Search

خطبات

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[15-1] የጌታን ድንቅ ሥራዎች በአየር ላይ ሆነው የሚያመሰግኑ ቅዱሳን፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 15፡1-8 ››

የጌታን ድንቅ ሥራዎች በአየር ላይ ሆነው የሚያመሰግኑ ቅዱሳን፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 15፡1-8 ››
‹‹ሌላም ታላቅና ድንቅ ምልክት በሰማይ አየሁ፡፡ የእግዚአብሄር ቁጣ በእነርሱ ስለሚፈጸምባቸው ኋለኛዎቹን ሰባት መቅሰፍቶች የያዙ ሰባት መላእክት ታዩ፡፡ በእሳትም የተቀላቀለውን የብርጭቆ ባህር የሚመስለውን አየሁ፡፡ በአውሬውና በምስሉም በስሙም ቁጥር ላይ ድል ነስተው የነበሩ የእግዚአብሄርን በገና ይዘው በብርጭቆ ባህር ላይ ሲቆሙ አየሁ፡፡ 
ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ
ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአህዛብ ንጉሥ ሆይ
መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ
የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? 
አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፤ የጽድቅም ሥራህ
ስለተገለጠ አህዛብ ሁሉ ይመጣሉ፤ 
በፊትህም ይሰግዳሉ
እያሉ የእግዚአብሄርን ባሪያ የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ፡፡ ከዚህም በኋላ አየሁ፤ የምስክርም ድንኳን መቅደስ በሰማይ ተከፈተ፡፡ ሰባቱንም መቅሰፍት የያዙ ሰባት መላእክት ከመቅደሱ ወጡ፡፡ ከተልባ እግርም የተሰራ ጥሩ የጌጥ ልብስ ለበሱ፡፡ ደረታቸውንም በወርቅ መታጠቂያ ታጠቁ፡፡ ከአራቱም እንስሶች አንዱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ የሚኖር የእግዚአብሄር ቁጣ የሞሉባቸውን ሰባት የወርቅ ጽዋዎች ለሰባቱ መላእክት ሰጣቸው፡፡ ከእግዚአብሄርም ክብርና ከሐይሉ ጢስ በመቅደሱ ሞላበት፡፡ የሰባቱም መላእክት ሰባት መቅሰፍት እስኪፈጸሙ ድረስ አንድ ስንኳ ወደ መቅደሱ ይገባ ዘንድ አልቻለም፡፡›› 
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
ቁጥር 1፡- ሌላም ታላቅና ድንቅ ምልክት በሰማይ አየሁ፡፡ የእግዚአብሄር ቁጣ በእነርሱ ስለሚፈጸምባቸው ኋለኛዎቹን ሰባት መቅሰፍቶች የያዙ ሰባት መላእክት ታዩ፡፡
ምዕራፍ 15 ሰባቱ መላእክቶች በሚያፈስሱዋቸው በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች የሚመጣውን የዓለም ፍጻሜ ይነግረናል፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ ያየው ይህ ‹‹ሌላ ታላቅና ድንቅ የሰማይ ምልክት›› ምንድነው? ይህ ቅዱሳን በብርጭቆ ባህር ላይ ቆመው የጌታን ሥራዎች የሚያመሰግኑበት ድንቅ ትዕይንት ነው፡፡
 
ቁጥር 2፡- በእሳትም የተቀላቀለውን የብርጭቆ ባህር የሚመስለውን አየሁ፡፡ በአውሬውና በምስሉም በስሙም ቁጥር ላይ ድል ነስተው የነበሩ የእግዚአብሄርን በገና ይዘው በብርጭቆ ባህር ላይ ሲቆሙ አየሁ፡፡
እዚህ ላይ ‹‹በእሳት የተቀላቀለ የብርጭቆ ባህር የሚመስል›› የሚለው ሐረግ በዚህ ምድር ላይ ያለው የስቃይ ሰቆቃ እግዚአብሄር የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች በምድር ላይ በሚያፈስስበት ጊዜ ከፍታው ላይ እንደሚደርስና በሌላ በኩል ቅዱሳን ጌታን በአየር ላይ እንደሚያመሰግኑ ይነግረናል፡፡ እግዚአብሄር በዚህች ምድር ላይ ያፈሰሳቸው የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ቅዱሳን ጠላቶቻቸውን ይበቀሉ ዘንድ እየወረዱ ናቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ቅዱሳን ከእግዚአብሄር በሆነው ትንሳኤያቸውና ንጥቀታቸው ከተሳተፉ በኋላ የእርሱን ሥራዎች ለማመስገን ከእሳት ጋር በተቀላቀለው በዚህ የብርጭቆ ባህር ላይ ይቆማሉ፡፡ በዚህች ምድር ላይ በጌታ ሐይል ሰማዕት በመሆን ትንሳኤን አግኝተው የተነጠቁት ቅዱሳን ስለ ማዳኑና ስለ ሐይሉ እርሱን ለዘላለም ያመሰግኑታል፡፡ አመስጋኞቹ ቅዱሳን እርሱን፣ ምስሉንና የስሙን ምልክት ወይም የስሙን ቁጥር ባልተቀበለው እምነታቸው ጸረ ክርስቶስን ድል በመንሳት የእምነት ድልን የተቀዳጁ ቅዱሳን ናቸው፡፡
 
ቁጥር 3፡- ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአህዛብ ንጉሥ ሆይ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤
በብርጭቆው ባህር ላይ የሚቆሙት ቅዱሳን የሙሴንና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ፡፡ የቅኔው ስንኞችም ‹‹ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው›› የሚሉ ናቸው፡፡ የዚህ ቅኔ ስንኞች ልክ እንደተጻፉት እግዚአብሄር ሁሉን በሚገዛ ሐይሉ ሊያደርገው የማይችለው ምንም ነገር የሌለ በመሆኑ እውነታ አምላክን የሚያመሰግኑ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ‹‹ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው›› ተብሎም ተጽፎዋል፡፡
እዚህ ላይ ‹‹ድንቅ›› የሚለው ቃል ‹‹ቃላቶች ሊገልጡት የማይችሉት አንድ ትልቅ ነገር›› ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ጌታ አምላካችን የብሉይና የአዲስ ኪዳን ቅዱሳኖችን በሙሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ማዳኑ፣ ሐጢያት አልባ እንዲሆኑ ማድረጉና በእምነታቸው የዳኑትን እነዚህን ቅዱሳኖች ከሥጋ ሞታቸው አስነስቶ ወደ አየር በመንጠቅ ጌታን በአየር ላይ እንዲያመሰግኑ ማድረጉ በአጭሩ ድንቅና ግሩም ነው፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ጌታ አምላክ አዳኛቸው፣ ጌታቸውና ሁሉን ቻይ በመሆኑ ያመሰግኑታል፡፡
ጌታ አምላክ ዩኒቨርስንና በወስጡ ያሉትን ነገሮችን ሁሉ እናንተንና እኔን ጨምሮ እንደፈጠረና እርሱ በእርግጥም ጌታችን እንደሆነ ታምናላችሁን? ጌታ በሰጠው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ምዕመናኖች መሆን የሚችሉት በዚህ እውነት የሚያምኑ ብቻ ናቸው፡፡ የዚህ ዓይነት እምነት ያላቸው ሰዎች እጅግ እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች ኢየሱስ መላውን ዩኒቨርስና በውስጡ ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠረ ፈጣሪ መሆኑን ማወቅና ማመን አለባቸው፡፡ የእርሱን ሥራዎች በማወቅና በማመንም ጌታ አምላክን ማመስገንና ማምለክ አለባቸው፡፡ ‹‹ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፡፡›› ይህ የእምነት ምስጋና የሙሴንና የበጉን ቅኔ የሚዘምሩትን በትክክል ዳግመኛ የተወለዱ ቅዱሳን እውነተኛ እምነት ያሳያል፡፡
ጌታ ኢየሱስ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላክ እንደሆነ ታምናላችሁን? ኢየሱስ ራሱ መላውን ዩኒቨርስ የፈጠረ አምላክ እንደሆነ የሚያምኑ ሰዎች ጌታ የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህች ምድር እንደመጣ፣ በ30 ዓመቱም የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በአንድ ጊዜ ለመውሰድ በዮሐንስ እንደተጠመቀ፣ በመስቀል ላይ ደሙን አፍስሶ እንደሞተና ዳግመኛም ከሙታን እንደተነሳ ያምናሉ፡፡ እነርሱ በእምነታቸው የሐጢያት ስርየትን ተቀብለው ቅዱሳን ይሆናሉ፡፡ ይህንን እውነት የሚያውቁና በዚህም ላይ እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች ታላቅ እምነት ያላቸው ሰዎች ተብለው በትክክል ሊገለጡ ይችላሉ፡፡
እዚህ ላይ ያለው ምንባብ የተነጠቁት ቅዱሳን ‹‹ሥራህ ታላቅና ግሩም ነው›› በማለት ጌታን በአየር ላይ እንደሚያመሰግኑት ይናገራል፡፡ በሌላ አነጋገር እነርሱ ዩኒቨርስንና የሰውን ዘር ስለፈጠረ ጌታ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ በአንድ ጊዜ በማንጻት በዚህች ምድር ላይ ሐጢያተኞችን በማዳኑና የእግዚአብሄር ልጆች የሚሆኑበትንም መብት በመስጠቱ ጌታ አምላክን ያመሰግኑታል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ነው፡፡ ቅዱሳን ለክርስቶስ ሰማዕት መሆናቸው፣ ትንሳኤን ማግኘታቸው፣ መነጠቃቸውና የዘላለምን ሕይወት መቀበላቸው እነዚህ ሁሉ እግዚአብሄር የሰጣቸው ባርኮቶች ናቸው፡፡
ቅዱሳን ሁሉ ጌታ ለሐጢያተኞች ላደረጋቸው የጽድቅ ሥራዎቹ ሁሉ ማለትም ሐጢያቶችን በሙሉ በማስወገዱና በዚህ ምድር ላይ በነበረ ጊዜ ለሰራቸው ሌሎች ሥራዎች ሁሉ የእርሱን ክብር ሁሉ የሚገልጥ ምስጋናን ለአምላክ መስጠት አለባቸው፡፡ ቅዱሳን የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ በአየር ላይ ይዘምራሉ፡፡ ሁሉን የሚገዛው አምላክ ለሐጢያተኞችና ለጠላቶቹ ያደረገው ነገር ምንኛ ታላቅና ግሩም እንደሆነ በመዘመር ጌታን ያመሰግናሉ፡፡
ጌታ ለቅዱሳንና እርሱን ለሚቃወሙት ሁሉ ያደረገው ነገር እኛን የሚያስገርም ብቻ ሳይሆን የሚያስደንቅም ነው፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ዓለም የፈጠረበት ዓላማ የሰውን ዘር የራሱ ሕዝብ ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ እርሱ ለሰው ዘር የሰራቸው ሥራዎች በሙሉ በፊታችን ድንቅና ግሩም ሆነው ተገልጠዋል፡፡ እርሱ ለእኛ ባደረገው ነገር በማመን ለእግዚአብሄር ክብርን እንሰጣለን፡፡ በእርሱ ሥራዎች ሁሉ በማመንም እናመሰግነዋለን፡፡
እግዚአብሄር ሰውን በራሱ አምሳል መፍጠሩም እንደዚሁ አስገራሚ ነው፡፡ ሕጉን ለሰው ሁሉ መስጠቱና ኢየሱስ ክርስቶስን ወደዚህ ምድር ለመላክ በድንግል ማርያም በኩል መስራቱም እንደዚሁ በዓይኖቻችን ፊት አስደናቂ ነው፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ እነዚህ ሥራዎች ሁሉ የተሰሩት ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ለማዳን መሆኑንም እናምናለን፡፡ ጌታ አምላካችን እያንዳንዱ የሰው ዘር ሐጢያት ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ በዮሐንስ እንዲጠመቅ በማድረግ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውነት የማስተላለፉ እውነታም እንደዚሁ ግሩም ነው፡፡
ጌታ አምላክ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ለሚያምኑት ሰዎች እንዲህ ዘላለማዊውን የሐጢያት ስርየትና መንፈስ ቅዱሱን መስጠቱም እንደዚሁ ግሩምና ድንቅ ነው፡፡ የዳኑት ቅዱሳኑ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመላው ዓለም መስበካቸውም ሌላ ድንቅ በረከት ማለትም እንደገና ለእኛ ግሩም የሆነ ነገር ነው፡፡ ጌታ አምላካችን የቅዱሳንን ሰማዕትነት መፍቀዱ፣ ትንሳኤን እንዲያገኙ መፍቀዱና በሰማይም ለዘላለም በክብር እንዲኖሩ ማድረጉ--እነዚህ ሁሉ ሥራዎችም እንደዚሁ ግሩም በረከቶች ናቸው፡፡
እግዚአብሄር እነዚህን ነገሮች ሁሉ ካቀደ በኋላ ጊዜው ሲደርስ ሁሉንም በዚያው መሰረት ይፈጽማቸዋል፡፡ ቅዱሳኖችን እንዲከብሩና እግዚአብሄርን እንዲያመሰግኑ የሚያደርጉዋቸው እነዚህ የጌታ ሥራዎች በልባችን ውስጥ ወደ ታላላቅ በረከቶች ይቀየራሉ፡፡ ጠላቶቹን በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች አማካይነት ሁሉን በሚገዛው ሐይሉ የሚበቀላቸው በመሆኑ እውነታም ጌታን በማመስገን እባረካለን፡፡
የጌታ አምላክ ሥራዎች በሙሉ በቅዱሳን ዓይኖች ሲታዩ ከእነርሱ ወሰኖች ባሻገር ሆነው ስለሚታዩ እርሱን ያመሰግኑታል፡፡ ጌታችን ከእያንዳንዱ የሰው ዘር ብቻ ሳይሆን በዩኒቨርስ ውስጥ ካለው ከእያንዳንዱ ፍጡርም እንደዚሁ ምስጋናን ሁሉ ሊቀበል የተገባው ነው፡፡ ሐሌሉያ!
ጌታ አምላካችን ለእነርሱ ያደረገላቸውን እያወቁ የተለማመዱና በራሳቸው ዓይኖች ያዩ ሰዎች እግዚአብሄርን ሁሉን ስለሚገዛው ሐይሉ፣ ፍጹም ስለሆነው ጥበቡ፣ ስለ ጽድቁ፣ ለዘላለም ስለማይለወጠው ቅን ፍርዱና ዘላለማዊና የማይለዋወጥ ስለሆነው ፍቅሩ ያመሰግኑታል፡፡ ጌታ ቅዱሳን ግሩም ስለሆኑት ሥራዎቹ ለዘላለም እንዲያመሰግኑት ፈቅዶዋል፡፡
ስለዚህ ቅዱሳን ለእነርሱ ስላደረገላቸው ሥራዎች ስለ በጎነቱና ታላቅነቱ ሁሉ ጌታ አምላክን ለዘላለም ያመሰግኑታል፡፡ ጌታ አምላካችን በዩኒቨርስ ውስጥ ካሉት ነገሮች ሁሉ ውስጥ ምስጋናን ሊቀበል የተገባው ነው፡፡ ምክንያቱም የእርሱ ሥራዎች በሙሉ ተግባራዊ መሆን የቻሉት ሁሉን በሚገዛው ሐይሉ ነውና፡፡ ሐሌሉያ! ጌታን ስለ ሐይሉ፣ ዘላለማዊ፣ የማይለወጥና የተባረከ ፍቅሩ አመሰግነዋለሁ!
 
ቁጥር 4፡- ጌታ ሆይ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፤ የጽድቅም ሥራህ ስለተገለጠ አህዛብ ሁሉ ይመጣሉ፤ በፊትህም ይሰግዳሉ እያሉ የእግዚአብሄርን ባሪያ የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ፡፡
በአየር ላይ ያሉት ቅዱሳን በአንደበታቸው የጌታን ሥራዎች እያመሰገኑ ይዘምራሉ፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው?›› ይህ ማንም የጌታ አምላክን ክብር መቋቋም እንደማይችልና ማንም እርሱ ምስጋናን እንዳይቀበል ለማስቆም መድፈር እንደማይችል በድፍረት የሚያውጅ በአመኔታና በእምነት የተሞላ ምስጋና ነው፡፡ በፍርሃት ሳይንቀጠቀጥ በጌታ ስም ፊት መቆም የሚችል ማነው? በዚህ ዓለም በመላው ዩኒቨርስና በሁሉም ዘላለማዊ ግዛቶች ውስጥ ጌታ አምላካችንን መቋቋምና ማሸነፍ የሚችል ማንም ምንም ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ የነገሥታት ንጉሥና ሁሉን የሚገዛ አምላክ ነውና፡፡
በዚህ ዓለም ላይ ያለ ሁሉም ነገርና ቅዱሳኖችም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሁሉን በሚገዛው የጌታ አምላካችን ሐይልና በእርሱ እውነት ፊት በፍርሃት የማይንቀጠቀጥ የለም፡፡ የጌታ አምላክ ሐይል ወሰን የሌለው ታላቅ ስለሆነ እርሱ እውነተኛና ፍጹም ስለሆነ በእርሱ ስም ፊት ፍጥረታት ሁሉ ምስጋናን፣ ክብርንና ውዳሴን ያቀርባሉ፡፡ እያንዳንዱ ሰው እግዚአብሄርን የሚፈራ ልብ ሊኖረው ይገባል፡፡ በዩኒቨርስ ውስጥ ያሉ ሁሉ የጌታችንን ስም ማመስገን አለባቸው፡፡ ለምን? ምክንያቱም ጌታችን ቅዱስ ነውና፡፡ የሰውን ዘር በሙሉም ከዓመጻቸው ሁሉ አድኖዋልና፡፡
ጌታ በዚህ ምድር ላይ በሚኖረው በጸረ ክርስቶስ፣ በተከታዮቹና በሐይማኖተኞች ላይ በሚያፈስሳቸው የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ስለሚገልጥ እርሱን እናመሰግነዋለን፡፡ የጌታ ጻድቅ ፍትህ በሰባቱ ታላላቅ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ስለሚገለጥ ጌታ አምላካችን ከሕያዋን ፍጥረታት፣ ከመላዕክቶችና ከቅዱሳኖች በአየር ላይ ክብርን፣ ምስጋናንና አምልኮን ሊቀበል ይገባዋል፡፡
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም የማይፈራ ደፋር ማነው? ጌታችን ፍጡር ሳይሆን ሁሉን የሚገዛ አምላክ ነው፡፡ ጌታ አምላክ የሰባቱን ጽዋዎች አስፈሪ መቅሰፍቶች እርሱን በሚቃወሙት ሁሉ ላይ በማፍሰስ ፍጥረቶቹ ሁሉ በግርማ ሞገሱና በሐይሉ ፊት እንዲያመሰግኑት ያደርጋል፡፡ 
‹‹የጽድቅም ሥራህ ስለተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ፤ በፊትህም ይሰግዳሉ፡፡›› ስለዚህ የጌታን ስም የሚቋቋምና የሚሳደብ ሰው መቼም ቢሆን በደስታ ሊኖር እንደማይችል መገንዘብ አለብን፡፡
ለስሙ የሚገባው የአምልኮ ዓይነት በጌታ ስም ፊት መንበርከክ፣ በበላይነቱ፣ በሁሉን ቻይነቱ፣ በምህረቱ፣ በታላቅ ማዳኑና ፍቅሩ በማመን ማወደስና ማመስገን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ፍጥረታቶች በሙሉ ጌታ በዚህች ምድር ሳለ ባደረጋቸው ነገሮች በማመን እርሱን ማመስገንና ማምለክ አለባቸው፡፡ ጌታችን ከሰዎችና ከአሕዛቦች ሁሉ ምስጋናን መቀበል ይገባዋል፡፡ አሜን ሐሌሉያ!
 
ቁጥር 5፡- ከዚህም በኋላ አየሁ፤ የምስክርም ድንኳን መቅደስ በሰማይ ተከፈተ፡፡
ይህ ቁጥር ጌታ አምላካችን በዚህች ምድር ላይ የሚያወርዳቸው የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ሲጠናቀቁ እግዚአብሄር ለቅዱሳን የሰማይ ቤቱን እንደሚሰጣቸው ይነግረናል፡፡ ጌታ አምላካችን እነዚህን ነገሮች ሁሉ ይፈጽማቸዋል፡፡ ታዲያ ይህ የምስክሩ ድንኳን መቅደስ ምንድነው? የዚህን ምድር ድንኳን የሚመስል የእግዚአብሄር ቤት ነው፡፡ ‹‹የምስክርም ድንኳን መቅደስ በሰማይ ተከፈተ›› የሚለው ሐረግ የጌታ አምላክ መንግሥት ዘመን ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ተከፍቷል ማለት ነው፡፡
የምስክሩ ድንኳን መቅደስ በር ሲከፈት የመጨረሻዎቹ መቅሰፍቶችና የጌታ አምላክ መንግሥት ወደዚህች ምድር ይመጣሉ፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የማያውቅ እምነት በእግዚአብሄር ፊት አይቀርብም፡፡ ስለዚህ ይህንን የእውነት ወንጌል ማወቅና ማመን አለብን፡፡ እንደዚሁም ወደ ክርስቶስ መንግሥት ገብተን የምንኖርበት ዘመንም አሁን ወደ እኛ እየቀረበ እንዳለ መረዳትና ማመን አለብን፡፡
 
ቁጥር 6፡- ሰባቱንም መቅሰፍት የያዙ ሰባት መላእክት ከመቅደሱ ወጡ፡፡ ከተልባ እግርም የተሰራ ጥሩ የጌጥ ልብስ ለበሱ፡፡ ደረታቸውንም በወርቅ መታጠቂያ ታጠቁ፡፡
ይህ ቃል እግዚአብሄር የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች በዚህች ምድር ላይ ሲያወርድ በእነዚህ በሰባቱ መቅሰፍቶች መሰረታዊ ፍትህና ትክክለኝነት በሚያምኑ መላእክቶች አማካይነት እንደሚሰራ ያሳየናል፡ በሌላ አነጋገር የእግዚአብሄር ባሮች የእርሱ አገልጋዮች ሆነው ጌታን ለማገልገል ብቁአን መሆን የሚችሉት ሁልጊዜም በእርሱ ጽድቅ ሲያምኑና ሙሉ እምነታቸውን በእርሱ ላይ ሲያኖሩ ብቻ እንደሆነም ይነግረናል፡፡
የእግዚአብሄር ባሮች እንዲህ ያሉ የጌታ ሥራዎችን መስራት የሚችሉት የጌታ ሥራዎች ሁልጊዜም ትክክል እንደሆኑ ሲያምኑ ብቻ ነው፡፡
 
ቁጥር 7፡- ከአራቱም እንስሶች አንዱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ የሚኖር የእግዚአብሄር ቁጣ የሞሉባቸውን ሰባት የወርቅ ጽዋዎች ለሰባቱ መላእክት ሰጣቸው፡፡
ይህ እግዚአብሄር በባሪያዎቹ አማካይነት ሲሰራ ሥርዓት ባለው ሁኔታ እንዲሰሩ እንደሚያደርጋቸውና እንደዚህ ያሉ ሥራዎችም በጥሩ ሥርዓት እንደሚከወኑ ይነግረናል፡፡ ‹‹ከአራቱም እንስሶች አንዱ›› የሚለው ሐረግ ጌታ ክቡር የሆኑ አገልጋዮቹን ለዓላማው እንዳስቀመጣቸውና በእነርሱም በኩል እንደሚሰራ ያሳየናል፡፡ እዚህ ላይ የተገለጡት አራቱ እንስሶች ሁልጊዜም በአጠገቡ የሚቆሙና የእርሱን ዓላማዎች ለማገልገልም ቀዳሚ የሚሆኑት አራቱ ክቡር የእግዚአብሄር አገልጋዮች ናቸው፡፡ የእግዚአብሄርን የበላይነትና ሁሉን ቻይነት መረዳት አለብን፡፡ እርሱ በባሮቹ አማካይነት እንደሚሰራም ማመን አለብን፡፡
 
ቁጥር 8፡- ከእግዚአብሄርም ክብርና ከሐይሉ ጢስ በመቅደሱ ሞላበት፡፡ የሰባቱም መላእክት ሰባት መቅሰፍት እስኪፈጸሙ ድረስ አንድ ስንኳ ወደ መቅደሱ ይገባ ዘንድ አልቻለም፡፡
ጌታ አምላክ በዚህ ምድር ላይ ፍርዱን እስኪፈጽም ድረስ ማንም ወደ እርሱ መንግሥት መግባት አይችልም፡፡ ይህም የእግዚአብሄር ቅድስና ምን ያህል ፍጹም እንደሆነ ይነግረናል፡፡ እንደዚሁም እርሱ በዓመጽ ደስ የሚለው አምላክ እንዳልሆነም ይነግረናል፡፡ (መዝሙረ ዳዊት 5፡4) ስለዚህ ወደ እግዚአብሄር መንግሥት መግባት የሚፈልግ ማንም ቢኖር ጌታ ለሰው ዘር በሰጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ማመን እንዳለበት ማስታወስ አለብን፡፡ ጌታ አምላካችን ወደ መንግሥቱ እንዲገቡ የሚፈቅድላቸው በዚህ የውሃና የመንፈስ ወንጌል የሚያምኑትን ብቻ ነው፡፡
እግዚአብሄር የሐጢያት ስርየትን ለተቀበሉት ቅዱሳን የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች በማዝነብ ጠላቶቹን ካጠፋ በኋላ በመንግሥቱ ውስጥ ለዘላለም የመኖርን በረከት ይሰጣቸዋል፡፡ የእግዚአብሄር ሥራዎች በሙሉ ከሰው አእምሮ በላይ ናቸው፡፡ የእርሱን ታላቅነትና የበላይነትም የሚገልጡ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር በጠላቶቹ ላይ በመፍረድ ሁሉን ቻይነቱን ይገልጣል፡፡ እግዚአብሄር እርሱን በመቃወም ለሰሩት ሐጢያት ጠላቶቹን የሚቀጣበት ሐይል ባይኖረው ኖሮ ከሁሉም ምስጋናን መቀበል ባልቻለም ነበር፡፡
ነገር ግን እግዚአብሄር እርሱን የተቃወሙትን ለመቅጣት ከበቂ በላይ የሆነ ሐይል ስላለው ጌታ አምላክ በጠላቶቹ ላይ ይፈርድና በዘላለማዊው የሲዖል ቅጣት ይፈርድባቸዋል፡፡
ጌታ አምላካችን በሰዎች ሁሉ ለዘላለም ሊመሰገን ከሚገባው በላይ ነው፡፡ እግዚአብሄር በዚህ ሁኔታ ስለ ሐጢያቶቻቸው ሁሉ በጠላቶቹ ላይ የሚሰጠውን ፍርድ ያጠናቅቅና መንግሥቱን ይከፍታል፡፡ አሜን፡፡ ጌታ አምላካችንን ስለ ታላቁ ሐይሉ፣ ስለ ክብሩና ቅድስናው እናመሰግነዋለን፡፡ ሐሌሉያ!