Search

တရားဟောချက်များ

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[20-2] ከሞት ወደ ሕይወት መሻገር የምንችለው እንዴት ነው? ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 20፡1-15 ››

ከሞት ወደ ሕይወት መሻገር የምንችለው እንዴት ነው?
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 20፡1-15 ››

እግዚአብሄር ይህንን ዓለም በሚያጠፋበትና በምትኩም አዲስ ሰማይና ምድር በሚሰጠን ጊዜ ከዚህ ቀደም በዚህ ምድር ላይ የኖረውንና በመቃብሩ ውስጥ ያንቀላፋውን እያንዳንዱን ሐጢያተኛ እንደሚያስነሳው ይነግረናል፡፡ እዚህ ላይ ቁጥር 13 እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሲዖልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፡፡›› ውሃ ውስጥ የሰመጠ ሰው አካል በአሳ መበላቱ የማይቀርለት ሲሆን በእሳት ተቃጥሎ የሞተ ሰው አካል ደግሞ ዳግመኛ ማን መሆኑ እስከማይታወቅ ድረስ ምንም ቅርጽ አይኖረውም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን እዚህ ላይ የመጨረሻው ዘመን ሲመጣ እግዚአብሄር ሁሉንም በሕይወት እንደሚያነሳቸውና ሰይጣን የዋጣቸው፣ በሲዖል የተገደሉ ወይም በእሳት ተቃጥለው የሞቱ ቢሆኑም ወደ ሰማይ ወይም ወደ ሲዖል ይሰዳቸው ዘንድ እንደሚፈርድባቸው ይነግረናል፡፡
ወደ ዘላለማዊው መንግሥተ ሰማይ የሚገቡ ሰዎች ስሞች የተጻፈበት የሕይወት መጽሐፍ በእግዚአብሄር ፊት ተዘርግቷል፡፡ ወደ ሲዖል የሚጣሉት ሰዎች ስሞችና ሐጢያቶች የተመዘገቡበት የምግባራት መጽሐፎችም እንደዚሁ አሉ፡፡ በእነዚህ የምግባራት መጽሐፎች ውስጥ ሰው በዚህ ምድር ላይ ሲኖር በነበረበት ጊዜ የሰራቸው ሐጢያቶች በሙሉ ተጽፈዋል፡፡ እነዚህን ነገሮች ሁሉ በቸርነቱ የወሰነው እግዚአብሄር ነው፡፡
 

ጌታ ሁለት ዓይነት መጽሐፎች አሉት፡፡

እግዚአብሄር ቀድሞውኑም በራሱ የጽድቅ መስፈርት መሰረት ሰዎችን በሁለት ልዩ የጋራ መደቦች መደቦዋቸዋል፡፡ ሙታን በሙሉ ትንሳኤን አግኝተው በሁለቱ መጽሐፎቹ ፊት እንዲቆሙና እንዲፈረድባቸው በእግዚአብሄር ተወስኖዋል፡፡ በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈው በዚህ ምድር ላይ ሳሉ በኢየሱስ ያመኑ፣ የሐጢያቶቻቸውን ስርየት የተቀበሉና ሰማይ እንዲገቡ የተወሰነላቸው ሰዎች ስሞች ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የመጨረሻ ፍርድ የሚወሰነው የአንድ ሰው ስም ከሁለቱ መጽሐፎች በየትኛው ላይ ተጽፎዋል በሚለው ላይ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር ማን ሰማይ እንደሚገባና ማን ሲዖል እንደሚጣል አስቀድሞ ወስኖዋል፡፡

በመሆኑም እግዚአብሄር ሙታንን ሁሉ ዳግመኛ ወደ ሕይወት ያስነሳቸውና ስሞቻቸው ከሁለቱ መጽሐፎች ውስጥ በየትኛው ላይ እንደተጻፈ ያያል፡፡ ከዚያም ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ የተጻፉትን ወደ ሰማይ ይልካቸዋል፡፡ በአንጻሩ ስሞቻቸው በዚህ የሕይወት መጽሐፍ ላይ የማይገኝ ሰዎች ግን ወደ ሲዖል ይወረወራሉ፡፡ እግዚአብሄር የወሰናቸውን እነዚህን የጸኑ እውነታዎች ማወቃችንንና ማመናችንን ማረጋገጥ አለብን፡፡ 
እግዚአብሄር ማን ወደ ሰማይ ማን ደግሞ ወደ ሲዖል እንደሚላክ ለመወሰን ሙታንን ሁሉ አስነስቶ ይፈርድባቸዋል፡፡ እግዚአብሄር ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ወይም በምግባራት መጽሐፎች (በፍርድ መጽሐፎች) ውስጥ በተጻፈው መሰረት ይፈርድባቸው ዘንድ ተወስኖዋል፡፡
እግዚአብሄር ሁሉም በፊቱ ይቆሙ ዘንድ አስቀድሞ ያቆማቸው ሁለት ስፍራዎች አሉ፡፡ እነርሱም ሰማይና ሲዖል ናቸው፡፡ እሳትና ዲን የሚንቀለቀሉበት የእሳት ባህር ነው፡፡ እግዚአብሄር ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ያልተጻፉ ሰዎች ወደ እሳት ባህር እንዲጣሉ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉ ደግሞ ሰማይ እንዲገቡ ወስኖዋል፡፡
በሰማይ የሕይወት ዛፍ በእያንዳንዱ ወቅት ላይ የተመረኮዙ አስራ ሁለት የተለያዩ ፍሬዎች ይዞ በሕይወት ውሃ ወንዝ አጠገብ ቆሞዋል፡፡ በዚህ ውብ ሰማይ ቅዱሳን በሽታም ሆነ ሕመም አይኖርባቸውም፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሄር ጋር ለዘላለም በደስታ ይኖራሉ፡፡ እግዚአበሄር ይህንን ሰማይ ለቅዱሳን ለመስጠት በመወሰኑ እውነታ ማመን አለብን፡፡
በሌላ በኩል በኢየሱስ የማያምኑ ሰዎች ስሞቻቸው በምግባራት መጽሐፎች ላይ ተጽፈዋል፡፡ ሐጢያተኞች በዚህ ምድር ላይ ሳሉ የሰሩዋቸው ሥራዎች በሙሉ በእነዚህ መጽሐፎች ውስጥ ስለተጻፉ በእነዚህ መጽሐፎች ውስጥ ለተመዘገቡት ሐጢያቶቻቸውና በኢየሱስ ባለማመን ለሰሩት ሐጢያታቸው ይቀጣቸው ዘንድ ሁሉንም ወደ እሳት ባህር እንደሚጥላቸው ይነግረናል፡፡ እዚህ ላይ ወሳኝ ጠቀሜታ ያለው ነገር የእናንተና የእኔ ስሞች በየትኛው መጽሐፍ ላይ የተጻፉ መሆናቸው ነው፡፡
በዚህ ምድር ላይ ስንኖር ሕይወት በዚህ ምድር ላይ ምሉዕ አለመሆኑን መረዳት አለብን፡፡ መዝሙረ ዳዊት 90፡10 እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፡፡ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፤ ከእኛ ቶሎ ያልፋልና እኛም እንገሰጻለንና፡፡›› በዚህ ምድር ላይ 70 ወይም 80 ዓመታትን ብንኖር እንኳን ፈጥኖ ወይም ዘግይቶ ሁላችንም በእግዚአብሄር ፊት እንቆማለን፡፡ በመጨረሻ እንዲህ በጌታችን ፊት በምንቆምበት ጊዜ ቁም ነገሩ ስሞቻችን በየትኛው መጽሐፍ ላይ-- በሕይወት መጽሐፍ ይሁን ወይም በምግባራት መጽሐፎች (በፍርድ መጽሐፎች) መጻፋቸው ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ ሰማይ መግባታችንን ወይም ወደ እሳት ባህር መጣላችንን የሚወስነው ይህ ይሆናልና፡፡ ሕይወት በዚህ ምድር ላይ ላይ ሁሉም ነገር ማለት እንዳልሆነ መረዳት ላይ መድረስ አለብን፡፡
 


ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ የተጻፉላቸው ሰዎች፡፡

 
ሉቃስ 16፡19-26ን እንመልከት፡- ‹‹ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለጠጋ ሰው ነበረ፡፡ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር፡፡ አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሃ በቁስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፡፡ ከባለጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፡፡ ውሾች እንኳ መጥተው ቁስሎቹን ይልሱ ነበረ፡፡ ድሃውም ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፡፡ ባለጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ፡፡ በሲዖልም በስቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ፡፡ እርሱም እየጮኸ፡- አብርሃም አባት ሆይ ማረኝ በዚህ ነበልባል እሰቃያለሁና፡፡ የጣቱን ጫፍ በውሃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ አለ፡፡ አብርሃም ግን፡- ልጄ ሆይ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደተቀበልህ አስብ፤ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፡፡ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል፤ አንተም ትሰቃያለህ፡፡ ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጓል አለ፡፡››
ኢየሱስ በዚህ ምንባብ ሰማይና ሲዖል በትክክል እንዳሉ ያስተምረናል፡፡ በዚህ ምንባብ ውስጥ እንደተጠቀሰው ባለጠጋ ሰው ብዙ ሰዎች ሰማይና ሲዖል ስለ መኖራቸው አያምኑም፡፡ አብርሃም የእምነት አባት ነው፡፡ እዚህ ላይ ለማኙ አልዓዛር ወደ አብርሃም እቅፍ ተወሰደ ሲል አብርሃም በእግዚአብሄር ቃል እንዳመነ ሁሉ አልዓዛርም ኢየሱስን አዳኙ አድርጎ በማመን የሐጢያቶቹን ስርየት ተቀብሎ ሰማይ ገብቷል ማለት ነው፡፡ እኛ ሁላችን በዚህ ዓለም ላይ ስንኖር በአልዓዛርና በባለጠጋው ሰው ዕጣ ፈንታዎች ላይ ማሰላሰልና ማሰብ ያስፈልገናል፡፡
እግዚአብሄር በዚህ ዓለም ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው በዚህ ምድር ላይ የሚኖረው ሕይወት ሁሉንም ነገር ማለት እንዳልሆነ ይነግረናል፡፡ ሰው በዚህ ዓለም ላይ ምንም ያህል ቢለፋም ቢበዛ መኖር የሚችለው 70 ወይም 80 ዓመት መሆኑ ብቻ ሳይሆን በመጨረሻ የሚተርፈው ነገር ቢኖር ልፋትና ሐዘን ብቻ መሆኑም ነው፡፡
ስለዚህ ሕይወታችንን ስንኖር ሁላችንም ለወዲያኛው ሕይወታችን መዘጋጀት አለብን፡፡ ልጆቻችንም ደግሞ ወደ መልካሙ ስፍራ መሄድ ይችሉ ዘንድ እምነታችንን ለእነርሱ ማስረከብም አለብን፡፡ ሰው በዚህ ምድር ላይ ኖሮ ሲያበቃ በመጨረሻ በእግዚአብሄር ፊት የሚቆመው በእርሱ ሊፈረድበትና ወደ እሳት ባህር ሊጣል መሆኑ ምንኛ አሳዛኝ ይሆን?
እግዚአብሄር የወሰነውን ማንም ሊለውጠው አይችልም፡፡ ስሞቻቸው በምግባራት መጽሐፎች ውስጥ የተጻፉላቸው ሁሉ ወደ እሳት ባህር ይጣላሉ፡፡ እኛ ከእሳቱ ባህር ማምለጥ የምንችልበት አንድ መንገድ ብቻ ያለ ሲሆን ስሞቻችንን በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ መጻፋቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ከእሳት ባህር ለማምለጥ ስሞቻችን በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ከመጻፍ በስተቀር ሌላ መንገድ የለም፡፡
ታዲያ ስሞቻችን በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ መጻፍ የሚችሉት እንዴት ነው? አልዓዛር ወደ አብርሃም እቅፍ እንደተወሰደ ሁሉ እኛም በቃሉ አማካይነት የእግዚአብሄርን የጽድቅ ምግባር በማወቅና በማመን የሐጢያቶቻችንን ስርየት መቀበል አለብን፡፡ (ሮሜ 5፡18) ሰማይ መግባት የምንችለው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ስሞቻችን በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይጻፉ ዘንድ በኢየሱስ ማመን አለብን፡፡ ኢየሱስ ራሱ አምላክና መሲሃችንም ነው፡፡ መሲህ ማለት በሐጢያት ውስጥ የወደቁትን የሚያድን ማለት ነው፡፡ በሐጢያቶቻችን ተፈርዶብን ወደ እሳት ባህር ልንጣል የነበርነውን ሊያድነን የሚችለው ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡
በዚህ ምድር ላይ በእግዚአብሄር ፊት መቼም ሐጢያት ሰርቶ የማያውቅና በመካከለችንም 100 እጅ በምግባሮቹ ጻድቅ የሆነ ማነው? ማንም የለም! ሁላችንም በጉድለቶች የተሞላን ስለሆንን በሐጢያት ውስጥ ከመውደቅ በቀር ማድረግ የምንችለው ነገር የለም፡፡ ለእነዚህ ሐጢያቶቻችንም ሁላችንም ታስረን ወደ እሳት ባህር መጣል ይኖርብናል፡፡
በዚህ ምድር ላይ በእግዚአብሄር ፊት መቼም ሐጢያት ሰርቶ የማያውቅና በመካከላችንም 100 እጅ በምግባሮቹ ጻድቅ የሆነ ማነው? ማንም የለም! ሁላችንም በጉድለቶች የተሞላን ስለሆንን በሐጢያት ውስጥ ከመውደቅ በቀር ማድረግ የምንችለው ነገር የለም፡፡ ለእነዚህ ሐጢያቶቻችንም ሁላችንም ታስረን ወደ እሳት ባህር መጣል ይኖርብናል፡፡
እግዚአብሄር ግን በሐጢያቶቻችን የተነሳ ወደ እሳት ባህር ከመጣል በቀር ምንም ማድረግ የማንችለውን እኛን ለማዳን ኢየሱስ ወደዚህ ምድር ላከው፡፡ ‹‹ኢየሱስ›› የሚለው ስም ‹‹ሕዝቡን ከሐጢያቶቻቸው የሚያድን›› ማለት ነው፡፡ (ማቴዎስ 1፡21) ስለዚህ ሰማይ መግባት የምንችለው ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በጽድቅ ምግባሩ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ያዳነን የመሆኑን እውነት ስናምን ብቻ ነው፡፡
 
 
ታዲያ ወደ እሳት ባህር የሚጣለው ማን ይሆናል? 

ዮሐንስ 21፡8 ወደ እሳት ባህር የሚጣለው ማን እንደሆነ ይነግረናል፡- ‹‹ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ፣ የርኩሳንም፣ የነፍስ ገዳዮችም፣ የሴሰኛዎችም፣ የአስማተኛዎችም፣ ጣዖትንም የሚያመልኩ፣ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባህር ነው፡፡ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው፡፡››
በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹የሚፈሩ›› የሚላቸው እነማንን ነው? ይህ የሚያመለክተው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ከመቀበል የጎደሉትን የስም ክርስቲያኖችን ነው፡፡ ስለዚህ በሆነ መንገድ በኢየሱስ ቢያምኑም እንኳን በእግዚአብሄር ፊት ፈሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ እሳት ባህር ይጣሉ ዘንድ እግዚአብሄር ወስኖዋል፡፡ እግዚአብሄር የማያምኑትን፣ ርኩሳኖችን፣ ነፍሰ ገዳዮችን፣ ሴሰኛዎችን፣ አስማተኞችን፣ ጣዖታትን የሚመልኩና ሐሰተኞችን ሁሉ ወደ ሲዖል እንዲጣሉ ወስኖዋል፡፡
በአፈ ታሪክ በኮርያ ብዙ ጣዖት አምላኪዎች ነበሩ፡፡ አሁም ድረስ እግዚአብሄር ራሱ በፈጠራቸው ፍጥረታቶቹ ምስሎች ፊት ተንበርክከው ለእነርሱ የሚጸልዩ ሰዎችን ማየት ያልተለመደ አይደለም፡፡ ሰዎች ይህንን የሚያደርጉት አላዋቂና ሞኞች ስለሆኑ ነው፡፡ ሰዎች አምላክ የሆኑ ይመስል ሕይወት ለሌላቸው ምስሎች መስገዳቸውን ይጠላል፡፡
እግዚአብሄር ሰውን በራሱ አምሳል ፈጠረው፡፡ (ዘፍጥረት 1፡27) የሰው ዘርም የፍጥረት ሁሉ የበላይ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ማመን የሚገባን ለዚህ ነው፡፡ እኛ የእግዚአብሄርን አምሳል ስለያዝን እግዚአብሄር ራሱ ለዘላለም እንደሚኖር ለዘላለም እንኖራለን፡፡ ከሞትን በኋላ የሚጠብቀን ዘላለማዊ ዓለም አለ፡፡ እግዚአብሄር ብቸኛ ለሆነው ዘላለማዊ አምላክ እንድንሰግድ የነገረን ለዚህ ነው፡፡ የእግዚአብሄር የራሱ ተራ ፍጥረታት ፊት ስናጎነብስ ምን ይፈጠራል? በእግዚአብሄር ፊት ትልቅ ሐጢያት እየሰራን ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር አጥብቆ የሚጠላውን ጣዖት አምልኮ እየተገበርን ነውና፡፡ የሰው ዘር እንዲህ ሞኝና ገልቱ ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህ ዓይነት የተዛባ እምነት ያላቸው ሰዎች በሙሉ ወደ እሳት ባህር ውስጥ እንደሚጣሉ እግዚአብሄር መወሰኑን መረዳት አለብን፡፡ ወደ ሲዖል የሚጣሉ ሰዎች ሁለት ጊዜ ይሞታሉ፡፡ ይህ እግዚአብሄር ራሱ የወሰነው ነው፡፡ የመጀመሪያው ሞት የሚመጣው በዚህ አሰልቺ ዓለም ላይ በመከራ በተሞላው የምድር ሕይወታቸው ፍጻሜ ላይ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ በመጀመሪያ በአራት እግሮቻቸው የሚኖሩ ሰዎች ቀጥሎ በሁለት እግሮቻቸው በመጨረሻም በሦስት እግሮቻቸው ኖረው ፍጻሜያቸው ሞት የሆነው ሌሎች ሳይሆኑ ሰዎች ራሳቸው ናቸው ይባላል፡፡
ሰዎች በዚህ መንገድ አንድ ጊዜ ከሞቱ በኋላ ሐጢያተኞች ሆነው በእግዚአብሄር ፊት ሲቆሙ ሁሉም ፍርዳቸውን ይጋፈጣሉ፡፡ ከቶውኑም ፍጻሜ የሌለው ነገር ግን ለዘላለም የሚዘልቀው ሁለተኛው ሞት ወደ እሳት ባህር በመጣል መልክ የሚጎበኛቸው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ የእሳት ባህር ውስጥ ቢሞቱ ቢያንስ ከስቃዩ ነጻ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ ስፍራ ከልባቸው ሊሞቱ ቢመኙም ሞት ከእነርሱ ይሸሻል፡፡
ሁሉም ሰው ፈጽሞ ሞትን ሳያይ ለዘላለም መኖር ይመኛል፡፡ በእርግጥ የሰው ዘር ኑባሬ ሰዎች እንደሚመኙት ዘላለማዊ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ሲሞት እንቅልፍ እንጂ ሞት አለመሆኑን የሚያብራራው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ወደ እሳት ባህር ውስጥ ከሚወረውረን ከሁለተኛው ሞት ማምለጥ አለብን፡፡ ስሞቻችን በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ እንዲጻፉ ማድረግ የሚኖርብን ምን እንደሆነ መረዳት ይገባናል፡፡ ስሞቻችን በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ እንዲጻፉም በትክክል በኢየሱስ ማመን አለብን፡፡
ሰዎች ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ፣ ቡድሃ፣ ኮንፊሺየስና መሐመድ ሁሉም ሰዎች ስለሆኑ ጥሩ ሰው ሆኖ መኖር ተገቢ ነው ብለው ያስባሉ፤ ይናገራሉም፡፡ በኢየሱስ ብቻ ማመን እንደሚኖርባቸው አበክረን የምንናገረውን መረዳት የማይችሉት ለዚህ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ እናንተና እኔ እንደዚሁም በዚህ ዓለም ላይ ያለ እያንዳንዱ ነገር በእግዚአብሄር ፊት ተራ ፍጥረትና ሰብዓዊ ፍጡራን እንጂ ምንም አይደለንም፡፡ ነገር ግን የኢየሱስን ውልደትና በዚህ ምድር ሳለ የፈጸመውን ነገር ስንመለከት እርሱ እንደቀሩት አራት ጥንታዊያን ሰዎች ሰው ብቻ አለመሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡ እርሱ የሰውን ዘር ለማዳን የሰውን መልክ ይዞ ወደዚህ ምድር የመጣ፣ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያታችንን በሙሉ የወሰደ፣ በእኛ ፋንታም የሐጢያቶቻችንን ቅጣት ሁሉ የተቀበለና የሰውን ዘር ከሐጢያት የማዳን ሥራውን የፈጸመ አምላክ ነው፡፡
የክርስቶስ ውልደት ከተራ ሰዎች ውልደት የተለየ ነበር፡፡ ሕጻናቶች የሚወለዱት በወንድና በሴት ጥምረት ነው፡፡ ሰው ሁሉ ወደዚህ ዓለም የተወለደው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ኢየሱስ የተወለደው ግን ወንድ ካላወቀች ድንግል ነበር፡፡ ራሱ አምላክ የሆነው ኢየሱስ እኛን ሰዎችን ለማዳንና ከ700 ዓመታት በፊት በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል የተተነበየውን የትንቢት ቃል ለመፈጸም በድንግል ሰውነት አማካይነት የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር ተወለደ፡፡ (ኢሳይያስ 7፡14) እርሱ በዚህ ምድር ላይ ሳለ ሙታንን ከማስነሳቱ፣ በሽተኞችንና ሽባዎችን ከመወፈሱም በላይ የዓለምን ሐጢያቶችንም በሙሉ አስወግዶዋል፡፡
ዩኒቨርስን ሁሉ የሰራው የፍጥረት ጌታ አምላክ የሰውን ዘር ከሐጢያቶቹ ሁሉ ለማዳን ሲል ለጊዜው ወደዚህ ምድር መጥቶ እርሱ ራሱ ሰው ሆነ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በኢየሱስ ማመን ያለብን እርሱ ራሱ አምላክ በመሆኑ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ስሞቻችን በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ እንዲጻፉ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወስዶ ሐጢያት አልባ ልጆቹ ስላደረገን ነው፡፡ አንድ ጊዜ ወደዚህ ምድር ከተወለድን ሁላችንም አንድ ጊዜ መሞት አለብን፡፡ ከሞትን በኋላም ሁላችንም ሊፈረድብን ይገባል፡፡
ነገር ግን ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወሰደ፡፡ በእኛ ፋንታም በመስቀል ላይ ተኮነነ፡፡ በእርሱ የምናምነውን ሰዎችም በዘላለማዊው መንግሥተ ሰማይ ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንድንኖር አስቻለን፡፡ በሌላ አነጋገር እኛን ከሐጢያት ፍርድ ለማዳን እግዚአብሄር ራሱ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አነጻን፡፡ ሁላችንም አዳኝ በሆነው በኢየሱስ ማመን የሚገባን ለዚህ ነው፡፡
ኢየሱስ ተራ ሰው አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ለሰው ዘር የማዳንን ተስፋ ስለሰጠና ይህንን ተስፋ ለመፈጸምም በድንግል አካል በኩል የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር ስለመጣ በእርግጥም ሁሉንም ከሐጢያቶቻቸው ስላዳነ ሁላችንም ራሱ አምላክ በሆነው በኢየሱስ ማመን አለብን፡፡ በትክክል በኢየሱስ ስናምን ስሞቻችን በሕይወት መጽሐፍ ላይ ይጻፋሉ፡፡ ሰው መንግሥተ ሰማይን ማየትና እዚያም መግባት የሚችለው ከውሃና ከመንፈስ ዳግመኛ ሲወለድ እንደሆነ እግዚአብሄር ነግሮናል፡፡ ሁላችንም በኢየሱስ ማመን አለብን፡፡
 


ወደ ሰማይ የሚያደርስ መንገድ የሆነው ኢየሱስ፡፡

 
ስለዚህ ኢየሱስ እንዴት በትክክል ሐጢያቶቻችንን እንዳስወገደ ማወቅ አለብን፡፡ ኢየሱስ ወደዚህ ምድር በመምጣት በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ (ማቴዎስ 3፡13-17) እርሱ የሰውን ዘር (የእናንተንና የእኔን ሁሉ ጨምሮ) ሐጢያቶች በሙሉ መውሰድ ይችል ዘንድ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ የሰው ዘር ሁሉ ወኪል በሆነው በአጥማቂው ዮሐንስ እጆች አማካይነት የሰው ዘር ሁሉ እያንዳንዱ ሐጢያት ወደ ኢየሱስ ተላለፈ፡፡ ኢየሱስ በዮሐንስ በኩል በዚህ መንገድ የዓለምን ሐጢያቶች ሁሉ ከወሰደ በኋላ በመስቀል ላይ ደሙን አፍስሶ ሞተ፡፡ ከዚያም በሦስት ቀናት ውስጥ ከሙታን ተነሳ፡፡
ጌታችን በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለምን ሕይወት እንደሚቀበል ቃል ገብቷል፡፡ እግዚአብሄር ኢየሱስ በራሱ ላይ የእርሱን/የእርስዋን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ በመውሰድ የእነዚህን ሐጢያቶች ቅጣት በሙሉ በመስቀል ላይ እንደተቀበለ በሚናገረው እውነት የሚያምን ሁሉ ወደ እሳት ባህር እንደማይጣል ነገር ግን በምትኩ ስሙ/ስምዋ በሕይወት መጽሐፍ ላይ እንደሚጻፍ እግዚአብሄር ወስኖዋል፡፡
ኢየሱስ በዮሐንስ 14፡6 ላይ እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም፡፡›› የሰው ዘር ወደ ሰማይ የሚያደርስ መንገድ በሆነው በኢየሱስ ማመን አለበት፡፡ ኢየሱስ አዳኛችን ነው፡፡ ኢየሱስ አምላካችን ነው፡፡ ኢየሱስ በዚህ ዓለም ላይ አንዱና ብቸኛው ተጨባጭ እውነት ነው፡፡ ኢየሱስ የሕይወትም ጌታ ነው፡፡ ስሞቻችን በሕይወት መጽሐፍ ላይ መጻፋቸውን ለማረጋገጥና በዚህ መንገድም መንግሥተ ሰማይ ለመግባት ሁላችንም በኢየሱስ ማመን አለብን፡፡
ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ከአጥማቂው ዮሐንስ ጥምቀቱን በመቀበል ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በተጨባጭ ስለወሰደ የስርየት አዳኝ በሆነው በእርሱ ማመን አለብን፡፡ እናንተና እኔ አሁን ሰማይ መግባት የምንችለው ኢየሱስ የሐጢያቶቻችንን ቅጣት ለመክፈል ሲል በመስቀል ላይ በመሰቀልና ደሙን በማፍሰስ ደህንነታችንን ስለፈጸመ ነው፡፡
ኢየሱስ ማን ወደ እሳት ባህር እንደሚጣል ወስኖዋል፡፡ የማያምኑና የሚፈሩ በሙሉ ወደ እሳት ባህር ይጣላሉ፡፡ በአለማመናቸው ወደ እሳት ባህር የሚጣሉት እነርሱ ራሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ልጆቻቸውና የሚመጡት ዘሮቻቸውም ጭምር ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ሰው የራሱን መንፈሳዊና አካላዊ ደህንነት ለመጠበቅ በእርግጠኝነትና ሙሉ በሙሉ በኢየሱስ ማመን አለበት፡፡
 


ኢየሱስ ባይጠመቅ ኖሮስ? 


ለእያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር በረከቶቹን ወይም እርግማኖቹን የሚለግስ እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ በእርሱ ማመን ያለብን ለዚህ ነው፡፡ የብዙ ሰዎች ሕይወት እንዲህ የተጎሳቆለው የዚህ ምድር መንግሥታቶች የሚወድቁት ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁን? እግዚአብሄር እርሱን የሚጠሉትንና ለጣዖታት የሚሰግዱትን ለሚመጡት ሦስት አራት ትውልዶች ድረስ እንደሚረግማቸው ስለተናገረ ነው፡፡ እግዚአብሄርን የሚያገለግሉትን፣ የሚወዱትንና ትዕዛዛቱን የሚጠብቁትን ግን እስከ ሺህ ትውልዶች ድረስ እንደሚባርክም ተናግሮዋል፡፡ (ዘጸዓት 20፡5-6)
ይህ ማለት አንድ ሰው በሆነ መንገድ በኢየሱስ ቢያምን እርሱ/እርስዋ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ይባረካሉ ማለት አይደለም፡፡ ሰው ኢየሱስን በትክክል አውቆ ማመን አለበት፡፡ በሌላ አነጋገር ሰዎች ኢየሱስ ወደዚህ ምድር የመጣ አምላክ እንደሆነ፣ እነዚህን ሐጢያቶች በሙሉ በጥምቀቱ በራሱ ላይ በመውሰድ ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ እንዳነጻና በእነርሱ ምትክ በመሰቀል እውነተኛ አዳኛቸው እንደሆነ ቢያምኑ -- በአጭሩ ኢየሱስ የእነርሱ የራሳቸው አምላክና አዳኝ እንደሆነ ቢያምኑ -- እግዚአብሄር እንዲህ የሚያምኑትን ለሚመጡት ሺህ ትውልዶች እንደሚባርካቸው ተናግሮዋል፡፡
ነገር ግን በዚያው ጊዜም እግዚአብሄር በኢየሱስ የሚያምኑትን ለሦስት አራት ትውልዶች እንደሚረግማቸው ተስፋ ሰጥቶናል፡፡ ማንም ይሁን ሰው ሁሉ በኢየሱስ ማመን ያለበትና ሰው ሁሉ ከውሃና ከመንፈስ ዳግመኛ መወለድ ያለበት የመሆኑን እውነት ማወቅና ማመን ያለበት ለዚህ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት እምነት ያላቸው ሰዎች ለሐጢያቶቻቸው ሁሉ ይቅርታን ያገኛሉ፡፡ የዘላለምን ሕይወት ይቀበላሉ፡፡ ሰማይ ይገባሉ፡፡ እንደዚሁም በዚህ ምድር ላይ ሳሉ እግዚአብሄር ቀድሞ ለአብርሃም የሰጠውን በረከቶች ሁሉ ያገኛሉ፡፡
ሁላችንም እግዚአብሄር ለእኛ በወሰነው በዚህ ቃል ላይ መኖር አለብን፡፡ እምነታችንም ሙሉ በሙሉ ከተጸፈው ቃል ጋር መስማማት አለበት፡፡ በእግዚአብሄር የማያምኑ ወደ እሳት ባህር እንደሚጣሉ ነገር ግን በአንጻሩ የሚያምኑ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጻፉና ወደ አዲስ ሰማይና ምድር እንደሚገቡ የሚናገረውን እውነታ መረዳትና ማመን አለብን፡፡ የምናምን ሰዎችም እንደገና በሕይወት እንደምንኖርም ማመን አለብን፡፡ ዳግመኛ መወለድ የምንችለው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ብቻ ነው፡፡
ማንም ሰው ያለ ውሃ መኖር ስለማይችል የውሃው ወንጌል ከደሙ ወንጌል ጋር አብሮ ለደህንነታችን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ኢየሱስ ሲጠመቅ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ ወሰደ፡፡ ወደ ውሃው ውስጥ ጠለመ፡፡ እንደገናም ከውሃው ውስጥ ብቅ አለ፡፡ ይህም የመስቀል ላይ ሞቱንና ትንሳኤውን ያመለክታል፡፡ በሌላ አነጋገር ጌታችን ስለ ሐጢያቶቻችን ሁሉ በእኛ ምትክ ተፈረደበት፡፡ ጌታ ከውሃው ውስጥ መውጣቱ ትንሳኤውን ያመለክታል፡፡ ይህም የምናምነው የእኛም ትንሳኤ ጭምር ነው፡፡
ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደወሰደ አበክረን እናምናለን፡፡ ኢየሱስ ባይጠመቅ ኖሮ ምን እንሆን ነበር? ከእሳት ባህር የምናመልጥበት መንገድ አይኖረንም ነበር፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ያለ ዝናብ መኖር የሚችል ሰው እንደሌለ ሁሉ ምድር እየኖረች ያለችውም በውሃ ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ የኢየሱስ ጥምቀትም ለእኛ ይህን ያህል አስፈላጊ ነው፡፡ የመስቀል ላይ ሞቱም እንደዚሁ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ማለት በእኛ ምትክ ለሐጢያቶቸችን ተፈርዶበታል ማለት ነውና፡፡ ከእግዚአብሄር እርግማንና ፍርድ ለመዳን የምንፈልግ ከሆንን ሙሉ በሙሉ በኢየሱስ ማመን አለብን፡፡ ከሐጢያቶቻችን መንጻት የምንፈልግ ከሆንን ሐጢያቶቻችን በሙሉ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ወደ እርሱ እንደተላለፉ ማመን አለብን፡፡ የክርስቲያን እምነት ከቶውኑም ሰዎችን በፍርሃት እንዲርዱ የሚያደርግ የሐይማኖት ዓይነት አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሰው በኢየሱስ ማመን አለበት፡፡ ዳግመኛ የተወለዱ ዳግመኛ ወደተወለደች ቤተክርስቲያን በመምጣት የእምነት እንክብካቤን ለማግኘት ቃሉን መስማት አለባቸው፡፡
አንዳንድ ሰዎች ለመዳንና በረከቶችን ለመቀበል በጎ ምግባሮችን ማድረግ አለብን ይላሉ፡፡ ይህ ግን የአጭበርባሪዎች የውሸት አባባል ነው፡፡ በጎ ምግባሮችን እያደረግን ጥሩ ክርስቲያኖች ሆነን መኖር ያለብን መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን የደህንነታችንን መሰረታዊ ችግር በተመለከተ ተፈጥሮዋችን ክፉ ስለሆነ ማናችንም በሥጋ ሕይወታቸን 100 እጅ ፍጹማን ሆነን መኖር አንችልም፡፡ ሰው በጎ ምግባሮችን በማድረግ መዳን አለበት የሚሉ ሰዎች በሙሉ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የማያውቁና ሰዎችን የሚያስቱ ውሸታሞች የሆኑት ለዚህ ነው፡፡
እኛ በመሰረቱ ሐጢያትን ለመስራት የታሰርን ስለመሆናችን ራሳችንን ስናውቅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን ጥምቀትና ስለ እኛ የተሸከመውን መስቀል ከተጻፈው የእግዚአብሄር ቃል ስናሰላስልና እነዚህን ነገሮች ሁሉ ስንቀበል ልባቸው ሐጢያት የሌለበት ጻድቃንና ሰማይ ለመግባትም ብቁ መሆን የምንችለው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ከማደሩና እኛን ከመምራቱ በፊት ማናችንም ምንም ያህል ጠንክረን ብንሞክርም ጥሩዎች መሆን አንችልም፡፡
እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በማስወገድ አዳነን፡፡ ለዘላለም ወደሚቃጠለው የእሳት ባህር ውስጥ በመጣል ፋንታ ስሞቻችንን በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ጻፈ፡፡ አዲስ ሰማይና ምድርን ሰጠን፡፡ ሙሽራይቶቹ ራሳቸውን ለሙሽራው እንደሚያስጌጡም እጅግ ንጹህና እጅግ ውብ የሆኑ ቤቶችን፣ ገነቶችንና አበቦችን ሰጠን፡፡ በሽታንም ሁሉ ከእኛ ያስወግዳል፡፡ በመንግሥቱ ውስጥም ከእኛ ጋር ለዘላለም አብሮ ይኖራል፡፡ ከሞት ወዲያ ስላለው ሕይወታችን ስንል በኢየሱስ ማመን አለብን፡፡ አሁን ለምንኖረው ሕይወታችንም እንደዚሁ በእርሱ ልናምን ይገባናል፡፡ ለልጆቻችን ስንልም ደግሞ ማመን አለብን፡፡
ሰማይ መግባት ትፈልጋላችሁን ወይስ ወደ እሳት ባህር መጣል? ለልጆቻችሁ የምታወርሱት ውርስ ምን ዓይነት ነው? በኢየሱስ በማመናችሁ አንዳንድ ችግርና መከራ ቢገጥማችሁም በእርሱ ማመናችሁን መቀጠል አለባችሁ፡፡ እንዲህ ማድረግ ለእናንተና ለልጆቻችሁ ታላላቅ በረከቶችን ያመጣልና፡፡
የምወዳችሁ ቅዱሳን እግዚአብሄር በቃሉ አማካይነት የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የምንሰብክበትን ምክንያትና ቤተሰቦቻችንም መዳን የሚገባቸው የመሆኑን ምክንያት ነግሮናል፡፡ እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ፡፡