Search

उपदेश

ርዕስ 8፡ መንፈስ ቅዱስ

[8-3] በኢየሱስ ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀብላችኋልን? ‹‹ የሐዋርያት ሥራ 19፡1-3 ››

በኢየሱስ ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀብላችኋልን?
‹‹ የሐዋርያት ሥራ 19፡1-3 ››
‹‹አጵሎስም በቆሮንቶስ ሳለ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ፡፡ ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀብላችኋልን? አላቸው፡፡ እነርሱም፡- አልተቀበልንም፤ መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት፡፡ እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ? አላቸው፡፡ በዮሐንስ ጥምቀት አሉት፡፡››
 
 
መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ከመጥምቁ ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል›› የሚለው ለምንድነው?
ምክንያቱም ሰዎች ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማስወገዱን በሚናገረው ውብ ወንጌል በማመን መንግሥተ ሰማይን መንጠቅ ስለሚችሉ ነው፡፡ 
 
ጳውሎስ የሰበከው ምን አይነት ወንጌል ነው? እርሱ የሰበከው የኢየሱስን የጥምቀትና የደሙ ወንጌል ነው፡፡ የሐዋርያት ሥራ 19፡1 እንዲህ ይላል፡- ‹‹አጵሎስም በቆሮንቶስ ሳለ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ፡፡ ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀብላችኋልን? አላቸው፡፡›› ሆኖም እነዚህ ሰዎች የኢየሱስን ጥምቀት በመተው ያመኑት በኢየሱስ ብቻ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ የሚመራቸውን ውብ ወንጌል አላወቁትም፡፡ ጳውሎስ ‹‹ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀብላችኋልን?›› ብሎ የጠየቃቸው ጥያቄ በኤፌሶን ላሉ አንዳንድ ደቀ መዛሙርት ያልተለመደ ጥያቄ ነበር፡፡ ሌሎች ሰዎች ቢሆኑ ኖሮ ‹‹በኢየሱስ ታምናላችሁን?›› ብለው ይጠይቁዋቸው ነበር፡፡ ጳውሎስ ግን እምነታቸውንም በውቡ ወንጌል በማደስ መንፈስ ቅዱስን መቀበል ይችሉ ዘንድ ጥያቄውን እንደዚህ ባለ የተለየ መንገድ ጠየቀ፡፡ የጳውሎስ አገልግሎት ውቡን የኢየሱስ ጥምቀትና የደሙን ወንጌል መስበክ ነበር፡፡ ጳውሎስ፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ በአጥማቂው ዮሐንስ ስለተደረገው የኢየሱስ ጥምቀት መስክረዋል፡፡      
ሐዋርያቶች ስለ ጥምቀት ወንጌል የመሰከሩትን ምስክርነት እንመልከት፡፡ በመጀመሪያ ጳውሎስ እንዲህ መሰከረ፡- ‹‹አይደለም፤ ለሐጢአት የሞትን እኛ ወደፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን? ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደተጠመቅን አታውቁምን?›› (ሮሜ 6፡2-3) እና ‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፡፡›› (ገላትያ 3፡27) ሐዋርያው ጴጥሮስም እንደዚሁ በ1ኛ ጴጥሮስ 3፡21 ላይ እንዲህ በማለት ለኢየሱስ ጥምቀት መስክሮለታል፡፡ ‹‹ይህም ውሃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፤ ለእግዚአብሄር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፡፡ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ነው፡፡ እርሱም መላዕክትና ስልጣናት ሐይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሄር ቀኝ አለ፡፡›› 
ዮሐንስም ስለዚሁ ውብ ወንጌል በ1ኛ ዮሐንስ 5፡5-8 ላይ መስክሮዋል፡- ‹‹ኢየሱስም የእግዚአብሄር ልጅ እንደሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማነው? በውሃና በደም የመጣ ይህ ነው፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ በውሃውና በደሙ እንጂ በውሃው ብቻ አይደለም፡፡ መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው፡፡ የሚመሰክሩት መንፈሱና ውሃው ደሙመም ሶስት ናቸውና፡፡ ሶስቱም በአንድ ይስማማሉ፡፡››
አጥማቂው ዮሐንስ ውቡን ወንጌል በማጠናቀቅ ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አጥማቂው ዮሐንስ በሚልክያስ 3፡1-3 እና በማቴዎስ 11፡10-11 ላይ የሚከተለውን ተናግሮዋል፡፡ አጥማቂው ዮሐንስ የሰው ዘር ወኪልና በብሉይ ኪዳን እንደተጻፈውም የሚመጣው ኤልያስ ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን በእጆች መጫን አማካይነት የአንድን ሰው ሐጢያቶች ከወሰደ በኋላ የሚገደልና ደሙን የሚያፈስስ የሐጢያት መስዋዕት ነበር፡፡ በአዲስ ኪዳን ግን የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በጥምቀቱ አማካይነት ወስዶ የሐጢያትን ዋጋ በመስቀል ላይ ላይ ለመክፈል የሞተው የሐጢያት ቁርባን ኢየሱስ ነበር፡፡ አጥማቂው ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ባደረገው ጥምቀት አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወደ ኢየሱስ በማሻገሩ ኢየሱስ የሰውን ዘር አዳነ፡፡
እግዚአብሄር የሰውን ዘር ከሐጢያቶቻቸው ለማዳንና ሁሉንም ለመፈጸም ሁለት አይነት ታላላቅ ምግባሮችን አቀደ፡፡ የመጀመሪያው ኢየሱስ በድንግል ማርያም አካል በኩል ወደዚህ አለም እንዲመጣና የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለመውሰድም እንዲጠመቅና እንዲሰቀል ማድረግ ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አጥማቂው ዮሐንስ ከኤልሳቤጥ እንዲወለድ ማድረግ ነበር፡፡ እግዚአብሄር እነዚህን ሁለት ክስተቶች ተግባራዊ ያደረገው የሰውን ዘር ከሐጢያቶቹ ለማዳን ነበር፡፡ እግዚአብሄር በስላሴ ውስጥ ያቀደው እቅድ ይህ ነበር፡፡ እግዚአብሄር አጥማቂው ዮሐንስን ከኢየሱስ ስድስት ወር በፊት አስቀድሞ ላከው፡፡ ከዚያም የሰውን ዘር ከሐጢያቶቻቸው ኩነኔ ነጻ ለማውጣት የሰው ዘር መድህን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ላከው፡፡
ኢየሱስ በማቴዎስ 11፡9 ላይ ስለ አጥማቂው ዮሐንስ መስክሮዋል፡- ‹‹ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነብይን አዎን እላችኋለሁ ከነብይም የሚበልጠውን፡፡›› ከዚህ በተጨማሪም የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወደ ኢየሱስ ያሻገረው አጥማቂው ዮሐንስ በቀጣዩ ቀን ተመለከተውና እንዲህ ሲል መሰከረለት፡- ‹‹እነሆ የዓለምን ሐጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ፡፡›› (ዮሐንስ 1፡29)  
መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን ስላጠመቀው ስለ ዮሐንስ ብዙ የተጻፉ ነገሮች አሉት፡፡ እኛም ስለ እርሱ የተሻለ እውቀት ለማግኘት መጣር አለብን፡፡ አጥማቂው ዮሐንስ ከኢየሱስ አስቀድሞ መጣ፡፡ የእርሱ ተልዕኮ የእግዚአብሄር ዕቅድ የሆነውን ውብ ወንጌል መፈጸም ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያት በሙሉ ከዮሐንስ እንደተቀበለና ዮሐንስም የዓለምን ሐጢያት በሙሉ ወደ ኢየሱስ እንዳስተላለፈ ይናገራል፡፡
አጥማቂው ዮሐንስ ብለን የምንጠራው ኢየሱስን ስላጠመቀው ነው፡፡ የኢየሱስ በዮሐንስ መጠመቅ ትርጉሙ ምንድነው? ‹‹ጥምቀት›› የሚለው ቃል ትርጉሙ ‹‹መታጠብ›› ማለት ነው፡፡ የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ በጥምቀቱ በኩል ወደ ኢየሱስ ስለተላለፉ ተወግደዋል፡፡ የኢየሱስ ጥምቀት በብሉይ ኪዳን ለሐጢያት የሚቀርበው መስዋዕት የሚቀበለውን አይነት ‹‹እጆችን የመጫን›› ትርጉም አለው፡፡ የጥምቀት መንፈሳዊ ትርጉም ‹‹ማሻገር›› ‹‹መታጠብ›› ወይም ‹‹መቀበር›› ነው፡፡ ኢየሱስ በዮሐንስ መጠመቁ በዓለም ላይ ያለውን ሕዝብ ሐጢያቶች በሙሉ ለመውሰድ የተደረገ የቤዛነት ድርጊት ነበር፡፡  
የኢየሱስ ጥምቀት እጆችን ከመጫን ጋር ተመሳሳይ ትርጉም አለው፡፡ በብሉይ ኪዳን ሐጢያቶች ለሐጢያት ወደቀረበው መስዋዕት የሚተላለፉበት መንገድ ይህ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር የእስራኤል ሕዝቦች አመታዊዎቹን ሐጢያቶቻቸውን በስርየት ቀን ለሐጢያት ወደቀረበው መስዋዕት የሚያሻግሩት በሊቀ ካህኑ እጆችን መጫን አማካይነት ነበር፡፡ ይህ የብሉይ ኪዳን መስዋዕት ልክ እንደ ኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ እንደሆነው ሞቱ ተመሳሳይ ተግባር አለው፡፡
እግዚአብሄር በወቅቱ የእስራኤላውያንን ሐጢያቶች ለማስወገድ የስርየትን ቀን ቀጠረ፡፡ በሰባተኛው ወር በአስረኛው ቀን ሊቀ ካህኑ ለሕዝቡ ሐጢያቶች ስርየትን ለማድረግ እጆቹን በመስዋዕቱ ራስ ላይ በመጫን የሕዝቡን አመታዊ ሐጢያቶች በሙሉ ለሐጢያት በቀረበው ቁርባን ላይ ያሻግራል፡፡ እግዚአብሄር የመሰረተው መስዋዕታዊ ስርአት ይህ ነበር፡፡ የሕዝቡን ሐጢያቶች ለማሻገር ብቸኛው መንገድ ይህ ነበር፡፡ ሐጢያቶችን በእጅ መጫን ማስተላለፍ እግዚአብሄር የመሰረተው ዘላለማዊ ሕግ ነበር፡፡  
‹‹አሮንም ሁለቱን እጆቹን በሕያው ፍየል ራስ ላይ ይጭናል፡፡ በላዩም የእስራኤልን ልጆች በደል ሁሉ፣ መተላለፋቸውንም ሁሉ፣ ሐጢአታቸውንም ሁሉ ይናዘዛል፡፡ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል፡፡ በተዘጋጀው ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰድደዋል፡፡›› (ዘሌዋውያን 16፡21-22)
በብሉይ ኪዳን ሐጢያተኛው የሐጢያቱን ይቅርታ ለማግኘት እጆቹን ለመስዋዕትነት በተዘጋጀው እንስሳ ራስ ላይ ይጭናል፡፡ በስርየት ቀን ሊቀ ካህኑ አሮን የእስራኤላውያን ሁሉ ወኪል ሆኖ የእስራኤልን ሐጢያቶች ለማሻገር እጆቹን በመስዋዕቱ ራስ ላይ ይጭናል፡፡ ከዚያም ሐጢያቶቻቸውን ከወሰደ በኋላ መስዋዕቱ ይታረዳል፡፡
በአዲስ ኪዳንም ኢየሱስ ከዮሐንስ የተቀበለው ጥምቀት (በግሪክ ባፕቲዝማ  ማለት (መታጠብ፣ መቀበር፣ ማሻገር ማለት ነው) ተመሳሳይ የሆነ ትርጉም አለው፡፡  በብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህኑ የእስራኤልን ሕዝብ ሐጢያቶች ለማሻገር እጆቹን በሐጢያት መስዋዕቱ ላይ እንደሚጭን ሁሉ የሰው ዘር ሐጢያቶች ሁሉ በአጥማቂው ዮሐንስ በኩል በሆነው ጥምቀቱ ወደ ኢየሱስ ተሻግረዋል፡፡ ከዚያ ለሐጢያቶቻችን ስርየት ለመስጠት በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ ይህ የውቡ ወንጌል እውነት ነው፡፡  
ሊቀ ካህኑ አሮን በእስራኤል ሕዝብ ምትክ ለስርየት የሚሆነውን መስዋዕት እንዳቀረበ ሁሉ ከአሮን ዝርያዎች አንዱ የነበረው አጥማቂው ዮሐንስም ኢየሱስን በማጥመቅና የሰውን ዘር ሐጢያቶችም ወደ እርሱ በማሻገር የሰው ዘር ወኪል ሆኖ ተግባሩን ፈጸመ፡፡ እግዚአብሄር እንደዚህ ያለውን የፍቅሩን ድንቅ እቅድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመዝሙረ ዳዊት 50፡4-5 ላይ እንዲህ አብራርቶታል፡- ‹‹በላይ ያለውን ሰማይ፤ ምድርንም በሕዝቡ ለመፍረድ ይጠራል፡፡ ከእርሱ ጋር ለመስዋዕት ኪዳን የቆሙትን ቅዱሳኑን ሰብስቡለት፡፡›› አሜን ሐሌ ሉያ፡፡   
የቤተክርስቲያን ታሪክ እንደሚለው በጥንቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ምዕተ አመታቶች የገና በዓል የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ የጥንቷ ቤተክርስቲያን ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ሐዋርያት ጋር ተባብረው ጥር 6ን በዮርዳኖስ በአጥማቂው ዮሐንስ የተደረገውን ጥምቀት ‹‹የኢየሱስ የጥምቀት ቀን›› አድርገው ያከብሩት ነበር፡፡ በእምነታቸው ውስጥ በኢየሱስ ጥምቀት ላይ እንደዚህ ያለ ትልቅ ትኩረት ያደረጉት ለምንድነው? መልሱ የሐዋርያትን ወግ ለያዘው ክርስትና ዋናው ቁልፍ ነው፡፡ ምዕመናኖች የሚጠመቁትን የውሃ ጥምቀት ከኢየሱስ ጥምቀት ጋር እንደማትደበላልቁት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ዛሬ እየሆነ ያለው የምዕመናን ጥምቀት ኢየሱስ ከዮሐንስ ከተቀበለው ጥምቀት በጣም የተለየ ትርጉም አለው፡፡ ስለዚህ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ለመቀበል ከፈለግን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የነበራቸው አይነት ተመሳሳይ እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ ሁላችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመን መንፈስ ቅዱስን መቀበል ይገባናል፡፡ 
የጥንቷ ቤተክርስቲያን ጥምቀት እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ስርዓት መሆኑን የተረዳችው በኢየሱስ ጥምቀት ላይ ወሳኝ የሆነ እምነት ስለነበራት ነው፡፡ እኛም ዛሬ በዮሐንስ የተከናወነውን የኢየሱስ ጥምቀት የደህንነታችን አስፈላጊ አካል አድርገን ልንመለከተው ይገባናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢየሱስ በዮሐንስ ስለተጠመቀ እንደተሰቀለ የሚናገረውን ፍጹምና ትክክለኛ የሆነ የእውቀት እምነት መያዝና መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ማደር የሚጀምረው ኢየሱስ መጠመቁን፣ በመስቀል ላይ መሞቱንና መድህናችን ይሆን ዘንድም ከሙታን መነሳቱን ስናምን ነው፡፡ ኢየሱስ በዮሐንስ መጠመቁና በመስቀል ደሙን ማፍሰሱ በውቡ ወንጌል ውስጥ እንዲህ ያለ የተለየ ትርጉም አለው፡፡
መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል አስተማማኙና የተረጋገጠው መንገድ በኢየሱስ ጥምቀትና ደም ማመን ነው፡፡ የኢየሱስ ጥምቀት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በአንዴ አነጻ፡፡ መንፈስ ቅዱስን እንድንቀበል የሚመራን የቤዛነት ጥምቀት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች የኢየሱስ ጥምቀት ያለውን ሐይል ስለማይገነዘቡ ተራ ስርዓት አድርገው ይቆጥሩታል፡፡
የኢየሱስ ጥምቀት የዓለምን ሐጢያቶች እንዴት እንደወሰደና በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስም የእነዚያን ሐጢያቶች ፍርድ እንዴት እንደተቀበለ የሚነግረንን የውቡን ወንጌል ክፍል ያዋቅራል፡፡ በዚህ የውቡ ወንጌል ቃሎች የሚያምን ማንኛውም ሰው የጌታ ንብረት የሆነችው ቤተክርስቲያን አባል ይሆንና በመንፈስ ቅዱስ በረከቶች ይደሰታል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለሐጢያቶቻቸው ይቅርታን ላገኙት ከእግዚአብሄር ዘንድ የሚሰጥ ስጦታ ነው፡፡
ኢየሱስ በጥምቀቱ ‹‹የዓለምን ሐጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ›› ሆኖዋል፡፡ (ዮሐንስ 1፡29) ዮሐንስ 1፡6-7 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከእግዚአብሄር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፡፡ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክርነት መጣ፡፡›› ኢየሱስን ሐጢያቶቻችንን በሙሉ የወሰደ አዳኛችን አድርገን ለማመን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን የዮሐንስን አገልግሎትና ምስክርነት መረዳት አለብን፡፡ ያን ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛችን አድርገን ማመን እንችላለን፡፡ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበልም ጠንካራው እምነታችን በእርሱ ምስክርነት መደገፍ ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ የውቡን ወንጌል እውነት ለማጠናቀቅ በዮሐንስ የተከናወነው የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመን አለብን፡፡
በማቴዎስ 11፡12 ላይ እንዲህ ተጽፎዋል፡- ‹‹ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግስተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል፡፡›› ይህ ምንባብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉ አስቸጋሪ ምንባቦች አንዱ ሆኖ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ‹‹ከመጥምቁ ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ›› የሚለውን ሐረግ ማጤን አለብን፡፡ ይህ የዮሐንስ አገልግሎት ኢየሱስ ለደህንነታችን ካደረገው አገልግሎት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መሆኑን ያሳየናል፡፡
ኢየሱስ እንደ ሐይለኛ ሰዎች ደፋር የሆነ እምነት ይዘን ወደ መንግስቱ እንድንገባ ይፈልጋል፡፡ እኛ በየቀኑ ሐጢያት እንሰራለን፡፡ ደካሞች ነን፡፡ ሐጢያታችን ምንም ቢሆን ደፋር በሆነ እምነት ወደ መንግስቱ እንድንገባ ፈቅዶልናል፡፡ ስለዚህ የዚህ ምንባብ ትርጉም ሰዎች ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንደደመሰሰ በሚናገረው ውብ ወንጌል እምነት ካላቸው መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉ ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሰማይ ሊወረስ የሚችለው በዚህ በውቡ የኢየሱስ ጥምቀትና ደም በድፍረት በማመን ነው፡፡
የኢየሱስ ጥምቀት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ አስወገደ፡፡ በዚህ ላይ ያለን እምነትም ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ለመቀበል ዋስትና ይሰጠናል፡፡ እኛ ይህንን ወንጌል ለጎረቤቶቻችን፣ ለዘመዶቻችን፣ ለምናውቃቸውና በአለም ላይ ለሚኖር ለእያንዳንዱ ሰው መስበክ አለብን፡፡ የዓለም ሐጢያቶች በጥምቀቱ አማካይነት ወደ ኢየሱስ መተላለፋቸውን በሚናገረው ውብ ወንጌል ማመን አለብን፡፡ በእምነታችን አማካይነት የቤዛነትን ሐሴትና ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ እናገኛለን፡፡
የኢየሱስ ጥምቀት ሐጢያቶቻችንን ሁሉ አስወገደ፡፡ ደሙም ለሐጢያት የተከፈለ ፍርድ ነበር፡፡ ለማያምኑ ሰዎች ውቡን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ማብራራት አለብን፡፡ እነርሱ በወንጌል ወደ ማመን የሚመጡትና መንፈስ ቅዱስን መቀበል የሚችሉት በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በዚህ እንድታምኑ እፈልጋለሁ፡፡ ሰው የሐጢያቶቹን ይቅርታ የሚያገኘውና ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ የሚቀበለው በዮሐንስ በተከናወነው የእርሱ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ሲያምን ብቻ ነው፡፡
ሰው ሁሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን በውስጡ መንፈስ ቅዱስ የሚያድርበት የእግዚአብሄር ልጅና የእኛም ወንድምና እህት መሆን ይችላል፡፡ እናንተም ልክ ጳውሎስ እንዳመነው በውቡ ወንጌል የምታምኑበት ተመሳሳይ እምነት ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ ጌታ ይህንን ውብ ወንጌል ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ፤ አወድሰዋለሁ፡፡ አሜን፡፡