Search

ወንጌል ምንድነው?

የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ምንድነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዩ፡- መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ሐጢያታችን ሞተ፤ ተቀበረም፡፡ መጽሐፍ እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፡፡›› (1ኛ ቆሮንቶስ 15፡3-4) ‹‹መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ሐጢያታችን ሞተ›› በሚለው ሐረግ ውስጥ ‹‹መጽሐፍ›› የሚለው ቃል ምን ማለት ነው? ብሉይ ኪዳን ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ቃል ኪዳንና መገለጥ መሠረት ለሐጢያታችን ሁሉ እንደሞተ ተናገረ፡፡ እርሱ ለሐጢያታችን ሁሉ ስርየትን የሰጠው እንዴት ነው? ይህንን ያደረገው በጽድቅ ድርጊቱ ማለትም በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ሞቱ ነው፡፡

በጥንቷ ቤተክርስቲያን ዘመን እስከ 2ኛው ምዕተ ዓመት ማብቂያ ድረስ የገና በዓል እንዳልነበረ ታውቃላችሁ፡፡ የጥንት ክርስቲያኖች ከሐዋርያቶች ጋር አብረው ጥር 6ን ‹‹የኢየሱስ ጥምቀት ቀን›› አድርገው አከበሩት፡፡ ይህም ብቸኛው የጥንቷ ቤተክርስቲያን ክብረ በዓል ነበር፡፡

ሐዋርያት በኢየሱስ ጥምቀት ላይ ትልቅ ትኩረት ያደረጉት ለምንድነው? ይህ እነርሱ ከኢየሱስ የተቀበሉትና ለዓለም የበኩት የእውነተኛው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ምስጢር ነው፡፡ ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- ‹‹ሰው ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ አግዚአብሄር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡›› (ዮሐንስ 3፡5) መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ እኛን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ለማዳን በውሃና በደም እንደመጣ ተናገረ፡፡ (1ኛ ዮሐንስ 5፡6) ደም ማለት መስቀል ነው፡፡ ታዲያ የውሃው ፍቺ ምንድነው?

(የአማኞችን የውሃ ጥምቀትና የኢየሱስን ጥምቀት እንደማትደበላልቁት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እባካችሁ ለኢየሱስ ጥምቀት ጠንከር ያለ ትኩረት ስጡ፡፡ እኛ አሁን በአማኞች የውሃ ጥምቀት ላይ ወይም በጥምቀታዊ መታደስ ላይ ጥኩረት እያደረግን አይደለም፡፡)

ኢየሱስ ለምን አጥማቂው ዮሐንስ ተጠመቀ ኢየሱስ የራሱን ጥምቀት ‹‹ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል›› (ማቴዎስ 3፡15) በማለት አወጀ?

ዕብራውያን 10፡1 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሕጉ (እነዚያ መስዋዕቶች) ሊመጣ ያለው በጎ ነገር እውነተኛ አምሳል…›› በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሄር ለደህንነታቸው ለሕዝቡ የሰጠውን ጥላዊ መስዋዕት እንይ፡፡ ማንኛውም ሰው ሐጢያት ከሠራና ከበደለ ሐጢያተኛው ለሐጢያቶቹ ስርየት ለማግኘት የሐጢያት ቁርባን ማቅረብ ነበረበት፡፡ ዘሌዋውያን 1፡3-5ን እንይ፡- ‹‹መባውም የሚቃጠል መስዋዕት ከላሞች መንጋ ቢሆን ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርባል፤ በእግዚአብሄር ፊት እንዲሠምር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ያቀርበዋል፡፡ እጁንም በሚቃጠለው መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ ያስተሰርይለትም ዘንድ የሠመረ ይሆንለታል፡፡ በሬውንም በእግዚአብሄር ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን ያቀርባሉ፤ ደሙንም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ባለው በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል፡›› እዚህ ላይ የሐጢያቱ ቁርባን በእግዚአብሄር ፊት ሕጋዊ ለመሆን ከታች ያሉትን ሦስት መስፈርቶች ማሟለት እንደነበረበት ማየት እንችላለን፡፡

እነርሱ፡-
  • (1) ነውር የሌለበት የመስዋዕት እንስሳ ማዘጋጀት (ቁ. 3)
  • (2) በሚቃጠለው ቁርባን ራስ ላይ እጆቹን መጫን (ቁ. 4).
  • (3) ለሐጢያቱ ስርየት መስዋዕቱን መግደል (ደሙን ማፍሰስ) (ቁ. 5) ማድረግ ነበረባቸው፡፡
ሊቀ ካህኑ አሮን እጆቹን በፍየሉ ራስ ላይ በጫነ ጊዜ የእስራኤላውያን ሐጢያቶች በሙሉ ወደ ፍየሉ ራስ ተላልፈው ነበር፡፡

ከላይ በተጠቀሱት በእነዚህ ቁጥሮች የመስዋዕቱ እንስሳ ከመገደሉ በፊት ሐጢያት በእጆች መጫን መንገድ ወደ መስዋዕቱ እንስሳ መተላለፍ የነበረበት የመሆኑን የእግዚአብሄር ሕግ ማረጋገጥ አለብን፡፡ ይህ በጣም አስፈላጊ እውነት ነው፡፡ በቀጣዮቹ የዘሌዋውያን ምዕራፎች ውስጥ ለሐጢያት ስርየት ‹‹በሐጢያት ቁርባን ራስ ላይ እጆችን መጫን›› የመሳሰሉ ብዙ መግለጫዎችን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ ዘሌዋውያን 16፡21 እንዲህ ይላል፡- ‹አሮንም ሁለቱን እጆቹን በሕያው ፍየል ራስ ላይ ይጭናል፤ በላዩም የእስራኤልን ልጆች በደል ሁሉ፣ መተላለፋቸውንም ሁሉ፣ ሐጢአታቸውንም ሁሉ ይናዘዛል፤ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል፤ በተዘጋጀው ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰድደዋል፡፡››

ሊቀ ካህኑ አሮን እጆቹን በፍየሉ ራስ ላይ በጫነ ጊዜ የእስራኤላውያን ሐጢያቶች በሙሉ ወደ ፍየሉ ራስ ተላልፈው ነበር፡፡ ሐጢያተኛው እጆቹን በመስዋዕቱ ላይ በጫነ ጊዜ ሐጢያቶቹ ወደ መስዋዕቱ ራስ ላይ ይተላለፋሉ፡፡ በተመሳሳይ መንገድ አንድ ሰው ለክህነት ሲሾም አገልጋይ ክህነቱን ለማስተላለፍ እጆቹን በግለሰቡ ራስ ላይ ይጭናል፡፡ ስለዚህ ‹‹እጆችን መጫን›› ሐጢያቶችን ወደ መስዋዕቱ የማስተላለፍ ድርጊት ነው፡፡ ይህም ‹‹ማሻገር›› ማለት ነው፡፡

ከዚያም ‹‹የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና…ለነፍሳችሁ ማስተሰርያ›› (ዘሌዋውያን 17፡11) በመሆኑ ምክንያት እንስሳው ደሙን በማፍሰስ መገደል ነበረበት፡፡

ሆኖም እስራኤላውያን ለሐጢያቶቻቸው በሙሉ ስርየትን ለማግኘት በጣም ደካሞች ነበሩ፡፡ ሐጢያት በሰሩ ጊዜ ሁሉ የሐጢያት ቁርባኖችን ቢያቀርቡም እንኳን በየቀኑ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ሐጢያት ከመስራት ማምለጥ የሚችሉ አልነበሩም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር በዓመት አንድ ጊዜ ዓመታዊ ሐጢያቶቻቸው ይቅር የሚባልበት ሌላ ዕድል ከፈተላቸው፡፡ ይህም የስርየት ቀን ስርዓት ነበር፡፡ በስርየት ቀን ሊቀ ካህኑ አሮን የእስራኤላውያንን ሁሉ ዓመታዊ ሐጢያቶች በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ለማስተላለፍ እጆቹን በሚለቀቀው ፍየል ራስ ላይ ጫነ፡፡ (ዘሌዋውያን 16፡21)

አሮን በእስኤላውያን ሁሉ ምትክ እጆቹን በፍየሉ ራስ ላይ በመጫኑ በዚያን ጊዜ የእስራኤላውያን ወኪል ነበር፡፡ እርሱ ራሱ እጆቹን በፍየሉ ራስ ላይ በጫነ ጊዜ የእስራኤላውያን (በዚያን ጊዜ ቁጥራቸው ከ2-3 ሚሊዮን አካባቢ ነበር) ዓመታዊ ሐጢያቶች በሙሉ በእርሱ ሕጋዊ ምግባር አማካይነት ወደሚለቀቀው ፍየል ራስ ላይ ተላለፈ፡፡ ይህም ለሰው ዘር ሁሉ የዘላለም ስርዓት ነበር፡፡ (ዘሌዋውያን 16፡29)

ያ ‹‹ሊመጣ ያለው በጎ ነገር›› (ዕብራውያን 10፡1) ነበር፡፡ አሁን እግዚአብሄር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ‹‹ሊመጣ ያለውን በጎ ነገር›› አጠናቀቀ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት ኪዳኑን እንደፈጸመ እንይ፡፡

በመጀመሪያ እግዚአብሄር አብ ተስፋ የተገባለት የእግዚአብሄር በግ አድርጎ ኢየሱስ ክርስቶስን ነውር በሌለበት የሰው መልክ ላከው፡፡ እርሱ የእግዚአብሄር አንድያ ልጅ ነው፤ እርሱ ቅዱስ አምላክም ደግሞ ነው፡፡ ስለዚህ እርሱ ምንም ነውር የሌለበት የሰው ዘር ሁሉ መስዋዕት ለመሆን ገጣሚ ነበር፡፡

ሁለተኛ እርሱ በአጥማቂው ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡ እዚህ ላይ ኢየሱስን ያጠመቀው አጥማቂው ዮሐንስ ማን እንደነበር ማወቅ ያስፈልገናል፡፡ አጥማቂው ዮሐንስ የሊቀ ካህኑ የአሮን ዘር ነበር፡፡ የዮሐንስ አባት ካህኑ ዘካርያስ የአሮን የልጅ ልጅ በሆነው በአብያ የዘር ሐረግ ውስጥ የተወለደ ነበር፡፡ (ሉቃስ 1፡5፤ 1ኛ ዜና 24፡10) ስለዚህ አጥማቂው ዮሐንስ የሊቀ ካህኑ የአሮን ዘር ነበር፡፡ ይህ ማለት እርሱ ሊቀ ካህን ለመሆን መብት ነበረው ማለት ነው፡፡ ከዚህም በላይ ኢየሱስ ዮሐንስ ከሰው ዘር ሁሉ መካከል ከተወለዱት እጅግ ታላቁ መሆኑን አረጋገጦለታል፡፡ ‹‹እውነት እላችኋለሁ፤ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም…ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፡፡›› (ማቴዎስ 11፡11,14) ይህ ማለት ዮሐንስ በምድር ላይ የመጨረሻው ሊቀ ካህንና እግዚአብሄር ተስፋ የገባለትና ያዘጋጀው ሕጋዊ የሰው ዘር ወኪል ነው ማለት ነው፡፡

ብሉይ ኪዳን ተንብዮለታል፡- ‹‹እነሆ መልዕክተኛዬን እልካለሁ፤ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፡፡›› (ሚልክያስ 3፡1) ‹‹ለእስራኤል ሁሉ ሥርዓትንና ፍርድን አድርጌ በኮሬብ ያዘዝሁትን የባሪያዬን የሙሴን ሕግ አስቡ፡፡ እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሄር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ፡፡ መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል፡፡›› (ሚልክያስ 4፡4-6) ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- ‹‹ልትቀበሉትስ ብትወዱ ሊመጣ ያለው ኤልያስ ይህ ነው፡፡›› (ማቴዎስ 11፡14)

አጥማቂው ዮሐንስ የሚመጣው ኤልያስ ሆኖ እርሱን እንዲቀበሉ በማዘጋጀት ሰዎችን ሁሉ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መለሰ፡፡ እርሱ የተወለደው ከኢየሱስ ስድስት ወር ቀደም ብሎ ነበር፡፡ እርሱ የጌታን መንገድ ለማዘጋጀት በምድረ በዳ ለሕዝቡ የንስሐን ጥምቀት አጠመቀ፡፡ እርሱ እነርሱን ለአዳኛቸው ለኢየሱስ ክርስቶስ ለማዘጋጀት ሕዝቡ የብሉይ ኪዳንን ሕግና የመስዋዕት ስርዓት እንዲያስታውሱ መምራት አስፈለገው፡፡ ስለዚህ ሰዎችን አጠመቀና አዳኙ በቅርቡ እንደሚመጣና በእጆች መጫን መልክ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንደሚያስወግድ እንዲገነዘቡ አደረጋቸው፡፡ የዮሐንስ ጥምቀት ሐጢያተኞችን ወደ እግዚአብሄር እንዲመለሱ ጠራ፡፡ ስለዚህ ብዙ ሰዎች በዮሐንስ በኩል የእግዚአብሄርን ቃሎች ሰሙና ጣዖቶቻቸውን በመተው ሐጢያቶቻቸውን እየተናዘዙ ወደ እግዚአብሄር ተመለሱ፡፡

በአዲስ ኪዳን ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ የተጠመቀው የዓለምን ሐጢያት በሙሉ ለማንጻት ነበር፡፡

ከዚያም ኢየሱስ ከገሊላ በአጥማቂው ዮሐንስ ለመጠመቅ ዮሐንስ ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡ ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- ‹‹አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና፡፡›› (ማቴዎስ 3፡15) እዚህ ላይ ጽድቅ ሁሉ በግሪክ ‹‹ዲካዮሱኔ›› ሲሆን ትርጉሙም ‹‹ሚዛናዊ፤ ፍትህ›› ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ኢየሱስ ሐጢያተኞችን ሁሉ ፈጽሞ ቅንና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ከሐጢያቶቻቸው አዳናቸው ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን በሰጠው ኪዳን መሰረት ‹‹በእጆች መጫን›› በኩል ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ መውሰድ ነበረበት፡፡ እርሱ ከዮሐንስ ጥምቀትን በመቀበል የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ መውሰዱ እጅግ ተገቢ መንገድ ነበር፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በመውሰዱ በማግስቱ አጥማቂው ዮሐንስ እንዲህ መሰከረ፡- ‹‹እነሆ የዓለምን ሐጢያት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ!›› (ዮሐንስ 1፡29) ዮሐንስ የመጣው በእጆች መጫን ኢየሱስን ለማጥመቅ ነበር፡፡ ዮሐንስ እጆቹን በኢየሱስ ራስ ላይ በጫነበት ቅጽበት የዓለም ሐጢያት በሙሉ በእግዚአብሄር ሕግ መሠረት ወደ እርሱ ተላለፈ፡፡

ሦስተኛ እርሱ ለሐጢያታችን ስርየት ተሰቀለ፡፡ የመጨረሻ እስትንፋሱን ከመስጠቱ በፊት እንዲህ አለ፡- ‹‹ተፈጸመ!›› (ዮሐንስ 19፡30) እርሱ የሐጢያታችንን ደመወዝ ለመክፈል ደሙን በሙሉ አፈሰሰ፡፡ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተነሳ፤ ወደ ሰማይም አረገ፡፡ እርሱ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ደሙ የዓለምን ሐጢያት በሙሉ ደመሰሰ፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ሰለ ሐጢአታችን ሞተ፡፡›› (1ኛ ቆሮንቶስ 15፡3) አሁን በብሉይ ኪዳን የመስዋዕቱ እንስሳ ለሐጢያት ስርየት ለምን እንደቀረበና ይህም ለምን ሊመጣ ያለው በጎ ነገር ጥላ እንደሆነ ገባችሁ?

የመስዋዕቱን እንስሳ ከማረድ በፊት ‹‹እጆች መጫን›› መኖር አለበት፡፡ አንድ ሰው የሐጢያት ቁርባን በሚያቀርብበት ጊዜ ‹‹እጆቹን በመስዋዕቱ ላይ መጫንን›› ከገደፈ በዓመጸኝነቱ ምክንያት የሐጢያቱን ይቅርታ ማግኘት አይችልም፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ ያለ ሕገ ወጥ መስዋዕት በጭራሽ አይቀበልም ነበር፡፡ ይህ በመስዋዕቱ ላይ እጆችን መጫንን መግደፍ መስዋዕትን በማቅረብ ረገድ እግዚአብሄር የጠውን ሕግ የሚጥስ ነበር፡፡

ኢየሱስ ወደዚህ ምድር የመጣው በጽድቅ ድርጊቱ ሐጢያታችንን በሙሉ ለማንጻት ነው፡፡ (ሮሜ 5፡18) የእርሱ የጽድቅ ድርጊት የዓለምን ሐጢያት ለመውሰድ በአጥማቂው ዮሐንስ መጠመቁና የሐጢያትን ደመወዝ ለመክፈል መሰቀሉ ነበር፡፡ እርሱ በጥምቀቱና በደሙ መጣ፡፡ ነገር ግን እንደ አለመታደል ሆኖ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች የሚያውቁት የእርሱን የጽድቅ ድርጊት ገሚሱን ክፍል ብቻ ነው፡፡ እኛ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሙሉውንም ክፍል ማወቅ ይገባናል፡፡ የወንጌሉን አስፈላጊ ክፍል በመግደፍ በእርሱ ማመን ሕገ ወጥነትና ባዶነት ነው፡፡

ሐዋርያው ዮሐንስ የወንጌሉን ሙሉውን ክፍል በመጀመሪያ መልዕክቱ ውስጥ ግልጥ አድርጎታል፡- ‹‹በውሃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውሃውና በደሙ እንጂ በውሃው ብቻ አይደለም፡፡›› (1ኛ ዮሐንስ 5፡6)

የተወለድነው ሐጢያተኛ ተፈጥሮ ይዘን ነው፤ እስከ መጨረሻው እስትንፋሳችን ድረስም ሐጢያትን እንሠራለን፡፡ ሐጢያት ከመስራት በቀር ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ ከእግዚአብሄር ፍርድም ማምለጥ አንችልም፡፡ እኛ የሰው ዘሮች በሙሉ ወደ ሲዖል ለመሄድ የተመደብን ነን፡፡ ‹‹የሐጢአት ደመወዝ ሞት ነው፡፡›› (ሮሜ 6፡23) ነገር ግን ሐጢያት በበዛበት ጸጋ ከመጠን ይልቅ በዛ፡፡ ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሄር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡›› (ዮሐንስ 3፡16)

የእግዚአብሄር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሄር በግ ሆኖ ወደዚህ ዓለም መጣ፡፡ በአጥማቂው ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ የዓለምን ሐጢያት በሙሉ ወሰደ፡፡ ዮሐንስ የሰው ዘር ሁሉ ወኪል ሆኖ በኢየሱስ ራስ ላይ እጆቹን ጫነ፤ በዚያ ቅጽበት የዓለም ሐጢያት በሙሉ ወደ ኢየሱስ ተላለፈ፡፡ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በጥምቀቱ ወሰደና በመስቀል ላይ ተሸከማቸው፡፡ ለሐጢያታችን ደመወዝ ይሆን ዘንድም የተቀደሰውን ደሙን በሙሉ አፈሰሰ፤ የዓለምንም ሐጢያት በሙሉ ፈጽሞ አስተሰረየ፡፡

ስለዚህ በመስቀል ላይ የመጨረሻውን እስትንፋሱን ከመስጠቱ በፊት ‹‹ተፈጸመ!›› ብሎ ጮኸ፡፡ በኢየሱስ የተፈጸመው ምን ነበር? ሐጢያትና ፍርዶቹ ሁሉ በእርሱ የጽድቅ ድርጊት ተፈጸሙ፡፡ በሌላ አነጋገር በእርሱ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ሞቱ ለሐጢያቶቻችን ሁሉ ይቅርታን አገኘን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከ2,000 ዓመታት በፊት የዓለምን ሐጢያት በሙሉ ደመሰሰና አዲስና ሕያው መንገድን ቀደሰ፡፡ (ዕብራውያን 10፡20) አሁን የእርሱ ጸጋ ዘመን ነው፡፡ በእርሱ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ሞቱ የሚያምን ሁሉ ለሐጢያቶቹ ሁሉ ይቅርታን ያገኝና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ይሆናል፡፡ (የሐዋርያት ሥራ 2፡38) ሐሌሉያ!

ምን እንላለን! የእርሱ ጥምቀት ለደህንነታችን አስፈላጊ የጽድቅ ምግባር መሆኑን የሚያረጋግጡ በጣም ብዙ ጥቅሶች አሉ፡፡ (ማቴዎስ 3፡13-17፤ 1ኛ ጴጥሮስ 3፡21፤ ዮሐንስ 6፡53-55፤ ኤፌሶን 4፡5፤ ገላትያ 3፡27፤ የሐዋርያት ሥራ 10፡37 ወ.ዘ.ተረፈ)

በዚህ እውነት ታምናለህን? በልብ ውስጥ ምንም ሐጢያት የለም? ኢየሱስ ከውልደትህ እስከ አሁን ያለውን ሐጢያትህን በሙሉ ወስዶዋል? እርሱ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞትህ ድረስ ያለውን ሐጢያትህን በሙሉ ከ2,000 ዓመት በፊት በጥምቀቱ ወስዶዋል? ታዲያ በእርሱ ጥምቀትና በደሙ በማመን ፈጽመህ ተቀድሰሃልን?

ዛሬ ክርስትና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ዳግመኛ መመለስ አለበት፡፡ ስለ ውሃውና መንፈሱ ወንጌል ይበልጥ በዝርዝር ማወቅ የሚፈልግ ሁሉ ከኒው ላይ ሚሽን ጋር ለመገናኘት አያመንታ፡፡ የሬቨረንድ ፖል ሲ. ጆንግን መጽሐፎች/ኢ-መጽሐፎች በነጻ ማግኘት ትችላለህ፡፡