Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 3፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል

[3-1] ዘላለማዊው ቤዛነት፡፡ ‹‹ ዮሐንስ 8፡1-12 ››

ዘላለማዊው ቤዛነት፡፡
‹‹ ዮሐንስ 8፡1-12 ››
‹‹ኢየሱስ ግን ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ማለዳም ደግሞ ወደ መቅደስ ደረሰ፡፡ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ፡፡ ተቀምጦ ያስተምራቸውም ነበር፡፡ ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ፡፡ በመካከልም እርስዋን አቁመው፡- መምህር ሆይ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች፤ ሙሴም እንደዚህ ያሉት በድንጋይ እንዲወገሩ አዘዘን፤ አንተስ ምን ስለ እርስዋ ትላለህ? አሉት፡፡ የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉት፡፡ ኢየሱስ ግን ጎንበስ ብሎ በምድር ላይ በጣቱ ጻፈ፡፡ መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ፡- ከእናንተ ሐጢአት የሌለበት አስቀድሞ ይውገራት አላቸው፡፡ ደግሞም ጎንበስ ብሎ በምድር ላይ በጣቱ ጻፈ፡፡ እነርሱም ይህንን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሎቹ ጀምሮ ወደኋላ አንዳንድ እያሉ ወጡ፡፡ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ፡፡ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች፡፡ ኢየሱስም ቀና ብሎ ከሴቲቱ ሌላ ባላየም ጊዜ፡- አንቺ ሴት እነዚያ ከሳሾችሽ የት አሉ? የፈረደብሽ የለምን? አላት፡፡ እርስዋም፡- ጌታ ሆይ አንድ ስንኳ አለች፡፡ ኢየሱስም፡- እኔም አልፈርድብሽም፤ ሒጂ ከአሁንም ጀምሮ ሐጢአትን አትስሪ አላት፡፡ ደግሞም ኢየሱስ፡- እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው፡፡››        
 
 
ኢየሱስ የደመሰሰልን ሐጢያት ምን ያህል ነበር? 
የአለምን ሐጢያቶች በሙሉ ነው፡፡ 

ኢየሱስ ዘላለማዊ ቤዛነትን ሰጠን፡፡ ኢየሱስን አዳኙ አድርጎ ቢያምን በዚህ ዓለም ላይ ቤዛነትን ማግኘት የማይችል አንድም ሰው የለም፡፡ እርሱ ሁላችንንም ዋጀን፡፡ በሐጢያቶች የሚሰቃይ ሐጢያተኛ ካለ ኢየሱስ በጥምቀቱና በስቅለቱ ከሐጢያቶቹ ሁሉ እንዴት እንዳዳነው የተሳሳተ እሳቤ በመያዙ ነው፡፡    
ሁላችንም የደህንነትን ምስጢር ማወቅና ማመን አለብን፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወሰደና በመስቀል ላይ ሞቶ የሐጢያቶቻችንን ፍርድ ተሸክሞዋል፡፡    
ከሐጢያቶች ሁሉ ዘላለማዊ ቤዛነት በሆነው የውሃውና የመንፈሱ ደህንነት ማመን ይገባችኋል፡፡ አስቀድሞ ጻድቃን ባደረጋችሁ በእርሱ ታላቅ ፍቅርም ማመን አለባችሁ፡፡ ለደህንነታችሁ ሲል በዮርዳኖስ ወንዝና በመስቀል ላይ ባደረገው ነገር እመኑ፡፡ 
ኢየሱስ የተደበቁ ሐጢያቶቻችንንም በሙሉ አውቋል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ስለ ሐጢያት የተዛባ እሳቤ አላቸው፡፡ አንዳንድ ሐጢያቶች ሊቤዡ አይችሉም ብለው ያስባሉ፡፡ ኢየሱስ ሁሉንም እያንዳንዳቸውንም ሐጢያቶች በሙሉ ዋጅቶዋቸዋል፡፡ 
ኢየሱስ ያላስወገደው አንድም ሐጢያት በዚህ ዓለም ላይ የለም፡፡ እርሱ በዚህ ዓለም ላይ ያሉትን ሐጢያቶች በሙሉ ስለደመሰሰ እውነቱ ምንም ሐጢያተኞች የሌሉ መሆናቸው ነው፡፡ ወንጌል ሐጢያቶቻችሁን፤ ወደፊት የምትሰሩዋቸውን ሐጢያቶች ሳይቀሩ እንደዋጀ ትገነዘባላችሁን? በዚህ አምናችሁ ዳኑ፤ ክብርንም ሁሉ ለእግዚአብሄር ስጡ፡፡   
 
 
ዝሙት ስትፈጽም የተያዘችው ሴት፡፡ 
 
በምድር ላይ ምን ያህል ሰዎች ዝሙትን ይፈጽማሉ?
ሁሉም፡፡ 

በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 8 ላይ ዝሙት ስትፈጽም ስለተያዘች ሴትና ኢየሱስም እንዴት እንዳዳናት እናያለን፡፡ እርስዋ የተጋራችውን ጸጋም መቀበል እንወዳለን፡፡ ሰዎች ሁሉ በሕይወታቸው በአንድ ወቅት ዝሙት እንደሚፈጽሙ መናገር ማጋነን አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሰው ዝሙት ይፈጽማል፡፡ 
እንደዚያ የማታስቡ ከሆነ ምክንያቱ ይህንን ሁልጊዜ ስለምናደርገው  የማናደርግ መስሎ ስለሚታየን ነው፡፡ ለምን? በሕይወታችን ውስጥ በጣም እየዘሞትን ስለምንኖር ነው፡፡   
በዮሐንስ 8 ላይ ያለችውን ሴት ስመለከት በእኛ መካከል ዝሙት ፈጽሞ የማያውቅ ሰው ስለ መኖሩ ወይም አለመኖሩ አስባለሁ፡፡ ዝሙት ስትፈጽም እንደተያዘችው ሴት ዝሙት ያልፈጸመ ማንም ሰው የለም፡፡ ሁላችንም አድርገነዋል፡፡ ነገር ግን እንዳላደረግን እናስመስላለን፡፡ 
እንደተሳሳትሁ ታስባላችሁን? አልተሳሳትሁም፡፡ ጠለቅ ብላችሁ በጥንቃቄ ተመልከቱ፡፡ በምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው ይህንን አድርጓል፡፡ እነዚህ ሰዎች ሴቶች በመንገድ ላይ ሲሄዱ አተኩረው በመመልከት በሐሳባቸውና በድርጊቶቻቸው በየትኛውም ጊዜ በየትኛውም ስፍራ ዝሙት ይፈጽማሉ፡፡ 
እነርሱ እያደረጉት እንዳለ አያውቁም፡፡ እስከሚሞቱበት ቀን ድረስ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ የማይቆጠር ዝሙት እንደፈጸሙ የማይገነዘቡ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ የተያዙት ብቻ ሳይሆኑ እኛም ያልተያዝነው ሁሉ ዝሙትን ፈጽመናል፡፡ ሰዎች ሁሉ በአእምሮዋቸውና በድርጊቶቻቸው ዝሙትን ይፈጽማሉ፡፡ ይህ የሕይወታችን ክፍል አይደለምን? 
ተበሳጫችሁ? ይህ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ ነገር የምንሸፋፍነው ስለምናፍር ነው፡፡ እውነቱ ሰዎች በዚህ ዘመን ሁሌም የሚዘሙቱ መሆናቸው ነው፡፡ 
ሰዎች በነፍሳቸውም ደግሞ ዝሙትን ይፈጽማሉ፡፡ እኛ በእግዚአብሄር የተፈጠርን ሰዎች በዚህ ምድር ላይ የምንኖረው መንፈሳዊ ዝሙትንም ደግሞ እንደምንፈጽም ሳንረዳ ነው፡፡ ሌሎች አማልክቶችን ማምለክ መንፈሳዊ ዝሙትን ከመፈጸም ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ዘር ባል ጌታ ነውና፡፡ 
ድርጊቱን ስትፈጽም የተያዘችው ሴት እንደተቀረነው ሰዎች ሰው ነበረች፡፡ እኛ ቤዛነትን ያገኘን ሰዎች የተቀበልነውን የእግዚአብሄር ጸጋም ተቀብላለች፡፡ ግብዞቹ ፈሪሳውያን ግን በፊታቸው አቁመው ዳኞች የሆኑ ይመስል ጣቶቻቸውን በእርስዋ ላይ ቀስረው በድንጋይ ሊወግሩት ተዘጋጁ፡፡ እነርሱ ራሳቸው ንጹህ የሆኑና ፈጽመው ዝሙትን ያልፈጸሙ ይመስል ሊወቅሱዋትና ሊፈርዱባት ተዘጋጁ፡፡  
አጋር ክርስቲያኖች ራሳቸውን የሐጢያት ክምር አድርገው የሚያውቁ ሰዎች በእግዚአብሄር ፊት በሌሎች አይፈርዱም፡፡ እነርሱ ራሳቸውም በሕይወት ዘመናቸው ዝሙትን እንደሚፈጽሙ በማወቅ ሁላችንንም የዋጀንን የእግዚአብሄር ጸጋ ይቀበላሉ፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ቤዛነትን ለማግኘት ብቁ የሚሆኑት ዝሙትን የፈጸሙ ሐጢያተኞች መሆናቸውን የሚገነዘቡ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡   
 
 

የእግዚአብሄርን ጸጋ የሚቀበለው ማነው? 

 
የእግዚአብሄርን ጸጋ የሚያገኘው ማነው?
የማይረባው፡፡

የእርሱን ጸጋ የሚቀበለው ዝሙትን ሳይፈጽም በንጽህና የኖረው ነው ወይስ ጸጋውን የሚቀበለው ሐጢያተኛ ስለመሆኑ የሚያምን የማይረባው ሰው ነው? ጸጋን የሚቀበለው የእርሱን የተትረፈረፈ የቤዛነት ጸጋ የተቀበለው ሰው ነው፡፡ ራሳቸውን መርዳት የማይችሉ ደካሞችና ረዳተ ቢሶች ቤዛነትን ይቀበላሉ፡፡ በእርሱ ጸጋ ውስጥ ያሉት እነርሱ ናቸው፡፡ 
ሐጢያት እንደሌለባቸው የሚያስቡ ሰዎች ቤዛነትን ሊያገኙ አይችሉም፡፡ የሚዋጅ ምንም ነገር ሳይኖር እንዴት የቤዛነቱን ጸጋ ሊቀበሉ ይችላሉ? 
ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ዝሙትን ስትፈጽም የተያዘችውን ሴት እየጎተቱ በኢየሱስ ፊት በማቅረብ ‹‹መምህር ይህች ስታመነዝር ተያዘች፤ ምን ትላለህ?›› ብለው ጠየቁት፡፡ ሴቲቱን ወደ እርሱ ያመጡዋትና የፈተኑት ለምንድነው?   
እነርሱ ራሳቸው ብዙ ጊዜ ዝሙትን ፈጽመዋል፡፡ ነገር ግን ስህተቱን በእርሱ ላይ ለማላከክ በመሞከር እርስዋን በኢየሱስ በኩል ሊፈርዱባትና ሊኮንኑዋት እየሞከሩ ነበር፡፡   
ኢየሱስ በአእምሮዋቸው ውስጥ ያለውን አወቀ፡፡ ስለዚህ እንዲህ አለ፡- ‹‹ከእናንተ መካከል ሐጢአት የሌለበት ሰው አስቀድሞ ይውገራት፡፡›› ያን ጊዜ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ከሽማግሌው ጀምሮ እስከ ልጁ ድረስ አንድ በአንድ ሄዱና ኢየሱስና ሴቲቱ ብቻቸውን ቀሩ፡፡
ትተው የሄዱት የሐይማኖት መሪዎች የነበሩት ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ነበሩ፡፡ እነርሱ ራሳቸው ሐጢያተኞች ያልነበሩ ይመስል ስታመነዝር በተያዘችው ሴት ላይ ሊፈርዱ ተዘጋጅተው ነበር፡፡  
ኢየሱስ ፍቅሩን በዚህ አለም ላይ አወጀ፡፡ እርሱ የፍቅር አስተናባሪ ነው፡፡ ኢየሱስ ለሰዎች ምግብን ሰጠ፤ ሙታንን አስነሳ፤ የመበለቲቱን ሴት ልጅም በሕይወት አኖረው፡፡ የቢታንያውን ዓልዓዛርን ከሞት አስነሳው፡፡ ለምጻሞችንም ፈወሰ፡፡ ለድሆችም ተዓምራትን አደረገ፡፡ የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች በሙሉ ወስዶ ደህንነትን ሰጠ፡፡   
ኢየሱስ ይወደናል፡፡ እርሱ ማንኛውንም ነገር ማድረግ የሚችል ሁሉን ቻይ አምላክ ነው፡፡ ፈሪሳውያንና ጸሐፍት ግን ጠላታቸው እንደሆነ አሰቡ፡፡ ሴቲቱን ወደ እርሱ ይዘው የመጡትና የፈተኑት ለዚህ ነው፡፡ 
እነርሱ እንዲህ በማለት ጠየቁት፡- ‹‹መምህር ሆይ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች፤ ሙሴም እንደዚህ ያሉት በድንጋይ እንዲወገሩ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ?›› ይወግሩዋት ዘንድ እንደሚነግራቸው አሰቡ፡፡ ለምን? በእግዚአብሄር ሕግ በተጻፈው መሰረት ብንፈርድባት ዝሙትን የፈጸመ ሰው ሁሉ ያለ ምንም አድልዎ ይወገራል፡፡  
ሁሉም መወገር ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሉም ሲዖል ለመውረድ ታጩ ናቸው፡፡ የሐጢያት ደመወዝ ሞት ነው፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ እንዲወግሩዋት አልነገራቸውም፡፡ በፈንታው እንዲህ አለ፡- ‹‹‹ከእናንተ መካከል ሐጢአት የሌለበት ሰው አስቀድሞ ይውገራት፡፡›› 
 
እግዚአብሄር 613ቱን የሕግ አንቀፆች የሰጠን ለምንድነው? 
ሐጢያተኞች መሆናችንን እንድንገነዘብ ነው፡፡ 

ሕጉ ቁጣን ያመጣል፡፡ እግዚአብሄር ቅዱስ ነው፤ ሕጉም ደግሞ ቅዱስ ነው፡፡ ይህ ቅዱስ ሕግ በ613 አንቀጾች ተከፋፍሎ ተሰጥቶናል፡፡ እግዚአብሄር 613 የሕግ አንቀጾችን የሰጠን ሐጢያተኞችና ጎዶሎ ፍጡራን መሆናችንን ሊያሳየን ነው፡፡ ሕጉ ለመዳን የእግዚአብሄርን ጸጋ መናፈቅ እንደሚኖርብን ያስተምረናል፡፡ ይህንን ሳናውቅ በሕጉ ውስጥ ስለተጻፈው ብቻ የምናስብ ከሆንን እጅ ከፍንጅ እንደተያዘችው ሴት በድንጋይ ተወግረን እንሞት ነበር፡፡ 
የእርሱን ሕግ እውነት ያላወቁት ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በሴቲቱ ላይና ምናልባትም በእኛም ላይ እንደዚሁ ድንጋይ መወርወር እንደሚችሉ አስበው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ራሱ ሐጢያተኛ ሆኖ ረዳተ ቢስ በሆነችው ሴት ላይ ድንጋይ ለመወርወር የደፈረ ማነው? እጅ ከፍንጅ ብትያዝም በዚህ ዓለም ማንም ሰው ድንጋዮችን ሊወረውርባት አልተቻለውም፡፡    
ሴቲቱና እያንዳንዳችን በሕጉ መሰረት ብቻ ብንፈረድ እኛም ሆንን ሴቲቱ አስከፊ ፍርድ እንቀበል ነበር፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ እኛን ሐጢያተኞችን ከሐጢያቶቻችንንና ከትክክለኛ ፍርድ አዳነን፡፡ በሐጢያታችን ሁሉ ላይ የእግዚአብሄር ሕግ በተጻፈው መሰረት በጥብቅ በእኛ ላይ ተተግብሮ ቢሆን ኖሮ ከመካከላችን በሕይወት መቆየት የሚችል ማን ነበር? እያንዳንዳችን መጨረሻችን ሲዖል ይሆን ነበር፡፡ 
ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ግን ሕጉን ያወቁት በተጻፈው መሰረት ብቻ ነበር፡፡ የእርሱ ሕግ በትክክል ተተግብሮ ቢሆን ኖሮ እነርሱ እንደፈረዱባት ሴት በእርግጠኝነት ይገድላቸው ነበር፡፡ የእግዚአብሄር ሕግ ለሰዎች የተሰጠው ሐጢያቶቻቸውን ማወቅ እንዲችሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ሕጉን በተሳሳተ መንገድ ስለተረዱትና በተሳሳተ መንገድ ስለተገበሩት ተቸገሩ፡፡   
የዛሬዎቹም ፈሪሳውያን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳሉት ፈሪሳውያን ሕጉን የሚያውቁት በተጻፈው መሰረት ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ጸጋ፣ ፍትህና እውነት መረዳት ይገባቸዋል፡፡ ለመዳንም የቤዛነትን ወንጌል መማር አለባቸው፡፡  
ፈሪሳውያን እንዲህ አሉ፡- ‹‹ሕጉ እንደዚህ ያሉት በድንጋይ እንዲወገሩ አዘዘን፤ አንተስ ምን ትላለህ?›› ድንጋዮቻቸውን ይዘው በድፍረት ጠየቁ፡፡ ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው አንዳች ነገር አይኖረውም ብለው በእርግጠኝነት አሰቡ፡፡ ኢየሱስ በወጥመዳቸው እንዲገባ ጠበቁት፡፡  
ኢየሱስ በሕጉ መሰረት ፈርዶ ቢሆን ኖሮ እርሱንም በድንጋይ በወገሩት ነበር፡፡ አላማቸው ሴቲቱንና ኢየሱስን መውገር ነበር፡፡ ኢየሱስ ሴቲቱን እንዳይወግሩዋት ቢናገር ኢየሱስ በእግዚአብሄር ሕግ ላይ በማላገጥ ተሳድቦዋል ብለው ይወግሩት ነበር፡፡ ይህ አስከፊ ሴራ ነበር!  
ኢየሱስ ግን ጎንበስ አለና በጣቱ መሬት ላይ ጻፈ፡፡ እነርሱም፡- ‹‹ምን ማለትህ ነው? በመሬት ላይ የምትጽፈውስ ምንድነው? ጥያቄያችንን ብቻ መልስ፤ ምን ትላለህ?›› ብለው መጠየቃቸውን ቀጠሉ፡፡ ጣቶቻቸውን በኢየሱስ ላይ ቀስረው መተንኮሳቸውን ቀጠሉ፡፡ 
ያን ጊዜ ኢየሱስ ተነስቶ ከእነርሱ መካከል ሐጢያት የሌለበት የመጀመሪያውን ድንጋይ እንዲወረውርባት ነገራቸው፡፡ ከዚያም ጎንበስ ብሎ በመሬት ላይ መጻፉን ቀጠለ፡፡ ይህንን የሰሙት ሕሊናቸው ስለወቀሳቸው ከሽማግሌው ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ አንድ በአንድ ትተው ሄዱ፡፡ ኢየሱስም በፊቱ ከቆመችው ሴት ጋር ብቻውን ቀረ፡፡ 
 
 
‹‹ከእናንተ ሐጢያት የሌለበት አስቀድሞ ይውገራት፡፡›› 
 
ሐጢያቶች የተመዘገቡት የት ነው? 
በልቦቻችን ጽላቶች ላይና በምግባሮች መጽሐፎች፡፡ 

ኢየሱስም እንዲህ ሲል ተናገራቸው፡- ‹‹ከእናንተ ሐጢያት የሌለበት አስቀድሞ ይውገራት፡፡›› በመሬት ላይም መጻፉን ቀጠለ፡፡ ከሽማግሌዎቹ አንድ ሁለቱ ተመልሰው መሄድ ጀመሩ፡፡ ብዙ ሐጢያቶችን የሰሩት ሽማግሌዎቹ ፈሪሳውያን መጀመሪያ ሳይሄዱ አልቀሩም፡፡ ወጣቶቹም ትተው ሄደዋል፡፡ ኢየሱስ በመካከላችን ቆሞ እኛ ደግሞ በሴቲቱ ዙሪያ ቆመን እናስብ፡፡ ኢየሱስ ከመካከላችን አንዱ አስቀድሞ በሴቲቱ ላይ ድንጋይ እንዲወረውር ቢነግረን ምን ታደርጋላችሁ?   
ኢየሱስ በመሬት ላይ ሲጽፍ የነበረው ምንድነው? እኛን የፈጠረን እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን በሁለት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ይጽፋል፡፡ 
በመጀመሪያ ሐጢያቶቻችንን በልባችን ጽላት ላይ ይጽፋል፡፡ ‹‹የይሁዳ ሐጢአት በብረት ብርዕና በተሾለ ዕብነ አልማዝ ተጽፎአል፡፡ በልባቸው ጽላትና በመሠዊያቸው ቀንዶች ላይ ተቀርጾዋል፡፡›› (ኤርምያስ 17፡1) 
እግዚአብሄር የእኛ ምሳሌ በሆነችው በይሁዳ በኩል ይናገረናል፡፡ የሰዎች ሐጢያቶች በብረት ብዕርና በተሾለ ዕብነ አልማዝ ተጽፈዋል፡፡ በልቦቻችን ጽላት ላይ ተመዝግበዋል፡፡ ኢየሱስ አጎንብሶ ሰዎች ሁሉ ሐጢያተኞች መሆናቸውን በመሬት ላይ ጻፈ፡፡  
እግዚአብሄር ሐጢያት እንደምንሰራ ያውቃል፡፡ ሐጢያቶችንም በልባችን ጽላት ላይ ይቀርጻል፡፡ በመጀመሪያ ሥራዎቻችንን ማለትም የተሰሩ ሐጢያቶችን መዝግቦዋል፡፡ ምክንያቱም እኛ በሕጉ ፊት ደካሞች ነንና፡፡ ሐጢያቶች በልቦቻችን ውስጥ ስለተመዘገቡ ሕጉን ስንመለከት ሐጢያተኞች እንደሆንን እንገነዘባለን፡፡ እርሱ እነዚህ ሐጢያቶች በልቦቻችንና በሕሊናዎቻችን ላይ እንደተመዘገቡ ስለሚያውቅ እኛ በእርሱ ፊት ሐጢያተኞች እንደሆንን እናውቃለን፡፡   
ኢየሱስ በመሬት ላይ ለመጻፍ ለሁለተኛ ጊዜ አጎነበሰ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ደግሞ ሐጢያቶቻችን ሁሉ በእግዚአብሄር ፊት በምግባሮች መጽሐፎች ውስጥ እንደተጻፉ ይናገራል፡፡ (ዮሐንስ ራዕይ 20፡12) የእያንዳንዱ ሐጢያተኛ ስምና ሐጢያቶቹ በመጽሐፍ ውስጥ የተመዘገቡ ናቸው፡፡ እነርሱ በግለሰቡ ልብ ውስጥም የተመዘገቡ ናቸው፡፡ ሐጢያቶቻችን በምግባሮች መጽሐፍና  በልቦቻችን ጽላት ላይ የተጻፉ ናቸው፡፡
ሐጢያቶች በወጣቱም ሆነ በሽማግሌው በእያንዳንዱ ሰው የልብ ጽላት ላይ የተመዘገቡ ናቸው፡፡ በኢየሱስ ፊት ስለ ሐጢያቶቻቸው የሚናገሩት አንዳች ነገር የማይኖረው ለዚህ ነው፡፡ ሴቲቱን ለመውገር የሞከሩት ሰዎች በእርሱ ቃሎች ፊት ረዳተ ቢስ ነበሩ፡፡   
 
በእነዚህ ሁለት ቦታዎች የተጻፉት ሐጢያቶቻችን የሚሰረዙት መቼ ነው?
በልባችን የኢየሱስን የውሃና የደም ቤዛነት ስንቀበል ነው፡፡ 
 
ነገር ግን የእርሱን ደህንነት ስትቀበሉ በምግባሮች መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ሐጢያቶቻችሁ በሙሉ ይደመሰሳሉ፡፡ ስማችሁም በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይመዘገባል፡፡ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ያለ ሰዎች ሰማይ ይገባሉ፡፡ በጎ ምግባሮቻቸው ማለትም በዚህ ዓለም ላይ ለእግዚአብሄር መንግሥትና ለጽድቁ ያከናወኑዋቸው ነገሮችም እንደዚሁ በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበዋል፡፡ ከሐጢያቶቻቸው የዳኑ ሰዎች ወደ ዘላለማዊው ስፍራ ይገባሉ፡፡ 
የእንዳንዱ ሰው ሐጢያቶች በሙሉ በሁለት ስፍራዎች ላይ እንደተጻፉ ይታወስ፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው እግዚአብሄርን ማታለል አይችልም፡፡ በልቡ ሐጢያትን ያልሰራ ወይም ያላመነዘረ ሰው የለም፡፡ ሰዎች ሁሉ ሐጢያተኞችና እንከን የሞላባቸው ናቸው፡፡  
የኢየሱስን ቤዛነት በልቦቻቸው ውስጥ ያልተቀበሉ ሰዎች በሐጢያቶቻቸው ከማዘን በቀር ማድረግ የሚችሉት ነገር የለም፡፡ እርግጠኞች አይደሉም፡፡ በሐጢያቶቻቸው ምክንያት እግዚአብሄርንና ሌሎች ሰዎችን ይፈራሉ፡፡ ነገር ግን የውሃውንና የመንፈሱን ቤዛነት ወንጌል በልባቸው ውስጥ በተቀበሉበት ቅጽበት በልቦቻቸው ጽላቶችና በምግባር መጽሐፎች ውስጥ የተጻፉት ሐጢያቶች በሙሉ ይነጻሉ፡፡ ከሐጢያቶቻቸውም ሁሉ ይድናሉ፡፡ በሰማይ የሕይወት መጽሐፍ አለ፡፡ በውሃውና በመንፈሱ የቤዛነት ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች ስሞችም በመጽሐፉ ውስጥ ስለተጻፈ ሰማይ ይገባሉ፡፡ ሰማይ የሚገቡት በዚህ ዓለም ላይ ሐጢያት ስላልሰሩ ሳይሆን በውሃውና በመንፈሱ የቤዛነት ወንጌል በማመን ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ስለዳኑ ነው፡፡ ይህ ‹‹የእምነት ሕግ›› ነው፡፡ (ሮሜ 3፡27)   
አጋር ክርስቲያኖች ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም በምንዝር ድርጊት እጅ ከፍንጅ እንደተያዘችው ሴት ሐጢያተኞች ነበሩ፡፡ 
እነርሱ ሐጢያተኞች እንዳልሆኑ ራሳቸውንና ሌሎች ሰዎችን በማታለል ስለሚያሳምኑ ብዙ ሐጢያቶችን መፈጸማቸው እርግጥ ነው፡፡ የሐይማኖት መሪዎቹ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው ሌቦች ነበሩ፡፡ በሌላ አነጋገር የነፍሳት ሌቦች፤ የሕይወት ዘራፊዎች ነበሩ፡፡ እነርሱ ራሳቸው ገና ያልተዋጁ ሆነው ሳሉ ሌሎችን በሥልጣን ለማስተማር ደፍረዋል፡፡   
በሕጉ መሰረት ሐጢያት የሌለበት ማንም ሰው የለም፡፡ ሰው ግን ጻድቅ የሚሆነው ሐጢያት ስላልሰራ ሳይሆን ከሐጢያቶቹ ሁሉ ስላልዳነ ነው፡፡ ይህ ሰው በሕይወት መጽሐፍ ላይ ተጽፎዋል፡፡ ዋናው ነገር የሰውየው ስም በሕይወት መጽሐፍ ላይ መጻፉ ወይም አለመጻፉ ነው፡፡ ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሐጢያቶችን ሳይሰሩ መኖር ስለማይችሉ በመጽሐፉ ውስጥ ለመጻፍ የዘላለም ቤዛነትን ማግኘት አለባቸው፡፡ 
በሰማይ ተቀባይነት ማግኘታችሁ የሚመረኮዘው በእውነተኛው ወንጌል በማመናችሁ ወይም በአለማመናችሁ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ጸጋ መቀበላችሁ ወይም አለመቀበላችሁ የሚወሰነው የኢየሱስን ደህንነት በመቀበላችሁ ላይ ነው፡፡ የተያዘችው ሴት ምን ደረሰባት? በጉልበቶችዋ ተንበርክካና ዓይኖችዋን ጨፍና ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እንደምትሞት ታውቅ ነበርና፡፡ ምናልባትም በፍርሃት ሳታለቅስና ንስሐ ሳትገባ አልቀረችም፡፡ ሰዎች ለራሳቸው ታማኞች የሚሆኑት ሞት ሲገጥማቸው ነው፡፡
‹‹ኦ አምላኬ መሞት የሚገባኝ መሆኑ ትክከል ነው፡፡ እባክህ ነፍሴን በእጆችህ ተቀበል፤ ራራልኝም፡፡ ኢየሱስ ሆይ እባክህ ራራልኝ፡፡›› ኢየሱስ የቤዛነትን ፍቅር እንዲሰጣት ተማጸነችው፡፡ ‹‹አምላኬ ሆይ ከፈረድክብኝ ይፈረድብኛል፤ ሐጢያት የለብሽም የምትል ከሆነም ሐጢያቶቼ ይደመሰሳሉ፡፡ ጉዳዩ ያንተ ነው፡፡›› ምናልባትም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ሳትል አልቀረችም፡፡ ሁሉም ነገር ለኢየሱስ እንደተተወ መስክራ ይሆናል፡፡
በኢየሱስ ፊት የቀረበችው ሴት ‹‹ተሳስቻለሁ፤ እባክህ ምንዝርናዬን ይቅር በለኝ›› አላለችም፡፡ እርስዋ እንዲህ አለች፡- ‹‹እባክህ ከሐጢያቶቼ አድነኝ፡፡ ሐጢያቶቼን ብትዋጅ እድናለሁ፤ ባትዋጅ ሲዖል እወርዳለሁ፡፡ የአንተን ቤዛነት እሻለሁ፡፡ የእግዚአብሄር ፍቅር ያስፈልገኛል፡፤ እንዲራራልኝም እፈልጋለሁ፡፡›› ዓይኖችዋን ጨፍና ሐጢያተኝነትዋን ተናዘዘች፡፡   
ኢየሱስም ‹‹ከሳሾችሽ ከወዴት አሉ? ማንምስ አልፈረደብሽምን?›› በማለት ጠየቃት፡፡ እርስዋም ‹‹ማንም ጌታዬ›› በማለት መለሰች፡፡  
ኢየሱስም እንዲህ አላት፡- ‹‹እኔም አልፈርድብሽም፡፡›› ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በተቀበለው ጥምቀቱ አማካይነት አስቀድሞ ሐጢያቶችዋን በሙሉ ስለወሰደና እርስዋም ቀድሞውኑም ስለተዋጀች አልኮነናትም፡፡ አሁን ለሐጢያቶችዋ ሊፈረድበት ያለው ኢየሱስ እንጂ እርስዋ አይደለችም፡፡   
 
 
እርሱ ‹‹እኔም አልፈርድብሽም›› አላት፡፡  
 
እርስዋ በኢየሱስ ተፈርዶባት ነበርን?
አልተፈረደባትም፡፡

ይህች ሴት በኢየሱስ ደህንነት ተባረከች፡፡ ከሐጢያቶችዋ ሁሉ ተዋጀች፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደዋጀና እኛም ሁላችን ጻድቃን እንደሆንን ይነግረናል፡፡ 
እርሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህንኑ ይነግረናል፡፡ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቅ ለወሰዳቸው ሐጢያቶችም ዋጋ ለመክፈል በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ እርሱ በጥምቀቱ ቤዛነትና በመስቀል ላይ በከፈለው ፍርድ የሚያምኑትን ሁሉ እንደተቤዠ ይናገራል፡፡ ሁላችንም የተጻፈው የኢየሱስ ቃል ያስፈልገናል፡፡ ቃሉንም አጥብቀን መያዝ ያስፈልገናል፡፡ ያን ጊዜ ሁላችንም በቤዛነት እንባረካለን፡፡ 
‹‹አምላኬ ሆይ በፊትህ ሰናይ ነገር የለኝም፡፡ በውስጤ ጥሩ ነገር የለም፡፡ ከሐጢያቶቼ በቀር የማሳይህ ምንም ነገር የለም፡፡ ኢየሱስ የቤዛነት ጌታዬ እንደሆነ ግን አምናለሁ፡፡ እርሱ በዮርዳኖስ ወንዝ ሐጢያቶቼን በሙሉ ወሰደና በመስቀል ላይ አስተሰረያቸው፡፡ በጥምቀቱና በደሙም ሐጢያቶቼን በሙሉ ወሰደ፡፡ ጌታ ሆይ በአንተ አምናለሁ፡፡››   
የዳናችሁት እንዲህ ነው፡፡ ኢየሱስ ‹አይኮንነንም፡፡› የእግዚአብሄር ልጆች የምንሆንበትን መብት ሰጠን፡፡ እርሱ በውሃውና በመንፈሱ ቤዛነት የሚያምኑትን ሰዎች ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ ወስዶ ጻድቃን አድርጎዋቸዋል፡፡ 
ውድ ወዳጆች! ሴቲቱ ቤዛነትን አገኘች፡፡ በምንዝር የተያዘችው ሴት በጌታችን በኢየሱስ ቤዛነት ተባርካለች፡፡ እኛም ደግሞ እንደዚያ ልንባረክ እንችላለን፡፡ ሐጢያቶቹን አውቆ እግዚአብሄር እንዲራራለት የሚጠይቅ ማንኛውም ሰው፤ በኢየሱስ በውሃውና በመንፈሱ ቤዛነትም የሚያምን ማንኛውም ሰው ከእግዚአብሄር ዘንድ የቤዛነትን በረከት ይቀበላል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያተኝነታቸውን የሚያምኑ ሰዎች ሊድኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሐጢያቶቻቸውን የማያውቁ ሰዎች በዚህ ቤዛነት ሊባረኩ አይችሉም፡፡ 
ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች ወሰደ፡፡ (ዮሐንስ 1፡29) በዓለም ላይ የሚኖር ማንኛውም ሐጢያተኛ በኢየሱስ ቢያምን መዳን ይችላል፡፡ ኢየሱስ ለሴቲቱ ‹‹እኔም አልፈርድብሸም›› አላት፡፡ እንደማይፈርድባት የተናገረው ሐጢያቶችዋ በሙሉ ቀድሞውኑም በእርሱ ጥምቀት አማካይነት ወደ እርሱ ስለተላለፉ ነው፡፡ እርሱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ ወሰደ፡፡ በእኛ ፋንታም ለእነዚያ ሐጢያቶች ተኮነነ፡፡  
 
 
በኢየሱስ ፊት ቤዛነትን ማግኘት አለብን፡፡ 
 
የሚበልጠው የትኛው ነው የእግዚአብሄር ፍቅር ወይስ የእግዚአብሄር ፍርድ? 
የእግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ 

በእጆቻቸው ድንጋዮችን ይዘው የነበሩት ፈሪሳውያን እንደዚሁም የዛሬዎቹ የሐይማኖት መሪዎች ሕጉን በፊደሉ መሰረት ይተረጉሙታል፡፡ ሕጉ እንዳናመነዝር ስለሚነግረን እነዚህን ሐጢያቶች የሚሰራ ሰው መወገር እንዳለበት ያምናሉ፡፡ እነርሱ እንደማያመነዝሩ እያስመሰሉ ሴቶችን በፍትወት ዓይኖቻቸው እየሰረቁ ያያሉ፡፡ እነርሱ መቤዠትም ሆነ መዳን አይችሉም፡፡ ፈሪሳውያንና ጸሐፍቶች የዚህ ዓለም ሞራሊስቶች ነበሩ፡፡ ኢየሱስ የጠራቸው ሰዎች አልነበሩም፡፡ እነዚህ ሰዎች ‹‹አልፈርድባችሁም›› የሚለውን ፈጽሞ አልሰሙም፡፡   
እነዚያን የሚያስደስቱ ቃሎች የሰማቸው በምንዝር የተያዘችው ሴት ብቻ ነበረች፡፡ በእርሱ ፊት እውነተኞች ከሆናችሁ እናንተም ደግሞ እንደ እርስዋ መባረክ ትችላላችሁ፡፡ ‹‹አምላኬ ሆይ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ አመነዝራለሁ፡፡ ይህንን የማላውቀው በተደጋጋሚ ስለማደርገው ነው፡፡ እኔ በእያንዳንዱ ቀን ይህንን ሐጢያት ብዙ ጊዜ አደርገዋለሁ፡፡›› 
‹‹አምላኬ ሆይ እኔ እንደዚህ ነኝ፡፡ እባክህ አድነኝ›› በማለት ሕጉንና ሞት የሚገባንና በእግዚአብሄር ፊት በቅንነት መቅረብ የሚገባን ሐጢያተኞች የመሆናችንን እውነታ ስንቀበል እግዚአብሄር በቤዛነቱ ይባርከናል፡፡  
የኢየሱስ ፍቅር የሆነው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የእግዚአብሄርን ቅን ፍርድ አሸንፎዋል፡፡ ‹‹እኔም አልፈርድብሽም፡፡›› እርሱ አይኮንነንም፡፡ እርሱ ‹‹ድናችኋል፡፡›› ይለናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የርህራሄ አምላክ ነው፡፡ ከዓለም ሐጢያቶችም ሁሉ አድኖናል፡፡
አምላካችን የፍትህ አምላክና የፍቅር አምላክ ነው፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ፍቅር ከፍርዱም የላቀ ነው፡፡ 
የእኛ እግዚአብሄር የፍርድና የፍቅር አምላክ ነው፡፡ የጥምቀቱና የመንፈስ ቅዱሱ ፍቅርም ከፍርዱ የበለጠ ነው፡፡  
 
 

ፍቅሩ ከፍርዱ ይበልጣል፡፡ 

 
እርሱ ሁላችንንም የዋጀን ለምንድነው? 
ፍቅሩ ከፍርዱ ስለሚበልጥ ነው፡፡ 

እግዚአብሄር የራሱን ፍትህ ለማጠናቀቅ ፍርዱን ተግብሮ ቢሆን ኖሮ በሐጢያተኞች ሁሉ ላይ ፈርዶ ሲዖል በላካቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ከፍርድ ያዳነን የኢየሱስ ፍቅር ስለሚበልጥ እግዚአብሄር አንድ ልጁን ኢየሱስን ላከው፡፡ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ ወስዶ ስለ ሁላችንም ቅን ፍርድን ተቀበለ፡፡ አሁን ኢየሱስን አዳኙ አድርጎ የሚያምን ማንኛውም ሰው የእርሱ ልጅና ጻድቅ ይሆናል፡፡ ፍቅሩ ከፍርዱ ስለሚበልጥ ሁላችንንም አዳነን፡፡   
እግዚአብሄር በፍርዱ ብቻ ስላልኮነነን ልናመሰግነው ይገባናል፡፡ አንድ ጊዜ ኢየሱስ ፈሪሳውያንን፣ ጸሐፍትንና ደቀ መዛሙርቶቻቸውን እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ምህረትን እወዳለሁ መስዋዕትንም አይደለም የሚለውን ሄዳችሁ ተማሩ፡፡ ሐጢያተኞችን ለንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና፡፡›› (ማቴዎስ 9፡13) አንዳንድ ሰዎች ‹‹አምላክ ሆይ በየቀኑ የምሰራቸውን ሐጢያቶች ይቅር በለኝ›› እያሉ በመጸለይ በየቀኑ ላም ወይም ፍየል እያረዱ በእግዚአብሄር ፊት ያቀርቡ ይሆናል፡፡ እግዚአብሄር የሚፈልገው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያለንን አመኔታ እንጂ ቁርባኖቻችንን አይደለም፡፡ እርሱ ቤዛነትን እንድናገኝና እንድንድን ይፈልጋል፡፡ ፍቅሩን ሊሰጠንና አመኔታችንን ሊቀበል ይፈልጋል፡፡ ይህንን ሁሉ ማየት ትችላላችሁን? ኢየሱስ ፍጹም የሆነውን ደህንነቱን ሰጥቶናል፡፡    
ኢየሱስ ሐጢያትን ይጠላል፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር አምሳል ለተፈጠርነው ሰዎች የሚያቃጥል ፍቅር አለው፡፡ የእርሱ ልጆች ሊያደርገንና በጥምቀቱና በደሙ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ሊደመስስ የወሰነው ከፍጥረት በፊት ነው፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረን ውሎ አድሮ ሊዋጀን፣ በኢየሱስ ሊያለብሰንና የራሱ ልጆች ሊያደርገን ነው፡፡ እርሱ ለፍጥረቶቹ ያለው ፍቅር ይህ ነው፡፡  
እግዚአብሄር ትክክለኛ በሆነው ሕጉ መሰረት ቢፈርድብን ኖሮ እኛ ሐጢያተኞች ሁላችንም በሞትን ነበር፡፡ እርሱ ግን በጥምቀቱና በመስቀል ላይ በሆነው የልጁ ፍርድ አማካይነት አዳነን፡፡ ታምናላችሁን? ይህንን ከብሉይ ኪዳን እናረጋግጥ፡፡  
 
 
አሮን በሚለቀቀው ፍየል ላይ እጆቹን ጫነ፡፡ 
 
የእስራኤልን ሐጢያቶች ወኪላቸው ወደሆነው የሚለቀቅ ፍየል ያስተላለፈው ማነው? 
ሊቀ ካህኑ፡፡ 

የዚህ ዓለም ሐጢያቶች በሙሉ በብሉይ ኪዳን ስርዓትና በአዲስ ኪዳን ጥምቀት በሚያምነው እምነት አማካይነት ተሰርየዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን የእስራኤሎች ዓመታዊ ሐጢያቶች በሙሉ እጆቹን አንዳች ነውሮች በሌሉበት ሕያው ፍየል ራስ ላይ በጫነው ሊቀ ካህን አማካይነት ስርየትን አግኝተዋል፡፡ 
‹‹አሮንም ሁለቱን እጆቹን በሕያው ፍየል ራስ ላይ ይጭናል፤ በላዩም የእስራኤል ልጆች በደል ሁሉ፣ መተላለፋቸውንም ሁሉ፣ ሐጢአታቸውንም ሁሉ ይናዘዛል፡፡ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል፡፡ በተዘጋጀው ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰድደዋል፡፡›› (ዘሌዋውያን 16፡21)
በብሉይ ኪዳን ዘመን ስርየትን ያገኙት እንደዚህ ነበር፡፡ አንድ ሰው ከዘወትር ሐጢያቶቹ ለመዳን እንከን የሌለበት በግ ወይም ፍየል ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣና በመሰውያው ላይ ያቀርበዋል፡፡ እጆቹን በቁርባኑ ራስ ላይ ይጭናል፡፡ ከዚያም ሐጢያቶቹ ወደ መስዋዕቱ ይተላለፋሉ፡፡ መስዋዕቱም ይታረዳል፡፡ ካህኑም ደሙን በመሰውያው ቀንዶች ላይ ይቀባዋል፡፡ 
በመሰውያው በአራቱ ማዕዘናት ላይ ቀንዶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ቀንዶች የሚያመላክቱት በዮሐንስ ራዕይ 20፡12 ላይ የተጻፉትን የምግባር መጽሐፎች ነው፡፡ ቀሪው የመስዋዕቱ ደምም በመሬቱ ላይ ይፈሳል፡፡ መሬቱ የሚያመላክተው የሰውን ልብ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው የተፈጠረው ከአፈር ነውና፡፡ ሕዝቡ የዘወትር ሐጢያቶቹን ስርየት ያገኘው በዚህ መንገድ ነው፡፡
ሆኖም በየቀኑ የሐጢያት ቁርባኖችን ማቅረብ ስለማይችሉ ለአመታዊዎቹ ሐጢያቶቻቸው ሁሉ በአመት አንድ ጊዜ ስርየትን እንዲያገኙ ፈቀደላቸው፡፡ ይህ የስርየት ቀን በሆነው በሰባተኛው ወር በአስረኛው ቀን የሚከናወን ነበር፡፡ በዚያ ቀን የእስራኤሎች ሁሉ ወኪል የሆነው ሊቀ ካህኑ ሁለት ፍየሎችን አቅርቦ የሕዝቡን ሐጢያቶች በሙሉ ወደ እነርሱ ያስተላልፍና ለእስራኤል ሕዝብ ማሰተሰርያ ያደርግ ዘንድ በእግዚአብሄር ፊት አቀረባቸው፡፡ 
‹‹አሮንም ሁለቱን እጆቹን በሕያው ፍየል ራስ ላይ ይጭናል፤ በላዩም የእስራኤል ልጆች በደል ሁሉ፣ መተላለፋቸውንም ሁሉ፣ ሐጢአታቸውንም ሁሉ ይናዘዛል፡፡ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል፡፡ በተዘጋጀው ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰድደዋል፡፡›› 
እግዚአብሄር የእስራኤልን ሊቀ ካህን አሮንን ወኪላቸው እንዲሆን ሾመው፡፡ እያንዳንዱ ሰው በግሉ እጆቹን በመስዋዕቶቹ ላይ ከሚጭን ይልቅ የሕዝቡ ሁሉ ወኪል የሆነው ሊቀ ካህን የአመቱን ሐጢያቶች ለማስተሰረይ እጆቹን በሕያው ፍየል ላይ ጫነ፡፡ 
እርሱ በእግዚአብሄር ፊት የእስራኤላውያንን ሐጢያቶች በሙሉ ይተርካል፡፡ ‹‹አምላክ ሆይ የእስራኤል ልጆችህ ሐጢያትን ሰርተዋል፤ ጣዖታትን አምልከናል፤ የሕግህን አንቀጾች ተላልፈናል፡፡ ስምህን በከንቱ ጠርተናል፡፡ ሌሎች ጣዖታትን ሰርተን ከአንተ ይልቅ ወደናቸዋል፡፡ የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገን አልጠበቅንም፡፡ ወላጆቻችንን አላከበርንም፡፡ ገድለናል፤ አመንዝረናል፤ ሰርቀናል፡፡…ቅንዓትንና ጥልን ተግብረናል፡፡››
እርሱ ሐጢያቶችን ሁሉ ዘረዘረ፡፡ ‹‹አቤቱ የእስራኤል ሕዝብም ሆነ እኔ ከሕግህ አንዳቸውንም መጠበቅ አልቻልንም፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ሐጢያቶች ለመዳን እጆቼን በዚህ ፍየል ራስ ላይ ጭኜ እነዚያን ሐጢያቶች በሙሉ ወደ እርሱ አስተላልፋለሁ፡፡›› ሊቀ ካህኑ በሕዝቡ ሁሉ ፋንታ እጆቹን በቁርባኑ ላይ ጭኖ ሐጢያቶችን ሁሉ ወደ ቁርባኑ ራስ ያስተላልፋል፡፡ እጆችን መጫን ማለት ‹ማስተላለፍ› ማለት ነው፡፡ (ዘሌዋውያን 1፡1-4፤16፡20-21)    
 
በብሉይ ኪዳን ዘመን ስርየት የተፈጸመው እንዴት ነበር? 
እጆችን በሐጢያት ቁርባኑ ራስ ላይ በመጫን ነበር፡፡  

እግዚአብሄር የመስዋዕቱን ስርዓት ለእስራኤል ሕዝብ የሰጣቸው ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ እንዲያስተላልፉና እንዲድኑ ነው፡፡ ሰው እንከን የሌለበትን የሐጢያት ቁርባን ማዘጋጀት እንደሚገባውና ያም ቁርባን በእርሱ ምትክ መሞት እንዳለበት በግልጽ ዘረዘረ፡፡ የግለሰብ ሐጢያተኞች ቤዛነት የሚከናወነው እንደዚህ ነበር፡፡ 
ሆኖም በስርየት ቀን የሐጢያት ቁርባኑ ይታረድና ደሙ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ተወስዶ በስርየት መክደኛው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጫል፡፡ በዚህም የእስራኤል ሕዝብ በሰባተኛው ወር በአስረኛው ቀን ከዓመቱ ሐጢያት ስርየትን ያገኛሉ፡፡  
ሊቀ ካህኑ መስዋዕቱን ለማቅረብ የሚገባው ብቻውን ነው፡፡ ሰዎች ግን በውጭ ተሰብስበው በሊቀ ካህኑ የኤፉድ ቀሚስ ዘርፍ ላይ ያሉትን የወርቅ ቃጭሎች ያዳምጣሉ፡፡ ደሙ በስርየት መክደኛው ላይ ሲረጭ የወርቅ ቃጭሎቹ ሰባት ጊዜ ይደውላሉ፡፡ ያን ጊዜ ሕዝቡ ሐጢያቶቻቸው ስርየትን ስላገኙ ይደሰታሉ፡፡ የወርቅ ቃጭሎቹ ድምጽ የሚያመለክተው የአስደሳቹን ወንጌል ድምጽ ነው፡፡
ኢየሱስ የሚወደው አንዳንድ የተመረጡ ሰዎችን ነው፤ የሚያድናቸውም እነርሱን ብቻ ነው የሚለው አባባል እውነት አይደለም፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለአንዴና ለዘላለም ወሰደ፡፡ ሐጢያቶቻችን በየቀኑ ሊዋጁ ስለማይችሉ በአንድ ጊዜ መደምሰስ ነበረባቸው፡፡  
በብሉይ ኪዳን ስርየት የሚሰጠው በሐጢያት ቁርባኑ ላይ እጅ በመጫንና በደም ነበር፡፡ አሮን በሕዝቡ ሁሉ ፊት እጆቹን በሕያው ፍየል ራስ ላይ ጭኖ ሕዝቡ በዓመቱ ውስጥ የሰራቸውን ሐጢያቶች በሙሉ ዘረዘረ፡፡ በእስራኤሎች ሁሉ ፊትም ሐጢያቶችን ወደ ፍየሉ አስተላለፈ፡፡ ሊቀ ካህኑ በሚለቀቀው ፍየል ላይ እጆቹን ከጫነ በኋላ የሕዝቡ ሐጢያቶች ወዴት ሄዱ? ሁሉም ወደ ፍየሉ ተላልፈው ነበር፡፡  
ከዚያም ፍየሉ ‹በተዘጋጀው ሰው› ይሰደዳል፡፡ የእስራኤሎችን ሐጢያቶች በሙሉ የተሸከመው ፍየል ውሃና ሳር ወደሌለበት ምድረ በዳ ይወስዳል፡፡ ከዚያም ፍየሉ በምታቃጥለው ጸሐይ እየነደደ በምድረ በዳ ይቅበዘበዝና በመጨረሻም ይሞታል፡፡ ፍየሉ የሞተው ለእስራኤላውያን ሐጢያቶች ነው፡፡  
ይህ የእግዚአብሄር ፍቅር ማለትም የቤዛነት ፍቅር ነው፡፡ በዚያ ዘመን የዓመቱ ሐጢያቶች ስርየትን የሚያገኙት በዚህ መንገድ ነው፡፡ እኛ የምንኖረው ግን በአዲስ ኪዳን ዘመን ነው፡፡ ኢየሱስ ወደ ዓለማችን ከመጣ 2,000 አመታት ሆነውታል፡፡ እርሱ መጥቶ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተሰጠውን ተስፋ ፈጸመ፡፡ መጥቶም ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ዋጀን፡፡ 
 
 
ሁላችንንም ለመዋጀት፡፡ 
 
የኢየሱስ ትርጉም ምንድነው?
ሕዝቡን ከሐጢያቶቻቸው የሚያድን አዳኝ ማለት ነው፡፡ 

ማቴዎስ 1፡20-21ን እናንብብ፡- ‹‹እርሱ ግን ይህን ሲያስብ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፡፡ እንዲህም አለ፡- የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ እርስዋ የጸነሰችው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ፡፡ ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱም ሕዝቡን ከሐጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ፡፡›› (ማቴዎስ 1፡20-21)  
በሰማይ የሚኖረው አባታችን የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለማንጻት ልጁን ወደዚህ ዓለም ለመላክ ሲል የድንግል ማርያምን ሰውነት ተበደረ፡፡ ወደ ማርያም መልአክን ልኮም እንዲህ አላት፡- ‹‹እነሆ ትጸንሻለሽ፤ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፡፡ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ፡፡›› ይህ ማለት በማርያም በኩል የሚመጣው ወንድ ልጅ አዳኝ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ማለት ሕዝቡን ከሐጢያቶቻቸው የሚያድን ማለትም አዳኝ ማለት ነው፡፡ 
ታዲያ ኢየሱስ ሁላችንንም ከሐጢያቶቻችን እንዴት አዳነን? ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ የወሰደበት መንገድ በዮርዳኖስ ወንዝ በተቀበለው ጥምቀት አማካይነት ነው፡፡ አጥማቂው ዮሐንስ ባጠመቀው ጊዜ የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ወደ እርሱ ተላልፈዋል፡፡ እስቲ ማቴዎስ 3፡13-17ን እናንብብ፡፡     
‹‹ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡ ዮሐንስ ግን፡- እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል፤ አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር፡፡ ኢየሱስም መልሶ፡- አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው፡፡ ያን ጊዜ ፈቀደለት፡፡ ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውሃው ወጣ፡፡ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ፡፡ የእግዚአብሄርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፡፡ እነሆም ድምጽ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ፡፡››   
ኢየሱስ ሁላችንንም ከሐጢያቶቻችን ሊያድነን ወደ አጥማቂው ዮሐንስ ሄደ፡፡ ውሃ ውስጥ ገብቶም በዮሐንስ ፊት ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡ ‹‹ዮሐንስ አጥምቀኝ፤ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና፡፡ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለመውሰድና ሐጢያተኞችንም ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው ለማዳን ሐጢያቶቻቸውን በጥምቀት መውሰድ ያስፈልገኛል፡፡ አሁኑኑ አጥምቀኝ! ፍቀድ!››  
ስለዚህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባል፡፡ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በአጥማቂው ዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ በዚያች ቅጽበትም ሐጢያቶቻችንን የዋጀው የእግዚአብሄር ጽድቅ በሙሉ ተፈጸመ፡፡ 
እርሱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ የወሰደው በዚህ መንገድ ነው፡፡ የእናንተንም ሐጢያቶች በሙሉ እንደዚሁ ወደ ኢየሱስ ተላልፈዋል፡፡ ይህ ይገባችኋልን? 
በኢየሱስ ጥምቀትና መንፈስ ቤዛነት አምናችሁ ዳኑ፡፡  
 
ጽድቅ ሁሉ የተፈጸመው እንዴት ነበር? 
በኢየሱስ ጥምቀት አማካይነት፡፡ 

እግዚአብሄር የዓለም ሐጢያቶች ለሐጢያት በሚቀርበው መስዋዕት ላይ በእጆች መጫን እንደሚወገዱ አስቀድሞ ለእስራኤል ተስፋ ሰጠ፡፡ ሆኖም እያንዳንዱ ሰው በግሉ እጆቹን በፍየሉ ራስ ላይ መጫን ስለማይቻለው እግዚአብሄር አሮንን ለሕዝቡ ሁሉ መስዋዕትን ማቅረብ እንዲችል ሊቀ ካህን አድርጎ ቀደሰው፡፡ እርሱም ዓመታዊውን ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ በአንድ ጊዜ ለሐጢያት በቀረበው ቁርባን ራስ ላይ አስተላለፈ፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ጥበብና የቤዛነቱ ሐይል ነበር፡፡ እግዚአብሄር ጠቢብና አስገራሚ ነው፡፡ 
እግዚአብሄር መላውን ዓለም ለማዳን ልጁን ኢየሱስን ላከው፡፡ የሐጢያቱም ቁርባን ተዘጋጀ፡፡ እጆቹን በኢየሱስ ራስ ላይ የሚጭንና የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወደ እርሱ የሚያስተላልፍ የሰው ዘር ሁሉ ወኪል መኖር ነበረበት፡፡ ያም ወኪል አጥማቂው ዮሐንስ ነበር፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ዘር ሁሉ ወኪል ከኢየሱስ አስቀድሞ እንደላከው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎዋል፡፡   
ይህም የመጨረሻው የሰው ሊቀ ካህን አጥማቂው ዮሐንስ ነበር፡፡ በማቴዎስ 11፡11 ላይ እንዲህ ተጻፈ፡- ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም፡፡›› እርሱ ብቸኛው የሰዎች ወኪል ነው፡፡ እግዚአብሄር ዮሐንስን የሰዎች ወኪል አድርጎ የላከው ኢየሱስን እንዲያጠምቅና የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወደ እርሱ እንዲያስተላልፍ ነበር፡፡ 
በምድር ላይ ያለው ስድስት ቢሊዮን ሕዝብ አሁኑኑ ወደ ኢየሱስ ቀርበው ሐጢያቶቻቸውን ለማስተላለፍ እጆቻቸውን በኢየሱስ ላይ ቢጭኑ ምን ይፈጠር ነበር? በዚህ ዓለም ላይ የሚኖረው ከስድስት ቢሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ እጆቻቸውን በኢየሱስ ላይ ቢጭኑ ደስ የሚል ትዕይንት አይታይም፡፡ አንዳንድ ስሜቶቻቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ሰዎች በጣም ስለሚጫኑት ጠጉሩ በሙሉ ከላዩ ላይ ይረግፍ ነበር፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር በጥበቡ ወኪላችን ሆኖ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ወደ ኢየሱስ እንዲያስተላልፍ ዮሐንስን ሾመው፡፡      
በማቴዎስ 3፡13 ላይ እንዲህ ተጽፎዋል፡- ‹‹ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡›› ይህ የሆነው ኢየሱስ 30 አመት በሆነው ጊዜ ነበር፡፡ ኢየሱስ የተገረዘው በተወለደ በ8 ቀኑ ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ 30 ዓመት እስኪሆነው ድረስ ስለ እርሱ የተጻፉት ነገሮች ጥቂቶች ናቸው፡፡    
ኢየሱስ 30 ዓመት እስኪሆነው ድረስ የጠበቀበት ምክንያት በብሉይ ኪዳን መሰረት ሕጋዊ የሰማይ ሊቀ ካህን ለመሆን ነበር፡፡ እግዚአብሄር በዘዳግም ውስጥ ሊቀ ካህኑ በሊቀ ክህነት ማገልገል ከመቻሉ በፊት ቢያንስ 30 ዓመት ሊሆነው እንደሚገባ ለሙሴ ነግሮታል፡፡ ኢየሱስ ሰማያዊ ሊቀ ካህን ነበር፡፡ ይህንን ታምናላችሁን?  
በአዲስ ኪዳን በማቴዎስ 3፡13-14 ላይ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡ ዮሐንስ ግን፡- እኔ በአንተ ልጠመቅ ይገባኛል፤ አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር፡፡›› የሰው ዘር ወኪል ማነው? አጥማቂው ዮሐንስ ነው፡፡ የሰማይ ወኪልስ ማነው? ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ወኪሎቹ ተገናኙ፡፡ 
በዚያ ዘመን ለነበሩት የሐይማኖት መሪዎች ‹‹የእፉኝት ልጆች! ንስሐ ግቡ!›› በማለት የጮኸው አጥማቂው ዮሐንስ ድንገት በኢየሱስ ፊት ትሁት ሆነ፡፡ ‹‹እኔ በአንተ ልጠመቅ ይገባኛል፤ አንተ ወደ እኔ ትመጣለህን?››  
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- ‹‹አሁንስ ፍቀድልኝ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና፡፡›› ኢየሱስ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ለመፈጸም መጣ፡፡ ይህም አጥማቂው ዮሐንስ ባጠመቀው ጊዜ ተፈጸመ፡፡ 
‹‹ያን ጊዜ ፈቀደለት፡፡ ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውሃ ወጣ፡፡ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ፡፡ የእግዚአብሄርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱም ላይ ሲመጣ አየ፡፡ እነሆም ድምጽ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ፡፡››  
እርሱ በተጠመቀ ጊዜ የሆነው ይህ ነው፡፡ እርሱ በአጥማቂው ዮሐንስ በተጠመቀና የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በወሰደ ጊዜ የሰማይ ደጆች ተከፈቱ፡፡ 
‹‹ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል፡፡›› (ማቴዎስ 11፡12)  
የእግዚአብሄር ነቢያትና ሕጉ ሁሉ እስከ አጥማቂው ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፡፡ ‹‹ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል፡፡›› በእርሱ ጥምቀት የሚያምን ሁሉ ያለ ምንም ገደብ መንግሥተ ሰማይ መግባት ይችላል፡፡   
 
 
‹‹እኔም አልፈርድብሽም፡፡›› 
 
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ለምን ተፈረደበት? 
የእኛን ሐጢያቶች በሙሉ ስለወሰደ ነው፡፡ 

ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ ተጠምቆ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወሰደ፡፡ በኋላም በምንዝር ለተያዘችው ሴት ‹‹እኔም አልፈርድብሽም›› አላት፡፡ እርሱ በዮርዳኖስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ስለወሰደ ለእነዚህ ሐጢያቶችም መኮነን የነበረበት እርሱ ራሱ እንጂ ሴቲቱ አልነበረችም፡፡   
ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ደመሰሰ፡፡ ‹‹የሐጢያት ደመወዝ ሞት›› ስለሆነ በመስቀል ላይ የሚደርስበትን ስቃይ ምን ያህል ፈርቶ እንደነበር ማየት እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ፍርድ እንዲያስወግድለት በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሦስት ጊዜ ጸልዮ ነበር፡፡ ኢየሱስ እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ ሥጋና ደም ስለነበር ስቃዩን መፍራቱ ተገቢ ነው፡፡ ኢየሱስ ፍርዱን ለመፈጸም መድማት ነበረበት፡፡   
በብሉይ ኪዳን ለሐጢያት የሚቀርቡት ቁርባኖች የሐጢያቶችን ዋጋ ለመክፈል ይደሙ እንደነበር ሁሉ እርሱም በመስቀል ላይ መስዋዕት መሆን ነበረበት፡፡ ቀደም ብሎ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወስዶዋል፡፡ አሁን ለእኛ ቤዛነት ሲል ሕይወቱን መስጠት ነበረበት፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ፍርድን መቀበል እንደነበረበት አወቀ፡፡ 
ኢየሱስ በልቡ ውስጥ ምንም ሐጢያት አልነበረበትም፡፡ ነገር ግን በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶች በሙሉ ወደ እርሱ ስለተላለፉ አሁን እግዚአብሄር በልጁ ላይ ፈረደ፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ የእግዚአብሄር ፍትህ ተፈጸመ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ እርሱ ለደህንነታችን ሲል ፍቅሩን ሰጠን፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ በመስቀል ላይ መኮነን ነበረበት፡፡   
‹‹እኔም አልኮንንሽም፤ አልፈርድብሽምም፡፡›› አቅደንም ሆነ ሳናቅድ፤ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ የሰራናቸው ሐጢያቶቻችን በሙሉ በእግዚአብሄር ሊፈረድባቸው ይገባ ነበር፡፡    
ሆኖም እግዚአብሄር አልፈረደብንም፡፡ እግዚአብሄር በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ በወሰደው በኢየሱስ ላይ ፈረደ፡፡ እግዚአብሄር ከፍቅሩና ከርህራሄው የተነሳ በሐጢያተኞች ላይ ሊፈርድ አልፈለገም፡፡ ጥምቀቱና በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደሙ እርሱ ለእኛ ያለው የቤዛነት ፍቅሩ ነበር፡፡ ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሄር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡›› (ዮሐንስ 3፡16) 
ፍቅሩን የምናውቀው በዚህ መልኩ ነው፡፡ ኢየሱስ በምንዝር የተያዘችውን ሴት አልኮነናትም፡፡ 
እርስዋ በምንዝርና ድርጊት ተይዛ ስለነበር ሐጢያተኛ መሆንዋን አውቃለች፡፡ እርስዋ በልብዋ ውስጥ ሐጢያት የነበረባት ከመሆንዋም በላይ ይህንን ሐጢያት በሥጋዋም ተሸክማ ነበር፡፡ ሐጢያትዋን የምትክድበት ምንም መንገድ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ሐጢያቶችዋን በሙሉ እንደወሰደ ስላመነች ዳነች፡፡ እኛም በኢየሱስ ቤዛነት ብናምን እንድናለን፡፡ ይህንን እመኑ! ለራሳችን ጥቅም ነው፡፡   
 
በእጅጉ የተባረኩት እነማን ናቸው? 
ሐጢያት የሌለባቸው ናቸው፡፡

ሰዎች ሁሉ ሐጢያትን ይሰራሉ፡፡ ሰዎች ሁሉ ዝሙትን ይፈጽማሉ፡፡ ነገር ግን ሰዎች ሁሉ ስለሰሩት ሐጢያቶቻቸው አልተፈረደባቸውም፡፡ ሁላችንም ሐጢያት ሰርተናል፡፡ ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት የሚያምኑ ሰዎች በልቦቻቸው ሐጢያት አልባ ናቸው፡፡ በኢየሱስ ደህንነት የሚያምን ሰው እጅግ ደስተኛ ሰው ነው፡፡ ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ የዳኑ ሰዎች እጅግ የተባረኩ ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር አሁን በኢየሱስ ጻድቃን ናቸው፡፡
እግዚአብሄር በሮሜ 4፡7 ላይ ስለ ብጽዕና ነገረን፡፡ ‹‹ዓመፃቸው የተሰረየላቸው ሐጢአታቸውም የተከደነላቸው ብጹዓን ናቸው፡፡›› ሁላችንም እስከምንሞትበት ጊዜ ድረስ ሐጢያት እንሰራለን፡፡ እኛ በእግዚአብሄር ፊት ሕግ አልባዎችና ጎዶሎዎች ነን፡፡ የእርሱን ሕግ ካወቅን በኋላም ሐጢያት በመስራት እንቀጥላለን፡፡ እኛ በጣም ደካሞች ነን፡፡ 
እግዚአብሄር ግን በአንድያ ልጁ ጥምቀትና ደም አድኖን ለእናንተና ለእኔ ዳግመኛ ሐጢያተኞች እንዳይደለንና አሁን በፊቱ ጻድቃኖች መሆናችንን ነገረን፡፡ የእርሱ ልጆች እንደሆንንም ነገረን፡፡  
የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የዘላለም ቤዛነት ወንጌል ነው፡፡ ይህንን ታምናላችሁን? እርሱ የማያምኑ ሰዎችን ጻድቃን፣ የተዋጁና የራሱ ልጆች ብሎ ይጠራቸዋል፡፡ በዚህ አለም ላይ እጅግ ደስተኛው ሰው ማነው? በእውነተኛው ወንጌል ያመነና የዳነ ሰው ነው፡፡ ድናችኋልን?  
ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን ሲወስድ ያስቀረው አለን? የለም፡፡ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወሰደ፡፡ ይህንን እመኑ፡፡ እመኑና ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ተዋጁ፡፡ ዮሐንስ 1፡29ን እናንብብ፡፡ 
 
 
ልክ በመጥረጊያ እንደተጠረገ ያህል፡፡ 
 
ኢየሱስ የወሰደው ምን ያህሉን ሐጢያት ነው? 
የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ነው፡፡ 

‹‹በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፡- እነሆ የዓለምን ሐጢያት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ፡፡›› (ዮሐንስ 1፡29) 
‹‹እነሆ የዓለምን ሐጢያት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ፡፡›› 
አጥማቂው ዮሐንስ በዮርዳኖስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወደ ኢየሱስ አስተላለፈ፡፡ እርሱ በነገውም ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ እንደሆነ መሰከረ፡፡ እርሱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በጫንቃዎቹ ተሸከመ፡፡  
የዓለም ሐጢያቶች ሁሉ የሚያመላክቱት ሰዎች ከፍጥረት ጀምሮ እስከ መጨረሻ ድረስ የሚሰሩዋቸውን ሐጢያቶች በሙሉ ነው፡፡ ኢየሱስ ከ2,000 አመታት በፊት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወሰደና አዳነን፡፡ የእግዚአብሄር በግ በመሆኑም ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወሰደ፡፡ ስለ እኛም ተፈረደበት፡፡  
እኛ ሰዎች የምንሰራው ማንኛውም ሐጢያት ወደ ኢየሱስ ተላለፈ፡፡ እርሱም የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ የወሰደ የእግዚአብሄር በግ ሆነ፡፡  
ኢየሱስ ትሁት ሆኖ የዓለምን ሐጢያተኞች በሙሉ የሚያድን ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም መጣ፡፡ እኛ ሐጢያት የምንሰራው ደካሞች፣ ክፉዎች፣ መሐይሞች፣ ገልቱዎችና ጎዶሎዎች ስለሆንን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሐጢያት የምንሰራው የሁላችንም አያት ከሆነው ከአዳም ሐጢያትን ስለወረስን ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ሐጢያቶች ተጠርገው በዮርዳኖስ ወንዝ ላይ በወሰደው ጥምቀት በኢየሱስ ራስ ላይ ተጫኑ፡፡ እርሱም በመስቀል ላይ በሥጋው ሞት ሁሉንም አስወገደ፤ ተቀበረ፡፡ እግዚአብሄር ግን በሦስተኛው ቀን ከሙታን አስነሳው፡፡ 
እርሱ አሁን የሐጢያተኞች ሁሉ አዳኝ፣ ድል አድራጊና ፈራጅ ሆኖ በእግዚአብሄር ቀኝ ተቀምጦዋል፡፡ እርሱ እኛን ደጋግሞ ማዳን አይኖርበትም፡፡ እኛ ለመዳን ማድረግ ያለብን በእርሱ ማመን ነው፡፡ የሚያምኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ይጠብቃቸዋል፡፡ የማያምኑ ሰዎች ግን ጥፋት ይጠብቃቸዋል፡፡ ሌላ ምርጫ የለም፡፡ 
ኢየሱስ ሁላችሁንም አዳናችሁ፡፡ እናንተ በምድር ላይ እጅግ ደስተኛ ሰዎች ናችሁ፡፡ በድክመቶቻችሁ ምክንያት ወደፊትም ሐጢያት እንደምትሰሩ የታወቀ ነው፡፡ እርሱ ግን እነዚያንም ሐጢያቶች በሙሉ ወሰደ፡፡ 
በልባችሁ ውስጥ የቀረ አንዳች ሐጢያት አለን?-- የለም፡፡ 
ኢየሱስ ሁሉንም ወስዶታል?--አዎን! ወስዶታል፡፡ 
ሰዎች ሁሉ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ማንም ሰው ከባልንጀራው በላይ ቅዱስ አይደለም፡፡ ነገር ግን ብዙ ሰዎች ግብዞች ስለሆኑ በእርግጥ ሐጢያተኞች ሆነው ሳሉ ሐጢያተኞች እንዳልሆኑ ያምናሉ፡፡ ይህ ዓለም ሐጢያትን የሚንከባከብ የጥላ ቤት (ግሪንሐውስ) ነው፡፡ 
ሴቶች ከቤታቸው ሲወጡ የከንፈር ቀለም ይቀባሉ፡፡ ፊታቸውን ያሰማምራሉ፤ ጸጉራቸውን ይጠቀልላሉ፤ ምርጥ ልብሶችን ይለብሳሉ፤ ታኮ ጫማ ያደርጋሉ፡፡…ወንዶችም ደግሞ ጠጉራቸውን ለመቆረጥ ወደ ጠጉር ቤት ይሄዳሉ፡፡ ራሳቸውንም ያሰማምራሉ፤ ንጹህ ሸሚዞችን ይለብሳሉ፡፡ አዲስ የመጡ ከረቫቶችን ያደርጋሉ፤ ጫማቻቸውንም ይወለውላሉ፡፡   
ነገር ግን በውጭ ሲታዩ መስፍንና እትጌ መስለው ቢታዩም ውስጣቸው ግን ፈጽሞ የረከሰ ነው፡፡ 
ገንዘብ ሰዎችን ደስተኛ ያደርጋልን? ጤና ሰዎችን ደስተኛ ያደርጋልን? አያደርግም፡፡ ሰዎችን እውነተኛ ደስተኞች የሚያደርጋቸው የዘላለም ቤዛነት የሐጢያቶች ሁሉ ይቅርታ ብቻ ነው፡፡ ሰው ከውጭ ሲታይ ምንም ያህል ደስተኛ ቢመስል በልቡ ውስጥ ሐጢያት ካለበት ይህ ሰው ምስኪን ነው፡፡ ይህ ሰው በፍርድ ፍርሃት ውስጥ ይኖራል፡፡
የዳነ ሰው ቡቱቶ ቢለብስም እንኳን እንደ አንበሳ ደፋር ነው፡፡ በልቡ ውስጥ ሐጢያት የለም፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ አመሰግንሃለሁ፡፡ እኔን ሐጢያተኛውን አዳንከኝ፡፡ እኔ ፍቅርህን ለመቀበል የተገባሁ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ስላዳንከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ እኔ ለዘላለም ከሐጢያቶች የዳንሁ ነኝ፡፡ ክብር ለእግዚአብሄር ይሁን!››  
የዳነ ሰው በእርግጥም ደስተኛ ሰው ነው፡፡ በእርሱ የቤዛነት ጸጋ የተባረከ ሰው በእርግጥም ደስተኛ ሰው ነው፡፡ 
‹‹የዓለምን ሐጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ፡፡›› ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ስለወሰደ እኛ ሐጢያት የለብንም፡፡ እርሱ በመስቀል ላይ ደህንነትን ‹‹ፈጸመ፡፡›› የእናንተንና የእኔን ጨምሮ ሐጢያቶቻችን በሙሉ ‹በዓለም ሐጢያት› ውስጥ ስለተካተቱ ሁላችንም ድነናል፡፡  
 
 

በእግዚአብሄር ፈቃድ፡፡ 

 
በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ስንሆን በልባችን ውስጥ ሐጢያት ይኖራልን? 
በፍጹም አይኖርም፡፡ 

ውድ ወዳጆች በምንዝር የተያዘችው ሴት በኢየሱስ ቃሎች አመነችና ዳነች፡፡ ታሪክዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈው በእርሱ የዘላለም ቤዛነት ስለተባረከች ነበር፡፡ ሆኖም ግብዞቹ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ከኢየሱስ ሸሹ፡፡ 
በኢየሱስ ብታምኑ የሚጠብቃችሁ ሰማይ ነው፡፡ ኢየሱስን ብትተዉት ግን ሲዖል ትወርዳላችሁ፡፡ በእርሱ የጽድቅ ምግባሮች ብታምኑ ሰማይ ይሆንላችኋል፡፡ በእርሱ ሥራዎች የማታምኑ ከሆነ ግን ሲዖል ይሆንባችኋል፡፡ ቤዛነት በማንኛውም ሰው ውጥኖች የሚገኝ ሳይሆን በኢየሱስ ደህንነት የሚገኝ ነው፡፡  
ዕብራውያን 10ን እናንብብ፡- ‹‹ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፤ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር የሚያቀርቡት በዚያ መስዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም፡፡ እንደዚህማ ባይሆን የሚያመልኩት አንድ ጊዜ ነጽተው ከዚያ በኋላ በሕሊናቸው ሐጢአትን ስላላወቁ ማቅረብን በተዉ አልነበረምን? ነገር ግን በዚያ መሥዋዕት በየዓመቱ የሐጢአት መታሰቢያ አለ፡፡ የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ሐጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና፡፡ ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ፡- መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም፤ ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፡፡ በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ሐጢአት በሚሰዋ መሥዋዕት ደስ አላለህም፡፡ በዚያን ጊዜ፡- እነሆ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደተጻፈ አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ላደርግ መጥቻለሁ ይላል፡፡ በዚህ ላይ መሥዋዕትንና መባን፣ በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንም፣ ስለ ሐጢአትም የሚሰዋ መሥዋዕትን አልወደድህም፤ በእነርሱም ደስ አላለህም ብሎ እነዚህም እንደ ሕግ የሚቀርቡት ናቸው፡፡ ቀጥሎ፡- እነሆ አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ ብሎአል፡፡ ሁለተኛውን ሊያቆም የፊተኛውን ይሸራል፡፡ በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል፡፡›› (ዕብራውያን 10፡1-10)
‹‹በእግዚአብሄር ፈቃድ፡፡›› ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በአንድ ጊዜ ለመውሰድ ሕይወቱን ሰጠ፡፡ በአንድ ጊዜ ተኮነነ፤ ትንሳኤንም አገኘ፡፡      
ስለዚህ ተቀድሰናል፡፡ ‹ተቀድሰናል› (ዕብራውያን 10፡10) የሚለው የተጻፈው ተፍጻሜትን በሚያሳየው የአሁን ጊዜ ነው፡፡ ይህ ማለት ቤዛነታችን ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፤ ዳግመኛም መጠቀስ አያስፈልገውም ማለት ነው፡፡ እናንተ ተቀድሳችኋል፡፡ 
‹‹ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ሐጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፡፡ እርሱ ግን ስለ ሐጢአት አንድን መሥዋዕት አንዴ ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሄር ቀኝ ተቀመጠ፡፡ ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪደረጉ ድረስ ወደፊት ይጠብቃል፡፡ አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና፡፡›› (ዕብራውያን 10፡11-14)  
ሁላችሁም ለዘላለም ተቀድሳችኋል፡፡ ነገ ሐጢያቶችን ብትሰሩ እንደገና ሐጢያተኞች ትሆናላችሁን? ኢየሱስ እነዚያንም ሐጢያቶች ደግሞ አልወሰደምን? ወስዶዋል፡፡ እርሱ ወደፊት የሚሰሩ ሐጢያቶችንም ደግሞ ወስዶዋል፡፡   
‹‹መንፈስ ቅዱስም ደግሞ ለዚህ ይመሰክርልናል፡፡ ከዚያ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው ይላል፤ በልባቸው ሕጌን አኖራለሁ፤ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ ብሎ ከተናገረ በኋላ ሐጢአታቸውንና ዓመጻቸውንም ደግሜ አላስብም ይላል፡፡ የእነዚህም ስርየት ባለበት ዘንድ ከዚያ ወዲህ ስለ ሐጢአት ማቅረብ የለም፡፡›› (ዕብራውያን 10፡15-18)    
‹የእነዚህም ስርየት› የሚለው ሐረግ እርሱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ አስተሰርዮዋል ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ አዳኛችን ነው፡፡ የእናንተም የእኔም አዳኝ ነው፡፡ በኢየሱስ ማመን አድኖናል፡፡ ይህ የኢየሱስ ቤዛነት ነው፡፡ ከእግዚአብሄር የተሰጠ እጅግ ታላቁ ጸጋና ሥጦታም ነው፡፡ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ የተዋጀነው እናንተና እኔ ከሰዎች ሁሉ እጅግ የተባረክን ነን!