Search

उपदेश

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[2-5] ከሐጢያት የዳነው ማነው? ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 2፡8-11 ››

ከሐጢያት የዳነው ማነው?
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 2፡8-11 ››
 
ይህ ምንባብ ጌታ በትንሽዋ እስያ ለምትገኘውና ቁሳዊ ደሃ ለሆነችው ነገር ግን በእምነት መንፈሳዊ ባለጠጋ ለሆነችው የሰርምኔስ ቤተክርስቲያን የላከው ደብዳቤ ነው፡፡ የእርስዋ ቅዱሳኖችና የእግዚአብሄር አገልጋይ በአይሁዶች ቢሰደዱም እምነታቸውን ጠብቀዋል፡፡ በሞት መከራዎቻቸው ውስጥም እንኳን ጌታንና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል አልካዱም፡፡ በእግዚአብሄር ቃል በማመን ተዋግተው አሸነፉ፡፡ 
 
ጌታ በሰርምኔስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙትን ቅዱሳን መጪውን መከራ እንዳይፈሩ ነገር ግን የሕይወትን አክሊል እንደሚሰጣቸው ተስፋ በመግባት እስከ ሞት ድረስ እንዲታመኑ ነገራቸው፡፡ 
 
እግዚአብሄር የእርሱ ሕዝብ ራሳቸውን ነቢያት ብለው የሚጠሩትን ሰዎች የሐሰት ትምህርቶች ተዋግተው እንዲያሸንፉ ነግሮዋቸዋል፡፡ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ለመዳን ምን ዓይነት እምነት እንደሚያስፈልገን ማወቅ አለብን፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እውነተኛ ወንጌል መሆኑን መገንዘብና በዚህ እምነትም የዘመኑን የክርስትና ዓለም እየቀሰፉ ያሉትን የሐሰት ትምህርቶችና ውሸቶች ተዋግተን ማሸነፍ አለብን፡፡ መላው ዓለም በሰይጣን ተታልሎ በነበረ ጊዜ እግዚአብሄር የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ይፈጽም ዘንድ ጌታችንን ላከው፡፡ እርሱ በዚህ የሚያምኑትን ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው በሙሉ አድኖዋቸዋል፡፡ ይህንን እውነት መረዳትና ማመን አለብን፡፡ 
 
በእግዚአብሄር ፊት ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ የዳኑ ሰዎች እነማን ናቸው? እነርሱ ጠንካራ ሰውነት ወይም ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ሳይሆኑ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ብቻ ከሐጢያቶቻቸው የዳኑ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማወቅና በማመን የሐሰት ትምህርቶችንና ውሸቶችን ተዋግተው አሸንፈዋል፡፡ እግዚአብሄር በዚህ ወንጌል በማመን የሐሰት ትምህርቶችን ድል ላደረጉ ሰዎች ሁለተኛውን ሞት የማምለጥ በረከትን ይሰጣቸዋል፡፡ 
 
 

ድል ለነሱት ሰዎች የተሰጠ የእግዚአብሄር ደህንነት፡፡ 

 
የራዕይ ቃል እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ድል የነሳው በሁለተኛው ሞት አይጎዳም፡፡›› እግዚአብሄር አዲስ ሕይወትንና አዲሱን መንግሥቱን የሚሰጠው ድል ለነሱት ብቻ ነው፡፡ ሁለት ጆሮዎች ስላሉን ሁለት የተለያዩ ታሪኮችን እንሰማለን፡፡ ማለትም በአንድ ጊዜ እውነትንም ሐሰትንም እንሰማለን፡፡ በእግዚአብሄር ቃልና በሰይጣን ቃል መካከል ዕጣ ፈንታችን የሚወሰነው የማንን ቃል በመቀበላችንና የማንን ቃል በመጣላችን ላይ ነው፡፡ 
 
ሁላችንም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን የሚገባንና በዚህ የእውነት ቃልና በእርሱ ላይ ባለን እምነታችንም የሐሰት ትምህርቶችን ተዋግተን ማሸነፍ ያለብን ለዚህ ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው በሐጢያት ጭነት እየተሰቃየ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ከሐጢያቶቻችን ሊያድነን የሚችለውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ፈልገን ማግኘት ይገባናል፡፡ ነገር ግን አስቀድመው በሐሰተኛ አስተማሪዎች በተመገቡዋቸው ውሸቶች ምክንያት እውነትን መቀበል የማይችሉ ብዙዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሐሳዊ ነቢያቶች የሚሰብኩት ደህንነት ተብዬ ሐጢያት የማትሰሩ ከሆነ ትባረካላችሁ በሚል አባባል ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ 
 
ነገር ግን እኛ ከመነሻችንም ለሐጢያት የታጨን ነን፡፡ ሐጢያት መስራት ልናስወግደው የማንችለው ተፈጥሮዋችን ነው፡፡ ስለዚህ ለዚህ ዓለም ሐጢያቶች ታስረን ብቻ እንቀራለን፡፡ የሐጢያተኞች ልብ በሐሰተኛ ነቢያቶች እንዲህ በዓለም ሐጢያቶች ከታሰረ እንዴት በእግዚአብሄር አምነው ከሐጢያቶቻቸው ሊድኑ ይችላሉ? እነርሱ ወደ እግዚአብሄር ቤተክርስቲያን መመለስ፣ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስማትና በሐጢያቶቻቸው ስርየት አማካይነት እውነተኛውን የልባቸውን ዕረፍት መቀበል አለባቸው፡፡ በዚህ ዓለም የሚኖሩ ብዙ ሰዎች እውነተኛዋን የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በመሻት ደህንነታቸውን ይናፍቃሉ፡፡ ነገር ግን ከእነርሱ አብዛኞቹ ያንን ማግኘት ስለሚሳናቸው መጨረሻቸው ሕግ አጥባቂ ቤተክርስቲያን ውስጥ ይሆናል፡፡ ለሲዖል የታጩት ለዚህ ነው፡፡ 
 
ታዲያ ሐጢያተኞች በእርግጥ የሚፈልጉዋት የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ምን ዓይነት ቤተክርስቲያን ናት? እያንዳንዱ ሐጢያተኛ የሚፈልጋት የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የምትሰብክ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተነገረላት የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን የኢየሱስን ጥምቀትና የመስቀል ላይ ሞቱን ትሰብካለች፡፡ የእግዚአብሄር እውነተኛ ቤተክርስቲያን ኢየሱስ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እንዴት በትክክል የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ እንደወሰደና እንዴት እንዳስወገዳቸው በትክክል እያብራራች ታስተምራለች፡፡ ከሐጢያቶቹ የዳነ እያንዳንዱ ሐጢያተኛ ይህንን ያደረገው በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን አማካይነት የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመስማት ከመጣው እምነት ነው፡፡ 
 
ነገር ግን ብዙ ክርስቲያኖች የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ስላልሰሙና ስላላወቁ ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ መዳን አልቻሉም፡፡ እግዚአብሄር ግን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑትንና የሐሰት ወንጌሎችን ተዋግተው የሚያሸንፉትን ከሐጢያት እንደሚያድናቸው ነግሮናል፡፡ እግዚአብሄር ድል የነሱ ሰዎች በሁለተኛው ሞት እንደማይጎዱ ተስፋ ሰጥቷል፡፡ 
 
ከሐጢያት የመዳኛው እውነተኛው ደህንነት የሚሰጠው ሐሰተኛ አስተማሪዎችን ታግለው ለሚያሸንፉ ብቻ ነው፡፡ ሐጢያተኞች ሆነን ስለተወለድን የሐሰት ትምህርቶችን ድል ካልነሳን መጨረሻችን በሐጢያት ታስረን የሰይጣን እሰረኞች መሆንና በመጨረሻም ለሲዖል መታጨት ነው፡፡ እግዚአብሄር እያንዳንዳችንን በምናደርገው የመንፈሳዊ ደህንነት ጦርነት ውስጥ ጠላቶቻችንን እንድናሸንፍ የነገረን ለዚህ ነው፡፡ 
 
እንደ አንበሶች ወይም ነብሮች ያሉ አንዳንድ እንስሶች ሆነ ብለው ደቦሎቻቸውን ከኮረብታ ላይ ወደ ታች በመግፋት እያሰለጠኑ ራሳቸው ተራራውን እንዲወጡ ያደርጉዋቸዋል ይባላል፡፡ የሚያድጉት ተራራውን መውጣት የቻሉት ደቦሎች ብቻ ይሆናሉ፡፡ ልክ እንደዚሁ እግዚአብሄርም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሰጥቶናል፡፡ እርሱ ሰማይ የሚፈቅደው በዚህ ወንጌል የሐሰት ትምህርቶችን ተዋግተው ለሚያሸንፉት ብቻ ነው፡፡ 
 
ደህንነታችን የተገኘው በራሳችን ደምና ሥጋ አይደለም፡፡ ከሐጢያት መዳን የምንችለው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ብቻ ነው፡፡ እውነተኛ ደህንነት የሚገኘው በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመን ነው፡፡ ልባችን የዓለምን ሐጢያቶች በወሰደው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም ሲያምን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ድነን እርግጠኛ ከሆነው ጥፋታችንም ነጻ እንወጣለን፡፡ ሰማይ የሚገባ ሰው ሁሉ ይህንን የሚያደርገው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ነው፡፡ ልባችን የዓለምን ሐጢያቶች በወሰደው ጥምቀትና በእግዚአብሄር ልጅ የፈሰሰ ደም ሲያምን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ድነን እርግጠኛ ከሆነው ጥፋታችንም ነጻ እንወጣለን፡፡ ሰማይ የሚገባ ሰው ሁሉ ይህንን የሚያደርገው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ነው፡፡ ሰው ሁሉ ሲዖል የሚገባው በዚህ ወንጌል ባለማመኑ ነው፡፡ ሁላችንም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመንና የሐሰት ወንጌሎችን መጣል የሚገባን ለዚህ ነው፡፡ 
 
ሰይጣን የሐሰት ትምህርቶችንና ውሸቶችን በማሰራጨት ሰዎች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን እንዳይድኑ ለመከላከል ይሞክራል፡፡ እነዚህ የሐሰት ትምህርቶች ታዲያ ምንድናቸው? የሐሰት ወንጌሎች ኢየሱስ በጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ አልወሰደም ብለው የሚያስተምሩ ወንጌሎች ናቸው፡፡ እነርሱ ኢየሱስ የአዳምን ሐጢያት ቢወስድም በየቀኑ የምንሰራቸው ሐጢያቶች በየቀኑ የምናቀርባቸው የንስሐ ጸሎቶች መንጻት አለባቸው ብለው ያስተምራሉ፡፡ እነዚህ ትምህርቶች ምናልባት በሐይማኖታዊ አግባብ ስሜት ይሰጡ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በእውነተኛው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ሲታዩ ግን በአጭሩ ውሸት ናቸው፡፡
 
የሰው ሁሉ ደህንነት የሚመጣው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ነው፡፡ የሐሰት ወንጌሎች ፈጽሞ ከሐጢያት አያድኑንም፡፡ እነዚህን የሐሰት ትምህርቶች ተዋግተን ማሸነፍ ያለብን ለዚህ ነው፡፡ ሰይጣንን መዋጋት ማለት ውሸት የሆነውን መቃወም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ወይም በሐሰት ወንጌሎች እናምን እንደሆነ መወሰን አለብን፡፡ ውሳኔያችንን ከወሰንን በኋላ ሌላውን መዋጋት አለብን፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑትም ቢሆኑ እምነታቸው ለብ ብሎ ብቻ የቀረ ከሆነ ሰይጣንን ማሸነፍ አይችሉም፡፡ 
 
ብዙዎቹ የዳኑ ሰዎች በእግዚአብሄር ቃልና በሰይጣን ቃል መካከል ይከራከራሉ፡፡ ሐጢያቶቻቸው ይቅር የተባሉት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ለማመን በወሰኑ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ከፍጥረት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የዳነ ሰው ሁሉ የሐሰት ወንጌሎችን ተዋግቶ ያሸነፈ ነው፡፡ ሁላችንም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማግኘት፣ የሐሰት ወንጌሎችን አለመቀበልና በእምነትም ከሐጢያቶቻችን ሁሉ መዳን አለብን፡፡ 
 
 

የሐሰት ወንጌሎች ምንድናቸው? 

 
ለማብራራት ያህል አንድ ዓይን ብቻ ያላቸው ሰዎች የሚኖሩባት መንደር አለች እንበል፡፡ ሁለት ዓይን ያለው ጎብኚ ወደዚህች መንደር መጣ፡፡ የመንደሪቱ ሰዎች ሁሉት ዓይን ያለውን ይህንን ጎብኚ ‹‹እንግዳ›› ‹‹በሽተኛ›› ‹‹በጣም የተለየ›› ወይም ምናልባትም ‹‹መናፍቅ›› ብለው ይጠሩታል፡፡ ጎብኚውን መናፍቅ ብለው የኮነኑበት ምክንያቱ ብዙሃን ከሆኑት ከእነርሱ የተለየ ስለሆነ ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ በዚህ ዓለም ላይም ‹‹ብዙሃኑ የሚገዛበት›› ወይም በሌላ አነጋገር ‹‹እውነት የብዙሃኑ የሚሆንበት›› አድልዎ አለ፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉ የፍርድ ሚዛኖችና ድምዳሜዎች የተሳሳቱ መሆናቸውን መገንዘብ አለብን፡፡ 
 
በዘላለማዊው ዓለም ውስጥ እውነት የሚወሰነው በብዙሃኑ ሳይሆን ፍጹምና መሰረታዊ በሆኑ ሚዛኖች ነው፡፡ ታዲያ ይህ እውነት ሊገኝ የሚችለው የት ነው? በሐጢያተኞች ደህንነትና ከጥፋት በመዳናቸው ውስጥ ሊገኝ ይችላል፡፡ ጻድቃን የሆኑ ሁሉ የጸደቁት የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በጆሮዎቻቸው ከሰሙና በልባቸውም በዚህ ወንጌል ካመኑ በኋላ ነው፡፡ 
 
ነገር ግን ብዙ ሰዎች ለረጅም ጊዜ በሐሰት ወንጌሎች ውስጥ ስለወደቁ ትክክለኛው ወንጌል ሲገለጥ እንግዳ ወንጌል እንዲያውም ኑፋቄ ነው ብለው በመጥራት ያጥላሉታል፡፡ ነገር ግን እነርሱ ያጥላሉት የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል መነሻው ከሐዋርያት ዘመን የሆነ ሐዋርያቶች ራሳቸው የገለጡት፣ ያመኑበትና የሰበኩት የእውነት ወንጌል ነው፡፡ የሐጢያት ችግር ሊፈታ የሚችለው በእግዚአብሄር ፊት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ብቻ ነው፡፡ 
 
እውነታችን ኢየሱስ ከአሮን ዘር በሆነው በዮሐንስ በመጠመቅ የዓለምን ሐጢያቶች በአንድ ጊዜ በራሱ ላይ በመውሰድ ስለ እኛ በመስቀል ላይ ደሙን ማፍሰሱ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ኢየሱስ በጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንደተሸከመ ይመሰክራል፡፡ ከዚያም በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ ከሙታንም ተነሳ፡፡ በእግዚአብሄር ቀኝ ለመቀመጥም ወደ ሰማይ አረገ፡፡ ይህ እውነት ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ደሙ በመውሰድ የእውነት ጌታ በሆነ ጊዜ የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ተፈጸመ፡፡ 
 
ነገር ግን ውሸቶችን በማመን የሳቱ ሰዎች አሁንም ድረስ በኢየሱስ በማመን ሙሉ በሙሉ ከሐጢያት እንደሚድኑ አያውቁም፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ በዛሬው የክርስትና ዓለም ውስጥ ያሉ ብዙ ነፍሳቶች በሐሰተኛ ወንጌሎች ግራ ተጋብተው በሐጢያት የጠፉ መሆናቸው ነው፡፡ በእውነተኛው የውሃና የመንፈስ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች ይህንን ወንጌል አብልጠውና ጨምረው መስበክና ማሰራጨት ያለባቸው ለዚህ ነው፡፡ ሰዎች ከሐጢያቶቻቸው መዳን የሚችሉት ይህንን እውነተኛ ወንጌል በማመን ብቻ ነው፡፡ 
 
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠው እውነት የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው፡፡ (ማቴዎስ 3፡13-17፤ኤፌሶን 1፡13) ከላይ በተጠቀሰው ምንባብ ውስጥ እግዚአብሄር ቁሳዊ ድሆች ቢሆኑም በእምነታቸው ባለጠጎች እንደሆኑ በመናገር የሰርምኔስን ቤተከርስቲያን አመስገኖዋል፡፡ አይሁዶችን ግን የሰይጣን አገልጋዮች ብሎ ጠራቸው፡፡ ምክንያቱም እነርሱ በእግዚአብሄር እናምናለን ቢሉም የእርሱን የደህንነት ወንጌል ገናም በልባቸው ውስጥ ለመቀበል አሻፈረኝ ብለዋልና፡፡ ጌታችን ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የወሰደላቸው ቢሆንም እነርሱ ኢየሱስን የእግዚአብሄር ልጅና አዳኝ አድርገው አላመኑትም፡፡ እነርሱ አሁንም ድረስ በያህዌህ አምላክ እናምናለን ቢሉም ኢየሱስ ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ የመውሰዱን እውነታ ባለመቀበላቸው በልባቸው ውስጥ ሐጢያት መኖሩን ቀጥሎዋል፡፡ 
 
እንደዚህ ያሉ ሰዎች በከንፈራቸው በእግዚአብሄር እናምናለን ይላሉ፤ በተጨባጭ ግን በእርሱ የማያምን ‹‹የሰይጣን ማህበር›› ናቸው፡፡ በኢየሱስ እናምናለን እያሉ ገናም መዳናቸውን በልባቸው ያልተቀበሉ ሰዎችም እንደዚሁ የሰይጣን ማህበር ናቸው፡፡ 
 
በዚህ ዓለም ላይ ሁለት ማህበሮች ያሉ ሲሆን አንዱ የሰይጣን ሌላው የእግዚአብሄር ነው፡፡ ጌታ ሲመለስ የሰይጣን ማህበር ለዘላለም ይጠፋል፡፡ የእግዚአብሄርም ማህበር ለዘላለም ይባረካል፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር ጻድቃንን ከሐጢያተኞች በግልጽ ይለያል፡፡ ኢየሱስን አዳኙ አድርጎ እንደሚያምን የሚናገር እያንዳንዱ ሰው ሰማይ አይገባም፡፡ 
 
ይህም ኢየሱስ በማቴዎስ 7፡21-23 ላይ በነገረን ነገር በግልጽ ተብራርቷል፡፡ ‹‹በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ በዚያ ቀን ብዙዎች፡- ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን በስምህስ ብዙ ተዓምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ የዚያን ጊዜ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመጸኞች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ፡፡›› 
 
በሌላ አነጋገር ሰማይ በኢየሱስ አምናለሁ ለሚልና ስሙን ለሚጠራ ሰው ሁሉ ዋስትና ሊሆን አይችልም፡፡ እነርሱ ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው ቢያምኑም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማያምኑ ከሆኑ በመጨረሻ ለሲዖል የታጩ የሰይጣን አገልጋዮች ናቸው፡፡ በኢየሱስ እናምናለን ቢሉም ሐሰተኛ ወንጌሎችን ስለሚከተሉ ወደ ሲዖል መውረዳቸው ትክክልና ተገቢ ይሆናል፡፡ 
 
ሐጢያት ያለባቸውና የሰይጣን ባሮች የሆኑ ሰዎች ለሲዖል የታጩ ናቸው፡፡ ነገር ግን እኛ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አምነን የሐጢያቶቻችንን ሁሉ ስርየት ያገኘን ሰዎች የሰማይ ደጆች ይከፈታሉ፡፡ በኢየሱስ የሚያምን ሰው ሁሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ሰማይ መግባት አለባቸው፡፡ 
 
እኛ ከዓለም ሐጢያቶች እንድንድን ስለ ሐጢያታችን ግልጽ የሆነ እውቀት ሊኖረን የሚገባ ብቻ ሳይሆን እውነትን ከውሸቶች የመለየት መንፈሳዊ ችሎታም ሊኖረን ይገባል፡፡ ይህንን ለማድረግ በተጻፈው የእግዚአብሄር ቃል ላይ መደገፍና በዚያ መሰረትም ማመን አለብን፡፡ ወደ እሳት ባህር መጣል የማትፈልጉ ከሆነ በእምነት የሐሰት ወንጌሎችን መጣል አለባችሁ፡፡ ከሐሰተኛ ወንጌሎች ጋር የምታደርጉትን ውጊያ ማሸነፍ አለባችሁ፡፡ የእምነት ድላችሁን ለማረጋገጥም የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ምን እንደሆነ ማወቅ አለባችሁ፡፡ ከሁለተኛው ሞት ማምለጥ የምትችሉት ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ወደ እግዚአብሄር ገነት መግባት የምትችሉት ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ 
 
2ኛ ዮሐንስ 1፡7 እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ገብተዋልና፤ እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የማያምኑ ናቸው፡፡ ይህ አሳቹና የክርስቶስ ተቃዋሚው ነው፡፡›› እዚህ ላይ አሳቹ የሚያመላክተው ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ወደዚህ ምድር መምጣቱን የማያምኑ ሰዎችን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እነርሱ ሥጋ ለብሶ የመጣው ጌታ የእግዚአብሄር ልጅ እንደሆነ፣ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉም በዮርዳኖስ ወንዝ በጥምቀቱ እንደወሰደና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ለሐጢያቶቻችን በእኛ ምትክ እንደተፈረደበት ይክዳሉ፡፡ 
 
እርሱ የሐጢያቶቻችንን ፍርድ በሙሉ ከእኛ እንደወሰደ እነዚህን እውነታዎች የማይቀበሉ ሰዎች አሳቾችና የሰይጣን አገልጋዮች ናቸው፡፡ እነዚህ የእግዚአብሄር ጠላቶችና ታማኝ የዲያብሎስ አገልጋዮች ናቸው፡፡ እነርሱ ግራ ተጋብተው የሐሰት ወንጌሎቻቸውን በማስተማርና በማሰራጨት፣ እንደዚሁም እውነተኛውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል በመቃወም ብዙ ሰዎችን ወደ ጥፋት ይነዳሉ፡፡
 
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እናምናለን እያሉ የሰይጣንን ሐሰተኛ ወንጌል በመቃወም መንፈሳዊውን ጦርነት የማይዋጉ ውለው አድረው የእግዚአብሄር መንግሥትና የሕዝቡ ጠላቶች ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ተከታዮቻቸው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ቢያምኑ ወይም ባያምኑ ግድ አይሰጣቸውም፡፡ እነርሱ ግድ የሚሰጣቸው ነገር ቢኖር ክብራቸውና ሐብታቸው ብቻ ነው፡፡ እነዚህ የራሳቸውን ሆድ የመሙላት ፍላጎት ብቻ ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በአጭሩ እነርሱ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርለት የጸረ ክርስቶስ ባሮች ናቸው፡፡
 
 
የመናፍቃን ማታለያዎች፡፡ 
 
ሕዝቅኤል 13፡17-18 እንዲህ ይላል፡- ‹‹አንተም የሰው ልጅ ሆይ ከገዛ ልባቸው ትንቢት በሚናገሩ በሕዝብህ ሴቶች ልጆች ላይ ፊትህን አድርግ፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፡፡ እንዲህም በል፡- ጌታ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፤ ነፍስን ለማጥመድ ለእጅ ድጋፍ ሁሉ መከዳ ለሚሰፉ ለሰውም ሁሉ ራስ እንደ የቁመቱ ሽፋን ለሚሰሩ ሴቶች ወዮላቸው! የሕዝቤንም ነፍስ ብታጠምዱ በውኑ ነፍሳችሁን ታድናላችሁን?›› ከዚህ ምንባብ የሰይጣን ባሮች የሰዎችን ነፍስ እንዴት ለመንጠቅ እንደሚሹ ማየት ትችላላችሁ፡፡
 
ምንባቡ የሰይጣን አገልጋዮች በሰዎች የእጅ ድጋፍ መከዳዎች ላይ አስማታዊ ማባበያዎችን እንደሚሰፉ ይነግረናል፡፡ በእጆቻችሁ ላይ መከዳዎች መሰፋታቸው ምን ያህል የማያመችና የሚረብሽ ምን ያህልም ለሌሎች የሚያስጸይፍ ይሆን? የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሳያውቁም ሆነ ሳያምኑ በቤተክርስቲያን ውስጥ የአመራር ቦታዎች የተሰጡዋቸው ሰዎች በትክክል ይህንን ይመስላሉ፡፡ አመቺ ያልሆነ የሚረብሽና የሚያስጸይፍ! ለምን? ምክንያቱም እነዚህ የቤተክርስቲያን ሥልጣኖች ለእነርሱ የሚመቹ አይደሉምና፡፡ እነርሱ እንዳልጸደቁ ወይም ዳግም እንዳልተወለዱ ያውቃሉ፡፡ ምክንያቱም ገና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን ይኖርባቸዋል፡፡
 
ታዲያ እንዴት ለጌታ ሊሰሩ ይችላሉ? ስለዚህ በቤተክርስቲያን ውስጥ አንዳች ሥልጣን ከመቀበላችሁ በፊት የእግዚአብሄርን ሥራዎች ለመስራት ልታደርጉት የሚገባችሁ የመጀመሪያው ነገር በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የሐጢያቶቻችሁን መቤዠት መቀበል፣ መንፈስ ቅዱስ በልባችሁ ውስጥ እንደሚኖር ማረጋገጥና ከዚያም በእግዚአብሄር ቃልና በእውነቱ በሚገባ መሰልጠን ነው፡፡
 
እግዚአብሄር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእርሱ ሕዝብ ለሆንነው ለእኛ በእርሱ እውነት በማመን ሐሰተኛ ነቢያቶች ተዋግተን ማሸነፍ እንደሚገባን ነግሮናል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዳግመኛ መወለድ ምንም ነገር ባለማድረግ አይገኝም፡፡ የሚገኘው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመንና የእግዚአብሄርን ጽድቅ በማግኘት ነው፡፡ ማቴዎስ 11፡12 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከመጥምቁ ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል፡፡›› ግፈኞች የተባሉት ከውሸት ጋር ስለሚዋጉ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ መዳን የምትችሉት የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በልባችሁ ውስጥ በመቀበልና የሐሰት ትምህርቶችን በማሸነፍ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በልባችሁ ውስጥ ማደር የሚችለው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡
ሰው ሙሉ ወደሆነ መዳን ይደርስ ዘንድ ወደዚህ ምድር የተወለደ ሁሉ ውሸትን በእግዚአብሄር የእውነት ቃል መዋጋትና ማሸነፍ አለበት፡፡ ይህ ዓለም በእውነት ሐይሎችና በውሸት ሐይሎች፤ ዳግመኛ በተወለዱና ዳግመኛ ባልተወለዱ መካከል ጦርነት የሚደረግበት አውድ ነው፡፡ አዳምና ሔዋን እግዚአብሄር ሕይወትን ቢሰጣቸውም የእግዚአብሄርን ቃል ከማመን ይልቅ የዲያብሎስን ውሸቶች በማመናቸው ይህ ዓለም በእግዚአብሄርና በሰይጣን መካከል የጦር ሜዳ ሆኖዋል፡፡
 
ይህ ዘመን በተለይ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰይጣን ቀኖቹ እንደተቆጠሩ ስለሚያውቅ ሰዎችን በሐሰተኛ ነቢያቶች ግራ በማጋባት፣ በሐሰተኛ ተዓምራቶች በማሳትና የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች ሆነው በተሸፈኑ የሐሰት ሥራዎቹ በማታለል የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ከማመን ሊያግዳቸው እየሞከረ ነውና፡፡ ‹‹ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና፡፡›› (2ኛ ቆሮንቶስ 11፡14) ሰይጣን ዋና ዋና ሐይማኖቶችን አሸንፎ ሲያበቃ ጻድቃንን ይቃወማል፡፡ ምንም እንኳን ይህ ዘመን ውሸቶች እውነትን የጋረዱበት ዘመን ቢሆንም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች በመጨረሻ ውሸት ከሆነው ሁሉ ነጻ ወጥተው አሸናፊዎች ይሆናሉ፡፡
 
እኛ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ለመዳን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመንና የሐጢያቶቻችንን ይቅርታ ለማግኘት በየቀኑ ንስሐ መግባት አለብን ከሚሉት የሐሰት ትምህርቶች መራቅ አለብን፡፡ እግዚአብሄር እነዚህን ውሸቶች በእርሱ እውነት የሚያሸንፉ ሰዎች በሁለተኛው ሞት እንደማይጎዱ ተስፋ ሰጥቷል፡፡ እኛም ደግሞ ለጌታ ባለን ታማኝነት ከእርሱ ዘንድ ምስጋናን እንቀበል ዘንድ በእግዚአብሄር ፊት እምነታችንን ለመጠበቅ ልክ በፊታችን እንደቀደሙት የሰርምኔስ ቤተክርስቲያን ቅዱሳኖች እንጋደል፡፡