ወቅት በለዓም ሐሰተኛ ነቢይ ቢሆንም በምድሪቱ ሁሉ የታወቀ አስማተኛ በመሆን ገንኖ ነበር፡፡
በለዓም ግን ንጉሥ ባላቅ እንዲያደርግ የጠየቀውን ለማድረግ አልተገደደም፡፡ ምክንያቱም እስራኤሎች የእግዚአብሄር ሕዝብ ስለነበሩ በለዓም እስራኤሎችን ለመርገም ከእግዚአብሄር ዘንድ ፈቃድ ያልነበረው ብቻ ሳይሆን እንደዚያ ለማድረግ መሞከርም መጨረሻው በራሱ ላይ እርግማንን ማምጣት ብቻ ነበር፡፡ በለዓም በእግዚአብሄር መንፈሳዊ ሐይል በመደናገጡ እስራኤሎችን ከመባረክ በስተቀር አንዳች ነገር ማድረግ አልቻለም፡፡ ባላቅ በዚህ ተቆጥቶ እርሱ እነርሱን ማየት ከማይችልበት ቦታ ሆኖ እስራኤሎችን እንዲረግም በለዓምን ጠየቀው፡፡
በለዓም ከባላቅ ከፍተኛ መጠን ያለው ሐብት ስለተቀበለ በምላሹ በእስራኤሎች ላይ እርግማንን የሚያመጣበትን መንገድ አስተማረው፡፡ ዕቅዱ እስራኤሎች ለሐጢያቶቻቸው በእግዚአብሄር ይቀጡ ዘንድ እነርሱን በሞዓባውያን ግብዣ ላይ እንዲገኙ ጋብዞ ሴቶቻቸውን ለእነርሱ በማቅረብ እንዲያመነዝሩ መፈተን ነበር፡፡ ሐሰተኛው ነቢይ በለዓም በእስራኤሎች ላይ ጥፋትን ለማምጣት ባላቅን ያስተማረው ይህንን ነው፡፡
እግዚአብሄር በለዓምን እንደጠላ የተናገረው በለዓም ገንዘብን የወደደ ሰው በመሆኑ ነበር፡፡ በዘመኑ የክርስቲያን ማህበረሰብ ውስጥ በለዓምን የመሰሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እንዲያውም ሁሉም ሐሰተኛ ነቢያቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ አሁንም ድረስ የተመሰገኑና የተከበሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን በለዓም የተከተለው ቁሳዊ ሐብትን ነበር፡፡ ገንዘብ ሲሰጠው ባረከ፤ ገንዘብ ሳይሰጠው ረገመ፡፡ በዘመኑ የክርስቲያን ማህበረሰብ ውስጥ የእግዚአብሄር አገልጋዮች መሆን የሚጠበቅባቸው እጅግ ብዙዎች ልክ እንደ በለዓም መሆናቸው አሳዛኝ ነው፡፡ በእግዚአብሄር የሚያምኑ ሰዎች መጨረሻቸው ቁሳዊ ትርፎችን ማግኘት ብቻ በሚሆንበት ጊዜ መጨረሻቸው ሐሰተኛ ነቢያቶች መሆን ነው፡፡ እግዚአብሄር ኒቆላውያንን የጠላው ለዚህ ነው፡፡
በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያንና በአገልጋዮቹ ላይ ጥፋትን የሚያመጣው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁን? የገንዘብ ፍቅር ነው፡፡ በዓይናቸው ፊት ቁሳዊ ትርፎችን ብቻ የሚከተሉ ሰዎች በእግዚአብሄር ፊት የራሳቸውን ጥፋት ይጋፈጣሉ፡፡
በለዓምን የተከተሉ ቤተክርስቲያኖች፡፡
ዛሬም እንደ ሐዋርያቶች ዘመን የበለዓምን መንገድ የሚከተሉ ብዙ ዓለማዊ ቤተክርስቲያኖችና ሐሰተኛ አገልጋዮች አሉ፡፡ ከተከታዮቻቸው ገንዘብን ለመሰብሰብ ማንኛውንም መንገድ ሁሉ ይጠቀማሉ፡፡ ለምሳሌ የአማኙ መዋጮ የእምነቱ መለኪያ ይመስል ጉባኤው እምነቱን በመንፈሳዊነቱ ሳይሆን በቁሳዊ መዋጮዎቹ ያሳይ ዘንድ እርስ በእርሱ እንዲፎካከር የሚያደርግ ይህ ዓይነት አጓጊ ግፊት አለ፡፡ ለቤተክርስቲያን ብዙ መዋጮ ያደረጉ ሰዎች እምነት ጥቂት ከሰጡት ሰዎች የሚበልጥ መሆኑን በመጠቆም የዚህ ዓይነቱን ብልሹ ግፊት የማደፋፈሩ ብቸኛው ዓላማ ቤተክርስቲያንን ማበልጠግ ነው፡፡
ምዕመናኖች ከቅን ልባቸው እግዚአብሄርንና ወንጌሉን ለማገልገል ከወሰኑ ይህ በእርግጥም ግሩም ነገር ነው፡፡ ነገር ግን እንደ በለዓም ያሉ ሐሰተኛ ነቢያት ሆዳቸውን ለመሙላት ምዕመናኖችን ያጠምዳሉ፡፡ ‹‹እኔ አስራቶቼን በታማኝነት ከፈልሁ፡፡ እግዚአብሄርም በንግድ ሥራዬ አማካይነት አስር ዕጥፍ በረከቶችን ሰጠኝ›› በማለት በቁሳዊ ምስክርነቶች ተከታዮቻቸውን ለፉክክር ያነሳሱዋቸዋል፡፡ ያልጠረጠሩት ምዕመናኖች በበለዓም ተታልለው ወደ እውነተኛው እምነት የሚያደርሰው ይህ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ይህ ግን ወደ መንፈሳዊና ቁሳዊ ድህነት፤ ወደ ሐሰተኛ ትምክህትና በመጨረሻም ራሳቸውን ወደ ማጥፋት የሚመራ መንገድ ነው፡፡
‹‹የኒቆላውያን ሥራ›› የበለዓም ሥራ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ በለዓም ስስታም በመሆኑ በእስራኤሎች ዘንድ ማሰናከያን ያደርግ ዘንድ እንዳስተማረው በዘመኑ የክርስትና ማህበረሰብ ውስጥ የእግዚአብሄር አገልጋዮች ነን የሚሉ ብዙዎች ፍላጎታቸው የጉባኤዎቻቸው ኪሶች ብቻ ናቸው፡፡ በእነዚህ ሐሰተኛ ነቢያቶች የተታለሉ ሰዎች ሐብታቸውን ሁሉ ለእነዚህ ሐሰተኛ እረኞች ከሰጡ በኋላ ባዶ እጃቸውን ቀርተዋል፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ወደ አእምሮዋቸው ተመልሰው ያመኑት ነገር ፈጽሞ ውሸት መሆኑን ማወቃቸው ነው፡፡ በመጨረሻ ሐሰተኛውን ቤተክርስቲያን ተብለው በሚጠሩት ውስጥም ቢሆን የተለመደ መሆኑ ነው፡፡ ብዙ ምዕመናን በዚህ ማጭበርበሪያ በበለዓም ተታልለው ቤተክርስቲያን ትተው ወጥተዋል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሄር የኒቆላውያንን ሥራዎች እንደሚጠላ ይነግረናል፡፡ ኒቆላውያንን የምንከተል ከሆንን በእግዚአብሄር ላይ ያለንን እምነት እናጣለን፡፡ እኛ እግዚአብሄር የሰጠን ብዙ ምስክርነቶች አሉን፡፡ እነዚህ ሁሉ በመንፈስ የሚያበለጥጉ መዝገቦች ናቸው፡፡ ምስክርነቶችን በመጠቀም ቁሳዊ ትርፎችን መከተል ግን ፈጽሞ ልንርቀው የሚገባን ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም ራሱ እግዚአብሄር የጠላው የኒቆላውያን መንገድ ነውና፡፡
እምነት ከጠባይ ጋር፡፡
እግዚአብሄር በእስያ ለሚገኙት ለሰባቱም ቤተክርስቲያኖች በሙሉ ስለ ኒቆላውያን ሥራዎች አስጠንቅቆዋቸዋል፡፡ በተጨማሪም ድል የነሳ ከሕይወት ዛፍ እንደሚበላም ተስፋ ሰጥቶዋቸዋል፡፡ ለቤዛነቱ ማመስገናችንና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማሰራጨትም መደረግ ያለበት ትክክለኛው ነገር መሆኑን በማወቃችን ጌታን ስናገለግል የምናገለግለው በእምነት ነው፡፡ ለሌሎች ታይታ ስንል ወይም በማንኛውም መንገድ ጥሩ መስለን ለመታየት ብለን እግዚአብሄርን አናገለግልም፡፡ እንዲህ ማድረግ እውነተኛ አገልግሎትም ሆነ እውነተኛ እምነት አይደለም፡፡ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ ስለ እነዚህ የኒቆላውያን ምግባሮች በጣም መጠንቀቅ አለብን፡፡ ጌታ ሰባቱን የእስያ ቤተክርስቲያኖች በሙሉ ስለ ኒቆላውያን ያስጠነቀቃቸው ለዚህ ነው፡፡
ብዙዎቹ ቤተክርስቲያኖች ማለትም ዳግመኛ ያልተወለዱ ቤተክርስቲያኖች በጣም ትልቅና በጣም ፈጣን ሆነው ያደጉት ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁን? ያደጉት እነዚህን ቤተክርስቲያኖች የገነቡት ሐሰተኛ እምነትና ሐሰተኛ ምስክርነቶች ስለነበሩ ነው፡፡ የእግዚአብሄር አገልጋዮች የራሳቸውን ሆድ ለመሙላት ሲሉ በጭራሽ መንጎቻቸውን መጠቀም የለባቸውም፡፡
እውነተኛው እምነት እግዚአብሄር በኢየሱስ ጥምቀት፣ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙና በእኛ ምትክ በወሰደው ፍርድ በሰጠን ደህንነት ማመን ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ ቤተክርስቲያኖች ዳግመኛ የተወለዱ ወይም ያልተወለዱ የጉባኤዎቻቸውን ኪሶች ለመበርበር ምስክርነቶችን ይጠቀማሉ፡፡ እውነተኛ ምስክርነቶች እምነታችሁን የሚያንጹና እግዚአብሄርን የሚያከብሩ፤ ሐሰተኛ ምስክሮች ደግሞ የራሳችሁ ወጥመድ እንደሚሆኑ ለማወቅ ጠንቃቃና ጠቢብ መሆን አለባችሁ፡፡
በዛሬው ዓለም ውስጥ ያሉ እጅግ ባለጠጋ የሆኑ ቤተክርስቲያኖች የሚመሩት በለዓምን በመሰሉ አገልጋዮች ነው፡፡ የበለዓምን መንገድ የሚከተሉ የቤተክርስቲያን መሪዎች የተከታዮቻቸውን ቁሳዊ ሐብት ለመዝረፍ ብቻ ቤተክርስቲያኖቻቸውን ይጠቀሙባቸዋል፡፡ እንደ በለዓም ያሉ ክርስቲያን መሪዎች በቁሳዊ ምስክርነቶች ፉክክር ውስጥ በማስገባት ከተከታዮቻቸው ገንዘብን ይዘርፋሉ፡፡ እኔ ምግባሮቻቸውን ክፉኛ እጠላዋለሁ፡፡
እውነተኛ የእምነት ሕይወት የሚጀምረው ከእምነት እንጂ ከሌላ አይደለም፡፡ ሰይጣን ያጠመዳቸውን የኒቆላውያንን ወጥመዶች ለማምለጥ ጠቢባን መሆን አለብን፡፡ እያንዳንዱ ሰው የኒቆላውያን ምግባሮች ምን እንደሆኑ ማወቅ አለበት፡፡ ስስታምነታቸው ገደብ በሌለው የሰይጣን አገልጋዮችም ፈጽሞ መታለል የለብንም፡፡ በተለይ የእግዚአብሄር አገልጋዮች በዚህ ረገድ እጅግ በጣም ጠንቃቆች መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ቀሳውስቶችንም ይጨምራል፡፡ ቀሳውስቶች በቁሳዊ ሐብታቸው ከመጠን በላይ የሚጨነቁ ከሆነ -- ምን ዓይነት መኪናዎችን እንደሚነዱ፣ ቤቶቻቸው ምን ያህል ትልቅ መሆን እንዳለባቸው፣ ምን ያህል ሪል ስቴት እንዳላቸው፣ የባንክ ተቀማጮቻቸውም ምን ያህል የደለቡ እንደሆኑ -- መጨረሻቸው ቤተክርስቲያኖቻቸውን ማበላሸትና በኒቆላውያን ጎዳና ላይ መንዳት ይሆናል፡፡
እግዚአብሄር በእስያ ያሉትን ቤተክርስቲያኖች ይህንን ጉዳይ በተለየ መንገድ እንዲጠነቀቁበት ነግሮዋቸዋል፡፡ የበለዓም ዓይነት እምነት ያለው ሰው የሚሻው ቁሳዊ ትርፎችን፣ በራስ መመካትንና ውሎ አድሮም የአንድ አምልኮተ ሰብ መስራች መሆንን ማሰብ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ቁሳዊ ሐብትን መሻት የለባትም፡፡ እግዚአብሄር የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የሚከተሉትን ሰዎች እንደሚባረክ ተስፋ ስለሰጠን ቁሳዊ ሐብታችንን ወንጌልን ለመስበክ ልንጠቀምበት እንጂ በዚህ ምድር ላይ ልናጠራቅመው አይገባንም፡፡
ሐሳዊ እረኞችን አተቀበሉዋቸው፡፡
ዳግመኛ የተወለዱ ምዕመናኖችም ቢሆኑ በኒቆላውያን ወጥመዶች ከተያዙ ይኮንናሉ፡፡ በመጀመሪያ የእነዚህ መሪዎች እምነት ግሩምና ጠንካራ ነው ብለው ያስቡ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሐሰተኛ እረኞች መታለል በመጨረሻ ያጠፋቸዋል፡፡
እግዚአብሄር ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን መልአክ የኒቆላውያንን ሥራ እንደሚጠላ ነገረው፡፡ በኒቆላውያን የተጠመደ ሰው ሁሉ መኮነኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ ዳግመኛ የተወለደ ምዕመን ቢሆን የእግዚአብሄር አገልጋይ ቢሆን ወይም ማንም ሌላ ሰው ቢሆን በኒቆላውያን ከተጠመደ መጥፋቱ እርግጠኛ ነው፡፡ መጥፎ እረኛ መንጎቹን ወደ ሞት እንደሚነዳ ሁሉ ሐሰተኛ ነቢያቶችም እርግማኖችን ያመጣሉ፡፡
እግዚአብሄር አገልጋዮቹን ‹‹በጎቼን መግቡ›› ብሎ የነገራቸው ለዚህ ነው፡፡ እረኞች ከአደጋ በመጠበቅና የሚያስፈልጋቸውን በማድረግ በጎችን እንደሚያሰማሩ ሁሉ የእግዚአብሄር ባሮችም ምዕመናንን ማሰማራት አለባቸው፡፡ እረኞች እንደመሆናቸው መንጎቻቸው እንዳይጠፉ ማረጋገጥ፣ በፊታቸው ምን ዓይነት አደጋዎች እንዳደፈጡ ማወቅና ወደ እነዚህ የአደጋ ሥፍራዎች እንዳይቀርቡ መከላከል ይገባቸዋል፡፡
በትክክል በጎችን ከሚያረቡ ሰዎች እንደሰማሁት በጎች እጅግ አስቸጋሪ ከሆኑ እንስሶች አንዱ ናቸው፡፡ እኛም በእግዚአብሄር ፊት እንደ እነዚህ አስቸጋሪ በጎች አይደለንምን? እግዚአብሄር እኛን ለመግለጥ የበጎችን ምሳሌ ሲጠቀም ጥሩ ምክንያት ነበረው፡፡ ምክንያቱም እኛ በመሰረታዊ ማንነታችን ምን ያህል አስቸጋሪዎች እንደሆንን በሚገባ ያውቃልና፡፡
እግዚአብሄር በእስያ ላሉት ለሰባቱ ቤተክርስቲያኖች በተደጋጋሚ ስለ ኒቆላውያን ሥራ፣ ስለ ኤልዛቤልና ስለ በለዓም የተናገረው ለምንድነው? ድል ለነሱት ከሕይወት ዛፍ ይበሉ ዘንድ እንደሚሰጣቸው ተስፋ የገባው ለምንድነው? ይህንን ያደረገው ከሐሰተኛ ነቢያቶች ማታለያዎች እንጠበቅ ዘንድ ሊያስተምረን ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል በማሰላሰል ራሳችንን ‹‹እውነተኛው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ምንድነው?›› ብለን መጠየቅ ይገባናል፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ከእያንዳንዱ ሰብዓዊ ትምህርቶች ጋር መቀላቀልና በሚመች መንገድ ማቅረብ ወንጌል ነው ማለት አይደለም፡፡ በዘመኑ ክርስትና ውስጥ ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው፣ ባማረ መንገድ የተቀናበሩና የቀረቡ ብዙ ስብከቶች አሉ፡፡ ብዙ ታዋቂ ሰባኪዎች በእነርሱ ፋንታ ሆነው ስብከቶችን የሚጽፉላቸው የተካኑ ንግግር ጸሐፊዎች አሉዋቸው፡፡ እነርሱ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር በሌላ ሰው የተዘጋጁትን እነዚህን ጽሁፎች ማንበብ ብቻ ነው፡፡
በኒቆላውያን ወጥመድ ውስጥ በጭራሽ መውደቅ የለብንም፡፡ ዳግም የተወለደች ቤተክርስቲያን ቁሳዊ ትርፎችን ላለመከተል እጅግ በጣም ጠንቃቃ መሆን አለባት፡፡ በተለይ አገልጋዮች ሁልጊዜም ንቁ መሆን አለባቸው፡፡ በጉባኤው ውስጥ ያለ እያንዳንዱም ሰው እንደዚሁ መንቃት አለበት፡፡ ከቤተክርስቲያን አባሎች ገንዘብን ለመሰብሰብ መሞከር ቤተክርስቲያንን በቁሳዊ ብክነት ማሸበረቅና የአምልኮ መቅደስ በመሆን ፋንታ ቤተ መንግሥት የሚመስሉ የቤተክርስቲያን ሕንጻዎችን መገንባት -- የጌታ ምጽዓትም በጣም እንደቀረበ መናገር -- ሁሉም የሐሳዊ እምነት ምግባሮች በግልጽ የኒቆላውያን ሥራዎች ናቸው፡፡
በተለይ ከሐሰተኛ እረኞች መጠንቀቅ አለብን፡፡ የእነርሱን እምነት በመከተልም ፈጽሞ መታለል እንደሌለብን እርግጠኞች መሆን አለብን፡፡ በአጭሩ ቅዱሳን ገንዘብን መውደድ የለባቸውም፡፡ በፋንታው ልንወደውና ልንጠብቀው የሚገባን የውሃውንና የደሙን ወንጌል የቀደመውን የእግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ ከእርሱ ጋር እስከምንገናኝበት ቀን ድረስ እርሱ በክርስቶስ ውሃና ደም ያዳነን የመሆኑን እውነት አጥብቀን በመያዝ የታመነውን ሕይወታችንን መኖር አለብን፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ሞቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ የወሰደ የመሆኑን የእግዚአብሄር ቃል ማመን አለብን፡፡
ኒቆላውያንን የሚከተሉ ሰዎች በፍጹም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል አይሰብኩም፡፡ ገንዘብን በመሰብሰብ ብቻ እንጂ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ሥራዎች አይደሰቱም፡፡ እነዚህ በእስራኤላውያን ፊት ማሰናከያን ያደረጉና ወደ ጥፋታቸው የነዱዋቸው የዘመኑ በለዓም ናቸው፡፡ ይህንን ማስታወስ ይገባችኋል፡፡
በለዓም ውሎ አድሮ በኢያሱ ተገደለ፡፡ የኢያሱ መጽሐፍ እንደመዘገበው ይህ ሐሰተኛ ነቢይ በኢያሱ ሰይፍ የተገደለው እስራኤሎች ከንዓንን ድል ባደረጉ ጊዜ ነበር፡፡ በለዓም የተገደለው የእግዚአብሄር እውነተኛ አገልጋይ ስላልነበረ ነው፡፡ ምስኪን የሆኑ ምዕመናኖችን ለመበዝበዝና የራሳቸውን ሆድ ለመሙላት የክርስቶስን ስም የሚጠቀሙ ሁሉ የዘመኑ በለዓም ናቸው፡፡ በለዓም የራሱን ስስት ለመሙላት እያንዳንዱን አማራጭ መንገድ እንደተጠቀመ ማስታወስ ይገባናል፡፡
እግዚአብሄር ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን አገልጋዮች እንዲህ ሲል ተናገረ፡- ‹‹ድል ለነሣው በእግዚአብሄር ገነት መካከል ካለችው የሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ፡፡›› በሌላ አነጋገር ይህ ምንባብ የሚሰናከሉና የሚሸነፉ ይሞታሉ ማለቱ ነው፡፡ የበለዓምን መንገድ መከተል ጥፋት የራስን የሞት መንገድ መከተል ነው፡፡ እግዚአብሄር በኒቆላውያን ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ የማስጠንቀቂያ ቃሉን ሰጥቶናል፡፡ ለዚህም አመሰግነዋለሁ፡፡ በቁሳዊ ፈተናዎች ተወስዳችሁ በስስታችሁ ምክንያት መጨረሻችሁ በእግዚአብሄር መተው እንዳይሆን ልባዊ ተስፋዬና ጸሎቴ ነው፡፡