‹‹የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ለሮሜ ሰዎች›› የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ ሆኖ ሊገለጥ ይችላል፡፡ መልዕክቱ በዋናነት ሰው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን እንዴት የእግዚአብሄርን ጽድቅ ማግኘት እንደሚችል የሚያሳይ ነው፡፡ ሮሜ ከያዕቆብ መልዕክት ጋር ሲነጻጸር አንድ ሰው ሮሜን ‹‹ቃለ ሐብቶች›› ያዕቆብን ደግሞ ‹‹ገለባ ቃሎች›› በማለት ገልጦዋቸዋል፡፡ ነገር ግን ያዕቆብም ልክ እንደ ሮሜ የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ ብቸኛው ልዩነት ሮሜ ክቡር መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስን ጠቅለል ያለ ዕይታ ያቀርባልና፡፡ ያዕቆብ ክቡር የሆነው ነገር ግን ጻድቁ በእግዚአብሄር ፈቃድ እንዲኖር የሚያደርገው ቃል ነው፡፡
ጳውሎስ የተባለው ሰው ማነው?
በመጀመሪያ ሮሜ 1፡1-7ን እንናብብ፡- ‹‹ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያ ጳውሎስ በነቢያቱ አፍ በቅዱሳን መጽሐፍት አስቀድሞ ተስፋ ለሰጠው ለእግዚአብሄር ወንጌል ተለየ፡፡ ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሳት የተነሳ በሐይል የእግዚአብሄር ልጅ ሆኖ ስለተገለጠ ስለ ልጁ ነው፡፡ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በእርሱም ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ከእምነት የሚነሳ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን፡፡ በእነርሱም መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ ልትሆኑ የተጠራችሁ እናንተ ደግሞ ናችሁ፡፡ በእግዚአብሄር ለተወደዳችሁና ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ በሮሜ ላላችሁት ሁሉ ከእግዚአብሄር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡››
እነዚህ መልዕክቶች ‹‹ጳውሎስ በሮሜ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ያቀረባቸው ሰላምታዎች›› ሆነው ሊቆጠሩ ይችሉ ይሆናል፡፡ ጳውሎስ የእግዚአብሄር ጽድቅ የሆነ የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያ ሆኖ ሰላምታ ያቀርብላቸዋል፡፡
ቁጥር 1 ‹‹ጳውሎስ ማነው?›› ስለሚለው ጥያቄ ይናገራል፡፡ እርሱ የተነሳውን ጌታ በደማስቆ መንገድ ላይ የተገናኘና ወንጌልን ለአሕዛቦች ለማዳረስ የጌታ የተመረጠ ዕቃ (የሐዋርያት ሥራ 9፡15) የነበረ አይሁዳዊ ነበር፡፡
ጳውሎስ በብሉይ ኪዳን የመስዋዕት ስርዓትና ትንቢቶች ላይ የተመሰረተውን እውነተኛ ወንጌል አሰራጨ፡፡
በቁጥር 2 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ በብሉይ ኪዳን ቃሎች ላይ የተመሰረተውን ወንጌል ሲያሰራጭ ነበር፡፡ ‹‹የእግዚአብሄርን ወንጌል›› ‹‹በነቢያቱ አፍ በቅዱሳን መጽሐፍት አስቀድሞ ተስፋ የሰጠው›› አድርጎ ገልጦታል፡፡ በዚህ ጥቅስ አማካይነት ሐዋርያው ጳውሎስ በብሉይ ኪዳን የመስዋዕት ስርዓት ላይ በመመስረት የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንደሰበከ ማየት እንችላለን፡፡ ከዚህም በላይ ቁጥር 2 ጳውሎስ የወንጌልን ሥራ ለመስራት የተመረጠ እንደነበር ይጠቁማል፡፡
‹‹በነቢያቱ አፍ በቅዱሳን መጻህፍት›› የሚለወ ሐረግ በብሉይ ኪዳን የመስዋዕት ስርዓት ወይም ትንቢቶች ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመላክ የተገቡትን የእግዚአብሄር ተስፋዎች ያመላክታል፡፡ ሙሴን፣ ኢሳይያስን፣ ኤርምያስንና ዳንኤልን ጨምሮ የብሉይ ኪዳን ነቢያቶች በሙሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ የዓለምን ሐጢያቶች ከወሰደ በኋላ እንደሚሞት የሚናገረውን እውነት መስክረዋል፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ያቀረበው ወንጌል ምን ይመስላል? እርሱ የእግዚአብሄር ልጅ ስለሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ሰበከ፡፡
አንዳንድ ሰዎች የብሉይ ኪዳን ቃሎች አስቀድመው ተፈጽመዋል ይላሉ፡፡ ሌሎችም የማቴዎስ 11፡13ን ቃሎች እንደ ማስረጃ በማቅረብ በዚህ ጉዳይ ላይ ግትር ይላሉ፡፡ አንዳንድ በጣም የታወቁ ወንጌላውያንም ብሉይ ኪዳንን በሙሉ ትተውታል፡፡
ሆኖም እግዚአብሄር በብሉይ ኪዳን አማካይነት ተስፋን ሰጥቶናል፡፡ ይህንን ተስፋም በአዲስ ኪዳን ውስጥ በኢየሱስ በኩል ፈጽሞታል፡፡ ስለዚህ በእምነት ዓለም ውስጥ አዲስ ኪዳን ከብሉይ ኪዳን ውጪ ሊኖር አይችልም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም የብሉይ ኪዳን ቃሎች ከአዲስ ኪዳን ቃሎች ውጭ ሊፈጸሙ አይችሉም፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ለእግዚአብሄር ወንጌል ተመረጠ፡፡ አሁን ጥያቄው ‹‹እርሱ ምን አይነት ወንጌል ሰበከ?›› የሚለው ነው፡፡ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም በመምጣት በብሉይ ኪዳን ላይ ተመስርቶ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ያዳነን የመሆኑን እውነታ ሰበከ፡፡ ስለዚህ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በምንሰብክበት ጊዜ ሁሉ ይህንን ማድረግ ያለብን በብሉይ ኪዳን ትንቢቶችና የመስዋዕት ስርዓት ላይ በመመርኮዝ ነው፡፡ ሰዎች የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እውነት መሆኑንና አዲስ ኪዳንም የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎች ፍጸሜ መሆኑን ወደ ማመን የሚመጡት ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡
ከአዲስ ኪዳን ጅማሬ አንስቶ ኢየሱስ ከዮሐንስ የተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደሙ ላይ ትኩረት እየተደረገ ማግኘት እንችላለን፡፡ በብሉይ ኪዳን ስልቻ ውስጥ ሐጢያተኛው ቤዛነትን የሚያገኝበት የመስዋዕት ስርዓት ነበረ፡፡ ሐጢያተኛው እጆቹን ለሐጢያት በቀረበው እንስሳ ራስ ላይ በመጫን ሐጢያቱን ያሻግርና ለሐጢያቱ ይቅርታን ያገኝ ዘንድ እንስሳውን ያርዳል፡፡
ያን ጊዜ በብሉይ ኪዳን የሐጢያት ስርየትን ለማግኘት እጆችን መጫንና የመስዋዕት እንስሶች ደም ያስፈልግ ከነበረ በአዲስ ኪዳንስ ምን ነበር? ኢየሱስ የተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደሙ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሰው ሊቀ ካህን (ዘሌዋውያን 16፡21) በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከአጥማቂው ዮሐንስ ጋር የሚተካከል ነበር፡፡
ቁጥር 3 እና 4 ‹‹ኢየሱስ ምን አይነት ሰው ነበር?›› ስለሚለው ጥያቄ ይናገራሉ፡፡ ቁጥሮቹ ስለ ትውልድ ባህሪው ያብራራሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ከዳዊት ቤተሰብ የተወለደ ነበር፡፡ በቅድስና መንፈስም በትንሳኤው ሐይል ከሙታን በመነሳቱ የእግዚአብሄር ልጅ ሆኖ ታወቀ፡፡ ስለዚህ ውሃውንና ደሙን በእርሱ ለሚያምኑት በመስጠት አዳኝ ሆነ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑት የደህንነት አምላክ፣ የነገሥታት ንጉሥና ዘላለማዊ የሰማይ ሊቀ ካህን ሆነ፡፡
በአንዳንድ የክርስትና ስነ መለኮት አስተምህሮቶች ውስጥ የኢየሱስ መለኮታዊነት ተክዶዋል፡፡ እነዚህ የስነ መለኮት አስተምህሮቶች ‹‹እርሱ ድንቅ ወጣት ብቻ ነበር›› ይላሉ፡፡ ከዚህም በላይ በአዲሱ የስነ መለኮት አስተምህሮት መሰረት ‹‹በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ ደህንነት አለ››፤ ስለዚህ ለዘብተኛ በሆኑ ሴሚናሪዎች ውስጥ ሰዎች ጥንቆላን፣ ቡዲዝምን፣ ካቶሊካዊነትንና በዚህ ዓለም ላይ የሚገኙ ሌሎች ሃይማኖቶችን ሁሉ ይቀበሉ ዘንድ ግፊት እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ለዘብተኛ ስነ መለኮት ወይም አዲሱ ስነ መለኮታዊ አስተምህሮት ተብዬ እያንዳንዱ ነገር ክብር ሊሰጠው ይገባል፤ ስለዚህ ሰዎች ሁሉ ተባብረው ‹‹አንድ›› መሆን ይገባቸዋል ይላል፡፡
ነገር ግን እግዚአብሄር በመጀመሪያ ሰማያትንና ምድርን እንደፈጠረ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ተነግሮዋል፡፡ ታዲያ እግዚአብሄር ማነው? ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹ክርስቶስ›› የሚለው ስም በዘይት የተቀባ ማለት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ሊቀ ካህኑ አንድን ንጉሥ ወይም ነቢይ ራሶቻቸውን ይቀባ ነበር፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ የነገሥታት ንጉሥ ሆኖ ተገልጦልናል፡፡ ኢየሱስ አምላክ እንደሆነ የሚክድ ሰው በእግዚአብሄር የሚያምን አማኝ አይደለም፡፡
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች እምነት በሃይማኖታዊ አንድነት ላይ ወደተመሰረተ አብሮነት እየተለወጠ ነው፡፡ እንደ ቡዲዝምና እንደ ኮንፊሺያኒዝም ካሉ አረማዊ ሃይማኖቶች የተወሰዱ ሁሉንም ነገሮች አንድ ላይ በማቀናበር ምስጋናንና አምልኮን ያቀርባሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጉባኤው በቡዲስት መንገድ ያመልካል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ በክርስቲያን መንገድ ያመልካል፡፡ ጣፋጭ ምግብ ይኖር ይሆናል፤ ነገር ግን እምነትን በሚመለከት ንጹህ ቢሆን ይመረጣል፡፡
ስለዚህ በቁጥር 3 እና 4 ላይ ‹‹ኢየሱስ ማነው?›› ለሚለው ጥያቄ መልሱ በትንሳኤው ሐይል ከሙታን በመነሳቱ የእግዚአብሄር ልጅ ሆኖ እውቅና የተሰጠው ነው የሚለው ነው፡፡ ክርስቶስ ጌታና አዳኝ ሆነልን፡፡
ቁጥር 5 እና 6 ጳውሎስ እንዴት ሐዋርያ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እርሱ አሕዛቦችም በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ደህንነትን ማግኘት ይችሉ ዘንድ ወንጌልን ለእነርሱ የሚሰብክ ምስክር ሆነ፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ምን አይነት ሥልጣን ነበረው?
በቁጥር 7 ላይ እንደተጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ ምዕመናንን በእግዚአብሄር ስም በኢየሱስ በኩል የመባረክ ሥልጣን ነበረው፡፡ የአንድ ሐዋርያ ሥልጣን ሰዎችን ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መባረክ የመቻል መንፈሳዊ ሐይል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ ጳውሎስ እንዲህ ማለት ቻለ፡፡ ‹‹ከእግዚአብሄር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡››
እዚህ ላይ ስለዚህ ቡራኬ ጥቂት ማሰብ እወዳለሁ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሰዎች ቡራኬዎችን የመስጠት ሥልጣን እንደነበረው ይመስላል፡፡ እኛም የእሁድ አምልኮዎችን በምንጨርስበት ጊዜ ሁሉ የምናጠናቅቀው በቡራኬዎች ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሄር ለቅዱሳን የዚህ አይነት በረከት መስጠት ይፈልጋል፡፡›› የመጀመሪያዎቹ የበረከት ቃሎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
በዘሁልቁ 6፡22 እንጀምር፡፡ ‹‹እግዚአብሄርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፡፡ ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው፡፡ የእስራኤልን ልጆች ስትባርኩዋቸው እንዲህ በሉአቸው፡፡ እግዚአብሄር ይባርክህ ይጠብቅህም፤ እግዚአብሄር ፊቱን ያብራልህ ይራራልህም፤ እግዚአብሄር ፊቱን ወደ አንተ ያንሳ ሰላምንም ይስጥህ፡፡››
ሊቀ ካህኑ አሮንና ልጆቹ ‹‹የእስራኤልን ልጆች ስትባርኩዋቸው እንዲህ በሉአቸው›› ተብሎ ተነገራቸው፡፡ እስራኤሎችን በዚህ መንገድ የሚባርኩ ከሆነ እግዚአብሄርም በመጽሐፍ ውስጥ እንደተናገረው በትክክል ይባርካቸዋል፡፡ የጳውሎስን መልዕክቶች በሙሉ ስንመለከት እርሱ ብዙውን ጊዜ ‹‹የጌታችን ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን›› ብሎ ሲናገር ማየት እንችላለን፡፡ ይህም በረከቶችን የሚሰጠው እርሱ ሳይሆን እግዚአብሄር መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክቶቹን ባጠናቀቀ ጊዜ ሁሉ ሁልጊዜም ቅዱሳኖችን ይባርካል፡፡
እግዚአብሄር ሰማያዊ ሥልጣን የሰጠው ለባሮቹ ብቻ ሳይሆን ዳግም ለተወለዱ ቅዱሳንም ሁሉ ነው፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሐጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፡፡ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል፡፡›› (ዮሐንስ 20፡23) እርሱ የዚህ አይነቱን ሥልጣን ለጻድቃን ሁሉ ሰጥቶዋል፡፡ ስለዚህ ዳግም የተወለዱ ቅዱሳኖች ወይም የእርሱን ባሮች ለመቃወም የሚሞክር ሰው ቢጠነቀቅ ይሻለዋል፡፡ ምክንያቱም ይህ እግዚአብሄርን እንደ መቃወም ነው፡፡ እግዚአብሄር የመባረክንና የመርገምን ሥልጣን ለሐዋርያቶቹ እንዲሁም ለባሮቹና ለቅዱሳኑ ሰጥቶዋል፡፡
መንፈሳዊ ስጦታን ለቅዱሳን ሊያካፍል የተመኘው ሐዋርያው ጳውሎስ፡፡
ሮሜ 1፡8—12ን እናንብብ፡- ‹‹እምነታችሁ በዓለም ሁሉ ስለተሰማች አስቀድሜ ስለ ሁላችሁ አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ፡፡ በልጁ ወንጌል በመንፈሴ የማገለግለው እግዚአብሄር ምስክሬ ነውና፡፡ ምናልባት ብዙ ቆይቼ ወደ እናንተ አሁን እንድመጣ በእግዚአብሄር ፈቃድ መንገዴን እንዲያቀናልኝ እየለመንሁ ሁልጊዜ ስጸልይ ስለ እናንተ ሳላቋርጥ አሳስባለሁ፡፡ ትጸኑ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታን እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እናፍቃለሁና፡፡ ይህንም ማለቴ በመካከላችን ባለች በእናንተና በእኔ እምነት አብረን በእናንተ እንድንጽናና ነው፡፡››
ሐዋርያው ጳውሎስ ከሁሉ አስቀድሞ እግዚአብሄርን ያመሰገነው ለምንድነው? በሮም ስላሉ ክርስቲያኖች እግዚአብሄርን አመሰገነ፡፡ ምክንያቱም እነርሱ በኢየሱስ አምነዋልና፡፡ በእነርሱ አማካይነትም ወንጌል ለሌሎች ሰዎች ተሰብኮዋል፡፡
በቁጥር 9 እና 10 ላይ ‹‹ሐዋርያው ጳውሎስ በወንጌል አገልግሎት ጉዞው ወቅት ወደ ሮም መሄድ የፈለገው ለምንድነው?›› የሚል ጥያቄ የሚያነሳ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በዚያን ጊዜ የውሃውና መንፈሱ ወንጌል በሮም ቢሰበክ በመላው ዓለም ይሰራጭ ስለነበር ነው፡፡ ዛሬ መላው ዓለም ወደ አሜሪካ እንደሚያንጋጥጥ ሁሉ ‹‹መንገዶች ሁሉ ወደ ሮም ያደርሳሉ›› እንደሚለው አባባል ሮም የዓለም ማዕከል ነበረች፡፡
እኛ በአሜሪካ ብዙ የወንጌል ሥራ እየሰራን ነው፡፡ ይህንን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በአሜሪካ የምናሰራጭ ከሆንን ብዙ ሚሽነሪዎች ይነሱና ይህንን ውብ ወንጌል ለሌሎች ለመስበክ ወደ ዓለም ሁሉ ይወጣሉ፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ ወደ ሮም ለመሄድ በጣም ተመኘ፡፡
ጳውሎስ የተናገረለት መንፈሳዊ ስጦታ፡፡
በቁጥር 11 ላይ እንዲህ ተጽፎዋል፡- ‹‹ትጸኑ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እናፍቃለሁና፡፡››
ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎች ይጸኑ ዘንድ አንዳች መንፈሳዊ ስጦታ ስለማካፈል ሲናገር ምን ማለቱ ነው? እየተናገረ ያለው መንፈሳዊ ስጦታ እኛ እየሰበክነው ያለው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው፡፡ በቁጥር 12 ላይ እንዲህ ተጽፎዋል፡- ‹‹ይህንንም ማለቴ በመካከላችን ባለች በእናንተና በእኔ እምነት አብረን በእናንተ እንድንጽናና ነው፡፡›› ትጸኑ ዘንድ አንዳች መንፈሳዊ ስጦታ ማካፈልና ሰዎችንም በጳውሎስና በእነርሱ የጋራ እምነቶች ላይ ተመርኩዞ ማደፋፈር ያስፈለገው ጳውሎስ የውሃውንና መንፈሱን ወንጌል በማቅረብ ሰዎች እንዲያርፉ፣ መጽናናትን እንዲያገኙ፣ በረከቶችን እንዲቀበሉና ተመሳሳይ በሆነ እምነት ውስጥ ሕብረት እንዲያደርጉ ስለፈለገ ነው፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ የጋራ በሆኑ እምነቶች ከእነርሱ ጋር አብሮ መጽናት እንደሚፈልግ መናገሩ የውሃውንና የመንፈስን ወንጌል እንደገና ለሮሜ ቤተክርስቲያን ለመስበክ እንደጓጓ ያሳያል፡፡ የቤተክርስቲያን አባሎቻችን በሙሉ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማወቅ በተጨባጭ ያምኑበታል፡፡ ነገር ግን በጊዜ ሂደት ውስጥ በእውነተኛው ወንጌል የማያምኑ አንዳንድ አስመሳይ ክርስቲያኖች ብቅ ይሉ ይሆናል፡፡ ልክ እንደዚሁ በሮሜ ያለችው ቤተክርስቲያንም የሚያጽናና ወንጌል ሳያስፈልጋት አልቀረም፡፡
ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ በውስጡ ባሉ የጋራ እምነቶች መጽናናት ይችል እንደሆነ ተናገረ፡፡ በእግዚአብሄር ፊት መጽነናትን መቀበላቸን እርግጥ ነው፡፡ ለውሃውና ለመንፈሱ ወንጌል ምስጋና ይድረሰውና ልቦቻችንም በሰላም ማረፍ አይሆንልንም፡፡
እንዲህ ተብሎ ተጽፎዋል፡- ‹‹ትጸኑ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እናፍቃለሁና፡፡›› ይህ መንፈሳዊ ስጦታ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው፡፡ አንድ ሰው የእግዚአብሄር ልጅ መሆንና በረከቶችን መቀበል የሚችለው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ሲያምን ብቻ ነው፡፡
ነገር ግን ሰዎች በሆነ መንገድ በኢየሱስ ቢያምኑም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሳያውቁ ሲጋራ ማጤስን፣ መጠጥ መጠጣትን በታማኝነት ቢያቆሙና አንዳች ስህተቶችን ባይፈጽሙ ምን ጥቅም አለው? የእነርሱ ምግባሮች ከእግዚአብሄር ጽድቅ ጋር የሚገናኙበት ምንም ነገር የለም፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ ከሰብአዊ ፍጡራኖች ጽድቅ እጅግ የላቀ ነው፡፡ ሰዎችን ወደ ቤተክርስቲያን ማምጣት ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን ለሐጢያቶቻቸው ሁሉ ይቅርታን በማግኘት የሰማይን መንፈሳዊ በረከቶች ለብሰው የእግዚአብሄር ልጆች መሆን እንዲችሉ ለእነዚህ አዳዲስ ነፍሳቶች የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስበክ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ያሉ ቅዱሳን በእርሱ እምነት እንዲጽናኑ ፈለገ፡፡ ስለዚህ እንዲህ አለ፡- ‹‹ይህንም ማለቴ በመካከላችን ባለች በእናንተና በእኔ እምነት አብረን በእናንተ እንድንጽናና ነው፡፡›› ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ እርሱ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ባለው እምነቱ ይጸኑ ዘንድ እምነት እንዲኖራቸው እውነተኛውን ወንጌል ለቤተክርስቲያን ሁሉ መስበክ ነበረበት፡፡ በሮም ቤተክርስቲያን ለሚገኙ ምዕመናን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስጠትና ይህ ወንጌል በተጨባጭ ምን እንደሆነም ማስተማር ነበረበት፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስን በዛሬው ዓለም ከሚገኙ ሌሎች ወንጌላውያን ለየት ያደረገው ይህ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ቤተክርስቲያን በጻፈው መልዕክቱ አንዳች መንፈሳዊ ስጦታን በማካፈል ሰዎች እንዲጸኑና በሕዝቡና በእርሱ የጋራ እምነቶችም እንዲጽናኑ እንደሚፈልግ ተናገረ፡፡ ዛሬ ባሉት ቤተክርስቲያኖች ውስጥ ያሉ ሰባኪዎች ሁሉ ከሐዋርያው ጳውሎስ መማር የሚገባቸው ይህንን ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እውነተኛ ወንድሞችን ከሐሰተኞቹ መለየት የሚያስችለውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል የመስበክ ልምድ ነበረው፡፡
በዚህ ዘመን ቤተክርስቲያናት አዲስ መጤዎች ለ6 ወራት ያህል የእምነት ትምህርቶችን እንዲማሩ ይፈቅዳሉ፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥም ደርሰው ይጠመቃሉ፡፡ በቃ አለቀ፡፡ ኢየሱስ ስለፈጸመው ስለ ውሃውና ወንጌል ቢያውቁ ወይም ባያውቁ ይጠመቃሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ሰዎች የቤተክርስቲያን አባሎች ቢሆኑም የእርሱን ጽድቅ ያገኙ የእግዚአብሄር ልጆች መሆን አይችሉም፡፡ የዛሬዎቹ ቤተክርስቲያናት አገልጋዮች አዳዲስ ምዕመናን እንዲያደርጉ የሚጠይቁዋቸው ብቸኛው ነገር አስርቱን ትዕዛዛትና የሐዋርያትን የእምነት መርሆዎች እንዲያስታውሱ ነው፡፡ አዳዲሶቹ ምዕመናን የማስታወሱን ፈተና የሚያልፉ ከሆነ ‹‹መጠጥ መጠጣት ታቆማለህ? ማጨስ ታቆማለህ? በየወሩ አስራትህን ትሰጣለህ? ጥሩ ሕይወት ትኖራለህ?›› ተብለው ይጠየቃሉ፡፡
የአውሮጳ፣ የእስያና የዓለም ቤተክርስቲያናት በሙሉ ከእግዚአብሄር ጽድቅ የራቁት የሰውን ጽድቅ ስለሚከተሉ ነው፡፡ በዘመናችን ‹‹የእስያ ኢየሩሳሌም›› ተብላ በምትጠራው ኮርያ እንኳን ሕዝበ ክርስቲያን እያሽቆለቆለ ነው፡፡ አሁን የምስጋና በዓል ወይም የፖፕ ኮንሰርት አይነት የተለየ ዝግጅት በቤተክርስቲያን ውስጥ እስካልቀረበ ድረስ ማንም ወደ ቤተክርስቲያን መምጣት የማይፈልግበት ዘመን ላይ ተደርሶዋል፡፡ ሰዎች ቢመጡ እንኳን ለወጣቶች የሚቀርቡት ‹‹አታጭስ፤ ጥሩ ሕይወት ኑር፤ ቅዱስ እሁድን አክብር፤ ብዙ የበጎ ተግባር ሥራ አድርግ›› የሚል ርዕስ ያላቸው የተለመዱ ስብከቶች ከእግዚአብሄር ጽድቅ ጋር ምንም የሚያገናኛቸው ነገር የለም፡፡
ሰው ሐጢያት ለመስራት ፈጣን፤ ሐጢያት መስራት ለማቆም ደግሞ በጣም ደካማ ስለሆነ እርሱ/እርስዋ በእግዚአብሄር መታመን ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህ ሰዎች ወደ እግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ሲመጡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ መቀበል ይችሉ ዘንድ የውሃውንና መንፈሱን ወንጌል ልናቀርብላቸው ይገባል፡፡ በእርግጥ ምንም እንኳን አሁንም ድረስ ብቃት የሌለን ብንሆንም እናንተና እኔ ሐጢያት አልባ እንደተደረግን የሚናገረውን የእግዚአብሄርን ጽድቅ ልናስተላልፍላቸው ይገባል፡፡
ይህንን በአእምሮዋችሁ ለመያዛችሁ እርግጠኞች ሁኑ፡፡ አንድ ሰው እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ መኖር የሚችለው በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን ሐጢያት አልባ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው ወንጌልን መስበክ የሚችለው የሐጢያት ችግሮቹ ከተወገዱ በኋላ ነው፡፡ ወንጌልን ለሌሎች የማሰራጨት ሥራችን የራሳችንን የሐጢያት ችግሮች ከማቃለል መቅደም የለበትም፡፡ አንድ ሰው የራሱ የሐጢያት ችግሮች መፍትሄ እስካላገኙ ድረስ ፈጽሞ እውነተኛውን ወንጌል ለሌሎች መስበክ አይችልም፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ አንዳንድ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ለሌሎች እንዳካፈለ ተናግሮዋል፡፡ ጳውሎስ የተናገረለት ስጦታ በዘመኑ ክርስትና በጴንጤ ቆስጤ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚነገርለት በእንግዳ ቋንቋዎች የመናገር ወይም የመፈወስ ስጦታ አይደለም፡፡ ብዙ ክርስቲያኖች ራዕዮችን እንደ ማየት፣ ትንቢትን እንደ መናገር፣ በሌሎች ልሳናት እንደ መናገር ወይም በሽታዎችን እንደ መፈወስ ያለውን እንግዳ ክስተት ስጦታዎች አድርገው ይመለከቱዋቸዋል፡፡
ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ከሰማይ የተሰጡ መንፈሳዊ ስጦታዎች አይደሉም፡፡ ጸሎት በማድረግ ላይ እያሉ ራዕዮችን ማየት በእርግጥም መንፈሳዊ ስጦታ አይደለም፡፡ ያለ ገደብ የሚጮህ ሰው ወይም ለሦስት ቀኖች ያህል ባለመተኛቱ እንግዳ ድምጾችን በሚሰማበት ጊዜ ሁሉ ወፈፍ የሚያደርገው ሰው ከእግዚአብሄር ዘንድ ስጦታን የተቀበለ ሰው አይደለም፡፡ ሌሎች ልሳናትን መናገር እንደሚችል የሚናገርና ‹‹ላ፣ ላ፣ ላ›› የሚሉ እንግዳ ቃሎችን በተለጎመ ምላስ ከተናገረ በኋላ ራሱን ስቶ ወለሉ ላይ የሚወድቅ ሰው መንፈስ ቅዱስን የተቀበለ ሰው አይደለም፡፡ በፋንታው በአእምሮ ሕሙማን ተቋም ውስጥ ካሉት የአእምሮ ሕሙማን ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡ ሆኖም ክርስቲያኖች እንዴት ሌሎች ልሳናትን እንደሚቀበሉ ወይም መንፈስ ቅዱስን እንደሚያገኙ ማስተማር የሚችሉ ‹‹የካራዝማቲክ አነቃቂዎች›› ተብዬዎች እንዳሉ በድርቅና ይናገራሉ፡፡ እነርሱ ስህተት የሆነ ነገር እየሰሩ ነው፡፡ የያዙዋቸውም እምነቶች ያለ ጥርጥር ትክክል አይደሉም፡፡
የእግዚአብሄርን መንፈሳዊ ሥራ በታማኝነት ስንሰራና ጌታን ስንከተል የመንፈስ ቅዱስ የሕይወት ውሃ ከልቦቻችን ውስጥ ይፈስሳል፡፡ የሥጋ ምግባሮችን ስንቀንስና በምትኩ መንፈሳዊ ምግባሮችን ስንከተል የመንፈስ ቅዱስ ውሃ በልባችን ውስጥ ይጎርፋል፡፡
ክርስቲያኖች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የሐጢያት ስርየትን ስጦታ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ አንድ ሰው በአሁኑ ጊዜ በርካታ ክርስቲያኖች በዛሬዎቹ የቤተክርስቲያናት መቀመጫዎች አማካይነት ወደ ሲዖል እየነጎዱ እንደሆነ ተናገረ፡፡ ይህም የዛሬዎቹ ቤተክርስቲያኖች የእግዚአብሄርን ጽድቅ በመስበክ ፋንታ የሰውን ጽድቅ እንደሚያደፋፍሩ ይጠቁማል፡፡
ወንድሞች አንድ ሰው ቤተክርስቲያን ከሄደ በኋላ ብዙ የሰው ጽድቅ ቢያከማችም ይህ በእነዚህ ምግባሮቹ መንፈሳዊ ስጦታ ሊቀበል ይችላል ማለት አይደለም፡፡ መንፈሳዊውን ስጦታ መቀበል እንችል ዘንድ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የእግዚአብሄርን ጽድቅ ወደ ልቦቻችን ማስገባት ይገባናል፡፡
ከቁጥር 13-17 ያለውን እናንብብ፡- ‹‹ወንድሞች ሆይ በሌሎቹ አሕዛብ ደግሞ እንደሆነ በእናንተም ፍሬ አገኝ ዘንድ ብዙ ጊዜ ወደ እናንተ ልመጣ እንዳሰብሁ ነገር ግን እንደተከለከልሁ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፡፡ ለግሪክ ሰዎችና ላልተማሩትም ለጥበበኞችና ለሚያስተውሉም ዕዳ አለብኝ፡፡ ስለዚህም በሚቻለኝ መጠን በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ደግሞ ወንጌልን ልሰብክ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ በወንጌል አላፍርምና አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሄር ሐይል ለማዳን ነውና፡፡ ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደተጻፈ የእግዚአብሄር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና፡፡››
ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮም መሄድ ፈለገ፡፡ ነገር ግን መሄድ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ተከልክሎዋልና፡፡ ስለዚህ የወንጌል ሥራው በር እንዲከፈትለት በመጠየቅ መጸለይ ነበረበት፡፡ ልክ እንደዚሁ በጽሁፍ አገልግሎቶች አማካይነት ወንጌልን በመላው ዓለም ስንሰብክ ተመሳሳይ ጸሎቶችን መጸለይ ይገባናል፡፡ የእግዚአብሄር ልብ የሚንቀሳቀሰው ስንጸልይ ብቻ ነው፡፡ የውሃውንና መንፈሱን ወንጌል ለመላው ዓለም ማቅረብ የምንችለው እግዚአብሄር በርንና መንገድን ሲከፍትልን ብቻ ነው፡፡
ለአሕዛብ ሁሉ ዕዳ ያለበት ጳውሎስ፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ዕዳ እንዳለበት የተናገረው ለማን ነው? በቁጥር 14 እና 15 ላይም ስለ ምን አይነት ዕዳ እየተናገረ ነው? ለግሪኮችና ላልተማሩት ዕዳ እንዳለበት፤ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለእነርሱ የመስበክ ዕዳ እንዳለበትም ተናግሮዋል፡፡ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉም ዕዳ እንዳለበት ጨምሮ ተናግሮዋል፡፡ ስለዚህ በሮም ላሉት ለእነዚህ ሰዎች በሚችለው ሁሉ ወንጌልን መስበክ ፈለገ፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ለቤተክርስቲያን የጻፈበት ዓላማ እውነተኛውን ወንጌል ለማቅረብ ነው፡፡ በሮም ባለችው ቤተክርስቲያን ውስጥ ባሉት ሰዎች ልቦች ውስጥ እንኳን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በእምነት ጸንቶ እንዳልቆመ ተረድቷል፡፡ ከዚህ የተነሳ ወንጌልን መንፈሳዊ ስጦታ ብሎ ሰየመው፡፡ ስለዚህም ቀድሞውኑም በቤተክርስቲያን ውስጥ ላሉትና ለዓለም ሕዝብ ሁሉ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሰበከ፡፡ እርሱ ለጥበበኞች፣ ለማያስተውሉ፣ ለግሪክ ሰዎችና ላልተማሩት ዕዳ እንዳለበት ተናገረ፡፡
ጳውሎስ ምን አይነት ዕዳ ነበረበት? እርሱ የውሃውንና የመንፈስ ቅዱስን ወንጌል በዓለም ላይ ላሉ ሰዎች የመስበክ ዕዳ ነበረበት፡፡ ያለበትን ዕዳ ሁሉ በዓለም ላይ ላሉ ሰዎች ለመክፈል ጣረ፡፡ ልክ እንደዚሁ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ያላቸው ሰዎችም ወንጌልን የማሰራጨት ዕዳ አለባቸው፡፡ የሚከፍሉት ዕዳ ወንጌልን የማሰራጨት ሥራ ነው፡፡ በዚህ ዘመን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለመላው ዓለም ማሰራጨት የሚገባን ለዚህ ነው፡፡
ሰዎች ደህንነት ሁሉ የሚገኘው በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደም ብቻ ነው ብለው በተሳሳተ መንገድ ያስባሉ፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚመሰክርለት ሰማያዊው ወንጌል ሐዋርያው ጳውሎስ የመሰከረለት የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ በሮሜ 6 ላይ በክርስቶስ ኢየሱስና በሞቱ ውስጥ እንደተጠመቀ ይናገራል፡፡ በሮም ባለችው ቤተክርስቲያን ውስጥ በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደም ብቻ የሚያምኑ ያልተለወጡ ክርስቲያኖች ስለነበሩ ጳውሎስ ኢየሱስ የተቀበለውን ጥምቀት የተሰወረ ምስጢር ሊያቀርብላቸው ፈለገ፡፡ ልክ እንደዚሁ እኛም ምንም እንኳን ለረጅም ጊዜ በቤተክርስቲያን ውስጥ ቢቆዩም መስማት ላልቻሉት ሰዎች የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስበክ ይኖርብናል፡፡
ክርስቲያኖች ሐጢያት እንዳለባቸው ወይም እንደሌለባቸው ሲጠየቁ ይህ ጥያቄ በራሱ ዕርባነ ቢስ ስብዕናቸውን የሚያዋርድ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ጥያቄ በእርግጥም ታላቅ ጠቀሜታና የላቀ ዋጋ አለው፡፡ ሰዎች በሐጢያቶቻቸው ምክንያት ወደ ሲዖል ለመውረድ የታጩ ከሆኑ የዚህ አይነት ጥያቄ የሚጠይቃቸውና መፍትሄ የሚያቀርብላቸው ማን ይኖራል? የዚህ አይነት ጥያቄ መጠየቅና ለሰዎችም ትክክለኛ መልስ መስጠት የሚችለው ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል ዳግም ከተወለደ በኋላ ሐጢያት አልባ የሆነ ሰው ብቻ ነው፡፡ ሐጢያተኞች ፈጽሞ ሰምተውት የማያውቁትን ትክክለኛ ወንጌል ማለትም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማቅረብ ሐጢያተኞች ዳግም እንዲወለዱ ማድረግ የሚችሉት ዳግም የተወለዱ ቅዱሳኖች ብቻ ናቸው፡፡
ወንድሞች ሰው በኢየሱስ ቢያምን ነገር ግን ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ባይወለድ ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ሊገባም ሆነ ያንን መንግሥት ሊያይ አይችልም፡፡ ስለዚህ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለእናንተ በማቅረብ ሐጢያተኞች የሐጢያት ስርየትን እንዲቀበሉ ከሚያደፋፍሩ ሰዎች ጋር ስትገናኙ አመስግኑ፡፡ ያን ጊዜ ታላቅ በረከት ትቀበላላችሁ፡፡
ጳውሎስ ያላፈረበት ወንጌል፡፡
በቁጥር 16 ላይ ጳውሎስ ያላፈረበት ወንጌል ምን አይነት ወንጌል ነበር? የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነበር፡፡ ይህ ወንጌል ለሚያምን ሁሉ ለማዳን የእግዚአብሄር ሐይል ስለሆነ ጳውሎስ ‹‹ወንጌሌ›› ብሎ ጠራው፡፡ (ሮሜ 2፡16፤16፡25) ስለዚህ በዚህ ወንጌል ከማፈር ይልቅ ኮራበት፡፡ እርሱ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ያላፈረው ይህ ወንጌል ሰዎችን ሙሉ በሙሉ ሐጢያት አልባ ስለሚያደርግና የሰውን ዘር በሙሉ ከእግዚአብሄር የሚለየውን የሐጢያት ግድግዳ ስለሚያፈርስ ነው፡፡
ሰዎች በመስቀሉ ደም ወንጌል ብቻ ቢያምኑ ከሐጢያት መንጻት ይችላሉን? እስከ አሁን ድረስ የተሰሩትን ሐጢያቶች በዚህ አይነቱ እምነት ማንጻት የሚቻል ይመስላል፤ ነገር ግን የወደፊቶቹን ሐጢያቶቻችንን ማንጻት አይቻልም፡፡ ስለዚህ የዚህ አይነት እምነት ያላቸው ሰዎች በየቀኑ የንስሐ ጸሎቶችን በመጸለይ ሐጢያቶቻቸውን ለማስወገድ ይሞክራሉ፡፡ ልቦቻቸው በሐጢያቶች ብቻ እንደተሞሉና እነርሱም የማይቀርላቸው ሐጢያተኞች እንደሆኑ ይናዘዛሉ፡፡ ሐጢያት ያለባቸው እነዚህ ክርስቲያን ሐጢያተኞች ወንጌልን ከልባቸው ለሌሎች መናገር አይችሉም፡፡ ምክንያቱም የያዙት ‹‹ወንጌል›› ለእነርሱ ‹‹የምሥራች›› አይደለምና፡፡
ወንጌል በግሪክ ‹‹ኢዋጂሊዮን›› ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ይህ ወንጌል በዚህ ዓለም ላይ ያሉትን ሐጢያቶች በሙሉ የማውደም ችሎታ ያለው ነው፡፡ ብቸኛው እውነተኛ ወንጌል ድማሚትን ይመስላል፡፡ የዚህን ዓለም ሐጢያቶች በሙሉ የሚያስወግደው ይህ እውነተኛው ወንጌል ነው፡፡ ስለዚህ ሐጢያትን የማስወገድ አቅም ባለው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ያመነ እንደ ጳውሎስ ያለ ሰው በዚህ ወንጌል አላፈረም፡፡ በዚህ ዘመን ክርስቲያኖች እንኳን ወንጌልን ለመስበክ የሚያፍሩ ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄርን ጽድቅ የያዙ ሰዎች ወንጌልን በሚሰብኩበት ጊዜ ሞገስንና ክብርን ለብሰው ይቆማሉ፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ወንጌልን ሲሰብክ ቅንጣት እንኳን አላፈረም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ይሰብከው የነበረው ወንጌል ለሚያምን ሁሉ ለማዳን የእግዚአብሄር ሐይል ስለነበር ነው፡፡
ይህ ወንጌል ማንም ያቅርበው በእርሱ የሚያምነውን የማንኛውንም ሰው ሐጢያቶች የሚያስቀር ብርቱ ወንጌል ነው፡፡ አድማጩ ወንጌልን በልቡ ከተቀበለ የዓለም ሐጢያቶች ሙሉ በሙሉ ይወገዳሉ፡፡ ነገር ግን በመስቀሉ ላይ ስለፈሰሰው ደም ብቻ የሚናገር ወንጌል ለሰዎች የሚናገረው ጎዶሎ ወንጌል ማለትም ይህ ደም የሚያስወግድላቸው የአዳም ሐጢያታቸውን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ተጨማሪ መተላለፎቻቸው መወገድ ያለባቸው በየቀኑ የንስሐ ጸሎቶችን በመጸለይ እንደሆነ ይነግራቸዋል፡፡ ለአድማጮቻቸውም የሐጢያትን ጣዕም ያስቀርላቸዋል፡፡
ኢየሱስ ሥልጣኑ ጥሩ ስላልነበር ያስወገደው ከፊል ሐጢያትን ብቻ ነበርን? ኢየሱስ ሰዎችን በሚገባ ስለሚያውቅ አንዳች ያስቀረው ሐጢያት የለም፡፡ ሐጢያቶችን በሙሉ በውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ ወሰደ፡፡ ይህ ውብ ወንጌል ኢየሱስን የጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰውን የደሙን ወንጌል አድምጦ ላመነ ለእያንዳንዱ ሰው ምሉዕ ደህንነትን እንደሚሰጥ አምናለሁ፡፡
ስለዚህ ወንጌል አይሁዶችንና ግሪኮችን ጨምሮ ለእያንዳንዱ ሰው ተመሳሳይ ሐይል አለው፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በተሰበከለት ጊዜ በኢየሱስ ላመነው ለእያንዳንዱ ሰው ተመሳሳይ ደህንነትን ይሰጠዋል፡፡ በሌላ በኩል አንድ ሰው ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል ውጭ የሆነ አንዳች ነገር ሲያቀርብ የእግዚአብሄርን ቁጣ ይቀበላል፡፡ ‹‹ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን፡፡›› (ገላትያ 1፡8) ሐዋርያው ጳውሎስ ከሌሎች ወንጌሎች ሁሉ እውነተኛ የሆነ አንድ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ብቻ እንዳለ በግልጽ ተናግሮዋል፡፡
ሰው አይሁድ ወይም አሕዛብ ቢሆን፣ በእስልምና፣ በቡዲዝም፣ በታዖይዝም፣ በጸሐይ አምላክ ወይም በሌላ በማንኛውም ነገር ቢያምን እያንዳንዱ ሰው ወንጌልን የሚሰማበት ዕድል ያገኛል፡፡ ከዚህም በላይ ይህ የውሃና የመንፈስ ቅዱስ ወንጌል ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ የሚድኑበትን ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን፣ አጽናፈ አለማትን እንደፈጠረ፣ እኛን ለማዳን በሰው አምሳል ወደዚህ ዓለም እንደመጣ፣ በዮሐንስ በመጠመቅም ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደወሰደና በመስቀል ላይም በመሞት የሐጢያቶቻችንን ኩነኔ እንደወሰደ መናገር አለብን፡፡
ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አላፈረም፡፡ መስቀሉን ብቻ የያዘ ወንጌል አሳፋሪ ወንጌል መሆን ያለበት ቢሆንም የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ፈጽሞ አያሳፍርም፡፡ ነገር ግን በኩራትና በክብር የሚጎርፍ ትክክለኛና ብርቱ ወንጌል ነው፡፡ በዚህ ወንጌል የሚያምን ማንኛውም ሰው የእግዚአብሄር ልጅ በመሆኑ እውነታ በማመን የመንፈስ ቅዱስን ሙላት ይቀበላል፡፡ ውብ የሆነው የውሃና የመንፈስ ቅዱስ ወንጌል ፈጽሞ አሳፋሪ ወንጌል ሊሆን እንደማይችል ደግሜ እነግራችኋለሁ፡፡ ነገር ግን በመስቀሉ ደም ብቻ የሚያምን ወንጌል አሳፋሪ ነው፡፡
ክርስቲያኖች ሆይ በመስቀል ላይ የፈሰሰውን ደም ወንጌል ብቻ በምትሰብኩበት ጊዜ ሁሉ አላፈራችሁምን? የኢየሱስን ጥምቀት ያልያዘውን የደሙን ወንጌል ብቻ ስትሰብኩና ስታምኑ ሐፍረት ተሰምቶዋችኋል፡፡ የዚያ አይነቱን አይረቤ ወንጌል ለመስበክ ስለምታፍሩ ሁልጊዜም ወደ ጌታ ትጮሃላችሁ ወይም ‹‹በኢየሱስ እመኑ! በኢየሱስ እመኑ!›› ብላችሁ ለመጮህ ወደ ጎዳና ከመውጣታችሁ በፊት ስሜቶቻችሁን ለማረጋጋት በሌሎች ልሳኖች ጥራዝ ነጠቅ ጸሎት ታቀርባላችሁ፡፡
ይህ አንድ ሰው በግንፍል ስሜቶቹ የሚያደርገው እንጂ በጭራሽ በትክክለኛ አስተሳሰብ ሊያደርገው የሚችለው ነገር አይደለም፡፡ በመስቀሉ ደም ብቻ የሚያምኑ ሰዎች ወንጌልን ለመስበክ ወደ ጎዳናዎች በሚወጡበት ጊዜ የሽብር ጩኸት የሚጮሁትና ረብሻ የሚፈጥሩት ለዚህ ነው፡፡ የድምጽ ማጉያውን ወደ አፎቻቸው አስጠግተው ‹‹ኢየሱስ፣ ወደ ሰማይ፣ አለማመን፣ ሲዖል›› የሚሉትን ቃሎች ብቻ ያስተጋባሉ፡፡ ነገር ግን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምን በጣም ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ወንጌልን ያቀርባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱንም ከፍቶ ሻዩን እየጠጣ ከሌላው ሰው ጋር ይነጋገራል፡፡
ስለ እግዚአብሄር ጽድቅ ወንጌል የተነገረው ምንድነው?
በቁጥር 17 ላይ በክርስቶስ ወንጌል ውስጥ ምን ተገልጦዋል ተብሎ ተነገረ? በእግዚአብሄር ወንጌል ውስጥ ‹‹የእግዚአብሄር ጽድቅ›› ተገልጦዋል ተብሎ ተነግሮዋል፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ በእውነተኛው ወንጌል ውስጥ በሙላት ተገልጦዋል፡፡ ስለዚህ በእርሱ ውስጥ ያለው የእግዚአብሄር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት ይገለጣል፡፡ ጻድቅም በእምነት ይኖራል ተብሎ ተነገረ፡፡ የመስቀሉን ደም ብቻ የሚያቀርብ ወንጌል የእግዚአብሄርን ጽድቅ አይዝም፡፡
ወንድሞች ሰው የቀድሞው ሐጢያቱ ከድሮውም ይቅር እንደተባለ እያወቀ በየቀኑ የንስሐ ጸሎቶችን ማቅረብ እንደሚኖርበት ተነግሮ ቢሆንና ይህ ሰው ቀስ በቀስ እየተቀደሰ ሄዶ ውሎ አድሮ ፍጹም የሆነ ጻድቅ ሰው ቢሆን የዚህ አይነቱ እምነት የእግዚአብሄርን ጽድቅ የያዘ ነውን? ይህ የእግዚአብሄር ጽድቅ የሚገለጥበት ነገር አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ የሚገለጥበት ነገር ፍጹም ስለሆኑ ነገሮች የሚናገር ነው፡፡ የውሃውና የመንፈስ ቅዱስ ወንጌል ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ፍጹም ስለሆነው ወንጌል ይናገራል፡፡
እናንተ ሰዎች በየቀኑ ሐጢያቶችን ስለምትሰሩ በየቀኑ ወይም ምናልባትም በየሳምንቱ ወይም በየወሩ አሳፋሪ ጎናችሁን ለመሸፈን ስትሉ ከበለስ ቅጠል አዳዲስ ልብሶችን መስራት ያለባችሁ ይመስል በየቀኑ የንስሐ ጸሎቶችን ታቀርባላችሁ፡፡ በየቀኑ የንስሐ ጸሎቶችን በማቅረብ በተደጋጋሚ ሐጢያተኛ የሚሆን ሰው የሚያሳፍር አካሉን በበለስ ቅጠሎች እንደሚሸፍን አይነት ሰው ነው፡፡ በመስቀሉ ደም ወንጌል ብቻ የሚያምኑ ሰዎች ሃይማኖታዊ ሕይወት ሁኔታ ይህ ነው፡፡ እነርሱ እግዚአብሄር በነጻ የሰጣቸውን የቁርበት ልብሶች ለመልበስ ከመመኘት ይልቅ የበለስ ቅጠል ልብሶችን በመልበስ የሚደሰቱ ሞኞች ናቸው፡፡
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደም የጥምቀቱ ውጤት ነው፡፡ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን መውሰድ የቻለው በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ አይደለም፡፡ እርሱ ሐጢያቶቻችንን የወሰደው በተጠመቀ ጊዜ ነበር፡፡ ከዚያም የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ተሸክሞ ወደ መስቀል በመሄድ የዓለምን ሐጢያቶች ለማስተሰረይ ሞተ፡፡ ስለዚህ መስቀሉ የጥምቀቱ ውጤት ነበር፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን ስለወሰደ በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደሙ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ለማስተሰረይ የሰራው የመጨረሻ ሥራው ነበር፡፡
ታዲያ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማወቅና በማመን ልናገኘው እንችላለን፡፡ ‹‹ታዲያ አንተ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የምታምን አማኝ ነህን?›› ብላችሁ ትጠይቁኝ ይሆናል፡፡ እኔም ለዚህ ጥያቄ ወዲያውኑ ግልጽ በሆነ መንገድ ‹‹አዎ›› ብዬ እመልስላችኋለሁ፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ለማግኘት ምስጢሩ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን ነው፡፡
ይህ የሆነበት ምክንያት የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እውነት ስለሆነና የእግዚአብሄርን ፍቅርና ጽድቁን ስለሚገልጥ ነው፡፡ እንደዚሁም የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እግዚአብሄር ለሰው ዘር በነጻ የሰጠውን የሐጢያት ስርየት ስለያዘ ነው፡፡ ይህም የእርሱ ልጆች ያልሆኑትን የሚኮንንበትና አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስን መቀበል የሚችልበት፤ የዘላለምን ሕይወት በረከት በምድር ላይም ሥጋዊና መንፈሳዊ በረከቶችን የሚያገኝበት ነው፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ የእግዚአብሄር ጽድቅ እርሱ በሚሰብከው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ውስጥ በሙላት እንደተገለጠ ተናግሮዋል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ሳያውቁ የሰውን ጽድቅ ማቆም በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያት እንደ ማድረግ ይቆጠራል፡፡ ከዚህም በላይ በመስቀሉ ደም ብቻ የሚያምን ነገር ግን የእግዚአብሄርን ጽድቅ ያልያዘ ወንጌል ውሸት ነው፡፡
የእግዚአብሄር ጽድቅ እርሱ የሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ይጠቁማል፡፡ ብሉይና አዲስ ኪዳናት ጥንዶች ሆነው ከሐጢያቶቻችን ያድኑናል፡፡ ብሉይ ኪዳን ለአዲስ ኪዳን ያዘጋጃል፡፡ አዲስ ኪዳንም በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያሉትን የተስፋ ቃሎች ይፈጽማል፡፡ እግዚአብሄር የእርሱ ጽድቅ በሙላት የተገለጠበትን እውነተኛ ወንጌል በመስጠት ከዓለም ሐጢያቶች አዳነን፡፡ በዚህም የሰውን ዘር ሁሉ ከሐጢያት አዳነ፡፡
መላው ዓለም አሁኑኑ ወደ ውሃውና መንፈሱ ወንጌል መመለስ አለበት፡፡ ሰዎችን ከሐጢያት የሚያድነው ብቸኛው ወንጌል የመጀመሪያው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ነው፡፡ ወንድሞች መላው ዓለም ወደ ውሃውና ደሙ ወንጌል መመለስ አለበት፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ወደያዘው ወደዚህ የውሃና የመንፈስ ወንጌል መመለስ አለበት፡፡
ይህ የሆነበት ምክንያት የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እኛን ከሐጢያት ሊያድነን የሚችል ብቸኛው እውነት ስለሆነ ነው፡፡ ሊያድነን፣ ሐጢያት አልባና የእግዚአብሄር ልጆች ሊያደርገን የሚችለው ብቸኛው ወንጌል የእግዚአብሄርን ጽድቅ የያዘው ወንጌል ነው፡፡ ከዚህም በላይ በልቦቻችን ውስጥ ያለው መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሄርን ሕዝብ ይጠብቃል፡፡ ይህ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ይማልዳል፤ ይባርከናል፡፡ ሁልጊዜም አብሮን ይሆናል፡፡ የዘላለምን ሕይወትም ስጦታ አድርጎ ሰጥቶናል፡፡
ለዚህ ወንጌል ትኩረት የማይሰጡ ብዙ ሰዎችን ማየት በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ የኢየሱስን ጥምቀት በሚገባ በመረዳት ሰው ሁሉ ይህንን የውሃና የመንፈስ ወንጌል እንዲያምን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ኢየሱስ ከዮሐንስ የተቀበለው ጥምቀት ኢየሱስ ጨዋ ስለሆነ የተቀበለው ነገር አይደለም፡፡ እርሱ የተጠመቀው የዚህን ዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ለመሸከም ነው፡፡ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል የሚበልጠው ዮሐንስ ኢየሱስን ባጠመቀው ጊዜ እጆቹን በራሱ ላይ ጭኖ ነበር፡፡ ይህም በብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህኑ ነውር በሌለበት የመስዋዕት እንስሳ ራስ ላይ እጆቹን ከመጫኑ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ (ዘሌዋውያን 16፡21) ኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞቱ ሐጢያቶችን በሥጋው ላይ የመሸከሙ ውጤት ነበር፡፡ ይህም እጆች ከተጫኑበት በኋላ ደሙን በማፍሰስ ከሚሞት የሐጢያት መስዋዕት ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡
ይህ የውሃውና የመንፈስ ቅዱስ ወንጌል በሁለቱም የብሉይና የአዲስ ኪዳናት ውስጥ የተጠቀሰ በመሆኑ የመጀመሪያው ወንጌል ውስጥ ማናቸውንም ክፍል በመተው በሌላው ወንጌል የሚያምን ማንኛውም ሰው እምነቱ የተሳሳተ ነው፡፡ ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ ያደረገው እጅግ ጠቃሚና የመጀመሪያው ዋና ነገር በዮሐንስ መጠመቅ ነበር፡፡ የኢየሱስ ጥምቀት ተምሳሌት ብቻ ነው ብላችሁ የምታምኑና ኢየሱስ የተጠመቀው በጨዋነቱ ነው ብላችሁ የምታሰቡ ከሆነ ተሳስታችኋል፡፡
መናፍቅ ምን አይነት ሰው ነው? በቲቶ 3፡10 ላይ እንዲህ ይላል፡- ‹‹መለያየትን የሚያመጣ ሰው ጠማማ እንዲሆን በራሱም ላይ ፈርዶ ሐጢአትን እንዲያደርግ አውቀህ አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜም ከገሰጽኸው በኋላ እንዲህ ከሚመስል ሰው ራቅ፡፡›› መለያየትን የሚያመጣ በራሱ የተኮነነ ነው፡፡ በራሱ የተኮነነ ሰው ማለት ሐጢያት እንዳለበት የሚያምንና የሚናዘዝ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹እኔ ሐጢያተኛ ነኝ›› የሚል ክርስቲያን መለያየትን የሚያመጣ ሰው ማለትም መናፍቅ ነው፡፡ እንዲህ ተብሎ ተጽፎዋል፡- ‹‹እንዲህ ከሚመስል ሰው ራቅ፡፡››
የዚህ አይነቱ ክርስቲያን የዞረበትና የተበላሸ ስለሆነ ሐጢያት አልባ የሆነ ቅዱስ ሰው ወደዚህ መናፍቅ መቅረብ አይኖርበትም፡፡ እርሱ ራሱን የኮነነ ሰው ነው፡፡ ምክንያቱም የገዛ ራሱ እምነትና የሃይማኖት ሕይወት ተበላሽቷልና፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ይቅር የማይባል ሐጢያት የሚሰራ ሰው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ሐጢያት አልባ መሆን የማይፈልግ ነገር ግን አሁንም ድረስ ሐጢያተኛ እንደሆነ በመናገር በእግዚአብሄር ፊት ፍጹም የሆነውን ደህንነት በመናቅ በሐጢያት የሚቀጥል ሰው ነው፡፡ ራሱን የኮነነ ሰው በኢየሱስ ቢያምንም ሐጢያት እንዳለበት በማሰብ ራሱን ሐጢያተኛ ብሎ የሚጠራ በመሆኑ ወደ ሲዖል እየተንደረደረ ያለ መናፍቅ ነው፡፡
አንዳንድ ክርስቲያኖች በመኪናዎቻቸው ጀርባ ላይ ‹‹ስህተቱ የእኔ ነው›› የሚል ስቲከር ይለጥፋሉ፡፡ ይህ በሰዎች አይን ሲታይ ቀናና ግሩም አባባል ይመስላል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይህ አባባል ሁሉም የአንድ ሰው ስህተት ስለሆነ ወደ ሲዖል መውረድ፣ መለያየትን የሚፈጥር ሰው መሆንና መረገምን የመሳሰሉ ጉዳዮች ሁሉም የአንድ ሰው ስህተት ናቸው ማለት ነው፡፡ ‹‹ስህተቱ የእኔ ነው›› የሚለው አባባል ሰናይ ሆኖ እንዲኖር በውስጠ ወይራ አነጋገር የታጀበ አባባል ነው፡፡ ነገር ግን ሰናይ ሆኖ መኖር እንደሚችል የሚያስብ የዚህ መፈክር ደጋፊ ሰዎች የክፉ ዘሮች መሆናቸውን ከሚያብራሩት የእግዚአብሄር ቃሎች ጋር በቀጥታ የተላተመ ነው፡፡ ያን አይነቱን ሰብአዊ አስተሳሰብ የሚከተሉ ሰዎች ውሎ አድሮ ሁሉም አይነት እርግማኖች ይደርሱባቸዋል፡፡
በሆነ አጋጣሚ በመካከላችሁ ራሳቸውን የኮነኑ ሰዎች አሉ? እንግዲያውስ ቆም ብላችሁ የሐጢያት ስርየት የመንጻትን ትምህርት እንደማይመለከት የሚናገረውንና በሮሜ ምዕራፍ 3 ላይ ያቀረብሁትን ስብከት በጥንቃቄ ልታዳምጡ ይገባችኋል፡፡ ሮሜ ስለዚህ ጉዳይ በስፋት ይናገራል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎች ከዕለታት አንድ ቀን ምን እንደሚሉ አስቀድሞ ስላወቀ ሐጢያት አልባ መሆን በእርግጥም ያለ ሐጢያት መሆንና ሐጢያተኛውንም ጻድቅ ብሎ መጥራት እንዳልሆነ አስቀድሞ ተናገረ፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ብቻም እውነት እንደሆነ በግልጽ መሰከረ፡፡ ስለዚህ በመስቀሉ ደም ብቻ የሚያምኑ ሰዎች ሮሜን በሚያነቡበት ጊዜ ደንቆሮና ዲዳ መሆናቸው የተለመደ ነው፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች የጻፈው መልዕክት ትልቅ መልዕክት ነው፡፡ ምክንያቱም ስለ ውሃውና መንፈሱ ወንጌል ይመሰክራልና፡፡ ሰው ወደ ማመን ከመምጣቱ በፊት ከመጀመሪያውም ሐጢያተኛ ቢሆንም በኢየሱስ ካመነ በኋላ ጻድቅ መሆን ይኖርበታል፡፡ አንድ ሰው በልቡ ውስጥ ሐጢያት የሌለበት በእርግጥም ጻድቅ ሰው መሆን ይኖርበታል፡፡ አንድ ሰው ትክክለኛውን እምነት የሚያገኘው እንዲህ ነው፡፡
በዚህች ቅጽበት የሰዎች እምነት ምሉዕ ባይሆንም ዳግም በተወለደችው ቤተክርስቲያን አማካይነት ለውሃውና ለመንፈሱ ወንጌል ጆሮዋቸውን ካዋሱ እምነታቸው ውሎ አድሮ ተፍጻሜት ላይ እንደሚደርስ ተስፋ አለኝ፡፡ እባካችሁ በእነዚህ ስብከቶች አማካይነት ስለ ውሃውና መንፈሱ ወንጌል አብዝታችሁ ተማሩ፡፡ የእውነትንም ቃሎች አጽኑ፡፡
እግዚአብሄር በሰማያዊ በረከቶቹ ባለጠግነት እንደሚሞላን አምናለሁ፡፡