Search

សេចក្តីអធិប្បាយ

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[17-2] ትኩረታችንን በእርሱ ፈቃድ ላይ ማድረግ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 17፡1-8 ››

ትኩረታችንን በእርሱ ፈቃድ ላይ ማድረግ
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 17፡1-8 ››
 
ዮሐንስ ራዕይ 17፡1-5 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሰባቱንም ጽዋዎች ከያዙ ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፡- ና በብዙም ውሃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ፡፡ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ፤ በምድርም የሚኖሩ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ ብሎ ተናገረኝ፡፡ በመንፈስም ወደ በረሀ ወሰደኝ፤ የስድብም ስሞች በሞሉበት ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶችም ባሉበት በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ፡፡ ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጎናጽፋ፣ በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮች፣ በዕንቆችም ተሸልማ ነበር፤ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኩሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች፡፡ በግምባርዋም ምስጢር የሆነ ስም፡- ታላቂቱ ባቢሎን የጋለሞታዎችና የምድር ርኩሰት እናት ተብሎ ተጻፈ፡፡››
 
ከላይ በተጠቀሰው ምንባብ ላይ የተገለጠችው ጋለሞታ የዚህን ዓለም ሐይማኖት ታመለክታለች፡፡ ይህም እነርሱ ጌታ በሰጠው የዓለም ነገሮችን ቁሳዊ መትረፍረፍ ከልክ በላይ በሆነ ቅንጦት እንደተሞሉ ይነግረናል፡፡ እነርሱ ራሳቸውን በሁሉም ዓይነት ቅንጦቶች በወርቅ የአንገት ጌጦችና በዕንቁ የጆሮ ጉትቻዎች ተሸልመዋል፡፡ ሁሉንም ዓይነት ዘይትም ተቀብተዋል፡፡ ምንባቡ በእጅዋ የወርቅ ጽዋ እንደያዘችና እርሱም በሚያስጸይፍና በዝሙትዋ ርኩሰት እንደተሞላ ይነግረናል፡፡ እግዚአብሄር ለዮሐንስ ያሳየው ይህንን ነው፡፡
 
ይህ ምንባብ የሚነግረን ሰይጣን በሰዎች ነፍስ እንደሚዶልትና በዓለም ነገሮች ሰክረው ለእርሱ እንዲያጎበድዱ እንደሚሻ ነው፡፡ የዓለም ነገሥታቶችም ሁሉ እንደዚሁ በሰይጣን አማካይነት በዓለም ነገሮች ሰክረዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱን ሰው የዓለምን ዝሙት ወይን ጠጅ ጠጥቶ ሰክሮዋል፡፡
ሰዎች በዚህ ዓለም ማዕበል፣ በተድላዎቹና በቁሳዊ ስስቱ ሲሰክሩ ሰይጣን ግቦቹን ያሳካል፡፡ እውነቱ የእርሱ ግብ ሰዎች ወደ እግዚአብሄር እንዳይመለከቱ መከልከሉ ነው፡፡ ሰይጣን ይህንን ለማድረግ ነፍሳቸው በዚህ ዓለም ቁሳዊ ነገሮች እንድትሰክር ያደርጋል፡፡ ይህንን እውነት መረዳት አለብን፡፡
 
በቁሳዊነት ወጥመድ ውስጥ የማይወድቅ ሰው በዚህ ዓለም ላይ የለም፡፡ እያንዳንዱ ሰው ቁሳዊ ነገር ላይ ይወድቃል፡፡ የዚህ ዓለም ዘመናዊ አዝማሚያዎች በሙሉ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያሉና የሚመሩ ናቸው፡፡ ሁሉም የራሱ የሆነ ዘይቤ እንዳለው ያስባል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በስተ ጀርባ አንድ ተጽዕኖ የሚያሳድር አካል ያለ ሲሆን እርሱም ሌላ ማንም ሳይሆን ሰይጣን ነው፡፡ በቁሳዊ ነገር ውስጥ ሰጥመን መኖር የሌለብን ለዚህ ነው፡፡ በፋንታው ግን በእርሱ ቃል በመነቃቃትና የእግዚአብሄርን ሥራዎች በመስራት መኖር አለብን፡፡
እግዚአብሄር በሐዋርያው ዮሐንስ በኩል የገለጠን የራዕይ ቃል እውነት ነው፡፡ ታዲያ እግዚአብሄር በዚህ ቃል ሊነግረን እየሞከረ ያለው ነገር ምንድነው? ጌታችን እየነገረን ያለው ይህንን ዓለም እንድንቃወም እንጂ ራሳችንን በውስጡ እንዳናሰምጥ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ለእኛ ለቅዱሳን እየነገረን ያለው እግዚአብሄርን በልባችን እንድናስበውና እንድናምነው ነው፡፡
 
1ኛ ዮሐንስ 2፡15 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፡፡ ማንም ዓለምን ቢውድድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም፡፡›› ልባችን የዓለምን ቁሳዊ ነገሮች የሚወድድ ከሆነ እግዚአብሄር በልባችን ውስጥ ሊያድር አይችልም፡፡ ነገር ግን ልባችን የዓለምን ነገሮች ወርውሮ ሲጥል ያን ጊዜ እግዚአብሄር በልባችን ውስጥ ያድራል፡፡ በዚህ ዓለም ነገሮች ውስጥ ሰጥመን ሕይወታችንን መኖር አይገባንም፡፡ እርሱ ሊመራን የሚችለው የጌታችንን ቃልና ዓላማዎች ስናሰላስል ብቻ ነው፡፡
እኛ በማናቸውም ጊዜ አሳባችንን ልንቀይር እንችላለን፡፡ የዓለም ነገሮች ወደ ልባችን ውስጥ ለመግባት ሲሞክሩ ሁልጊዜም አሻፈረኝ ልንላቸው ይገባናል፡፡ ያን ጊዜ የዓለምን ርኩሰቶች በሙሉ ከልባችን ማራቅ እንችላለን፡፡ ልባችንም ወዲያውኑ በጌታ ልብ ውስጥ ይሰጥማል፡፡ ጌታችን ከእኛ የሚፈልገው ምንድነው? እንድናደርግ የሚነግረንስ ምንድነው? እንዲህ ያሉ ያማሩ አስተሳሰቦች በልባችን ውስጥ እንደሚበቅሉ ማረጋገጥና ዓለማዊ ነገሮችንም ከልባችን ውስጥ መደምሰስ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር ብዙ በረከቶችን ሰጥቶናል፡፡ አሁን በቀሪው ዘመናችን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመላው ዓለም ለሚኖሩ ሕዝቦች መስበክ ይገባናል፡፡ ስለዚህ ችላ ሳንል ትኩረታችንን በእርሱ ፈቃድ ላይ እናደርጋለን፡፡ መንፈሳዊ ሥራዎችን በማሰብ በልባችን ውስጥ የሚገኙትን የዓለም ነገሮች ማስወገድ እንችላለን፡፡
 
እኛ ቅዱሳኖች የዓለምን ነገሮች ማስወገድ አለብን፡፡ ጌታ ዳግመኛ እስኪመጣ ድረስ የክርስትና ሕይወታችንን በእምነት መኖር አለብን፡፡ በቀሪው ሕይወታችን በእርሱ ፊት እስክንቆም ድረስ ጌታ በአደራ የሰጠንን ማድረግ አለብን፡፡ እርሱ እናደርግ ዘንድ የፈቀደልንን ማናቸውንም ሥራዎች በመስራት ጌታን መውደድና በእምነት መኖር አለብን፡፡