በአራት ማዕዘን የተሰራው የመገናኛው ድንኳን አጥር ቁመቱ 100 ክንድ ነበር፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክንድ ከክርን እስከ ጣት ጫፍ የሚዘረጋ ሲሆን በዛሬው መለኪያ ወደ 45 ሳንቲ ሜትር (1.5 ጫማ) አካባቢ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የመገናኛው ድንኳን አደባባይ አጥር 100 ክንድ ነበር ማለት 45 ሜትር (150 ጫማ) ሲሆን ወርዱ 50 ክንድ ነበር ማለት ደግሞ በግምት 22.5 ሜትር (75 ጫማ) ይሆናል ማለት ነው፡፡
የመገናኛው ድንኳን በአደባባይና የእግዚአብሄር ቤት በሆነው በራሱ በመገናኛው ድንኳን የተከፈለ ነበር፡፡ በእግዚአብሄር ቤት ውስጥ ቤተመቅደስ ተብሎ የሚጠራ አንድ አነስተኛ መዋቅር ነበር፡፡ ቤተ መቅደሱ በአራት የተለያዩ ሽፋኖች ተሸፍኖ ነበር፡፡ በጥሩ ጥልፍ በተሰራ የበፍታ፣ የሰማያዊ፣ የሐምራዊና ቀይ ሽፋኖች ተሸፍኖ ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ በፍየል ቁርበቶች፣ በቀይ በተነከረ የጠቦት ቁርበቶችና በአቆስጣ ቁርበቶች ተሸፍኖ ነበር፡፡
በመገናኛው ድንኳን አደባባይ የምሥራቅ ወገን በሰማያዊ፣ በሐምራዊ፣ በቀይ ግምጃና በጥሩ በፍታ የተሸፈነው የመግቢያ በር አለ፡፡ አንድ ሰው ይህንን በር አልፎ ሲገባ የሚቃጠል መስዋዕት የሚቀርብበትን መሰውያና የመታጠቢያውን ሰን ያያል፡፡ የመታጠቢያውን ሰን ስናልፍ ራሱን የመገናኛውን ድንኳን እናያለን፡፡ የመገናኛው ድንኳን በቅድስትና የእግዚአብሄር የምስክር ታቦት በሚገኝበት በቅድስተ ቅዱሳን ተከፍሎዋል፡፡ የመገናኛው ድንኳን አደባባይ አጥር ከነጭ በፍታ የተሰሩ መጋረጃዎች የተንጠለጠሉባቸው 60 ምሰሶዎች ነበሩት፡፡ በሌላ በኩል የመገናኛው ድንኳን ራሱ በ48 ሳንቃዎችና በ9 ምሰሶዎች የተሰራ ነበር፡፡