Search

خطبات

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[22-1] የሕይወት ውሃ የሚፈስበት አዲስ ሰማይና ምድር ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 22፡1-21 ››

የሕይወት ውሃ የሚፈስበት አዲስ ሰማይና ምድር
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 22፡1-21 ››
‹‹በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሄርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውሃ ወንዝ አሳየኝ፡፡ በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አስራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፡፡ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም፡፡ የእግዚአብሄርና የበጉም ዙፋን በእርስዋ ውስጥ ይሆናል፡፡ ባሪያዎቹም ያመልኩታል፤ ፊቱንም ያያሉ፤ ሥሙም በግምባሮቻቸው ይሆናል፡፡ ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፡፡ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፡፡ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣሉ፡፡ እርሱም፡- እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፡፡ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ የሚሆነውን ነገር ለባርያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ፡፡ እነሆም በቶሎ እመጣለሁ፤ የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብጹዕ ነው አለኝ፡፡ ይህንን ያየሁትና የሰማሁት እኔ ዮሐንስ ነኝ፡፡ በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት እሰግድ ዘንድ ተደፋሁ፡፡ እርሱም፡- እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሄር ስገድ አለኝ፡፡ ለእኔም፡- ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማህተም አትዝጋው፡፡ ዓመጸኛው ወደፊት ያምጽ፤ ርኩሱም ወደፊት ይርከስ፤ ጻድቁም ወደፊት ጽድቅ ያድርግ፤ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ፡፡ እነሆም በቶሎ እመጣለሁ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ፡፡ አልፋና ዖሜጋ፣ ፊተኛውና ኋለኛው፣ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ፡፡ ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱ እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው፡፡ ውሻዎችና አስማተኞች፣ ሴሰኛዎችም፣ ነፍሰ ገዳዮችም፣ ጣዖትንም የሚያመልኩት፣ ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ፡፡ እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ፡፡ እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፡፡ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ፡፡ መንፈሱና ሙሽራይቱም ና ይላሉ፡፡ የሚሰማም ና ይበል፡፡ የተጠማም ይምጣ፤ የወደደም የሕይወትን ውሃ እንዲያው ይወስድ፡፡ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል ለሚሰማ ሁሉ እኔ እመሰክራለሁ፡፡ ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሄር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሰፍቶች ይጨምርበታል፡፡ ማንም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት መጽሐፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሄርን ዕድሉን ያጎድልበታል፡፡ ይህን የሚመሰክር አዎን በቶሎ እመጣለሁ ይላል፡፡ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን፡፡›› 
 
 

ትንታኔ፡፡

 
ቁጥር 1፡- በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሄርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውሃ ወንዝ አሳየኝ፡፡
እዚህ ላይ ዮሐንስ ‹‹እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ወንዝ›› አየ፡፡ ውሃ በዚህ ዓለም ላይ ጥቅሙ ከሕይወት ጋር የተመሳሰለ ነው፡፡ እዚህ ላይ ያለው ቁጥር ይህ የሕይወት ውሃ ቅዱሳን ለዘላለም በሚኖሩበት አዲስ ሰማይና ምድር ውስጥ እንደሚፈስስ ያሳያል፡፡ የሕይወት ውሃ ወንዝ ከበጉ ዙፋን እየፈሰሰ መንግሥተ ሰማይን ያረሰርሳል፡፡ ሁሉንም ነገሮች ያድሳል፡፡ ‹‹የበጉ ዙፋን›› በሚለው ሐረግ ውስጥ ‹‹በጉ›› የሚያመለክተው በዚህ ምድር ላይ ሳለ የሰውን ዘር በውሃና በመንፈስ ወንጌል ያዳነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፡፡
እግዚአብሄር ለቅዱሳን በሰጠው አዲስ ሰማይና ምድር ውስጥ የሕይወት ውሃ ይፈስሳል፡፡ ይህ ገነት ልክ በውሃ ቀለም እንደተሳለ ውብ ስዕል ጥርት ያለና ንጹህ በመሆኑ ሊገለጥ የሚችለው ዕጹብ ድንቅ በሚል ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰጠን የሕይወት ውሃ ተራ ወንዝ ሳይሆን እዚያ ለሚኖሩ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ የሕይወት ወንዝ ጋር በሚገናኝ በእያንዳንዱ ነገር ውስጥ ሕይወት ይለመልማል፡፡ በዚህ የሕይወት ውሃ ወንዝ አጠገብ የሚኖሩ ቅዱሳንም ይህንን ውሃ በመጠጣት በዘላለም ሕይወት እየተደሰቱ ለዘላለም ይኖራሉ፡፡
የሕይወትን ውሃ ወንዝ ከእግዚአብሄርና ከበጉ ዙፋን ይፈስሳል፡፡ ቅዱሳን በአዲሱ የሰማይ መንግሥት ውስጥ የእግዚአብሄርንና የበጉን ጸጋ ከማመስገን በቀር ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር የሕይወት ጸጋውን ለግሶዋቸዋልና፡፡ የዚህ አዲስ ሕይወት ጸጋ በሙሉ ከጌታ ዙፋን ስለሚፈስስ አመስጋኝ ነኝ፡፡
 
ቁጥር 2፡- በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አስራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፡፡ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ፡፡
ጌታ ለቅዱሳን የሚሰጣቸው ድንቅ በረከቶች በሰማይም ይቀጥላሉ፡፡ ምክንያቱም እዚህ ላይ ቃሉ ጌታ በወንዙ ወዲያና ወዲህ ያለውን የሕይወት ዛፍ እንደሚሰጠንና ከፍሬዎቹም እንድንበላ እንደሚፈቅድልን ይነግረናል፡፡ አስራ ሁለት ዓይነት ፍሬዎችን የሚያፈራው የሕይወት ዛፍ በየወሩ አዳዲስ ፍሬዎችን እያፈራ የአዲስ ሕይወትን ጉልበት ያመጣል፡፡ እዚህ ላይ ቅጠሎቹም ለሕዝብ መፈወሻ እንደሆኑ ተነግሮዋል፡፡
ጌታ ለቅዱሳኑ የለገሰው ጸጋው ታላቅና አመርቂ ስለሆነ እኛ ማድረግ የምንችለው ነገር ቢኖር እርሱንና እግዚአብሄር አብን ማመስገን ብቻ ነው፡፡ አሁን ቅዱሳኖች ሊያደርጉት የሚገባቸው ነገር በራሳቸው ጥረት ለጌታ አንዳች ዋጋ ያለው ነገር ለማከናወን መሞከር ሳይሆን አዲስ ሰማይና ምድር እና አዲስ ሕይወት ስለሰጣቸው አመስጋኝ በሆኑት ልቦቻቸው ጌታን ማመስገን ብቻ ነው፡፡ የቅዱሳን ልቦች ‹‹አቤቱ ተመስገን! ሐሌሉያ!›› ብለው እንዲጮሁ በማድረጉ ጌታን አመሰግናለሁ፡፡
 
ቁጥር 3፡- ከእንግዲህ ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም፡፡ የእግዚአብሄርና የበጉም ዙፋን በእርስዋ ውስጥ ይሆናል፡፡ ባሪያዎቹም ያመልኩታል፤
እግዚአብሄር በመንግሥተ ሰማይ ውስጥ ለሚኖሩት ቅዱሳን መርገምን ለዘላለም የሚያስወግዱበትን በረከት ሰጥቶዋቸዋል፡፡ የእግዚአብሄርና የበጉ ዙፋን በቅዱሳን መካከል መሆኑ በመንግሥተ ሰማይ ውስጥ የሚኖሩ ቅዱሳን በጉን በልባቸው ማዕከል ላይ እንደሚያኖሩት ያሳየናል፡፡ ስለዚህ የቅዱሳን ልቦች ሁልጊዜም በውበትና በእውነት ይፍለቀለቃሉ፡፡ ሕይወታቸውም በደስታ ይሞላል፡፡
‹‹ባሪያዎቹም ያመልኩታል›› ከሚለው ሐረግ በመንግሥተ ሰማይ የሚኖሩት ቅዱሳን የእርሱ ቅርብ ሆነው ጌታን የማገልገልን ክብር እንደሚለብሱ እናያለን፡፡ ጌታችን የሚኖርበት መንግሥተ ሰማይ እጅግ ውብና ማራኪ መንግሥት ነው፡፡
ስለዚህ ከጌታ አጠገብ ቆመው የሚያገለግሉት ባሪያዎቹ ቀረብ ብለው በእርሱ ክብር ሁሉ ሊደሰቱ ይችላሉ፡፡ ይህም በመንግሥተ ሰማይም የጌታ ባሪያዎች እንደሚኖሩ ይነግረናል፡፡ ባሪያ የሚለው ቃል ዝቅ ማለትን የሚያሳይ ቃል ነው፡፡ የከበረውን ጌታችንን ቀርበው የሚያገለግሉ ባሪያዎች ግን በመንግሥተ ሰማይ ውስጥ እጅግ የተባረኩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እንዲህ በማይነገር ታላቅ ግርማ ሞገስ የተላበሱ ናቸውና፡፡ በመንግሥተ ሰማይና በዚህ ምድር ላይ የጌታ ባርያዎች የሆኑ ሰዎች የሰማይን ክብር ሁሉ የሚለብሱና ከሁሉም ይልቅ እጅግ ደስተኞች የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡
 
ቁጥር 4፡- ፊቱንም ያያሉ፤ ሥሙም በግምባሮቻቸው ይሆናል፡፡
የጌታ ቅዱሳንና ባሪያዎች የማን ናቸው? የጌታ ናቸው፡፡ እነርሱ የጌታ ሕዝብና የእግዚአብሄር ልጆች ናቸው፡፡ ስለዚህ በመንግሥተ ሰማይ ጌታን የሚያገለግሉ በግምባሮቻቸው ላይ የጌታ ስም ተጽፎዋል፡፡ ጌታ ሁልጊዜም ይጠብቃቸዋል፤ ይባርካቸውማል፡፡ እነርሱ የእርሱ ናቸውና፡፡ ቅዱሳን የእርሱ አገልጋዮች በመሆናቸው እጅግ አስደሳችና እጅግ ክቡር ከሆኑት ውበቶች አንዱን ይለብሳሉ፡፡ የእርሱን የጌታ ባሪያዎች መሆኑ የሚያፍሩ ሰዎች የእርሱን ውበት የማያውቁ ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱ ከቶውኑም የሰማይ ዜጎች ሊሆኑ አይችሉም፡፡
በሰማይ በሚኖሩት ቅዱሳን ግምባሮች ላይ የጌታ ስም ተጽፎዋል፡፡ ይህ ጌታ የሰጠው በረከት ነው፡፡ ከአሁን ጀምሮ ቅዱሳን የእርሱ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ ሰይጣንም እንኳን የጌታ የሆኑትን ቅዱሳን ሊጎዳ አይችልም፡፡ ቅዱሳንና ጌታ በሰማይ ውበት ሁሉ ውስጥ አብረው ይኖራሉ፡፡ ቅዱሳን የጌታን ፊት ሁሌም ያያሉ ማለት ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ በፍቅሩና ድንቅ በሆኑት በረከቶቹ ውስጥ ይኖራሉ ማለት ነው፡፡
ቅዱሳን ሊያውቁት የሚያስፈልግ አንድ ሌላ ነገር አለ፡፡ እግዚአብሄር አብና መንፈስ ቅዱስም ከጌታ ኢየሱስ ጋር አብረው የእነርሱ ቤተሰብ በመሆን ከቅዱሳን ጋር ይሆናሉ፡፡ በመንግሥተ ሰማይ እግዚአብሄር አብ፣ ልጁ ኢየሱስ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ ቅዱሳን መላዕክቶችና ሁሉም ነገር አንድ ቤተሰብ ሆነው ፍጹም በሆነ ሰላም አብረው ይኖራሉ፡፡ የራሱ ስላደረገን ጌታን አመሰግናለሁ፡፡
 
ቁጥር 5፡- ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፡፡ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፡፡ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣሉ፡፡
እዚህ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ቅዱሳን ከጌታ ጋር በአዲሱ ሰማይና ምድር ይነግሳሉ፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የእርሱ ቅዱሳን የሆኑ ከጌታ ጋር በሰማይ እንዲነግሱ የሚያስችላቸውን ደህንነት ተቀብለው በእርሱ ባለጠግነት፣ ግርማና ሥልጣን ለዘላለም ይኖራሉ፡፡ እንደገና በዚህ ወንጌል ተደንቀናል፤ እንዴት ያለ ግሩም ሐይል ያለው ወንጌል አለን!
ለእነዚህ ሁሉ ባርኮቶችና ክብር ስላሴ አምላካችንን አመስግነዋለሁ፡፡ በዚህ ምድር ላይ ሳሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ያመኑ ቅዱሳን በመንግሥተ ሰማይ ይነግሳሉ፡፡ ይህ በረከት ምንኛ ድንቅ ነው! እኛም ጌታን ከማመስገን በቀር ሌላ ማድረግ አንችልም፡፡ እነርሱም ጌታን አብዝተው ማመስገን ያለባቸው መሆን በጣም ትክክልና ተገቢ ነው፡፡
ቅዱሳን በሚኖሩበት አዲስ ሰማይና ምድር መብራቶች የኤሌክትሪክ አምፖሎች ወይም ፀሐይ አያስፈልጉም፡፡ ለምን? እግዚአብሄር ራሱ የአዲሱ ሰማይና ምድር ብርሃን ሆንዋልና፡፡ በዚያም ጨለማ የለም፡፡ እግዚአብሄር ቅዱሳን የእርሱ ልጆች ሆነው እንዲነግሱ ፈቅዶዋል፡፡ ይህ በረከት ቅዱሳን ከጌታ የተቀበሉት ጻ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ዳግመኛ ያስታውሰናል፡፡
እኛ ቅዱሳን ደህንታችንን ካገኘን በኋላ የተሰጡን የሰማይ ባርኮቶች ምን ያህል ታላቅ እንደሆኑ መገንዘብ አለብን፡፡ ጌታ ለቅዱሳኑ የሰጠው ጸጋ ከሰማይ ከፍ ያለና የተለቀ ነው፡፡ ቅዱሳን ጌታ የሰጣቸው ድንቅ በረከት እንዲያልፋቸው መፍቀድ የለባቸውም፡፡ ቅዱሳን ዘላለማዊ ምስጋናን ማቅረብና ለታላቅነቱ፣ ለክብሩና ለሰጣቸው በረከት ጌታን ማመስገንና ለዘላለምም በብልጥግናና በክብር መኖር ይችላሉ፡፡ አሜን! ሐሌሉያ! ጌታችንን አመሰግናለሁ!
 
ቁጥር 6፡- እርሱም፡- እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፡፡ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ የሚሆነውን ነገር ለባርያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ፡፡
‹‹እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፡፡›› ጌታ በራዕይ አማካይነት ለቅዱሳን የገለጠላቸውን ተስፋዎቹን ሁሉ በእርግጥም ይፈጽማቸዋል፡፡ ጌታ በአምላክ ባርያዎቹ በኩል እንደ መንፈስ ቅዱስ በመናገር ሁሉን ነገር ለቅዱሳኑ ሁሉ አስቀድሞ የተናገረው ለዚህ ነው፡፡ በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ እጅግ የተባረከው ቃል እግዚአብሄር ቅዱሳን በአዲሱ ሰማይና ምድር ከጌታ ጋር አብረው እንዲኖሩና በሥልጣንና በክብር እንዲኖሩ መፍቀዱ ነው፡፡
እግዚአብሄር ይህንን ሥራ ፈጥኖ የሚፈጽም መሆኑ በሚገባ የተረጋገጠ ስለሆነ ቅዱሳን እምነታቸው እንዲበተን ወይም በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዲጠመድ ከቶውኑም ሊፈቅዱ አይችሉም፡፡ ቅዱሳን ተስፋን በያዘው እምነታቸው ችግሮቹንና መከራዎችን ሁሉ ማሸነፍ አለባቸው፡፡ ጌታችን ለቅዱሳንና ለቤተክርስቲያኑ የሰጣቸውን ትንቢቶችና ተስፋዎች በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ አይሳነውም፡፡ ጌታችን ባሪያዎቹን ወደዚህ ምድር በመላክ የትንቢት ቃሎችን እንዲናገር ያደረገው ለቅዱሳኑና ለቤተክርስቲያኑ እነዚህን ሁሉ በረከቶች ለመንገር ነው፡፡
 
ቁጥር 7፡- እነሆም በቶሎ እመጣለሁ፤ የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብጹዕ ነው አለኝ፡፡
የዚህ ራዕይ መጽሐፍ የትንቢት ቃሎች ቅዱሳን ወደፊት የሚገጥማቸውን ሰማዕትነት ስለሚነግረን ቅዱሳን በጸረ ክርስቶስ የሚሰደዱበትና እምነታቸውን እስከ ሞት ድረስ የሚጠብቁበት ዘመን እንደሚመጣ ይገልጥናል፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ፈቃድ ስለሆነ ቅዱሳን ሰማዕትነታቸውን ይቀበላሉና፡፡ ንጥቀታቸውን አግኝተው በሚመጣው የሺህ ዓመቱ የክርስቶስ መንግሥትና ከዚያም በአዲሱ ሰማይና ምድር ለዘላለም ይነግሳሉ፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን ጌታችን የነገራቸውን የአምላክ ቃል በሙሉ በማመን እምነታቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡ በመጨረሻው ዘመን እጅግ ብሩካኖቹ ሰዎች የጌታችንን ቃል የሚያምኑና በእምነት የሚኖሩ ናቸው፡፡
እግዚአብሄር ለቅዱሳኑ ፈጥኖ እንደሚመጣ ነግሮዋቸዋል፡፡ ጌታችን ብዙም ሳይዘገይ ወደ እኛ ይመጣል፡፡ ቅዱሳኖችን ከሐጢያት ካዳነው የውሃና የመንፈስ ቃል የሚፈልቁትን የእግዚአብሄር በረከቶች በሙሉ ለመፈጸም ጌታችን ፈጥኖ ወደ ምድር ይመጣል፡፡፡
ቅዱሳኖች ከዳኑ በኋላ ጌታ ለእነርሱ ቃል የገባላቸውን የባርኮቶች ቃል አጥብቀው መያዝና እምነታቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡ ልባቸው በጌታ ቃል ማመን ሲያቆም ሁሉን ነገር ያጣሉ፡፡ በጌታ ቃል ላይ ያላቸውን እምነታቸውን መጠበቅ የሚገባቸው ለዚህ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር ለቅዱሳን በጌታ ያላቸውን እምነት እንዲጠብቁ ነግሮዋቸዋል፡፡
 
ቁጥር 8፡- ይህንን ያየሁትና የሰማሁት እኔ ዮሐንስ ነኝ፡፡ በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት እሰግድ ዘንድ ተደፋሁ፡፡
የእግዚአብሄርን የትንቢት ቃል የሚያሰራጩት ነቢያቶችና ቅዱሳን ናቸው፡፡ ስለዚህ ለእነርሱ በተናገረው መሰረት የሚሰራውን አምላክ ማመስገንና ለእርሱ ብቻ መስገድ አለብን፡፡ አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ራሳቸውን እንደ አምላክ ከፍ ለማድረግና እንደዚያም ለመቆጠር ይሞክራሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ወይ አጭበርባሪዎች አለበለዚያም ሐሰተኛ ነቢያት ስለሆኑ ነው፡፡ ምስጋና፣ ክብር፣ ስግደትና አገልግሎት ሁሉ የሚገባው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡
 
ቁጥር 9፡- እርሱም፡- እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሄር ስገድ አለኝ፡፡
የእግዚአብሄር እውነተኛ ነቢያቶች ለመሆን ምን ማድረግ አለብን? በመጀመሪያ ጌታ በሰጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ምስጢር ማመን አለብን፡፡ ያን ጊዜ የእግዚአብሄር ሕዝብ ቅዱሳንና እርስ በርሳችንም ወንድሞችና እህቶች እንሆናለን፡፡ እግዚአብሄር ሥራዎቹን ሊያስረክበን የሚችለው ከዚህ በኋላ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ባሪያዎች የሆኑ ሰዎች በቃሉ ማመንና ቃሉንም በእምነታቸውም መጠበቅ አለባቸው፡፡ ክብሩን ለራሳቸው ከመሸሸግ ፋንታ ለእግዚአብሄር የሚሰጡት እነዚህ ናቸው፡፡ ጌታችን በዚህ ዓለም ላይ ከሚኖር ከእያንዳንዱ ሰው ስግደትንና ክብርን ሁሉ ሊቀበል ይገባዋል፡፡ ሐሌሉያ!
 
ቁጥር 10፡- ለእኔም፡- ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማህተም አትዝጋው፡፡
በራዕይ ውስጥ የተጻፈው የተስፋ ቃል ተደብቆ መቅረት አይገባውም፡፡ ይህ የተስፋ ቃል ፈጥኖ ስለሚፈጸም ለሁሉም ሰው ሊመሰክር ይገባል፡፡ አሜን! ሁላችንም በራዕይ መጸሐፍ ውስጥ ባለው የትንቢት ቃል አምነን እንስበከው፡፡
 
ቁጥር 11፡- ዓመጸኛው ወደፊት ያምጽ፤ ርኩሱም ወደፊት ይርከስ፤ ጻድቁም ወደፊት ጽድቅ ያድርግ፤ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ፡፡
ጌታ የሚመጣበት ቀን ሲቀርብ ሐጢያትን የሚሹ ሐጢያትን በመሻት እንዲቀጥሉ፣ ቅዱስ የሆኑትም ቅዱስ ሆነው እንዲቀጥሉ፣ ርኩስ የሆኑትም ርኩስ ሆነው እንዲቀጥሉ ይፈቀዳል፡፡ የመጨረሻው ዘመን ሲመጣ በጌታ የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ሐጢያት አልባ የሆኑ ሰዎች አሁንም በዚህ ምድር ላይ ወንጌልን ያገለግላሉ፡፡ ጌታ የሰጣቸውን ቅድስና የሚጠብቁና ሕይወታቸውንም በእምነት የሚኖሩ እንደዚያ ሆነው መኖራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ጌታችን አሁን የያዝነውን እምነት እንድንጠብቅ መክሮናል፡፡
 
ቁጥር 12፡- እነሆም በቶሎ እመጣለሁ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ፡፡
በሌላ አነጋገር ጌታችን በቶሎ ይመጣና በምድር ያለውን ገነትና አዲሱን ሰማይና ምድር የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለማሰራጨት ላገለገሉትና ለለፉት ቅዱሳን ይሰጣቸዋል፡፡ ለከፈሉዋቸው መስዋዕቶችም ሽልማቶችን ይሰጣቸዋል፡፡ ቅዱሳን በራዕይ ውስጥ ባለው የትንቢት ቃል ሲያምኑ እምነታቸውን እስከ መጨረሻው ድረስ መጠበቅ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ተስፋቸውን በጌታ ላይ አኑረዋልና፡፡ ጌታ የቅዱሳኖችን ልፋት እጅግ በላቁ በረከቶች እንደሚመለስ መረዳትና ማመን አለብን፡፡ ምክንያቱም ጌታችን የከበረና መሐሪ ነውና፡፡
 
ቁጥር 13፡- አልፋና ዖሜጋ፣ ፊተኛውና ኋለኛው፣ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ፡፡
ጌታችን የእያንዳንዱ ነገር መጀመሪያና መጨረሻ ነው፡፡ እርሱ ብቻ ሊሰጠን የሚችለውን ደህንነት የሚያመጣልን አዳኛችንና ራሱም አምላክ ነው፡፡ የመላው ዩኒቨርስ ታሪክ፤ የሰማይና ምድር ታሪክ የጀመረው በጌታ ነው፡፡ የሚጠናቀቀውም በእርሱ ነው፡፡
 
ቁጥር 14፡- ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱ እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው፡፡
ጌታ የነገረን ሁሉ ሕይወት ስለሆነ ቅዱሳን በእርሱ ቃል ያምናሉ፤ ይሰብኩታል፤ ይጠብቁታልም፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ጌታችን ለቅዱሳንና በዩኒቨርስ ውስጥ ላሉት ነገሮች ሁሉ እውነት ስለሆነ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቅዱሳንና ባርያዎች በልቡናቸው የእግዚአብሄርን ቃል መጠበቅ ያለባቸው ለዚህ ነው፡፡ በአዲሱ ሰማይና ምድር ውስጥ ከተተከለው የሕይወት ዛፍ ፍሬዎች መብላት ይችሉ ዘንድ የእግዚአብሄርን ቃል ይበልጥ በጥንካሬ በማመን እምነታቸውን ይጠብቃሉ፡፡
ጌታ በሰጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ሐጢያት አልባ የሆኑት ቅዱሳን እምነታቸውን ለመጠበቅ ይሞክራሉ፡፡ ምክንያቱም በሰማይ ከሕይወት ዛፍ ፍሬዎች የመብላት መብት አላቸውና፡፡
 
ቁጥር 15፡- ውሻዎችና አስማተኞች፣ ሴሰኛዎችም፣ ነፍሰ ገዳዮችም፣ ጣዖትንም የሚያመልኩት፣ ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ፡፡
በዚህ ምንባብ ውስጥ የተጠቀሱት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማያምኑና እስከ መጨረሻው ዘመን ድረስም ዳግመኛ ያልተወለዱ ሰዎች ናቸው፡፡ ጸረ ክርስቶስና ተከታዮቹ በምልክቶቹና በተዓምራቶቹ ሰዎችን በማሳት ጸረ ክርስቶስ አዳኝ ነው ብሎ በውሸት በማወጅ በተደጋሚ አታለዋል፡፡ እነርሱ ሰዎችን ለጸረ ክርስቶስ ምስል እንዲሰግዱ በማድረግ ወደ ጥፋት ነድተዋቸዋል፡፡ ጌታችን እንደዚህ ያሉ ሰዎች ከቶ ወደ አዲሱ ሰማይና ምድር እንዳይገቡ ከቅድስቲቱ ከተማ በስተ ውጭ ያስቀራቸዋል፡፡ የጌታ ከተማ የምትከፈተው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምነውን እምነታቸውን ለጠበቁ ቅዱሳን ብቻ ነው፡፡
 
ቁጥር 16፡- እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ፡፡ እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፡፡ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ፡፡
ጌታችን ለአምላክ ቤተክርስቲያንና ለቅዱሳን ሲል የእግዚአብሄርን ባርያዎች ልኮ ሊመጡ ያሉትን ነገሮች ሁሉ እንዲመስክሩልን አድርጎዋቸዋል፡፡ እነዚህን ነገሮች እንዲመሰክሩ ያደረገው የቅዱሳን አዳኝና ራሱ አምላክ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
 
ቁጥር 17፡- መንፈሱና ሙሽራይቱም ና ይላሉ፡፡ የሚሰማም ና ይበል፡፡ የተጠማም ይምጣ፤ የወደደም የሕይወትን ውሃ እንዲያው ይወስድ፡፡
ጌታችን በዚህ ምድር ላይ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ለሚራቡና ለሚጠሙ ሁሉ ወደ ሕይወት ውሃ ቃል እንዲመጡ ግብዣን አቅርቦዋል፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ የተራበና የተጠማ ማንኛውም ሰው ወደ ጌታ የመምጣት በረከት፣ ጌታ በሰጠው የውሃወና የመንፈሱ ወንጌል የማመንና በዚህም የሕይወትን እንዲጠጡ ተሰጥቶታል፡፡ ጌታችን እያንዳንዱ ሰው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመጣ የተናገረው ለዚህ ነው፡፡ ማንም ሰው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በነጻ መቀበል ይችላል፡፡ ይህ ፍላጎት የሌላቸው ሰዎች ግን ከሕይወት ውሃ የተገለሉ ናቸው፡፡ ፍላጎቱ ካላችሁ እናንተም ደግሞ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ጌታ ከሰጠው የሕይወት ውሃ መጠጣት ትችላላችሁ፡፡
 
ቁጥር 18፡- በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል ለሚሰማ ሁሉ እኔ እመሰክራለሁ፡፡ ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሄር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሰፍቶች ይጨምርበታል፡፡
ቅዱሳት መጻህፍት የእግዚአብሄር ቃል ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ ቃል ስናምን በቃሉ ላይ አንጨምርም፤ ከእርሱም አንቀንስም፡፡ ይህ ቁጥር የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የእግዚአብሄር ቃል ስለሆነ በተጻፈው የእውነት ቃል ላይ በመጨመር ወይም በመቀነስ ማንም በቃሉ ሊያምን አይችልም፡፡ የተጻፈውን እውነት አውጥቶ በመተውም ማመን አይችልም፡፡ ስለዚህ መጠንቀቅ አለብን፡፡ እግዚአብሄር የተናገረው እያንዳንዱ ቃል አስፈላጊ ነው፡፡ የማያስፈልግ ነው ተብሎ ሊጣል የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡
ሰዎች ግን አሁንም ጌታ የሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ቸል ማለት ቀጥለዋል፡፡ ገናም ከሐጢያቶቻቸው መዳን ያለባቸው ለዚህ ነው፡፡ አሁንም ድረስ ሐጢያተኞች ሆነው የቀሩት ለዚህ ነው፡፡ ኢየሱስ አዳኛቸው እንደሆነ ቢናገሩም እንኳን የሚጠፉት ለዚህ ነው፡፡ ጌታችን ሐጢያተኞችን ለማዳን ውሃውንና ደሙን ሰጥቶዋቸዋል፡፡ (1ኛ ዮሐንስ 5፡4-5፤ ዮሐንስ 3፡3-7) ነገር ግን ብዙ ሰዎች ትኩረት የሚያደርጉት ኢየሱስ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ላይ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም አሁንም ድረስ ከሐጢያቶቻቸው አልዳኑም፡፡ ስለዚህ በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት መቅሰፍቶችም ሁሉ ይወርዱባቸዋል፡፡
በኢየሱስ እናምናለን የሚሉ ነገር ግን ክርስቶስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ የማስወገዱን እውነት ቸል በማለት የሚቀጥሉ እጅግ አስፈሪ የሲዖል ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡ ለምን? ጌታ በሰጣቸው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ስለማያምኑ ገና ዳግመኛ አልተወለዱም፡፡ ጌታ የሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ቸል የሚል ማንኛውም ሰው ለዘላለም በሚነድድ የእሳት ባህር ውስጥ ተጥሎ የዘላለም ስቃይን ይሰቃያል፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች ሁሉ የሚጸጸቱበት ጊዜ በእርግጥም ይመጣል፡፡
 
ቁጥር 19፡- ማንም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት መጽሐፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሄርን ዕድሉን ያጎድልበታል፡፡
የክርስቲያን እምነቱ ኢየሱስ ከዮሐንስ በመጠመቅ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ የመውሰዱንና በስቅለቱም ሐጢያቶችን በሙሉ በአንድ ጊዜ የማንጻቱን የእውነት ቃል የሚያጎድል በመካከላችን ይገኛልና? እንደዚያ ከሆነ ይህንን የሚያደርጉ ሰዎች በእርግጥም ወደ እግዚአብሄር ቅድስት ከተማ የመግባት መብታቸውን ያጣሉ፡፡ ምክንያቱም ጌታችን የሰውን ዘር ሐጢያቶች በአንድ ጊዜ በራሱ ላይ ለመውሰድ ጥምቀትን ከዮሐንስ እንደተቀበለ አያምኑምና፡፡ እነርሱ ጌታ የሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ቸል የማለት ሐጢያት እየሰሩ ነው፡፡
ስለዚህ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ የሰውን ዘር ሐጢያቶች የወሰደ የመሆኑን እውነት በልቦቻቸው ውስጥ ማኖር አለባቸው፡፡ ይህንን እስካላደረጉ ድረስ ሁሉም ጌታ ወደሰጠው ቅድስት ከተማ የመግባትን ክብር ከማግኘት ይገለላሉ፡፡ ኢየሱስ አዳኛችሁ እንደሆነ የምታምኑ ከሆናችሁ ኢየሱስ ወደዚህ ምድር እንደመጣ፣ የሰውን ዘር ሁሉ ከዓለም ሐጢያቶች ሙሉ በሙሉ ለማዳን በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እንደተጠመቀና የሰው ዘር የሰራቸውን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ በመውሰድ እንዳነጻቸው ከሙሉ ልባችሁ በማመን ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ መንጻት አለባችሁ፡፡ ከርኩሰታችሁ ሁሉ መንጻት የምትችሉበት ምንጭ ጌታችን የተቀበለው ጥምቀት ነው፡፡ ጌታችን በዚህ መንገድ የዓለምን ሐጢያቶች በራሱ ላይ ከወሰደ በኋላ በገዛ ራሱ ሞት የሐጢያቶቻችንን ደመወዝ በሙሉ ለመክፈል በመስቀል ላይ ደሙን አፍስሶ ሞተ፡፡
ኢየሱስ ከዮሐንስ የተቀበለው ጥምቀት ከሐጢያት ለመዳናችን ጠንካራው ማስረጃ ነው፡፡ 1ኛ ጴጥሮስ 3፡21 እንዲህ ነግሮናል፡- ‹‹ይህም ውሃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፤ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም ለእግዚአብሄር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፡፡ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ነው፡፡›› ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በመስቀል ላይ ተሸከመ፡፡ የሰው ዘር የሰራቸውን ሐጢያቶች ደመወዝም በሁላችንም ፋንታ ሆኖ በራሱ ሞት ለመክፈል ደሙን አፈሰሰ፡፡
እግዚአብሄር እንደገና በቁጥር 19 ላይ የማስጠንቀቂያ ቃሉን ለመላው የሰው ዘር እየሰጠ ያለው ለዚህ ነው፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ቃል ሳንጨምርበት ወይም ሳንቀንስበት ባለበት ሁኔታ ልናምነው ይገባናል፡፡
 
ቁጥር 20፡- ይህን የሚመሰክር አዎን በቶሎ እመጣለሁ ይላል፡፡ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና፡፡
ጌታችን በቅርቡ ወደዚህ ዓለም ይመጣል፡፡ በጌታ በማመንና የሰማይን ክብር በመልበስ የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ያገኙ ቅዱሳን የጌታን ዳግመኛ ምጽዓት ከልባቸው ይጠብቃሉ፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች በሙሉ አሁንም እንኳን የሚመጣውን ጌታ ለመገናኘት ዝግጁ በመሆናቸው ጌታ ተመልሶ ለቅዱሳን ተስፋ የሰጣቸውን በረከቶቹን ለመልበስ ይጠባበቃሉ፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን የጌታን መምጣት በእምነትና በምስጋና በጉጉት እየተጠባበቁ ነው፡፡
 
ቁጥር 21፡- የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን፡፡››
ሐዋርያው ዮሐንስ የራዕይን መጽሐፍ የሚደመድመው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እግዚአብሄር ወደሰጣት ቅድስት ከተማ የመግባት ፍላጎት ካላቸው ጋር እንዲሆን በሚል የቡራኬ ጸሎት ነው፡፡ እኛም እንደዚሁ ሳንታክት በእምነት አማካይነት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደሰጣት ቅድስት ከተማ የምንገባ ቅዱሳን እንሁን፡፡