Search

መልዕክቶች ከአጋር ሠራተኞች፤

የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ከሐጢያት አድኖኛል፡፡

  • Kassahun Ayele
  • Ethiopia
  • 10/31/2021 1994

ከዓመታት በፊት በአንድ ቢሮ ውስጥ እየሰራሁ አንድ ወጣት ባለ ጉዳይ ወደ ቢሮዬ መጣ፡፡ በእጁ ‹‹Have You Truly Been Born Again of Water and The Spirit?›› የሚል በእንግሊዝኛ የተጻፈ መጽሐፍ ይዞ ነበር፡፡ ርዕሱ ትንሽ እንግዳ ስለሆነብኝ ወጣቱ የሚፈልገውን ካሰተናገድሁት በኋላ መጽሐፉን አየው ዘንድ ቢፈቅድልኝ ብዬ ጠየቅሁት፡፡ ወጣቱም ‹‹እንዲያውም ትርፍ ስላለኝ ውሰደውና አንብበው›› በማለት ሰጠኝ፡፡ በአክብሮት ተቀበልኩት፡፡ ወደ ቤት ከተመለስሁ በኋላ በመደርደሪያዬ ላይ አስቀመጥሁት፡፡ ለአንድ ሳምንት ያህል አላየሁትም፡፡    
አንድ ቀን ሌላ መጽሐፍ ስፈልግ ዓይኖቼ በዚህ መጽሐፍ ላይ አረፉ፡፡ የምፈልገውን መጽሐፍ ትቼ ይህንን መጽሐፍ ከመደርደሪያው ላይ ሳብ አድርጌ እንደ ነገሩ ማገላበጥ ጀመርሁ፡፡ የአንድ መጽሐፍ ምንነት የሚታወቀው መቅድሙን በማንበብ እንደሆነ ስለማውቅ የዚህን መጽሐፍ መቅድም ማንበብ ጀመርሁ፡፡ ምንም እንኳን በሃይማኖት ቤት ለረጅም ጊዜ ባሳልፍም የኢየሱስ ጥምቀት ከደህንነቴ ጋር ይገናኛል ብዬ አንዴም እንኳን አስቤ አላውቅም ነበር፡፡  
በእጄ ላይ ያለው መጽሐፍ ፈጽሞ አዲስ የደህንነት እሳቤን አሳየኝ፡፡ የኢየሱስ ጥምቀትና ዳግመኛ ከውሃና ከመንፈስ መወለድ ለእኔ ፈጽሞ አዲስ መገለጦች ነበሩ፡፡ ይህንን መጽሐፍ በታላቅ ጉጉትና አውቆ ለመዳን በተከፈተ ልብ ማንበቤን ተያያዘሁት፡፡ የብሉይ ኪዳን የመሥዋዕት ስርዓት፤ የእጆች መጫን፤ የመሥዋዕቶችን ደም የማፍሰስ ስርዓት በአዲስ ኪዳን ከኢየሱስ ጥምቀትና ሞት ጋር ያላቸውን ቁርኝት በሰፋት በተረዳሁ ጊዜ፤ ኢየሱስ የአዲስ ኪዳን የእግዚአብሄር በግ ሆኖ ወደዚሀ ምድር በመምጣት የሰው ዘር ወኪል (ዮሐንስ 11፡11) በሆነው በአጥማቂው ዮሐንስ አማካይነት ሐጢያቶቼን በሙሉ በራሱ ላይ በጥምቀቱ መወሰዱን ሳውቅና ይህም በጥላው ለመስዋዕቶች በሚቀርቡት እንስሶች ላይ በሚደረገው የእጆች መጫን ስርዓት አማካይነት ከሚተላለፉት የሐጢያተኛው ሐጢያቶች ጋር መሳ ለመሳ እንደሚመሳሰል ስረዳ ለዚህ ትልቅ የመዳን ዕውቀት እጄን ወደላይ አንስቼ ከመማረክ በቀር ላደርገው የምችለው ነገር አልነበረም፡፡ 
ይህ የእውነት ብርሃን በልቤ ላይ በራ፡፡ ሐጢያት አልባ ያደረገኝ የኢየሱስ ጥምቀትና የመስቀል ላይ ሞቱ ነፍሴን በሐሴት ሞላት፡፡ ኢየሱስ ተጠምቆ ‹‹ጽድቅን ሁሉ በመፈጸም›› (ማቴዎስ 3፡15) የዘላለም ጽድቁን ስላወረሰኝ አሁን ጻድቅ ነኝ፡፡ ዳግመኛ ከተወለድሁም 18 ዓመት አልፎኛል፡፡ አሁን የ18 ዓመት መንፈሳዊ ወጣት ነኝ፡፡ ይህንን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ገናም በሐጢያት እስራት ውስጥ ላሉና በጨለማ ውስጥ ለሚዳክሩ መስበኬን አላቋረጥሁም፡፡ 
ክብር በውሃ፣ በደምና በመንፈስ (1ኛ ዮሐንስ 5፡6) ለመጣው፣ ሐጢያቴን ከላዬ ላይ እንዳረጀ  ልብስ ገፎ ለጣለውና አዲሱን የጽድቅ ልብስ ላለበሰኝ ለኢየሱስ ክርስቶስ ይሁን! አሜን!! 
ካሳሁን አየለ, Ethiopia