Search

በክርስቲያን እምነት ላይ አዘውትረው የሚጠየቁ ጥያቄዎች፤

ርዕስ 1፡ ከውሃና ከመንፈስ ዳግመኛ መወለድ፤

1-30. ‹‹የውሃና የመንፈስ›› ግንዛቤህ ትክክል ከሆነ በመስቀል ላይ የተሰቀለው ሌባ ደህንነትን አያገኝም ነበር፡፡ በመስቀል ላይ የተሰቀለው ሌባ በልዩ ሁኔታ የሚታይ ከሆነ እግዚአብሄር ቅን አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ወደ መንግሥቱ ለመግባት ራሱ ያወጣውን ሕግ ጥሶዋልና፡፡ በመስቀል ላይ የተሰቀለው ሌባ ያገኘውን ደህንነት እንዴት ልታብራራው ትችላለህ? 

በዚያ ዘመን አይሁዶች በሙሉ ትንቢት የተነገረለትን መሲህ ይጠብቁ ነበር፡፡ ስለዚህ እነርሱ ማንኛውም ሌላ ሕዝብ ይበልጥ እግዚአብሄር በሙሴ አማካይነት ስለሰጠው ‹‹ሕግና የመስዋዕት ስርዓት›› በሚገባ ያውቁ ነበር፡፡ እነርሱ መሲህ በእግዚአብሄር የማስተሰርያ ሕግ መሰረት እንደሚመጣና ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ እንደሚያላቅቃቸው አምነዋል፡፡ 
ነገር ግን በአጥማቂው ዮሐንስ የሆነው የኢየሱስ ጥምቀት ከእግዚአብሄር እንደነበርና የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በኢየሱስ ላይ የሚያኖር እንደነበር (ማርቆስ 11፡27-33) አላመኑም፡፡ በፋንታው እርሱን የተመለከቱት ሕዝቡን የሚያስት ሰው አድርገው ስለነበር ሰቀሉት፡፡ 
ሮማውያን በሮም ሕግ መሰረት ከመገረፍ ወይም ከመሰቀል ከለላ ስለነበራቸው (የሐዋርያት ሥራ 2፡25-29፤23፡27) በመስቀል ላይ የተሰቀሉት ወንበዴዎች አይሁዶች እንጂ ሮማውያኖች እንዳልነበሩ እናውቃለን፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ›› (ሉቃስ 23፡42) ከሚሉት ቃሎች የተነሳም ሌባው እግዚአብሄርን የፈራ አይሁድ እንደነበርም እናውቃለን፡፡ አይሁዳዊው ሌባ እግዚአብሄር ለሙሴ የሰጠውን ሕግና የመስዋዕት ስርዓት ቀድሞውኑም የሚያውቅ ነበር፡፡ ስለዚህ መሲሁ በእግዚአብሄር የስርየት ሕግ መሰረት እንደሚመጣ አምኖዋል፡፡ 
ወደ እግዚአብሄር የሚቀርቡ ሰዎች በሐጢያቶቻቸው ምክንያት ሲዖል ለመውረድ የታጩ ሐጢያተኞች እንደሆኑ መናዘዝ አለባቸው፡፡ ሌባው ‹‹ስላደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና ለእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው›› (ሉቃስ 23፡41) በማለት ሐጢያቶቹን ተናዘዘ፡፡ ሌባው እግዚአብሄርን እንደፈራና ተስፋውም መንግሥተ ሰማይ መግባት እንደሆነ ‹‹ጌታ ሆይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ›› (ሉቃስ 23፡42) ከሚሉት ቃሎች እናውቃለን፡፡ 
እርሱም እንዲህ አለ፡- ‹‹ይህ ሰው ምንም ስህተት አልሰራም፡፡›› (ሉቃስ 23፡41) ሌባው ኢየሱስ ስላደረገው ነገር እንዴት አወቀ? ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ እንደተጸነሰ፣ ከድንግል ማርያም እንደተወለደ፣ የሰው ዘር ሁሉ ወኪል በሆነው በአጥማቂው ዮሐንስ እንደተጠመቀ፣ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንደወሰደና እንደተሰቀለ አምኖዋል፡፡ በምድር ላይ ለሰራቸው ምግባሮች ዋጋውን ለመክፈል ቢሰቀልም ኢየሱስ እርሱን ጨምሮ ለሕዝቡ ሁሉ ያደረገውን ያመነ አይሁድ ነበር፡፡ 
በዮሐንስ ጥምቀት አማካይነት ሐጢያቶቻቸውን የተናዘዙ ሰዎች ሐጢያቶቻቸው በእርሱ ጥምቀት አማካይነት ወደ ኢየሱስ እንደተላለፉ ሲሰሙ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ተቀብለዋል፡ ነገር ግን የዮሐንስን የንስሐ ጥምቀት ያልተቀበሉ ሰዎች የእግዚአብሄርን ፈቃድ ንቀዋል፡፡ ምክንያቱም በኢየሱስ ጥምቀት አላመኑምና፡፡ (ሉቃስ 7፡28-30) 
በተቃራኒው የዳነው ሌባ ኢየሱስ ያደረገው ነገር ሁሉ ትክክልና ጻድቅ እንደነበር ሲናዘዝ ሌላው አይሁዳዊ ሌባ ግን ያንን አላደረገም፡፡ እርሱ በመካከላቸው የተፈጸሙትን እነዚያን ነገሮች በሙሉ ከሰሙ አይሁዶች አንዱ ይሆናል፡፡ (ሉቃስ 1፡1) በመጨረሻም ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት የእርሱን ሐጢያቶች በሙሉ እንደወሰደ ወደ ማመን ስለመጣ ኢየሱስ ጻድቅና ትንቢት የተነገረለት መሲህ እንደነበር መናገር ቻለ፡፡ በዚህም ዳነ፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማመንም ድኖዋል፡፡ እግዚአብሄር ጻድቅ ስለሆነ በሕይወት መንፈስ ሕግ መሰረት በኢየሱስ ጥምቀትና መስቀል የሚያምኑትን ያጸድቃል፡፡