Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 8፡ መንፈስ ቅዱስ

[8-19] የቤተ መቅደሱን መጋረጃ የቀደደው ውብ ወንጌል ‹‹ ማቴዎስ 27፡45-54 ››

የቤተ መቅደሱን መጋረጃ የቀደደው ውብ ወንጌል
‹‹ ማቴዎስ 27፡45-54 ››
‹‹ከስድስት ሰዓትም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ፡፡ በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፡፡ ይህም አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውከኝ? ማለት ነው፡፡ በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው፡- ይህስ ኤልያስን ይጠራል አሉ፡፡ ወዲያው ከእነርሱ  አንዱ ሮጠ፤ ሰፍነግም ይዞ ሆምጣጤ ሞላበት፡፡ በመቃም አድርጎ አጠጣው፡፡ ሌሎቹ ግን፡- ተው ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደሆነ እንይ አሉ፡፡ ኢየሱስ ሁለተኛ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፤ ነፍሱንም ተወ፡፡ እነሆ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፡፡ ምድርም ተናወጠች፤ አለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም  ተከፈቱ፡፡ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሱ፡፡ ከትንሳኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ፡፡ የመቶ አለቃውም ከእርሱም ጋር ኢየሱስን የሚጠብቁ መናወጡን የሆነውን ነገር አይተው፡- ይህ በእውነት የእግዚአብሄር ልጅ ነበረ ብለው እጅግ ፈሩ፡፡››     
 
 
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ነፍሱን በተወ ጊዜ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ለሁለት የተቀደደው ለምን ነበር?
ምክንያቱም የእግዚአብሄር መንግሥት በእርሱ ጥምቀትና ስቅለት ለሚያምኑ ሰዎች ስለተከፈተች ነበር፡፡
 
አንድ ሰው የዚህን ውብ ወንጌል እውነት ለመረዳት በመጀመሪያ በብሉይ ኪዳን በእግዚአብሄር ፊት የሕዝቡን ሐጢያቶች ይቅር ለማለት ይፈጸም የነበረውን መስዋዕታዊ ስርዓት ማወቅና መረዳት ይኖርበታል፡፡ ተከታዩን እውነት ማወቅና ማመን አለባችሁ፡፡
በብሉይ ኪዳን በዘሌዋውያን ምዕራፍ 16 ላይ እንደተመዘገበው በጥንቱ የስርየት መስዋዕት መሰረት ሊቀ ካህኑ በሕይወት በቀረበው ፍየል ራስ ላይ እጆቹን በመጫን በዓመቱ ሁሉ ውስጥ በሕዝቡ የተከማቹትን ሐጢያቶች በሙሉ ያሻግራል፡፡ ከዚያም መስዋዕቱ በእስራኤላውያን ፋንታ ይታረዳል፡፡ ሊቀ ካህኑም ደሙን በስርየት መክደኛው ላይ ይረጨዋል፡፡ ይህም ለእስራኤሎች ሐጢያቶች ሁሉ ስርየትን ያስገኛል፡፡ ልክ እንደዚሁ ወደ ቅዱሱ መቅደስ መግባት የሚችሉት በእጆች መጫን፣ በደሙና በእግዚአብሄር ቃሎች ያመኑ ብቻ ናቸው፡፡
ካህናት አገልግሎቶችን ለመፈጸም ሁልጊዜም በመገናኛው ድንኳን የመጀመሪያው ክፍል ውስጥ ይገባሉ፡፡ ነገር ግን ቅድስተ ቅዱሳን ወደሆነው ወደ ሁለተኛው ክፍል ሊቀ ካህኑ ብቻ በዓመት አንድ ጊዜ ይገባበታል፡፡ እርሱም ወደዚያ የሚገባው ለራሱና በአለማወቅ ለተፈጸሙት የሕዝቡ ሐጢያቶች የሚሆን ደም ይዞ ነው፡፡ (ዕብራውያን 9፡6-7) ልክ እንደዚሁ ሊቀ ካህኑም ቢሆን በእምነት እጆችን በመጫን አማካይነት የተዘጋጀውን የመስዋዕት ደም ሳይዝ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት አይችልም፡፡
 
 

በአዲስ ኪዳን እንደተነገረው ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ መስዋዕት ሆነ

 
በአዲስ ኪዳን ውስጥ አንድ ሰው ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ሊገባ የሚችለው በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመን እንደሆነ ተነግሮናል፡፡ የእግዚአብሄር መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት የተቀደደው መቼ ነበር? ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ በተሰቀለ ጊዜ ነበር፡፡
ለዚህ የተሰጠው ምክንያት ምን ነበር? ኢየሱስ መስዋዕት ማለትም የእግዚአብሄር በግ ሆኖ ወደዚህ ዓለም በመምጣት በዮሐንስ ተጠምቆ የዓለምን ሐጢያቶች አስወገደ፡፡ በተሰቀለ ጊዜም የሰውን ዘር ሁሉ ከሐጢያቶቹ አነጻ፡፡ የመጋረጃው መቀደድ ከእግዚአብሄር የለዩን የሰው ልጅ ሐጢያቶች በሙሉ በእርሱ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ለመንጻታቸው ምሳሌ ነበር፡፡
ኢየሱስ ራሱ ሞት የሆነውን የሐጢያት ደመወዝ በመክፈል ይህንን ግድግዳ አፈረሰው፡፡ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች ለማስወገድ ተጠመቀና ተሰቀለ፡፡ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ለሁለት የተቀደደበት ምክንያት ይህ ነበር፡፡ ካህናቶች እጆችን በመጫን አምነው ወደ መገናኛው ድንኳን ይገቡ እንደነበር ዛሬም እኛ በኢየሱስ ጥምቀትና ደም ላለን እምነት ምስጋና ይድረሰውና መንግሥተ ሰማይ መግባት እንችላለን፡፡
ኢየሱስ በተሰቀለ ጊዜ በታላቅ ድምጽ እንዲህ ሲል ጮኸ፡- ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ?›› ትርጓሜውም ‹‹አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?›› (ማቴዎስ 27፡46) ማለት ነው፡፡ በመጨረሻም ነፍሱን በተወ ጊዜ ‹‹ተፈጸመ›› አለ፡፡ (ዮሐንስ 19፡30) ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ ከተጠመቀ ጊዜ አንስቶ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ስለተሸከመ በመስቀል ላይ ሳለ ለቅጽበት ያህል በእግዚአብሄር ተተወ፡፡
እርሱ ለሰው ዘር ሁሉ ደህንነት ሞተ፡፡ ከኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ከሆነው ሞቱ የተነሳ በእርሱ ያመኑ ሁሉ ዳኑ፡፡ እኛ ሐጢያተኞች ሆነን ስለተወለድንና ለኩነኔ ስለተመደብን ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ለማስወገድ ተጠመቀ፡፡
የመንግሥተ ሰማይ በር ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ እስከሚያስወግድ ድረስ ጥርቅም ተደርጎ ተዘግቶ ነበር፡፡ ኢየሱስ በዮሐንስ በተጠመቀና በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ውብ በሆነው ወንጌል የሚያምን ማንኛውም ሰው ወደ ሰማያዊው የእግዚአብሄር መቅደስ ይገባ ዘንድ የእግዚአብሄር መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፡፡
እኔ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እምነት ስላለኝ ጌታን አመሰግነዋለሁ፡፡ አሁን ኢየሱስ በጥምቀቱና በደሙ አማካይነት በፈጸመው ውብ ወንጌል በማመኔ መንግሥተ ሰማይ መግባት እችላለሁ፡፡ በራሴ ሐይሎች፣ በጥረቶቼና በክንውኖቼ ደህንነትን ማግኘት አልቻልሁም፡፡
ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚመራን በረከት በተራ ጸሎቶች፣ በልግስናዎችና ራስን በመስጠት የሚገኝ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ከሐጢያት መዳን የሚችለው በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመን ነው፡፡ አንድ ሰው መንግሥተ ሰማይ መግባት የሚችለው በዚህ ውብ ወንጌል በማመን ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ የሰማይ በር ነው፡፡ በኢየሱስ ለሚያምኑ ሌሎች አመኔታዎች አስፈላጊ አይደሉም፡፡ ሰማይ መግባት ለልግስናው፣ ለዓለማዊ ጥረቶቹ ወይም ለሌሎች በጎ ምግባሮች ካሳ ሆኖ አልተሰጠም፡፡ ምዕመናን ወደ መንግሥቱ ለመግባት የሚያስፈልጋቸው አንድ እውነተኛ አስፈላጊ ነገር በዮርዳኖስ በሆነው የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመን ነው፡፡
በውሃውና (በዮርዳኖስ ወንዝ በሆነው የኢየሱስ ጥምቀት) በደሙ (መስቀል) ማመን ወደ መንግሥተ ሰማይ ይመራችኋል፡፡ በልቡ ውስጥ ሐጢያት ያለበት ሰው በኢየሱስ ቢያምንም በአንድ ነገር ማመን አለበት፡፡ እርሱም የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው፡፡ ‹‹እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል፡፡›› (ዮሐንስ 8፡32)
እኛ የሞትንበትን ትክክለኛ ጊዜ በጭራሽ አናውቅም፡፡ ኢየሱስ ግን ሁሉን ያውቃል፡፡ እርሱ የሐጢያት ተፈጥሮዋችንን ከሁለት ሺህ አመት በፊት በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን ሁሉ አነጻ፡፡
 
 

የቤተ መቅደሱን መጋረጃ ለሁለት በተረተረው ውብ ወንጌል ማመን አለብን

 
የሰውን ዘር ከሐጢያቶቻቸው ለማዳን አዳኝ ከድንግል ተወለደ፡፡ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ያስወገደው በ30 አመቱ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ ነበር፡፡ ምስጋና ለኢየሱስ ይግባውና ከድካሞቻቸውና ከጉድለቶቻቸው የተነሳ የተከሰቱት የሰው ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ይቅር ተብለዋል፡፡ የእርሱ ጥምቀትና ደም ለሰው ዘር ሁሉ ደህንነት የዘላለም ቁልፎች ናቸው፡፡ ኢየሱስ ተጠምቆ በመስቀል ላይ ደሙን አፈሰሰ፡፡ አሁን በዚህ ወንጌል እምነት ያላቸው ሁሉ መንግሥተ ሰማይ መግባት ይችላሉ፡፡
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ነፍሱን በሰጠ ጊዜ የእግዚአብሄር መቅደስ መጋረጃ ተቀደደ፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የእግዚአብሄር መቅደስ እንዴት ለሁለት ሊቀደድ ቻለ? ምክንያቱ የሰው ዘር ደህንነት ውብ በሆነው ወንጌል በእርሱ ስለተከናወነ ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን ስለ እስራኤል የመገናኛ ድንኳን እንማራለን፡፡ እዚያ የሚቃጠለው መስዋዕት መሰዊያና የመታጠቢያው ሳህን አለ፡፡ ይህንን የመታጠቢያ ሳህን አልፎ የመገናኛው ድንኳን አለ፡፡ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከመጋረጃው በስተ ጀርባ የእግዚአብሄር ሕልውናና ክብር ያደረበት ታቦቱ አለ፡፡ መጋረጃው በደምብ የተሸመነ ስለነበር  በአራቱም አቅጣጫ አራት ፈረሶች ቢጎትቱት እንኳን ሊተረትሩት አይችሉም ነበር፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን የመገናኛውን ድንኳን በመቅደስ ቢተካውም መሰረታዊው ቅርጽ አልተለወጠም፡፡ መጋረጃው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚያስገባውን መንገድ ጋርዶ እዚያው ነበር፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ደሙን በመስቀል ላይ አፍስሶ በሞተ ጊዜ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፡፡ ይህም በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ የተፈጸመው ወንጌል ምን ያህል ውብና ፍጹም እንደሆነ ይመሰክራል፡፡
እግዚአብሄር የሰውን ዘር ሁሉ ውብ በሆነው ወንጌል በማቀፍ በሐጢያት ይቅርታና በዘላለም ሕይወት ባረካቸው፡፡ ኢየሱስ መስዋዕት ሆኖ በዮሐንስ በተጠመቀና በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የሐጢያትን ደመወዝ ከፈለ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹የሐጢአት ደመወዝ ሞት ነው፡፡›› (ሮሜ 6፡23) በብሉይ ኪዳን ዘመን አንድ ሰው በመስዋዕቱ ደም ወደ እግዚአብሄር መቅደስ እንደሚገባና የሐጢያት ስርየትን ሊያገኝ እንደሚችል ሁሉ እኛም መስዋዕታችን በሆነው በኢየሱስ ወደ እግዚአብሄር ቀርበን ከመተላለፎቻችን ሁሉ ይቅርታን ማግኘት እንችላለን፡፡ እውነቱ ይህ ነው፡፡ ‹‹የሐጢአት ደመወዝ ሞት ነው›› የሚሉት ቃሎችም ውብ የሆነው ወንጌል ምን ያህል ፍጹም እንደሆነ ያሳያሉ፡፡
የሰማይ መንገድ ውብ በሆነው ወንጌል ማመን ነው፡፡ መጋረጃው ለሁለት መቀደዱ የእግዚአብሄርን መንግሥት መከፈት ያመለክታል፡፡ ይህንን ወንጌል ‹‹ኦ ኢየሱስ ሐጢያቶቼን ሁሉ አስወገደ፡፡ ኦ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሐጢያትን ደመወዝ በሙሉ ከፈለ!›› ብለን ስናውቀውና ስናምነው የሰማይ በር በፊታችን ይከፈታል፡፡ አሁን ሰማይ በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ አማካይነት በማመን ቤዛነትን ላገኙት የተከፈተ ነው፡፡ የኢየሱስ ደም ሐጢያተኞችን ከሞት አዳነ፡፡ የእርሱ ጥምቀትም የሰውን ዘር ሁሉ ሐጢያቶች ለመውሰድ መንገድ ነበር፡፡
ጌታ በመስቀል ላይ ነፍሱን በሰጠ ጊዜ ምድር ተናወጠች፤ አለቶችም ተሰነጠቁ፡፡ ያን ጊዜ ደሙ በምድር ላይ ተንጠባጥቦ ወደ ታችኛው መሬት መፍሰስ ጀመረ፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የሰው ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ተወገዱ፤ ውብ የሆነው ወንጌልም ተጠናቀቀ፤ አማኞች ሁሉም ወደ መንግሥተ ሰማይ ለመግባት ብቃት ያላቸው ሆኑ፡፡ ዳግም የመወለድ እውነት ይህ ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ሰው መሆኑን ለመካድ ብዙ ሊቃውንቶች ምርምር አድርገዋል፡፡ ነገር ግን የእርሱን ኑባሬነት የሚያሳዩትን በርካታ ታሪካዊ መረጃዎች መቃወም ባለመቻላቸው መላ ምቶቻቸው አልጸኑም፡፡ ከእነርሱ መካከል ብዙዎቹ  ተስፋ ቆርጠው በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ ወደ ማመን መጥተዋል፡፡ የኢየሱስ ማስረጃ ሊካድ በማያስችል ሁኔታ የተረጋገጠ እንደነበር ተረድተዋል፡፡ በዚህ ውብ ወንጌል ማለትም በውልደቱ፣ በጥምቀቱ፣ በሞቱ፣ በትንሳኤው፣ በዕርገቱና በዳግም ምጽዓቱ ማመንና እነዚህን ነገሮች ማወቅ ስለቻሉ ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው ተቀበሉ፡፡
እኛ የኢየሱስን ጥምቀት አላየንም፡፡ የዛሬ 2,000 አመት የሆነውን ነገር አይኖቻችን አላዩትም ነገር ግን በተጻፈው አማካይነት ማንም ሰው ከዚህ ውብ ወንጌል ጋር መገናኘት ይችላል፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱና በደሙ አማካይነት በእግዚአብሄርና በሰው መካከል የነበረውን ግድግዳ አፈረሰ፡፡ በዚህም የእግዚአብሄር መንግሥት መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፡፡
አሁን በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ በተጠናቀቀው በዚህ ውብ ወንጌል የሚያምን ማንኛውም ሰው መንግሥተ ሰማይ መግባት ይችላል፡፡ የኢየሱስ ጥምቀትና ደሙ ማለትም ይህ ውብ ወንጌል የመንግሥተ ሰማይ ቁልፍ መሆኑን ታምናላችሁን?
እኔ ራሴ ኢየሱስ አዳኜ እንደሆነ የማምን ነገር ግን ውብ የሆነውን ወንጌል የማላውቅ ሐጢያተኛ ነበርሁ፡፡ ሆኖም አንድ ቀን እርሱ ለእኔ ስላለው የማያልቅ ፍቅር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አነበብሁ፡፡ እርሱ ለእኔ እንደተጠመቀ፣ በመስቀል ላይ ለእኔ እንደሞተና ለእኔ እንደተነሳ አወቅሁ፡፡ ኢየሱስ ለእኛ ካለው ፍቅር የተነሳ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቅ አዳነን፡፡ የሐጢያትንም ደመወዝ ለመክፈል ተሰቀለ፡፡ በዚህ ውብ ወንጌል በማመን መንግሥተ ሰማይ መግባት እንችላለን፡፡
ይህ እግዚአብሄር ለሰው ዘር የሰጠው እጅግ ታላቁ ጽድቅና ታሪክ ሰሪ ኩነት ነው፡፡ የእርሱ አገልግሎት-- ውልደቱ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ የሆነው ጥምቀቱ፣ የመስቀል ላይ ሞቱና ትንሳኤው-- በሙሉ እኛን ከሐጢያቶቻችን ለማዳን የተከናወነ ነው፡፡ ስንሞት ፍጻሜያችን ሲዖል ነበር፡፡ ኢየሱስ ግን ለዘላለም በሲዖል ከመቆየት ነፍሳችንን አዳናትና ወደ መንግሥተ ሰማይ እንገባ ዘንድ ውብ የሆነውን ወንጌል ሰጠን፡፡
ውድ ወንድሞች ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ አንድ ወታደር ጎኑን በጦር ወጋው፡፡ ወዲያውም ደምና ውሃ ወጣ፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጻፈው መሰረት የሆነ ነው፡፡ ይህ ውብ ስለሆነው የኢየሱስ ጥምቀትና ስለ ደሙ ወንጌል ይመሰክራል፡፡
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመን እናንተን ከሐጢያቶቻችሁ ነጻ ለማውጣት በቂ ነው ብላችሁ ታስባላችሁን? የኢየሱስ ጥምቀት ለደህንነታችሁ ኢምንት ወይም በአጋጣሚ የሆነ ነገር ብቻ ነውን? እንደዚያ የምታምኑ ከሆነ እባካችሁ ንስሐ ግቡ፡፡ አሁን በኢየሱስ ጥምቀትና ደም ወንጌል ማመንና ይህንንም የእግዚአብሄር እውነት አድርገን መቀበል ይኖርብናል፡፡
 
 

ከሐጢያቶቻችሁ በሙሉ መንጻት ትፈልጋላችሁን?

 
ከዕዳ መውጣት የምንፈልግ ከሆነ ዕዳችንን መክፈል እንደሚያስፈልገን ሁሉ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ለመንጻም ውብ በሆነው የኢየሱስ ጥምቀትና ደም ወንጌል ማመን አለብን፡፡ የኢየሱስን ጥምቀትና ደም ወንጌል ያለማመን ሐጢያት መስራት የለብንም፡፡ ሐጢያቶቻችንን በቀጥታ ወደ ኢየሱስ ባናሻግርም አጥማቂው ዮሐንስ ተብሎ የተጠራ መካከለኛ ሥራውን ስለ እኛ ሰራ፡፡
ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ በኢየሩሳሌም ያሉ አንዳንድ የቅዱሳን መቃብሮች ተከፈቱ፡፡ ከሦስት ቀናት በኋላም እርሱ ትንሳኤን አግኝቶ ወደ ገሊላ ሄደ፡፡ ይህ ድንቅ ኩነት በእርግጥም ሆንዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ኩነት ያላመኑ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡
ጌታችን የሐጢያት ስርየትን ለተቀበልነው ለእኛ ለጻድቃን መንግሥተ ሰማይን ሰጠን፡፡ የዳንነውና ዳግም የተወለድነው በሥጋችን ሐይል ወይም በሐይማኖታዊ ጥረቶቻችን ሳይሆን ውብ የሆነውን ወንጌል በማመናችን ነው፡፡ ይህ ወንጌል ልብ ወለድ ታሪክ አይደለም፡፡ የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ወደ እርሱ ተሻግረዋል፡፡ በእርሱ ውስጥ ሐጢያት አልነበረም፡፡ ነገር ግን በጥምቀቱ ወቅት ለወሰዳቸው ሐጢያቶች ስርየትን ለመስጠት በመስቀል ላይ መሞት ነበረበት፡፡
ኢየሱስ ነፍሱን በሰጠ ጊዜ ምድር ተናወጠች፡፡ አለቶችም ተሰነጠቁ፡፡ የኢየሱስን ሬሳ ሲጠብቁ የነበሩት የመቶ አለቃውና አብረውት የነበሩት የመሬት መናወጡንና የሆኑትን ነገሮች ሲያውቁ እጅግ ስለፈሩ እንዲህ ሲሉ መሰከሩ፡- ‹‹በእርግጥም ይህ የእግዚአብሄር ልጅ ነበር፡፡›› (ማቴዎስ 27፡54)
ከአርማትያ የመጣው ባለጠጋው ዮሴፍ የኢየሱስን ሬሳ ወስዶ በንጹህ በፍታ ከጠቀለለው በኋላ በራሱ መቃብር ውስጥ አኖረው፡፡ ሊቀ ካህኑና ፈሪሳውያኖችም መቃብሩ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ ተጠብቆ እንዲቆይ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡
ሆኖም ኢየሱስ ውብ በሆነው ወንጌል ለሚያምኑት አዲስ ሕይወትን ለመስጠት ተነሳ፡፡ ከመሰቀሉ በፊት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመገናኘት ቃል በገባው መሰረት ወደ ገሊላ ሄደ፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች--ውልደቱ ጥምቀቱ ስቅለቱ ትንሳኤ ዕርገቱና ዳግም ምጽዓቱ-- ያነጣጠሩት ውብ በሆነው ወንጌል በሚያምኑት ላይ ነው፡፡ እኔም ራሴ ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሄር ልጅና አዳኜ መሆኑን እመሰክራለሁ፡፡
 
 
እውነተኛው ወንጌል የሚሰበከው በማን ነው?
 
በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ የሚያምኑ አማኞች ውብ የሆነውን የእውነት ወንጌል ይመሰክራሉ፡፡ ውብ የሆነው ወንጌል ከሐጢያቶቻቸው በዳኑት በእነዚህ ሰዎች ምስክርነት አማካይነት ያሰራጫል፡፡ አንድ ሰው በወንጌል በማመን ከሐጢያቶቹ ነጻ ሲወጣ የእግዚአብሄር መንፈስ ሊገዛው ይጀምራል፡፡ ፈቃዱ ምንም ይሁን ይለውጠዋል፡፡ ነፍስን የሚያድኑት የእግዚአብሄር ቃሎች ጻድቁን በየጊዜው ይለውጡታል፡፡ ነፍስን የሚለውጡት የእግዚአብሄር ቃሎች ጻድቁን ሰው ለዘለቄታው ይለውጡትና ጠንካራ እምነትን ይሰጡታል፡፡ እርሱም ጌታን ያመሰግናል፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በውስጡ ይኖራል፡፡ ከዚያ የተነሳ በየቀኑ ውስጡ ይታደሳል፡፡ ሰዎችም በዚህ መንገድ ተለውጦ ሲያዩት ‹‹እርሱ በእርግጥም ነጻ የወጣ ሰው ነው፡፡ እውነተኛ ክርስቲያንና የእግዚአብሄር ልጅ ሆነ›› ብለው ይመሰክሩለታል፡፡
ዲያብሎስም ቢሆን ይህንን ውብ ወንጌል ይቀበልና መቃወም ይሳነዋል፡፡ ‹‹ተማርኬያለሁ!›› ይላል፡፡ ‹‹ነገር ግን በዓለም ላይ ሐጢያት የሌለ መሆኑ እውነት ነው፡፡ ማንም በልቡ ውስጥ ሐጢያት የለበትም፡፡›› ስለዚህ ዲያብሎስ በታመነው ሕይወታቸው ውስጥ ጣልቃ በመግባት በሰዎች አስተሳሰቦች ውስጥ ይሰራል፡፡ የዲያብሎስ ሥራ መንፈሳዊዎቹን የወንጌል በረከቶች ከመቀበል እነርሱን ማገድ ነው፡፡
ሰይጣን ከኢየሱስ ጋር ባደረገው ጦርነት ሙሉ በሙሉ ተሸነፈ፡፡ ሰይጣን የሰዎችን አእምሮ በመቆጣጠር ኢየሱስን እንዲሰቀል በማድረጉ ተሳካለት፡፡ ሆኖም ኢየሱስ በተጠመቀና የሐጢያትን ደመወዝ ለመክፈል በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የዓለምን ሐጢያቶች አስቀድሞ አስወግዶዋል፡፡ ከዚህ የተነሳ በወንጌል የሚያምኑትን ሁሉ ሙሉ በሙሉ አዳናቸው፡፡
ዲያብሎስ እግዚአብሄር የሰውን ዘር ከሐጢያቶቻቸው ለማዳን ያቀደውን ዕቅድ ማደናቀፍ አልቻለም፡፡ ኢየሱስ ውብ የሆነውን ወንጌል ለማጠናቀቅ ሲል በጥምቀቱና በደሙ የሰውን ዘር ሐጢያቶች ደመወዝ ከፈለ፡፡ አሁን በዚህ ዓለም ላይ ሐጢያት የለም፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያትን ሁሉ አስወግዶ ‹‹ተፈጸመ›› (ዮሐንስ 19፡30) በማለት በመስቀል ላይ ሞቱ ሐጢያትን ሁሉ ወደ ፍጻሜ አመጣ፡፡ ሰይጣን ውብ በሆነው ወንጌል የሚያምኑትን የሚከስበት ሐይሉ ተነጥቋል፡፡ ኢየሱስ በውልደቱ በጥምቀቱ በስቅለቱና በትንሳኤው ዲያብሎስን አሸነፈ፡፡
አሁን በልቦቻችሁ ውስጥ ሐጢያት አለን? የለም፡፡ ክርስቲያኖች ውብ በሆነው የእውነት ወንጌል መሰረት በመተማመን ‹‹በልቤ ውስጥ ሐጢያት የለም›› ማለት ይችላሉ፡፡ ውብ በሆነው የኢየሱስ የጥምቀትና ደም ወንጌል የሚያምን ግለሰብ በልቡ ውስጥ አንዲት ቅንጣት ሐጢያት የለበትም፡፡
አሁን ውብ የሆነው ወንጌል በልቦቻችሁ ውስጥ ተቀርፆዋል፡፡ አሁን በእግዚአብሄር ፊት ከማንኛውም የሞራል ዝቅጠት ነጻ ነን፡፡ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ጥምቀቱ ሐጢያቶቻችሁን ሁሉ እንደወሰደ ሁላችሁም ታምናላችሁን? ካመናችሁ ለእግዚአብሄር ያላችሁ ምስጋናና ደስታ ሙሉ ይሆናል፡፡ ውብ በሆነው ወንጌል በማመን ተቀድሰናል፡፡ በዚህ ዓለም ላይም ከሐጢያቶቻችን ነጻ ወጥተናል፡፡ እግዚአብሄርን እናመሰግናለን፡፡
‹‹እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፤ ቤዛነቱንም እርሱንም የሐጢአት ስርየትን ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን፡፡›› (ቆላስያስ 1፡13-14) ሐሌሉያ ጌታ ይመስገን፡፡
ኢየሱስ ውብ በሆነው ወንጌል አማካይነት የደህንነትን በር ከፈተ፡፡ የመቅደሱ መጋረጃ ለሁለት እንደተቀደደ ሁሉ እናንተም ውብ በሆነው ወንጌል ሐይል በልባችሁ ውስጥ ያለውን ግድግዳ በአንድ ጊዜ ማፍረስ አለባችሁ፡፡ ውብ የሆነው ወንጌል የተበጀው ለእናንተና ለእኔ ነው፡፡ ይህንን ወንጌል በማመን መንግሥተ ሰማይ መግባት እንችላለን፡፡ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ እንድንቀበል የሚፈቅድልን ፍጹም የሆነው እውነት ይህ ነው፡፡