Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[2-1] ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን የተጻፈ ደብዳቤ፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 2፡1-7 ››

ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን የተጻፈ ደብዳቤ፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 2፡1-7 ››
‹‹በኤፌሶን ወዳለው ወደ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፡- በቀኝ እጁ ሰባቱን ከዋክብት የያዘው በሰባቱም የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚሄደው እንዲህ ይላል፡- ሥራህንና ድካምህን ትዕግስትህንም አውቃለሁ፡፡ ክፉዎችንም ልትታገስ እንዳትችል እንዲሁም ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉትን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፡፡ ታግሰህማል፤ ስለ ስሜም ብለህ ጸንተህ አልደከምህም፡፡ ዳሩ ግን የምንቅፍብህ ነገር አለኝ፡፡ የቀደመውን ፍቅር ትተሃልና፡፡ እንግዲህ ከወዴት እንደወደቅህ አስብ፡፡ ንስሐም ግባ፡፡ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፡፡ አለዚያ እመጣብሃለሁ፤ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ፡፡ ነገር ግን ይህ አለህ፤ እኔ ደግሞ የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ ጠልተሃልና፡፡ መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡ ድል ለነሣው በእግዚአብሄር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ፡፡›› 
 
 

ትንተና፡፡

 
ቁጥር 1፡- ‹‹በኤፌሶን ወዳለው ወደ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፡- በቀኝ እጁ ሰባቱን ከዋክብት የያዘው በሰባቱም የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚሄደው እንዲህ ይላል፡-››
የኤፌሶን ቤተክርስቲያን ጳውሎስ በሰበከው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በማመን የተተከለች የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ነበረች፡፡ በዚህ ምንባብ ውስጥ ‹‹ሰባቱ መቅረዞች›› የሚያመላክቱት የእግዚአብሄርን አብያተ ክርስቲያናት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑትን ሰዎች ጉባኤዎች ሲሆን ‹‹ሰባቱ ክዋክብቶች›› የሚያመላክቱት ደግሞ በዚያ ያሉትን የእግዚአብሄርን ባሮች ነው፡፡ ‹‹በቀኝ እጁም ሰባቱን ከዋክብት የያዘው›› የሚለው ሐረግ እግዚአብሄር ራሱ ባሮቹን ይዞ ይጠቀምባቸዋል ማለት ነው፡፡
እግዚአብሄር በባርያው በዮሐንስ በኩል በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የተናገረው ነገር የፍጻሜውን ዘመን መቃረብ እየተጋፈጡ ላሉት የአሁኑ ዘመን ቤተክርስቲያኖቹም ሁሉ የተነገሩ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር በቤተክርስቲያኖቹና በባሪያዎቹ አማካይነት ይናገረናል፡፡ የሚጠብቁንንም ችግሮችና መከራዎች እንዴት እንደምናሸንፋቸውም ይነግረናል፡፡ የራዕይን ቃል በማድመጥና በመስማት ሰይጣንን ማሸነፍ አለብን፡፡ እግዚአብሄር ለቤተክርስቲያኖቹ ለእያንዳንዳቸው ይናገራል፡፡
 
ቁጥር 2፡- ‹‹ሥራህንና ድካምህን ትዕግስትህንም አውቃለሁ፡፡ ክፉዎችንም ልትታገስ እንዳትችል እንዲሁም ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉትን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፡፡››
ጌታ የኤፌሶንን ቤተክርስቲያን ስለ ሥራዎችዋ፣ ስለ ድካምዋና ስለ ትዕግስቷ፣ ክፋትን ስለ መቃወምዋና ሐሰተኛ ነቢያቶችን መርምራ ስለ ማጋለጥዋ ተመስግናለች፡፡ የኤፌሶን ቤተክርስቲያን እምነትና መሰጠት ምን ያህል ታላቅ እንደነበር ከዚህ ምንባብ መረዳት እንችላለን፡፡ ነገር ግን የእምነት ጅማሬ ምንም ያህል ጥሩ የነበረ ቢሆንም ያ እምነት በኋላ አቅጣጫውን ከሳተ የማይጠቅም እንደሚሆን መገንዘብ አለብን፡፡ እምነታችን ጅማሬውና ፍጻሜው በጽናት ያው ሆኖ የሚቆይ እውነተኛ እምነት መሆን አለበት፡፡
ነገር ግን የኤፌሶን ቤተክርስቲያን አገልጋይ እምነት እንደዚያ አልነበረም፡፡ ለዚህም ክፉኛ በእግዚአብሄር ተወቅሶ መቅረዙን ከስፍራው እንደሚወስድበት አስጠነቀቀው፡፡ የቤተክርስቲያን ታሪክ እንደሚገልጠው በትንሽዋ እስያ የነበሩት ሰባቱ አብያተ ክርስቲያኖች በእርግጥም መቅረዞቻቸው ተወስደው ተረግመዋል፡፡ ከኤፌሶን ቤተክርስቲያን ትምህርቶች መማርና የእኛም ቤተክርስቲያኖች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ በእምነት እንዲተከሉ አድርገን የእግዚአብሄር ድጋፍ ያላቸው ሊሆኑ እንደሚገባና እኛም በዚህ እምነት ቤተክርስቲያኖቻችንን የምንጠብቅ የእግዚአብሄር ባሮች መሆን እንዳለብን ማስታወስ ይገባናል፡፡
 
ቁጥር 3፡- ‹‹ታግሰህማል፤ ስለ ስሜም ብለህ ጸንተህ አልደከምህም፡፡››
ጌታችን የእርሱን ቤተክርስቲያኖች በሙሉ ይጠብቃል፡፡ የእርሱ ቅዱሳኖችም ስለ ስሙ ሲሉ ምን ያህል እንደለፉ በሚገባ ያውቃል፡፡ የኤፌሶን ቤተክርስቲያን ቅዱሳን ግን የመጀመሪያውን ፍቅራቸውን ትተው ንጹህ የሆነውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በሌሎች እምነቶች በመበረዝ በተሳሳተ መንገድ ላይ መውደቅ ጀምረው ነበር፡፡
 
ቁጥር 4፡- ‹‹ዳሩ ግን የምንቅፍብህ ነገር አለኝ፡፡ የቀደመውን ፍቅር ትተሃልና፡፡››
የኤፌሶን ቤተክርስቲያን አገልጋይና የቅዱሳኑ የእምነት ሥራዎች ታላቅ ስለነበሩ ጌታ ራሱ ለሥራዎቻቸው፣ ለድካሞቻቸውና ለትዕግስታቸው አመሰገናቸው፡፡ እነርሱ ሐሰተኛ ነቢያቶችን መርምረው አጋለጡ፡፡ ለጌታ ስም ሲሉ ታገሱ፤ ለፉም፡፡ አልደከሙም፡፡ ነገር ግን በእነዚህ እጅግ ታላላቅ የተመሰገኑ ሥራዎች መካከል ከእነዚህ ከማናቸውም ሁሉ ይልቅ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የማያከራክረውን አንድ ነገር አጡ፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጣቸውን የቀደመውን ፍቅራቸውን ተዉ፡፡
ይህ ምን ማለት ነው? ጌታን በመቀበላቸውና በእምነታቸው በአንድ ጊዜ ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ እንዲድኑ የፈቀደላቸውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መጠበቅ ተሳናቸው ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መተው ማለት ወደ ቤተክርስቲያናቸው ሐሰተኛ ትምህርቶችና ሌሎች ወንጌሎች ሾልከው እንዲገቡ ፈቅደዋል ማለት ነው፡፡
ታዲያ እነዚህ ሌሎች ወንጌሎችና ትምህርቶች ምን ነበሩ? ዓለማዊ ፍልስፍናዎችና ሰውኛ አስተሳሰቦች ነበሩ፡፡ እነዚህ ነገሮች አሁንም እግዚአብሄር ለሰው ዘር የሰጠውን የደህንነት እውነት የሚቃወሙ ናቸው፡፡ ለሰው ሥጋ ይጠቅሙ ይሆናል፤ ወይም ምናልባት በሰዎች መካከል አንድነትንና ሰላምን ለማምጣት ተስማሚ ይሆኑ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሰዎች ልብ ከእግዚአብሄር ልብ ጋር እንዲቆራኝ ማድረግ አይችሉም፡፡ የኤፌሶን ቤተክርስቲያን አገልጋይና ቅዱሳን እምነታቸውን በእግዚአብሄር ፊት በተረገሙ ከሐዲዎች እምነት የለወጡት ለዚህ ነው፡፡ ጌታ የወቀሳቸውም ለዚህ ነው፡፡
የቤተክርስቲያንን ታሪክ ስንመለከት የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል መዝቀጥ የጀመረው በጥንቷ ቤተክርስቲያን ክፍለ ዘመን ጅማሬ ላይ እንደነበር ማየት እንችላለን፡፡ እኛም ከዚህ ትምህርት በመውሰድና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በጽናት መያዝ፣ ጌታን በማይዋዥቅ እምነት ማስደሰትና ከእነርሱ ጋር በምናደርገው ትግልም ሰይጣንንና ዓለምን ማሸነፍ አለብን፡፡
የኤፌሶን ቤተክርስቲያን አገልጋይና ቅዱሳን ‹‹የቀደመው ፍቅር›› ምን ነበር? የቀደመው ፍቅራቸው እግዚአብሄር የሰጣቸው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ የውሃውና መንፈሱ ሕግ እያንዳንዱን ሰው ከዓለም ሐጢያቶች በሙሉ የማዳን ሐይል ያለው የደህንነት ቃል ነው፡፡
እግዚአብሄር ለጳውሎስ፣ ለዮሐንስና በእስያ ላሉት የሰባቱ ቤተክርስቲያናት አገልጋዮች የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ምን እንደሆነ በመግለጥ እንዲያስተውሉት ፈቅዶላቸዋል፡፡ በዚህ ወንጌል ማመን የቻሉት ለዚህ ነው፡፡ በእነርሱ የተሰበከውን ወንጌል ሰምተው ያመኑ ሰዎችም ከዓለም ሐጢያቶች በሙሉ መዳን የቻሉት በዚህ መንገድ ነው፡፡
በጌታችን የተሰጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በክርስቶስ የጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ቃል ውስጥ ይገኛል፡፡ የኤፌሶን ቤተክርስቲያን አገልጋይ ግን ጌታን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ተገናኝቶ ገና ከመጀመሪያው በምስጋና ቢሰብከውም በኋላ ግን ይህንን ወንጌል ተወው፡፡ ስለዚህ ጌታ በዚህ ምንባብ ውስጥ ስለ ስህተቱ ወቀሰው፡፡
 
ቁጥር 5፡- ‹‹እንግዲህ ከወዴት እንደወደቅህ አስብ፡፡ ንስሐም ግባ፡፡ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፡፡ አለዚያ እመጣብሃለሁ፤ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ፡፡››
የኤፌሶን ቤተክርስቲያን አገልጋይ ከእግዚአብሄር ፍቅር ወድቋል ማለት ጉባኤው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ትቶዋል ማለት ነው፡፡ ጌታ እምነታቸውን የት እንደጣሉ እንዲያስቡ፣ ንስሐ እንዲገቡና የቀደመውን ሥራ እንዲሰሩ የነገራቸው ለዚህ ነው፡፡
ታዲያ የኤፌሶን ቤተክርስቲያን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንድታጣ ሊያደርጋት የቻለው ምንድነው? ቤተክርስቲያኒቱን ያሳታት ከአገልጋይዋ ጋር የተያያዙት ሥጋዊ አስተሳሰቦች የኤፌሶንን ቤተክርስቲያን እምነት በማድከማቸው ነው፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ከእግዚአብሄር የመጣ የዚህን ዓለም ሐይማኖቶች ሁሉ የሐሰት ትምህርቶችና አስተምህሮቶች ያጋለጠ ፍጹም እምነት ነው፡፡ ይህ ማለት የኤፌሶን ቤተክርስቲያን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በሰበከችና ባሰራጨች ጊዜ ከዓለማዊ ሰዎች ጋር መጋጨት አይቀሬ ነበር ማለት ነው፡፡
ይህ ግጭት በተራው የኤፌሶን ቤተክርስቲያን ምዕመናኖች ከዓለማዊ ሰዎች ጋር ለመግባባት አሰቸግሮዋቸው ነበር፡፡ እንዲያውም ስለ እምነታቸው ወደ መሰደድ መርቶዋቸዋል፡፡ ይህንን ለመሸሽና ሰዎችም ወደ ቤተክርስቲያን እንዲገቡ ለማቅለል የኤፌሶን ቤተክርስቲያን አገልጋይ ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል ተለይቶ ይበልጥ ፍልስፍናዊ የሆነ ወንጌል እንዲስተማር ፈቀደ፡፡
እዚህ ላይ ‹‹ፍልስፍናዊ ወንጌል›› በእግዚአብሄርና በሰው መካከል ያለውን ግንኙነት ለመመለስ ብቻ ሳይሆን በሰዎች መካከል ባለው ግንኙነትም ሰላምን ለማምጣት የሚሻ ከሰውኛ እሳቤዎች የመነጨ የሐሰት ወንጌል ነው፡፡
የኤፌሶን ቤተክርስቲያን አገልጋይ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ያጣው በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ ተቀባይነት የሌለውን ማለትም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማያምኑትን ሰዎች ለመቀበልና ትምህርቶቹንም ከእነርሱ አስተሳሰብ ጋር ለማስማማት በመሞከሩ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ልትተከል የምትችለው በውሃውና በመንፈሱ የወንጌል ቃል መሰረት ላይ ብቻ ነው፡፡
ሆኖም በዚህ ዘመንም ልክ እንደ ጥንቷ ቤተክርስቲያን ክፍለ ዘመን ለመዳን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በኢየሱስ ማመን በቂ ነው ብለው የሚያስቡና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ለምን ማመን እንደሚገባቸው የማያዩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር የተሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ቸል ብሎ በኢየሱስ ማመን በአያሌው የተሳሳተ እምነት ነው፡፡ ጌታን ሃይማኖታዊ ምግባር ብቻ አድርገው በከፊል ልብ በመንገታገት የሚያምኑ ሰዎች የእግዚአብሄር ጠላት ይሆናሉ፡፡ ጌታ የኤፌሶንን ቤተክርስቲያን አገልጋይ ከተሳሳተ እምነቱ ንስሐ እንዲገባና ለመጀመሪያ ጊዜ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በሰማ ጊዜ ወደነበረው የቀድሞ እውነተኛና ቀና እምነት፤ ወደ መጀመሪያው እምነት እንዲመለስ የነገረው ለዚህ ነው፡፡
እዚህ ላይ ለእኛ የሚሆን ጠቃሚ ትምህርት አለ፡፡ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ካላት እምነቷ ከወደቀች እግዚአብሄር ዳግመኛ የእርሱ ቤተክርስቲያን ብሎ አይጠራትም፡፡ ጌታ መቅረዙን ከስፍራው እንደሚወስድና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ለሚያምኑ ምዕመናኖች እንደሚሰጥ የተናገረው ለዚህ ነው፡፡
የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የተወችና የማትሰብክ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን አይደለችም፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማመን መከላከልና መስበክ ከማናቸውም ሌሎች ምግባሮች ይልቅ ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ መረዳታችን ፈጽሞ ወሳኝ ነው፡፡
ከላይ በተጠቀሰው ምንባብ ላይ ሰባቱ ቤተክርስቲያናት የሚገኙባት ትንሽዋ እስያ አሁን የሙስሊም ክልል ናት፡፡ ስለዚህ ጌታ መቅረዙን ማለትም የእግዚአብሄርን ቤተክርስቲያን ወስዶዋል፡፡ እኛንም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመላው ዓለም እንድንሰብክ አድርጎናል፡፡ በእውነተኛዋ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ ግን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል አለ፡፡ ያለዚህ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ልትኖር አትችልም፡፡ አስራ ሁለቱ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሐዋርያት ዘመን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ተለዋዋጭ ያልሆነ እምነት ነበራቸው፡፡ (1ኛ ጴጥሮስ 3፡21፤ሮሜ ምዕራፍ 6፤ 1ኛ ዮሐንስ ምዕራፍ 5)
ነገር ግን በጣም የሚያሳዝነው ነገር በትንሽዋ እስያ የነበሩት የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያናት ከጥንቷ ቤተክርስቲያን ዘመን ጀምሮ እውነተኛውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ማጣታቸውና ከዚህ የተነሳም ይህ ክልል ሙስሊም መሆኑ ነው፡፡ ከዚህም በላይ የሮሜ ቤተክርስቲያንም እንኳን በሮማዊው ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ በተደነገገው የሚላን ድንጋጌ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማጣትዋ መርዶ መመታትዋ ነው፡፡
 
ቁጥር 6፡- ‹‹ነገር ግን ይህ አለህ፤ እኔ ደግሞ የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ ጠልተሃልና፡፡››
ኒቆላውያን ዓለማዊና ቁሳዊ ትርፎችን ለማግኘት ሲሉ የኢየሱስን ስም የተጠቀሙ ሰዎች ነበሩ፡፡ የኤፌሶን ቤተክርስቲያን ግን የኒቆላውያንን ትምህርቶችና ምግባሮች ጠላች፡፡ ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን ከእግዚአብሄር ዘንድ በአያሌው ያስመሰገናት አንድ ነገር ነበር፡፡
 
ቁጥር 7፡- ‹‹መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡ ድል ለነሣው በእግዚአብሄር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ፡፡››
የእግዚአብሄር አገልጋዮችና ቅዱሳን መንፈስ ቅዱስ የሚላቸውን መስማት አለባቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሚነግራቸው ነገር እምነታቸውን እንዲከላከሉና የውሃውንና የመንፈሱንም ወንጌል እስከ መጨረሻው እንዲያሰራጩ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ውሸትን የሚያሰራጩ ሰዎችን መታገልና ማሸነፍ አለባቸው፡፡
ውሸትን በመዋጋት መሸነፍ ማለት ጥፋት ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ምዕመናኖችና አገልጋዮች ጠላቶቻቸውን በመሳሪያዎቻቸው ማለትም በእግዚአብሄር ቃልና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማሸነፍና ድል ማድረግ ይገባቸዋል፡፡
እግዚአብሄር እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹ድል ለነሣው በእግዚአብሄር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ፡፡›› እግዚአብሄር የሕይወት ዛፍን ፍሬ የሚሰጠው ‹‹ድል ለነሳው›› ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ምንን ወይም ማንን ድል መንሳት? በእምነታችን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማያምኑትን ሰዎች ድል መንሳት አለብን፡፡ ምዕመናን ከዋሾዎች ጋር በማያቋርጥ መንፈሳዊ ተጋድሎዎች ውስጥ መሳተፍና በእምነታቸውም ከእነዚህ ተጋድሎዎች ውስጥ ድል አድራጊ ሆነው መውጣት አለባቸው፡፡ እግዚአብሄር በሰጠው በአዲሲቱ ሰማይና ምድር ላይ መኖር የሚችሉት በእውነት ላይ ባላቸው እምነት በትግላቸው ጠላቶቻቸውን ያሸነፉ ብቻ ናቸው፡፡
በጥንቷ ቤተክርስቲያን ዘመን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመንና እርሱንም መከላከል የፈለጉ ሰዎች ሰማዕትነትን መጋፈጥ ነበረባቸው፡፡ ልክ እንደዚሁ ጸረ ክርስቶስ ብቅ የሚልበት ዘመን ሲመጣም ብዙ ሰማዕታቶች ይኖራሉ፡፡