Search

उपदेश

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[6-1] እግዚአብሄር የወሰናቸው ሰባቱ ዘመናቶች፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 6፡1-17 ››

እግዚአብሄር የወሰናቸው ሰባቱ ዘመናቶች፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 6፡1-17 ››
‹‹በጉም ከሰባቱ ማህተም አንዱን በፈታ ጊዜ አየሁ፡፡ ከአራቱም እንስሶች አንዱ ነጎድጓድ በሚመስል ድምጽ፡- መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ፡፡ አየሁም እነሆም አምባላይ ፈረስ ወጣ፡፡ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፡፡ አክሊልም ተሰጠው፡፡ ድልም እየነሳ ወጣ ድል ለመንሳት፡፡ ሁለተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ፡- መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ፡፡ ሌላም ዳማ ፈረስ ወጣ፡፡ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፡፡ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው፡፡ ሦስተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ፡- መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ፡፡ እነሆም ጉራቻ ፈረስ ወጣ፡፡ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ፡፡ በአራቱም እንስሶች መካከል ድምጽ፡- አንድ አርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፤ ዘይትንና ወይንንም አትጉዳ ሲል ሰማሁ፡፡ አራተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምጽ፡- መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ፡፡ እነሆም ሐመር ፈረስ ወጣ፡፡ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ፡፡ ሲዖልም ተከተለው፡፡ በሰይፍና በራብም፣ በሞትም፣ በምድርም አራዊት ይገደሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛው እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው፡፡ አምስተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ ስለ እግዚአብሄርና ቃልና ስለጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሰውያው በታች አየሁ፡፡ በታላቅ ድምጽም እየጮሁ፡-ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ፡፡ ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፡፡ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቁጥር እስኪፈጸም ድረስ እንዲያርፉ ተባለላቸው፡፡ ስድስተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ አየሁ፡፡ ታላቅም ምድር መናወጥ ሆነ፡፡ ጸሐይም እንደ ማቅ ጠጉር ጥቁር ሆነ፡፡ ጨረቃም በሞላው እንደ ደም ሆነ፡፡ በለስም በብርቱ ነፋስ ተናውጣ ቃርያዋን ፍሬ አንደምትጥል የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ወደቁ፡፡ ሰማይም እንደ መጽሐፍ ተጠቅልሎ አለፈ፡፡ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከሥፍራቸው ተወሰዱ፡፡ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት፣ ሻለቃዎችም፣ ባለጠጋዎችም፣ ሐይለኛዎችም፣ ባርያዎችም፣ ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ፡፡ ተራራዎችንና ዓለቶችንም፡- በላያችን ውደቁ፤ በዙፋንም ላይ ከተቀመጠው ከበጉ ቁጣ ሰውሩን፤ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና ማንስ ሊቆም ይችላል? አሉአቸው፡፡›› 
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
ቁጥር 1፡- ‹‹በጉም ከሰባቱ ማህተም አንዱን በፈታ ጊዜ አየሁ፡፡ ከአራቱም እንስሶች አንዱ ነጎድጓድ በሚመስል ድምጽ፡- መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ፡፡››
ይህ ቁጥር ኢየሱስ እግዚአብሄር ለሰው ዘር ያለውን ጠቅላላ ዕቅድ የተመዘገበበትን የመጀመሪያውን የመጽሐፉን ዕቅድ እንደከፈተ ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 2፡- ‹‹አየሁም እነሆም አምባላይ ፈረስ ወጣ፡፡ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፡፡ አክሊልም ተሰጠው፡፡ ድልም እየነሳ ወጣ ድል ለመንሳት፡፡››
የመጀመሪያው የእግዚአብሄር ማህተም የሰውን ዘር ከሐጢያት ለማዳን በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሄር ዕቅድ ውስጥ ስለተመሰረተው የውሃና የመንፈስ ወንጌልና የዚህን ዕቅድ ድል አድራጊነት ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር አብ የሰውን ዘር ከሐጢያቶቻቸው በማዳን ሕዝቡ ለማድረግ ያቀደው ዕቅድ የጀመረው በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ማለትም የሰውን ዘር በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ አማካይነት ከሐጢያት በማዳን ነው፡፡
እግዚአብሄር በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ነፍሳቶችን ከዓለም ሐጢያቶች አድኖዋል፡፡ አሁን እየተነጋገርን ሳለንም ይህንን ማድረጉን ቀጥሎዋል፡፡ እግዚአብሄር ለሰው ዘር ያቀደው የመጀመሪያው ዕቅድ ይህ ነው፡፡ ይህ የመጀመሪያው የእግዚአብሄር ዕቅድ በኢየሱስ ወደዚህ ምድር መምጣት፣ በጥምቀቱ፣ በስቅለቱና በትንሳኤው አማካይነት የሰውን ዘር ያዳነበት ዕቅዱ ነው፡፡
ይህ የአምባላዩ (ነጩ) ፈረስ ዘመን እግዚአብሄር የሰውን ዘር ከሐጢያቶቹ ሁሉ ለማዳን በፈጸመው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የጽድቅ ጦርነት ውስጥ ያለውን ድል ያመላክታል፡፡ ይህ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ማሸነፉን እንደሚቀጥልም ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 3-4፡- ‹‹ሁለተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ፡- መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ፡፡ ሌላም ዳማ ፈረስ ወጣ፡፡ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፡፡ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው፡፡››
ይህ እግዚአብሄር በወሰነው በሁለተኛው ዘመን ዓለም ወደ ሰይጣን ዓለምነት እንደሚለወጥ ይነግረናል፡፡ የዳማው (ቀዩ) ፈረስ መገለጥ ማለት ዓለም በሰይጣን ግዛት ሥር ይወድቃል ማለት ነው፡፡
ሰይጣን በዚህ ዓለም ላይ ጦርነትን በማምጣት ሰላምዋን እየወሰደ ነው፡፡ ከእርሱ የተነሳ አለም በሁለት የዓለም ጦርነቶች ውስጥ አልፎ በዚህ ምክንያት በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ የተረፉትም ሰዎች ባልተረጋጋና በማያስተማምን ሰላም ውስጥ ኖረዋል፡፡ አሁንም እንኳን በመላው ዓለም የሚገኙ አገሮችና መንግሥታቶች እርስ በርሳቸው ስለማይተማመኑ እርስ በርሳቸው እየተዋጉ በመሆናቸው በብዙ ሥፍራዎች ሰላም እየጠፋ ነው፡፡ ይህ ዘመን የጦርነትና የዕልቂት ዘመን ነው፡፡
 
ቁጥር 5-6፡- ‹‹ሦስተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ፡- መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ፡፡ እነሆም ጉራቻ ፈረስ ወጣ፡፡ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ፡፡ በአራቱም እንስሶች መካከል ድምጽ፡- አንድ አርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፤ ዘይትንና ወይንንም አትጉዳ ሲል ሰማሁ፡፡››
እግዚአብሄር የሚናገረው ሦስተኛው ዘመን የጉራቻው (ጥቁሩ) ፈረስ ዘመን ለሰው ዘርም የሥጋዊና የመንፈሳዊ ረሃብ ዘመን ነው፡ ዛሬ በመላው ዓለም ከመንፈሳዊ ረሃባቸው የተነሳ ብዙ ሰዎች አልዳኑም፡፡ እጅግ ብዙ ሰዎችም በሥጋዊ ረሃብ እየሞቱ ነው፡፡ አሁን እየኖርን ያለነው በዚህ በሦስተኛው ዘመን ውስጥ እንደሆነ ማስታወስ አለብን፡፡ ይህ ዘመን ሲያልፍ የሐመሩ ፈረስ ዘመን ይመጣል፡፡
 
ቁጥር 7-8፡- ‹‹አራተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምጽ፡- መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ፡፡ እነሆም ሐመር ፈረስ ወጣ፡፡ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ፡፡ ሲዖልም ተከተለው፡፡ በሰይፍና በራብም፣ በሞትም፣ በምድርም አራዊት ይገደሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛው እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው፡፡››
እግዚአብሄር የወሰነው አራተኛው ዘመን የሐመሩ ፈረስ ዘመን ነው፡፡ ጸረ ክርስቶስ ተግባሮቹን የሚጀምረው በዚህ ዘመን እንደሆነና ይህ ዘመንም ለቅዱሳን የሰማዕትነት ዘመን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ይህ ዘመን ጸረ ክርስቶስ የቅዱሳኖችን እውነተኛ እምነት ለመስረቅ ለእርሱ የማይሰግዱትን ወይም ምልክቱን የማይቀበሉትን የሚያሳድድበትና የሚገድልበት ዘመን ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዓለም በሰባቱ መቅሰፍቶች ቅጣት ውስጥ ይወድቃል፡፡ በዚህ ዘመን ቅዱሳኖች ሰማዕት ከመሆን አያመልጡም፡፡
 
ቁጥር 9-11፡- ‹‹አምስተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ ስለ እግዚአብሄርና ቃልና ስለጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሰውያው በታች አየሁ፡፡ በታላቅ ድምጽም እየጮሁ፡-ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ፡፡ ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፡፡ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቁጥር እስኪፈጸም ድረስ እንዲያርፉ ተባለላቸው፡፡››
አምስተኛው የእግዚአብሄር ዘመን የቅዱሳኖች ትንሳኤና ንጥቀት ዘመን ነው፡፡ ከዚህ ዘመን በኋላ የሺህው ዓመት መንግሥት ይጀምራል፡፡ ይህ ምንባብ እኛን በሚጠብቀን ሰማዕትነት፣ ትንሳኤና ንጥት ማመን እንደሚገባንና እግዚአብሄር ተስፋ በሰጠን አዲስ ሰማይና ምድር ላይ ባለን እምነታችንና ተስፋችን መኖር እንዳለብን ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 12፡- ‹‹ስድስተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ አየሁ፡፡ ታላቅም ምድር መናወጥ ሆነ፡፡ ጸሐይም እንደ ማቅ ጠጉር ጥቁር ሆነ፡፡ ጨረቃም በሞላው እንደ ደም ሆነ፡፡››
ስድስተኛው የእግዚአብሄር ዘመን እግዚአብሄር የፈጠረው የመጀመሪያው ዓለም የሚጠፋበት ዘመን ነው፡፡ የሰባቱ ጸዋዎች መቅሰፍቶች በዓለም ላይ የሚወርዱት በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ጸሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብቶች ይጨልማሉ፡፡ ምድርም ከመሬት መናወጦች የተነሳ ውሃ ውስጥ ትሰምጣለች፡፡
 
ቁጥር 13፡- ‹‹በለስም በብርቱ ነፋስ ተናውጣ ቃርያዋን ፍሬ አንደምትጥል የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ወደቁ፡፡ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከሥፍራቸው ተወሰዱ፡፡››
በዚህ በስድስተኛው ዘመን እግዚአብሄር የፈጠረው ዩኒቨርስ በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ይወድማል፡፡ ከዋክብቶች ከሰማይ ሲወድቁና ምድርም ስትገለባበጥ ታላቅ ግርግር ይፈጠራል፡፡
 
ቁጥር 14፡- ‹‹ሰማይም እንደ መጽሐፍ ተጠቅልሎ አለፈ፡፡ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወሰዱ፡፡››
ይህ ቁጥር የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ሲወርዱ ሰማይ እንደ መጽሐፍ ተጠቅልሎ እንድሚያልፍ ይናገራል፡፡ ተራሮችና ደሴቶችም ሁሉ ከሥፍራቸው ይወሰዳሉ፡፡ እነዚህ የዓለምን ተፈጥሮአዊ መዋቅር የሚለውጡ ምድር አንቀጥቅጥ ጥፋቶች ናቸው፡፡
 
ቁጥር 15፡- ‹‹የምድርም ነገሥታትና መኳንንት፣ ሻለቃዎችም፣ ባለጠጋዎችም፣ ሐይለኛዎችም፣ ባርያዎችም፣ ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ፡፡››
በዚህ በስድስተኛው ማህተም ዘመን እግዚአብሄር የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች ሲያወርድ በዚህች ምድር ላይ በበጉ ቁጣ የማይንቀጠቀጡ ነገሥታቶችም ሆኑ ሐይለኛዎች ማናቸውም በሕይወት አይኖሩም፡፡
 
ቁጥር 16፡- ‹‹ተራራዎችንና ዓለቶችንም፡- በላያችን ውደቁ፤ በዙፋንም ላይ ከተቀመጠው ከበጉ ቁጣ ሰውሩን፤››
የእግዚአብሄር ቁጣ በጣም ታላቅ ስለሚሆን የሰው ዘር በፍርሃት ይንቀጠቀጣል፡፡ እያንዳንዱ የሰው ዘር በፍርሃት የሚመታበት የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ጊዜ ይህ ይሆናል፡፡
 
ቁጥር 17፡- ‹#ታላቁ የቁጣው ቀን መጥጦአልና ማንስ ሊቆም ይችላል? አሉአቸው፡፡››
የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ሲወርዱ እያንዳንዱ ሰው ምንም ያህል ሐያል ወይም ብርቱ ቢሆን ከላይ ከእግዚአብሄር ቁጣ በሚወረዱባቸው ታላላቅ ጥፋቶች ፈርተው ይንቀጠቀጣሉ፡፡ ሳይፈራ በእግዚአብሄር ቁጣ ፊት መቆም የሚችል ሰው የለም፡፡
ታዲያ ሰባተኛው ዘመን ምንድነው? በእግዚአብሄር የተወሰነው ሰባተኛው ዘመን ቅዱሳን በሺህው ዓመት መንግሥት ውስጥ የሚኖሩበት ዘመን ነው፡፡ እርሱን ተከትሎም ለዘላለም የሚኖሩበት አዲስ ሰማይና ምድር ይመጣል፡፡