Search

በክርስቲያን እምነት ላይ አዘውትረው የሚጠየቁ ጥያቄዎች፤

ርዕስ 2፡ መንፈስ ቅዱስ፤

2-2. እርሱ ወይም እርስዋ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ቢያምኑ መንፈስ ቅዱስ ሁሌም ዳግም በተወለደው ግለሰብ ውስጥ ይኖራል ወይስ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ዙሪያ እያንዣበበ እርዳታን በሚጠይቁበት ጊዜ ሁ ወደ እነርሱ ይገባል? 

መንፈስ ቅዱስ ረዳት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ክርስቶስ በአጥማቂው ዮሐንስ ከተጠመቀ በመስቀል ላይ ከሞተና ከተነሳ ጊዜ ጀምሮ (ዮሐንስ 15፡26) ከውሃና ከመንፈስ ዳግም ለተወለዱ ጻድቃን ሁሉ በእግዚአብሄር የተሰጠ የእውነት መንፈስ ነው፡፡ ኤፌሶን 1፡13 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ሰምታችሁ ደግሞም በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፡፡›› 
ጌታ በዮሐንስ 14፡6 ላይ እንዲህ አለ፡- ‹‹እኔም አብን እለምናለሁ፤ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፡፡›› የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ በጥምቀቱ አማከይነት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንደወሰደ በማመን ለሐጢያታቸው ሁሉ ይቅርታን ተቀበሉ፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ‹‹እነሆ የዓለምን ሐጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ›› (ዮሐንስ 1፡29) ያለው ለዚህ ነበር፡፡ 
‹‹የዓለም ሐጢያቶች›› ማለት የዚህ ዓለም ሰዎች በሙሉ ከአለም መጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ሲሰሩዋቸው የነበሩት ሐጢያቶች በሙሉ ናቸው፡፡ እርሱ በአንድ ጊዜ የአለምን ሐጢያቶች ተቀበለ፤ በመስቀል ላይ ሞተ፤ ተነሳ፤ በዚህም ለዘላለም ጻድቃን አደረገን፡፡ በዕብራውያን 10፡12-14 እንዲህ ተጽፎዋል፡- ‹‹እርሱ ግን ስለ ሐጢአት አንድን መስዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሄር ቀኝ ተቀመጠ፤ ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪደረጉ ድረስ ወደፊት ይጠብቃል፡፡ አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን ለዘላለም ፍጹማን አደረጋቸው፡፡›› 
ጌታ በዮሐንስ ተጠመቀ፤ ተሰቀለ፤ ከዚያም ተነሳ፡፡ በዚህም ለዘላለም ጻድቃን አደረገን፡፡ እኛ በኢየሱስ አማካይነት በአንድ ጊዜ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ይቅርታን አገኘንና የእግዚአብሄር ልጆች ሆንን፡፡ ይህ እውነት ለዘላለም የማይሻር ነው፡፡ በእምነት አማካይነት ጻድቃን የሆኑ ሰዎች በልቦቻቸው ውስጥ ሐጢያት የለባቸውም፡፡ ሰዎች በድክመቶቻቸው ምክንያት ሐጢያት ቢሰሩም ኢየሱስ ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ ስለወሰደ ለዘላለም ሐጢያት የለባቸውም፡፡ ስለዚህ እንደገና በጭራሽ ሐጢያተኞች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ 
መንፈስ ቅዱስ በተቀደሱት ጻድቃን ልቦች ውስጥ ለዘላለም ይኖራል፡፡ እኛ በጉድለቶቻችን ምክንያት ሐጢያት እንሰራለን፡፡ ነገር ግን ሐጢያት በምንሰራበት ጊዜ ሁሉ ሐጢያተኞች ሆነን ቢሆን ኖሮ እኛን ለዘላለም ጻድቃን ያደረገን የኢየሱስ ክርስቶስ ስጦታ ይባክን ነበር፡፡ እርሱም ሐጢያቶቻችንን ከተቀበለ በኋላ እንደገና በሞተልን ነበር፡፡ ይህ መንፈስ ቅዱስን የመሳደብ ሐጢያት ነው፡፡ (ዕብራውያን 6፡4-8፤10፡26-29) 
መንፈስ ቅዱስ የሚያድረው የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ በተቀበሉትና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማመን ዳግም በተወለዱት ጻድቃን ውስጥ ነው፡፡ ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹እንዲሁም እግዚአብሄር ተናገረ እንዲህ ሲል፡- በእነርሱ እኖራለሁ፤ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ፡፡›› (2ኛ ቆሮንቶስ 6፡16)
መንፈስ ቅዱስ ሁሌም የሚያድረው ለዘላለም በተቀደሱት የእግዚአብሄር ልጆች ውስጥ ነው፡፡ እዚህ ላይ ‹‹ማደር›› የሚለው ቃል በዙሪያን ያንዣብብና በምንጸልይና እርሱን በምንጠራው ጊዜ ሁሉ ወደ እኛ ይመጣል ማለት ሳይሆን በፋንታው ‹‹ሁሌም በእኛ ውስጥ ይኖራል›› ማለት ነው፡፡ እርሱ ሁሌም ከውሃና ከመንፈስ ዳግም በተወለዱ ሰዎች ውስጥ ይኖርና ሁሉንም ነገር ያስተምራቸዋል፤ የእግዚአብሄርንም ቃሎች እንዲያውቁ ይመራቸዋል፡፡ (ዮሐንስ 14፡26) 
ስለዚህ የእግዚአብሄር መንፈስ ቅዱስ የሌለው ማንኛውም ሰው የእርሱ አይደለም፡፡ (ሮሜ 8፡9) መንፈስ ቅዱስ በነጹትና ሐጢያት አልባ በሆኑት ውስጥ ያድርና ሰማያዊ ነገሮችን ሁሉ ያስተምራቸዋል፤ የእግዚአብሄር ልጆች መሆናቸውንም ይመሰክራል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለጥረቶቻችን ዋጋ ይሆን ዘንድ ወደ እኛ በመምጣት የሚቀርበን መሆኑ እውነት አይደለም፡፡ በፋንታው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ዳግም በተወለዱ የእግዚአብሄር ልጆች ውስጥ ሁሌም ያድራል፡፡ 
ሆኖም ብዙ ሰዎች ይህ እውቀት ስለሚጎድላቸው በሐጢያት በተሞሉት ልቦቻቸው ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ለመቀበል ይሞክራሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ ግለት በተሞላባቸው የንስሐ ጸሎቶች ውስጥ ጥረትን ሲያኖሩ በእነርሱ ላይ እንደሚመጣ ሐጢያት ሲሰሩም እንደሚሄድ ያስባሉ፡፡ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ያልተቀበሉ ሰዎች እምነት ይህ ነው፡፡ እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ በሐጢያቶች ይቅርታ አማካይነት እንደ ስጦታ እንደሚቀበሉ ያምናሉ፡፡ ሰው የራሱን አስተሳሰቦች መተውና በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ወደሚገኘው እምነት መመለስ ይገባዋል፡፡