Search

တရားဟောချက်များ

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[19-1] ሁሉን ቻዩ የሚነግስበት መንግሥት ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 19፡1-21 ››

ሁሉን ቻዩ የሚነግስበት መንግሥት
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 19፡1-21 ››
‹‹ከዚህ በኋላ በሰማይ፡- ሃሌ ሉያ፤ በዝሙትዋ ምድርን ያጠፋችይቱን ታላቂቱን ጋለሞታ ስለፈረደባት የባሪያዎቹንም ደም ከእጅዋ ስለተበቀለ ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸውና፤ ማዳንና ክብር ሐይልም የአምላካችን ነው ብሎ ሲናገር እንደ ብዙ ሕዝብ ታላቅ ድምጽ ያለ ድምጽን ሰማሁ፡፡ ደግመውም፡- ሃሌ ሉያ አሉ፤ ጢስዋም ለዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል፡፡ ሀያ አራቱም ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች በፊታቸው ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለእግዚአብሄር፡- አሜን፤ ሃሌ ሉያ እያሉ ሰገዱለት፡፡ ድምጽም፡- ባሪያዎቹ ሁሉ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆችም ሆይ አምላካችንን አመስግኑ ሲል ከዙፋኑ ወጣ፡፡ እንደ ብዙ ሕዝብም ድምጽ፣ እንደ ብዙ ውሃዎችም ድምጽ፣ እንደ ብርቱም ነጎድጓድ ድምጽ ያለ ድምጽ ሰማሁ እንዲህ ሲል፡- ሃሌ ሉያ፤ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና፤ የበጉ ሰርግ ስለደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ፤ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ፡፡ ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጎናጸፍ ተሰጥቶአታል፡፡ ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ ነውና፡፡ እርሱም፡- ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው ብለህ ጻፍ አለኝ፡፡ ደግሞም፡- ይህ የእግዚአብሄር እውነተኛ ቃል ነው አለኝ፡፡ ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ፡፡ እርሱም፡- እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባርያ ነኝ፡፡ ለእግዚአብሄር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ፡፡ ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆም አምባላይ ፈረስ፤ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፤ በጽድቅም ይፈርዳል፤ ይዋጋልም፡፡ ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፡፡ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፤ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፡፡ በደምም የተረጨ ልብስ ተጎናጽፎአል፤ ስሙ የእግዚአብሄር ቃል ተብሎአል፡፡ በሰማይም ያሉት ጭፍራዎች ነጭና ጥሩ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በአምባላዮች ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር፡፡ አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል፤ እርሱም በብረት በትር ይገዛቸዋል፤ እርሱም ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሄርን የብርቱ ቁጣውን ወይን መጥመቂያ ይረግጣል፡፡ በልብሱና በጭኑም የተጻፈበት፡- የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ የሚል ስም አለው፡፡ አንድም መልአክ በፀሐይ ውስጥ ቆሞ አየሁ፡፡ በሰማይም መካከል ለሚበሩ ወፎች ሁሉ፡- መጥታችሁ የነገሥታትን ሥጋና የሻለቃዎችን ሥጋ፣ የብርቱዎችንም ሥጋ፣ የፈረሶችንም በእነርሱም የተቀመጡትን ሥጋ፣ የጌታዎችንና የባሪያዎችንም፣ የታናናሾችንና የታላላቆችንም ሁሉ ሥጋ እንድትበሉ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሄር እራት ተከማቹ ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፡፡ በፈረሱ የተቀመጠውን ጭፍራዎቹንም ይወጉ ዘንድ አውሬውና የምድር ነገሥታት ጭፍራዎቻቸውም ተከማችተው አየሁ፡፡ አውሬውም ተያዘ፤ በእርሱም ፊት ተዓምራትን እያደረገ የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትን ለምስሉም የሰገዱትን ያሳተ ሐሰተኛው ነቢይ ከእርሱ ጋር ተያዘ፤ ሁለቱም በሕይወት ሳሉ በዲን ወደሚቃጠል ወደ እሳት ባህር ተጣሉ፡፡ የቀሩትም በፈረስ ላይ ከተቀመጠው ከአፉ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ፤ ወፎችም ሁሉ ከሥጋቸው ጠገቡ፡፡›› 
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
ቁጥር 1፡- ከዚህ በኋላ በሰማይ፡- ሃሌ ሉያ፤ ማዳንና ክብር ሐይልም የአምላካችን ነው ብሎ ሲናገር እንደ ብዙ ሕዝብ ታላቅ ድምጽ ያለ ድምጽን ሰማሁ፡፡
ይህ ምንባብ ከበጉ ጋር የሚሰረጉት የሰርጋቸው ቀን በመቃረቡ ቅዱሳን ጌታ አምላክን ሲያመሰግኑ ያብራራል፡፡ ጌታ አምላካችን እርሱን የሚያመሰገኑበት ያማረ ምክንያት ይኖራቸው ዘንድ ለቅዱሳን መዳናቸውንና ክብርን ሰጥቶዋቸዋል፡፡ ስለዚህ በአየር ላይ የተነጠቁት ቅዱሳን ጌታ አምላክን ማመስገናቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ምክንያቱም እነርሱን ከሐጢያቶቻቸውና ከማያመልጡዋቸው ኩነኔዎቻቸው የሚያድንበት ጸጋው ታላቅ ነውና፡፡
‹‹ሃሌ ሉያ›› የሚለው ቃል ‹‹ሃላል›› ማለትም ምስጋና የሚለውንና ‹‹ያሃ›› ማለትም ‹‹ያህዌህ›› የሚሉትን የዕብራይስጥ ቃሎች ያቆራኘ ቅልቅል ቃል ነው፡፡ ስለዚህ ፍቺው ‹‹ያህዌህ ይመስገን›› ነው፡፡ በተለይ በብሉይ ኪዳን ውስጥ መዝሙረ ዳዊት 113-118 ‹‹የግብጽ ሃላል›› ተብሎ ሲጠራ መዝሙረ ዳዊት 146-150 ደግሞ ‹‹የሃላል መዝሙረ ዳዊት›› ተብሎ ተጠርቷል፡፡
 
ቁጥር 2፡- በዝሙትዋ ምድርን ያጠፋችይቱን ታላቂቱን ጋለሞታ ስለፈረደባት የባሪያዎቹንም ደም ከእጅዋ ስለተበቀለ ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸውና፤
ጌታ አምላክ የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች በምድር ሐይማኖተኞችና በማያምኑ ሁሉ ላይ በማውረድ ቅዱሳኖችን የሚበቀል መሆኑ እውነተኛና ጻድቅ የእግዚአብሄር ፍርድ ነው፡፡ የዚህ ዓለም ሐይማኖቶች ሐጢያት የሌለባቸውንና ጻድቅ የሆኑትን የእግዚአብሄር ባሮች በመግደላቸው እነርሱም በተራቸው በእግዚአብሄር ለዘላለም ሞት ሊኮነኑ ይገባቸዋል፡፡
የእግዚአብሄር ባሮች በዓለማዊ ሐይማኖተኞች ይገደሉ ዘንድ በዚህ ምድር ላይ የሰሩት አንዳች ነገር አለን? በእርግጥ የለም! ነገር ግን የዓለም ሐይማኖተኞች በሙሉ የጌታ አምላክ ልጆችን ለመግደል በመዶለት ተባብረዋል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች በእነዚህ ነፍሰ ገዳዮች ላይ ማውረዱ ትክክልና የእግዚአብሄርንም ጽድቅ የሚገልጥ ነው፡፡
 
ቁጥር 3፡- ደግመውም፡- ሃሌ ሉያ አሉ፤ ጢስዋም ለዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል፡፡
ቅዱሳን ጌታ አምላክን በአየር ላይ የሚያመሰግኑት ከበጉ ከኢየሱስ ጋር የሚያደርጉት ሰርግ ስለተቃረበ ነው፡፡
‹‹ጢስዋም ለዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል፡፡›› ይህ የሚያመለክተው እግዚአብሄር ባወረዳቸው በሰባቱ ጽዋዎች ታላላቅ መቅሰፍቶች ከወደመችውና ከተቃጠለችው ከዚህች ዓለም የሚወጣውን ጢስ ነው፡፡ ይህም ይህች ዓለም ጥፋትዋ አደገኛና ዘላለማዊ በመሆኑ ከፍርስራሽዋ ከቶ እንዳታገግም ያሳየናል፡፡
 
ቁጥር 4፡- ሀያ አራቱም ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች በፊታቸው ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለእግዚአብሄር፡- አሜን፤ ሃሌ ሉያ እያሉ ሰገዱለት፡፡
ቅዱሳን ከጌታ ኢየሱስ ጋር የሚያደርጉት የጋብቻ ቀን የመድረሱ እውነታ ክቡር ሁነት በመሆኑ በሰማይ ያሉት ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ጌታ አምላክ በመስገድ ያመሰግኑታል፡፡ የእግዚአብሄር ባሮች በሙሉ ጌታ አምላክን በአየር ላይ የሚያመሰግኑት ለዚህ ነው፡፡
 
ቁጥር 5፡- ድምጽም፡- ባሪያዎቹ ሁሉ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆችም ሆይ አምላካችንን አመስግኑ ሲል ከዙፋኑ ወጣ፡፡
በጉ ከቅዱሳን ጋር የሚያደርገው የሰርግ ቀን ጌታ አምላክን በማመን ለዳኑት የእርሱ አገልጋዮችና ቅዱሳን ሁሉ ቋንቋ የማይገልጠው ታላቅ ደስታ ስለሆነ ከዙፋኑ የሚመጣው ድምጽ ሁሉም እግዚአብሄርን እንዲያመሰግኑ ያዛቸዋል፡፡ አሁን የእግዚአብሄር ባሮችና ቅዱሳን ሁሉ የሚደሰቱበትና ጌታን የሚያመሰግኑበት ጊዜ መጥቷል፡፡
 
ቁጥር 6፡- እንደ ብዙ ሕዝብም ድምጽ፣ እንደ ብዙ ውሃዎችም ድምጽ፣ እንደ ብርቱም ነጎድጓድ ድምጽ ያለ ድምጽ ሰማሁ እንዲህ ሲል፡- ሃሌ ሉያ፤ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና፤
ይህ ቁጥር ጌታ አምላክ የሚነግስበት ጊዜ ሲደርስ የእርሱ ቅዱሳኖችና ባሮች ዘላለማዊ ሰላማቸውን፣ ደስታቸውንና እንደ ወንዝ የሚፈስሱትን ባርኮቶች ለመቀበል ጊዜያቸው ይሆናል፡፡ ጌታ አምላክን የሚያመሰግኑት ለዚህ ነው፡፡ ቅዱሳን ታላላቆቹ መቅሰፍቶች በዚህ ምድር ላይ መውረዳቸውን እየቀጠሉ ሳሉ አምላካችንን በአየር ላይ የሚያመሰግኑት በጌታ አምላክ የሚነግሱበት ዘመን ስለመጣ ነው፡፡ ይህ ማለት አሁን ጊዜው እግዚአብሄር ቅዱሳኖቹን የሚያከብርበት ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የቅዱሳን የምስጋና ድምጽ ልክ እንደ ነጎድጓድና እንደ ብዙ ውሆች ድምጽ ነው፡፡ ስለዚህ የጌታ መንግሥት የሰርግ እራት የሚጀምረው ውብ በሆነው የቅዱሳን ምስጋና ነው፡፡
 
ቁጥር 7፡- የበጉ ሰርግ ስለደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ፤ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ፡፡
አሁን እግዚአብሄር ያመጣቸው የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች እየተጠናቀቁ በመሆናቸው ይህ ቁጥር ቅዱሳን ሁሉ የሚደሰቱበትና ሐሴት የሚያደርጉበት ጊዜ እንደመጣ ይነግረናል፡፡ እዚህ ላይ ቅዱሳን የሚደሰቱትና ሐሴት የሚያደርጉት ጌታችንን የሚያገቡበትና በመንግሥቱ ውስጥ የሚኖሩበት ቀን ስለደረሰ ነው፡፡ ጌታ አምላካችን ከቅዱሳን ጋር አብሮ ለመኖር አዲሱን ሰማይና ምድር ቅድስቲቱን ከተማና ገነቶችዋን፣ ክብርንና ብልጥግና ሁሉ አዘጋጅቷል፡፡ እነርሱን ብቻ እየጠበቀ ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቅዱሳን ለዘላለም ከጌታ ጋር ይነግሳሉ፡፡
 
ቁጥር 8፡- ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጎናጸፍ ተሰጥቶአታል፡፡ ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ ነውና፡፡
ጌታ ለቅዱሳን ከጥሩ በፍታ የተሰሩ አዳዲስ ልብሶችን ሰጥቶዋቸዋል፡፡ ጌታ አምላክን እያገለገለ የሚኖር ማንኛውም ሰው እነዚህን ልብሶች ይጎናጸፋል፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር ለቅዱሳን የሰማይን ልብሶች ያለብሳቸዋል፡፡ እነዚህ ከጥሩ የተልባ እግር የተሰሩ ልብሶች በላቦት የረሰረሱ አይደሉም፡፡ ይህም እኛ የበጉ ሙሽሮች የሆንነው በሰው ሰራሽ ጥረቶቻችንና ብቃቶቻችን ሳይሆን ጌታ አምላክ በሰጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ላይ ባለን እምነታችን የመሆኑን እውነታ ይነግረናል፡፡
ጸረ ክርስቶስ ከለበሰው ቀይና ሐምራዊ ልብስ ጋር በግልጽ ሲነጻጸር ይህ ጥሩ የበፍታ ልብስ ለካህናትና ለነገሥታት የሚሆኑ ልብሶችን ለመስራት የሚያገለግል የከበረ በፍታ ነው፡፡ ከላቦች ነጻ የሆነው ነጩና ጥሩው በፍታ የእግዚአብሄርን ጸጋና ጽድቅ የሚለብሱ ሰዎች አሁን የእርሱ ሕዝብ መሆናቸውን ያሳየናል፡፡
‹‹ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ ነውና›› የሚለው ሐረግ ጌታ አምላካችን በሰጠው የደህንነት ጸጋ ቅዱሳን የሆኑ ሰዎች እምነታቸውን ለመጠበቅ በጸረ ክርስቶስና በተከታዮቹ ሰማዕት በመሆን ለእግዚአብሄር ክብርን ሰጥተዋል ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ‹‹የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ›› የሚያመለክተው የሕጉን ጽድቅ ሳይሆን ክቡር እምነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ቅዱሳን የተገደሉበትን ሰማዕትነታቸውን ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ የመጨረሻው ዘመን የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽሮች በሙሉ በጌታ ያላቸውን የእምነታቸውን ንጽህና ለመጠበቅ ሲሉ በዚህ ምድር ላይ ሳሉ ጸረ ክርስቶስንና ተከታዮቹን ተቃውመው የተዋጉት ሰማዕታቶች ናቸው፡፡
ቅዱሳን ሁሉ ሰማዕት ለሚሆኑበት እምነታቸው ይዘጋጁ ዘንድ በታላቁ መከራ የመጀመሪያ ሦስት ዓመታት ተኩል ውስጥ መመገብ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሦስት ዓመታት ተኩል ሲያልፉ በእርግጥም ሰማዕት ይሆናሉና፡፡
 
ቁጥር 9፡- እርሱም፡- ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው ብለህ ጻፍ አለኝ፡፡ ደግሞም፡- ይህ የእግዚአብሄር እውነተኛ ቃል ነው አለኝ፡፡
የእግዚአብሄር መቅሰፍቶች በዚህ ዓለም ላይ ሳይጠናቀቁ ጌታ አምላክ ቅዱሳንን ሁሉ ወደ በጉ ሰርግ እራት (በጌታ ወደተገነባችውና ወደምትገዛው መንግሥት) በመጋበዝ በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ እንዲኖሩ ይፈቅድላቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጋበዙት ብጹዓኖች ናቸው፡፡ አምላካችን ይህንን የተስፋ ቃል መፈጸም እንደማይሳነው ነግሮናል፡፡ ይህ ቀን ቅዱሳን ጌታን በሚያገቡበት ጊዜ በመጨረሻ ይመጣል፡፡ ጌታችን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ የነጹትን ሙሽሮቹን ለመውሰድ ወደዚህ ምድር ይመለሳል፡፡ ጌታም በመንግሥቱ ውስጥ ከሙሽሮቹ ጋር ከዘላለም እስከ ዘላለም ይኖራል፡፡
ቅዱሳን ከጌታ ጋር የሚያደርጉት ጥምረት የሚጠናቀቀው በክርስቶስ ሲነጠቁ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በሺህ ዓመት መንግሥት ማለቂያ የሌለውን ክብርና ሽልማቶች ይቀበላሉ፡፡ ሃሌሉያ! የእርሱ ሕዝብ ያደረገንን ጌታ አምላክ አመሰግናለሁ፤ አወድሳለሁም፡፡
 
ቁጥር 10፡- ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ፡፡ እርሱም፡- እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባርያ ነኝ፡፡ ለእግዚአብሄር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ፡፡
ቅዱሳኖች እነዚህን ክብሮች ሁሉ መስጠት ያለባቸው ለጌታ አምላክ ነው፡፡ ከቅዱሳኖች ስግደትንና ምስጋናን መቀበል የሚኖርበት ሥላሴ አምላክ ብቻ ነው፡፡
‹‹የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና›› የሚለው ሐረግ የኢየሱስ ምስክርና ትንቢት የሚመጣው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ነው ማለት ነው፡፡
 
ቁጥር 11፡- ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆም አምባላይ ፈረስ፤ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፤ በጽድቅም ይፈርዳል፤ ይዋጋልም፡፡
የመጨረሻው ዘመን ሲመጣ ጌታ አምላካችን በነጭ ፈረስ እየጋለበ ሰይጣንን በጽድቁ በመዋጋት በጥልቁ ጉድጓድ በእሳት ባህር ውስጥ በመጣል ያስረዋል፡፡
እዚህ ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ‹‹የታመነ›› እና ‹‹እውነተኛ›› ነው፡፡ ‹‹የታመነ›› የሚለው ቃል ክርስቶስ የሚታመን ነው ማለት ሲሆን እውነተኛነቱንና ተዓማኒነቱን ይገልጣል፡፡ ‹‹እውነተኛ›› የሚለው ቃልም ከውሸት የጸዳ ነው ማለት ሲሆን ክርስቶስ ጻድቅ በሆነው የእግዚአብሄር ፍርድ ጸረ ክርስቶስን እንደሚያሸንፍ ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 12፡- ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፡፡ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፤ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፡፡
የጌታ ዓይኖች ‹‹እንደ እሳት ነበልባል›› መሆናቸው እርሱ በሁሉም ላይ የመፍረድ ሥልጣን እንዳለው ይነግረናል፡፡ በሌላ አነጋገር ‹‹በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ›› የሚለው ሐረግ ጌታችን ሁልጊዜም ከእርሱ ጋር በሚያደርገው ውጊያው ሰይጣንን ያሸንፋል ማለት ነው፡፡ እርሱ ሁሉን አዋቂና ሁሉን የሚገዛ አምላክ ነውና፡፡
 
ቁጥር 13፡- በደምም የተረጨ ልብስ ተጎናጽፎአል፤ ስሙ የእግዚአብሄር ቃል ተብሎአል፡፡
ጌታችን እርሱን የተቃወሙትን እነዚህን ጠላቶቹን በአስፈሪው ቁጣው በመፍረድ ለቅዱሳኖቹ ይፈርድላቸዋል፡፡ ይህ አምላክ ከራሱ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ማንም አይደለም፡፡ ጌታችን በቃሉ ውስጥ በሰጠው ተስፋ መሰረት የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር በመምጣት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለመሸከም በዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ እነዚያን ሐጢያቶችም በመስቀል ላይ ተሸከመ፡፡ የሰውን ዘር ሐጢያቶችም በሙሉ አስወገደ፡፡
‹‹በደም የተረጨ ልብስ፡፡›› ይህ ደም የሚያመለክተው የራሱን የኢየሱስን ደም አይደለም፡፡ አስፈሪውን የቁጣውን ፍርድ በእነርሱ ላይ በማምጣቱና እግሮቹ በሥልጣን እነርሱን በመርገጣቸው በጌታ ልብስ ላይ የተረጩትን የጠላቶቹን ደም ነው፡፡
‹‹የእግዚአብሄር ቃል›› የሚያመለክተው የኢየሱስን ጠባይ ነው፡፡ ጌታችን ብርቱ በሆነው ቃሉ ሁሉን ነገር ስለሚያደርግ ‹‹የእግዚአብሄር ቃል›› ተብሎ ተሰይሞዋል፡፡
 
ቁጥር 14-16፡- በሰማይም ያሉት ጭፍራዎች ነጭና ጥሩ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በአምባላዮች ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር፡፡ አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል፤ እርሱም በብረት በትር ይገዛቸዋል፤ እርሱም ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሄርን የብርቱ ቁጣውን ወይን መጥመቂያ ይረግጣል፡፡ በልብሱና በጭኑም የተጻፈበት፡- የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ የሚል ስም አለው፡፡
የጌታ አምላክ ጭፍሮች በእርሱ የከበረ ሞገስ ተሸፍነው ሁልጊዜም የእርሱን ሥራዎች ያገለግላሉ፡
እግዚአብሄር ከአፉ በሚወጣው ቃሉ ይህንን ዓለም ይፈርዳል፡፡ ጌታችን ሁልጊዜም በአፉ ቃል ተስፋ ሰጥቶናል፡፡ እርሱ ሁልጊዜም እነዚህን ተስፋዎች በሐይሉ ይፈጽማቸዋል፡፡ ዓለምን የሚፈርደውና ሰይጣንን የሚያጠፋው የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
 
ቁጥር 17፡- አንድም መልአክ በፀሐይ ውስጥ ቆሞ አየሁ፡፡ በሰማይም መካከል ለሚበሩ ወፎች ሁሉ፡- መጥታችሁ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሄር እራት ተከማቹ ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፡፡
ይህ ዓለም ከሰይጣንና ከተከታዮቹ ጋር አብሮ በኢየሱስ ክርስቶስ ይጠፋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን ዓለም ጥፋት የእግዚአብሄር ታላቅ ድግስ ብሎ ገልጦታል፡፡
 
ቁጥር 18፡- መጥታችሁ የነገሥታትን ሥጋና የሻለቃዎችን ሥጋ፣ የብርቱዎችንም ሥጋ፣ የፈረሶችንም በእነርሱም የተቀመጡትን ሥጋ፣ የጌታዎችንና የባሪያዎችንም፣ የታናናሾችንና የታላላቆችንም ሁሉ ሥጋ እንድትበሉ፡፡
ይህ ቃል የጌታ አምላክ ታላላቅ መቅሰፍቶች በሚጠናቀቁበት ጊዜ መላው ዓለምና በእርሱ ውስጥ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው ስለሚሞት በሰማይ የሚበሩ ወፎች ሬሳዎቻቸውን በመብላት እንደሚጠግቡ ይነግረናል፡፡ ይህንን የሚያደርጉት እግዚአብሄር የሰባቱን ጽዋዎች ታላላቅ መቅሰፍቶች በዚህ ዓለም ላይ ስላወረደ ነው፡፡ ጌታችን እንዲህ በማለት ነግሮናል፡- ‹‹በድን ባለበት በዚያ አሞሮች ይሰበሰባሉና፡፡›› (ማቴዎስ 24፡28) በመጨረሻው ዘመን በሚኖረው ዓለም ላይ የሚወርደው ጥፋት፣ ሞትና በሐጢያተኞች ላይ የሚደርሰው የሲዖል ቅጣት ብቻ ነው፡፡ ቅዱሳን ግን በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ በመንገስ ይባረካሉ፡፡
 
ቁጥር 19፡- በፈረሱ የተቀመጠውን ጭፍራዎቹንም ይወጉ ዘንድ አውሬውና የምድር ነገሥታት ጭፍራዎቻቸውም ተከማችተው አየሁ፡፡
የሰይጣን ባርያ የሆነው ጸረ ክርስቶስና የእርሱ ተከታዮች የእግዚአብሄርን ባሮችና ቅዱሳኖችን በመቃወም ድል ሊያደርጉዋቸው እስከ መጨረሻው እስትንፋሳቸው ድረስ ይቀጥላሉ፡፡ ነገር ግን ጌታችን የነገሥታት ንጉሥ ስለሆነ ጸረ ክርስቶስንና ሐሰተኛውን ነቢይ በመያዝ ወደ እሳት ባህር ይጥላቸውና አገልጋዮቻቸውን በሙሉ በቃሉ ሰይፍ ይገድላቸዋል፡፡
 
ቁጥር 20፡- አውሬውም ተያዘ፤ በእርሱም ፊት ተዓምራትን እያደረገ የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትን ለምስሉም የሰገዱትን ያሳተ ሐሰተኛው ነቢይ ከእርሱ ጋር ተያዘ፤ ሁለቱም በሕይወት ሳሉ በዲን ወደሚቃጠል ወደ እሳት ባህር ተጣሉ፡፡
እዚህ ላይ ‹‹አውሬው›› የሚያመለክተው ጸረ ክርስቶስን ነው፡፡ ‹‹ሐሰተኛው ነቢይ›› ተዓምራቶችንና ምልክቶችን በማድረግ ሰዎችን የእውነትን ቃል ከማመን ያራቃቸው የጸረ ክርስቶስ ባርያ ነው፡፡ ጌታ አምላካችን ሰይጣንን፣ አውሬውን (ጸረ ክርስቶስን)፣ ሐሰተኛውን ነቢይና ለጸረ ክርስቶስ ምስል የሰገዱትን፣ እግዚአብሄርን፣ ቅዱሳንና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የተቃወሙትን ያጠፋቸዋል፡፡
‹‹በዲን የሚቃጠል የእሳት ባህር›› የሚያመለክተው ሲዖልን ነው፡፡ ሲዖል ከጥልቁ ጉድጓድ ይለያል፡፡ ጥልቁ ጉድጓድ የሰይጣን ሐይሎች ለጊዜው የሚሰሩበት ስፍራ ሲሆን ‹‹የእሳት ባህር›› የዘላለም ቅጣት የሚቀጡበት ስፍራ ነው፡፡ በተለይ እሳትና ዲን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሄር ቅጣትና ፍርድ መሳርያ ሆነው ሁልጊዜም አገልግለዋል፡፡
ይህ ዓለም ከጠፋ በኋላ ጌታችን ከቅዱሳኑ ጋር ወደዚህ ምድር ተመልሶ በመጀመሪያ ሰይጣንንና አገልጋዮቹን ያጠፋል፡፡ ከዚያም የክርስቶን መንግሥት ይመሰርታል፡፡ ያን ጊዜ ቅዱሳን ለመጭዎቹ ሺህ ዓመታት በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ከጌታ ጋር እየኖሩ ይነግሳሉ፡፡
 
ቁጥር 21፡- የቀሩትም በፈረስ ላይ ከተቀመጠው ከአፉ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ፤ ወፎችም ሁሉ ከሥጋቸው ጠገቡ፡፡
ይህ ዓለም የተፈጠረው ከጌታ አምላካችን አፍ በወጣ ቃል ነበር፡፡ ልክ እንደዚሁ የእግዚአብሄርም ጠላቶች ሁሉ ከእርሱ አፍ በሚወጣው የፍርድ ቃል ይጠፋሉ፡፡ ያን ጊዜ የክርስቶስ መንግሥት በዚህ ምድር ላይ ትመሰረታለች፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን ተስፋቸወን በክርስቶስ መንግሥት ላይ ማኖርና ሰይጣንን፣ ጸረ ክርስቶስንና የእርሱን ተከታዮች በመዋጋትና ሰማዕትነታቸውን በእምነት በመቀበል ለእግዚአብሄር ክብርን መስጠት አለባቸው፡፡