Search

တရားဟောချက်များ

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[16-1] የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ጅማሬ፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 16፡1-21 ››

የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ጅማሬ፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 16፡1-21 ››
‹‹ለሰባቱም መላእክት፡- ሄዳችሁ የእግዚአብሄርን ቁጣ ጽዋዎች በምድር ውስጥ አፍስሱ የሚል ታላቅ ድምጽ ከመቅደሱ ሰማሁ፡፡ ፊተኛውም ሄዶ ጽዋውን በምድር ውስጥ አፈሰሰ፤ የአውሬውም ምልክት ባለባቸው ለምስሉም በሚሰግዱ ሰዎች ክፉኛ የሚነዘንዝ ቁስል ሆነባቸው፡፡ ሁለተኛውም ጽዋውን በባህር ውስጥ አፈሰሰ፤ እንደ ሞተም ሰው ደም ሆነ፤ በባህርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ፡፡ ሦስተኛውም ጽዋውን በወንዞችና በውሃ ምንጮች ውስጥ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ፡፡ የውሃውም መልአክ፡- ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ ቅዱስ ሆይ እንዲህ ስለፈረድህ ጻድቅ ነህ፤ የቅዱሳንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል የሚገባቸው ነውና ብሎ ሲናገር ሰማሁ፡፡ ከመሰዊያውም፡- አዎን ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ ፍርዶችህ እውነትና ጽድቅ ናቸው ብሎ ሲናገር ሰማሁ፡፡ አራተኛውም ጽዋውን በጸሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ሰዎችንም በእሳት ልታቃጥል ተሰጣት፡፡ ሰዎችም በታላቅ ትኩሳት ተቃጠሉ፤ በነዚህም መቅሰፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሄርን ስም ተሳደቡ፡፡ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሐ አልገቡም፡፡ አምስተኛውም ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ መንግሥቱም ጨለማ ሆነች፡፡ ከስቃይም የተነሳ መላሶቻቸውን ያኝኩ ነበር፡፡ ከስቃያቸውና ከቁስላቸውም የተነሳ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ፤ ከስራቸውም ንስሐ አልገቡም፡፡ ስድስተኛውም ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው ውሃው ደረቀ፡፡ ከዘንዶውም አፍና ከአውሬው አፍ፣ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጉንቸሮች የሚመስሉ ሦስት ርኩሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ፤ ምልክት እያደረጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፤ በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሄር ቀን ወደሚሆነው ጦር እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ፡፡ እነሆ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብጹዕ ነው፡፡ በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ አስከተቱአቸው፡፡ ሰባተኛውም ጽዋውን በአየር ውስጥ አፈሰሰ፤ ከመቅደሱም ውስጥ፡- ተፈጽሞአል የሚል ታላቅ ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ፡፡ መብረቅና ድምጽም፣ ነጎድጓድም፣ ትልቅም የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ መናወጥ ከቶ አልነበረም፤ ከሁሉ በለጠ፡፡ ታላቂቱም ከተማ በሦስት ተከፋፈለች፤ የአሕዛብም ከተማዎች ወደቁ፡፡ ታላቂቱም ባቢሎን የብርቱ ቁጣው ወይን ጠጅ የሞላበትን ጽዋ እንዲሰጣት በእግዚአብሄር ፊት ታሰበች፡፡ ደሴቶችም ሁሉ ሸሹ፤ ተራራዎችም አልተገኙም፡፡ በሚዛንም አንድ ታላንት (አንድ ታላንት ሦስት ፈረሱላ የሚያህል ነው) የሚያህል ታላቅ በረዶ በሰዎች ላይ ከሰማይ ወረደባቸው፡፡ ሰዎቹም ከበረዶው መቅሰፍት የተነሳ እግዚአብሄርን ተሳደቡ፤ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ነውና፡፡›› 
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
ቁጥር 1፡- ለሰባቱም መላእክት፡- ሄዳችሁ የእግዚአብሄርን ቁጣ ጽዋዎች በምድር ውስጥ አፍስሱ የሚል ታላቅ ድምጽ ከመቅደሱ ሰማሁ፡፡
እግዚአብሄር በሰባቱ የቁጣ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ገናም በዚህች ምድር በሚኖሩት የጸረ ክርስቶስ አገልጋዮችና ሕዝቦች ላይ ቁጣውን ያወርዳል፡፡ ፍጥረታትና ሰዎች በሙሉ ከብዙ ዓመታቶች ትዕግስት በኋላ በሚፈነዳው የእግዚአብሄር ቁጣ ማዕበል ይጠረጋሉ፡፡ በቀረው የሰባቱ ዓመት ታላቅ መከራ ክፍለ ጊዜ ወቅት በሚወረዱት ታላላቅ መቅሰፍቶች ይሰቃያሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ይህ ዓለም ሲፈረካከስ፣ ሲበታተንና ሲወድም ወደ አመድነት ይቀየራል፡፡
ዮሐንስ ራዕይ 16 የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች የሚወርዱበት ምዕራፍ ነው፡፡ እስከዚህ የመጨረሻ መቅሰፍት ድረስ በጌታ ወደ አየር እንዲነጠቁ የሚያደርጋቸውን የደህንነት ምስክርነት የያዘውን ወንጌል ማለትም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የማያውቁም ሆኑ የማያምኑ ሰዎች ሁሉም በእነዚህ መቅሰፍቶች ይጠፋሉ፡፡
 
ቁጥር 2፡- ፊተኛውም ሄዶ ጽዋውን በምድር ውስጥ አፈሰሰ፤ የአውሬውም ምልክት ባለባቸው ለምስሉም በሚሰግዱ ሰዎች ክፉኛ የሚነዘንዝ ቁስል ሆነባቸው፡፡
እግዚአብሄር በመልአኩ አማካይነት የሚያፈሰሰው ክፉኛ የሚነዘንዝ ቁስል መቅሰፍት የአውሬውን ምልክት በተቀበሉት ላይ ይወርዳል፡፡ ይህ የቁስል መቅሰፍት በቆሰሉት የሰው ቆዳዎች ላይ የሚያመረቅዝና ምርቅዙም ከቆዳዎች አልፎ የሚሰራጭ የማይድን ቁስል ነው፡፡ የቆሰሉት ሰዎች እስኪሞቱ ድረስ በዚህ ክፉኛ የሚነዘንዝ የቁስል መቅሰፍት ሲሰቃዩ ስቃዩ እንዴት ታላቅ ይሆናል? ነገር ግን እግዚአብሄር የአውሬውን ምልክት በተቀበሉት ሁሉ ላይ የቁስል መቅሰፍቱን የሚያፈስስ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላም ስድስት ተጨማሪ መቅሰፍቶችን በራሳቸው ላይ ያወርዳል፡፡ ስለዚህ ሁሉም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ከእነዚህ መቅሰፍቶች የሚያመልጡበትን መንገድ ማግኘትና አሁኑኑ በዚህች ቅጽበት በዚህ ወንጌል በማመን እነዚህን አስፈሪ መቅሰፍቶች ማስወገድ አለባቸው፡፡
ጌታችን ለአውሬውና ለምስሉ በሚሰግዱት ላይ ተጨማሪ ስድስት መቅሰፍቶችን እንደሚያወርድ ተናግሮዋል፡፡ እግዚአብሄር አብዝቶ የሚጠላው ሐጢያት ምንድነው? ይህ ሐጢያት ከእግዚአብሄር ውጪ ለሌላ አንድ ነገር ወይም ሰው ምስሎችን በመስራት እርሱን ማክበርና ለእርሱ ማጎብደድ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታ አምላካችንና ኢየሱስ ክርስቶስ በትክክል ማን እንደሆኑ ማወቅና ክርስቶስ ኢየሱስን አምነን ለእርሱ መስገድ አለብን፡፡ ከራሱ ከጌታ አምላክ ሌላ በዚህ በመላው ዩኒቨርስ ውስጥ አምላካችን ሊሆን የሚችል ምንምና ማንም የለም፡፡
የቁስሉን መቅሰፍትና ስድስቱን ተጨማሪ መቅሰፍቶች ማስወገድ የምትፈልጉ ከሆናችሁ ጌታ የሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ተምራችሁ እመኑበት፡፡ በቀን ተቀን ሕይወታቸው እግዚአብሄርን የተቃወሙና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ለማመን አሻፈረኝ ያሉ እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በመጨረሻ ይጠፋሉ፡፡
 
ቁጥር 3፡- ሁለተኛውም ጽዋውን በባህር ውስጥ አፈሰሰ፤ እንደ ሞተም ሰው ደም ሆነ፤ በባህርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ፡፡
ሁለተኛው መቅሰፍት ባህር ወደ ደም የሚለወጥበት ነው፡፡ እግዚአብሄር በዚህ መቅሰፍት በባህር ውስጥ ያሉትን ፍጥረታቶች በሙሉ ይገድላል፡፡ እግዚአብሄር ባወረደው በዚህ የሁለተኛው ጽዋ መቅሰፍት ባህር ይገማል፡፡ በዚያ ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታትም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖሩም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ይህንን ሁለተኛውን መቅሰፍት ሲያመጣ ከባህር የሚገኝ ምግብ የሚበላ ሰው አይኖርም፡፡ እግዚአብሄር በሁለተኛው መቅሰፍት አማካይነት እርሱ ሕያው እንደሆነና የሕይወትም ሁሉ ጌታ እንደሆነ ያሳያል፡፡
ይህ ሁለተኛው መቅሰፍት እግዚአብሄር ለፍጥረታቶቹ ሁሉ ለጌታ አምላክ በመስገድ ፋንታ የአምላክ ጠላት ለሆነውና የቅዱሳንን ደም ላፈሰሰው የአውሬው ምስል በማጎንበሳቸው በዓለም ሰዎች ሁሉ ላይ የሚያወርደው ፍርድ ነው፡፡ ይህ ሁለተኛው መቅሰፍት በጣም ተገቢ ነው፡፡ እግዚአብሄር አምላክ ስለፈጠራቸው ፍጥረቶቹ ሁሉ ጌታን ከማያመሰግኑት ዘንድ የተፈጥሮን ባለጠግነት ይወስዳል፡፡
 
ቁጥር 4-7፡- ሦስተኛውም ጽዋውን በወንዞችና በውሃ ምንጮች ውስጥ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ፡፡ የውሃውም መልአክ፡- ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ ቅዱስ ሆይ እንዲህ ስለፈረድህ ጻድቅ ነህ፤ የቅዱሳንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል የሚገባቸው ነውና ብሎ ሲናገር ሰማሁ፡፡ ከመሰዊያውም፡- አዎን ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ ፍርዶችህ እውነትና ጽድቅ ናቸው ብሎ ሲናገር ሰማሁ፡፡
ወንዞችንና የውሃ ምንጮችን ወደ ደም የሚቀይረው ሦስተኛው መቅሰፍት በእርግጥም እጅግ አሰቃቂ ከሆኑት መቅሰፍቶች አንዱ ነው፡፡ በእግዚአብሄር በማያምኑት ሁሉ ላይ ቅጣት ሆኖ የሚወርደው ይህ መቅሰፍት የውሃ ምንጮችን ወደ ደም በመቀየር በዚህች ምድር ላይ እንዳይኖሩ ያደርጋቸዋል፡፡ እግዚአብሄር በዚህች ምድር ላይ ያሉትን ወንዞችና የውሃ ምንጮች ወደ ደም ይለውጣቸዋል፡፡ ይህም መቅሰፍት የሕይወት ሁሉ ምንጭ የሆነው ውሃ የሰጣቸውን አምላክ በሚቃወሙት ላይ ዋጋና ቅጣት ሆኖ በዓለም ሕዝቦች ላይ የሚወርድ ፍርድ ነው፡፡
እግዚአብሄር ይህንን መቅሰፍት እርሱን በሚቃወሙት ላይ የሚያወርደው በዚህ ምድር ላይ ሳሉ ቅዱሳኖቹንና ነቢያቶቹን ስለገደሉ ነው፡፡ እነርሱ እግዚአብሄርን አምላክ አድርገው ለማመን አሻፈረኝ ያሉ ብቻ ሳይሆኑ ከጸረ ክርስቶስ ጋር ተባብረው እርሱን የተቃወሙ ሰዎችም ናቸው፡፡
በዚህ ዓለም ላይ በጸረ ክርስቶስ ሐይል ተሸንፈው የእግዚአብሄርን ፍቅር የሚቃወሙ ሰዎች እግዚአብሄር አብዝቶ የሚወዳቸውን ቅዱሳኖችና የእርሱን አልጋዮች ያሳድዳሉ፤ ይገድላሉም፡፡ አሁን ጌታችን የዚህን ዓለም ሕዝብ ከሐጢያት ለማዳን በሰጠን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማያምኑ ሰዎች በዘመን መጨረሻ የሚኖሩ ብዙ ቅዱሳኖችንና ነቢያቶችን ይገድላሉ፡፡ ደማቸውንም ያፈስሳሉ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር እርሱ ጠላቶች በሚኖሩበት በዚህ ዓለም ላይ ሦስተኛውን መቅሰፍት በማፍሰስ የሕይወት ምንጭ የሆነውን ውሃ ወደ ደም ይለውጠዋል፡፡ በዚህም ያጠፋቸዋል፡፡
ይህ የእግዚአብሄር ቅን ፍርድ ነው፡፡ በዚህም በአየር ላይ ያሉት ቅዱሳን ሁሉ ይደሰታሉ፡፡ ለምን? እግዚአብሄር ቅዱሳኑን በገደሉት ጠላቶቹ ላይ የጽድቅ ፍርዱን በመስጠት የቅዱሳኖችን ደም በእነርሱ ላይ ይበቀላልና፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሄር ቅዱሳንና ባሮች መፍራት የለባቸውም፡፡ በፈንታው ሰማዕትነት ሲገጥማቸው በጌታ አምላክ ላይ ያላቸውን እምነት መጠበቅና የእግዚአብሄርን ተስፋና ሐይል መመልከት አለባቸው፡፡
 
ቁጥር 8-9፡- አራተኛውም ጽዋውን በጸሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ሰዎችንም በእሳት ልታቃጥል ተሰጣት፡፡ ሰዎችም በታላቅ ትኩሳት ተቃጠሉ፤ በነዚህም መቅሰፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሄርን ስም ተሳደቡ፡፡ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሐ አልገቡም፡፡
አራተኛው መልአክ የአራተኛውን መቅሰፍት ጽዋ በጸሐይ ላይ ሲያፈስስ ሰዎችን ከማቃጠልዋ የተነሳ እስከ ሞት ድረስ ይጋያሉ፡፡ እግዚአብሄር እርሱን በሚቃወሙት ላይ የሚያቃጠለውን የፀሐይ ሙቀት ያመጣል፡፡ ይህች ምድር በፀሐይ ምህዋር ዙሪያ በትክክል ስለምትሽከረከር ምድር ከዚህ ምህዋር ብታፈነግጥና እጅግ ኢምንት በሆነ ርቀት እንኳን ወደ ፀሐይ ብታቀርብ ነዋሪዎችዋ በሙሉ ተቃጥለው ይሞታሉ፡፡ ስለዚህ ይህ አራተኛው መቅሰፍት ሲወርድ ገናም በዚህች ምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ በመቃጠል ይሰቃያሉ፡፡
ሆኖም እግዚአብሄርን ከሚቃወመው ሐጢያታቸው አሁንም ንስሐ አይገቡም፡፡ ለምን? ምክንያቱም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመቃወም ቀድሞውኑም ለጥፋት ታጭተዋልና፡፡ ስለዚህ ሰው ሁሉ አሁኑኑ በተቻለ ፍጥነት ከእግዚአብሄር ቁጣ እንዲያመልጥ ሊፈቅድለት የሚችለውን እምነቱን ማዘጋጀት አለበት፡፡ ይህ እምነት ለደህንነት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን ነው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው በውሃውና በመንፈሱ እውነት ማመን አለበት፡፡
 
ቁጥር 10-11፡- አምስተኛውም ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ መንግሥቱም ጨለማ ሆነች፡፡ ከስቃይም የተነሳ መላሶቻቸውን ያኝኩ ነበር፡፡ ከስቃያቸውና ከቁስላቸውም የተነሳ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ፤ ከስራቸውም ንስሐ አልገቡም፡፡
የአምስተኛው ጽዋ መቅሰፍት ጨለማንና ስቃይን ያመጣል፡፡ እግዚአብሄር ይህንን የአምስተኛውን መቅሰፍት ጽዋ በጸረ ክርስቶስ ዙፋን ላይ በማወረድ የጨለማንና የስቃይን መቅሰፍት ያወርዳል፡፡ ሰዎች በዚህ መቅሰፍት ከስቃያቸውና ከመከራቸው የተነሳ ምላሶቻቸውን ያኝካሉ፡፡ እግዚአብሄር በሁለት ዕጥፍ ታላቅ በሆነ ስቃይ የቅዱሳኖችን መከራ በእነርሱ ላይ መበቀሉን ያረጋግጣል፡፡
በሌላ አነጋገር እነርሱ ቀደም ብለው ቅዱሳኖችን ባሰቃዩበት መጠን ያሰቃያቸዋል፡፡ ያም ሆኖ በእነዚህ ቁስሎች እየተሰቃዩ ቢሆንም አሁንም እግዚአብሄርን ይሳደባሉ፡፡ ንስሐም አይገቡም፡፡ ስለዚህ በእሳትና በዲን የሚቃጠለውን ዘላለማዊ የሲዖል ቅጣት ይቀበላሉ፡፡
 
ቁጥር 12፡- ስድስተኛውም ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው ውሃው ደረቀ፡፡
እግዚአብሄር የሚያፈስሰው የስድስተኛው መቅሰፍት ጽዋ የኤፍራጥስን ወንዝ የሚያደርቅ የረሃብ መቅሰፍት ነው፡፡ የሰው ዘርም በዚህ መቅሰፍት ነው፡፡ የሰው ዘርም በዚህ መቅሰፍት ነው፡፡ የሰው ዘርም በዚህ መቅሰፍት እጅግ ታላቅ ስቃይን ይሰቃያል፡፡ የረሃብ መቅሰፍት ለእያንዳንዱ ሰው ሕይወት እጅግ አስፈሪ መቅሰፍት ነው፡፡ ጌታ የሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በናቁት ላይ የሚወርደው ይህ መቅሰፍት የእግዚአብሄርን ፍቅር ንቀው እርሱን በተቃወሙት ላይ የሚወርደው ቅጣት ምንኛ ታላቅ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ በኋላም የእግዚአብሄር የሰማይ ሰራዊትና የዚህችም ምድር የሰይጣን ሰራዊት በዚህ የጦር አውድ ላይ የመጨረሻውን ጦርነት ይዋጋል፡፡ ነገር ግን ሰይጣንና ተከታዮቹም ተይዘው በእግዚአብሄር ይጠፋሉ፡፡
 
ቁጥር 13፡- ከዘንዶውም አፍና ከአውሬው አፍ፣ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጉንቸሮች የሚመስሉ ሦስት ርኩሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ፡፡
ይህ ቁጥር የርኩሳን መናፍስቶችና የአጋንንቶች ሥራዎች ሁሉ የሚመነጩት ከሰይጣን፣ ከአውሬውና ከሐሰተኛ ነቢያቶች አፍ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ የዓለም መጨረሻ ሲቃረብ የአጋንንት ሥራዎች በዓለም ሁሉ ይሰለጥናሉ፡፡ አጋንንቶች በሰይጣን፣ በሐሰተኛ ነቢያቶችና በጸረ ክርስቶስ አማካይነት ተዓምራቶችንና ምልክቶችን በማድረግ ሰዎችን እያሳቱ ወደ ጥፋት ይነዱዋቸዋል፡፡ የዘመን መጨረሻዋ ዓለም የአጋንንቶች ዓለም ትሆናለች፡፡ ነገር ግን የእነርሱ ዓለም በሙሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያወርዳቸው በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶችና በእርሱ ዳግመኛ ምጽዓት ወደ ፍጻሜ ይመጣል፡፡
 
ቁጥር 14፡- ምልክት እያደረጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፤ በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሄር ቀን ወደሚሆነው ጦር እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ፡፡
የአጋንንት መናፍስቶች እግዚአብሄርን ይዋጉ ዘንድ የመላውን ዓለም ነገሥታቶች ልብ በማሸፈት በአንድ ስፍራ ይሰበስቡዋቸዋል፡፡ በመጨረሻው ዘመን በምትኖረው ዓለም ውስጥ ሰው ሁሉ በአጋንንቶች መናፍስቶች ይገዛል፡፡ በዚህም የዲያብሎስን ሥራዎች የሚያደርግ የሰይጣን አገልጋይ ወደ መሆን ይቀየራል፡፡
 
ቁጥር 15፡- እነሆ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብጹዕ ነው፡፡
ጌታ እንደ ሌባ ሆኖ ወደዚህ ዓለም ይመጣል፡፡ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች እስከሚወርዱ ድረስ እምነታቸውን የሚጠብቁና ወንጌሉን የሚሰብኩ ሰዎች በአያሌው ይባረካሉ፡፡ ጌታችን በመጨረሻው ዘመን በዓለም ውስጥ ለሚኖሩ ቅዱሳኖቹ ጌታ በሰጣቸው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ባላቸው እምነት እንዲኖሩና እስከ መጨረሻው ቀናቸው ድረስም ይህንን እምነት እንዲጠብቁ ይነግራቸዋል፡፡ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ከመውረዳቸው በፊት በጌታ ያላቸውን እምነት የሚጠብቁ ሰዎች ከእርሱ ዘንድ ታላላቅ ሽልማቶችን ይቀበላሉ፡፡ ጌታችን በረከቶቹን የሚሰጣቸውን እነዚያን ሰዎች ለማግኘት በእርግጥም ይመጣል፡፡
 
ቁጥር 16፡- በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ አስከተቱአቸው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በሰይጣንና በእግዚአብሄር መካከል የሚደረገው የመጨረሻው ጦርነት አርማጌዶን ተብሎ በሚጠራ ስፍራ እንደሚሆን ይተነብያል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ሁሉን ቻይ ስለሆነ ሰይጣንን ያሸንፍና አውሬውን በእሳትና በዲን ባህር ውስጥ ይወረውረዋል፡፡ ሰይጣን ሁልጊዜም አሳች እንደሆነ መረዳትና በእግዚአብሄር ፊት የምንቆምበት ቀን እስኪመጣ ድረስም በጌታ ያለንን እምነታችንን መጠበቅ አለብን፡፡
 
ቁጥር 17-21፡- ሰባተኛውም ጽዋውን በአየር ውስጥ አፈሰሰ፤ ከመቅደሱም ውስጥ፡- ተፈጽሞአል የሚል ታላቅ ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ፡፡ መብረቅና ድምጽም፣ ነጎድጓድም፣ ትልቅም የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ መናወጥ ከቶ አልነበረም፤ ከሁሉ በለጠ፡፡ ታላቂቱም ከተማ በሦስት ተከፋፈለች፤ የአሕዛብም ከተማዎች ወደቁ፡፡ ታላቂቱም ባቢሎን የብርቱ ቁጣው ወይን ጠጅ የሞላበትን ጽዋ እንዲሰጣት በእግዚአብሄር ፊት ታሰበች፡፡ ደሴቶችም ሁሉ ሸሹ፤ ተራራዎችም አልተገኙም፡፡ በሚዛንም አንድ ታላንት (አንድ ታላንት ሦስት ፈረሱላ የሚያህል ነው) የሚያህል ታላቅ በረዶ በሰዎች ላይ ከሰማይ ወረደባቸው፡፡ ሰዎቹም ከበረዶው መቅሰፍት የተነሳ እግዚአብሄርን ተሳደቡ፤ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ነውና፡፡
እግዚአብሄር የሰባተኛውን ጽዋ መቅሰፍት በአየር ላይ ሲያፈስስ ነጎድጓድና መብረቅ ሰማይን ያናውጣል፡፡ ይህችን ምድርም ታላቅ የመሬት መናወጥና ከዚህ በፊት ፈጽሞ ታይቶ የማያውቅ ታላቅ በረዶ ይመታታል፡፡ የመጀመሪያው ዓለም በእነዚህ ጥፋቶች ምንም ፍንጭ ሳያስቀር ይጠፋል፡፡ ከዚህ በላይ ቅዱሳን ለሚመጣው ሺህ ዓመት በዚህች የታደሰች ምድር ላይ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረው በክብር ይኖራሉ፡፡
ሺህው ዓመት አልፎ ለቅዱሳን የተሰጠው የእግዚአብሄር አዲስ ሰማይና ምድር ተስፋ የሚፈጸምበት ጊዜ ሲመጣ እግዚአብሄር የመጀመሪያውን ዓለም እንዲጠፋ በማድረግ ለቅዱሳን ሁለተኛውን ሰማይና ምድር ይሰጣቸዋል፡፡ ያን ጊዜ ቅዱሳን በዚህ አዲስ ሰማይና ምድር ላይ ለዘላለም ከእግዚአብሄር ጋር ይነግሳሉ፡፡ ቅዱሳን በሺህው ዓመት የክርስቶስ መንግሥት ውስጥ እደሚኖሩና ከዚያም በእርሱ አዲስ ሰማይና ምድርም ለዘላለም በክብር እንደሚኖሩ ማመን አለባቸው፡፡ የጌታን መምጣት እየጠበቁ በዚህ ተስፋ መኖር አለባቸው፡፡