Search

በክርስቲያን እምነት ላይ አዘውትረው የሚጠየቁ ጥያቄዎች፤

ርዕስ 3፡ ዮሐንስ ራዕይ፤

3-9. ትክክለኛው የቱ ነው የቅድመ መከራ ንጥቀት ወይስ የድህረ መከራ ንጥቀት? በታላቁ መከራ ወቅት ቅዱሳን ገናም በዚህ ምድር ላይ ይኖራሉን? 

የክርስትናን ታሪክ ስንመለከት እሰከ ዛሬ ድረስ በርካታ ውሸታሞች እንደተነሱ ማየት እንችላለን፡፡ እነዚህ ዋሾዎች የራዕይን መጽሐፍ በመተርጎምና በራሳቸው ዘዴዎች የመነጠቅን ጊዜ በማስላት አንድን የተለየ ቀን የመነጠቅ ቀን አድርገው በመወሰን ጌታ እነርሱ በመረጡት በዚህ ቀን እንደሚመጣና ቅዱሳንም እንደሚነጠቁ ማስተማርን ያዘወትራሉ፡፡ 
ሆኖም እነዚህ ሁሉ አባባሎች አልተሳካላቸውም፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ጋር ተመሳሳይ የሆነው አንዱ ባህርይ ሁሉም የቅድመ መከራን ንጥቀት ጽንሰ አሳብ ማራመዳቸው ነው፡፡ እነዚህ ዋሾዎች ለተከታዮቻቸው ታላቁ መከራ ከመምጣቱ በፊት ሁሉም ስለሚነጠቁና ወደ አየር ስለሚወሰዱ ዓለማዊ ብልጥግናዎቻቸው ፈጽሞ ጥቅም እንደሌላቸው በመናገር ብዙ ሰዎችን አስተዋል፡፡ ሐብት ብልጥግናቸውንም ዘርፈዋል፡፡ 
ይህ ሰይጣን የዚህን ዓለም ሕዝብ በሙሉ ለማሳትና በእነዚህ ዋሾዎች አማካይነትም የራሱ ባርያዎች ለማድረግ የሚሞክርበት ብልጣ ብልጥ ማታለያ እንደሆነ መገንዘብ አለብን፡፡ 
ለቅዱሳን እጅግ አስፈላጊውና እነርሱም አብዝተው የሚጓጉለት ጥያቄ የቅዱሳን ንጥቀት የሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡ ዮሐንስ ራዕይ 10፡7 እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምጹም በሚሰማበት ዘመን ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሄር ምስጢር ይፈጸማል›› ሲል ምን ማለቱ ነው? ‹‹የእግዚአብሄር ምስጢር›› የሚያመለክተው የቅዱሳኖችን ንጥቀት ነው፡፡ 
ከእግዚአብሄር ሰባት መለከቶች መቅሰፍቶች ስድስተኛው ሲጠናቀቅ ጸረ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ተገልጦ ዓለምን ይገዛል፡፡ ሰው ሁሉ የአውሬውን ምልክት እንዲቀበል ይጠይቃል፡፡ በእርሱ ስደት የተነሳም ቅዱሳን ሰማዕት ይሆናሉ፡፡ ወዲያውም የሰባተኛው መለከት መነፋት ይከተላል፡፡ በዚህ ጊዜም እምነታቸውን የጠበቁት ሰማዕት የሆኑት ቅዱሳንና በሕይወት የተረፉት ቅዱሳን ይነሱና ይነጠቃሉ፡፡ 
ሰባተኛው ማህተም ሲነፋ እግዚአብሄር በዚህ ምድር ላይ መቅሰፍት አያወርድም፡፡ ይህ ጊዜ የቅዱሳኖች ንጥቀት የሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡ ንጥቀቱን ተከትሎ እግዚአብሄር ወዲያውኑ በዚህ ምድር ላይ የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች ለማውረድ ይንቀሳቀሰል፡፡ ስለዚህ የሰባቱ የእግዚአብሄር ጽዋዎች መቅሰፍቶች የሚወርዱበት ጊዜ ሲመጣ ቅዱሳን በዚህ ምድር ላይ አይገኙም፡፡ ነገር ግን ከጌታ ጋር በአየር ላይ ይሆናሉ፡፡ የቅዱሳን ንጥቀት የሚሆነው ሰባተኛው መልአክ የመጨረሻውን መለከት በሚነፋበት ጊዜ መሆኑን ሁላችንም መገንዘብ አለብን፡፡ 
ነገር ግን አሁንም እንኳን ብዙ ክርስቲያኖች በቅድመ መከራ ጽንሰ አሳብ ማመናቸውን ቀጥለዋል፡፡ እምነታቸው ለመጨዎቹ የተፈጥሮ ጥፋቶችና ለጸረ ክርስቶስ መገለጥ ስላልተዘጋጀ ከሰይጣንና ከጸረ ክርስቶስ ጋር በሚያደርጉት ውጊያ ተሸንፈው የእነርሱ አገልጋዮች በመሆን ከዓለም ጋር አብረው ይጠፋሉ፡፡ 
የታላቁ መከራ ሰባት ዓመታት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ተኩል ዓመታት ይህች ምድር በተፈጥሮ ጥፋቶች የምትመታበት የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ጊዜ ናቸው፡፡ የፀሐይ ሲሶና የከዋክብቶች ሲሶ ይጨልማሉ፡፡ የዚህ ምድር ጥብቅ ደኖች ሲሶ ይቃጠላሉ፡፡ የባህር ሲሶም ወደ ደም ይለወጥና ሲሶ ነፍሳቶችን ይገድላል፡፡ ጅራታም ኮከቦችም ከሰማይ ይወድቃሉ፡፡ የውሃውንም ሲሶ ወደ እሬትነት ይለውጡታል፡፡ በዚህ የተነሳም ብዙ ሰዎች በእነዚህ ሁሉ ይሞታሉ፡፡ በእነዚህ መቅሰፍቶችም ዓለም ውጥንቅጥ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል፡፡ ጦርነትም ያለማቋረጥ በየስፍራው ይቀሰቀሳል፡፡ 
ስለዚህ ጸረ ክርስቶስ ተነስቶ እንዲህ ባሉ ውጥንቅጥ ሁኔታዎች ውስጥ የተከሰቱትን እነዚህን ነገሮች በሙሉ ሲፈታ ብዙ ሰዎች ይከተሉታል፡፡ በዚህም በዚህ ምድር ላይ እጅግ አስፈሪ የሆኑትን መቅሰፍቶች ያመጣሉ፡፡ 
ስለዚህ ይህ ዓለም የመንግሥታቶችን የጋራ ፍላጎቶች የሚደግፍ በፖለቲካ የተቆራኘ ዓለም አቀፍ የአደረጃጀት ስርዓት ሲነሳ ያያል፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተባበረ መንግሥት ጸረ ክርስቶስ ሲገለጥ በሰይጣን እጅ ላይ ይወድቅና እገግዚአብሄርንና የእርሱን ቅዱሳን የሚቃወም መንግሥት ይሆናል፡፡ የዚህ ዓለም ዓቀፋዊ የተባበረ መንግሥት መሪ አህዛቦችን ሁሉ ይቆጣጠራል፤ ይገዛልም፡፡ በመጨረሻም ጸረ ክርስቶስ ሆኖ ይሰራል፡፡ በሰይጣን ሐይል የሚሰራ ሰው የእግዚአብሄር ጠላትና የዲያብሎስ አገልጋይ ነው፡፡ 
አሁን ጸረ ክርስቶስ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ እንዳያመልኩ ነገር ግን በምትኩ እርሱን እንደ አምላክ ቆጥረው እንዲሰግዱለት በማስገደድ እውነተኛ ማንነቱን ይገልጣል፡፡ ለዚህም በእነርሱ ፊት ብዙ ምልክቶችን ያደርጋል፡፡ በሰይጣን ሐይልም ብቻውን የዓለምን አስቸጋሪና ውጥንቅጥ የሆኑ ጉዳዮችን ይፈታል፡፡ እንዲህ በማድረግም የሰውን ሁሉ ልብ ይማርካል፡፡ 
በመጨረሻም የራሱን ምስል ጣዖት በማድረግ ሰዎች ምስሉን አምላክ አድርገው እንዲሰግዱለት ይጠይቃቸዋል፡፡ በዚህ የመከራ ዘመን ሰዎችን ሁሉ በእርሱ ቁጥጥር ሥር ለማድረግም ምልክቱን በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው እንዲቀበሉ ያስገድዳል፡፡ይህ ምልክት የሌላቸው እንዳይነግዱ ይከለክላል፡፡ ቁጥራቸው ምንም ያህል ይሁን ለእርሱ ለመስገድ አሻፈረኝ የሚሉትንም ይገድላቸዋል፡፡ ስለዚህ ስሙ በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ያልተጻፈ ሰው ሁሉ መጨረሻው ምልክቱን መቀበልና ለአውሬው መስገድ ይሆናል፡፡ 
ሆኖም ቅዱሳን ለጸረ ክርስቶስ አያጎበድዱም፡፡ ምልክቱንም አይቀበሉም፡፡ መንፈስ ቅዱስ በልባቸው ውስጥ ስለሚኖር የአምልኮዋቸው ማዕከል ሁሉን የሚገዛው አምላክና ጌታቸው እንጂ ማንም ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን ለሰይጣንና ለጸረ ክርስቶስ መስገድንና የእነርሱ ባሮች ለመሆን አሻፈረኝ ብለው ያሸንፉዋቸዋል፡፡              
ዮሐንስ ራዕይ 13፡10 እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ይማረክ ዘንድ ያለው ማንም ቢኖር ወደ ምርኮነት ይሄዳል፤ በሰይፍ የሚገደል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል፡፡ የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት በዚህ ነው፡፡›› ጸረ ክርስቶስ ተገልጦ ሰዎች ምልክቱን እንዲቀበሉ ሲያስገድድ የታላቁ መከራ የመጀመሪያ ሦስት ዓመታት ተኩል አልፈው ሁለተኛው የሦስት ዓመታት ተኩል ጊዜ ጀምሮዋል፡፡ ቅዱሳን በጸረ ክርስቶስ የሚሳደዱትና ሰማዕት የሚሆኑት በዚህ ጊዜ ነው፡፡ 
ነገር ግን ጸረ ክርስቶስ ሥልጣን እንዲይዝና ቅዱሳኖችን እንዲያሳድድ በእግዚአብሄር የተፈቀደለት በጣም ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታ ለቅዱሳኑ ሲል የመከራውን ዘመን ያሳጥረዋልና፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱሳን እምነታቸውን ለመጠበቅ ከጸረ ክርስቶስ ጋር በመዋጋትና በሰማዕትነታቸው እርሱን በማሸነፍ ለእግዚአብሄር ክብርን ይሰጣሉ፡፡ 
ዳግመኛ የተወለዱት ቅዱሳን በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ተኩል ታላቅ መከራ ውስጥ ካለፉ በኋላ ሁለተኛው የመከራ አጋማሽ እስከሚጀምርበት የሰማዕትነታቸው ጊዜ ድረስ በዚህ ምድር ላይ ይቆያሉ፡፡ ስለዚህ በእምነታቸው ሰይጣንንና ጸረ ክርስቶስን ተዋግተው ማሸነፍ አለባቸው፡፡ እግዚአብሄር ድል ለሚነሱት ሰማይን እንደሚሰጣቸው የራዕይ መጽሐፍ የሚነግረን ለዚህ ነው፡፡ በመሆኑም የታላቁ መከራ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ተኩል አልፈው ጸረ ክርስቶስ ሲገለጥ ቅዱሳን በጌታችን ጥበቃና ምሪት እምነታቸው በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ ማደግ ይኖርበታል፡፡ 
ስለዚህ ሰዎች የቅድመ መከራ ጽንሰ አሳብ ተብሎ ከሚጠራውና በክርስቲያን ማህበረሰቦች ውስጥ ከተሰራጨው ከዚህ የሠይጣን የሐሰት ትምህርት ነጻ መውጣትና አሁኑኑ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ሁሉም የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ተቀብለው ዳግመኛ መወለድና ከእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ጋር መቀላቀል አለባቸው፡፡ በታላቁ የመከራ ዘመን የመጀመሪያ ሦስት ዓመታት ተኩል በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በኩል እምነታቸው የሚዳብረው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እነርሱ አስከፊው የመከራ ዘመን ሲመጣም ጸረ ክርስቶስን ተዋግተው ሰማዕትነታቸውን መቀበል የሚያስችል እምነት የሚኖራቸው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡