Search

တရားဟောချက်များ

ርዕስ 8፡ መንፈስ ቅዱስ

[8-9] ንጹህ ያደረገን የኢየሱስ ጥምቀት ወንጌል ‹‹ ኤፌሶን 2፡14-22 ››

ንጹህ ያደረገን የኢየሱስ ጥምቀት ወንጌል
‹‹ ኤፌሶን 2፡14-22 ››
‹‹እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሃደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትዕዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፤ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሄር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፡፡ መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፤ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና፡፡ እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሄር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም፡፡ በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተመቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሄር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ፡፡››
 
 

በድህነቱ ምክንያት በማደጎ የተሰጠ ልጅ

 
ሰውን ከእግዚአብሄር የነጠለው ምንድነው?
የነጠለው ሐጢያቱ ነው፡፡
 
የኮርያ ጦርነት ካለፈ ግማሽ ክፍለ ዘመን አልፎታል፡፡ ሆኖም በኮርያ ሕዝቦች መካከል ከፍተኛ ቁስልን ትቶ አልፎዋል፡፡ በኮርያ ጦርነት ማግስት ብዙ ልጆች በውጪ አገራት ለማደጎ ተሰጥተዋል፡፡ በዚያን ወቅት የተባበሩት መንግስታት ጦር ወደ ኮርያ ገብቶ በብዙ ቢያግዘንም ወታደሮቹ ከወጡ በኋላ ግን ብዙ ሕጻናት ያለ አባት ቀርተዋል፡፡
እዚህ ሚስቶችና ልጆች የነበሩዋቸው ብዙዎቹ የተባበሩት መንግስታት ወታደሮች ወደ አገራቸው በተመለሱ ጊዜ ቤተሰቦቻቸውን ትተው ነበር፡፡ ከእነዚህ ልጆች ብዙዎቹም በእናቶቻቸው ወደ ማደጎ ልጆች ማሳደጊያ ማዕከሎች በማደጎነት ተላኩ፡፡ ከዚያም ማደጎ ሆነው ወደተለያዩ የውጪ አገሮች ተወሰዱ፡፡ እነዚህ ልጆች አሳዳጊ ወላጆች አግኝተው በደንብ ማደግ መቻላቸው በጣም ጥሩ ዕድል ነበር፡፡ 
እነዚህ በማደጎ የተወሰዱ ልጆች እየጎለመሱ ሲሄዱ ከወላጆቻቸውና ከጎረቤቶቻቸው የተለዩ መሆናቸውን ሲያውቁ ኮርያ ከምትባል ሩቅ አገር በማደጎነት እንደመጡ ተረዱ፡፡ ‹‹ወላጆቼ ለምን ተዉኝ? ወደዚህ አገር የላኩኝ ስለጠሉኝ ነውን?›› እነዚህ ልጆች በጨቅላ አእምሮዋቸው ምን እንደተከሰተ መረዳት አልቻሉም፡፡  
እውነተኛ ወላጆቻቸውን ለማወቅ ያላቸው ጉጉትና ለእነርሱ ያላቸው ጥላቻ እነርሱን ለመገናኘት ከነበራቸው ናፍቆት ጋር ጎን ለጎን ሆኖ ማደግ ጀመረ፡፡ ‹ወላጆቼ ምን ይመስሉ ይሆን? ይህንን ያደረጉት ስለጠሉኝ ነውን? አይደለም፤ ምናልባት ለዚህ ምክንያት ይኖር ይሆናል፡፡› እነርሱ ምናልባትም ብዙ የማይገቡዋቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ጥላቻም ሊሰማቸው ይችል ይሆናል፡፡ በሌላ ጊዜም ስለዚህ ጉዳይ ዳግመኛ ላለማሰብ ወስነው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ከማወቃቸው በፊት ጊዜው ነጉዶ ልጆቹ ጎለመሱ፤ ትዳር መሰረቱ፤ ልጆችንም ወለዱ፤ የራሳቸውንም ቤተሰብ መሰረቱ፡፡
በእነዚህ ልጆች የተመሰጥሁት በአገር ውስጥ ከሚሰራጩት የቴሌቪዥን ስርጭቶች በአንዱ ፕሮግራም አማካይነት ነበር፡፡ በዚህ ፕሮግራም አንድ የቴሌቪዥን ሪፖርተር በማደጎነት ተወስዳ አሁን ጀርመን አገር ከምትኖር አንዲት ሴት ጋር ቃለ ምልልስ ታደርግ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ይህች ሴት በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል ላይ የምትገኝ ነበረች፡፡ የምታጠናውም ስነ መለኮት ነበር፡፡ በመጀመሪያ ሴቲቱ ከሪፖርተሮቹ ጋር ላለማግኘት በጣም ሞክራ ነበር፡፡ እርስዋ የማደጎ ልጅ እንደሆነች ማንም እንዲያውቅባት አልፈለገችም ነበር፡፡ ሪፖርተሩ ለቃለ ምልልስ ፈቃደኛ መሆን ወደ ውጪ አገሮች በማደጎነት የመወሰዱን ማዕበል ሊገታ እንደሚያግዝ መረዳት እንዳለባት ባሳመናት ጊዜ ተስማማች፡፡
ጋዜጠኛዋ ካቀረበችላት ጥያቄዎች አንዱ ‹‹እውነተኛ ወላጆችሽን ብታገኚያቸው ምን ትያለሽ? ብዙ ለማወቅ የምትጓጊው ምንድነው?›› የሚል ነበር፡፡ ሴቲቱም ስትመልስ ‹‹ለምን በማደጎነት እንደሰጡኝ መረዳት አልቻልሁም፡፡ ጠልተውኝ እንደሆነ እጠይቃቸዋለሁ›› አለች፡፡ የወለደቻት እናቷ ሴቲቱ በቴሌቪዥን የምታደርገውን ቃለ ምልልስ ተመልክታ ከጣቢያው ጋር ተገናኘች፡፡ ሴት ልጅዋን መገናኘት እንደምትፈልግም ተናገረች፡፡ ሁለቱ የተገናኙት በዚህ መንገድ ነበር፡፡   
እናት በጣም ቀደም ብላ ወደ አየር ማረፊያ በመሄድ የሴት ልጅዋን መምጣት ጠበቀች፡፡ ያቺ ወጣት ሴት ከመውጫው በር ብቅ ስትል እናቷ እዚያ ቆማ ታለቅስ ነበር፡፡ 
እነዚህ ሁለት ሰዎች በጭራሽ ፊት ለፊት ተገናኝተው አያውቁም፡፡ እናት ያደገችውን ሴት ልጅዋን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየቻት በቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ ስታደርግ ነበር፡፡ የሚናገሩት ቋንቋ የተለያየ ቢሆንም በልቦቻቸውና በተለዋወጡት የስሜት ምልክቶች መነጋገር ችለዋል፡፡ የእርስ በርሳቸውን ፊቶች እየዳሰሱ ሳለ እናት ላደረገችው ነገር ይቅርታን ለመነች፡፡ ማድረግ የቻለችው ነገር ቢኖር ማልቀስና ማዘንዋን ደጋግማ መናገር ነበር፡፡
እናት ሴት ልጅዋን ወደ ቤቷ ይዛት መጣች፡፡ ሁለቱም አብረው ማዕድ ተቋደሱ፡፡ ሴት ልጅዋ መናገር የምትችለው የጀርመን ቋንቋ ብቻ ነበር፡፡ እናት ደግሞ መናገር የምትችለው የኮርያ ቋንቋ ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህ በቃላት ልውውጥ መግባባት አልቻሉም፡፡ ነገር ግን እናትና ልጅ በመሆናቸው እርስ በርሳቸው መግባባት ችለው ነበር፡፡ ብዙ ቃላት አልባ ንግግሮችን አድርገዋል፡፡ በፊት ገጽታዎቻቸው አንዳቸው የሌላኛውን ፊት በመዳሰስና በልቦቻቸውና በአይኖቻቸው በመነጋገር ራሳቸውን ገልጠዋል፡፡  
ሴቲቱ ወደ ጀርመን በተመለሰች ጊዜ የወለደቻት እናቷ እንደወደደቻት አወቀች፡፡ ቀደም ያለውን ቃለ ምልልስ ያደረጉት እነዚያው ጋዜጠኞች ከመሄድዋ በፊት እንደገና አነጋግረዋት ነበር፡፡ ‹‹እናቴ ለምን በማደጎነት እንደሰጠችኝ መጠየቁ አስፈላጊ አይደለም፡፡ እናቴ አሁንም እንኳን ደሃ ናት፡፡ በዚህ አገር የሚኖሩ ባለጠጎች በጣም ሐብታሞች ስለሆኑ ከውጪ የገቡ መኪኖችን ይነዳሉ፡፡ እናቴ ግን አሁንም በድህነት እየኖረች ነው፡፡›› እንዲህ በማለትም ቀጠለች፡፡ ‹‹ያንን ጥያቄ እናቴን ጠይቄ መልስ ባላገኝም እኔን የሰደደችኝ ከድህነት ልታድነኝ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ ያንን ጥያቄ መጠየቁ አስፈላጊ ሆኖ ያልተሰማኝና ጥርጣሬዎቹና ጥላቻው ሁሉ የጠፉት ለዚህ ነው፡፡››  
 
 
ሰዎች በልባቸው ውስጥ ካለው ሐጢያት የተነሳ ከእግዚአብሄር ተለይተዋል
 
ከእግዚአብሄር ለምን ተነጠልን? ለምንስ ወደ እርሱ መቅረብ አልቻልንም? በማደጎነት የተሰጠችው ሴት የወለደቻት እናቷ እርስዋን የሰደደቻት ከድህነት ልታድናት መሆኑን ተማረች፡፡ ይህ ስለ እግዚአብሄርም እውነት ነውን? እግዚአብሄር በራሱ አምሳል ፈጥሮናል፡፡ ከእርሱ ሊለየን የቻለው ምንድነው? መልሱ ሰይጣን ሰው ሐጢያትን እንዲሰራ ፈተነው፤ ሐጢያትም ከእግዚአብሄር ለየው የሚል ነው፡፡
በመጀመሪያ እግዚአብሄር በራሱ አምሳል ፈጠረውና ፍጥረቱንም በእጅጉ ወደደ፡፡ ሰዎች የተፈጠሩት የእግዚአብሄር ፍቅር መገለጫ ሆነው ነበር፡፡ ከማንኛውም ሌላ ፍጥረት ሁሉ የሚበልጥም ክብር ነበራቸው፡፡ ሆኖም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራ የወደቀ መልአክ ሰውን ከእግዚአብሄር ለመነጠል ሰራ፡፡ ሰይጣን ሰው በእግዚአብሄር ቃሎች እንዳያምን ፈተነውና መልካምንና ክፉን ከምታስታውቀው ዛፍ ፍሬ እንዲበላ አደረገው፡፡
ከዚህ የተነሳ ሰው በሐጢያቱ ምክንያት ከእግዚአብሄር ተለየ፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ላይ አመጸ፡፡ ሰው የዘላለምን ሕይወት ከሚሰጠውና እግዚአብሄር ከፈቀደው የሕይወት ዛፍ አልበላም፡፡ ነገር ግን የመልካምንና የክፉን ዕውቀት ከሚሰጠው የተከለከለ ዛፍ በላ፡፡ በውጤቱም ሰው ከእግዚአብሄር ተለየ፡፡   
ቀደም ብሎ የእግዚአብሄር ፍቅር መገለጫ የነበረው ሰው አመጸና ከዕብሪት የተነሳም ከአምላክ ተለየ፡፡ ሰው በልቡ ውስጥ ባለው ሐጢያት ምክንያት ውሎ አድሮ ከእግዚአብሄር ተነጠለ፡፡ ከዚያ በኋላ ሰው ለረጅም ጊዜ ከእግዚአብሄር ተነጠለና ‹‹እግዚአብሄር ከፈጠረን በኋላ ለምን ተወን? ለምን ሐጢያት እንድንሰራ ፈቀደልን? ደካሞች ካደረገን በኋላስ ለምን ወደ ሲዖል ይልከናል? ከመጀመሪያውኑ ባይፈጥረን ይሻል ነበር›› እያለ ማጉረምረሙን ቀጠለ፡፡ ዳግም ከመወለዳችን በፊት ጥያቄዎችን እንደዚሁም የማወቅ ጉጉቶችን፣ ጥርጣሬዎችንና ጥላቻን ይዘን ስንኖር ነበር፡፡  
በማደጎ የተወሰደችውን ሴት በቴሌቪዥን ፕሮግራም ባየኋት ጊዜ በሰውና በእግዚአብሄር መካከል ያለው ግንኙነትም እርስዋ ከእውነተኛ እናቷ ጋር ከነበራት ግንኙነት ጋር ተመሳሳይ እንደነበር ተረድቻለሁ፡፡ ችግር፣ አለመግባባት፣ ዕርግማን ወይም ማንኛውም አይነት ሐጢያት ሰውን በማናቸውም ሁኔታዎች ከእግዚአብሄር ሊነጥለው ይችላል፡፡ ምንም እንኳን በእግዚአብሄርና በሰው መካከል ያለው ግንኙነት የተመሰረተው በፍቅር ላይ መሆኑን ብረዳም አለመግባባቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡   
እናት ሴት ልጅዋን የሰደደቻት ከጥላቻ የተነሳ እንዳልነበረ ሁሉ እግዚአብሄርም ራሱን ከሰው የነጠለው ከጥላቻ የተነሳ  ሳይሆን ከሐጢያት የተነሳ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የሚጠላበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ሰዎችም እግዚአብሄርን የሚጠሉበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ እኛ እርስ በርሳችን እንዋደዳለን፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ተለይቶ የቀረው በሰይጣን ከተታለለ በኋላ ሐጢያተኛ ስለሆነ ነው፡፡
 
 

እግዚአብሄር በኢየሱስ አማካይነት አቅፎናል  

 
‹‹አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋልና፡፡ እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሃደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትዕዛዛት ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድ አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፡፡›› (ኤፌሶን 2፡13-15) ኢየሱስ የትዕዛዛትን ሕግ ለመሻር በዮሐንስ ተጠምቆ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወሰደ፡፡ ከዚያም ሰውን ከሐጢያቶቹ ለማዳንና በእግዚአብሄር ለመታቀፍ እንዲፈቀድለት በመስቀል ላይ ደሙን አፈሰሰ፡፡ አሁን እግዚአብሄር በእርሱ የነጹትን አቅፎዋቸዋል፡፡
ውሃ ስለሌበት ዓለም አስባችሁ ታውቃላችሁን? በቅርቡ በኮርያ ከሚገኙት እጅግ ታላላቅ ወደቦች አንድዋ በሆነችው በኢንቾን ከተማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጉባኤ ላይ ተገኘሁ፡፡ በዚያን ወቅት የቧንቧ ውሃ ለጥቂት ቀኖች መስራት አቁሞ ስለነበር ‹‹ሰዎች ያለ ውሃ መኖር አይችሉም›› ብዬ አሰብሁ፡፡
እግዚአብሄር ይህንን ዓለም ለአንድ ወር ያህል ውሃ አልባ ቢያደርገው ከሽታው ከቆሻሻውና መቋቋም ከማይቻለው ጥማት ጋር አብሮ በከተማ ውስጥ መኖር የማይቻል በሆነ ነበር፡፡ እግዚአብሄር የሰጠንን ውሃ ዋጋ ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ውሃ ለሰዎች ፈጽሞ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ኢየሱስ በዮሐንስ በኩል በዮርዳኖስ ወንዝ የተቀበለውም ጥምቀት በእኩል ደረጃ አስፈላጊ ነው፡፡
ኢየሱስ በዮሐንስ ለመጠመቅ ወደዚህ ዓለም ባይመጣ ኖሮ በኢየሱስ የሚያምኑ ምዕመናን እንዴት የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ማግኘት ይችሉ ነበር? ሰዎች ያለ ውሃ መኖር እንደማይችሉ ዮሐንስም ኢየሱስን ባያጠምቀው ኖሮ በዚህ ዓለም ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው ከሐጢያቶቹ የተነሳ ይሞት ነበር፡፡
ሆኖም የኢየሱስ ጥምቀት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ስለወሰደ አሁን ልባችን እንደነጻና በደህንነት እንደተባረክን በማወቃችን ድፍረት ይሰማናል፡፡ የኢየሱስ ጥምቀት ለእምነታችን ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የእርሱ  ጥምቀት ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ለመቀበል ፈጽሞ አስፈላጊያችን ነው፡፡
ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ የሆነው ጴጥሮስ እንዲህ አለ፡- ‹‹ይህም ውሃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፡፡›› (1ኛ ጴጥሮስ 3፡21) የጴጥሮስ አረፍተ ነገር ኢየሱስ ከሐጢያቶቻችን ሊያድነን በአጥማቂው ዮሐንስ እንደተጠመቀና ደሙን እንዳፈሰሰ ይናገራል፡፡ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ያነጻው የኢየሱስ ጥምቀት እውነተኛ ወንጌል ነው፡፡  
አሁን በዘጸአት 30፡17-21 ላይ ስላለው የመታጠቢያ ሰን የተጻፈውን ምንባብ እንመልከት፡- ‹‹እግዚአብሄርም ሙሴን እንዲህ እንዲህ ብሎ ተናገረው፡- የመታጠቢያ ሰንና መቀመጫውን ከናስ ስራ፡፡ በመገናኛው ድንኳንና በመሰዊያው መካከል እርሱን አድርገህ ውሃን ትጨምርበታለህ፡፡ ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡበታል፡፡ ወደ መገናኛው ድንኳን በገቡ ጊዜ ለእግዚአብሄርም የእሳት መሥዋዕት ያቃጥሉ ዘንድ ወደ መሠዊያው ሊያገለግሉ በቀረቡ ጊዜ እንዳይሞቱ ይታጠቡበታል፡፡ እንዳይሞቱም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡ፡፡ ይህም ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ የዘላለም ሥርዓት ይሆንላቸዋል፡፡››       
በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በድንኳኑና በመሠዊያው መካከል የተቀመጠ የእጥበት ውሃ የያዘ የመታጠቢያ ሳህን ነበር፡፡ ይህ የመታጠቢያ ሳህን በመገናኛው ድንኳን ባይኖር ኖሮ መስዋዕቶችን የሚያቀርቡት ካህናቶች ምን ያህል ቆሻሻ በሆኑ ነበር፡፡
ለሕዝቡ በጣም ብዙ የዘወትር መስዋዕቶችን ያቀርቡና እጆቻቸውን በሐጢያት ቁርባኖች ላይ በመጫን ከዚያም ይገድሉዋቸው የነበሩትን ካህናት ምን ያህል ደምና ቆሻሻ ያቆሽሻቸው ነበር? በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የመታጠቢያው ሰን ባይኖር ኖሮ ካህኑ በጣም ቆሻሻ ይሆን ነበር፡፡   
እግዚአብሄር የመታጠቢያውን ሰን ያዘጋጀላቸው በንጹህ እጆች ወደ እርሱ መቅረብ ይችሉ ዘንድ ነበር፡፡ ሐጢያተኞች እጆቻቸውን ለሐጢያት በሚያቀርቡዋቸው ቁርባኖች ራስ ላይ በመጫን ሐጢያቶቻቸውን አሻገሩ፡፡ ከዚያም ካህናቶች በእነርሱ ፋንታ ለእግዚአብሄር ሰዉላቸው፡፡ እግዚአብሄር የናሱን የመታጠቢያ ሰን ያዘጋጀው ካህናቶች ወደ ቅድስቱ ክፍል እንዲገቡና እንዳይሞቱም በውሃ ይታጠቡ ዘንድ ነው፡፡ ካህኑ እንኳን ለመስዋዕት በቀረበው እንስሳ ደም ረክሶ ወደ ቅድስቱ ስፍራ ሊገባ አይችልም፡፡ ካህናቶች ለሕዝቡ መስዋዕቶችን ካቀረቡ በኋላ ወደ እግዚአብሄር መቅረብ ይችሉ ዘንድ ቆሻሻውን ሁሉ በመታጠቢያው ሰን ውስጥ ባለው ውሃ መታጠብ የነበረባቸው ለዚህ ነው፡፡  
 
 

የኢየሱስ ጥምቀት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ አነጻ

 
ኢየሱስ በዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቁ የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ወደ እርሱ ተሻገሩ፡፡ ሙሉ በሙሉ በውሃ ውስጥ መጥለሙም ሞቱን ሲያመለክት ከውሃው መውጣቱ ደግሞ ትንሣኤውን ያመለክታል፡፡ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ በዮሐንስ የተጠመቀው የዓለምን ሐጢያት በሙሉ ለመውሰድ ነው፡፡ በመስቀል ላይ በመሞትም የሐጢያትን ዋጋ ከፈለ፡፡ የእርሱ ሞት የሐጢያታችንን ዋጋ የሚከፍል ነበር፡፡ ትንሳኤውም የዘላለምን ሕይወት ሰጠን፡፡ 
ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን ሁሉ እንደወሰደ ባናምን ኖሮ ልቦቻችን በሐጢያት የተሞሉ ይሆን ነበር፡፡ እንደዚያ ከሆነ እንዴት ወደ እግዚአብሄር መቅረብ ይቻለን ነበር? የሐጢያቶቻችንን ስርየት የሚነግረን ወንጌል የአንድ ቤተክርስቲያን ትምህርት ሳይሆን የእግዚአብሄር እውነት ነው፡፡ 
ፍጹም የሆነ እውቀት ሳይኖረን እምነታችንን መተግበር አንችልም፡፡ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ በዮሐንስ ስለመጠመቁ ግድ የማይሰጠን ከሆነ ዓለምን ማሸነፍ አንችልም፡፡ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ በሕይወት ለመቆየት ውሃ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ በእምነት ለመኖርና መንግስተ ሰማያት ለመግባት የሐጢያቶቻችን ስርየትና የኢየሱስ ጥምቀት ውሃ ያስፈልገናል፡፡ ኢየሱስ እኛን ከሐጢያቶቻችን ለማዳን መጠመቅ፣ በመስቀል ላይ መሞትና መነሳት ነበረበት፡፡ ይህ ከሙሉ ልባችን ልናምነው የሚገባን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው፡፡ 
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ቢሞትም እንዲህ ያለ ቅጣት እንዲቀበል የሚያደርገው ምንም ነገር አልሰራም፡፡ እርሱ ሐጢያቶቻችንን ለማንጻት ወደዚህ ዓለም መጣ፡፡ በ30 አመቱ ተጠመቀ፡፤ በ33 አመቱም በመስቀል ላይ በመሞት መድህናችን ሆነ፡፡ ምንም ያህል ሐጢያተኞችና ደካሞች ብንሆንም እግዚአብሄር የሰውን ዘር ልጆቹ ለማድረግ ፈለገ፡፡ ኢየሱስ የተጠመቀው ለዚህ ነበር፡፡ እግዚአብሄር የሐጢያቶቻችንን ስርየትና የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ በተመሳሳይ ጊዜ ሰጥቶናል፡፡ 
‹‹ኢየሱስም መልሶ፡- እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሄር መንግስት ሊገባ አይችልም፡፡›› (ዮሐንስ 3፡3-5) ኢየሱስ የተጠመቀው ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ለማንጻት መሆኑን ማወቅና ማመን ይኖርባችኋል፡፡ አንድ ሰው ዳግም የተወለደ ክርስቲያን ቢሆንም እንኳን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንደወሰደ የሚናገረውን እውነት ደጋግሞ የማያሰላስለው ከሆነ ልቡ ፈጥኖ ይረክሳል፡፡ እኛ ሥጋዊ ፍጡራን ስለሆንን በቀን ተቀን ሕይወታችን በሐጢያት ወደ መርከስ እናዘነብላለን፡፡ የኢየሱስን ጥምቀት፣ ደሙንና ትንሳኤውን በማሰላሰል ሁሌም በእምነት መኖር ያለብን ለዚህ ነው፡፡ ይህ እምነት መንግስተ ሰማያት እስክንገባበት ቀን ድረስ ደግፎ ይይዘናል፡፡ 
ኢየሱስ ለሐጢያቶቻችን ከመጠመቅና ከመሞት በቀር ሌላ ምርጫ አልነበረውም፡፡ እንደዚህ በማድረጉ ደህንነትን እንደሰጠን ማመን አለብን፡፡ ከዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ለመዳን በዚህ ውብ ወንጌል ከማመን በቀር የምናደርገው አንዳች ነገር የለም፡፡
የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የሰጠንን ጌታን እናመሰግነዋለን፡፡ እግዚአብሄር የሰጠን እጅግ ትልቁ ስጦታ እኛን በጥምቀቱ አማካይነት ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ለማዳን አንድያ ልጁን መላኩ ነው፡፡
ወደ እግዚአብሄር መቅረብ ያልቻልነውና ከእርሱ ተለይተን ለመኖር የተገደድነው በልቦቻችን ውስጥ ሐጢያት ስላለብን ነው፡፡ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለመውሰድ በዮሐንስ ተጠምቆ እግዚአብሄርንና ሰውን የለየውን ግድግዳ ለማፍረስ በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ በእግዚአብሄርና በሰው መካከል ያለው ግንኙነት የተመለሰው በጥምቀቱና በደሙ ነው፡፡ ሥጋዊ ወላጅ ለልጁ ያለው ፍቅር ታላቅ ነው፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ሐጢያተኞችን ካዳነበት የእግዚአብሄር ፍቅር ጋር አይወዳደርም፡፡
የኢየሱስ ጥምቀትና ደሙ ሁለቱም አስፈላጊ ናቸው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ውሃ ባይኖር ኖሮ ሕይወት ያለው ነገር በሕይወት ይቆይ ነበርን? ያለ ኢየሱስ ጥምቀት በልቡ ውስጥ ሐጢያት የሌለበት ሰው ባልኖረም ነበር፡፡ ኢየሱስ ባይጠመቅና በመስቀል ላይ ባይሞት ኖሮ ማንም የሐጢያቶችን ስርየት አያገኝም ነበር፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ኢየሱስ ተጠመቀና ለእኛ ፍጹም የሆነ መስዋዕት ሆነልን፡፡ እኛ ጎዶሎዎችና ውዳቂዎች ብንሆንም በእርሱ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ በማመን መንፈስ ቅዱስን መቀበል እንችላለን፡፡
በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ሞቱ የሚያምኑ ሰዎች ወደ እግዚአብሄር መቅረብ፣ መጸለይና እርሱን ማመስገን ይችላሉ፡፡ አሁን የእርሱ ልጆች ስለሆንን ጌታን ማመስገንና ማምለክ እንችላለን፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ጸጋና በረከት ነው፡፡ የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደሙ ወንጌል በእርግጥም ድንቅ ነው፡፡ ሁላችንም በዚህ ውብ ወንጌል በማመን ደህንነትንና መንፈስ ቅዱስን መቀበል እንችላለን፡፡