Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[8-1] ሰባቱን መለከቶች የሚያውጁት መለከቶች፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 8፡1-13 ››

ሰባቱን መለከቶች የሚያውጁት መለከቶች፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 8፡1-13 ››
‹‹ሰባተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ እኩል ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ፡፡ በእግዚአብሄርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላዕክት አየሁ፡፡ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው፡፡ ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰውያው አጠገብ ቆመ፡፡ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰውያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው፡፡ የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሄር ፊት ወጣ፡፡ መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰውያውን እሳት ሞላበት፡፡ ወደ ምድርም ጣለው፡፡ ነጎድጓድና ድምጽም፣ መብረቅም፣ መናወጥም ሆነ፡፡ ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ሊነፉ ተዘጋጁ፡፡ ፊተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፡፡ ወደ ምድርም ተጣለ፡፡ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ፡፡ የዛፎችም ሲሶ ተቃጠለ፡፡ የለመለመም ሳር ሁሉ ተቃጠለ፡፡ ሁለተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባህር ተጣለ፡፡ የባህርም ሲሶው ደም ሆነ፡፡ በባህርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ፡፡ የመርከቦችም ሲሶው ጠፋ፡፡ ሦስተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፡፡ በወንዞችና በውሃ ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ፡፡ የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል፡፡ የውሃውም ሲሶ መራራ ሆነ፡፡ መራራም ስለተደረገ በውሃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ፡፡ አራተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ የጸሐይ ሲሶና የጨረቃም ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፡፡ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ የቀንም ሲሶ እንዳያበራ እንዲሁም የሌሊት፡፡ አየሁም አንድ ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምጽ፡- ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላዕክት መለከት ስለሚቀረው ድምጽ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው፣ ወዮላቸው፣ ወዮላቸው ሲል ሰማሁ፡፡›› 
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
ራዕይ 8 እግዚአብሄር በዚህች ምድር ላይ የሚያመጣቸውን መቅሰፍቶች መዝግቦዋል፡፡ እዚህ ላይ እጅግ ወሳኝ ከሆኑ ጥያቄዎች አንዱ ቅዱሳኖች በእነዚህ መቅሰፍቶች ከሚሰቃዩት መካከል መሆን ወይም አለመሆናቸው ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳኖችም እንደዚሁ በሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ውስጥ እንደሚያልፉ ይነግረናል፡፡ ሰባቱን መቅሰፍቶች በሚመለከትም ከመጨረሻው መቅሰፍት በቀር በሁሉም መቅሰፍቶች ውስጥ ያልፋሉ፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተገለጡት እነዚህ የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች እግዚአብሄር በዚህች ምድር ላይ በገሃድ የሚያመጣቸው መቅሰፍቶች ናቸው፡፡ እግዚአብሄር መላዕክቶቹ ሰባቱን መለከቶች በመንፋት ሲጀምሩ ዓለምን በመቅሰፍቶች እንደሚቀጣ ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 1፡- ሰባተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ እኩል ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ፡፡
ይህ የእግዚአብሄር ቁጣ በሰው ዘር ላይ ከመውረዱ ጥቂት ቀደም ብሎ ያለውን ጸጥታ ያመላክታል፡፡ እግዚአብሄር አስፈሪዎቹን መቅሰፍቶቹን በምድር ላይ ከማምጣቱ በፊት ለጥቂት ጊዜ ዝም ይላል፡፡ ይህም የእርሱ የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ምን ያህል አስከፊና አሰቃቂ እንደሆኑ ያሳየናል፡፡ የሰው ዘር በእነዚህ መቅሰፍቶች ውስጥ ካለፈ በኋላ በእግዚአብሄር ፊት ሲቆም የዳኑት የዘላለም ሕይወት ይቀበላሉ፡፡ ስለዚህ ይህ ዘመን ምን ዓይነት ዘመን እንደሆነ በመረዳት መንቃትና የወንጌላውያኖችን ሥራ መስራት አለብን፡፡
 
ቁጥር 2፡- በእግዚአብሄርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላዕክት አየሁ፡፡ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው፡፡
እግዚአብሄር ሥራዎቹን በመስራት ሰባቱን መላዕክቶች ተጠቀመ፡፡ ነገር ግን በዚህ ዘመን እግዚአብሄር በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ቃል በሚያምኑ ጻድቃን በኩል እንደሚሰራ መርሳት የለብንም፡፡
 
ቁጥር 3፡- ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰውያው አጠገብ ቆመ፡፡ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰውያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው፡፡
ይህም እግዚአብሄር በሰይጣንና በተከታዮቹ በደረሰባቸው ስደትና መከራዎች መካከል ቅዱሳን ያቀረቡትን ጸሎት ከሰማ በኋላ መቅሰፍቶቹን ሁሉ በምድር ላይ እንደሚያወርድ ያሳየናል፡፡ እዚህ ላይ ‹‹የወርቁ ጥና›› የሚያመለክተው የቅዱሳኖችን ሁሉ ጸሎቶች ነው፡፡ ይህም ማለት የእነርሱ ጸሎቶች ወደ እግዚአብሄር ሲቀርቡ የእርሱን ሥራዎች በሙሉ ይፈጽማሉ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር የቅዱሳን ጸሎቶች በመስማት ይሰራል፡፡
 
ቁጥር 4፡- የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሄር ፊት ወጣ፡፡
ይህም ጸረ ክርስቶስ በዚህች ምድር ላይ ምን ያህል ቅዱሳኖችን እንዳሰቃየ ያሳያል፡፡ በዘመኑ መጨረሻ ከሚመጡት መከራዎች የተነሳ ቅዱሳን ጸረ ክርስቶስን እንዲያሸሽላቸው፣ ፈጥነውም መከራዎቻቸውን እንዲያልፉ የእግዚአብሄር ቁጣ ምን ያህል እንደከፋባቸው ግድያዎቻቸውን ለማሳየት ሲሉ ወደ እግዚአብሄር ይጸልያሉ፡፡ ይህ ጥቅስ እግዚአብሄር የቅዱሳንን ጸሎቶች በሙሉ እንደሚቀበል ያሳያል፡፡ እግዚአብሄር እነዚህን የቅዱሳን ጸሎቶች ከተቀበለ በኋላ የሰባቱን መለከቶች መቅሰፍቶችና ሰባቱን ጽዋዎች በማውረድ በጸረ ክርስቶስና በተከታዮቹ ላይ የሚያወርደው ፍርድ ለቅዱሳን ጸሎቶች የሚሰጠው የመጨረሻ መልሱ ነው፡፡
 
ቁጥር 5-6፡- መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰውያውን እሳት ሞላበት፡፡ ወደ ምድርም ጣለው፡፡ ነጎድጓድና ድምጽም፣ መብረቅም፣ መናወጥም ሆነ፡፡ ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ሊነፉ ተዘጋጁ፡፡
እግዚአብሄር በዚህች ምድር ላይ የሚወርዱትን የሰባቱን መለከቶች መቅሰፍቶች እያዘጋጀ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ዓለም ከድምጽ፣ ከነጎድጓድ፣ ከመብረቅና ከመሬት መናወጦች አያመልጥም፡፡
 
ቁጥር 7፡- ፊተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፡፡ ወደ ምድርም ተጣለ፡፡ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ፡፡ የዛፎችም ሲሶ ተቃጠለ፡፡ የለመለመም ሳር ሁሉ ተቃጠለ፡፡
የመጀመሪያው መቅሰፍት የምድር ሲሶ፣ የዛፎች ሲሶና ሳር ሁሉ የሚቃጠልበት ነው፡፡ ይህ መቅሰፍት በዚህ ዓለም ላይ ባሉ ደኖች ላይ ይወርዳል፡፡
እግዚአብሄር የዚህ ዓይነት መቅሰፍት የሚያመጣው ለምንድነው? ምክንያቱም ሰዎች የእግዚአብሄርን ፍጥረት ውበት በዓይኖቻቸው ቢያዩም ‹‹በፈጣሪ ፋንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ›› (ሮሜ 1፡25) እግዚአብሄርን ፈጣሪ አድርገው ስላላወቁትና ስላላመለኩት ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ለአምላክ ክብርን ከመስጠት ይልቅ እርሱን በሚቃወሙት ላይ የሰባቱን መለከቶች መቅሰፍቶች ያመጣባቸዋል፡፡
 
ቁጥር 8-9፡- ሁለተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባህር ተጣለ፡፡ የባህርም ሲሶው ደም ሆነ፡፡ በባህርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ፡፡ የመርከቦችም ሲሶው ጠፋ፡፡
የሁለተኛው መለከት መቅሰፍት የሚወድቅ ኮከብ ምድርን መምታቱ ነው፡፡ ይህ አስትሮይድ በባህር ላይ ይወድቅና የባህርን ሲሶ ወደ ደም በመቀየር በባህር ውስጥ ያሉትን ሕያዋን ፍጥረታት ሲሶ በመግደል የመርከቦችን ሲሶም ያጠፋል፡፡ የሰው ዘር እግዚአብሄር በፈጠረው ፍጥረት አማካይነት ብዙ በረከቶችን ተቀብሎዋል፡፡ እነርሱ ግን ለተፈጥሮ በረከቶች እግዚአብሄርን በማመስገን ፋንታ ዕብሪተኞች ሆነው በእግዚአብሄር ላይ ተነሱ፡፡ ሁለተኛው መቅሰፍት ለዚህ ሐጢያት ይቀጣቸዋል፡፡
 
ቁጥር 10፡- ሦስተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፡፡ በወንዞችና በውሃ ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ፡፡
እግዚአብሄር አስትሮይድ ‹‹በወንዞችና በውሃ ምንጮች ሲሶ ላይ›› እንዲወርድ የፈቀደው ለምንድነው? ምክንያቱም የሰው ዘር ሕይወት ባለቤት በሆነው በጌታ የሚኖር ቢሆንም እርሱን ከማምለክና ከማመስገን ይልቅ ይህንን የሕይወት ጌታ ስላጥላሉት ነው፡፡
 
ቁጥር 11፡- የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል፡፡ የውሃውም ሲሶ መራራ ሆነ፡፡ መራራም ስለተደረገ በውሃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ፡፡
በዚህ መቅሰፍት የወንዞችና የውሃ ምንጮች ሲሶ ወደ እሬትነት ይለወጣሉ፡፡ ይህንን ውሃ የሚጠጡ ብዙዎችም ይሞታሉ፡፡ ይህ እግዚአብሄርን በተቃወሙና የቅዱሳኖችን ልብ ባሰቃዩ ሐጢያተኞች ላይ የሚወርድ የቅጣት መቅሰፍት ነው፡፡ እግዚአብሄር ሐጢያተኞች በጻድቃን ላይ ለፈጸሙዋቸው ምግባሮቻቸው ሁሉ ከመበቀል ፈጽሞ አይታክትም፡፡ ሐጢያተኞች ጻድቃኖችን ሲያሰቃዩ እግዚአብሄር ይፈርድባቸዋል፡፡ ሦስተኛው መቅሰፍት እንደገና በተፈጥሮ ላይ የተቃጣ ሌላ መቅሰፍት ነው፡፡ የወረደውም ሰዎች እግዚአብሄር የሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ባለማመናቸው የዓመጻ ሐጢያት ስለሰሩ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‹‹እሬት›› ሁልጊዜም የሚያመለክተው እግዚአብሄርን በማይታዘዙና በሚቃወሙ ላይ የሚወርደውን ፍርድ ነው፡፡
 
ቁጥር 12፡- አራተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ የጸሐይ ሲሶና የጨረቃም ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፡፡ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ የቀንም ሲሶ እንዳያበራ እንዲሁም የሌሊት፡፡
አራተኛው መቅሰፍት የጸሐይ፣ የጨረቃና የከዋክብት ሲሶ መጨለም ነው፡፡ የሰው ዘር ይህንን ያህል ጊዜ ሁሉ ሰይጣንን ሲከተልና ጨለማን ሲወድ ነበር፡፡ በዚህም በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ያበራውን የደህንነት ብርሃን ጠሉት፡፡ በዚህም የጨለማው ዓለም በእርግጥ ምን ያህል አስፈሪና የተረገመ እንደሆነ ሊያስተምራቸው እግዚአብሄር ይህንን የጨለማ መቅሰፍት ያመጣባቸዋል፡፡ መቅሰፍቱ ኢየሱስ ክርስቶስን ጠልተው ጨለማን ለመውደዳቸው ሐጢያት የእግዚአብሄር ቁጣ ምን ያህል አስከፊ እንደሆነም የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ የጸሐይ፣ የጨረቃና የከዋክብቶች ሲሶ ብርሃናቸውን ያጡና ይጨልማሉ፡፡
 
ቁጥር 13፡- አየሁም አንድ ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምጽ፡- ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላዕክት መለከት ስለሚቀረው ድምጽ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው፣ ወዮላቸው፣ ወዮላቸው ሲል ሰማሁ፡፡››
ይህ ቁጥር ገናም በዚህች ምድር ላይ የሚመጡ ሦስት ተጨማሪ ወዮታዎች እንዳሉ ይነግረናል፡፡ ስለዚህ ሐጢያተኞች ሁሉና እግዚአብሄርን የሚቃወሙ ሁሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን በተቻለ ፍጥነት ከሐጢያቶቻቸው መዳን ይኖርባቸዋል፡፡