Search

တရားဟောချက်များ

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 3-3] ስለ ጌታ አምላክን ታመሰግናላችሁን? ‹‹ ሮሜ 3፡10-31 ››

‹‹ ሮሜ 3፡10-31 ››
‹‹እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፡- ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ እግዚአብሄርንም የሚፈልግ የለም፡፡ ሁሉም ተሳስተዋል፤ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፡፡ ቸርነትን የሚያደርግ የለም፤ አንድ ስንኳ የለም፡፡ ጉሮሮአቸው እንደተከፈተ መቃብር ነው፡፡ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፡፡ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፡፡ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፡፡ እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፡፡ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፡፡ የሰላምንም መንገድ አያውቁም፡፡ በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሄርን መፍራት የለም፡፡ አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሄር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን፡፡ ይህም የሕግን ሥራ በመስራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፡፡ ሐጢያት በሕግ ይታወቃልና፡፡ አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሄር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፡፡ እርሱም ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሄር ጽድቅ ነው፡፡ ልዩነት የለምና ሁሉ ሐጢአትን ሰርተዋልና የእግዚአብሄርም ክብር ጎድሎአቸዋል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ፡፡ እርሱንም እግዚአብሄር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተሰርያ አድርጎ አቆመው፡፡ ይህም በፊት የተደረገውን ሐጢያት በእግዚአብሄር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፡፡ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፡፡ ትምክህት እንግዲህ ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል፡፡ በየትኛው ሕግ ነው? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፡፡ በእምነት ሕግ ነው እንጂ፡፡ ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና፡፡ ወይስ እግዚአብሄር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ ደግሞ አምላክ አይደለምን? አዎን የተገረዘን ስለ እምነት ያልተገረዘንም በእምነት የሚያጸደቅ አምላክ አንድ ስለሆነ የአሕዛብ ደግሞ አምላክ ነው፡፡ እንግዲህ ሕግን በእምነት እንሽራለንን? አይደለም፤ ሕግን እናጸናለን እንጂ፡፡››
 
 

ሰዎች በሥጋ የሚመኩበት ምንም ነገር የላቸውም፡፡

 
ሮሜ 3፡10-12 እንዲህ ይናገራል፡- ‹‹ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ እግዚአብሄርንም የሚፈልግ የለም፡፡ ሁሉም ተሳስተዋል፤ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፡፡ ቸርነትን የሚያደርግ የለም፤ አንድ ስንኳ የለም፡፡›› ከሥጋ የተነሳ ሁላችንም በእግዚአብሄር ፊት በሐጢያቶች የተሞላን ነው፡፡ ሰው በሥጋው በራሱ ጻድቅ መሆን ይችላልን? በእግዚአብሄር ፊት በተፈጥሮ ጻድቅ የሆነ ሥጋ ሊኖር ይችላልን? ሰው በሥጋው በፍጹም ጻድቅ ሊሆን አይችልም፡፡ ሥጋ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ከሐጢያቶቹ ሳይድን በፍጹም ጻድቅ ሊሆን ይችላል፡፡
 
ሐጢያቶቻቸው የተደመሰሱላቸው ሰዎች በሥጋቸው የሚመኩበት ምንም ነገር የላቸውም፡፡ እኛም ሐጢያቶቻችን የተደመሰሱልን ሰዎች በሥጋችን ከመሳሳት አንቆጠብም፡፡ መልካም የማድረግ አቅምም የለንም፡፡ እግዚአብሄርን ካላገለገልንና መንፈሳዊ ሥራን ካልሰራን በስተቀር ጥሩ ሕይወት ኖረናል ማለት አንችልም፡፡ ኢየሱስ ‹‹ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፡፡ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው›› (ዮሐንስ 3፡6) እንዳለው በመንፈስ ምሪት ለመመላለስ ሲፈልግ ሥጋ ግን የእርሱን ፍትወት ለማርካት ብቻ ይሻል፡፡ ሥጋ በፍጹም ወደ መንፈስ ሊቀየር አይችልም፡፡
 
ሰዎች ሁሉ ሐጢያተኛ ሆነው ይወለዳሉ፡፡ ከሐጢያት በታች ይኖራሉ፡፡ በከንቱ ይሞታሉ፡፡ ውሎ አድሮም ሲዖል ባለው የእሳት ባህር ውስጥ ይጣላሉ፡፡ እግዚአብሄር ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ሊያድናቸው አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ባይልከው ኖሮ ተስፋ ባልኖራቸውም ነበር፡፡ አንዳች ተስፋ ያለን ከሆንን ይህ የሆነው እግዚአብሄር እውነተኛ ተስፋ ስለሰጠን ነው፡፡ በእግዚአብሄር ባይሆን ኖሮ ጽድቅም ሆነ ተስፋ ባልኖረን ነበር፡፡ እናንተንና እኔን ጨምሮ በዚህ ዓለም ላይ ያለውን የእያንዳንዱን ሰው ዕጣ ፋንታ ብንመረምር ይህ እውነት ነው፡፡
 
‹‹የፍጥረት ሁሉ ጌቶች›› ተብለን ብንጠራም ፈቃዳችን ምንም ይሁን ሐጢያተኞች ሆነን ለመወለድ፣ በከንቱ ለመኖርና ወደ ሲዖል ለመውረድ የታጨን ነን፡፡ እኛ ምንኛ አላፊዎች ነን! ብዙውን ጊዜ የሰዎችን አላፊ ሕይወት በአንድ ቀን ተወልዶ ሕይወቱን ሙሉ ያቺን አንድ ቀን ከኖራት በኋላ ሞቶ ትቢያ ከሚሆነው የእሳት ራት ጋር እናመሳስለዋለን፡፡ ያለ ኢየሱስ ተስፋ የለንም፡፡ ሰዎች ምንም ያህል ታዊቂ ቢሆኑ ወይም ዝናዎቻቸው ምንም ያህል ታላላቅ ቢሆኑ በሕይወት ዘመናቸው የሚያደርጉዋቸው አስፈላጊ ነገሮች መወለድ፣ መብላት፣ መጠጣት፣ መሞትና ሲዖል መውረድ ብቻ ናቸው፡፡ በከንቱ ኖረን በከንቱ እንጠፋለን፡፡ ዘላለማዊ ፍርድንም ለመቀበል ታጭተናል፡፡
 
ነገር ግን እግዚአብሄር ሐጢያትን እንድናውቅ ሕጉን ከሰጠን በኋላ በኢየሱስ በኩል በሆነው የሐጢያቶች ስርየት በኩል በነጻ አጸደቀን፡፡ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በመውሰድም በኢየሱስ ጥምቀትና ደም ለሚያምኑት ማስተሰርያ ይሆን ዘንድ የተሰቀለውን አንድያ ልጁን ኢየሱስን ላከው፡፡ እግዚአብሄር ኢየሱስን ማስተሰርያ አድርጎ በማቆም አጸደቀን፡፡
 
የሐጢያትን ስርየት ያገኙ ሰዎች ጻድቃን ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው? የሐጢያቶችን ስርየት ያገኘን እኛ ጽድቃችን ከሥጋ ነውን? በእግዚአብሄር ፊት የምንመካበት ነገር አለን? በሥጋ የምንመካበት ምንም ነገር የለንም፡፡ ከጌታ አምላክ የተነሳ ተደስተናል፡፡ ለእርሱም ምስጋናን እናቀርባለን፡፡ ምክንያቱም የሐጢያቶችን ስርየት የደህንነትን ማረጋገጫና የዘላለም ሕይወትን አግኝተናል፡፡
 
እኛ የሐጢያቶችን ስርየት ያገኘን ሰዎች ያለ እግዚአብሄር ምንም አይደለንም፡፡ የሰው ሥጋ የሚመካበት አንዳች ነገር አለውን? ሥጋ ጻድቅ ነውን? በ70-80 የዕድሜ ዘመናችን ውስጥ የምንመካበት አንዳች ነገር አለን? ሥጋ በእርግጥም የሚመካበት አንዳች ነገር የለውም፡፡ ሥጋ በእግዚአብሄር ፊት የሚመካበት 0.1% ቢሆን እንኳን የሚመካበት የለውም፡፡
 
 

ልንመካበት የምንችልበት ብቸኛው ነገር የእግዚአብሄር ጽድቅ ነው፡፡

 
የምንመካው ጌታ ከሐጢያቶቻችን ስላዳነን ነው፡፡ እንዲህ ተብሎ ተጽፎዋል፡- ‹‹አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሄር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦዋል፡፡›› ጌታ ዘላለማዊ ሕይወታችንና አዳኛችን ነው፡፡ እርሱ አጽድቆናል፡፡ ኢየሱስ ፈጽሞ ስላዳነን ጻድቃን ነን፡፡ በሥጋ ወይም በሕግ ሥራዎች የምንመካበት ምንም ነገር የለንም፡፡ ጌታ ጽድቅን ሁሉ ለመፈጸም በመጠመቁና የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በማንጻቱ አመስጋኞች ነን፡፡ እርሱንም እናወድሰዋለን፡፡
 
የእምነትን ጽድቅ አግኝተናል፡፡ ጌታ አንድም ሰው ሳያስቀር በዓለም ላይ ያሉትን ሰዎች ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው አድኖዋቸዋል፡፡ የእግዚአብሄር ማዳን ደስተኞች አድርጎናል፡፡ ተስፋም ሰጥቶናል፡፡ ከጌታ በቀር የምንመካበት ምንም ነገር የለንም፡፡ እኛ በእግዚአብሄር ፊት በጽድቃችን ከመመካታችን በላቀ መልኩ አሳፋሪዎች ነን፡፡ ብዙ ሰዎች በምግባሮቻቸውና በራሳቸው ጽድቅ እየተኮፈሱ ጥረቶቻቸውን በእግዚአብሄር ፊት ለማቅረብ ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን በራስ ጽድቅ የተጠቀለሉት እኔነቶቻቸው የመርገም ጨርቅ ናቸው፡፡ እርስ በርሳቸው ወይም ለራሳቸው የሚመኩበት ነገር ይኖራቸው ይሆናል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ግን ምንም የሚመኩበት ነገር የላቸውም፡፡
 
ጌታ ለእኛ ፍጹም አዳኝ ነው፡፡ ‹‹ኢየሱስ›› ማለት ‹‹አዳኝ›› ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ እንደሆነም ተናግሮዋል፡፡ ይህ ማለት በሰዎች አምሳያ የመጣው አዳኝ አምላክ ነበር ማለት ነው፡፡ እኛ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ›› ብለን እንጠራዋለን፡፡ ኢየሱስ አዳኛችንና አምላካችን ነው፡፡ እኛም እናመሰግነዋለን፡፡ እናወድሰዋለን፡፡ በፊቱም የጽድቅ ሥራዎችን እንሰራለን፡፡ ታማኝ ሕይወትን እንመራለን፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር ሙሉ በሙሉ አድኖናልና፡፡ የጽድቅ ሥራዎችን መስራት የሚችሉት በእግዚአብሄር የሚያምኑ ምዕመናን ብቻ ናቸው፡፡
 
ያለ ሐጢያት ሆነን የጽድቅ ሥራ መስራት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ጌታ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወስዶ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ያነጻን አዳኛችን ሆንዋል፡፡ በራሳችን የሐጢያትን ችግር መፍታት አንችልም፡፡ ሰው በሥጋው መልካም ምግባሮችን በማድረግ ሐጢያቶቹን ማስወገድም ሆነ የእግዚአብሄርን ጽድቅ መጠበቅ አይችልም፡፡
 
እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ደምስሶዋል፡፡ እኛም ጽድቅን ከእግዚአብሄር ተቀብለናል፡፡ እኛ ጻድቃን ነን፡፡ ሥጋችንን በሰናይ ምግባሮች በመቀደስ የራሳችንን ጽድቅ መጠበቅ እንችላለንን? እንዲህ ማድረግ የሚችል ሰው ካለ ለኢየሱስ ታላቅ ወንድም/እህት ይሆናል፡፡ ኢየሱስ እንደዚህ ላለ ሰው በጭራሽ አዳኝ ሊሆን አይችልም፡፡ የራሳችንን ጽድቅ በሥጋችንና በስሜቶቻችን አቅም ሳናውቀው የመጠበቅ ደመ ነፍስ አለን፡፡ ሥጋ የሚንቀሳቀሰው በደመ ነፍስ ነው፡፡ አደጋ ሲገጥመን አደጋ ውስጥ እንዳንወድቅ በደመ ነፍስ እንታገላለን፡፡ ጣፋጭ ምግብ ስናይ ብዙ መብላት እንፈልጋለን፡፡ የሚያስደስት ነገር ስናይ ደግሞ መጫወት እንፈልጋለን፡፡
 
ሥጋ በደመ ነፍስ ስለሚንቀሳቀስ የእግዚአብሄርን ጽድቅ በደመ ነፍስ መጠበቅ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን አንችልም፡፡ መዳናችን በራሳችን ጽድቅ አልተገኘም፡፡ ሕግን በሚገባ በመጠበቅ፣ በሥጋ መልካም ምግባሮችን በማድረግ ወይም ራሳችንን ለእግዚአብሄር ቀድሰን በመስጠት በፍጹም ልንድን አንችልም፡፡ የእኛ ጀግንነት በእግዚአብሄር ጽድቅ ውስጥ 0.1% እንኳን ቦታ የለውም፡፡ የጸደቅነው እግዚአብሄር በሰዎች አምሳል ወደ ዓለም መጥቶ እኛን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ፈጽሞ ያዳነንን ጽድቅ ሁሉ ለመፈጸም ከመሰቀሉ በፊት በአጥማቂው ዮሐንስ መጠመቁን በማመናችን ነው፡፡
 
 
እኛን ያዳነን ጌታ ፍጹም አዳኝ ነው፡፡
 
ጌታችን ሰዎች ከመሞታቸው በፊት የፈጸሙዋቸውን ሐጢያቶች በሙሉ በመውሰድ ጽድቅን ሁሉ ፈጸመ፡፡ ፍጹም አዳኝም ሆነላቸው፡፡ እኛንም አጸደቀን፡፡ እግዚአብሄር ጽድቅን ሁሉ በመፈጸም ፍጹማን አደረገን፡፡ እግዚአብሄር መንፈሳዊ ሥራ እንድንሰራ አስቻለን፡፡ ሥጋችን የሥጋ ሥራ በመስራት ቢቀጥልም የእርሱን ጽድቅ ተቀብለን ሐጢያት አልባ በመሆን መንፈሳዊ ሥራ የመስራት መብት አለን፡፡ ነገር ግን ሐጢያቶቻቸው ገና ያልተደመሰሱላቸው ሰዎች መንፈሳዊ ሥራ መስራት አይችሉም፡፡ ያንን ለማድረግም ብቃት የላቸውም፡፡
 
እኛ መንፈሳዊ ነገሮች ለማድረግ በእግዚአብሄር ብቁ ሆነናል፡፡ አሁን የመንፈስን ነገሮች ማድረግ እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር አዳኛችን መሆኑ ምንኛ ድንቅ ነው! ሁሉን ነገር እንደዚሁም እኛን ሰዎችን የፈጠረው እግዚአብሄር የደህንነት ጌታ ሆኖ ተገልጦልናል፡፡ ምክንያቱም እርሱ ወደ ዓለም መጥቶ ጽድቅን ሁሉ ፈጽሞዋልና፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ባለው ግንኙነት ጌታችንና ያዳነን አዳኛችን ሆንዋል፡፡
 
ደካማና አቅም የሌለው ሰው ቢያድነን ኖሮ ደህንነት የተሟላ አይሆንም ነበር፡፡ በአንድ ወቅት የመውደቅ አጋጣሚ ሊከሰት ይችላል፡፡ እኛን ያዳነን ሰው ግን እንዲህ ያለ ሰው አይደለም፡፡ እርሱ አምላክና ሁሉን የፈጠረ ፈጣሪ ነው፡፡ ዮሐንስ 1፡3 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሁሉ በእርሱ ሆነ፡፡ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም፡፡›› ኢየሱስ ማነው? አዳኝ ነው፡፡ እርሱ አምላክ ፈጣሪ ነው፡፡ እግዚአብሄር ፈጽሞ አድኖናል፡፡ እርሱ ስላዳነን መዳናችን ፍጹም ነው፡፡ ለዘላለምም ይዘልቃል፡፡ እርሱ ፈጣሪ በመሆን ፋንታ ከፍጥረታት አንዱ ቢሆን ኖሮ ደህንነታችን ከንቱ ይሆን ነበር፡፡ ዘለቄታም አይኖረውም፡፡ ጽድቁም ልክ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፡፡ ሰው ያማረ የቆዳ ልብስ ቢለብስ ኳስ ቢጫወት ወይም በመንሸራተቻ ቢንሸራትት ያ ልብስ ቶሎ አያረጅም፡፡
 
እኛን ከሐጢያቶቻችን ያዳነን ጌታ እንከን ያለበት አይደለም፡፡ እኛን ያዳነን ጌታ ፍጹም የሆነ አምላክ ነው፡፡ የምዕመናን ሥጋ ደካማ ቢሆንም ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ለመሸከም የተጠመቀው፣ የተሰቀለው፣ ዳግመኛም ከሙታን የተነሳውና በእግዚአብሄር ቀን የተቀመጠው የኢየሱስ ማዳን በፍጹም ከንቱ አይሆንም እግዚአብሄር የሰጠን ደህንነት ይህ ነው፡፡
 
 
እኛ በእምነት እንኖር ዘንድ የራሳችን ጽድቅ መፍረስ አለበት፡፡
 
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በራሳቸው ጽድቅ የተሞሉ ሰዎች በተለያዩ መከራዎች ውስጥ ሆነው እንደኖሩ ተጽፎዋል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር ጽድቃቸውን በእነዚያ መከራዎች መስበር ፈልጎዋልና፡፡ በነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ ‹‹ነገር ግን የኮረብታ መስገጃዎች አልተወገዱም›› የሚሉ ብዙ ምንባቦች አሉ፡፡ ይህ ማለት ሰው በሥጋው ፍጹም አይደለም፤ የሚጸድቀው በጌታ በማመን ነው ማለት ነው፡፡
 
ውድ ቅዱሳኖች ምንም ያህል ደካሞች ብንሆንም አምላካችን ፈጽሞ አድኖናል፡፡ በራሳችን ጽድቅ ብቻ የምንኖር ከሆንን እንሞታለን፡፡ እግዚአብሄር አምላክ ግን ፈጽሞ ከሐጢያቶቻችን አድኖናል፡፡ ምንም ያህል ደካሞች ብንሆንም በጌታ ጽድቅ የምንኖር ከሆንን በእኛ ይደሰታል፡፡ ኢሳይያስ 53፡5 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቆሰለ፡፡ ስለ በደላችንም ደቀቀ፡፡›› እግዚአብሄር በደሎቻችንን ለአንዴና ለመጨረሻ አስወግዶዋቸዋል፡፡ ጽድቃችን ይፈርሳል ብለን በመፍራት ጠንቃቆች መሆን አያስፈልገንም፡፡
 
አንዳንድ ሰዎች ከመስተዋት ከተሰሩ ዕቃዎች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ስብዕናዎች አሉዋቸው፡፡ ወደ አሜሪካ የሄደች አንዲት እህት አውቃለሁ፡፡ በጣም ጨዋ ነበረች፡፡ ከእርስዋ ጋር ስገናኝ በአነጋገርዋ ቁጥብ ነበረች፡፡ ፈጽሞ አትራገምም፡፡ የሐጢያቶችን ስርየት ያገኘች ብትሆንም ቁልጭ ያለ ሐጢያተኛ ሰው ስታገኝ ‹‹ኦ! አቶ መጥፎ ሰው›› ማለት ለምዳለች፡፡ የራስዋ በሆነ ጽድቅ የተሞላች ብትሆንም በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመን የሐጢያቶችን ስርየት ተቀብላለች፡፡ ነገር ግን የሐጢያቶችን ስርየት ከተቀበለች በኋላም ገናም በራስዋ ጽድቅ የተሞላች ስለነበረች ጽድቅዋ እንዳይፈርስ በመፍራት ራስዋን እንዳታስገምት በጣም ትጠነቀቅ ነበር፡፡ እርስዋን የመሰሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ጽድቃቸው ይዘልቃልን? ፈጥኖ ይፈርሳል፡፡
 
የዳናችሁ ብትሆኑም ሥጋችሁ ድካሞች አሉትን? አዎ፡፡ ፍጹም የሆነ መልካም ሕይወት ትኖራላችሁን? የሐጢያቶችን ስርየት ከተቀበልን በኋላ ፍጹም ሆነን መኖር የምንችለው በመንፈስ ስንመላለስ ብቻ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፊት መልካም ተቀባይነት ለማግኘት ብቃት ያላቸው የጽድቅ ሥራዎች ብቻ ናቸው፡፡ በመንፈስ ስንሰራና ስንመላለስ እንመሰገናለን፡፡ በሥጋ የምንመካበት ምንም ነገር የለም፡፡ የሐጢያቶች ስርየት ባገኙ ቅዱሳን መካከል ያሉ አንዳንድ ሰዎች እንዳይፈርስባቸው በመፍራት ጽድቃቸውን ለመጠበቅ ይሞክራሉ፡፡
 
ነገር ግን ጌታ በእነርሱ አይደሰትም፡፡ ሆነም ቀረም የሰው ጽድቅ ይፈርሳል፡፡ ፈጥኖ ቢፈርስ የተሻለ ነው፡፡ ከ10 ወይም ከ20 ዓመታት በኋላ መፍረሱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ውስጣዊው ሰው በእምነት መኖር ይችል ዘንድ ውጫዊው ሰው አሁኑኑ ቢፈርስ የተሻለ ይሆናል፡፡ ሰዎች ጽድቃቸው መፍረሱ ላይቀር እንዳይፈርስ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡
 
ጌታ አዳኛችን ሆንዋል፡፡ ምንኛ ፍጹም ነው! እግዚአብሄር አምላካችን አዳኛችን ሆነ፡፡ እናንተንና እኔንም አዳነን፡፡ ከሥጋችሁ ድካም የተነሳ ዳግመኛ ሐጢያተኛ ትሆናላችሁን? አትሆኑም፡፡ እግዚአብሄር ጽድቅን ሁሉ ፈጽሞዋል፡፡ ከውሃውና ከመንፈሱ ዳግም ከተወለድን በኋላ ጽድቃችን ብዙ ጊዜ ፈርሶዋል፡፡ ጌታን ስንከተል ክፋታችን ብዙ ጊዜ ተገልጦዋል፡፡ አይነ አፋር ይመስል ራሱን ለመደበቅ ሲሞክር ተገልጦዋል፡፡ ለሌሎች ሰዎች ደግ ለመምሰል ሲሞክርም ተጋልጦዋል፡፡ ጽድቃችን ሲገለጥ የሚፈርሰው የእኛ ጽድቅ ብቻ ነው፡፡ የጌታ ጽድቅ ግን ጸንቶ ይቆማል፡፡
  
 
ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፡፡ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው፡፡
 
ጌታ አምላክ ፍጹም የሆነ አዳኛችን እንደሆነ ታምኑ ዘንድ እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህ በእምነት ልንኖር ይገባል፡፡ እግዚአብሄር ጽድቃችን እንዲፈርስ ይፈልጋል፡፡ በዚህም ይደሰታል፡፡ ዮሐንስ 3፡6 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው፡፡›› ሥጋ መንፈስ ሊሆን አይችልም፡፡ በቡድሃ ሃይማኖት ‹‹ከዓለማዊ ኑሮ የመፈታት ትምህርት›› የሚባል ነገር አለ፡፡ ሥጋ ፈጽሞ መንፈስ ሊሆን አይችልም፤ አይሆንም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ ማን ሊያደርገው ይችላል? ማንም ሊያደርገው አይችልም፡፡
 
በዘመኑ የቡድሃ ሃይማኖት ውስጥ በጣም ታዋቂ የሆነው የኮርያ መነኩሴ ሱንግ-ቹል ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ሞተ፡፡ ለ2 አስርተ ዓመታት ያህል ፊቱን ወደ ግድግዳ አዙሮ ጥልቅ ተመስጦ በማድረግ እውነትን መፈለግ ያዘ፡፡ መንፈሳዊ አብርሆት ላይ ለመድረስ ሲል ለመተኛት ተጋድሞ አያውቅም፡፡ በእነዚያ 10 ዓመታት ውስጥ በተቀመጠበት ሆኖ ያንቀላፋ ነበር፡፡ ክፉ አሳቦችንና ከውስጡ የሚወጡትን ምንዝርናን፣ ዝሙትን፣ ነፍስ መግደልን፣ ስርቆትን፣ ክፋትን፣ ትዕቢትንና ስንፍናን ለማሸነፍ የሚችልበት ጥሩ አእምሮ ይኖረው ዘንድ ብቻ ጣረ፡፡ ብዙ ሰዎች ይህ ሰው ሕያው የሆነ ቡድሃ እንደሆነ አድርገው አሰቡ፡፡ ነገር ግን የሥጋውን ፍትወት በጭራሽ ማጥፋት እንደማይችል ያውቅ ስለነበር አእምሮውን በተራሮች ልብ ውስጥ ለ2 አስርተ ዓመታት ያህል ከኮተኮተ በኋላ ሊሞት ሲቃረብ ትንሽ የኒርቫና ግጥም ትቶ ተሰናበተ፡፡
 
‹‹በዕድሜዬ ዘመን ብዙ ወንዶችንና ሴቶችን ስላሳሳትሁ ሐጢያቶቼ እጅግ ከፍተኛ ከሆኑት ተራሮች የገዘፉ ናቸው፡፡ ፍጻሜ ወደሌለው ሲዖል እወርዳለሁ፡፡ ልቅሶዬም በአስር ሺህ መንገዶች ይከፋፈላል፡፡ ቀዩዋ ጸሐይም ከሰማያዊዎቹ ተራሮች በታች አዘቅዝቃለች፡፡
 
የዓለም የሃይማኖት ሰዎች ሁሉ የዚህን ሰው የላቀ ስብዕናና ድንቅ የሚመስሉ አስተምህርቶችን አድንቀዋል፡፡ ነገር ግን እርሱ ራሱ ወደ ሲዖል እንደሚወርድ በግልጥ ተናግሮዋል፡፡
 
ሥጋ በፍጹም መንፈስ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን በእርሱ ማዳን በማመን ዳግም ስንወለድ የእግዚአብሄር ልጆች እንሆናለን፡፡ በጽድቅ ትንሳኤን በሰጠን በእግዚአብሄር ጸጋ አዲስ ፍጥረቶች ሆነናል፡፡ ሰው በራሱ ጥረቶች ሊታደስ አይችልም፡፡
 
በግዞት አገልግሎት ላይ የሚሳተፉ አገልጋዮች፣ መነኩሴዎችና የካቶሊክ አባቶች እስረኞችን በቀሪው የሕይወት ዘመናቸው ሰናይ ሕይወትን እንዲኖሩ ይመክራሉ፡፡ ነገር ግን ሥጋ በጭራሽ አይለወጥም፡፡ እግዚአብሄር የራሳችንን ጽድቅ ትተን ጌታ አዳኛችን መሆኑን አጥብቀን እንድናምን ይፈልግብናል፡፡ በኢየሱስ ጥምቀትና መስቀል እመኑ፡፡ ያን ጊዜ በደህንነት ላይ ትልቅ እምነት ይኖራችኋል፡፡
 
 
አሁን እግዚአብሄር ምዕመናንን ይፈልጋል፡፡
 
ጌታ ማስተሰርያ ሆነልን፡፡ እግዚአብሄር አብን ከሰዎች የለዩትን ነገሮች ሁሉ ለመውሰድም ተጠመቀ፡፡ የሐጢያታችንን ዋጋ ለመክፈል ተሰቀለ፡፡ በእኛም ፋንታ ተኮነነ፡፡ ከሐጢያቶች ሁሉም አዳነን፡፡ እግዚአብሄር ማስተሰርያ ሆነልን፡፡
 
እርሱ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እርሱንም እግዚአብሄር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተሰርያ አድርጎ አቆመው፡፡ ይህም በፊት የተደረገውን ሐጢያት በእግዚአብሄር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፡፡ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፡፡›› (ሮሜ 3፡25-26)
 
እግዚአብሄር ወደ ዓለም መጥቶ ጽድቅን ሁሉ ፈጸመ፡፡ በዓለም የሚኖር ሰው ሁሉ ሐጢያት አልባ ነው፡፡ ፍጹም በሆነው የእግዚአብሄር ደህንነት ቢያምን ማንም ሲዖል አይወርድም፡፡ ሲዖል የሚወርደው ባለማመኑ ነው፡፡ ሰው የራሱን ጽድቅና ግብዝነት ትቶ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ሞቱ በማመን እግዚአብሄርን አዳኙ አድርጎ ቢቀበል መዳን ይችላል፡፡ እኛ በእግዚአብሄር እይታ የምንኖረው ያለ ሐጢያት በሆነ ሁኔታ ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ ወስዶ አስወግዶዋቸዋልና፡፡
 
እኔ በእግዚአብሄር አምናለሁ፡፡ እናንተም ታምናላችሁ፡፡ እርሱ አዳኝ ነው፡፡ እኛ ሐጢያት የለብንም፡፡ እግዚአብሄር አምላክ ፈጽሞ አድኖናል፡፡ ያልተፈታው ብቸኛው ችግራችን ቀሪውን ሕይወት የምንኖረው እንዴት ነው የሚለው ነው፡፡ መኖር የሚገባን እንዴት ነው? በመንፈስ መመላለስ ይገባናል፡፡ ሐጢያቶቻችንን ስለ ማስወገድ የምንጨነቅበት ምክንያት የለም፡፡ ‹‹እግዚአብሄር በፊት የተደረጉትን ሐጢያቶች ትቶዋቸዋል›› የሚሉት ቃሎች እግዚአብሄር ስለ ሐጢያቶቻችን አይኮንነንም የሚሉ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን ለመውሰድ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅና በመሰቀል አስቀድሞ ከሐጢያቶቻችን ስላዳነን ሐጢያት የለብንም፡፡ የሚፈረድብንም ምንም ነገር የለም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ስለ ሐጢያቶቻችን አይኮንነንም፡፡ እርሱ ይህንን እውነት በልባቸው የሚያምኑትን ይፈልጋል፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስ ጻድቅ የለም ይላል፡፡ እኛ ግን በእግዚአብሄር በማመን ጸድቀናል፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፡- ‹‹እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፡- ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ እግዚአብሄርንም የሚፈልግ የለም፡፡ ሁሉም ተሳስተዋል፤ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፡፡ ቸርነትን የሚያደርግ የለም፤ አንድ ስንኳ የለም፡፡ ጉሮሮአቸው እንደተከፈተ መቃብር ነው፡፡ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፡፡ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፡፡ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፡፡ እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፡፡ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፡፡ የሰላምንም መንገድ አያውቁም፡፡ በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሄርን መፍራት የለም፡፡›› (ሮሜ 3፡10-18)
 
እግዚአብሄር ወደ ዓለም መጥቶ በዚህ ዓለም ላይ እየኖሩ ሁሉንም አይነት ክፋቶች የሚሰሩትን፣ ጽድቅ የሌላቸውንና የማይጠቅሙ ሰዎችን ሐጢያቶች በሙሉ በዮርዳኖስ ወንዝ ላይ ወሰደ፡፡ ይህንን ታምናላችሁን?
 
አሁን እግዚአብሄር ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ እንዳዳናቸው የሚያምኑ ሰዎችን ይፈልጋል፡፡ እርሱ እኛን ጻድቃኖች ያደፋፍረናል፤ ይጠነቀቅልናል፡፡ ሁልጊዜም ከእኛ ጋር ነው፡፡ ይጠብቀናል፤ አብሮንም ይሰራል፡፡ እግዚአብሄር የጽድቅን ሥራዎች በአደራ ሰጥቶናል፡፡ እኛ በሥጋ ሐጢያቶቻችን ከምናዝነው የበለጠ እግዚአብሄር ያዝናል፡፡ ‹‹አስቀድሞ ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ አድኛችሁ ሳለ ስለምን ታዝናላችሁ?››
 
አሁን እኛ ማድረግ ያለብን በእግዚአብሄር ማመን፣ በመንፈስ መመላለስና ነፍሳቶችን ለመሰብሰብም ወንጌልን መስበክ ነው፡፡ እኛ ልናደርጋቸው የሚገቡን ነገሮች እነዚህ ናቸው፡፡ ይህንን ታምናላችሁን? የራሳችሁን ጽድቅ አትግለጡ፡፡ በራሱ ጻድቅ ያልሆነውን ሰው አትዝለፉት፡፡ በእርግጥም በተፈጥሮው ጻድቅ የሆነ ሰው የለም፡፡
 
 
በጥምቀቱና በመስቀሉ ያዳነንን ጌታ እናመሰግናለን፡፡
 
እኛን ፈጽሞ ባዳነን ፍቅሩ ካልሆነ በቀር በእግዚአብሄር ፊት የምንመካበት ምንም ነገር የለም፡፡ እኛ ማድረግ ያለብን በእግዚአብሄር ደህንነት መመካት፣ ያንን ማመስገን፣ እርሱን ማክበርና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስበክ ነው፡፡ ስለ ሐጢያትና ሲዖል ስለ መውረድ መጨነቅ አያስፈልገንም፡፡ ‹‹እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም፡፡›› (ሮሜ 8፡1) በፍጹም! አያችሁ? ሰው ሲዖል የሚወርደው ጌታ በጽድቅ ድርጊቱ ያዳነው ከመሆኑ እውነታ ጋር ካልተባበረ ነው፡፡ ነገር ግን ሰው በዚህ የሚያምን ከሆነ ሲዖል ስለ መውረድ መጨነቅ አያስፈልገውም፡፡
 
እግዚአብሄር አምላክ በኢየሱስ ጥምቀትና ደም ከሐጢያቶቻችን አድኖናል፡፡ ምንኛ አመስጋኞች ነን! ‹‹ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና፡፡ ወይስ እግዚአብሄር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ ደግሞ አምላክ አይደለምን?›› (ሮሜ 3፡28-29)
 
እግዚአብሄር የአይሁዶች አምላክ ብቻ አይደለም፡፡ አሕዛብም አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር አምላክ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አድኖናል፡፡ ይህንን ለማድረግም ወደ ዓለም መጥቶ ሐጢያቶቻችንን ለመሸከም ተጠመቀ፡፡ ለሐጢያቶች ሁሉ ተኮንኖም ተሰቀለ፡፡ ስለዚህ የሰዎች ሁሉ አምላክና አዳኝ ሆነ፡፡ የሮሜ ምዕራፍ 3 ድምዳሜ ይህ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን አመነ፡፡ እኛም እንዲሁ እናምነዋለን፡፡
 
ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረው ስለ ሥጋ ድካም ብቻ ሳይሆን ከሕግ ውጪ ስለሆነውም የእግዚአብሄር ጽድቅ ነው፡፡ በሕግ ሥራዎች መዳን አንችልም፡፡ መዳን የምንችለው በምንድነው? በእግዚአብሄር ማዳን በማመን ነው፡፡ እግዚአብሄር አምላክ ማስተሰርያ ሆነልን፡፡ በፊት የተደረጉትንም ሐጢያቶች ተወ፡፡ ስለዚህ የማያምኑ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ላይ ሐጢያት በመስራታቸው ይፈረድባቸዋል፡፡ እርሱ በሥጋ ደካሞች ለተሰሩት ሐጢያቶች አይፈርድም፡፡ ምክንያቱም በዓለም ላይ ሐጢያት የለም፡፡
 
ስለዚህ በእግዚአብሄር አምላክ ማመን አለብን፡፡ አማኞች ፍርድ ወይም ኩነኔ የለባቸውም፡፡ እግዚአብሄር የአማኞች አምላክ ነው፡፡ ስለዚህ ቀሪ ሕይወታችንን በመንፈስ በመመላለስ ልንኖር ይገባናል፡፡ ሥጋችን በፍትወት እየተመራ ሊኖር ቢፈልግም ሐጢያቶቻችን በሙሉ ቀድሞውኑም ይቅር ስለተባሉ ሁልጊዜም የመንፈስን ነገሮች ማድረግ እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር አምላክ የአይሁዶችና የአሕዛቦች አምላክ ነው፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሄር ሰዎች ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው እንዲድኑ ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ እርሱ የማያምኑ ሰዎች አዳኝ መሆንም ይችላል፡፡ እርሱ ቀድሞውኑም የአማኞች አምላክ ሆንዋል፡፡
 
እግዚአብሄር አምላክን ከውስጥ ከልቤ አመሰግነዋለሁ፡፡ በእግዚአብሄር አምላክ ባይሆን ኖሮ የሰው ሥጋ አምሳል ወደዚህ ዓለም ባይመጣ ኖሮ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ለመውሰድም በዮርዳኖስ ወንዝ ባይጠመቅ ኖሮ ምንኛ ጎስቋላ በሆንሁ ነበር፡፡ እርሱ ፍጹም አዳኛችን ባይሆን ኖሮ የሐጢያቶችን ስርየት ካገኘን በኋላ እንደገና ሐጢያተኞች እንሆን ነበር፡፡ ምክንያቱም እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ ደካሞች ነንና፡፡ እግዚአብሄር አምላክን አመሰግናለሁ፡፡