በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከሚገኙት ዕቃዎች አንዱ የሆነው የሕብስት ገበታ ከግራር እንጨት የተሰራና በንጹህ ወርቅ የተለበጠ ነበር፡፡ ርዝመቱ ሁለት ክንድ (90 ሳንቲ ሜትር፤ 3 ጫማ)፣ ቁመቱ አንድ ተኩል (67.5 ሳንቲ ሜትር፤ 2.2 ጫማ)፣ ወርዱ ደግሞ አንድ ክንድ (45 ሳንቲ ሜትር፤ 1.5 ጫማ) ነበር፡፡ በሕብስቱ ገበታ ላይ ሁልጊዜም 12 ሕብስቶች ይቀመጡበታል፡፡ እነዚህን ሕብስቶች መብላት የሚችሉት ካህናቶች ብቻ ነበሩ፡፡ (ዘሌዋውያን 24፡5-9)
ከሕብስቱ ገበታ ባህሪያቶች መካከል በዙሪያው ሁሉ አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ ያለው መሆኑ፣ በዚህ ክፈፍ ዙሪያ ሁሉ የወርቅ አክሊል የተደረገ መሆኑ፣ በአራቱም ማዕዘኖች አራት የወርቅ ቀለበቶች መደረጋቸው፣ ቀለበቶቹም ገበታውን ለማጓጓዝ የሚያገለግሉና ከግራር እንጨት ተሰርተው በወርቅ የተለበጡ መሎጊያዎችን የያዙ መሆናቸው ይጠቀሳሉ፡፡ በገበታው ላይ ያሉት ዕቃዎች፣ ወጭቶች፣ ጽዋዎች፣ ጭልፋዎችና መቅጃዎች ሁሉም ከወርቅ የተሰረሩ ነበሩ፡፡
ዘጸዓት 37፡11-12 ይህንን መዝግቦዋል፡- ‹‹በጥሩም ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አደረገለት፤ በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አደረገለት፡፡ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አደረገለት፡፡›› በእግዚአብሄር ቤት ቅድስት ስፍራ ውስጥ የሚገኘው የሕብስት ጠረጴዛ የአንድ ጋት ያህል ከፍ ያለው ክፈፍ ነበረው፡፡ በክፈፉም ዙሪያ የወርቅ አክሊል ተደርጎለት ነበር፡፡ እግዚአብሄር ሙሴን እንዲህ ያለ ክፈፍ እንዲያደርግ ያዘዘው ለምንድነው? ይህ 10 ሳንቲ ሜትር (3.9 ኢንች) ያህል ርዝማኔ ያለው የጋት ክፈፍ በገበታው ላይ ሕብስት እንዳይወድቅ የሚከላከል ነበር፡፡
በሕብስቱ ገበታ ላይ ያለውን ሕብስት መብላት የሚችሉ ካህናቶች ብቻ እንደሆኑ ሁሉ ይህንን ሕብስት በመንፈሳዊ መንገድ መብላት የሚገባንም እኛ ነን፡፡ ይህንን ሕብስት መብላት የሚችሉት በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና በመስቀሉ ደም በማመን ከሐጢያት የዳኑና የዘላለምን ሕይወት የተቀበሉ ማለትም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ደህንነታቸው አድርገው ያመኑ ብቻ ናቸው፡፡