Search

በክርስቲያን እምነት ላይ አዘውትረው የሚጠየቁ ጥያቄዎች፤

ርዕስ 3፡ ዮሐንስ ራዕይ፤

3-6. የአዲሲቷ ኢየሩሳሌም ከተማ ምንድነች?  

የአዲሲቷ ኢየሩሳሌም ከተማ እግዚአብሄር የመጀመሪያውን ትንሳኤ ለሚያገኙት ቅዱሳን ባዘጋጀው አዲስ ሰማይና ምድር ውስጥ ያለች ቅድስት ከተማ ናት፡፡ እግዚአብሄር የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች በዚህ ምድር ላይ ካጠናቀቀ በኋላ ሰይጣንን በጥልቁ ጉድጓድ ውስጥ ለሺህ ዓመት ያስረዋል፡፡ የመጀመሪያውን ትንሳኤ ላገኙት ቅዱሳንም በሺህው ዓመት መንግሥት ውስጥ ከጌታ ጋር የሚነግሱበትን በረከት ይለግሳቸዋል፡፡ ሺህ ዓመቱ ከተጠናቀቀ በኋላም የመጀመሪያው ምድርና ሰማይ እንዲጠፉ ይደረግና ለቅዱሳን የአዲስ ሰማይና ምድር ስጦታን ይሰጣቸዋል፡፡ 
እነዚህን በረከቶች የሚቀበሉት ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠው የውሃውና የመንፈሱ ቅዱስ ወንጌል በማመን የሐጢያቶቻቸውን ሰርየት ያገኙ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ጌታም የቅዱሳን ሙሽራ ይሆናል፡፡ ቅዱሳኖችም ሙሽራቸው የሆነው የበጉ ሙሽሪቶች በመሆን በእርሱ የክብር መንግሥት ውስጥ የሙሽራውን ጥበቃ፣ በረከትና ሐይል ለብሰው በክብር ይኖራሉ፡፡ 
እግዚአብሄር ለእነዚህ ቅዱሳን አዲሲቷን ከተማ በአዲሱ ሰማይና ምድር ላይ ያዘጋጃል፡፡ ይህች ከተማ ሌላ ሳትሆን አዲሲቷ የኢየሩሳሌም ከተማ ናት፡፡ ይህም የተዘጋጀው ለእግዚአብሄር ቅዱሳን ብቻ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ለቅዱሳን የተዘጋጀው ጌታ አምላክ ዩኒቨርስን ከመፍጠሩ በፊት ነው፡፡ አስገራሚ በሆነው የጌታ አምላክ ሐይል በሺህው ዓመት የክርስቶስ መንግሥት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቅድስቲቱ ከተማ ወደምትገኝበት አዲስ ሰማይና ምድር እንዲዛወሩ ብቁ ይሆናሉ፡፡ 
ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ ቅዱሳኖች በእግዚአብሄር መቅደስ ውስጥ ለዘላለም ከጌታ ጋር አብረው ይኖራሉ፡፡ እግዚአብሄር ከእነርሱ ጋር ስለሆነ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት፣ ሐዘን፣ ዋይታ፣ መከራ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያው ሰማይና የመጀመሪያው ምድር አልፈው እግዚአብሄር ሁሉን አዲስ ያደርጋልና፡፡ 
አዲሲቷ የኢየሩሳሌም ከተማ የእግዚአብሄር ክብር ስላለባት ብሩህ ሆና ታበራለች፡፡ ብርሃንዋም ልክ እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያስጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበር፡፡ ስለዚህ በእርስዋ ውስጥ ለሚኖሩ ሁሉ የእግዚአብሄር ክብር ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አብሮዋቸው ይሆናል፡፡ ከተማይቱ በእያንዳንዱ አቅጣጫ ሦስት ደጆች የያዘ አስራ ሁለት ደጆች ያሉት ታላቅና ረጅም ቅጥር ነበራት፡፡ ደጆቹም በአስራ ሁለት መላዕክቶች ይጠበቃሉ፡፡ በደጆቹም ላይ የአስራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸዋል፡፡ የከተማይቱ ቅጥር አስራ ሁለት መሰረቶች ያሉት ሲሆን በእነርሱም ላይ አስራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያቶች ስሞች ተጽፈውባቸዋል፡፡ 
ከተማይቱ እንደ አንድ ታላቅ አራት ማዕዘን ሆና ተሰርታለች፡፡ አንዱ ወገን 1,200 ምዕራፎች ማለትም ወደ 2,200 ኪ.ሜ (1,390 ማይሎች) ልኬት አለው፡፡ ቅጥርዋ 144 ክንድ በግምት 72 ሜትር ተለክቷል፡፡ ይህ ቅጥር የተሰራው በኢያስጲድ ነው፡፡ ከተማይቱም ልክ እንደ ንጹህ ብርሌ ንጹህ ወርቅ ነች፡፡ የቅጥሩ መሰረቶች በሁሉም ዓይነት የከበሩ ድንጋዮች ተሸልመዋል፡፡ የከተማይቱ አስራ ሁለቱ ደጆች ከዕንቁ የተሰሩ ነበሩ፡፡ 
ጌታ አምላክና በጉ በከተማይቱ ውስጥ ስላሉ ፀሐይ ወይም ጨረቃ ማብራት አያስፈልጋቸውም፡፡ የሕይወት ውሃ ወንዝም ከእግዚአብሄርና ከበጉ ዙፋን እየፈሰሰ መንግሥተ ሰማያትን ያረጥባል፡፡ ሁሉንም ነገሮች ያድሳል፡፡ በወንዙ በሁለቱም ወገን አስራ ሁለት ፍሬዎችን የሚያፈራና በየወሩም ፍሬዎቹን የሚሰጠው የሕይወት ዛፍ ተተክሎዋል፡፡ ቅጠሎቹም ለሕዝብ መፈወሻ ናቸው፡፡ ዳግመኛ እርግማኖች አይኖሩም፡፡ እዚያ የሚገኘው ዘላለማዊ ባርኮት ብቻ ነው፡፡